Home › Forums › Semonegna Stories › ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ እና «የኔ ዜማ» አልበሙ
Tagged: ልቤ ሰው ይወዳል, የኔ ዜማ, ደሃ አይጣላ ከውሃ, ዳዊት ፅጌ
- This topic has 1 reply, 1 voice, and was last updated 11 months, 3 weeks ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
January 26, 2020 at 11:52 pm #13433SemonegnaKeymaster
ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ «ባላገሩ አይድል» በሚል ስያሜ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይተላለፍ በነበረ የሙዚቃ ዉድድር ከዓመታት በፊት አሸናፊ ነበር። ዉድድሩ ሲጠናቀቅም ለአሸናፊዉ የሙዚቃ አልበም ማዘጋጀት የሽልማቱ አካል ስለነበር፤ በዉድድሩ ዳዊት ፅጌ ያሳየዉ ድንቅ ችሎታ በሙዚቃ አፍቃሪ ኢትዮጵያውያን ዘንድ አልበሙ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎት ነበር።
እናም እንደተጠበቀዉ በቅርቡ «የኔ ዜማ» በሚል መጠሪያ የመጀመሪያ የሙዚቃ አልበሙን (debut album) ለአድናቂዎቹ እንካችሁ ብሏል። የአልበሙን መለቀቅ ተከትሎ በኢትዮጵያ ሙዚቃ አድማጮችና አድናቂዎች ዘንድ በብዛት መነጋጋሪያ የሆነው ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ ጥር 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ከጀርመኑ የዶይቸ ቬለ ሬድዮ አማርኛ ዝግጅት ክፍል ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል።
አሥራ አራት የሙዚቃ ሥራዎች የተካተቱበት የድምፃዊ ዳዊት ፅጌ «የኔ ዜማ» አልበም ዉድድሩን ካሸነፈ ከአራት አመታት በኋላ የወጣ በመሆኑ የሙዚቃ አልበሙ ዘግይቷል የሚሉ ብዙዎች ናቸዉ። የዶይቸ ቬለ ጋዜጠኛም ለዳዊት በመጀመሪያ ያነሳችለት ይህንኑ ጥያቄ ነበር።
በዉድድሩ የተለያዩ አንጋፋና ወጣት ድምፃዉያንን ሙዚቃ ይጫወት ስለነበር የአራት ዓመት ቆይታዉ የራሱን የሙዚቃ ቀለም ፈልጎ ለማግኘት የጣረበት እንደነበርም ድምፃዊዉ ገልጿል። ለዚህም አንጋፋዉ የሙዚቃ ሰዉ አበበ መለሰ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጎለታል።
በዳዊት ፅጌ «የኔ ዜማ» አልበም የ«ባላገሩ አይድል» አዘጋጅ የነበረውና የእውቁ የሙዚቃ ባለሙያ የአብርሃም ወልዴ አሻራ ያረፈበት ሲሆን፥ «ባላገሩ » ቁጥር አራት በዚህ አልበም ተካቷል። «አስመሪኖ»በሚለዉ ዜማዉ ደግሞ ፀሀይቱ ባራኪን የመሳሰሉ አንጋፋ የኤርትራ ድምፃዉያን ተዘክረዉበታል። (አብርሃም ወልዴ ከተለያዩ ድምጻውያን ጋር በመተባበር “ባላገሩ” በሚል ርዕስ ከዚህ በፊት አራት ሥራዎችን ሠርቷል። የመጀመሪያው ባላገሩ ፩ ድምፃዊ ደሳለኝ መልኩ፣ ሁለተኛው ባላገሩ ፪ ድምፃውያን ኤፍሬም ታምሩ እና ጎሳዬ ተስፋዬ (በኅብረት)፣ ሦስተኛው ባላገሩ ፫ ድምፃዊ መስፍን ዘበርጋ /ጉራጊኛ/ ናቸው።)
