የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ አዲስ ተማሪዎችን ተቀበለ

Home Forums Semonegna Stories የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ አዲስ ተማሪዎችን ተቀበለ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #8516
    Semonegna
    Keymaster

    የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምራቸው ተማሪዎች ብቃት ያላቸው ዜጎች ሆነው እንዲወጡና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየሠራ መሆኑን፤ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ለተማሪዎቹ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱንም የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ አስታውቀዋል።

    ጋምቤላ (ኢዜአ) – የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለዘንድሮው የትምህርት ዘመን ወደ ካምፓሳቸው ሲገቡ የጋምቤላ ከተማና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ያደረገላቸው አቀባበል አብሮነታቸውን በማጠናከርም ሊቀጥል እንደሚገባ ወላጆችና ተማሪዎቹ ገለጹ። ዩኒቨርሲቲው በተያዘው የትምህርት ዘመን የተመደቡለትን ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሏል።

    አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የሰጡት ወላጆችና ተማሪዎች እንደተናገሩት ማኅብረሰቡ ያደረገላቸውን አቀባበል በመማር ማስተማሩ ሂደትና በዩኒቨርሲቲ በሚኖራቸው ቆይታ ድጋፍ በመስጠት ሊጠናከር ይገባዋል።

    ልጃቸውን ለማድረስ ወደ ዩኒቨርሲቲው ከመጡት ወላጆች መካከል አቶ ተሾመ ደሳሳ በሰጡት አስተያየት ለተማሪዎቹ የተደረገው አቀባበል ከጠበቅኩት በላይ አግኝቼዋለሁ ብለዋል። በአቀባበሉ ላይ የታየው አብሮነት በቀጣይም ተማሪዎቹ የመጡበትን ዓላማ እንዲያሳኩ ከጎናቸው እንዲሆን ጠይቀዋል።

    ማንኛውም ወላጅ ልጆቹን ወደ ዩኒቨርሲቲዎች የሚልከው ከተቋሙ በተጨማሪ ለአካባቢው ማህበረሰብ አደራ በመስጠት ነው ያሉት ደግሞ ሌላው ወላጅ አቶ ሂርጳ ደጉ ናቸው። በመሆኑም ኅብረተሰቡ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን ድርሻቸውን እንደሚወጡ እምነት አለኝ ብለዋል።

    ተማሪ ጫላ ቶላ በሰጠው አስተያየት በዩኒቨርሲቲው በተደረገለት አቀባበል መደሰቱን ገልጾ፣ በቀጣይም የመጣበትን ዓላማ ለማሳካት በሚያደርገው ጥረት ማኅበረሰቡ ከጎኑ እንዲሆን ጠይቋል።

    ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምርጥ የአዝዕርት ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማከፋፈል ምርትን በማሳደግ አመርቂ ውጤት ተገኝቷል

    ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አቶ ኒያል ኮት በሰጡት አስተያየት ወላጆች ልጆቻቸውን ከዩኒቨርሲቲው ባሻገር ለአካባቢው ኅብረተሰብ መስጠታቸው ተገቢ መሆኑን አመልክተው፣ አደራውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ይህንንም ለማሳካት በተለይም ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ላይ ተማሪዎች ከመምጣታቸው በፊት ከዩኒቨርሲቲው ማህብረሰብ ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

    የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶ/ር ከተማ ጥላሁን እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የትምህርትና የምርምር ሥራዎቹን ሰላማዊና ስኬታማ ለማድረግ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

    በተለይም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ብቃት ያላቸው ዜጎች ሆነው እንዲወጡና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ለተማሪዎቹ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።

    የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ አዲስ የተቀበላቸውን አንድ ሺህ አምስት መቶ ተማሪዎችን ጨምሮ ከሦስት ሺህ አምስት መቶ በላይ ተማሪዎች በመደበኛ መርሐ ግብር ተቀብሎ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች እያስተማረ ነው። የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ በሆነችው ጋምቤላ ከተማ ውስጥ የተቋቋመው በ2007 በኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት ነበር።

    ምንጭ፦ ኢዜአ | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.