Home › Forums › Semonegna Stories › የኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት፣ የቀጣዩ ምርጫ አገራዊ ፋይዳ እና የተደቀኑ አደጋዎች ― ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ (ኢዜማ) ያስተላለፉት መልዕክት
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 4 years, 11 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
February 27, 2020 at 3:55 am #13726AnonymousInactive
የኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት፣ የቀጣዩ ምርጫ አገራዊ ፋይዳ እና የተደቀኑ አደጋዎች ― ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ (ኢዜማ) ያስተላለፉት መልዕክት
ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፤ እንደምን ከረማችሁ?
በዛሬው ዕለት እንደ ኢዜማ መሪም ሆነ እንደ አንድ ዜጋ፣ ከኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ጋር በዚህ መልክ ለመገናኘት ምክንያት የሆነኝ ከፊታችን በተደቀነው ምርጫ ላይ ኢዜማን እንድትመርጡ ለመቀስቀስ አይደለም። እሱ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች የምርጫው ቅስቀሳ ጊዜ በግልጽ ሲታወጅ የምናደርገው ይሆናል። ይልቁንም ዛሬ ላዋያችሁ የምፈልገው እንደ ሀገርም እንደ ሕዝብም ልንጋፈጠው የሚገባን ፊት ለፊታችን የተጋረጠ አንድ ትልቅ እውነትን ነው፤… ዛሬ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሚከሰቱ አለመረጋጋቶች፣ ግጭቶችና ከዕለት ወደ ዕለት አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የሰላም እጦት፣ ‘ነገ ደግሞ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን?’ የሚል ስጋት/ ጭንቀት አለ።
በየሜዲያው የሚወጡ፤ የተጨበጡና ያልተጨበጡ ሁላችንንም የሚያስጨንቁ በርካታ መረጃዎችን እንሰማለን። ተማሪዎች ታገቱ/ ተገድሉ፥ መስጊድና ቤተ-ክርስቲያን ተቃጠሉ፥ ባንኮች ተዘረፉ፥ መንገድ ተዘጋ፥ ንብረት ተዘረፈ ወይም ወደመ፣ የሚሉ ዜናዎችን መስማት ከምንግዜውም በላይ እየተለመደ ነው። ከመደበኛ ሥራችን ውጭ በተለያዩ ማኅበራዊ ስብስቦች ስንገኛኝ የምንወያያቸው ጉዳዮች ለመሆኑ ሀገራችን ወዴት እየሄደች ነው? በዚህ በምናየውና በምንሰማው ሁኔታ ከቀጠልን እንደ ሀገር መቀጠል እንችላለን ወይ? ከዚህ ከገባንበት አዘቅት መቼና እንዴትስ ነው የምንወጣው? የኛም ሆነ የልጆቻችን ዕጣ ፈንታስ ምን ይሆናል? የሚሉና ሌሎችም ብዙ ይህ ትውልድ ወደደም ጠላ መመለስ ያለባችው አንኳር ሀገራዊ ጥያቄዎች፤ አዋቂና ህጻን ሳይለይ ሁላችንንም ከምንም በላይ ያስጨነቁና እንቅልፍ እየነሱ የሚገኙ ጥያቄዎች ሆነዋል።
ዛሬ ሀገራችን ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ቆማለች፥ በዚህ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ የሀገራችን የወደፊት እጣ ፈንታ ሲወሰን ውሳኔዉ እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ይመለከታልና በዚህ ትልቅና ታሪካዊ ውሳኔ ላይ እኛ ምን ያገባናል? ምንስ ሚና አለን? ለሀገራችን ይበጃል የምንለውና የምንፈልገው የመልካም ዘመን መዳረሻ ጋር እንድንደርስ ምን ማድረግ አለብን?” ለሚሉ ጥያቄዎች መልስ ማቅረብ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የነቃ ተሳትፎ የሚጠይቁ ነገር ግን ዛሬ ላይ ሁላችንንም ግራ ያጋቡ ጥያቄዎች ናቸው።