«ባላገሩ አይድል» በሚለዉ የሙዚቃ ዉድድር በነበረዉ ቆይታ በሙዚቃ አፍቃሪዎች ልብ ዉስጥ ትልቅ ቦታ ይዞ የቆየዉ ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ፤ በቅርቡ ያወጣዉ አዲሱ አልበም በአድማጩ ዘንድ ጥሩ ምላሽ እየተቸረዉ መሆኑን በቃለ ምልልሱ ላይ ገልጿል። ከአዲሱ የሙዚቃ አልበሙ ዉስጥም «ልቤ ሰዉ ይወዳል» ለሚለዉ ሙዚቃዉ የተለየ ስሜት አለዉ።
ከዶይቸ ቬለ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ሙሉውን እዚህ ጋር በማስፈንጠር መስማት ይችላሉ።
ልቤ ሰው ይወዳል (ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ)
ልቤ ሰው ይወዳል (2x)
ልቤ ሰው ይወዳል ወድያው ይላመዳል፣
የቀረበኝ ሁሉ ወዳጅ ይመስለዋል፤
ይላመዳል ሰው ያምናል ይወዳል፣
ይሄ ልቤ ሰው ያምናል ይወዳል፤
ይመስለዋል ወዳጅ ይመስለዋል፣
ይሄ ልቤ ሰው ያምናል ይወዳል።አይቶ አለመራመድ እግሩን ቢያስነክሰው፣
በማጣት ቢያሳሹት እንዴት ይድናል ሰው?
በእሳት ከነደደ አመድ መች ይገዳል?
ሰው ሁሉ እንደዚህ ነው አጥፊውን ይወዳል። (2x)አንዳንዴ እንዲ ነው አንዳንዴ እንዲ ነው፣
ሰው ወዶ ሰው መጥላት ለካስ ፈተና ነው።
ጥርስ አልሰንፍ አለ እንጂ ቀድሞ ለመሳቁ፣
እኔን ባይ አይጠፋም ተገፍተው ስወድቁ።ልቤ ሰው ይወዳል ወድያው ይላመዳል፣
የቀረበኝ ሁሉ ወዳጅ ይመስለዋል፤
ይላመዳል ሰው ያምናል ይወዳል፣
ይሄ ልቤ ሰው ያምናል ይወዳል፤
ይመስለዋል ወዳጅ ይመስለዋል፣
ይሄ ልቤ ሰው ያምናል ይወዳል።ቀን ይዞ ቢጠልቅም ወዳጅ እንደጀንበር፣
ሰው ጨረቃ አያጣም ባመሸበት ሀገር፤
ልቤ አይጉደል እንጂ በሰው ያለ ተስፋ፣
በመጪው ይካሳል በሄደው የከፋ። (2x)፤አንዳንዴ እንዲ ነው፥ አንዳንዴ እንዲ ነው፣
ሰው ወዶ ሰው መጥላት ለካስ ፈተና ነው።
አንዳንዴ እንዲህ፥ ነው አንዳንዴ፣
ሰው ወዶ ሰው መጥላት አይለምደውም ሆዴ።አረ አይጣል ነው (8x)
አንዳንዴ እንዲ ነው፥ አንዳንዴ እንዲ ነው፣
ሰው ወዶ ሰው መጥላት ለካስ ፈተና ነው።ደሃ አይጣላ ከውሃ (ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ)
አንዲት ሴት ነበረች የቤት ሠራተኛ፣
ቀን ስትደክም ውላ ሌሊ’ትን የማት’ተኛ፤
ኑሮዋ ሆነና የአርባ ቀን ዕድሏ፣
ልጅ እያጠባች ነው የተለያት ባሏ፤
ለአንድ ልጇ ስትል በነፃ እየሠራች፣
ደሞዟን ሳትል ለፍታ ያሳደገች።
እንደወጣ ቢቀር ያ’ ባሏ ያ’ ጎበዝ፣
ስትረግም ትኖራለች ያሻገረውን ወንዝ።ለራሷ’ምትቀምሰው ’ምትልሰው ሳይኖራት፣
ምን ልታጠባው ነው የምትወልደው ሲሏት፤
ልጅ ስህተት አይደለም ከመጣ በኋላ፣
ብላ ተስፋ ቆርጣ ሄደች ዳግም ጥላ።
ሀገር ጥላ ጠፍታ ተሰዳ በርቁ፣
ትኑር ትሙት እንኳን አንዳቸው ሳያውቁ፤
ስንት ዘመን አልፎ ናፍቃ ብትመለስ፣
ይኸው ፊት አስነሳት የታቀፈችው ነፍስ።
ምን አለ ብትተወው የባሏን እሮሮ፣
ያሻገረውን ወንዝ መርገም በእንጉርጉሮ።
ወንዙን አለችው ብላ ጠጋ፣
ለአንተም አለ በጋ!!
