Search Results for 'የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን'

Home Forums Search Search Results for 'የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን'

Viewing 9 results - 1 through 9 (of 9 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ በ3 ቢሊዮን ብር ለሚያስገነባው ገርጂ የመኖሪያ መንደር ከተቋራጮች ጋር ስምምነት ተፈራረመ

    አዲስ አበባ (ኢብኮ)፦ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ገርጂ አካባቢ በሶስት ቢሊዮን ብር ለሚያስገነባው ዘመናዊ መንደር (ገርጂ የመኖሪያ መንደር ፕሮጀክት/ Gerji Village Project) ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ተቋራጮች ጋር ነሐሴ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ስምምነት ፈፅሟል። ኮርፖሬሽኑ ስምምነቱም ያደረገው ከኮሪያ፣ ከህንድ እና ከኢትዮጵያዊያን የህንጻ ተቋራጮች መሆኑን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) ዘግቧል።

    ገርጂ የመኖሪያ መንደር ፕሮጀክትን ይፋ ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስተሩ የካቢኔ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የቦርድ ኃላፊ ወ/ሮ ደሚቱ ሐምቢሳ ናቸው።

    በስምምነቱ መሠረት ገርጂ የመኖሪያ መንደር ውስጥ በሚቀጥሉት 18 ወራት ውስጥ 510 መኖሪያ ቤቶች ይገነባሉ። የሚገነቡት መኖሪያ ቤቶች ባለ 10 ወለል የሚኖራቸው 16 ህንጻዎች መሆናቸው ተገልጿል።

    ገርጂ የመኖሪያ መንደር ሲጠናቀቅ በከተማዋ የሚታዩ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግርን በተወሰነ መልኩ የሚያቃልል መሆኑን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ረሻድ ከማል ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት ገልጸዋል።

    ግንባታው በዘመናዊ መንገድ የሚገነባ በመሆኑ የግንባታ ወጪውንም ሆነ ጊዜውን የሚያቀላጥፍ መሆኑ ተመክቷል፤ አንድ የህንጻ ወለልን በአምስት ቀናት ውስጥ ሠርቶ የሚያጠናቅቅ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ይውላል ተብሏል።

    አዲአ አበባ ውስጥ ሲ.ኤም.ሲ ከሚገኘው የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የመኖሪያ መንደር ልምድ ተወስዶ፥ በሦስት ሔክታር ላይ የሚገነባው የገርጂ የመኖሪያ መንደር ሲጠናቀቅ ዘመናዊነትን የተላበሰ የመኖሪያ መንደር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። የመኖሪያ መንደሩ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ለመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ይውሏል ተብሏል።

    የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከ28 ዓመት በኋላ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ወደ ቤቶች ግንባታ ራሱን በመመለስ፣ በተለያዩ ስምንት የግንባታ ቦታዎች ቤቶችን እየገነባ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ረሻድ ከማል በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተናግረዋል። ኮርፖሬሽኑ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ገቢውን እያሳደገ ሰፊ የቤት አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ ይሠራልም ብለዋል አቶ ረሻድ።

    ምንጭ፦ ኢብኮ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ሌሎች ዜናዎች

    ገርጂ የመኖሪያ መንደር

    Semonegna
    Keymaster

    የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በ2012 በጀት ዓመት 715 ኪ.ሜ. የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎችን ማከናወኑን አስታወቀ

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – በ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት 715 ኪ.ሜ. የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎችን ማከናወኑን፣ 21 የመንገድ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቁንና አዳዲስና ግዙፍ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ማስጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።

    ባለስልጣኑ ለአዲስ አድማስ ዕለታዊ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ በበጀት ዓመቱ 706 ኪ.ሜ. የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎችን ለማከናወን አቅዶ 715 ኪ.ሜ. በማከናወን ከዕቅድ በላይ አፈፃፀም አስመዝግቧል። በዚሁ በጀት ዓመት ከተሠራው አጠቃላይ የመንገድ ሥራ ውስጥ 167 ኪ.ሜ. አዳዲስ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 544 ኪ.ሜ. ልዩ ልዩ የመንገድ ጥገና ሥራዎች ናቸው።

