ትምህርት፣ ጤና እና ሕብረተሰብ ― ሰሞነኛ ዜናዎች፣ መረጃዎች

Home Forums Semonegna Stories ትምህርት፣ ጤና እና ሕብረተሰብ ― ሰሞነኛ ዜናዎች፣ መረጃዎች

Viewing 15 posts - 1 through 15 (of 15 total)
  • Author
    Posts
  • #8979
    Semonegna
    Keymaster

    የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የካንሰርና የልብ ህክምና ማዕከል ግንባታ 56 በመቶ ደርሷል

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ከ986 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የሚያስገነባው የካንሰርና የልብ ህክምና ማዕከልን በተያዘለት ግዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን ተገለጸ።

    የሆስፒታሉ የምህንድስና ኢንጂነሪንግ ክፍል አስተባባሪ ኢንጅነር ሞቲ አሰፋ ለ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደገለጹት እየተገነቡ ያሉት የካንሰርና የልብ ህክምና ማዕከላት መጀመሪያ አካባቢ ቶሎ ወደ ሥራ ያለመግባትና በብረት ዋጋ ንረት ምክንያት መዘግየት የታየበት ቢሆንም ግንባታው 56 በመቶ ደርሷል።

    የማዕከላቱ መሠረት በ12 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን ባለ12 እና 10 ወለል ህንፃዎች ይኖሩታል ብለዋል። ህንፃዎቹ ከ600 በላይ የመኝታ ክፍሎች እንደሚኖራቸው ነው ኢንጂነር ሞቲ ያብራሩት።

    ከዚሁ ጎን ለጎን ከተጀመረ ስምንት ዓመታትን ያስቆጠረውና ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የእናቶችና ህጻናት ማዕከል ባለ 8 ወለል ህንፃም በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

    በህንጻ ተቋራጩ እና ክትትል በሚያደርገው ተቆጣጣሪ ድክመት ምክንያት ተጓትቶ የነበረው ፕሮጀክቱ ባለሙያዎችን በመቀየር በአሁኑ ወቅት ሥራው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝና በዚህ ሳምንት ከፊሉን ሥራ ለማስጀመር እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል።

    ◌ Ethiopia: Are Ethiopian hospitals constructed in environment-suitable and climate-friendly way?

    የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሜዲካል አገልግሎት ዋና ፕሮቮስት ዶ/ር ወንድማገኝ ገዛኸኝ በበኩላቸው ማዕከላቱ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ በሀገሪቱ በካንሰርና በልብ ህመም ለሚሰቃዩ ዜጎች የሚሰጡት ጥቅም ከፍተኛ ነው ብለዋል። በተለይ ህክምናዎቹ የሚጠይቁት ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ አብዛኛውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ያደርጋል ነው ያሉት።

    ከሰባት ዓመት በፊት ሆስፒታሉ በቀን ከ500 ያልበለጡ ህሙማንን ብቻ ያስተናግድ እንደነበር የተናገሩት ዶክተር ወንድማገኝ፥ በአሁኑ ወቅት በየቀኑ ለሁለት ሺህ ሰዎች ህክምና አገልግሎት እያገኙ ነው ብለዋል።

    በአሁኑ በወቅት በወር ለ1 ሺህ 500 እናቶች የወሊድ አገልግሎት እየተሰጠ ሲሆን በግንባታ ላይ የሚገኘው የእናቶችና ህፃናት ህንፃ ሲጠናቀቅ በቀን ለ400 እናቶች የወሊድ አገልግሎት መስጠት እንደሚችል ጠቁመዋል።

    ህንፃው 15 የማዋለጃ ክፍሎች እንደሚኖሩት የጠቀሱት ዶ/ር ወንድማገኝ በቅርቡ አገልግሎቱን ለማስጀመር ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።

    የሆስፒታሉ ሀኪም ዶ/ር ዮናስ ገብረጊዮርጊስ በበኩላቸው የሚገነቡት የካንሰርና የልብ ህክምና ማዕከላት በሀገሪቱ በመንግስት በብቸኝነት አገልግሎት እየሰጠ ካለው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተጨማሪ በመሆን ህብረተሰቡ የጤና አገልግሎቱን በአቅራቢያው እንዲያገኝ ያስችላል ብለዋል።

    የማዕከላቱ መገንባት በሀገሪቱ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣውን የካንሰር ህመም ለመከላከል የሚሰጠው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ዮናስ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

    ፕሮጀክቱ በሁለት ዓመት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም ተነግሯል።

    ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የካንሰርና የልብ ህክምና ማዕከል

    #9525
    Anonymous
    Inactive

    ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የመካንነት ምርመራ እና ሕክምና የፊታችን የካቲት 3 ሊጀምር ነው
    —–

    ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የመካንነት ምርመራ እና ሕክምና የፊታችን የካቲት 3 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡

    ሆሰፒታሉ በዓመት 5መቶ ጥንዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጀቱት ማጠናቀቁንም ተነገሯል፡፡

    ከሚቀጥሉት ሁለት አመታት በኋላ በዓመት ተቀብሎ የሚስተናግዳቸውን ጥንዶች 2ሺህ የማደረስ እቅድ ያለው መሆኑም ታውቋል፡፡

    የእናቶችና የህጻናት ጤና አግልግሎት ማስፋፈያ ያደረገው ሆስፒታሉ አሁን ላይ በየወሩ በአማካይ ለ1 ሺህ እናቶች የወሊድ አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል፡፡

    ለዚሁ አገልግሎትም 400 አልጋዎችን የሚይዝ ባለስምንት ወለል ሕንፃ እያስገነባ ሲሆን÷ በአንድ ወር ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎይ ይጠበቃል፡፡

    ባለፉት ጊዚያትም የእናቶችና ህፃናትን ሞት በመቀነስ ከፍተኛ ድረሻ እንደነበረው ነው የሆስፒሉ መረጃ የሚያመለክተው፡፡

    ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን

    #16136
    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ የ2020 አለም አቀፍ (P3) ተጽዕኖ ፈጣሪ ሽልማት አሸናፊ ሆነ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – አሜሪካ፥ ሻርሎትስቪል ከተማ በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቨርጂንያ ዳርደን የቢዝነስ ኢንስቲትዩት (the University of Virginia, Darden School of Business) ዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ጽሕፈት ቤት ኮንኮርዲያ (ኒው ዮርክ) በሚያዘጋጀው ዓለምአቀፍ የተጽዕኖ ፈጣሪዎች ዓመታዊ ጉባዔ ላይ (Concordia Summit) የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ የ2020 “የሕዝብና የግል ተቋማት አጋርነት የተጽዕኖ ፈጣሪዎች” (P3 Impact Award) አሸናፊ በመሆን ተመርጧል።

    የኢትዮጵያ ዓይን ባንክ አሸናፊ የሆነው ከቀረቡት አምስት ዕጩዎች መካከል የተሻለ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑ ተገልጿል።

    የውድድሩ አሸናፊ የሆነው የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን በዓይን ብሌን ጠባሳ እና ተያያዥ ምክንያት የሚከሰተውን ዓይነ-ስውርነት ለማጥፋት እያደረገ ባለው ከፍተኛ ጥረት እና ለማኅበረሰቡ እያበረከተ ባለው ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሆነ ተነግሯል።

    የኢትዮጵያ ዓይን ባንክ “የሕዝብና የግል ተቋማት አጋርነት የተጽዕኖ ፈጣሪዎች” ሽልማት (public-private partnership (P3) Impact Award) ተብሎ የሚጠራውን ሽልማት በማሸነፍ ሰባተኛው ተቋምም ሆኗል።

    በዓለም ዙሪያ ከ 12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በዓይን ብሌን ጠባሳ ዓይነ-ስውርነት ምክንያት በጨለማ የሚሰቃዩ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ ከ300,000 የሚልቁት ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውንም በመግለጫው ተነስቷል።

    “የሕዝብና የግል ተቋማት አጋርነት የተጽዕኖ ፈጣሪዎች” ሽልማት (P3 Impact Award) ተብሎ የሚጠራውንና በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ጥምረት ቢሮ፣ ኮንኮርዲያ በተባለ ተቀማጭነቱን ኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ ባደረገ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እና በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቨርጂንያ ዳርደን የቢዝነስ ኢንስቲትዩት አማካኝነት የሚሰጠው ይህ ሽልማት የሕብረተሰቡን ችግሮች ለሚፈቱና እና ማኅበረሰባዊ አገልግት ለሚሰጡ የመንግሥት፣ የግል፣ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ወይም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማወዳደር የሚሰጥ ሽልማት ነው።

    የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ከሰሃራ በታች ካሉ ሃገራት ውስጥ በብቸኝነት በሀገር ውስጥ የዓይን ብሌን በመሰብሰብ ለንቅለ-ተከላ ማዕከላት በማሰራጨት ለዓይን ብሌን ንቅለ-ተከላ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

    ዓይን ባንኩ እስከ ፈረንጆቹ 2019 መጨረሻ ለ2,400 (ሁለት ሺህ አራት መቶ) ወገኖች ንቅለ-ተከላ ተደርጎላቸው ብርሃናቸው እንዲመለስ አድርጓል።

    የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ የብሌን ጠባሳ ዓይነ ስውርነት ለማስወገድ ከአጋር ድርጅቶቹ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር፣ ሳይትላይፍ (SightLife) እና ከሂማሊያ ካታራክት ፕሮጀክት (Himalayan Cataract Project) ጋር በመሆን በአፍሪካ የልህቀት ማዕከል ሆኖ ለመሥራት አልሞ የሚሠራ የማኅበረሰብ ተቋም ነው።

    የዚህን ዜና ዋነኛ ምንጭ (በእንግሊዝኛ) ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ

    Eye Bank of Ethiopia የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ

    #48250
    Semonegna
    Keymaster

    ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሁለተኛውን የምገባ ማዕከል ለማቋቋም የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከአዲስ አበባ ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር ለድርጅቱ ሁለተኛውን የምገባ ማዕክል (ተስፋ ብርሀን አሙዲ ቁጥር 2) ለማቋቋም የስምምነት ሰነድ ሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ተፈራርሟል።

    በከተማዋ የሚገኙ በቀን አንድ ጊዜ መመገብ ለማይችሉ ዜጎች ጤናውን የጠበቀ ምግብ እንዲያገኙ ስድስት የምገባ ማዕከላት መገንባታቸውን ከተማ አስተዳደሩን በመወከል የስምመነት ሰነድ የተፈራረሙት የአዲስ አበባ ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሀና የሺንጉስ ተናግረዋል።

    መንግሥት ከድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር በመተባበር ስራዎች እያከናወነ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊዋ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከዳሽን ባንክ ኃ.የተ.የግ.ማ. ጋር በመተባበር ለከተማችን ሰባተኛ ለድርጅቱ ደግሞ ሁለተኛ የሆነ የምገባ ማዕከል ለማቋቋም አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል፤ ለዚህ የሚውል የ40 ሚልየን ብር ወጪ ለማድረግ የስምምነት ሰነድ መፈራረሙንም አስረድተዋል።

