ለተከበሩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ― ድምጻዊ ዳን አድማሱ

Home Forums Semonegna Stories ለተከበሩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ― ድምጻዊ ዳን አድማሱ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #10533
    Semonegna
    Keymaster

    ለተከበሩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ― ድምጻዊ ዳን አድማሱ
    አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ

    ለተከበሩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ፥ እኔ እንደ አንድ ኢትዮጽያዊ ወጣት ይህን ማለት እወዳለሁ ተወልጄ ባደኩባት ሀገር ነፍስ ካወኩባት ጊዜ በሀገሬ ጉዳይ በነፍስ በስጋዬ ስሟገት እዚህ ደርሻለሁ።

    በተለይም እድሜ ለቅንጅት ፓርቲ ወጣቱ መብቱን እንዲጠይቅ አንቅቶታል ብዬ አምናለሁ፤ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እየተገደለ፣ እየተቀጠቀጠ፣ እየታሰረ እዚህ ወንበር ላይ እርሶን አምጥቷታል።

    እኔ የለውጡን ዋጋ የምሰጠው ለእግዚአብሔር ነው። ለውጡ የመጣው ፈጣሪ ለዚህች የቃልኪዳን ምድር ስለራራላት ነው፤ እንዲራራላት ደግሞ ወይባ ለብሰው በገረገራ የፆሙ፣ የፀለዩ፣ በየመስጊዱ ውስባህ ይዘው ዱአ ያደረጉ፣ የትውልድ ወላጆች ፈጣሪ ከሰማይ እንዲወርድ፣ ከመንበሩ እንዲነሳ አድርገውታል። ሲቀጥል የደም ትንሽ ትልቅ የለውም፤ ድፍን ኢትዮጵያዊ ዋጋ ከፍሏል፤ የድሀ እንባ፣ የወጣት ደም፣ የእናት፥ የአባት ለቅሶ ወደ ላይ ጮሆ አምላክ ለኢትዮጵያ ወርዷል፤ በዚች የአኬልዳማ ምድር ግን የአቤል ደም አሁንም ይጮሀል።

    በሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በሀገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ‘ሆ!’ ብለን ስንወጣ፥ ስለ እርሶ በቂ ዕውቀት እንኳን ኖሮን አይደለም። መጀመሪያ ሰው ኖት፤ ሲቀጥል ‘ኢትዮጽያ’ ብለው መጡ። ያኔ ሁለቴ አላሰብንም! እንደ ምድር አሸዋ በዝተን፣ እንደ ሰማይ ኮከብ ደምቀን መጣን። የኢትዮጵያ አምላክ ቀድሞን ባይወጣ ኖሮ እነዛ ሰማዕትት ከሁለት ሰው ወደ ሀያ ሚሊየን ላለመድረሳቸው ማንም እርግጠኛ አልነበረም። ወጣቱ ሰማዕት ከሞት ጋር ተናንቆ ‘የኔ ችግር የለም፤ አብይን አደራ’ ሲል ምን እንደተሰማዎት ባላቅም ኢትዮጵያን አደራ እያሎትም ጭምር ነበር። ከዛች ቀን ጀምሮ በርካታ መልካም ጅማሮዎትን አይተን እግር በእግር እየተከተልን ምስጋናን እና ማበረታታትን አልተውንም፤ ግን እውነቱን ማወቅ ከፈለጉ ይህን አንድ ዓመት በጥፍር ቆመን አሳልፈናል፤ ጠዋት ስንነቃ ከአዋውፋት መዝሙር ይልቅ የሕዝብ እሮሮ ቅርባችን ነው፤ ማታ የእንቁራሪት ሲርሲርታ ሳይሆን የሕዝቦች ዋይታ ቤታችን ነው።

    ለምን ደጋግመው ሲሉት እንደሰማሁት ማሰር እና መግደል ስለማያዋጣ እየታገስን ነው ማለት ምን ማለት ነው? በማን ደም ነው ትዕግስት የምንለማመደው? በማንስ ለቅሶ ነው ትከሻ የምናሰፋው? በጌዲኦ፣ በአጣዬ የሚሞተው ህፃን የእርሶ ልጅ ቢሆን ትንሽ ልታገስ ይሉ ነበር? ቆይ ታግሰው ሁለተኛ ልጆን ቢነጠቁ ‘መግደል መሸነፍ ነው’ ይላሉ? አይመስለኝም።

    ስለዚህ እርሶ ኪጋሊ፣ ሩዋንዳ ያስቀመጡትን አበባ የሩዋንዳው ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ እዚህ መጥተው እንዳያስቀምጡት ትዕግስቱ ገደብ ቢኖረው የተሻለ ነው እላለሁ። ይህን ሁሉ ችግር መፍታት ቀላል እንዳልሆነ ብንረዳም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና የአዲስ አበባ ልጅ ላይ የተሰጠውን ጠንከር ያለ መግለጫ ዓይነት መስጠት ግን ከባድ አይመስለኝም። እዚህ ላይ መጨመር የምፈልገው ከእያንዳንዱ ችግር ጀርባ በሚሊየን የሚቆጠረውን ደግ እና ሀገር ወዳድ የኦሮሞ ህዝብ ለእያንዳንዱ ችግር አብረን ባንወቅጠው ጥሩ ነው፤ ካልሆነ ግን እኛ እርሶን ከልባችን ላለማውጣት የምንታገለውን ያክል እርሶ ከልባችን ለመውጣት እየታገሉ ይመስለኛል።

    ዳን አድማሱ (ድምጻዊ)
    አንድ ኢትዮጵያ
    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ዳን አድማሱ


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.