በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በተካሄደው የሰላም ንቅናቄ ላይ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ እና በተለያዩ ሙያዎች ላይ የተሰማሩ የአገራችን ታዋቂ ሰዎች ስለ ሰላም እና በሰላም እጦት ምክንያት የሚከሰቱ አስከፊ ጉዳቶች ለታዳሚው አቅርበዋል።
ወልቂጤ (ሰሞነኛ)– “ጥበብ ለሰላም” በሚል መሪ ቃል በጉራጌ ዞን ከሚገኙ 17 ወረዳዎችና ከ4 ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የአገራችን ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ አመራሮች፣ የሲቪል ሰርቪስ (civil service) ሠራተኞች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ትልቅ ስብሰባ/ውይይት በድምቀት ተካሂዷል።
በዚህም ዞን አቀፍ የሰላም ንቅናቄ የአገራችን ታዋቂ ሰዎች (በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል ደራሲና መምህር ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ ደራሲ እንዳላጌታ ከበደ፣ ደራሲ ህይወት ተፈራ፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራልና የሙዚቃ ሀያሲው አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት እና ደራሲ ተስፋዬ ጎይቴ ስለ ሰላም እና በሰላም እጦት ምክንያት የሚከሰቱ አስከፊ ጉዳቶች ለታዳሚው አቅርበዋል። የሁሉም የመቋጫ ሀሳብ የአገራችን ህዝቦች አጥር ሳይገድባቸው በብሔር፣ በዘር፣ በጎሳ፣ በሀይማኖትና በመሳሰሉ ከፋፋይ ጉዳዮችን ትተው በአንድነትና በሰብዓዊነት ስሜት ተዋደውና ተቻችለው እንደቀድሞው አብረው ሊኖሩ እንደሚገባ ነው።
በዚህ ታላቅ የሰላም ንቅናቄ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማልና የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ወ/ሮ መሠረት አመርጋ ሰላም ለሁሉም ጉዳዮች መሠረት መሆኑ እና ሰላም በሌለበት ምንም ሊኖር እንዳማይችል ገልፀው የዞኑ ህዝብ በሙሉ ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል።
“ጥበብ ለሰላም” በሚል በተካሄድው በዚህ መርሀግብር ታዋቂ የአገራችን ደራሲያን፣ የጉራጌ ዞን የባህል ኪነት ቡድን፣ ከወልቂጤና ከቡታጅራ ከተማ አስተዳደሮች የኪነ ጥበብ ክበባት የተውጣጡ አማተር ኪያንያን ድንቅ የሙዚቃ፣ ድራማና የሥነ ግጥም ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል። እንዲሁም በሱዑዱ አብደላ የተሳሉ ድንቅ የሥነ ስዕል ሥራዎቹን አቅርቧል። የ11ኛ ክፍል ተማሪ ይዘዲን የፈጠራ ሥራዎች በመድረኩ ከቀረቡ ሥራዎች ይገኝበታል።
በመጨረሻም ለፕሮግራሙ መሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት የዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ያዘጋጃቸው ባህላዊ ስጦታዎች፣ የማበረታቻ ሽልማትና የምስጋና የምስክር ወረቀት አበርክቷል።
ምንጭ፦ የጉራጌ ዞን አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