Home › Forums › Semonegna Stories › ፊቼ ጫምባላላ – የሲዳማ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል – በድምቀት ተከበረ — አይዴ ጫምበላላ!
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 7 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
May 31, 2019 at 5:53 am #10980SemonegnaKeymaster
ፊቼ ጫምባላላ በዩኔስኮ ከማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ ከተመዘገቡ ቅርሶቻችን ውስጥ አንዱ ነው። የፊቼ ጨምበላላ በዓል የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት በዓል መሆኑን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ ገልጸዋል።
ሀዋሳ (ሰሞነኛ) – የሲዳማ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል የሆነው ፊቼ ጫምባላላ በሀዋሳ ከተማ በድምቀት ተከብሯል። በበዓሉ ላይ ከተለያዩ ወረዳዎች የመጡ የሲዳማ አባቶች የቄጣላ ሥነ-ስርአት አድርገዋል።
በሀዋሳ ጉዱማሌ አደባባይ በልዩ ሁኔታ የተከበረው በዓል ላይ የሲዳማ ሴቶች በባህላዊ አለባበስ እና ባህላዊ የፀጉር አሰራር አሸብርቀው የበዓሉ ድምቀት ሆነዋል።
በበዓሉ ላይ ከተለያዩ ክልሎች የተጋበዙ ልዑካንም የተገኙ ሲሆን፥ ከደቡብ ክልልም ከተለያዩ ብሄረሰቦች የተውጣጡ ልዑካን ታዳሚዎች ሁነው ነበር።
የፊቼ ጫምባላላ በዓል በዩኔስኮ ከማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ ከተመዘገቡ ቅርሶቻችን ውስጥ አንዱ ነው። የፊቼ ጨምበላላ በዓል የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት በዓል መሆኑን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ ገልጸዋል።
በዓሉ በጋራና በድምቀት እንዲከበር ዋጋ ከፍለው በዓሉን እዚህ ላደረሱት አባቶች ምስጋና አቅርበዋል – አቶ ሚሊዮን። አክለም በዓሉ በይቅርታና በፍቅር የምናከብረው በዓል በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፍቅር እንዲያከብረውም ጥሪ አቅርበዋል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፥ ፊቼ ጫምበላላ የኛም ባህል በመሆኑ ለማድመቅ ሳይሆን ለማክበር ነው ወደ ሀዋሳ የመጣነው ሲሉ ገልጸዋል። ባህሉ ተጠብቆ የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲቆይ አባቶቻችን ታላቅ ሚና በመጫወታችሁ ምስጋና ይገባችሀል በማለትም ተናግረዋል።
አቶ ሽመልስ መልዕክታቸውን ከማጠቃለላቸው በፊት የሲዳማና የኦሮሞ ህዝብ አብሮ ብዙ መስዋዕትነትን የከፈለና ድል ያስመዘገበ ህዝብ ነው ሲሉም ገልጸዋል – አቶ ሽመልስ። እኩልነትን፣ ነፃነትንና ወንድማችነትን በማጠንከርና በማሳደግ የተገኘውን ድል ለማስቀጠል መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል። ልዩነታችንን ጠብቀን አንድ በሚያደርጉን ነገሮች ላይ በመሥራት ለበለጠ ድል መትጋት ይጠበቅብናል ብለዋል። በዚህም የሁለቱም ወገኖች የሆኑት ኤጀቶና ቄሮዎች ተባብረው ለክልሎቻቸውም ሆነ ለኢትዮጵያ እድገት መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው፥ ባህሉ ከትውልድ ትውልድ ተጠብቆ እንዲተላለፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ተገቢውን ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል። ከቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን የወረስናቸውን እንደ ፍቼ ጫምበላላ ያሉ ባህሎቻችንን ጠብቀንና ተንከባክበን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የፖለቲካ አክቲቪስትና የኦሮሚያ ሚድያ ኔትዎርክ (ኦ.ኤም.ኤን) ቴሌቭዥን ጣቢያ መሥራች የሆነው አቶ ጃዋር መሀመድ በበኩሉ፥ ፊቼ ጫምበላላ በዓልን ያለ አንዳች ችግር ማክበር መቻሉ እንደሚያስደስት ገልጿል። በዓሉ ቀደምት አባቶች በከፈሉት መስዋዕትነት እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ እየተከበረ ያለ ቅርስ መሆኑን ተናግሯል። በዓሉ እንዲህ እንዲከበር ኤጀቶና ቄሮዎች ለሰላም ያደረጉት ትግል ውጤት መሆኑንም ገልጿል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.