ጃፓን የትምህርትና ጤና ዘርፎችን ለመደገፍና በአ/አ/ዩ ውስጥ የሚገኘውን የራስ መኰንን አዳራሽ የገንዘብ እርዳታ አደረገች

Home Forums Semonegna Stories ጃፓን የትምህርትና ጤና ዘርፎችን ለመደገፍና በአ/አ/ዩ ውስጥ የሚገኘውን የራስ መኰንን አዳራሽ የገንዘብ እርዳታ አደረገች

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #8956
    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ ለትምህርትና ጤና አገልግሎት የሚውል ከ452 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረገ። የጃፓን መንግስት አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲው በኩል ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ አራት ፕሮጀክቶችን ለመገንባትና ለማስፋፋት ያስችላል።

    በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ (Daisuke Matsunaga) የፕሮጀክት ግንባታና ማስፋፊያ ከሚደረግላቸው ትምህርት ቤቶች ኃላፊዎች ጋር የድጋፍ ስምምነት ተፈራርመዋል።

    ፕሮጀክቶቹ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን የጉንችሬ እና እነሞር ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታና በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የሀሮ ሾጤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ናቸው።

    በተጨማሪም ለሻሻመኔ ከተማ የአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች የምግባረ ሰናይ መጠለያ ግንባታና ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የዩሮሎጂ እና ድንገተኛ ክፍል የህክምና መሣሪያዎች ግዥ የሚውል ነው።

    እነዚህ አራት የትምህርት እና የጤና ፕሮጀክቶች ከአራት ሺህ በላይ ህዝብ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።

    አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ እንዳሉት አገራቸው ለኢትዮጵያ ልማት ተሳትፎ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች። ጃፓን በኢትዮጵያ እ.አ.አ ከ1989 ጀምሮ በተለያዩ ክልሎች ከ400 በላይ ፕሮጀክቶችን በመሥራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገች ነው።

    በትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ በኢኮኖሚ ልማትና ሌሎችም መስኮች ድጋፍ ስታደርግም ቆይታለች።

    በስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽነር እርስቱ ይርዳው የተደረገው ድጋፍ የዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል የትምህርት ፍላጎት ለማሟላት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

    ድጋፉ በተለይም ትምህርት ቤት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች መሆኑ የትምህርት ሽፋንን በማስፋት የመንግስትን ጥረት እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡

    ከዚህ ጋር በተያያዘ የጃፓን ኤምባሲ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኘውን የራስ መኰንን አዳራሽ ለማደስ የ85 ሺሕ 679 ዶላር (2,403,500 ብር) ዕርዳታ መለገሱን ሪፖርተር ጋዜጣ በእሁድ ታህሳስ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. እትሙ ዘግቧል።

    አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ እና የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር አህመድ ሐሰን (ዶ/ር) የእርዳታ ስምምነቱን የተፈራረሙ ሲሆን፣ ገንዘቡም የራስ መኰንን አዳራሽ ባህላዊና ታሪካዊ ዳራው ሳይጠፋ ለማደስ፣ የተበላሹ ክፍሎችን ለመጠገን፣ ውስጣዊ ክፍሉን ለማደስ እና አዳዲስ ቁሳቁስ ለማስገባት መሆኑ ታውቋል።

    የጃፓን መንግስት ትምህርታዊ ድጋፍ ከማድረጉም በተጨማሪ የራስ መኰንን አዳራሽን ለማደስ መነሳቱ፣ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ኢትኖሎጂካል ሙዚየም በርካታ ጎብኚዎች እንዲስብ ያስችላል ተብሏል።

    በሙዚየሙ ከአሥር ሺሕ በላይ የኢትዮጵያ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች የሚገለጹባቸው አልባሳትና ቁሳቁሶች አሉ፤ ይህም በአፍሪካ አንዱ ታዋቂ ሙዚየም እንዲሆን አስችሏል።

    በቀድሞው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ሕንፃ ውስጥ የሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ ከ50 ዓመታት በላይ ዕድሜው በስሩ ያቀፋቸው ቤተ-መጻሕፍት፣ የኢትኖግራፊክ ሙዚየም የምርምርና የጥናት ማዕከልን ነው። በውስጡም መጻሕፍት፣ ታሪካዊ ሰነዶችና መዛግብት፣ የዳግማዊ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱን ጨምሮ የድምፅና የምስል ቅጂዎች፣ ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ የጥናት ድርሳኖች፣ ጆርናሎች፣ ረጅም ዕድሜን ያስቆጠሩ የብራና መጻሕፍትንም ይዟል።

    እንዲሁም እስከ 20 ሺሕ የሚደርሱ የኅትመት ክምችቶች ከቅድመ ምረቃ እስከ ድኅረ ምረቃ ተማሪዎች፣ ለተመራማሪዎች ጥናትና ምርምር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

    የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2010 ዓ.ም. መስከረም ወር ከጃፓኑ ኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ ጋር ትምህርታዊ ልውውጥና የጥናት ትብብር ለማድረግ የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙ ይታወሳል።

    ምንጭ፦ ኢዜአ እና ሪፖርተር ጋዜጣ

    የጃፓን መንግስት

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.