ከደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

Home Forums Semonegna Stories ከደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #11407
    Semonegna
    Keymaster

    የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ ላለፉት 10 ተከታታይ ቀናት ባካሄደዉ ስብሰባ ሀገራዊ የስላምና ፀጥታ ሁኔታን ከአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ገምግሟል።

    ከደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

    ድርጅታችን የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ባለፉት 28 ዓመታት የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን አስተባብሮ በመምራት በክልሉ ዉስጥ የልማት፤ የሰላም፤ የዴሞክራሲ ድሎችን አስመዝግቧል። በሀገራችን ከሚገኙ ብሔሮች ብሔረሰቦች 70 በመቶዉ ይዞ የተደራጀ ነዉ። የደቡብ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና፤ ሕዝቦች ክልል ሕዝቦችን በህብረ-ብሔራዊ አንድነት እየመራ የሚገኝ ዲሞክራሲያዊና ሕዝባዊ ድርጅት ነው። ይህም ክልላችን የብዝሀነት ማዕከል፤ የአብሮነትና የአንድነት ማሳያ እንዲሆን አድርጓል።

    ደኢህዴን ለሕዝቦች እንድነትና ለሀገር ግንባታ ግንባር ቀደም ሚናዉን የተወጣና እየተወጣ የሚገኝ ድርጅት ሲሆን ሀገራችን የገጠማትን ተግዳሮቶች ለመፍታት መፍትሄ የሚሆኑ ዉሳኔዎችን ያስተላለፈና ስኬቶችን ያስመዘገበ ድርጅት እንደሆነም ገምግሟል። በሀገራችን ያጋጠሙ ችግሮችን ለማለፍ በተደረጉ ትግሎች ከእህት ድርጅቶች ጋር በመሆን የራሱን ጉልህ ሚና የተወጣ ድርጅት ነዉ። በሀገራችን ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያገጠሙ ችግሮችን ለመፍታት በተደረጉ ትግሎች ሠላማዊ የስልጣን ሸግግር ለማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነት ተወጥቷል። ስለሆነም ድርጅታችን ሀገራዊ ለዉጡ እዉን እንዲሆን ግንባር ቀደም ሚና የተወጣና ታሪካዊ ዉሳኔ ያስተላለፈ ድርጅት እንደመሆኑ ለቀጣይነቱም ግንባር ቀደም ሚናዉን እንዲወጣ ማዕካላዊ ኮሚቴዉ አጽንዖት ሰጥቷል።

    የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ላለፉት 10 ተከታታይ ቀናት ባካሄደዉ ስብሰባ ሀገራዊ የስላምና ፀጥታ ሁኔታን ከአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ገምግሟል።

    አሁን ሀገራችን ያለችበት ሁኔታም በዝርዝር አይቷል። ሁኔታዉን ለመቀየር ሁሉንም ሕዝቦች በማረባረብ ሠላማችንን ማስከበር ከቻልን ግን ብሩህ ተስፋ እንዳለን በአፅንዖት አይቷል።

    የሠላምና የፀጥታ ሁኔታዉ ከመቼዉም ጊዜ በላይ ለመንግስት ብቻ የሚተዉ ሳይሆን የነቃ የሕዝብ ተሳትፎ ጭምር የሚጠይቅ መሆኑን በመገንዘብ ድርጅቱ ሕዝብን በማስተባበር የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን የሠላምና የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ለማድረግ ግንባር ቀደም ሆኖ እንደሚታገል አስምሮበታል።

    ዛሬም ዋነኛዉ ጠላት ድህነትና ኃላቀርነት መሆኑን የገመገመዉ ማዕከላዊ ኮሚቴዉ ይህንን ሁኔታ ለመቀየር የሚደረገዉን ትግል የሚፈታተኑ ሁኔታዎች መግጠማቸዉን አይቷል። የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ትኩረት ማነስ የስራ አጥነትና ድህነት የኑሮ ዉድነት የወጣቶችና የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ዛሬም ያልተሻሻለ መሆኑን፡ ዘላቂ ሠላም የማረጋገጥና የሕዝቦችን ደህንነት የማረጋገጥ ጉዳይ ትኩረት የሚሹ ተግባራት መሆናቸውን ገምግሟል።