    በሚድሮክ ኢቨስትመንት ግሩፕ የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አምባሳደር አሊ ሱለይማን በበኩላቸው ሀገራችን እያስተናገደችው ያለው ማኅበራዊ ችግር በሀገሪቷ ብሎም በከተማዋ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ቁጥር ከፍ አድርጎታል ብለዋል። ለዚህም ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለፈው ዓመት “ተስፋ ብርሀን አሙዲ” የተሰኘ የምገባ ማዕከል በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አቋቁሞ እየሠራ መሆኑን አስታውሰዋል።

    በዚህ ሰዓትም ቁጥር ሁለት ተስፋ ብርሀን አሙዲ የምገባ ማዕከልን በልደታ ክፍለ ከተማ በመገንባት ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ስራ መጀመሩን ገልፀዋል።

    በስምነት ሰነዱም ቢሮው የመገንቢያ ቦታ የማመቻቸት፣ ከቦታው ጋር ተያይዘው ለሚነሱ የሦስተኛ ወገን የመብት ጥያቄ ኃላፊነት ወስዶ ለማመቻቸት እና የተመጋቢ ምልመላና መረጣ የመሳሰሉ የከተማ አስተዳደሩ ኃላፊነቶችን እንደሚወጣ ተገልጿል።

    ሚድሮክ የኢንቨስትመንት ግሩፕ ከዳሽን ባንክ ኃ.የተ.የግ.ማ. ጋር በመተባበር በሚገነቡበት ቦታ ላይ የሚገኙና በዝቅተኛ ኑሮ ለሚኖሩ ስምንት አባወራዎች ስምንት የመኖሪያ ቤቶች ለመገንባት እንዲሁም ባሉበት የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን 16 የሱቅ ቤቶች በመገንባት ለማስረከብ እንደሚሠራምዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

    ከዚህም በተጨማሪ በምገባ ማዕከሉ ቅጥር ግቢ ያለውን ክፍት ቦታ በከተማ ግብርና ለማልማትና የልማቱን ውጤትም ለተመጋቢዎች በምግነት እንዲጠቀሙ ለማድረግ እንደሚሠራ በሚድሮክ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት አምባሳደር አሊ አረጋግጠዋል።

    በተያያዘ ዜና፥ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ (ኢትዮ አግሪ ሴፍት ኃላ/የተ/የግል ማኅበር) እና በላይነህ ክንዴ ግሩፕ (ፊቤላ ኢንዱስትሪስ ኃላ/የተ/የግል ማኅበር) በጥምረት በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ውስጥ በምትገኘው ማንኩሳ ከተማ ያስገነቡት ዘመናዊ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቆ ሥራውን ጀምሯል

    ማንኩሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፥ ግንባታው ብቻ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል፤ የወጪው 75 በመቶ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ተሸፍኗል፤ ትምህርት ቤቱን ገንብቶ ለመጨረስ የወሰድው ጊዜ ስምንት ወራትን ብቻ ሲሆን፥ ትምህርት ቤቱ 36 የመማሪያ ክፍሎች፣ ዘመናዊና የተሟሉ የአስተዳደር ህንጻዎች፣ ቤተ-መጽሐፍት፣ የተሟላ ቤተ-ሙከራ፣ የመረጃና ግንኙነት ቴክኖሎጂ (ICT)፣ ንጹህ የሴትና የወንድ መፀዳጃ ቤት ህንጻዎች እና ሌሎችም የትምህርት ግብዓቶች ተሟልተውለታል።

    ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ

    #48575
    Semonegna
    Keymaster

    በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሪፈራልና ማስተማሪያ ሆስፒታል የእድሳት ግንባታ ሥራ በይፋ ተጀመረ

    ሰሞነኛ (ዲላ ዩኒቨርሲቲ) – በዲላ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሪፈራልና ማስተማሪያ ሆስፒታል የእድሳት ግንባታ ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ተካሄደ። የእድሳት ሥራው መጀመሩን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ ይፋ አድርገዋል።

    ዶ/ር ችሮታው ባደረጉት ንግግር፥ ሆስፒታሉ ያሉበትን መሠረታዊ ችግሮች በትኩረት መፍታት ከተቋሙ ዋና ዋና ተግባራት አንዱ መሆኑን ገልፀዋል።

    በተለያዩ ሀገራዊና ተቋማዊ ምክንያቶች ግንባታው ቶሎ ያልተጠናቀቀውን አዲሱን የሕክምና እና ማስተማሪያ ሆስፒታል ለማጠናቀቅ ከሚደረገው ጥረት በተጓዳኝ ነባሩን ሆስፒታል በልዩ ሁኔታ እድሳት አድርጎ ለታካሚሆችና ለአካሚዎች ጭምር በሚመጥን ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

    ነባሩ ሆስፒታል አሁን ባለበት ደረጃ የጌዴኦ ዞንን እና አጎራባች አካባቢዎችን ማኅበረሰቦች የሕክምና ፍላጎት ለማስተናገድ ችግሮች እንዳሉ የሚታወቅ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ችሮታው፥ ስለሆነም በሆስፒታሉ ሥራ አመራር ቦርድ ታምኖበት አጠቃላይ የእድሳት ሥራው መንግሥት በሚፈቅደው የፋይናንስ ሂደት አልቆ ዛሬ [ሐምሌ 5 ቀን፥ 2014 ዓ.ም] በይፋ እንዲጀመር ተደርጓል ብለዋል።

    ዶ/ር ችሮታው አክለውም፥ እንደ ሀገር ከፍተኛ የሆነ የግንባታ ዘርፉ መቀዛቀዝ ውስጥ ቢሆንም ሆስፒታሉ ካለበት ደረጃ እንዲሁም ከሕብረተሰቡ የሕክምና አገልግሎት አንገብጋቢ ጥያቄ አንፃር አዲሱ እንሰኪጠናቀቅ ነባሩን ሆስፒታል በልዩ ሁኔታና በጥራት አድሶ ጥቅም ላይ ማዋል በትኩረት የሚሠራ ነው ብለዋል። ለዚህም ሥራውን በተቀላጠፈ እና ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ አድሶ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚመለከተው ሁሉ በርብርብ እንደሚሠራ ተገልጿል።

    የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ አብዮት ደምሴ በበኩላቸው፥ ሆስፒታሉ ለጌዴኦ ዞን ብቻ ሳይሆን ለአጎራባች ክልሎች ጭምር አገልግሎት ሰጪ በመሆኑ “መከፈል ያለበት መስዋዕትነት ሁሉ ተከፍሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ እድሳቱ እንዲጠናቀቅ ቦርዱም ሆነ የዞን አመራሩ ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል” ብለዋል። የሥራ ተቋራጭ ድርጅቱ የተጣለበት ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው፥ የዩኒቨርሲቲው አመራር፣ የዞኑና አካባቢው አመራር እንዲሁም ሕብረተሰቡ በጋራ ተባብረው ውጤታማ የሆነ እድሳት እንዲከናወን ይሠራሉ ብለዋል።

    የዲላ ከተማ ከንቲባና የሆስፒታሉ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተስፋፅዮን ዳካ በበኩላቸው፥ ሆስፒታሉ ብዙ ማኅበረሰብ የሚገለገልበት ሆኖ ሳለ ከጊዜ ወደ ጊዜ አገልግሎት አሰጣጡ እየተዳከመ ከአቅም በታች የሆነ አገልግሎት እየሰጠ መጥቷል፤ ስለሆነም ከዚህ ችግር እንዲወጣ እና ሕብረተሰቡ ማገኘት ያለበትን አገልግሎት የመስጠት አቅሙን በተሻለ ለመመለስ በርብርብ ይሠራል ብለዋል።

    የእድሳት ሥራውን ለማከናወን ውል የወሰደው ደሳለኝ አሥራደ ህንጻ ሥራ ተቋራጭ የተባለ ድርጅት ሲሆን ተወካዩ አቶ ፍጹም እምሩ ሆስፒታሉ ከአምስት ሚሊዮን ህዝብ በላይ የሚታከምበት ብቸኛ የዞኑ ሆስፒታል እንደመሆኑ የእድሳት ግንባታውን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ በትኩረት እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

    ተወካዩ አክለውም የተሻለ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች በመመደብ በተሻለ ጥራትና በተፋጠነ ጊዜ ግንባታውን አጠናቀው በማስረከብ ሕብረተሰቡ እና ዩኒቨርሲቲው የጣሉብንን አደራ እንወጣለን ነው ያሉት።

    የዲላ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ፕሮጀክት ፅሕፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር በፍቃዱ መኩሪያ በዕለቱ የእድሳት ግንባታውን አስመልክቶ ባቀረቡት ገለፃ የሆስፒታሉን አጠቃላይ ገፅታ በከፍተኛ ጥንቃቄ ጥናት ተደርጎ ዲዛይን ተሠርቷል ብለዋል።

    ይሄው የእድሳት ዲዛይን ለጤና ሚኒስቴር ቀርቦ ከተገመገመ በኋላ የሚጠበቀውን ደረጃ ማሟላቱ በመረጋገጡ የእድሳት ግንባታው መፈቀዱን ገልፀው፣ በጥናቱ የተለየቱን ችግሮች የሚፈታ እድሳት እንደሚሠራ እና የተወሰኑ ተጨማሪ አዳዲስ ግንባታዎችም እንደተካተቱ አስረድተዋል።

    በእድሳት ግንባታ ሥራ ማስጀመሪያ መርሃግብሩ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሆስፒታሉ የሥራ አመራር ቦርድ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲውና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሆስፒታሉ ማኅበረሰብ አካላት የተገኙ ሲሆን ግንባታው መጀመሩን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ ይፋ አድርገዋል።

    ምንጭ፦ ዲላ ዩኒቨርሲቲ

    የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሆስፒታል እድሳት ተጀመረ

    #49343
    Semonegna
    Keymaster

    በሦስት ዓመታት ከ70 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ያገኛሉ

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – በኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ከ70 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ እንዲኖራቸው የሚደረግ መሆኑን የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ፕሮጀክት አስታወቀ።

    የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር በዲጅታል መታወቂያ የሕግ አግባብነት፣ ዓላማና አዋጅ ጋር በተያያዘ ውይይት አድርጓል።

    የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት የባለድርሻ አካላት ግንኙነት መሪ ሚና አወል፤ ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ አንድን ሰው ማንነት በእርግጠኝነት መለየት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። መታወቂያው ዕድሜ፣ ፆታ፣ የአስር ጣቶች አሻራ፣ የመኖሪያ አድራሻና ሌሎች ገላጭ መረጃዎችን የሚይዝ መሆኑንም አስረድተዋል።

    በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሮችና በገጠር አካባቢ ያሉ ሰዎች እንዴት መመዝገብ ይችላሉ የሚለውን ለማወቅ በአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ሲዳማ ክልሎች 125 ሺህ ዜጎች በሙከራ ደረጃ ተመዝግበው ውጤታማነቱ ተረጋግጧል ብለዋል። በ2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሚኖሩ 12 ሚሊዮን ዜጎችን የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል። ለዚህም በንግድ ባንክ፣ ኢትዮ-ቴሌኮም እና መሰል አገልግሎት በሚሰጥባቸው ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት ሲሄዱ በቀላሉ መመዝገብ ይችላሉ ብለዋል።

    የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮዳሄ ዘሚካኤል፥ ዲጅታል መታወቂያ በኢትዮጵያ የሚኖር ማንኛውም ዜጋ የራሱን ማንነት የሚገልጽበት መለያ ነው። ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ በኪስ የሚያዝ ወረቀት ሳይሆን የራሱ መለያ /ፋይዳ/ የሚባል ቁጥር ብቻ ይዞ በማንኛውም ቦታ በቁጥሩ ምክንያት አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ዘመናዊ አሠራር መሆኑንም አስረድተዋል። ከቤቱ ሆኖ የባንክ አካውንት መክፈት፣ የኢንሹራንስ አገልግሎት ማግኘትና በአገልግሎት ሰጭውና ተቀባዩ ዘንድ መተማመን መፍጠር ያስችላል ብለዋል።

    በዚህም እስከ 2018 ዓ.ም ከ70 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ እንዲኖራቸው ለማስቻል ዕቅድ መያዙን አቶ ዮዳሄ ተናግረዋል። የፎቶ ኮፒና ሌሎች የህትመት ሥራዎች ሁሉ የንግዱ ማኅበረሰብ በየሱቆቹ ማስመዝገብ የሚችልበትን አሠራር እንዘረጋለን ሲሉም ተናግረዋል።

    የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፥ ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ብዙ ትኩረት ሳይሰጠው የቆየ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ለጤናው ዘርፍ የጎላ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያ ባለመኖሩ ምክንያት ዲጅታል የጤና መሣሪያዎችን ወደ ሥራ ማስገባት እንዳልተቻለም ጠቅሰዋል። በመሆኑም ብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያው ሥራ መጀመር በመላ ሀገሪቱ ያሉ ከ40 ሚሊየን በላይ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች መታወቂያቸውን በቀላሉ አድሰው የተቀላጠፈ የጤና አገልግሎት ማግኘት ያስችላቸዋል ብለዋል። የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ የኢትዮጵያን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸው በቅርቡ ወደ ሥራ እንዲገባ አስፈላጊውን ሁሉ እገዛና ትብብር እናደርጋለን ሲሉ አረጋግጠዋል። ዘገባው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ነው።

    የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ

    #51035
    Semonegna
    Keymaster

    አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ይዟቸው የመጡ አዳዲስ ነገሮች ምን ምን ናቸው?

    የትምህርት ሚኒስቴር በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ትግበራ፣ በ2015 ዓ.ም ትምህርት አጀማመር እና በተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥቷል።

    በያዝነው 2015 ዓ.ም ተግባራዊ የሚደረገው አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ተገቢውን ዕውቀትና ክህሎት ከሥነ ምግባር ትምህርት ጋር አጣምሮ ለመስጠት የሚያስችል በመሆኑ በትምህርት ዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው በትምህርት ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ ዛፉ አብርሃ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አብራርተዋል።

    መስከርም 6 ቀን 2015 ዓ.ም የትምህርት ሚኒስቴር ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት ወ/ሮ ዛፉ፥ ከዚህ በፊት የነበረው ሥርዓተ ትምህርት የነበሩበት ክፍተቶች በጥናት የተለየ መሆኑንም አክለው ገልፀዋል።

    በመሆኑም አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ሀገር በቀል እውቀትን፣ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን፣ እንዲሁም ተግባር ተኮር ትምህርትን ከሥነ ምግባር ትምህርት ጋር አቀናጅቶ ለመስጠት እንዲያስችል ተደርጎ የተቀረጸ በመሆኑ በእውቀትና ከህሎት የታነጸ ትውልድ ከመገንባት አንጻር ፋይዳው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።

    በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የአደረጃጀት ለውጥ የተደረገ ሲሆን፥ በዚህም 6፣2፣2፣2 የነበረው አደረጃጀት ቅድመ መደበኛ 2 ዓመት፣ አንደኛ ደረጃ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል (6 ዓመት)፣ መካከለኛ ደረጃ 7 እና 8ኛ ክፍል (2 ዓመት)፣ እንዲሁም 2ኛ ደረጃ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል (4 ዓመት) /2፣6፣2፣4/ እንዲሆን ተደርጓል።

    በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ከፍል አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን በ9ኛ እና 10ኛ ክፍል ደግሞ የሙከራ ትግበራ በተመረጡ 80 ትምህርት ቤቶች የሚካሄድ መሆኑን ወ/ሮ ዛፉ ገልፀዋል።

    በሌላ በኩል የትምህርት ፕሮግራሞች ጥራትና ማሻሻል መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮሃንስ ወጋሶ በሀገሪቱ ሁሉም ክልሎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች መስከረም 9 /2015 ዓም ተከፍተው የመማር ማስተማር ሥራ እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።

    በልዩ ልዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ሰኞ መስከረም 9 ቀን፥ 2015 ዓ.ም ትምህርት የማይጀምሩ ትምህርት ቤቶች ቢኖሩ ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲጀምሩ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

    የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አመለወርቅ ህዝቅኤል በበኩላቸው ሁሉም እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ሕብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

    አምስት ዓመታትን በፈጀውና ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ክለሳ የያዛቸው አዳዲስ ነገሮች

    • አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ባሉ የግል እና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚተገበር ቢሆንም፤ ኢንተርናሽናልና የማህበረሰብ አቀፍ ትምህርትቤቶችን አያካትትም፤
    • በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ግብረ ገብ፣ ሀገር በቀል ዕውቀት፣ ሙያና የቀለም ትምህርት፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርትና ተግባር፣ ጥናትና ምርምር ትኩረት ተደርጎባቸው እንዲሰጡ ይሆናሉ፤
    • ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ላሉ የክፍል ደረጃዎች ትምህርት በአፍ መፍቻ ቋንቋ ይሰጣል፤
    • ከሰባተኛ ክፍል እስከ 12ኛ ክፍል ያሉት ደግሞ ሁሉም ተማሪ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ይማራል፤
    • ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ያሉት ተማሪዎች የእንግሊዘኛ ቋንቋን እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ይወስዳሉ፤
    • ሦስተኛ ክፍል ላይ ተጨማሪ ቋንቋዎችን መስጠት ይጀመራል፤ በክልሎቹ ውስጥ በስፋት የሚነገረውን ተጨማሪ ቋንቋ በመምረጥ ተማሪዎቹ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንዲወስዱት ይደረጋል፤
    • በቀድመው የትምህርት ሥርዓት 10ኛ ክፍል ይሰጥ የነበረው ሀገራዊ የመልቀቂያ ፈተና ይቀርና በምትኩ አጠቃላይ ፈተናው በክልል ደረጃ ስድስተኛ ክፍል እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ስምንተኛ እና 12ኛ ክፍል ላይ ይሰጣል፤
    • ከዚህ ቀደም ሦስት ዓመት የነበረው የተማሪዎች የዩኒሸርስቲ ቆይታ ደግሞ ዝቅተኛዉ አራት ዓመት ይደረጋል፤
    • ለሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች በመጀመሪያ ዓመት ከሚሠጡ ትምህርቶች ውስጥ እንደ ጂኦግራፊ፣ አንትሮፖሎጂ፣ ሶሺዮሎጂ እና ሥነ-ምግባር የመሳሰሉት ይካተታሉ፤
    • ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል የግብረገብ ትምህርት ይሰጣል፤ በተጨማሪም የማኅበራዊና የተፈጥሮ ሳይንስ (social and natural sciences) ውህድ የሆነ ትምህርት ይሰጣል፤
    • ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍል በተናጠል ይሰጡ የነበሩት ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ እና ባይሎጂ አጠቃላይ ትምህርት ወይም ጀነራል ሳይንስ (general science) ተብለው እንዲሁም ጆግራፊና ታሪክም ተቀናጅተው የሚሰጡ ይሆናል፤
    • የሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች የእርሻ ትምህርት፣ አካውንቲንግ፣ ቢዝነስ እና ጀነራል የሆነውን የሥራና ክህሎት ትምህርት በሙያ ትምህርት ተካቶላቸው የሚሰጣቸው ይሆናል፤
    • 11ኛ እና 12ኛ ክፍሎች ላይ ደግሞ ጤና፣ ግብርና፣ የእርሻ ትምህርት፣ ማኒፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ ቢዝነስ፣ አካውንቲንግ የመሳሰሉት የሙያ ትምህርትነቶችን እንዲማሩ ይደረጋል፤
    • የዘጠነኛ እና የ10ኛ ክፍልን እንዲሁም ከአንድ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያሉ የተመረጡ አምስት የትምህርት ዓይነቶችን መጽሐፍት ዝግጅት ትምህርት ሚኒስቴር ያከናውነዋል፤
    • ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለውን የትምህርት መጽሐፍት ክልሎች በራሳቸው ባህልና አካባቢያዊ ሁኔታ ቃኝተው ያዘጋጁታል።

    ምንጭ፦ የትምህርት ሚኒስቴር/ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

    አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት

    #51849
    Semonegna
    Keymaster

    ኦቲዝም

    ኦቲዝም የሚለው ቃል የግሪክ ሲሆን ፍቺውም “ብቸኛ” የሚል ነው። ምክንያቱ ደግሞ ኦቲዝም (በሙሉ ስሙ ኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር) ያለባቸው ልጆች ከሌሎች ልጆች ጋር የማይቀላቀሉ፣ የሚረዳቸው ሰው ካላገኙ በቀር ማንም ሊረዳቸው ስለማይችል ብቸኛ ይሆናሉ። ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች ኦቲስቲክ ይባላሉ። እነዚህ ልጆች የራሳቸው ዓለም ያላቸው ስለሆኑ የሚረዳቸው ሰው ይፈልጋሉ። የማያቋርጥ ክትትል ይጠይቃሉ።

    በሀገራችን አብዛኛው ሕዝብ ስለ ኦቲዝም ብዙም ዕውቀት ስለሌለው ብዙዎቹ የዚህ በሽታ ተጠቂዎች ከማኅበረሰቡ ይገለላሉ። አንዳንድ ወላጆች ስለሚያፍሩባቸው ከቤት ስለማያስወጧቸው፣ አንዳንዶቹ ባለመረዳት መንፈስ ወይም አጋንንት አለባቸው በሚል የተሳሳተ ምልከታ ምክንያት በማሰር ያሰቃዩአቸዋል። ኦቲዝም ልክ እንደ ጨጓራ ቁስለት ወይም ኩላሊት ህመም እንጂ በሽታ አይደለም። የአዕምሮ መዛባት ችግር (disorder) ነው። ማወቅ ያለብን ነገር ኦቲስቲክ የሆነ ልጅ ማንም ሰው አጭር ወይም ጠይም ሆኖ እንደተፈጠረው ተፈጥሮአዊ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ማኅበረሰብ ያንን መረዳት አለበት።

    ኦቲስቲክ ስለሆኑ ልጆች ምን ምን መረዳት አለብን?

