የዘንድሮው የፀረ-ሙስና ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ለ14 ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ የተከበረ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበርያ ጽህፈት ቤት ዘግቧል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በአዲስ አበባ ከተማ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ እና በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ትብብር የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ዓመታዊ የፀረ-ሙስና ቀን “ሁለንተናዊ ሰላማችንና እድገታችንን ለማረጋገጥ በሙስና ላይ በጋራ እንዝመት፤ ጊዜው የተግባር ነው” በሚል መሪ-ቃል በፓናል ውይይት እሁድ ኅዳር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ተከብሮ ውሏል።
በዕለቱም የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታከለ ሉሊና ሙስና ተሸሞንሙኖ የሚጠራ ሳይሆን ሌብነት እንደሆነ ሁሉም ዜጎች ተገንዝበው መታገል እና ሙስና በዓይነቱም የተለያየ እንደሆነ በመግለፅ ሁላችንም ተረባርበን መከላከል አለብን ብለዋል።
አቶ ታከለ አያይዘውም ከትንሽ ከህዝብና መንግስት ሰዓትና ንብረት ጀምሮ ትኩረት በመስጠት ያለአግባብ እናዳይባክኑ በቀጣይነትም ልንሠራ ይገባል፤ ለዚህም ሁላችንም የበኩላችንን ሚና መወጣት አለብን ብለዋል።
በዓሉን አስመልክቶ በተዘጋው የፓናል መወያያ መነሻ ሃሳብ ላይም የኢፌዲሪ ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የአዲስ አበባ ማስተባበሪ ቅርንጫፍ የሕግ ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ከፋለ እንደተናሩት በርካታ የሙስና መገለጫዎች አሉ እነዚህንም እንደየዓይነታቸው ነጣጥለን መከላከል ያስፈልጋል፤ ህብረተሰቡም ሊያግዝ ይገባል በጉዳዩም ላይ ባለቤት ነኝ ይመለከተኛል ማለት ይገባል ብለዋል።
ሙስና በአሠራር፣ በአስተሳሰብ፣ በአመለካከት፣ በጥቅም ትስስር፣ በዝምድናና በመሳሰሉት የሚፈፀም በረቀቀና ሚስጢራዊ በሆነ መንገድ የሚከወን በመሆኑ የኮሚሽኑን ስራም በተገቢው እንዳይወጣ ሲያደርግ እንደነበርም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
◌ የአዲስ አበባ ከተማ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ችግሯን ለመፍታት አማራጮች እየተፈለጉ ነው
አክለውም ሙስና ለአገር ዕድገት ፀር፣ ለዲሞክራሲ ጋንግሪን እንደሆነ በማስታወስ ለአንዲት አገር ህዝብ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ውድቀት የሚያስከትል በመሆኑ ሁሉም ዜጋ እንደሚመለከተው በማብራራት ይህን ለመከላከል ሁሉም ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል።
በመጨረሻም እንደአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ያለው የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ በመሆኑና ብዙውን ጊዜ ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚታዩ የሙስና ወንጀሎችን ለመቀነስ በትኩረት መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የዘንድሮው የፀረ-ሙስና ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ለ14 ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ የተከበረ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበርያ ጽህፈት ቤት (TPMO) ዘግቧል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሙስናን ለመዋጋት የተደረገው ስምምነት (United Nations Convention Against Corruption) እ.ኤ.አ ጥቅምት 31 ቀን 2003 ቀን መጽደቁን ተከትሎ በየዓመቱ ኅዳር 30 ቀን “የፀረ-ሙስና ቀን” ሆኖ እንዲከበር ተወስኗል።
ምንጭ፦ TPMO | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