Home › Forums › Semonegna Stories › ፓምፋሎን ― ኢትዮጵያዊው ቦብ ማርሌ?
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 5 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
August 4, 2019 at 1:10 am #11565AnonymousInactive
ፓምፋሎን ብዙ ልታይ ልታይ የሚል ሰው አይደለም። ሙዚቃውን ለሕዝብ በሚያቀርብበት ጊዜ የአድማጮቹ ትኩረት በመልዕክቱ ላይ እንዲሆን እንደሚፈልግ ይናገራል። ለዚህም ነው ብዙ የሙዚቃ ክሊፖችን የማይሠራው።
ቅድመ ነገር – ለምን የሙዚቃ ስሙን ፓምፋሎን ብሎ ሰየመው?
የሁለት ሰዎችን ሕይወት የሚተርክ በልጆች መጽሐፍ ውስጥ ያለ ታሪክ ነው። አንደኛው ገፀ-ባሕሪ መንፈሳዊ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ዓለማዊ ነበር።
መንፈሳዊው ከሰዎች እና ከዓለማዊ ኑሮ ርቆ ለሠላሳ ዓመታት ከፈጣሪው ጋር በመወያየት ቆየ። አንድ ቀን ድንጋይ ላይ ቁጭ ብሎ ሳለ ለመንፈሳዊው ግለሰብ ፈጣሪ ይገለጥለትና ወደ ፓምፋሎን እንዲሄድ ይነግረዋል።
ይህም ሰው ለመንፈሳዊ ጥያቄዎቹ እንዴት ወደ ፓምፋሎን እንደተላከ ሊገባው አልቻለምና ፈጣሪውን “ለምን ወደ እርሱ ትልከኛለህ?” ብሎ ሲጠይቅ “በሰዎች ዓይን ፓምፋሎን ዓለማዊ ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን የሰው ልጅ መንፈሳዊነት በልቡ ያለ እንጂ በሰዎች የሚታይ አይደለም” ብሎ ይመልስለታል። “እኔም ለዚያ ነው የሙዚቃ ስሜን ፓምፋሎን ያልኩት” ይላል ፓምፋሎን።
የፓምፋሎን ተረት በሩስያዊ ደራሲ የተፃፈ ቢሆንም ፓምፋሎን ግን ከልጅነቱ ጀምሮ በጀርመን ሃገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ ነው። ያለ እናትና አባት ያደገው ፓምፋሎን ከ16 ዓመቱ ጀምሮ ነው ራሱን ማስተዳደር የጀመረው።
ስለ ሕይወት ታሪኩ እና ወደ ጀርመን እንዴት እንደሄደ ሲጠየቅ “እሱን ሌላ ጊዜ በሌላ መልኩ ለሕዝብ ለማቅረብ ስለምፈልግ ለጊዜው ስለ ታሪኬ ለመናገር ዝግጁ አይደለሁም” ይላል።
በየወቅቱ ወደ ኢትዮጵያ ጎራ የሚለው ፓምፋሎን ነገሮች ቢመቻቹለት ኑሮውን ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያደርግ ይወዳል። ለጊዜው በሙዚቃ ስሙ ብቻ እንዲታወቅ እንደሚፈልግ ይናገራል።
ወደ ሙዚቃ የገባው በተለያዩ ነገሮች ተገፋፍቶ ነበር። “የተለያዩ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ የምጠቀምበት ስለሆነ ነው ሙዚቃ መሥራት የጀመርኩት። ጥበበኛ ነኝ ወይም ችሎታ አለኝ ማለትም አልፈልግም ምክንያቱም ለጊዜው ሙዚቃውን መልዕክት ማስተላለፊያ ነው ያደረግኩት” በማለት በትህትና ይናገራል።
ፓምፋሎን ብዙ ልታይ ልታይ የሚል ሰው አይደለም። ሙዚቃውን ለሕዝብ በሚያቀርብበት ጊዜ የአድማጮቹ ትኩረት በመልዕክቱ ላይ እንዲሆን እንደሚፈልግ ይናገራል። ለዚህም ነው ብዙ የሙዚቃ ክሊፖችን የማይሠራው።
“ለጊዜው የሙዚቃ ዓለሙን ተቀላቀልኩ እንጂ ወደፊት ሌሎች ነገሮችን የመሥራት ፍላጎት አለኝ” የሚለው ፓምፋሎን በሙዚቃዎቹ የተለያዩ ሰዎችን ንግግሮች ያካትታል። ከእነዚህም መካከል የማንዴላ፣ የማልኮም ኤክስ እና የዶ/ር አብይ አሕመድ ይገኙበታል።
ለምን ብሎ ሲጠየቅም በአንድ ወቅት ንግግሮቹ ስሜቱን ከነኩት የሙዚቃውን መንፈስ ለአድማጮቹ ለማስተላለፍ እንደሚያስችሉት በማሰብ እንደሆነ ይናገራል።
ገቢው በሙዚቃ ሥራዎቹ ላይ እንዳልተመሰረት የሚናገረው ኢትዮ-ጀርመናዊው ሙዚቀኛ “ሙዚቃዬ እያበላኝ አይደለም። የምተዳደረው በግራፊክ ዲዛይን፣ ፎቶግራፎችን በመሸጥ እና ሌሎች ነገሮች በመሥራት ነው” ይላል።
የሕይወቱን ሦስት አራተኛ በጀርመን ስለኖረ አልፎ አልፎ በጀርመንኛ መልዕክቱን ለማስተላለፍ ይቀለዋል። ሆኖም ግን በአማርኛ ነው አልበሙን የሠራው። “ቋንቋ እንደአጠቃቀማችን ነው እና ጀርመንኛው ቀለል ይለኛል ግን ሆን ብዬ በሃገሬ ቋንቋ ነው ሙዚቃዬን የምሠራው ምክንያቱም የኢትዮጵያ ልጅ ነኝ” በማለት ይናገራል።
አክሎም “በልጅነቴ የተለያዩ የራፕ ቡድኖችን ተቀላቅዬ በጀርመንኛ ራፕ አደርግ ነበር። ሳድግ ግን ምንድነው ማድረግ የምፈልገው ብዬ አሰብኩበት። መልዕክቴን ለኢትዮጵያ ማስተላለፍ እንደሆነ ሳውቅ በአማርኛ መሥራት ጀመርኩኝ” ይላል።
የሚሠራቸውን የተለያዩ የጥብብ ሥራዎች በእኩል እንደሚመለከት የሚጠቅሰው ፓምፋሎን ቢገደድ እንኳን አንዱን ብቻ ለመመረጥ በጣም እንደሚከብደው የሚናገረው በመግለጽ እየሳቀ “ከሙዚቃውና ከፎቶግራፍ ምረጥ የሚለኝን ሰው እንደጠላት ነው የምቆጥረው” በማለት ይናገራል።
“የግጥም አፃፃፌ እራሱ ከኢትዮጵያ ገጣሚያን የተለየ ነው። ብዙዎችም ለየት እንደሚል ይነግሩኛል” በማለት በሃገሩ ቋንቋ ሥራዎቹን ለሕዝብ ማቅረብ መቻሉ እንደሚያስደስተው ይገልፃል።
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.