በሦስት ዓመታት ከ70 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ያገኛሉ

Home Forums Semonegna Stories ትምህርት፣ ጤና እና ሕብረተሰብ ― ሰሞነኛ ዜናዎች፣ መረጃዎች በሦስት ዓመታት ከ70 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ያገኛሉ

#49343
Semonegna
Keymaster

በሦስት ዓመታት ከ70 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ያገኛሉ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) – በኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ከ70 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ እንዲኖራቸው የሚደረግ መሆኑን የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ፕሮጀክት አስታወቀ።

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር በዲጅታል መታወቂያ የሕግ አግባብነት፣ ዓላማና አዋጅ ጋር በተያያዘ ውይይት አድርጓል።

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት የባለድርሻ አካላት ግንኙነት መሪ ሚና አወል፤ ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ አንድን ሰው ማንነት በእርግጠኝነት መለየት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። መታወቂያው ዕድሜ፣ ፆታ፣ የአስር ጣቶች አሻራ፣ የመኖሪያ አድራሻና ሌሎች ገላጭ መረጃዎችን የሚይዝ መሆኑንም አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሮችና በገጠር አካባቢ ያሉ ሰዎች እንዴት መመዝገብ ይችላሉ የሚለውን ለማወቅ በአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ሲዳማ ክልሎች 125 ሺህ ዜጎች በሙከራ ደረጃ ተመዝግበው ውጤታማነቱ ተረጋግጧል ብለዋል። በ2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሚኖሩ 12 ሚሊዮን ዜጎችን የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል። ለዚህም በንግድ ባንክ፣ ኢትዮ-ቴሌኮም እና መሰል አገልግሎት በሚሰጥባቸው ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት ሲሄዱ በቀላሉ መመዝገብ ይችላሉ ብለዋል።

የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮዳሄ ዘሚካኤል፥ ዲጅታል መታወቂያ በኢትዮጵያ የሚኖር ማንኛውም ዜጋ የራሱን ማንነት የሚገልጽበት መለያ ነው። ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ በኪስ የሚያዝ ወረቀት ሳይሆን የራሱ መለያ /ፋይዳ/ የሚባል ቁጥር ብቻ ይዞ በማንኛውም ቦታ በቁጥሩ ምክንያት አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ዘመናዊ አሠራር መሆኑንም አስረድተዋል። ከቤቱ ሆኖ የባንክ አካውንት መክፈት፣ የኢንሹራንስ አገልግሎት ማግኘትና በአገልግሎት ሰጭውና ተቀባዩ ዘንድ መተማመን መፍጠር ያስችላል ብለዋል።

በዚህም እስከ 2018 ዓ.ም ከ70 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ እንዲኖራቸው ለማስቻል ዕቅድ መያዙን አቶ ዮዳሄ ተናግረዋል። የፎቶ ኮፒና ሌሎች የህትመት ሥራዎች ሁሉ የንግዱ ማኅበረሰብ በየሱቆቹ ማስመዝገብ የሚችልበትን አሠራር እንዘረጋለን ሲሉም ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፥ ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ብዙ ትኩረት ሳይሰጠው የቆየ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ለጤናው ዘርፍ የጎላ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያ ባለመኖሩ ምክንያት ዲጅታል የጤና መሣሪያዎችን ወደ ሥራ ማስገባት እንዳልተቻለም ጠቅሰዋል። በመሆኑም ብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያው ሥራ መጀመር በመላ ሀገሪቱ ያሉ ከ40 ሚሊየን በላይ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች መታወቂያቸውን በቀላሉ አድሰው የተቀላጠፈ የጤና አገልግሎት ማግኘት ያስችላቸዋል ብለዋል። የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ የኢትዮጵያን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸው በቅርቡ ወደ ሥራ እንዲገባ አስፈላጊውን ሁሉ እገዛና ትብብር እናደርጋለን ሲሉ አረጋግጠዋል። ዘገባው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ነው።

የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