Home › Forums › Semonegna Stories › ያልተመዘገቡ የስንፈተ ወሲብ መድኃኒቶች በገበያ ላይ መገኘታቸው፣ በህብረተሰቡ ላይም ዘርፈ ብዙ ችግር እየፈጠሩ እንደሆነ ተጠቆመ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years, 1 month ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
November 2, 2018 at 3:35 am #8358SemonegnaKeymaster
የስንፈተ ወሲብ መድኃኒቶች እንደአግባቡ ከሆነ በሀኪም ትዕዛዝ የሚሰጡ መሆናቸውን በመግለጽ፥ ነገር ግን በሕገ-ወጥ መንገድ ያለሀኪም ትዕዛዝ ለኅብረተሰቡ የሚያሰራጩ ሕገ-ወጥ የመድኃኒት ተቋማት እንዳሉ ተጠቅሟል።
አዲስ አበባ – የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ፈዋሽነቱና ደኅንነቱ ያልተረጋገጠ በንግድ ስሙ “ቪጋ፣” “ቪጎ” እና “ፊካ” (ቪጎ 50፣ ቪጎ 100/ Vigo50/100፣ ቬጋ 50፣ ቬጋ 100/Vega 50/100፣ ፊካ 50፣ ፊካ 100/Fika 50/100) የተሰኙ የወሲብ ማነቃቂያ መድኃኒቶች (የስንፈተ ወሲብ መድኃኒቶች) በሕገ-ወጥ መንገድ በሀገር ውስጥ መሰራጨታቸውንና በተጠቃሚዎች ላይም የጤና እና የኢኮኖሚ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን አስታወቀ።
ባስልጣን መሥሪያ ቤቱ ጥቅምት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተገለጸው በድህረ-ገበያ ቅኝት በተደረገው የቁጥጥር ሥራ ለማወቅ እንደተቻለው በተቋሙ ያልተመዘገቡና ጥራት እና ደኅንነነታቸው ያልተረጋገጡ እንዲሁም በሕገ-ወጥ መንገድ ወደሀገር ውስጥ የገቡት የስንፈተ ወሲብ (የወሲብ ማነቃቂያ) መድኃኒቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመገኘታቸው ህብረተሰቡ ምርቶቹን ከመጠቀም ራሱን እንዲቆጥብና ጥንቃቄ እንዲያደርግ ባለስልጣን መስሪያቤቱ አሳስቧል።
ከዚህ በተጨማሪ ችግሩን የከፋ የሚያደርገው የስንፈተ ወሲብ መድኃኒቶች እንደአግባቡ ከሆነ በሀኪም ትዕዛዝ የሚሰጡ መሆናቸውን በመግለጽ፥ ነገር ግን በሕገ-ወጥ መንገድ ያለሀኪም ትዕዛዝ ለኅብረተሰቡ የሚያሰራጩ ሕገ-ወጥ የመድኃኒት ተቋማት እንዳሉ የተደረሰበት ስለሆነ ህብረተሰቡ መሰል ተግባር ሲፈጸም ከተመለከተ በነጻ የስልክ መስመር 8482 በመደወል ለባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ እንዲያሳውቅ አስገንዝቧል።
የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱን መግለጫ በመጥቀስ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደዘገበው ከላይ የተጠቀሱት ሕገ-ወጥ መድኃኒቶች ለስንፈተ ወሲብ (ፈዋሽነት (በሌላ አባባል፥ ለወሲብ ማነቃቂያነት) ጥቅም ላይ እየዋሉ ሲሆን፥ በአዲስ አበባ፣ በዲላ፣ በወላይታ፣ በወራቤ፣ በሆሳዕና፣ በሀዋሳ፣ በደሴ፣ በኮምቦልቻ እና በጎንደር በስፋት እየተሰራጩ ነው። እነዚህ ሕገ-ወጥ መድኃኒቶች በህብረተሰቡ ላይ እይሳደሩ ያለው ዘርፈ ብዙ ጫና እና ተጽዕኖዎች ከፍተኛ ነው። እንደዘገባው ከሆነ ይህ እጅግ አሳሳቢ ችግር በስፋት ከተከሰተ ሁለት ዓመትና ከዚያ በላይ ቢሆነውም በአሁኑ ጊዜ የተጠቃሚው ቁጥር እየጨመረና እያስከተለ ያለውም ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። መግለጫውን መስጠት ያስፈለገውም ስርጭቱ በመስፋፋቱ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ እና በድርጊቱ ላይ የሚሳተፉም ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ለማሳሰብ ነው።
በባለስልጣኑ የመድኃኒት ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ እንዳለ እንደገለጹት፤ ባለስልጣኑ ባከናወነው የክትትልና ቁጥጥር ስራ በደቡብ ክልል ‹‹ቪጋ› እና ‹‹ቪጎ›› የተባለውን ጨምሮ በህገወጥ መንገድ የገቡ መድኃኒቶች ሲሸጡ የተደረሰባቸው ከ30 በላይ የሚሆኑ የግል መድኃኒት ቤቶች የክልሉ ተቆጣጣሪ አካል እርምጃ እንዲወስድ ስም ዝርዝራቸውን አሳውቋል። በከሚሴና በደሴም በተመሳሳይ የተሰማሩ ወደ 20 ድርጅቶች እርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረጉን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ባለስልጣኑ በተለያየ ጊዜ በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ መድኃኒቶችን ከፍትህ አካላትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመውጫ በሮች ላይ ቁጥጥር በማድረግ ህገወጦችን በመከላከል ረገድ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ቢሆንም የህብረተሰብ ተሳትፎ መኖር እንዳለበት አመልክተዋል። ህብረተሰቡ ያለ ሀኪም ትዕዛዝ ከመውሰድ እንዲቆጠብና ህገወጥነትንም እንዲከላከል ጥሪ አቅርበዋል።
በባለስልጣኑ የመድኃኒት ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብደላ ቃሶ ባለስልጣኑ ፈዋሽነታቸውና ጥራታቸው የተረጋገጠ መድኃኒቶችን ህብረተሰቡ በቀላሉ የሚለይበትን አሠራር ዘርግቶ ችግሩን ለመቅረፍ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል። ተገልጋዮች ከዚህ በኋላ ሕጋዊና ሕጋዊ ያልሆኑ መድኃኒቶችን በባለስልጣኑ ድረ-ገጽ (http://www.mris.fmhaca.gov.et) ማየት እንደሚችሉና በድረ-ገጹ ላይም ስለመድኃኒቱ ዝርዝር የሆነ መረጃ እንደሚያገኝ አመልክተዋል። ቀደም ሲል እስከ አንድ ዓመት ጊዜ ይወስድ የነበረውን መድኃኒቶችን በዓይነትና በብዛት የመመዝገብ ሥራም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.