    የክልላችን ሕዝቦች መንግስታዊ አገልግሎት የማግኘት ዕድሉን በሚመለከቱ የተለያዩ የአደረጃጀት ችግሮች በየደረጃው እየፈታ መምጣቱን ማዕከላዊ ኮሚቴው ገምግሟል። የክልል እንሁን ጥያቄዎችን ለመፍታት ሳይንሳዊ ጥናት በምሁራን ቡድን ያስደረገው ድርጅታችን በጥናቱ ግኝት ላይም ሰፊ ውይይት በማካሄድ መግባባት ፈጥሯል። ድርጅታችን የክልሉን ሕዝቦች ጥያቄ በበቂ መረጃና ዕውቀት ላይ ተመስርቶ እና ሕዝቡን ባሳተፈ መንገድ ለመመለስ ላለፉት ሰባት ወራት ባስጠናው ጥናት መሰረት ምላሽ ለመስጠት የተወያየ ሲሆን የሁሉንም ሕዝቦች ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ውሳኔም አስተላልፏል።

    ጥናቱ ደረጃውን የጠበቀ አሳታፊ እና ትክክለኛ ውሳኔ ላይ ለመድረስ በሚያግዝ አግባብ መመራቱንም አረጋግጧል። በጥናቱ ደኢህዴን የክልሉን ሕዝብ መምራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተገኙ ትሩፋቶች፣ ተግዳሮቶች፣ መንስዔዎችና የመፍትሄ አማራጮች የያዘ ስለመሆኑ በጥልቀት በመፈተሸ ለቀጣይ የድርጅት የመሪነት ሚና እና የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን በጥንካሬ ወስዷል።

    በመሆኑም በወቅታዊ ሀገራዊ እና ክልላዊ የፖለቲካ እና የፀጥታ ሁኔታ እንዲሁም በክልሉ የሚነሱ ተጨማሪ ክልል ሆኖ የመደራጀት ጥያቄዎች ላይ ጊዜ ወስዶ በጥልቀት፤ ኃላፊነት በተሞላበትና በሰከነ ሁኔታ የመከረው የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ የሚከተሉትን ባለ 6 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