    ኦቲዝም በሽታ ቢሆንም ኦቲስቲክ ያለባቸውን ልጆች ፍቅር፣ ትዕግስትና ጊዜ ከሰጠናቸው ከሰው ጋር ወደ መግባባት ወደ መሻሻል ይመጣሉ። ማኅበረሰቡ ያንን አውቆ ከታገሰ በየቤታችን፣ በየሰፈራችን በዚህ በሽታ የተያዙ ልጆችን ልንረዳቸውና ልናሽላቸው እንችላለን። ፍቅር፥ ትዕግስትና ጊዜ ግን ይፈልጋሉ።

    በኦቲዝም እና ዳውን ሲንድሮም (down syndrome) መካከል ያለው ልዩነት

    ሰዎች መረዳት ያለባቸው ነገር ኦቲዝም ክትትል ካገኘ መሻሻልን የሚያመጣ ሲሆን ዳውን ሲንድሮም ግን ከዘረመል መዛባት /genetic disorder/ (ወይም ደግሞ የክሮሞዞም ከተለመደው ውጪ መሆን /chromosome abo=normality/) ምክንያት የአዕምሮ እድገት ውስንነት ነው። የሚወለዱ ልጆች ለዳውን ሲንድሮም የመጋለጣቸው ዕድል ከእናቶች ዕድሜ ጋር ተያያዥነት አለው። በአሃዝ ለማስቀመጥ ያህል፥ ዕድሜዋ 25 ዓመት የሆነች እናት ልጇ ለዳውን ሲንድሮም የመጋለጥ ዕድሉ ከ1,250 አንድ ብቻ ሲሆን፥ ዕድሜዋ 40 ዓመት የሆናት እናት ግን ልጇ ለዳውን ሲንድሮም የመጋለጥ ዕድሉ ከ100 አንድ አካባቢ ነው (ምንጭ)።

    ጥናቶች ስለ ኦቲዝም ምን ይላሉ?

    የእንግሊዝና የጣሊያን ተመራማሪዎች በጋራ ባደረጉት ጥናት እንደገለጹት አስቀድሞ የኦቲዝም ተጠቂዎችን ለመለየት የሚያስችል የደምና የሽንት ምርመራ በሕፃናት ላይ በማድረግ ለኦቲዝም ሕክምና መስጠት የሚቻልበት ደረጃ ላይ እየደረሱ መሆኑን በቅርብ ጊዜ ተዘግቦ ነበር (ምንጭ)። ሕፃናት የኦቲዝም ተጠቂ መሆናቸውን ለማወቅ በደም ውስጥ የሚገኝ የፕሮቲን መጠንን በመለካት ማወቅ እንደሚቻልም ጥናቶች ያረጋግጣሉ። የኦቲዝም ተጠቂ የሆኑትንና ያልሆኑትን ሕፃናት በማነጻጻር በተደረገው የሽንትና የደም ናሙና ምርመራ በኦቲዝም የተጠቁት ሕፃናት ከፍ ያለ የፕሮቲን ጉዳት እንደታየባቸውና በኦቲዝም ያልተጠቁት ደግሞ የተሻለ የፕሮቲን ስብጥር በደማቸው መገኘቱን ገልጸዋል። ሕፃናት በደማቸው አነስተኛ የፕሮቲን ስብጥር በሚኖርበት ጊዜ ለኦቲዝም የመጋለጥ ዕድላቸውን እንዲሰፋ ያደርገዋል (ምንጭ)።

    ኦቲዝም ከፍተኛ የሆነ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነትን በማምጣት በሰው ሥነ ባህርይ ላይ ጉዳት በማድረስ በማኅበራዊ ህይወት ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራል። ከሦስት ዓመታት በፊት በአምስት ሀገራት የተደረገ ትልቅ ጥናት እንደሚያመለከው 80 በመቶ ለኦቲዝም የተጋለጡ ሕፃናት በዘር የተላለፈባቸው እንደሆኑ ያመላክታል (ምንጭ)። ሌላ የብዙ ጥናቶች ውሁድ ጥናት (meta-analysis) እንደሚያሳየው ደግሞ በዘር በመተላለፍ ለኦቲዝም የመጋለጥ ዕድል ከ60 እስከ 91 በመቶ ሲሆን፥ በሥነ ህይወት እና አካባቢ ምክንያት (environmental factors) ለኦቲዝም የመጋለጥ ዕድልም አሌ የማይባል እንደሆነ ያስረዳል (ምንጭ)።

    የኦቲዝም የመጀመሪያ ምልክቶች

    ኦቲዝም ትልቅ የጤና ሁኔታ ነው፤ ከቀላል ምልክት እስከ ጥልቅ እና በጣም ከባድ የሆነ የጤና እክል ነው። በሽታው በአእምሮ ዘገምተኛ ሕፃናት እና በደንብ ባደጉ የአካዳሚክ ክህሎት ባላቸው ሰዎች ላይ እንደሚገኝ ኦቲዝምን የሚከታተሉ የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። የመጀመሪያዎቹ የኦቲዝም ምልክቶች በጣም ቀደም ብለው ይታያሉ፤ ብዙውን ጊዜ ከአስራ ሁለት ወራት በላይ በሆኑ ሕፃናት ላይ ይታያሉ፤ እንዲሁም ከ 3 ዓመት በፊት በግልጽ ይታያሉ።

    በልጅ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ምልክቶች ብዙውን ጊዜ በወላጆች ይሰተዋላሉ። በአንዳንድ ሁኔታዎች ቀድሞውኑ በጨቅላነታቸው ሕፃኑ በጣም ጨዋ፣ ረጋ ያለ፣ በጩኸት የማይፈነዳ፣ ወደ ዓይኑን ውስጥ በሚገቡ ሰዎች ላይ የማያተኩር፣ እና ሲያነሱት ጠንካራ ነው። በተጨማሪም ሕፃኑ በአንድ ነጥብ ላይ ለሰዓታት ይመለከታል፤ ለምሳሌ አይጮኽም ወይም ንግግር አያዳብርም። በተጨማሪም የልጁ እድገት መጀመሪያ ላይ መደበኛ እና ያልተለመዱ ባህሪያት በድንገት ሊከሰቱ ይችላሉ።

    የኦቲስቲክ ባህሪያት

    ኦቲዝም በማኅበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ ሁከት ይፈጥራል። የኦቲዝም ልጆች ብዙውን ጊዜ አይታዩም፣ ለምሳሌ፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር የዓይን ንክኪ (eye contact) አይፈጥሩም፤ አሊያም ቢፈጣሩም በጣም ለአጭር ጊዜ ነው። ኦቲስቲክ ልጅ እንደ ታመመ ብቻውን ጊዜ ማሳለፍ ይመርጣል። አንዳንድ ጊዜ አይታየኝም እና አይሰማኝም የሚል ስሜት ይሰማቸዋል።

    የኦቲዝም ልጆችም ግንዛቤ በማጣት ምክንያት ማኅበራዊ ሕጎችን ለማክበር ይቸገራሉ፤ አብዛኛዎቹ የዕለት ተዕለት ትዕዛዛትን አይከተሉም። በተጨማሪም የጠባይ መታወክ ብዙ ጊዜ ይስተዋልባቸዋል። ሕፃኑ ራሱን በአዲስ እርግጠኛ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ካጋጠመው በተቀነባበረ መልኩ ምላሽ ሊሰጥ ይችላል። ለምሳሌ መሸሽ ሊፈልግ ይችላል፤ ወደ ንዴት ሊያመራ ይችላል። አንዳንድ ሀረጎችን ይደግማል፤ ተደጋጋሚ እንቅስቃሴዎችን መድገም፣ መጥራት፣ መነጋገር፣ ወዘተ.. ሊጀምር ይችላል። የባህሪው ልዩነት በጣም ትልቅ ነው። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ወላጁ አቅመ ቢስ እና ብቃት እንደሌለው ይሰማዋል፤ በውጤቱም ዘመዶቹን እና ጓደኞቹን መጎብኘት ያቆማል፤ እና እስከ ቀኑ መጨረሻ ድረስ ያለ ግርግር በመትረፍ ላይ ያተኩራል። በዚህ መንገድ ሕፃኑ እድገትን የሚወስኑ አንዳንድ ልምዶችን ራሱ ያመጣል፤ በየቀኑ አንድ እና ተመሳሳይ መንገድ በመጓዝ ከተማዋን ለማወቅ እንደመሞከር ሊታይ ይችላል።

    ኦቲዝም ልጆች ብዙውን ጊዜ በጨዋታዎች ውስጥ ድንገተኛነት ወይም የፈጠራ ችሎታ ማጣት ተለይተው ይታወቃሉ። እንቅስቃሴዎችን አያቀርቡም ወይም ጨዋታዎችን አይፈጥሩም፤ ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች ብዙውን ጊዜ በአሻንጉሊት አይጫወቱም። በክበቦች ውስጥ ይሽከረከራሉ፤ ይወዛወዛሉ፤ ያለመታከት መጫዎቻቸውን ማሰለፍ ወይም መደርደር ዋነኛ መዝናኛቸው ይሆናል። እንዲሁም በምሳሌያዊ ሁኔታ መጫወት አይችሉም።

    የኦቲዝም ምርመራ በሁለት ደረጃዎች ይከፈላል፦

    1. የልጆች እድገት ጥናት – የጤና ባለሙያው (ኦቲዝም ስፔሻሊስቱ) ሕፃኑ ለተወሰነ የህይወት ጊዜ መሠረታዊ ክህሎቶች እንዳሉት ወይም አንዳንድ መዘግየቶች እንዳሉት ለማሳየት ፈተናን ያካሂዳል። በዚህ ምርመራ ወቅት ባለሙያው ለወላጆቹ ብዙ ጥያቄዎችን ይጠይቃል። ለምሳሌ ሕፃኑ በደንብ እየተማረ እንደሆነ፣ እንዴት እንደሚናገር፣ እንዴት እንደሚሠራ፣ በደንብ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ይጠይቃል። ይህ አስፈላጊ ነው ምክንያቱም በእነዚህ ቦታዎች ላይ መዘግየት የእድገት ችግሮችን ሊያመለክት ይችላል፤ ወደ ልዩ ባለሙያተኛ (ኦቲዝም ስፔሻሊስት) የሚላክ እያንዳንዱ ልጅ በ9፣18፣ 24 ወይም 30 ወር እድሜው ውስጥ የእድገት መዘግየት እና የአካል ጉዳተኝነት ምርመራ ይደረግበታል።

    በቤተሰቡ ውስጥ ያሉ ሌሎች ሰዎች ኦቲዝም ያለጊዜው መውለድ ወይም ዝቅተኛ የመውለድ ክብደት ስላላቸው አንድ ልጅ ለዕድገት መታወክ ከፍተኛ ተጋላጭነት እንዳለው ሲጠረጠር ተጨማሪ የማጣሪያ ምርመራዎች ይከናወናል። በመቆጣጠሪያው ወቅት የማጣሪያ ምርመራዎች ከ1፣5 እና 2 ዓመት ዕድሜ ላይ ባሉ ልጆች ላይ መደረግ አለበት።

    1. የልጁ አጠቃላይ ግምገማ – ይህ ሁለተኛው የምርመራ ደረጃ ሲሆን የልጁ ግምገማ የልጁን ባህሪ እና ከወላጆች ጋር ቃለ-መጠይቅ ያካትታል፤ በተጨማሪም የነርቭ እና የጄኔቲክ ምርመራዎች እና ሌሎች የሕክምና ሙከራዎች ሊደረጉ ይችላሉ። በተለየ ሁኔታ የልጁ ግምገማ ብዙውን ጊዜ የሚከናወነው በነርቭ ሐኪሞች የአንጎልንና የነርቮችን ሥራ በመገምገም ነው። በሌላ በኩልም የሕፃናት እድገት ሐኪሞች የልጁን እድገት የሚገመግሙ ሲሆን የሕፃናት ሳይኮሎጂስቶች ወይም የሥነ-አእምሮ ባለሙያዎች ደግሞ ስለ አእምሮአዊ ጤንነቱ ምርመራ ያደርጋሉ።

