የጣልያን መንግስት አዲስ አበባን ከምፅዋ የሚያገናኘውን የባቡር መስመር ፕሮጀክት ጥናት ወጪ ለመሸፈን ተስማማ

Home Forums Semonegna Stories የጣልያን መንግስት አዲስ አበባን ከምፅዋ የሚያገናኘውን የባቡር መስመር ፕሮጀክት ጥናት ወጪ ለመሸፈን ተስማማ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #9318
    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– አዲስ አበባን ከኤርትራዋ ምጽዋ ጋር ለሚያገናኘው የባቡር መስመር ፕሮጀክት ጥናት ወጪ ለመሸፈን የጣሊያን መንግስት መስማማቱን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

    በጣሊያን ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጣሊያን አቻቸው ጁሴፔ ኮንቴ ጋር ተወያይተዋል። መሪዎቹ ከውይይቱ በኋላ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ጣልያን አዲስ አበባን ከምፅዋ ለሚያገናኘው የባቡር መስመር ፕሮጀክት የመጀመሪያ ጥናት ወጪ ለመሸፈን ተስማምታለች።

    ከጥናቱም በኋላ በሚገኘው ውጤት በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላት ጁሴፔ ኮንቴ እንደገለጹላቸውና ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ምስጋናውን እንደሚያቀርብ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናግረዋል።

    አዲስ አበባ እንደ ስሟ እንድትሆንና ነዋሪዎች ወጥተው ሲገቡ የሚዝናኑበትን ቦታ ከመፈለግ አንጻር በአዲስ አበባ በሚገኙ ኤምባሲዎች የተወሰነ ቦታቸውን ለህዝብ መዝናኛ ፓርክ እንዲያውሉ ጥያቄ ቀርቧል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የጣልያን መንግስትም ለዚህ ቅን ምላሽ መስጠቱን ተናግረዋል።

    ◌ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከጣሊያን አቻቸው ጁሴፔ ኮንቴ የሰጡት የጋራ መግለጫ

    የኢትዮጵያ መንግስት የብሔራዊ ቤተ መንግስቱን ግማሽ የህዝብ መዝናኛ ፓርክ ለማድረግ እየሠራ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጠቅሰዋል። በአዲስ አበባ ለተቸገሩ ወገኖች ምግብ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት ጣልያን በመዲናዋ የዳቦ መጋገሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ፍላጎት እንዳላትም አንስተዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጣልያን ቆይታቸው ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በልማትና በሰላም ውይይቶች እንዳደረጉና ከአቻቸው ጁሴፔ ኮንቴ ጋር ያደረጉት ሁለገብ ምክክርም የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማሳደግ ፈር ቀዳጅ እንደሆነ ተናግረዋል።

    በምስራቅ አፍሪካ ሰላም፣ ልማትና አንድነት እንዲረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የጣሊያን መንግስት ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ዶ/ር አብይ አመልክተዋል።

    በኢትዮጵያና በጣልያን መካከል የተደረገው ውይይት ፍሬያማ እንዲሆን በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚካሄዱ የሁለትዮሽ ውይይቶች አገራቱ በሰላም፣ በልማትና በቱሪዝም ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባም አንስተዋል። አገራቱ ለጋራ እድገትና ሰላም በጋራ እንሥራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

    በአጠቃላይ ከልዑካን ቡድኑ ጋር በጣልያን የነበራቸው ቆይታ ስኬታማ እንደነበረ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት። “እንደ ወንድም አገርና እንደ ጠንካራ ወዳጅ ከምናያት ከጣልያን የምንፈልገውን ነገር አግኝተናል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

    የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ምርቱን ለመጨመር እና የኤክስፖርት መጠኑን ለማሳደግ እየሠራ ነው

    የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጄሴፔ ኮንቴ በበኩላቸው ሁለቱ አገራት ታሪካዊ የሚባል ግንኙነት እንዳላቸውና በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራና በትብብር ለመሥራት መግባባታቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው የልማት ሥራዎች የጣሊያን መንግስት የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ቃል ገብተዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በጣልያን ጉብኝት ያደረጉት የጣሊያኑ አቻቸው ጁሴፔ ኮንቴ በ2011 ዓ.ም መጀመሪያ በኢትዮጵያ ጉብኝት ባረደጉበት ወቅት ባቀረቡላቸው ግብዣ መሠረት ነው።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጣሊያን ቆይታቸው ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ፣ ከዓለም የምግብ ድርጅት ዋና ዳሬክተር ዴቪድ ቤዝሊ፣ ከተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆዜ ግራዚያኖ ዳ ሲልቫና ከግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ፈንድ ፕሬዝዳንት ጊልበርት ሆዉንግቦ ጋር ተወያይተዋል።

    በሌላ በኩል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተጓዘው የልዑካን ቡድን በሮም ከጣሊያን ባለሃብቶች ጋር ውይይት አካሂዷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ አምባሳደር ፍጹም አረጋ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አበበ አበባየሁን ያካተተው የልዑካን ቡድን ለባለሃብቶቹ ሃገሪቱ ስላላት የተለያዩ የኢንቨሰትመንት ዘርፎችና አማራጮች ማብራሪያ መስጠታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

    በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ምርታቸውን ወደውጭ ሀገራት መላክ ጀምረዋል

    ካርቪኮ ግሩፕ በአሁኑ ሰዓት በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ23 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ ግንባታውን እያጠናቀቀ ሲሆን፥ በጣሊያንና በቬትናም በሚገኙ ፋብሪካዎች የሠራተኛ ስልጠና በማድረግ ዝግጅቱን ለመጀመር በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

    በውይይቱ የተገኙት ሌሎች ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በመድኃኒት፣ በግንባታ፣ በግብርና ማቀነባበርያ እና አልባሳት ዘርፍ በስፋት ለመሰማራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ተብሏል።

    በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራው የልዑካን ቡድን ከጣልያን ቆይታው በኋላ በስዊዘርላንድ ዳቮስ ከተማ በሚካሄደው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ለመሳተፍ ወደ ስፍራው ያቀናል ተብሎ ይጠበቃል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከጣሊያን አቻቸው ጁሴፔ ኮንቴ ጋር


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.