    1. ወቅታዊ ሀገራዊ የፖለቲካና የፀጥታ ሁኔታን በተመለከተ በእስካሁኑ ሂደት የታዩ አዎንታዊ ውጤቶችን የሚፈታተኑ ጉዳዮች መኖራቸውን የገመገመው ማዕከላዊ ኮሚቴ በድርጅታችን ኢህአዴግ መሪነትና በሕዝቦች ተሳትፎ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ እንዳይቀለበስ ሁሉም አካላት በጋራ የኃላፊነት መንፈስ እንደሚገባቸው አስምሮበታል። በሀገር ደረጃ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ተስፋ የፈነጠቁ ጅምር ውጤቶች የታዩበት ሲሆን በጥንቃቄ ካልተያዘ የሀገርን ህልውና የሚፈታተኑና ሕዝባችንን ስጋት ውስጥ ሊያስገቡ የሚችሉ ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታዎች እየተስተዋሉ መሆናቸውን ተገንዝቧል። በቅርቡ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች እና የሀገሪቱ የጦር መኮንኖች እስከ ህይወት ማጥፋት ድረስ የደረሰውን ጥቃት ድርጅታችን በፅኑ ያወግዛል፣ በፅኑም ይታገላል።
    2. በእህት ድርጅቶች መካከል ከድርጅታዊ ዲስፕሊን ውጪ የሚወጡ መግለጫዎች ይህንንም ተከትሎ እየተደረሱ ያሉ ድምዳሜዎች ከኢህአዴግ መርህ ውጪ መሆናቸውን በመገምገም የትኛውም ዓይነት የሃሳብ ልዩነቶችን እንደወትሮው ሁሉ በድርጅቱ ባህል መሠረት ማስተናገድ እንደሚገባ ታይቷል። በሌላ መልኩ ደኢህዴን በውስጡ ያሉ ችግሮችን ታግሎ የሚያርምና የሚያጋጥሙ ችግሮችና ፈተናዎችን ከሕዝቡ ጋር በመሆን የመፍታት ባህልና ልምድ ያለው ድርጅት ነው። ከዚህ ውጪ እኔ አውቅልሃለሁ በሚመስል መንገድ ከሩቅ የሚሰነዘሩ ሂደቱን ያልተከተለ አመራር የማይቀበል መሆኑን ማዕከላዊ ኮሚቴው ያስገነዝባል።
    3. ክልላዊ ወቅታዊ ፖለቲካና ፀጥታ ሁኔታ ልዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑን ማዕከላዊ ኮሚቴው በዝርዝር ገምግሟል። ሀገራዊ ፖለቲካ እና ፀጥታ ድባብ ተከትሎ በክልሉ ውስጥ የሚታዩ አዝማማያዎች የህግ የበላይነት አደጋ ውስጥ የመግባት የኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች እንቅስቃሴዎች ስርአት መያዝ ያለባቸው መሆኑን ተሰምሮበታል። በዚህ ሂደት ለታዩ ጉድለቶች ሀገራዊ ሁኔታ የራሱ አሉታዊ አስተዋዕፆ ያለው ቢሆንም ዋናው ችግር የድርጅታችን ውስጣዊ ሁኔታ መሆኑን ማዕከላዊ ኮሚቴው በጥልቀት ተወያይቷል። ከድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ጀምሮ በየደረጃው ያለው አመራር ድርሻ ሰፊ መሆኑም ታይቷል። ስለሆነም እንደ ሀገር እና እንደ ክልል ከገባንበት ያለመረጋጋት ለመውጣት የድርጅቱ ውስጣዊ ጥንካሬ ወሳኝ መሆኑን የድርጅቱ አመራሮች በከፍተኛ የሃላፊነት መንፈስ እና ሕዝባዊ ውግንና መንቀሳቀስ የሚጠይቀን ወቅት ላይ መሆናችንን መተማመን ላይ ተደርሷል። በመብት ጥያቄ ሽፋን የሚደረጉ የትኛውንም ኢ-መደበኛ እንቅስቃሴዎችን ስርዓት ለማስያዝ እንዲሁም የሕዝቦችን ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ እና የህግ የበላይነትን ማስከበር ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን ማዕከላዊ ኮሚቴው ድምዳሜ ላይ ደርሷል።
    4. በክልል የመደራጀት ጥያቄን በተመለከተ የሕዝቦች ህገ-መንግስታዊ መብት መሆኑን ድርጅታችን ይገነዘባል። በክልል የመደራጀት ጥያቄ ሲነሳ የነበረው ከአንድ አካባቢ ብቻ ባይሆንም ጥያቄውን በጥናት ላይ ተመስርቶ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት ድርጅቱ በአስረኛ ድርጅታዊ ጉባኤ በወሰደው አቋም መሰረት በዝርዝር ሕዝቡን ያሳተፈ ጥናት ሲያደርግ ቆይቷል። በጥናቱ የቀረቡ አማራጮችን በጥልቀት በመመርመር፣ የሕዝቡን የጋራ ዘላቂ ጥቅም የሚያረጋግጠውን አማራጭ በመውሰድ የክልል አደረጃጀት ጥያቄዎች በሚመለሱበት አግባብ ላይ አቋም ተወስዷል። በክልላችን መላው ሕዝብ ምክክርና ውይይት የሚያደርግበት ሆኖ በአንድ በኩል በጥናቱም የተገኘውን የክልሉ ሕዝቦች አብሮ የመቀጠል ፍላጎትን ባከበረ በሌላ ጎኑ ደግሞ ጉባኤውን ውሳኔ ተግባራዊ ባደረገ መንገድ እና ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ የመምራት ኃላፊነት ለመወጣት ማዕከላዊ ኮሚቴው ተስማምቷል።
    5. የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በህብረ-ብሔራዊነት ላይ እየተገነባ ያለው የፌዴራል ሥርዓት ትሩፋቶችን ያስመዘገበ ሲሆን በሂደቱ የታዩ ተግዳሮቶች በማረም ሀገራችን በደረሰችበት የዕድገት ደረጃ በማሻሻል ለፌዴራል ሥርዓቱ ይበልጥ መጎልበትና ቀጣይነት የምንታገል መሆኑን አቋም ተወስዷል። ከሁሉ በላይ ህበረ-ብሔራዊ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ለማጎልበት ማዕከላዊ ኮሚቴው አጽንኦት ሰጥቷል።
    6. በእያንዳንዱ አከባቢ ያለውን የልማት ሁኔታ በተመለከተ በድርጅታችን መሪነት በክልላችን የተመዘገቡ የልማት ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆነው በተለያየ መልኩ የሚገለጽ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የመልካም አስተዳደር እና የአመራር ሥርዓታችን ላይ የሚታዩ ችግሮች መፈታት እንዳለባቸው ተወስዷል። ከዚህም በመነሳት በክልሉ ሁሉም አከባቢዎች የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ በክልሉ ያሉ ሕዝቦች በጋራ መልማት እንዳለብን በመግባባት ሕዝቡን ባሳተፈ ሁኔታ የክልሉን ህገ-መንግስት ከማሻሻል ጀምሮ ሌሎች ዝርዝር የህግ ማዕቀፎች እንዲዘጋጁ አቋም ተወስዷል።