ከፊታችን ያለውን ምርጫ እንኳን በሚመለከት የምናደርገው ውይይት በምርጫው ማን ያሸንፋል? ወይንም ማን ቢያሸንፍ ጥሩ ነው? የሚል ክርክር ሳይሆን “ለመሆኑ በዚህ አይነት ሀገራዊ ሁኔታ ነፃና ሚዛናዊ ምርጫ ማድረግስ ይቻላል ወይ?” “ቢቻልስ ሀገራችን ውስጥ የሚታዩት ዘርፈ-ብዙና ዉስብስብ ችግሮች ሀገራዊ ምርጫ በማድረግ የሚፈቱ ናቸው ወይ?” የሚሉ የጊዜው ሁኔታ የፈጠራቸው ፍርሀቶችና ጭንቀቶች ላይ ደርሰናል። ይህ ሁሉ የሚያሳየን ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ጊዜያዊ ከሆነ የራሳችንን ጥቅምና ፍላጎት ለጊዜውም ቢሆን ተወት አድርገን በጋራ ልንሰራባቸው የሚገቡ የሀገራችንን ትላልቅ ችግሮች በጋራ ለመፍታት አንድ ላይ ካልቆምን የሀገራችን የኢትዮጵያ ህልውና ከምን ጊዜውም በላይ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይወድቃል።
የሀገራችንን ሁኔታ በተመለከተ ከተለያዩ የዜና ምንጮች ከምንሰማው በተጨማሪ፣ ኢዜማ ሀገራዊ ፓርቲ ሆኖ ከተፈጠረ በሁዋላም ሆነ ከዚያ በፊት፣ በገጠርና በከተማ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሀገራችንን ሁኔታ በተመለከተ ሰፊ ውይይቶች አድርገናል። አሁንም በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በዘረጋነው የፓርቲያችን መዋቅር አማካኝነት አካባቢያዊ መረጃዎችን ስለምንሰበስብ ስለ ሀገራችን ሁኔታ፥ ፊት ለፊታችን ስለተጋረጡት ችግሮች፣ በሕዝቡ ውስጥ ስለሚንፀባረቁ ጭንቀቶች፣ ስጋቶችና ተስፋዎች በቂ መረጃ አለን ብለን እናምናለን።
ኢዜማ በአንድ በኩል እንደ አንድ ኃላፊነት የሚሰማው ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰቱ የተለያዩ ችግሮችን እያየ ከንፈር በመምጠጥ፥ በማዘንና በመተከዝ አያልፍም። በሌላ በኩል ደግሞ ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የሕዝቡን ስሜት አነሳስቶ ችግሮችን የበለጠ አያጦዝም። ድርጅታዊ አቅማችን እስከፈቀደ ድረስ ፊታችን ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን በመረጃ ላይ ተመርኩዘን በመተንተን አደጋዎቹ ከቁጥጥር ውጭ ወጥተው የሀገራችንን ህልውና አደጋ ላይ ከመጣላቸው በፊት ለማኅበረሰባችን የማንቂያ ደውል እናሰማለን። አደጋዎቹን መከላከልና ብሎም ማቆም የሚያስችል ስትራቴጂ እንቀይሳለን። ከተለያዩ የሀገራችን ባለድርሻዎች፥ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ ምሁራንና ከመንግስት አካላት ጋር በመሆን፣ በሀገራችን የተደቀኑትን አደጋዎች በጋራ መመከት እንዲቻል የማስተባበር ሥራ እንሰራለን። ከሁሉም በላይ ደግም በፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ያለው የፖሊሲና የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ አሁን የምናያቸውን ሀገራዊ አደጋዎች መከላከል ብቻ ሳይሆን እንደገና እንዳይከሰቱም ለማድረግ “የብሔራዊ ጥቅሞቻችንና የሀገር አጠቃላይ ደኅንነት ጉዳዮች ” (National Interest & Security Agendas) ናቸው በሚባሉ ጉዳዮች ላይ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር አብሮ ለመሥራት ባለን ድርጅታዊ አቅም ሁሉ እንዘጋጃለን።
ዛሬ በዚህ ንግግር ላይ የማተኩረው ኢዜማ እንደ ድርጅት በሀገራችን ያለውን ሁኔታ ገምግሞ የደረሰባቸውን ከፊታችን የሚታዩ አደጋዎች ምንነት፤ እነኝህን አደጋዎች በሚመለከት የጋራ ሀገራዊ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችል የሰከነ ውይይት ለመክፈትና፤ እኛ የሚታየን አደጋ በርግጥም ሌሎቹም የሀገራችን ባለድርሻዎች ይታያቸው ከሆነ፣ ይህን አደጋ ለመከላከል የሚያስፈልገውን የጋራ ስምምነትና እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ሀገራዊ ጥሪ ለማስተላለፍ ነው።
እኛ ባደረግነው የሀገራዊ አደጋ ትንተና የማይስማሙ ኃይሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ እንገነዘባለን። እነሱም ቢሆኑ ግን ዝም ብሎ የተለመደውን ጭፍን ወገንተኛ የሆነ፤ በቅጡ ያልታሰበበት የጥቅል ተቃውሞ ከማሰማት ይልቅ “በርግጥ ይህ አደጋ አለ ወይ?” ብለው በጥሞና እንዲያስቡ ካደረጋቸውና ወደ ሰከነ ውይይት ከመራቸው፣ የዚህ መልዕክት ዓላማ በከፊልም ቢሆን ተሳክቷልና ለምን ከእኛ ትንተናና ድምዳሜ ጋር ሙሉ ለሙሉ አልተስማማችሁም አንልም።
ሙሉ መልዕክቱን ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.