    ትኩረት

    ልጅዎ በትክክል እያደገ እንዳልሆነ በሚጠራጠሩበት ጊዜ ሁሉ ባለሙያን ያነጋግሩ፤ እንዲሁም ለሳይኮሎጂካል ምክክር ቀጠሮ መያዝ ያስፈልጋል። የሕፃናት የሥነ ልቦና ባለሙያዎችን መገኘትም ወቅታዊ ችግሮችን ለመረዳት ያግዛል።

    ኦቲዝምን ስንመረምር ከኦቲዝም ጋር እየተገናኘን እንዳለን፣ የተለመዱ በሽታዎች (የመስማት ወይም የማየት ችግሮች) ወይም ከሕፃናት እድገት ደረጃዎች (developmental stages) ውስጥ የአንዱን መታወክ፣ ለምሳሌ ንግግርን መለየት አስፈላጊ ነው። ኦቲዝምን የሚመስሉ አንዳንድ በሽታዎች ወይም የጤና እክሎች አሉ፤ ስለዚህ በተገቢው ምርመራ መወገድ አለበት። ምርመራ ለማድረግ ልጁን መከታተል እና ከወላጆች/አሳዳጊዎች ጋር መነጋገር አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። የትምህርት አቅም የሚፈተነው ሁለገብ ቡድን ነው።

    ኦቲዝም – ጠቃሚ ምክሮች ለወላጆች

    ልጅዎ ከሚከተሉት ሁኔታዎች ውስጥ አንዱን ወይም ጥቂቱን የሚያስተውሉበት ከሆነ ሐኪምዎን ያማክሩ — የንግግር እድገትን መዳከም፣ ከአካባቢው ጋር አለመገናኘት፣ ማኅበራዊ ግንኙነቶችን አለማድረግ፣ ሲጠራ መልስ አለመስጠት።

    ምንጭ፦ አዲስ ዘመን ጋዜጣ (በመጠኑ ተሻሽሎ የቀረበ)

    ኦቲዝም

    #53711
    Semonegna
    Keymaster

    ቡራዩ የተሰጥኦ ማበልፀጊያ መዕከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተመርቆ 500 ተማሪዎችን ለመቀበል ተዘጋጅቷል

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቡራዩ ከተማ የተገነባውን የተሰጥኦ ማበልፀጊያ ትምህርት ቤት (ቡራዩ የተሰጥኦ ማበልፀጊያ መዕከል ) መርቀው መክፈታቸው ተገለጸ፡፡

    በመደበኛ ትምህርት ቤቶች፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በማሰልጠኛ ተቋማትና ሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች የወጣቶችን ተሰጥኦ የማጎልበት ሥራ ማከናወን አስፈላጊ ነው።

    አሁን ባለው እውነታ ወጣቶቹ ተሰጧቸውን አበልጽገው ወደምርትና አገልግሎት ለመቀየር ከፈለጉ የትምህርት ሥርዓቱ የሚፈልገውን ቆይታ ማጠናቀቅ ግድ ይሆንባቸዋል።

    ወጣቶቹ የሚያጋጥማቸውን ውጣ ውረድ ማለፍ ሲሳናቸው ደግሞ ተሰጥኦዋቸውን ለመረዳት፣ ለማውጣትና ለመተግበር ስለሚቸገሩ ባክነው የሚቀሩበት ዕድል ሰፊ ነው።

    በመሆኑም ከመደበኛው መማር ማስተማር ሳይለዩ ተሰጧቸውን ያለጊዜ ገደብ ወደ ምርትና አገልግሎት እንዲለወጡና አገር እንዲጠቅሙ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ይነገራል።

    የተገነባው ማዕከልም በሀገራዊ ለውጥ ምክንያት በነበሩ ጫናዎች ውስጥ ሆኖ መጠናቀቁና የአካባቢው ሕዝብ በግንባታ ሂደቱ ንብረት እንዳይጠፋና እንዳይባክን ጠብቆ ለምረቃ ያበቃው መሆኑ ተገልጿል።

    የአካባቢው ነዋሪ ከመሬት ስጦታ እስከ ጉልበት ያለምንም ካሳ አስተዋጽኦ ያደረገበት በመሆኑ ሕዝብ ከተባበረ ምንም ነገር ማሳካት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑም ተመልክቷል።

    የማዕከሉ መገንባት አዲስ ከተማ ከመፍጠር ባለፈ ከትምህርት፣ ከሰው ኃይል ልማትና ከሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ከሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ልማትና ምርምር አኳያ መሠረት ይጥላል ተብሏል።

    በአንድ ጊዜ 1 ሺህ ባለተሰጥኦ ወጣቶችን ተቀብሎ ማስተናገድ የሚችለው ትምህርት ቤቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ 500 ሰልጣኞችን የሚያስተናግድ ይሆናል።

    የፕሮጀክቱ ተጨማሪ ማስፋፊያ ሲገነባ በ10 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን አሁን የተመረቀው በ4.3 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ መሆኑ ታውቋል።

    በአፍሪካ ደረጃ የመጀመሪያ ነው የተባለው ማዕከል የመመገቢያ አዳራሽ፣ የአስተዳደር ሕንጻ፣ የሕክምና ማዕከል፣ የመማሪያ ክፍሎችና የጋራ መማሪያ አዳራሽ እንዲሁም ቤተ ሙከራን የያዘ ዘጠኝ ብሎክ ህንፃ ያለው መሆኑ ታውቋል።

    በተጨማሪም ኤሌክትሮ መካኒካል፣ የኬሚካልና ዲጅታል፣ ወርክሾፖች፣ ቤተ መጻሕፍት እና ተጨማሪ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎችን ያሟላ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ለትምህርት ቤቱ የተሟሉት ቁሳቁሶቹ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁና የጥራት ደረጃቸው ከፍተኛ እንደሆኑም ተመልክቷል።

    ፕሮጀክቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጠንሳሽነት የተጀመረና በእርሳቸው ጥብቅ አመራር የተፈጸመ መሆኑ ታውቋል።

    በዚሁ አጋጣሚ ለአካባቢው ሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ 2 ኪሎ ሜትር መንገድ፣ የጎዳና እና የውስጥ ለውስጥ መብራትና የውሃ አገልግሎት ማቅረብ ማስቻሉም ተመላክቷል፡፡

    የፕሮጀክቱ ግንባታ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መሠረቱ ተጥሎ ሥራው የተጀመረው በ708 ሚሊዮን 693 ሺህ ብር መሆኑ ታውቋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    ቡራዩ የተሰጥኦ ማበልፀጊያ መዕከል

    #55189
    Semonegna
    Keymaster

    በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ተጀመረ 

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – ከታኅሳስ 13 ቀን እስከ ታኅሳስ 22 ቀን፥ 2015 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጀ የሚካሄደው የተቀናጀ የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ዘመቻ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት፣ የኮቪድ-med19 መከላከያ ክትባት፣ የአጣዳፊ የምግብ እጥረት ልየታ፣ የቫይታሚን ኤ ጠብታ እደላ፣ የሆድ ጥገኛ ትላትል መድኃኒት እደላ፣ የሕፃናት የዞረ እግር ልየታ እንዲሁም በወሊድ ምክንያት የሚከሰት ፊስቱላ ልየታ በቅንጅት የሚሠራበት ዘመቻ ነው።

    በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ሰርጢ ጤና ጣቢያ የማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ እንደገለጹት፥ ለእናቶች እና ለሕፃናት ትኩረት ያደረገው የጤና ፖሊሲ ውስጥ አንዱ እና ባለፉት አራት አስርት ዓመታት በትግበራ ላይ የቆየው የክትባት ፕሮግራም መሆኑን ገልፀው፤ እንደሀገር ከ14 በላይ የሚሆኑ የክትባት ዓይነቶችን በመስጠት ዜጎችን ከህመምና ከሞት መታደግ እንደተቻለ ገልጸዋል።

    በሀገራችን በተወሰኑ አካባቢዎች ተከስተው በነበሩ ሰው ሠራሽና ተፈጥራዊ ችግሮች ምክንያት በሥርዓተ ምግብ እጥረት እና በኩፍኝ በሽታ የሚያዙ ሕፃናት ከፍ ብሎ መታየቱን የገለፁት ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ፥ በዚህ ዘመቻ ዕድሜያቸው ከዘጠኝ ወር እስከ አምስት ዓመት የሆኑ ሕፃናትን የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት፣ የአጣፊ የምግብ እጥረት፣ የዞረ እግር ልየታ እንደሚከናወን እና በወሊድ ምክንያት የሚከሰት ፊስቱላ ልየታም ይካሄዳል።

    ሕፃናት በመደበኛ ክትባት መርሃ-ግብር የሚሰጠውን የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ካልወሰዱ በቀላሉ በኩፍኝ በሽታ የመያዝና ለከፋ የጤና ችግር የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ  ነው ያሉት የእናቶች እና ሕፃናት ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር መሠረት ዘላለም፥ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን  ባለፉት 3 ወራት ብቻ የኩፍኝ በሽታ ወረርሽኝ በ6 ክልሎች የታየ ሲሆን፤ በወረርሽኙም ከተያዙ ውስጥ 47 በመቶ  የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ሲሆኑ፥ ከእነዚህም መካከል 46 በመቶ የሚሆኑት ምንም ዓይነት የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ያልወሰዱ ናቸው ብለዋል። ለዘመቻው እንቅስቃሴ መሳካት አጋርና ለጋስ አካላት ላደረጉት የተቀናጀ አስተዋጽኦ አመስግነዋል።

    በአዲስ አበባ ከተማ ከ5 ዓመት በታች ለሆናቸው ለ520 ሺህ ሕፃናት ክትባቱ እንደሚሰጥም እና በስድስት የመንግሥት ሆስፒታሎች በ101 የመንግሥት ጤና ጣቢያዎች ከሰኞ አስከ አርብ በሥራ ሰዓት እንደሚሰጥ የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዮሐንስ ጫላ ናቸው።

    ሀገር አቀፍ የተቀናጀ  የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ዘመቻ  የማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ የጤና ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል።

    ዘመቻው ለአስር ቀን የሚቆይ ሲሆን ከ15 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ተደራሽ የሚሆን ሲሆን፤ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት መርሃ-ግብርም በተያያዘ የሚከናወን ይሆናል። ለዘመቻው ስኬታማነት በየተዋረድ ያሉ የጤናው ዘርፍ ባለሙያዎችና አመራሮች፣ አጋር ድርጅቶችና የየመገናኛ ብዙኃን አካላት ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

    ምንጭ፦ የጤና ሚኒስቴር

    የኩፍኝ መከላከያ ክትባት

    #55406
    Semonegna
    Keymaster

    በዲላ ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ሆስፒታል በመጀመሪያ ዙር መልሶ ግንባታ የተጠናቀቁ ህንፃዎች ተመረቁ
    የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ጠቅላላ ሆስፒታል ደረጃን ለማሻሻል በተሠሩ ሁለተናዊ የለውጥ ሥራዎች በአጭር ጊዜ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ መሆኑ ተገለፀ

    ዲላ (ዲላ ዩኒቨርሲቲ እና የጤና ሚኒስቴር) – የዲላ ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ሆስፒታል ደረጃን ለማሻሻል የሚደረግ የመልሶ ግንባታ አካል የሆኑና በመጀመሪያው ዙር ታድሰው የተጠናቀቁ ህንፃዎች የምረቃ በሥነ ሥርዓት ታኅሣሥ 27 ቀን፥ 2015 ዓ.ምተካሂዷል።

    በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ማስተማሪያ ጠቅላላ ሆስፒታል የእድሳት ግንባታ ሥራ በከፊል ርክክብ ሥነ ሥርዓት ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በተገኙበት ታህሳስ 27/2015 ዓ.ም ተካሂዷል።

    ከስድስት ወራት በፊት በአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም በመልካም አስተዳደር እጦት ከፍተኛ የሕብረተሰብ እሮሮ የተነሳበት የዲላ ዩኒቨርስቲ ማስተማሪያ ጠቅላላ ሆስፒታል ከፌደራል እና ክልል ከፍተኛ አመራሮች በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ሁሉን አቀፍ የሥርዓት ማሻሻያ የሪፎረም ሥራዎችና ምቹና ደህንነቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የሥራ ቦታ ለመፍጠር የግንባታ እድሳት ሥራ በተቀላጠፈ መልኩ እየተከናወነ እንደሆነ በመልስ ምልከታ ማየት ተችሏል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት እንደገለጹት የዩኒቨርስቲ ማኔጅመንት ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ከሐምሌ ወር መጨረሻ 2014 ዓ.ም ጀምሮ 112 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የመማር ማስተማር እና የሕክምና አገልግሎት ሳይቋረጥ በሦስት ዙር እድሳቱ እንዲካሄድ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

    በሥነ ሥርዓቱ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጠቅላላ ሆስፒታል ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ምፅዋ ሩፎ እንደገለፁት፥ አዲሱ የሆስፒታል አመራር ወደ ሥራ ሲገባ የአሠራር ሥርዓት ክፍተት ስለነበር ክፍተቶችን ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሰፋፊ ሥራዎች እንደተሠሩ እድሳቱንም በቅርብ ክትትል እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።

    ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚንስትር እና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ እንደተናገሩት፥ የሆስፒታሉን አገልግሎት ለማጠናከር በየደረጃው ያለው አመራር ቁርጠኝነት እንደሚፈልግ ገልፀው፤ ለዚህም አስፈላጊ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ ገልጸዋል።

    በጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ የተጀመረው ሪፎርም፣ የ”SBFR” ትግበራ እና የህንፃዎች እድሳት የሆስፒታሉን ደረጃ ከፍ ከማድረግ ባሻገር የጤና አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል እና የጤና ባለሙያው ላይ ከፍተኛ መነቃቃት እንዲሁም የተገልጋይ እርካታን መጨመር መቻሉን ገልፀው ለዚህ ውጤት መምጣት በቁርጠኝነት ለሠሩት የዪኒቨርስቲው፣ የጌዲዮ ዞን፣ የዲላ ከተማና የሆስፒታሉ አመራር አካላት እንዲሁም መላው የሆስፒታል ማኅበረሰብ በተለይም በሥራ አንጋፋ (senior) ሐኪሞችና ነርሶች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

    በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ አባገዳዎች፣ የጤና ሚኒስቴር፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ጤና ቢሮ፣ የጌዲዮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የሆስፒታሉ የበላይ አመራሮች፣ የሕክምና ባለሙያዎች፣ የአከባቢው ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ ሠራተኞች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።

    ምንጮች፦ ዲላ ዩኒቨርሲቲ እና የጤና ሚኒስቴር

    ዲላ ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ሆስፒታል

    #55623
    Semonegna
    Keymaster

    የጫሞ ሐይቅ ተፋሰስን ወደነበረበት ለመመለስ ለሚሠራው ፕሮጀክት የአመራሮች የጋራ መድረክ ተመሠረተ

    አርባ ምንጭ (አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ) – ከጀርመን ልማት ባንክ በተገኘ 25 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ የጫሞ ሐይቅ ተፋሰስን ወደነበረበት ለመመለስ በቅርቡ ሥራ የሚጀምረው ፕሮጀክት ስኬታማ እንዲሆን ከጋሞና ኮንሶ ዞኖች እንዲሁም ከደራሼ፣ ቡርጂና አማሮ ልዩ ወረዳዎች የተወጣጡ አስተዳዳሪዎችን እና የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኃላፊዎችን ያካተተ የአመራሮች የጋራ መድረክ ጥር 10 ቀን፥ 2015 ዓ.ም በይፋ ተመሥርቷል። በዕለቱ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴም የአመራር መድረኩ ሰብሳቢ ሆነው ተመርጠዋል።

    የዕለቱን መርሃ-ግብር በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ሰብሳቢ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በጫሞ ሐይቅ ተፋሰስ በሁለት ዞኖችና ሦስት ልዩ ወረዳዎች ባሉ 10 ወረዳዎች የሐይቁን ህልውና ለመታደግ በቅርቡ ከጀርመን ልማት ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን አሳታፊና ዘላቂ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንደሚጀመር ተናግረዋል። ለ5 ዓመታት በሥራ ላይ የሚቆየው ፕሮጀክቱ ሕብረተሰቡን ማዕከል አድርጎ የሚሠራ ሲሆን፥ ሕብረተሰቡን በማስተባበርና በማንቀሳቀስ ሂደት ውስጥ የአካባቢው አመራሮች የሚኖራቸው ሚና የጎላ በመሆኑ፥ ይህንን የአመራሮች መድረክ መፍጠር አስፈልጓል ብለዋል። የአካባቢው አመራሮችም ፕሮጀክቱ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን ወደነበሩበት ከመመለስ ባሻገር ከሥራ ዕድል ፈጠራና የማኅበረሰቡን የአኗኗር ሁኔታ ከመቀየር አንፃር ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት በታማኝነትና በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባም አጽንዖት ሰጥተው አሳስበዋል።

    እንደ አቶ ኃይለማርያም ለፕሮጀክቱ እውን መሆን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ የተደረጉ ሳይንሳዊ የምርምር ሥራዎች ሚናቸው የጎላ ሲሆን፥ በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው በፕሮጀክቱ አፈፃፃም ወቅት የተጣለበትን በዕውቀትና ሳይንስ ላይ የተመሠረተ የቁጥጥርና ክትትል ሥራዎች በአግባቡ እንደሚወጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

    በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፕ/ር እያሱ ኤሊያስ በበኩላቸው በተፋሰሱ ላይ የሚጀመረው ፕሮጀክት የሐይቁን ህልውና ከመጠበቅ ባሻገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዲሁም የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል። በጫሞ ተፋሰስ ላይ የሚሠራው ዘላቂ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንደሀገር ትኩረት የተሰጠው ሲሆን ለውጤታማነቱ የአካባቢው አመራሮች ማኅበረሰቡን በተለይ ወጣቶችን በስፋት በማሳተፍ የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። እንደ ግብርና ሚኒስቴርም ጽ/ቤታቸው በፕሮጀክቱ የተጣለበትን ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

    የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ሲገልጹ፥ ከዚህ ቀደም በወዜ ሻራ ተፋሰስ፣ አሁን ላይ ደግሞ በቤራ ተራራ ላይ እየሠራ ያለው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተጠቃሽ ነው ብለዋል። ፕሮጀክቱ የጫሞ ሐይቅ ተፋሰስን ሙሉ በሙሉ በሸፈነ መልኩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን የታቀደ መሆኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚኖረው ጠቀሜታ ጉልህ መሆኑን ያወሱት ፕሬዝደንቱ የአካባቢው አመራሮችም ይህን በብዙ ጥረት የተገኘ ዕድል በአግባቡ መጠቀም አለባቸው ብለዋል። ዩኒቨርሲቲውም ሆነ የዘርፉ ተመራማሪዎች ለፕሮጀክቱ እውን መሆን እንዳደረጉት ጥረት ሁሉ ለአፈፃፀሙም የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ዶ/ር ዳምጠው ተናግረዋል።

    የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው የዚህ ፕሮጀክት እውን መሆን ችግር ከማውራት ወጥተን ወደመፍትሄው እንድንገባ በር የከፈተ መሆኑን ጠቅሰው በዕለቱ የተመሠረተው የአመራሮች መድረክም አመራሩ ሥራውን በባለቤትነት ወስዶት እንዲሠራ ያስችላል ብለዋል። የችግሩን አንገብጋቢነት በመገንዘብ አመራሩ ማኅበረሰቡን የማንቃትና የማስተባበር እንዲሁም ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት የሚውሉ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን በመወሰን ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበው እንደመድረኩ ሰብሳቢነታቸውም የበኩላቸውን ሚና በቁርጠኝነት ለመወጣት ቃል ገብተዋል።

    በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ”AMU-IUC” ፕሮግራም ማኔጀርና የውሃ ሥነ-ምኅዳር ተመራማሪው ዶ/ር ፋሲል እሸቱ ብዙ ጊዜ መሰል ፕሮጀክቶች በፖለቲካ አመራሩ ዘንድ የባለቤትነት ስሜት መፈጠር ባለመቻሉ ስኬታማ ሳይሆኑ እንደሚቀሩ አውስተዋል። አሁን ላይ የተመሠረተው የአመራሮች የጋራ መድረክ ማኅበረሰቡን ከማስተባበር አንፃርና ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት የተለያዩ ውሳኔዎችንና እርምጃዎችን መውሰድ የሚችሉ አመራሮችን በሥራው ሂደት ላይ በኃላፊነት ስሜት ማሳተፍ የሚያስችል በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል። እንደዘርፉ ተመራማሪ በግላቸውም ሆነ በሚመሩት ፕሮግራም አማካኝነትና በፕሮጀክቱ ለዩኒቨርሲቲው በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ለፕሮጀክቱ ስኬት አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ፋሲል የሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብ ሥራው የጫሞ ሐይቅ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ለፕሮጀክቱ ስኬት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

    የአመራሮች መድረኩ በፕሮጀክቱ አፈፃፀም ሂደት ውስጥ ፈጣን ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ውሳኔዎችንና እርምጃዎችን የሚወስድ የአስተዳደር መዋቅር ለመፍጠር የተዘጋጀ መሆኑ በዕለቱ በቀረበው መመሪያ ላይ ተመላክቷል። በመመሪያው እንደተመላከተው መድረኩ በፕሮጀክቱ የተያዙ የሥራ ዕቅድና ሀብት በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውሉ የመሥራትና ቁጥጥር የማድረግ፣ የፕሮጀክቱ አፈፃፀምን በየጊዜው የመገምገም፣ በፕሮጀክቱ አፈፃፀም ሂደት ውስጥ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችንና ማነቆዎችን ለይቶ በፍጥነት የመፍታት፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ በፕሮጀክቱ ላይ በስፋት መሳተፉንና ተጠቃሚ መሆኑን የማረጋገጥና ሌሎች ኃላፊነቶች ተሰጥቶታል።

    ምንጭ፦ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

    የጫሞ ሐይቅ ተፋሰስን ወደነበረበት የመመለስ ፕሮጀክት

    #55729
    Semonegna
    Keymaster

    በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና ግማሽ (50%) እና ከዚያ በላይ ውጤት ያስመዘገቡ
    እና የማጠናከሪያ መርሐ ግብር የሚከታተሉ ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት እንደሚገቡ ተገለፀ