    ውድ የድርጅታችን አመራሮች፥ አባላትና ደጋፊዎች፣ ድርጅታችን ደኢህዴን ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ ያበረከታችሁት ድርጅታዊ አስተዋጽኦ ከገባንበት ፈተና ለመውጣት ያስቻለ ሆኗል። የድርጅት ቀጣይነት ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ አቋም የተወሰደበት ወቅት ላይ ደርሰናል። ስለሆነም የተጀመረው ድርጅታዊ ሪፎርም በማጠናከር እንደወትሮ ሁሉ ግንባር ቀደምትነት ሚናችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪ ያቀርባል።

    የተከበራችሁ የክልላችን ሕዝቦች፥ በተለያዬ መልኩ የሚገለጽ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እና የአደረጃጀት ጥያቄዎች ውስጥም ሆናችሁ ምላሽ እንዲሰጣችሁ ላሳያችሁት ትዕግስት ድርጅቱ ምስጋና ያቀርባል። ይህ ትዕግስታችሁ በመሪ ድርጅቱ እና በመንግስት ላይ እምነት በመጣል የሚታዩ ችግሮች በጋራ ቆመን እንድንፈታ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንዳበረከታችሁ ያሳየን ነው። ችግሮችን በውይይትና በምክክር የመፍታት አማራጭ ብቻ በመከተል ዛሬ ለደረስንበት ደረጃ ያበረከታችሁት አስተዋጽኦ ታሪክ የሚረሳው አይደለም። ዛሬም ድርጅታችን በጽኑ መስመር ላይ በጽናት በመቆም የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች በድል ለመወጣት ያለውን ዝግጁነት ያረጋግጣል። ስለሆነም በድርጅቱ ላይ ያላችሁን እምነት በማጎልበት ለውጡን ከዳር ለማድረስ የሚጠበቅባችሁን ሕዝባዊ አስተዋጽኦ እንድታበረክቱ ጥሪ ያቀርባል።

    የተከበራችሁ የክልላችን አርሶ እና አርብቶ አደሮች፥ የክልላችን ሕዝብ አብዘኛውን ቁጥር በመያዛችሁ ብቻ ሳይሆን ባለፉት ዓመታት ለተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለሕዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና ለድርጅታችን ቀጣይነት ዋልታና ማገር መሆናችሁን ነጋሪ አያሻውም። ያገኛችሁትን ትሩፋቶች ጠብቃችሁ በቀጣይ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር መዋቅራዊ ችግሮች እንዳሉ ተገንዝበናል። በመሆኑም ከድህነት ለመላቀቅና ለተሻለ ህይወት የምታደርጉትን ጥረት ከጎናችሁ በመቆም አለኝታነታችንን ለማረጋገጥ ዛሬም የፀና እምነት እንዳለን እናረጋግጣለን።

    የተከበራችሁ የክልላችን ወጣቶች፥ በክልሉ በሁሉም አከባቢዎች የወጣቶች የተሳትፎና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄ አንገብጋቢና የተለየ ምላሽ መስጠት የሚጠይቅ መሆኑን በጥልቀት ያየው ማዕከላዊ ኮሚቴው በቀጣይ የክልሉ የልማት ኮሪደሮችን ለይቶ የጋራ ሀብቶችን በማልማት፣ ወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚሰራ መሆኑን አቅጣጫ አስቀምጧል። በመሆኑም በክልላችን ያለውን የጋራ ፀጋ መሰረት ያደረጉ አዳዲስ የልማት ቀጠናዎችን በመፍጠር የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ቆርጠን መነሳታችንን እንገልጻለን። ስለሆነም የክልላችን ወጣቶች ከድርጅታችን ጎን በመሰለፍ የማይተካ አዎንታዊ ሚናችሁን እንድትወጡ ጥሪ ያቀርባል።

