ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ተወያዩ

Home Forums Semonegna Stories ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ተወያዩ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #11904
    Semonegna
    Keymaster

    በለውጡ ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ጋር በተደረገው ውይይት ላይ የተነሱ ሲሆን፥ በአንዳንድ አካላት እየተፈጸሙ ያሉ ጥፋቶችን በማንሳት ቅዱስ ሲኖዶስ ለጠቅላይ ሚኒስትር አቅርበዋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ጳጉሜን 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠዋት በቢሯቸው ተወያይተዋል። የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት በተደረገው ውይይት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከለውጡ ወዲህ መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ ያለውን አቋምና ያከናወናቸውን ተግባራት አውስተዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እና ሌሎችም ሊቃነ ጳጳሳት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን የተከናወኑ በጎ ተግባራትን በመዘርዘር ምስጋና አቅርበዋል።

    በለውጡ ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎች በውይይቱ የተነሡ ሲሆን፥ በአንዳንድ አካላት እየተፈጸሙ ያሉ ጥፋቶችን በማንሳት ጳጳሳቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም የእርሳቸውም ሆነ የመንግሥታቸው ፍላጎት የተጠናከረች፣ ለሀገር ግንባታ የሚቻላትን ሁሉ የምታደርግና አንድነቷ የተጠበቀ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ማየት መሆኑን ገልጠዋል። የኢትዮጵያ የእምነት ተቋማት መጠናከርና አንድ መሆን ጥቅሙ ለእምነት ተቋማቱ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ጭምር መሆኑንም ተናግረዋል።

    የቀረቡት ችግሮች በለውጥ ውስጥ ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ያነሱ ሲሆን ዓይነታቸው ቢለያይም የተለያዩ የእምነት ተቋማት በለውጡ ሂደት ፈተና አጋጥመዋቸዋል፣ በመሆኑም ዕንቅፋት የሚፈጥሩትን አካላት መታገል ያለብን በጋራ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። የቀረቡትን ችግሮች በዝርዝር በማጥናትና በየደረጃው ካሉ አመራሮች ጋር በመነጋገር በጋራ እንደሚፈቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል። በሀገር ላይ የሚደርሱ ጥፋቶች በሁሉም ላይ የሚደርሱ በመሆናቸው መንግሥትና የእምነት ተቋማት በጋራ በመሥራት መፍታት እንዳለባቸው ገልጠዋል።

    በመጨረሻም የተፈጠሩትን ችግሮች የጋራ በማድረግ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነትና ክብር በጠበቀ መልኩ በጋራ ለመፍታት ከስምምነት ላይ ተደርሷል።

    ምንጭ፦ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስት ቢሮ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    —–
    ሌሎች ዜናዎች፦

    ቅዱስ ሲኖዶስ


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.