Home › Forums › Semonegna Stories › ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የ2019 የሰላም የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ሆኑ
Tagged: የሰላም የኖቤል ሽልማት, የኖቤል ሽልማት
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 2 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
October 11, 2019 at 11:17 am #12227SemonegnaKeymaster
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የ2019 የሰላም የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ሆኑ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሰላም የኖቤል ሽልማት ለመቀበል የበቁት ከኤርትራ ጋር ለ20 ዓመታት የዘለቀው አለመግባባት በሰላም በመቋጨታቸውና በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን ባበረከቱት አስተዋጽኦ መሆኑ ሽልማቱን የሚሰጠው ኮሚቴ ገልጿል።
በሐምሌ 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ኤርትራ ያደረጉት ጉብኝት ዓለምን ያስገረመና ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ያልተቀመጠለት የቅርብ ወዳጅ ዘመድ ጥየቃ ዓይነት ቃና የነበረው ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉብኝት ተከትሎ ሁለት ዓይነት ሀሳቦች ቢስተናገዱም ሚዛን የሚደፋው ጉብኝቱ ሰላምን ለማምጣት መሠረት የተደረገ መሆኑ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአገር ውስጥና በአጎራባች አገሮች እያመጡ ያለውን ጉልህ ለውጥ ተከትሎ ‘ሽልማቱ ይገባቸዋል’ የሚሉ ድምጾች አሸናፊነታቸውን ቀድመው እንዳወጁላቸው ያመለክታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጠቃላይ በጎረቤት አገሮች መካከል ሰላምንና አብሮነት ለማስረጽ ባደረጉት ጥረት የዘንድሮው የሰላም ኖቤል አሸናፊ ሆነው ተመርጠዋል።
ኖርዌይ ላይ አሸናፊው ይፋ ሲደረግ በኮሚቴው እንደተገለጸው፥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረት እውቅናና ማበረታቻ ያስፈልገዋል።
በእንግሊዝ ኪል ዩኒቨርሲቲ (Keele University) የህግ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ኢትዮጵያዊው አወሎ አሎ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው ገጭት እንዲያበቃ በማድረጋቸው ሽልማቱ ይገባቸዋል” ማለት ግጭቱ በሁለቱ አገሮች ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እንዳስከተለና የማይተካውን ብዙ ህይወት እንደቀጠፈም ተናግረዋል።”
ከኤርትራ ጋር የወረደው ሰላም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍ ያለ ሙገሳ ያስገኘላቸው ሲሆን ለሁለቱ አገሮች ወንድማማች ህዝቦች ደግሞ ትርጉሙ ከዚህ የላቀ ነበር። በተለይ ተለያይተው የነበሩ ቤተሶች ሲገናኙ ያፈሰሱት የደስታ እምባ ሰላም ምን ያህል ዋጋ እንዳላት በተጨባጭ የመሰከረ ነው።
- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአገር ውስጥ የጀመሯቸው የለውጥ ማሻሻያዎች የፖለቲካ እስረኞችንና ጋዜጠኞችን በመልቀቅ ተጀምሮ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው አስከመቀበል የዘለቀ ነው።
- ኢትዮጵያና ኤርትራ በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም. የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረውን አለመግባባት በመፍታት በቀጠናው የሰላም አየር እንዲነፍስ መሠረት ጥሏል።
- በሱዳን የተነሳውን የለውጥ ፍላጎት ከዳር ለማድረስ የተጀመረው ተቃውሞ በሰላም እንዲጠናቀቅና ተቃዋሚዎች ከወታደራዊ ቡድኑ ጋር ሰላም እንዲያወርዱ ያደረጉት አስተዋጽኦ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሱዳናውያን ልብ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዲያገኙ አድርጓቸዋል። በተለይ በሰኔ 2011 ዓ.ም ወደ ሱዳን በማቅናት ሁለቱን አገሮችለማስማማት የጀመሩትን ጥረት ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኢምሬት እንዲደግፉት በማድረግ ለውጤት እንዲበቃ አድርገዋል።
- ከዚህ ባለፈ ኤርትራና ጂቡቲ ጀርባ የተሰጣጡበትን አለመግባባቶች በሰላም እንዲቋጩና ለጋራ እድገት በጋራ እንዲነሱ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል።
- በደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር በአፍሪካ ቀንድአገሮች መካከል የኢኮኖሚ ህብረት እንዲኖር ያደረጉት ጥረት ለሰላምና ወንድማማችነት ያላቸውን ክፍት ልብ ያሳየ ነው።
- ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ከግብ ለማድረስና ሁሉንም ያማከለ እንዲሆን የማይደፈረውን ደፈረው ተንቀሳቅሰዋል።
- በዚህም ከዚህ በፊት በተቃዋሚነት ተፈርጀው ለእስር የተዳረጉትን አቶ ዳንኤል በቀለን የአገሪቱ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አድርገው የሾሟቸው ሲሆን ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ደግሞ የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር አድርገዋቸዋል።
- በተጨማሪም ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጋር ፊት ለፊት በመገናኘት በአገሪቱ መፃኢ ዕድል ላይ ውይይት ማድረጋቸው ሌላው ስኬታቸው ነው። በውጭ አገር ተቀምጠው የአገሪቱን ፖለቲካ ለመዘወር ሲጥሩ ከነበሩት ተቃዋሚዎች ጋርም ሰላም በማውረድ አገራቸው ገብተው እንዲታገሉ ሜዳውን ከፍተውላቸዋል።
- የደህንነቱንና የፍትህ ዘርፉንም ተአማኒ ለማድረግ በሩን ክፍት በማድረግ ተቋማዊ ለውጥ እንዲያመጡ እያገዙ ነው።
- በአገሪቱ ወደ ኋላ የቀረውን የሴቶች ተሳትፎ ከነበረበት አዘቅት በማውጣት ሴቶች በአመራርነት ቦታ ላይ ተመጣጣኝ ውክልና እንዲኖራቸውም አድርገዋል።
- በአንድ ጀንበር 200 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ለአየር ንብረት ለውጥ መስተካከል ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል። በዚህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አብሮነቱንና ዕውቅናውን ሰጥቷቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኖቤል ሽልማት 100ኛው አሸናፊ ናቸው። የኖቤል የሰላም ሽልማትን የሚያሸንፉ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች 900 ሺ ዶላር የሚሰጣቸው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በመጪው ታህሳስ ወር በኦስሎ ሽልማታቸውን ይወስዳሉ።
በአጠቃላይ 301 ዕጩዎች ለዚህ ታላቅ ክብር ታጭተው የነበረ ሲሆን ከነዚህ መካከል 223 ግለሰቦችና 78 ድርጅቶች ይገኙበታል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.