እሷም አለችው ብላ ጠጋ፣
ለአንተም አለ በጋ!!ከሀገር ሀገር ስትዞር ተሸክማ ጓዟን፣
ስንት አሳር አይታለች ለማሳደግ ልጇን፤
እረፍት እንኳን ሳታውቅ በነፃ እየሠራች፣
ወዟን አራግፋ ነው ለፍታ ያሳደገች።ታድያ አንድ ቀን ጥዋት ማለዳ ተነስታ፣
ቅጠል ጠርጋ መጥታ ሳታርፍ እንኳን ላፍታ፤
ልጇን በአንቀልባ አዝላው ውሃ ልትቀዳ፣
ከለመደችው ወንዝ መሸት ሲል ወርዳ፤
ጎንበስ ባለችበት በድካም ስሜቷ፣
አመለጣት ልጇ አይ እድሏ ሀብቷ፤
ደራሽ ወሰደባት የት ገባ ጸሎቷ?
የምትወደው ልጇን ሆነ የውሃ ሽታ!ምን ያደርግላታል ብታለቅስ ብትረግመው፣
ከውሃ ተጣልታ የትም ለማትደርሰው?
እሷም አለችው ብላ ጠጋ፣
ለአንተም አለ በጋ!!
እሷም አለችው ብላ ጠጋ፣
ለአንተም አለ በጋ!!ድሃ አይጣላ ከውሃ! (5x)
ድሃ ኣኣኣ አይጣላ ከውሃ!! (8x)ምንጭ፦ ዶይቸ ቬለ ሬድዮ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
February 1, 2024 at 1:00 am #61288SemonegnaKeymaster“የደጋ ሰው” በተሰኘው የሙዚቃ ስብስብ ላይ ሙያዊ ውይይት ተከናወነ
በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ-ጥበባት ማዕከል አዘጋጅነት “የደጋ ሰው” በተሰኘው የሙዚቃ ስብስብ ላይ ሙያዊ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ አጠቃላይ ሙያዊ ትንታኔውን የሙዚቃ ባለሙያና የሙዚቃ ሃያሲ አቶ ሰርጸ ፍሬስብሃት ያቀረቡ ሲሆን፥ የሙዚቃው አቀናባሪና ፕሮዲዩሰር ኢዩኤል መንግሥቱ እና ድምጻዊቷ የማርያም ቸርነት (የማ) የሙዚቃ ስብስቡን ሥራ ታሪክና ውጣ ውረድ አብራርተዋል።
አቶ ሰርጸ ፍሬስብሃት ሙዚቃው የዓለም ሙዚቃ ዘውግ (World music genre) ላይ የሚመደብ ምርምራዊ ሥራ መሆኑን አመላካች፣ አስረጅ እና ታሪካዊ ዳራዎችን በመጥቀስ ያብራሩ ከመሆኑም ባሻገር፥ እስካሁን በዓለም ሙዚቃ ዘውግ ከተሠሩ የኢትዮጵያዊያን ሙዚቃዎች ውስጥ የቀለለ ዕድል በሌለበት በጥረትና ትጋት የተፈጠረ የጥበብ ሥራ መሆኑን አብራርተዋል።
ከዚህ አስቀድሞ በየዓለም ሙዚቃ ዘውግ (World music genre) አስቴር አወቀ፣ እጅጋየሁ ሽባባው፣ ምንይሹ ክፍሌ፣ ዣን ስዩም ሔኖክን የመሰሉ ከያንያን በውጭ ሀገር ከመኖራቸውና ለወርልድ ሙዚቃ ካላቸው ተጋላጭነት አንጻር በመመዘንም “የደጋ ሰው” የሙዚቃ ስብስብ በተለየ ሁኔታ በምርጫና በጥረት የተሠራ ሥራ መሆኑን አቶ ሰርጸ አብራርተዋል።