    አዲስ አበባ (ትምህርት ሚኒስቴር) – የትምህርት ሚኒስቴር የ2014 ዓ.ም 12ኛ ክፍል ፈተና የዉጤት ትንታኔ፣ ወደ ከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤትና ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

    መግለጫውን የሰጡት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የተገኘው የፈተና ውጤት ከስርቆትና ከኩረጃ በፀዳ መልኩ በትክክል የተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።

    በ2014 ዓ.ም ለተሰጠው ፈተና በጠቅላላ የተመዘገቡት ተፈታኞች ቁጥር 985,354 ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ውስጥ 92 ከመቶ የሚሆኑት ፈተናውን ወስደዋል። 20,170 ተማሪዎች በፈተናው ከተገኙ በኋላ በተለያዩ የደንብ ጥሰቶች ምክንያት ተባረዋል።

    ከፍተኛ ውጤት የተበመገበበት የትምህርት መስክ — በተፈጥሮ ሳይንስ 666 ከ700 ከፍተኛ ውጤት ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 524 ከ600 ከፍተኛ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ፈተናውን ካስፈተኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሰባት ትምህርት ቤቶች ያስፈተኑትን ተማሪዎች 100% አሳልፈዋል ተብሏል።

    በጾታ ደረጃ የወንዶች አማካይ ውጤት 30.2 ከመቶ ሲሆን፤ የሴቶች አማካይ ውጤት ደግሞ 28.1 ከመቶ እንደሆነ፥ ይህም በወንዶች እና በሴቶች መካከል በአሐዛዊ ምልከታ (statistically) የጎልላ ልዩነት እንዳለና፤ ወንዶች ከሴቶች አሐዛዊ ብልጫ (statistically higher) ውጤት እንዳስመዘገቡ አስረድተዋል።

    በክልሎች ደረጃ በዉጤት ደረጃ የጎላ ልዩነት እንደሌለ ገልፀው፤ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የሐረሪ ክልል አሐዛዊ የተሻለ (statistically significantly higher) ውጤት ያስመዘገቡ መሆኑን ፕሮፌሰር ብርሃኑ አብራርተዋል።

    በ2014 ዓ.ም በተሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሊያስገባ የሚችል ወጤት፥ ማለትም ግማሽ (50%) እና ከዚያ በላይ ያስመዘገቡት ተማሪዎች ቁጥር ሲታይ፥ የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና ከወሰዱት አጠቃላይ 339,642 ተማሪዎች መካከል 22,936 (6.8%) ተማሪዎች፣ የማኅበራዊ ሳይንስ ፈተና ከወሰዱት አጠቃላይ 556,878 ተማሪዎች መካከል 6,973 (1.3%) ተማሪዎች ግማሽ (50%) እና ከዚያ በላይ አስመዝግበዋል።  የሁለቱም የትምህርት መስኮች በድምር ሲታይ፥ ፈተናውን ከወሰዱት 896,520 ተማሪዎች ውስጥ 29,909 (3%) የሚሆኑት ተማሪዎች 50% እና ከዚያ በላይ ያስመዘገቡ መሆናቸውን ገልፀዋል።

    ከተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች የተገኘው አማካይ ውጤት 31.6 ከመቶ ሲሆን፤ ከማኅበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች የተገኘው አማካይ ውጤት ደግሞ 27.8 ከመቶ ነው። በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች አማካይ ውጤት ከማኅበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች አማካይ ውጤት አሐዛዊ ጉልህ (statistically significant) ብልጫ እንዳላቸው ሚኒስትሩ አመላክተዋል።

    በአጠቃላይ ከፍተኛ ውጤት፥ በመላው ሀገሪቱ በማኅበራዊ ሳይንስ  ከ500 በላይ (ከሙሉ 600 ነጥብ) ያስመዘገቡ 10 (አስር) ተማሪዎች ብቻ ሲሆኑ፤ በተፈጥሮ ሳይንስ ከ600 በላይ (ከሙሉ 700 ነጥብ) ያስመዘገቡ ደግሞ 263 (ሁለት መቶ ስድሳ ሦስት) ተማሪዎች ናቸው። ወደፊት ጊዜው ሲደርስ እነዚህን እጅግ ከፍተኛ (great distinction) ላመጡ ተማሪዎች ትምህርት ሚኒስቴር ልዩ እውቅና እንደሚሰጣቸው ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስታውቀዋል።

    ፈተናውን ከወሰዱ አጠቃላይ 485,393 ወንድ ተማሪዎች መካከል ግማሽ (50%) እና ከዚያ በላይ ያገኙት 20,343 (4.2 በመቶ) ወንድ ተፈታኞች ሲሆኑ፤ ከተፈተኑት አጠቃላይ 411,127 ሴት ተማሪዎች መካከል ግማሽ (50%) እና ከዚያ በላይ ያገኙት 9,566 (2.3 በመቶ) ሴት ተፈታኞች ናቸው።

    ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች በማጠናከሪያ መርሐግብር (remedial program) እንደ ዩኒቨርሲቲዎቹ የመቀበል አቅም ተማሪዎችን ውጤት መሠረት አድርጎ በሚጸም የምልመላ መስፈርት ለዚህ ዓመት ብቻ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው በልዩ ሁኔታ በደከሙባቸው የትምህርት ዓይነቶች የተሻለ ዉጤት እንዲያስመዘግቡ የሚያስችል ድጋፍ ተደርጎላቸዉ ፈተና ተፈትነው የሚያልፉ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ይደረጋል ብለዋል። በዚህ የማጠናከሪያ መርሐግብር መሠረት፥ ዩኒቨርሲቲ ከሚቀላቀሉት እና መደበኛ ትምህርት (regular course) ከሚጀምሩ 29,909 ተማሪዎች ውጭ ያሉ ሌሎች ከ100 ሺህ የሚልቁ ተማሪዎች በውጤታቸው ተለይተው እንደ ዩኒቨርሲቲዎች የመቀበል አቅም እየታየ ለአንድ ዓመት የማሻሻያ ትምህርት ወስደው በድጋሚ እንዲፈተኑ ይደረጋል ብለዋል።

    የዚህ ዓመት የ12ኛ ክፍል ፈተና አንድምታ ለዓመታት ሲንከባለል የቆ የበርካታ ችግሮች መገለጫ እና ተሸፋፍኖ የቆየውን እውነተኛ የትምህርት ሥርዓታችን ያለበትን ደረጃ ያመላከተ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን ለዚህም ሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላት በጋር የሚወስዱት ኃላፊነት በመሆኑ ለቀጣይ ሥራ መረባረብ ይገባል ብለዋል።

    ከዚሁ ጋር በተያያዘ የትምህርት ሚኒስትሩ ከተገኘው የፈተናና የተፈታኞች ውጤት ባሻገር፥ አጠቃላይ ስለ አዲሱ የትምህርት እና ምዘና ሥርዓት አንዳንድ ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል። ከዚህ በፊት የነበረው የትምህርት እና ምዘና ሥርዓት በርካታ ብልሹ አሠራሮች እንደነበሩበት ያነሱት ሚንስትሩ፤ የአሁኑ የፈተና ሥርዓት ይህን ብልሹ አሠራር ለማረም የተወሰደ የመጀመሪያ እርምጃ ነው ብለዋል።

    የዚህ ዓመት ውጤት አንድምታ ሲታይ፥ ለዓመታት ከትውልድ ትውልድ ሲንከባለል የተሻገረውን እና ተሸፋፍኖ የቆየውን የትምህርት ሥርዓት ብልሽት የሚያሳይ ነው ብለዋል ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በመግለጫቸው።

    ለዚህም መንግሥት የትምህርት ሥርዓቱን ባለማሻሻል፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ባለመከታተልና በሥነ ምግባር ባለመቅረፅ፣ ትምህርት ቤቶች እና ባለሀብቶች በጋራ የወድቀቱ ተጠያቂ ናቸው ብለዋል። ከላይ የተጠቀሱ አካላት ቀጣይ መፍትሄዎች ላይ የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

    በ2014 ዓ.ም ከተሰጠው ፈተና እና ተፈታኞች የተገኘው ውጤትአስደንጋጭ እንደሆነ እንረዳለን ያሉት ሚኒስትሩ፥ ነገ የተሻለ ትውልድ ለመፍጠር በዚህ ውስጥ ልናልፍ ግድ ይለናል፤ ይህ የማንቂያ ደወል ሊሆን ይገባል ብለዋል። በበጎ ጎን ከተነሱጥ ነጥቦች መካከል፥ ፈተናው ሙሉ ለሙሉ ከስሮቆት የፀዳ እንደነበረም ተነስቷል።

    የፈተናው አሰጣጥ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈ እንደሆነ አንስተው፤ በስኬት ለመጠናቀቁ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

    ምንጭ፦ ትምህርት ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት መግለጫ ከትምህርት ሚኒስቴር

    #56088
    Semonegna
    Keymaster

    ቦረና ዞን ውስጥ በተከሰተው ድርቅ ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች የተሟላ ድጋፍ ለማድረግ በቅንጅት እየተሠራ ነው

    ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች በሚፈለገው ደረጃ ድጋፍ ማሠራጨት የሚያስችል የቅንጅት ሥራ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ። እስካሁን ከ204 ሺህ በላይ ኩንታል እህል ለተጎጂ ዜጎች መሠራጨቱም ተጠቁሟል።

    የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በቦረና ዞን በድርቅ አደጋ ጉዳት ከደረሰባቸው ዜጎች ውስጥ በ13 ወረዳዎች ውስጥ ለሚገኙ ወደ 604 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የዕለት ድጋፍ ቀርቦላቸዋል። ካለፉት ሁለት ወራት በ15 ቀናት ውስጥም ለእነዚሁ ወገኖች 204 ሺህ 765 ኩንታል ምግብ ወደ አካባቢው ተልኮ ተሠራጭቷል። ከጉዳቱ አንጻርና የተጎጂዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ በመንግሥትና በአጋር አካላት ቀጣይ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል የቅንጅት ሥራ እየተሠራ ነው።

    እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፥ ኮሚሽኑ በተለይ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡሮች፣ አጥቢ እናቶችና አቅመ ደካሞች የሚሆን 10 ኩንታል አልሚ ምግብ ወደ አካባቢው ተልኳል። ከዚህ በተጨማሪ የአካባቢው ሕብረተሰብ፣ ባለሀብቱ፣ ድጋፍ ሰጪዎችና መንግሥትም በዚሁ መልኩ ለወገኖች ሊደርስ የሚችለውን ድጋፍ እያቀረቡ ይገኛሉ።

    የኦሮሚያ ክልል 800ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የዕለት ድጋፍ መጠየቁን ገልጸው፥ በዚሁ ቁጥር ልክ ድጋፉ እንዲሰጥ ከአጋር አካላት ጋር አብሮ የሚሠራ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

    ድርቅን በሚመለከት በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ክስተቱ እንዳለ የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ ክስተቱ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል ብለዋል።

    በኢትዮጵያ የተፈጥሮ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜም በሦስት አካላት ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመው፤ እነዚህም መንግሥት፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። እነዚህም በየአካባቢው ጉዳት ባጋጠመባቸው ስፍራዎች የየድርሻቸውን በመያዝ ምግብና ምግብ-ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ከክልል ጋር በመሆን ለሥርጭት እንዲበቃ ያደርጋሉ ነው ያሉት።

