Home › Forums › Semonegna Stories › አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ የመጀመሪያዋ የኢፌዴሪ ሴት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ
Tagged: ሳህለወርቅ ዘውዴ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years, 2 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
October 25, 2018 at 3:08 am #8238SemonegnaKeymaster
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄዱት ልዩ ስብሰባቸው አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን 4ኛው የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሄር (ፕሬዝዳንት) አድርጎ በሙሉ ድምፅ መርጧል።
ፕሬዝዳት ሳህለወርቅ ዘውዴ ቃለ መሃላ ፈፅመው ኃላፈነታቸውን በትጋትና በታኝነት አገርና ህዝብን ለማገልገል ቃል ገብተዋል።
አምባሳደር ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ላለፉት አመስት ዓመታት በፕሬዝዳንትነት ላይ የነበሩትን ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን በመተካት አገሪቱን በፕሬዝዳንትነት የሚመሩ ይሆናል። ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመም ከተመራጯ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር የስልጣን ርክክብ አድርገዋል።
አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ማን ናቸው?
ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሲሆን የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ነው። አራት ሴት ልጆች ለነበሯቸው ወላጆቻቸው የመጀመሪያ ልጅ የሆኑት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገና በ17 ዓመታቸው ነጻ የትምህርት ዕደል አግኝትው ወደ ፈረንሳይ በማቅናት ሞንትፔልየር (Montpellier) በምትባለው የፈረንሳይ ከተማ በሚገኘው ዮኒቨርሲቲ ኦፍ ሞንትፔልየር (University of Montpellier) የተፈጥሮ ሳይንስን አጥንተዋል። በሀገረ ፈረንሳይ ለዘጠኝ ዓመታት ከቆዩ በኋላ ወደ ኢትዮጵይ በመመለስ በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ የሕዝብ ግንኙነት ክፍልን ማገልገል ጀመሩ። ቆይተውም የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉን በበላይነት መርተዋል። ከዚያም ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመዘዋወር በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች አገልግለዋል።
ወሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ በአምባሳደርነት ለመሾም ከአምባሳደር ዮዲት እምሩ ቀጥሎ ሁለተኛዋ እንስት ናቸው። በመጀመሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙትም ሴኔጋል ሲሆን የአምባሳደርነት ስልጣናቸውም ሴኔጋልን ጨምሮ ማሊን፣ ኬፕ ቨርዴን፣ ጊዚ ቢሳውን፣ ጋምብያን እና ጊኒን (እ.ኤ.አ 1989–1993) ያጠቃልል ነበር። ቀጥሎም እ.ኤ.አ 1983–2002 በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደርና በኢጋድ (IGAD) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል። እ.ኤ.አ ከ2002 ጀምሮ እስከ 2006 ድረሰ በፈረንሳይ (ሞሮኮን ጨምሮ) የኢትዮጵያ አምባሳደርና በዩኔስኮ (UNESCO) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል። እ.ኤ.አ ከ2006 ጀምሮ እስከ 2009 ድረስ በአፍሪካ ህብረት (AU) እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው ሀገራቸውን አገልግለዋል።
ከሀያ ዓመታት በላይ በተለያዩ ሀገራትና ዓለማቀፋዊ ድርጅቶች የኢትዮጵያ አምባሳደርና ተጠሪ በመሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን ያገለገሉት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ እ.ኤ.አ በ2009 የተበባሩት መንግስታት ድርጅትን (ተመድ) በመቀላቀል የድርጅቱ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ የተቀናጀ ሰላም ግንባታ መሪ (Head BINUCA) በመሆን ማገልገል ጀመሩ። ይህ አገልግሎታቸውም ወደ ሚቀጥለው ኃላፊነት አሸጋግሯቸው እ.ኤ.አ በ2011 ዓም የዚያን ጊዜ የተመድ ጠቅላይ-ጸሀፊ ባን ኪ-ሙን (Ban Ki-moon) አዲስ ለተቋቃመው በናይሮቢ የተመድ ጽህፈት ቤት (UNON) የመጀመሪያዋ ጠቅላይ-መሪ አድርገው ሾማቸው። በዚያም ለሰባት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ እ.ኤ.አ በሰኔ ወር 2010 የአሁኑ የተመድ ጠቅላይ-ጸሀፊ አንቶንዮ ጉቴሬስ (António Guterres) አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን በተመድ ጠቅላይ-መሪ ስር (Under-Secretary-General) የአፍሪካ ህብረት ልዩ ተጠሪ (UN’s Special Representative to the AU) እና በአፍሪካ ህብረት ውስጥ የተመድ ጽህፈት ቤት ዋና ኃላፊ (Head of UNOAU) አድርገው ሾሟቸው እስካሁን ድረስ በዚሁ ሹመታቸው እያገለገሉ ይገኛሉ።
አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ባለትዳርና የሁለት ወንድ ልጆች እናት ናቸው።
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.