የሙዚቃ ስብስቡ የአፍሪካ፣ የአውሮፓ እና የሰሜን አሜሪካ ሙዚቀኞች ከኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ጋር የተጣመሩበት እና በአቀናባሪው ምርጫና ትጋት ወደ እውንነት የተቀየረ መሆኑ ተገልጿል።
የሙዚቃው አቀናባሪ እና ፕሮዲዩሰር ኢዩኤል መንግሥቱ ሥራው በቦኬ ማኅበረሰብ ሙዚቃ በመሳብ እና ምርምሮችን በማስፋት ሀገር በቀል የሙዚቃ ቅንጣቶችን ከዓለም አቀፍ የሙዚቃ እሳቤዎች ጋር በመቀየጥ የባሕል ውህደትና ቅንብር ለመፍጠር የተሠራ ሥራ መሆኑን የሙዚቃ ስብስቡን ታሪክ አስረድተዋል።
ድምጻዊቷ የማርያም ቸርነት ከእንግሊዝኛ የሙዚቃ ድምጻዊነት በሽግግር ወደእንዲህ አይነት የባሕል ቅይጥ እና ዓለማቀፋዊ መልክ ወዳለው ሥራ የተሻገረችበትን መልክ ሆኔታዎች አንስታ ገልጻች። “የደጋ ሰው” የሙዚቃ ስብስብ ከሰባት ሀገራት፣ ከሃያ በላይ ሙዚቀኞች የተሳተፉበት ሙዚቃ ስብስብ ሲሆን፥ በሙዚቃ ድርሰት፣ በሁለት የዘፈን ግጥሞች፣ በቅንብር እና በፕሮዲዩሰርነት ኢዩኤል መንግሥቱ፣ ጎላ ጎሕ (የብዕር ስም) ስምንት የሙዚቃ ግጥሞችን በማበርከት፣ አንጋፋው ይልማ ገብረአብ አንድ የሙዚቃ ግጥም ድርሰት በመስጠት የተሳተፉበት ስብስብ ነው።
በውይይቱ ላይ በርካታ ታዳምያን ተገኝተው ስለሙዚቃ ሥራው የተሰማቸውን ስሜት እና በቀረቡት መነሻ ሃሳቦች ላይ ጥያቄና ማብራሪያ በማቅረብ ጠንካራ ተሳትፎ አድርገዋል።
በውይይቱም ላይ ከሙዚቃው ድርሰትና ቅንብር በተጨማሪ የተለየ ሆኖ በሀሳብ ላይ ትኩረት አድርጎ ስለመጣው የሙዚቃው ግጥሞች በርካቶች አድናቆታቸውን ሰጥተዋል። በሌላም በኩል ምርምርና የሥነ-ጥበብን ከፍታ ይዘው ለሚመጡ አድካሚና ውድ ሥራዎች አድማጩ ሊሰጠው ስለሚገባው ትኩረት በማንሳት ጠንካራ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።
በዝግጅቱም ላይ ከራያ ማኅበረሰብ የተላኩ ወኪሎች በቦታው ተገኝተው ለድምጻዊቷ፣ ሙዚቃው አቀናባሪና ገጣሚ እንዲሁም በሥራው ላይ ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ለየማርያም ቸርነትም የራያ ባሕል ልብስ ስጦታ አበርክተዋል።
የካቲት 2 ቀን፥ 2016 ዓ.ም በ “ነገረ መጻሕፍት” ዝግጅት የገብረሕይወት ባይከዳኝ “ሕዝብና የመንግሥት አስተዳደር” መጽሐፍ የታተመበትን 100ኛ ዓመት በማስመልከት ከፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ ጋር በሚደረገው ውይይት ላይ እንድትገኙ ከወዲሁ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋብዟል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.