    የተከበራችሁ የክልላችን ሴቶች፥ እስካሁን ለተገኙ ትሩፋቶች ሚናችሁ የላቀ ሲሆን ባጋጠመን ተግዳሮቶች ቀዳሚ ተጎጂ መሆናችሁ ግልጽ ነው። በመሆኑም የሴቶችን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማስፋት በእስካሁኑ ጉዟችን የነበሩ ጉድለቶችንም ለማረም ከምንም ጊዜ በላይ ዝግጁነታችንን እናረጋግጣለን። የክልላችን ሴቶች ከህብረተሰቡ ውስጥ ከቤተሰብ ጀምሮ ያላችሁን ግዙፍ ሚናችሁን ይዛችሁ ከድርጅታችን ጎን ሆናችሁ ትግላችሁን እንድታጠናክሩ ጥሪ ያቀርባል።

    የተከበራችሁ የክልላችን ምሁራን፥ ድርጅታችን ባስመዘገበው ስኬቶች ለነበራችሁ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ክብር አለን። አሁንም ከሰፊው የዕውቀት ማዕድ ካገኛችሁት ልምድና የህብረተሰብ ችግሮች ላይ መፍትሄ ለመስጠት ያላችሁ የመተንተን አቅማችሁን ሳትነፍጉ ለሀገራችሁና ለሕዝባችሁ ለወገናችሁ ለማበርከት ከጎናችን እንድትሰለፉ ጥሪ ያቀርባል።

    ውድ የሀገራችን ባለሀብቶችና የንግዱ ማኅበረሰብ፥ በክልላችን ብሎም በሀገራችን ለተመዘገበው ልማት የጀርባ አጥንት በመሆን ለምታበረክቱት ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ ምስጋናችንን እናቀርባለን። በክልላችን ያለውን የመልማት ጸጋ በጋራ ለማልማትና ሕዝባችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከምንግዜውም በላይ ተዘጋጅተናል። ስለሆነም በግልና በጋራ ሆናችሁ አብረን ለመስራት ጥሪ ያቀርባል።

    ውድ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፥ የክልላችን ሕዝቦች መለያና መታወቂያ የሆነውና እየተገነባ የመጣውን ደቡባዊ ስነ ልቦና ለክልላችን ሕዝቦችም ሆነ ለሀገር ግንባታ ያለው ፋዳ ትርጉም ያለው ነው። ይሁንን እምቅ አቅም ይበልጥ በማውጣት ረገድ ኪነ ጥበብ ያለው ሃይል ላቅ ያለ በመሆኑ የሕዝቦችን ትስስርና አንድነት በቀጣይነት ለመገንባት እንድታውሉ ጥሪ ያቀርባል።

    የተከበራችሁ እሀት ደርጅቶችና አጋሮች፥ ደኢህዴን/ኢህአዴግ የክልሉን ሕዝቦች ሰላም ልማት ዴሞክራሲ ብሎም ለሀገራዊ አንድነትና ክብር የበኩሉን አዎንታዊ ሚና ሲጫወት የቆየ ድርጅት ነው። በሀገር ግንባታ ሂደት የበኩሉን ሚና እየተወጣ እንደመጣ ሁሉ ዛሬም ለሀገራችንና ለሕዝቦቿ እንዲሁም ለዜጎቿ ክብር መብት ነፃነት ብልጽግና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ተግቶ ይታገላል።በዚህ ሂደት ከጎናችን እንደቆማችሁ ሁሉ ዛሬም የተለመደው አዎንታዊ ሚናችሁ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀርባል።

    የተከበራችሁ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፥ በተለያየ ሙያ ውስጥ ያላችሁ በሙሉ ደኢህዴን የስካሁን ስኬቶቹን ጠብቆ ማቆየት ሳይሆን ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች በመወጣት ለሀገራችን መፃኢ ተስፋ አዎንታዊ ሚና ለመጫወት ቆርጦ ተነስቷል። ይህ ሂደት የሁላችሁም አዎንታዊ ድጋፍና እይታ ይፈልጋል። ስለሆነም በድርጅታችን የሚቀመጡ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች መመዘን ያለባቸው ከሕዝቡ ሰላምና የህግ የበላይነት ዘላቂ ጥቅም አንጻር መሆናቸው ይታወቃል። ስለሆነም ገንቢ ሚናችሁ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀርባል።

    የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን)

    የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ - ደኢህዴን


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.