ጨፌ ኦሮሚያ ወ/ሮ ሎሚ በዶን አፈ ጉባዔ አድርጎ ሲመርጥ፥ የአግልግሎት ሰጪ ተቋማትን ቁጥር ከ42 ወደ 38 ዝቅ አድርጓል

Home Forums Semonegna Stories ጨፌ ኦሮሚያ ወ/ሮ ሎሚ በዶን አፈ ጉባዔ አድርጎ ሲመርጥ፥ የአግልግሎት ሰጪ ተቋማትን ቁጥር ከ42 ወደ 38 ዝቅ አድርጓል

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #7971
    Semonegna
    Keymaster

    ጨፌ ኦሮሚያ ባደረገው ሶስተኛ አስቸኳይ ጉባዔ ላይ ወ/ሮ ሎሚ በዶ አፈ ጉባዔ ሆነው ሲመረጡ አዲስ በጸደቀ አዋጅም በክልሉ በቁጥር 42 የነበሩት የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቁጥራቸው ወደ 38 ዝቅ ተደርጎ በአዲስ መልክ እንዲዋቀሩ ተወስኗል።

    አዳማ (ሰሞነኛ)– የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) በአዳማ ከተማ እያደረገ ባለው አራተኛ ዓመት፣ አምስተኛ የሥራ ዘመን፣ ሶስተኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ባደረገው ውሎ ወ/ሮ ሎሚ በዶን አፈ ጉባዔ አድርጎ መርጧል።

    ወ/ሮ ሎሚ በዶ  በአሁኑ ወቅት የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ የሆኑትን አቶ እሸቱን ደሴን የሚተኩ ሲሆን በጉባዔው ላይ እንደተገለጸው አቶ እሸቱ ደሴ በተደራረበባቸው የሥራ ኃላፊነት ምክንያት ከቦታቸው እንዲነሱ ተደርገዋል።

    በተያያዘ ዜና ጨፌ ኦሮሚያ እያደረገ ባለው የጠቅላላ ጉባዔ ላይ የክልሉን የሥራ አስፈጻሚ አካላት መልሶ ለማደራጀት እና በተለያየ እርከን ደረጃ ያሉትን ሰዎች ስልጣንና ኃላፊነታቸውን ለመወሰን የሚያስችል አዋጅ አጽድቋል።

    በተጨማሪም ጨፌ ኦሮሚያ  የየክልሉን  ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለማቋቋም የወጣው ረቂቅ አዋጅ አጽድቋል። በዚህ ረቂቅ አዋጅ መሠረት ከዚህ በፊት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የፍትህ ቢሮ ተብሎ ይጠራ የነበረው በአዲሱ አደረጃጀት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተብሎ ተሰይሟል።

    በክልሉ ውስጥ በርካታ የአስተዳደራዊ ችግሮች መኖራቸውን፣ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ብዙ ተግባራትና ማሻሻያዎች ቢከናወኑም ሕዝቡ እያቀረበ ያለውን ቅሬታ አሉታዊ በሆነ መልኩ ቀርፎ ለሕዝቡ እርካታን መፍጠር ስላልተቻለ የመዋቅራዊ አደረጃጀት ለውጥ ማድርግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ አስረድተዋል።

    አቶ ለማ እንዳሉት የተቀላጠፈና ጥራት ያለው አገልግሎት ከመስጠት አኳያ ጉልህ ክፍተት እንዳለና፣ በተለያዩ ቢሮዎች ተሀድሶ ተብለው የተጀመሩ የ አሠራር ለውጦችም በሰራተኞችና አገልግሎት ሰጪዎች ላይ አመለካከት ከመቀየር (ከማደስ) ባለፈ በሕዝቡ ዘንድ በሚያገኘው አገልግሎት እርካታን ሊፈጥር እንዳልቻለ ገልጸዋል።

    በዚህም መሠረት የተጀመሩ ለወጦች አሁንም እንዲቀጥሉና፣ ተጨማሪ ወይም አማራጭ ለውጥ የሚያስፈልጋቸው ቦታውን በተገቢው መንገድ ትግባራቸውን እንዲወጡ መዋቅራዊና አደረጃጀታዊ ለወጥ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ እንደተገኘ አቶ ለማ መገርሳ ተናግረዋል።

    በጸደቀው አዋጅ መሠረት ከዚህ በፊት በቁጥር 42 የነበሩት የክልሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት (ቢሮዎች) ወደ 38 ዝቅ ተደርገው የተዋቀሩ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ በክልሉ ውስጥ በዞን፣ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ የተዋረዱ የአገልግሎት ተቋማትም በአዋጁ መሠረት በአዲስ እንደሚዋቀሩ ከጠቅላላ ጉባዔል ለማወቅ ተችሏል።

    ጨፌ ኦሮሚያ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.