    እንዲህ ዓይነት ችግሮች በሚያጋጥሙበት ጊዜ እንደ ኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የማስተባበር ሥራን በመሥራት ከሌሎች ሴክተር መሥሪያ ቤቶችና ከክልሎች ጋር አብሮ የሚሠራባቸው ስልቶች እንዳሉ ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል። ከእነዚህ ሥራዎች ውስጥም በክልል ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል ማቋቋም አንዱ እንደሆነና በዞን ደረጃ ብዙ ቁጥር ያላቸው ወገኖች ጉዳት ሲደርስባቸው የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት እንደሚቋቋም ጠቅሰዋል።

    ይህም በክልል የሚመራና ኮሚሽኑ የሚደግፈው የጤና፣ የግብርና፣ የውሃ፣ የትምህርትና ሌሎች ጉዳዮች እንደመኖራቸው ሌሎች ሴክተር መሥሪያ ቤቶችን አስተባብሮ ማስኬድ የሚያስችል ድጋፍ በቅንጅት እየተሠራ እንዳለ አመላክተዋል።

    በዓለም አቀፍ ደረጃ ባሉ ሁኔታዎች ምክንያት በአጋር አካላት የሚደርሰው ድጋፍ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳርፉ ይችላሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፥ የተበታተነውን ሁኔታ መሰበሰብ የሚያስችል ከሀገር ቤት እስከ ውጭ ያሉ አካላት የሚሳተፉበት ተግባራትም እንዳሉ ጠቁመዋል።

    አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያምን ጨምሮ በየቢሯቸው በመገኘት አጋር አካላትን፣ ኤምባሲዎችን፣ የመንግሥታቱ ኅብረት ተወካዮችን እያነጋገሩ እንዳለ ገልጸዋል። በዚህ መልክ ድጋፉ እንዲጠናከር ይደረጋል ሲሉም አስታውቀዋል።

    ዳይሬክተሩ እንዳሉት፥ በሀገሪቷ ድርቅና ሌሎች ተዛማች ችግሮች አሉ። በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ለመቋቋም ከሀገር ውስጥ አቅም ባሻገር የአጋር አካላት አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው። ለዚህም አጋር አካላት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥረት እየተደረገ ነው። በአሁኑ ወቅትም ድጋፉ እየመጣ ነው፤ ለዚህም በሚፈለገው ደረጃ ማሠራጨት የሚያስችል የቅንጅት ሥራ እየተሠራ ነው።

    ከመንግሥት እንቅስቃሴ በተጨማሪ የተለያዩ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያዊ ተቋማት ቦረና ዞን ውስጥ በተከሰተው ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የተለያዩ እርዳታዎችን እያሰባሰቡ ይገኛሉ። እርስዎም በዚህ ድጋፍ ለመሳተፍ የሚከተሉትን ማስፈንጠሪያዎች ይጫኑ።

    1. ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት (GARE) በጎፈንድሚ (GoFundMe) በኩል፦ GARE4Borena
    2. በሀገር ውስጥ ደግሞ የጉዞ አድዋ ማኅበር አስተባባሪ ያሬድ ሹመቴ (Yared Shumete) እና መምህር ታዬ ቦጋለ አረጋ “ዓድዋ 127 ለቦረና” በሚል እንቅስቃሴ በመጀመር የተለያዩ ድጋፎችን (ገንዘብ፣ የምግብ ምርቶችን፣ ወዘተ) እያሰባሰቡ ነው። ያግኟቸው፦ http://www.facebook.com/shumeteyared እና http://www.facebook.com/tayebogale.arega

    #60175
    Semonegna
    Keymaster

    ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ የክብር ዶክትሬታቸውን ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተቀበሉ

    ባሕር ዳር፥ ኢትዮጵያ (ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ) – ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሐምሌ 16 ቀን፥ 2015 ዓ.ም ባካሄደው የተማሪዎች ምረቃ ለጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ የክብር ዶክትሬት መስጠቱ ይታወሳል። በዕለቱ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ በሥራ መደራረብ ምክንያት በምረቃ ዕለቱ ተገኝተው ባለመቀበላቸው፥ ኅዳር16 ቀን፥ 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ስካይላይት ሆቴል በአካል ተገኝተው ተቀብለዋል።

    በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የ2015 ዓ.ም የተማሪዎች ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የመጀመሪያዋ የክብር ዶክትሬት ተሸላሚ የጠንካራ ጋዜጠኝነት ተምሳሌቷ እና የባለታሪኮች ባለአደራ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ናት።

    የክብር ዶክተር መዓዛ ብሩን ለክብር ዶክትሬት ሽልማት ያበቋቸው ሥራዎች በዝርዝር:-

    • በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል ኤፍ ኤም ሬዲዮ (ሸገር ኤፍ ኤም 1) መሥራች እና ባለቤት፤
    • የመጀመሪያዋ ሴት የሬዲዮ ማሰራጫ ድርጅት መሥራችና ባለቤት፤
    • በእንግዶች ምርጫዋ፤ በምርምር በተደገፈ የመጠይቅ ዘይቤዋ፣ በትህትናዋ፣ በአነጋገር ለዛዋ በቀጥታ አዘጋጅታ ከምታቀርባቸው መርሃ ግብሮች (የቅዳሜ ጨዋታ እና ሸገር ካፌ) በተጭማሪ በተለያዩ የሸገር ሬዲዮ መርሃ ግብሮች እንዲሁም በሌሎች ሬዲዮም ሆነ ቴሌቪዥን መርሃ ግብሮች ላይ አሻራ የተወች እና ባጠቃላይ በዚህ ዘርፍ ለተሰማሩ ጋዜጠኞች አርአያ የሆነች፤

    ምናልባት ከሁሉ በላይ ታዋቂ የሆነችበትና አምሳያ የሌለው የላቀ አስተዋፅኦ ተብሎ ሊወሰድ ከሚችሉት ሥራዎቿ ውስጥ አንዱ፥ በቀላሉ ተተኪ የማይገኝላቸውን በርካታ ባለታሪክ ምሁራን፣ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፤ የኪነ-ጥበብ ሰዎች፤ ጋዜጠኞች እና ሌሎች ባለሙያዎች የህይውት ታሪክ፣ ሥራ፣ አስተሳሰብ እና ለሌሎች አርአያ የሚሆነውን የሕይወት ፍልስፍናቸው በራሳቸው አንደበት ተሰናድቶ ለታሪክ እንዲቆይ ማድረጓ ነው። በዚህም ለኢትዮጵያውያን በዓይነቱ ተወዳዳሪ የሌለውና ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ የሚሄድ የታሪክ የድምጽ መዘክር አበርክታለች ማለት ይቻላል። የጨዋታ እንግዳ መሰናዶ እንግዶቿ ያካበቱት ልምድ፤ አበርክቶታቸው፤ ያልተጻፉ ሃገራዊ ጉዳዮች እና ሚስጥሮች ከኃላፊ ባለታሪኮቹ ጋር እንዳያልፉ፤ በመቅረጸ-ድምጽ ተሰንቀው በሰፊው እንዲታወቁ እና ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፉ አድርጋለች። በእርግጥም ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ከየተደበቁበት ፈልጋ ቃለ መጠይቅ ካደረገቻቸው ጉምቱ እንግዶች መካከል ጥቂት የማይባሉት አሁን በመሃከላችን አይገኙም፤ ታሪካቸው ግን ህያው ሆኗል።

    ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ በ1950 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ የተወለደች ሲሆን፥ ዘጠኝ ዓመት ገደማ እስኪሆናት በምዕራብ ሃረርጌ በምትገኘው ሂርና ከተማ አደገች። ሂርና ሳለች ጎረቤቶቿ የኦሮሞ፣ የሃረሪና የሶማሌ እንዲሁም የየመን ተወላጆች ስለነበሩ በተለያዩ ባሕላዊ ዕሴቶች እና እርስ በእርስ ትስስር የዳበረ አስተዳደግ ነበራት። ይህም ለሥነ-ጽሁፍ ከነበራት ዝንባሌ ጋር ተዳምሮ ለዛሬው ማንነቷ መሠረት ሆኗታል።

    • ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩዘጠኝ ዓመት ሲሆናት ወላጆቿ አዲስ አበባ ወደሚገኘው የቅድስተ ማርያም የልጃገረዶች ካቶሊክ አዳሪ ትምህርት ቤት አሰገቧት።
    • 1967 ዓ.ም. የሁለትኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለች በእድገት በሕብረት ዘመቻ ወደ ውቅሮ፥ ትግራይ ተልካ ለስድስት ወራት አገልግላለች።
    • በ1970 ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብታ በሥነ ልሳን ትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ተቀብላለች።
    • ከሬዲዮ ሥራ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀችው የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳለች በአጋጣሚ ሲሆን፥ በወቅቱ ተወዳጅ ከነበረው የእሁድ ፕሮግራም ጋር ለነበራት ለስምንት ዓመታት ያክል የቆየ ትስስር ምክንያት ሆኖታል። ይሁን እንጂ በመጀመሪያ በቋሚነት የተመደበችበት ሥራዋ በባህል ሚኒስቴር ስር የመርሃ ስፖርት ጋዜጣ የስፖርት ዘጋቢነት ነበር።
    • በመቀጠልም በኢትዮጵያ ሬዲዮ የእሁድ ፕሮግራም ተሳትፎዋን ሳታቆም በባህል ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ አግልግሎት ክፍል አገልግላለች።
    • ከዚያም በብሔራዊ ባንክ የብሪቱ መጽሄት ዋና አዘጋጅ በመሆን የፋይናንስ ዜናዎችን እና አጫጭር ታሪኮችን በመጻፍ እና በአርትኦት አገልግላለች።
    • በ1984 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ተቀላቅላ የፕሬስ እና ኮሚኒኬሽን ኦፊሰር በመሆን ለአራት ዓመታት ሠርታለች።
    • ከዚያም በግል በአማካሪነት እና በሕዝብ ግንኙነት እና ማስታወቂያ ስትሠራ ከቆየች በኋላ፤ በ1987 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሬዲዮ በ1 የሬዲዮ ጣቢያን የአየር ሰዓት በመጠቀም የቅዳሜ ከሰዓት የጨዋታ መርሀ ግብርን ከባለቤቷ ከአርቲስት አበበ ባልቻ እና ከረዥም ጊዜ ጓደኛዋ አርቲስት ተፈሪ ዓለሙ ጋር የማዘጋጀት ዕድል አግኝታ መርሀ ግብሩን ለስምንት ዓመታት ያክል ስታቀርብ ቆይታለች።
    • በመጨረሻም በ2000 ዓ.ም. አንጋፋና ተወዳጅ የሆነውን ሸገር ኤፍ ኤም1ን እዉን ለማድረግ በቅታለች።

    በአጠቃላይ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ የጥንካሬ ተምሳሌትና በዘርፉ ለበርካቶች አርአያ ለመሆኗ ተገቢ ዕውቅና ይሆን ዘንድ የባሕር ዳር ዩኒቨርሰቲ ሴኔት በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1152 / 2011 በተሰጠው ስልጣን መሠረት በአርት የዓመቱ የክብር ዶክትሬት እንዲሰጣቸው ወስኗል።

    ምንጭ፦ ባሕር ዳር ዩኒቨርሰቲ

Viewing 15 posts - 1 through 15 (of 15 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.