    ባለስልጣኑ በግንባታ ላይ ከነበሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል 21 የሚሆኑትን በማጠናቀቅ አስመርቆ ለትራፊክ ክፍት ያደረገበት በጀት ዓመትም መሆኑን ጠቅሶ፥ በሁለት ዙር በይፋ የተመረቁት የመንገድ ግንባታዎች በድምሩ ከ33 ኪ.ሜ. በላይ ርዝመት እና የእግረኛ መንገድን ጨምሮ ከ10 እስከ 30 ሜትር የጎን ስፋት ያላቸውና ለግንባታቸውም ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሆነባቸው መሆኑን አመልክቷል።

    በ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት በዓይነታቸው ለሀገሪቱም ሆነ ለመዲናዋ አዲስና ግዙፍ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ማስጀመሩንም የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አስታውሶ፥ ከእነዚህም መካከል የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስፋፋት የተጀመረው የዊንጌት–ጀሞ ሁለት የፈጣን አውቶቡስ መንገድ እና የፑሽኪን አደባባይ–ጎተራ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች እንደሚገኙበት ገልጿል።

    በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግባቸው እና ከ90 ኪ.ሜ. በላይ ርዝመት ያላቸው 22 የመንገድ ፕሮጀክቶች መጀመራቸውንም ባለስልጣኑ ጠቅሷል። በ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት የተጀመሩት እነዚህ ታላላቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች በሁለት ዓመት ውስጥ ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሠራ እንደሚገኝም ባለስልጣኑ ጠቁሟል።

    በበጀት ዓመቱ በመንገድ መሠረተ ልማት ሀብቶች ላይ በርካታ ጉዳቶች መድረሳቸውንም አያይዞ የጠቀሰው ባለስልጣኑ፥ በ12 ወራት ውስጥ በተሽከርካሪ ግጭት ብቻ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት በመንገድ መሠረተ ልማት ሀብቶች ላይ መድረሱንና ይህም በመንገድ መሠረተ ልማት ሀብቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን እንደሚያሳይ አመልክቷል።

    በተሽከርካሪ ግጭት በብዛት ጉዳት ከደረሰባቸው የመንገድ ሀብቶች መካከል የመንገድ ዳር መብራት ምሰሶዎች፣ የትራፊክ ምልክቶች፣ የአቅጣጫና ርቀት አመላካች ሰሌዳዎች፣ የእግረኛ መከላከያ አጥሮች፣ የመንገድ ማካፈያ ግንቦች፣ ውሃ መውረጃ ቱቦዎችና ክዳኖች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ዘርዝሯል።

    የወሰን ማስከበር ችግር፣ የተቋራጮች አቅም ውስንነት፣ የገልባጭ መኪና እና ግብዓት እጥረትና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራ ወቅት የገጠሙ ዋነኛ ፈተናዎች እንደነበሩም ባለስልጣኑ አስታውሶ፥ ችግሮቹን በመፍታት በአፈፃፀም ላይ ሊያሳድሩ የነበረውን ተፅዕኖ መቀነስ መቻሉን አስታወቋል። በበጀት ዓመቱ ለመንገድ ፕሮጀክቶች እና ለመደበኛ ሥራዎች አስከአሁን ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም ባለስልጣኑ ጠቅሷል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

    የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን

    Semonegna
    Keymaster

    ከ19.9 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 12 መንገዶችን ለመገንባት የሚያስችል ውል ስምምነት ፊርማ ተካሄደ
    የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን 

    አዲስ አበባ (ኢመባ) – የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን (ኢመባ) ከ19.9 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 12 መንገዶችን በአስፋልት ደረጃ ለመገንባት የሚያስችል ውል ስምምነት ፊርማ ከተለያዩ ሀገር በቀል እና የውጭ ተቋራጮች ጋር አካሄደ።

    አሥራ ሁለቱ የሚፈረሙት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በደምሩ 825.23 ኪ.ሜ ርዝማኔ ያላቸው ሲሆን፥ ለግንባታቸው የሚወጣው ወጪ የሚሸፈነው የአስሩን መንገዶች በኢትዮጵያ መንግሥት፣ የሁለቱን መንገዶች ደግሞ ከዓለም ባንክ (World Bank) በተገኘ ብድር ነው። የውል ስምምነት ከፈጸሙት የሥራ ተቋራጮች መካከል ስድስቱ አገር በቀል የሥራ ተቋራጮች ሲሆኑ፥ የተቀሩት አራቱ አለም አቀፍ የውጭ ሥራ ተቋራጭ ድርጅቶች ናቸው።

    የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በሰጠው መግለጫ፥ መንገዶቹን ገንብቶ ለማጠናቀቅ እንደመንገዶቹ ሁኔታ ከአንድ ዓመት ከአምስት ወር ጀምሮ እስከ አራት ዓመት ጊዜ ተሰጥቷቸዋል።

    • የአስራ ሁለቱን የመንገድ ፕሮጀክቶች ዝርዝር እና እያንዳንዱን የመንገድ ፕሮጀክት ለመገንባት ያሸነፈውን ተቋራጭ ዝርዝር ለማየት እዚህ ጋር ይጫኑ።

    የግንባታ ፕሮጀክቶቹ የመንገድ ግራና ቀኝ ትከሻን ጨምሮ በገጠር በአማካይ ከስምንት እስከ አስር ሜትር ስፋት ሲኖራቸው፥ በከተማ ውስጥ የሚገነቡት ምንገዶች ተጨማሪ  ስፋት እንዲኖራቸው ተደርገው የሚገነቡ ይሆናል። በተጨማሪም ግንባታው የአነስተኛ፣ ከፍተኛ ፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎች እና ድልድዮችንም አካቷል።

    የመንገዶቹ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከዚህ በፊት በአካባቢው የነበረውን የትራንስፖርት ችግር በመቅረፍ የአካባቢው ሕብረተሰብ በቀላሉ ወደ ፈለገው ቦታ የሚንቀሳቀስበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ከዚህም ባለፈ አንድን ክልል ከሌላ ክልል፣ እንዲሁም በየክልሎቹ ውስጥ የሚገኙ ዞኖችንና ወረዳዎችን እርስ በእርስ የሚያስተሳስሩ ይሆናሉ። ከተፈረሙት መንገዶች መካከልም ወደ ጎረቤት አገር የሚያዘልቁ መንገዶችም በመኖራቸው አገራዊ ፋይዳቸው ላቅ ያለ እንደሚሆን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን መግለጫ ያስረዳል።

    መንገዶቹ የተሽከርካሪዎችን የጉዞ ጊዜና ወጪን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንሱ ከመሆኑም በተጨማሪ የምርትና የሸቀጥ ልውውጥ ያለምንም እንግልት በቀላሉ እንዲከናወን ከማድረግ አኳያ የተፈረሙት መንገዶች ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ ያደርገዋል።

    እነዚህ መንገዶች በአገሪቱ ካለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲሁም መንግሥት ከያዘው የድህነት ቅነሳ ስልት (poverty reduction strategy) አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ይታመናል። ስለሆነም የመንገድ ኘሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲጠናቀቁ በአካባቢው የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጉዳዮች ከፍተኛ ትብብር እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ያሳስባል።

    ምንጭ፦ ኢመባ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን

    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አውሮፕላኖቹ ከበረራ አገልግሎት እንዲወጡ መወሰኑን አስታወቀ
    —–

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አውሮፕላኖቹን በሙሉ ላልተወሰነ ጊዜ ከበረራ አገልግሎት እንዲወጡ መወሰኑን አስታወቀ።

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫው ነው አውሮፕላኖቹን ላልተወሰነ ጊዜ ከበረራ ማስወጣቱን ያስታወቀው።

    አየር መንገዱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰውም በትናንትናው እለት ቦይንግ 737-8 ማክስ በበረራ ቁጥር ኢቲ 302 የደረሰበትን የመከስከስ አደጋ ተከትሎ መሆኑንም አስታውቋል።

    በዚህም መሰረት የአደጋው መንስኤ ተጣርቶ እስኪታወቅ ድረስ ለመንገደኞች ደህንነትና ጥንቃቄ ሲባል ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አውሮፕላኖቹን በሙሉ ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ከበረራ አገልግሎት እንዲወጡ መወሰኑን ገልጿል።

    አየር መንገዱ ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አምስት አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን፥ በትናንትናው እለት የተከሰከሰውም ከአራት ወራት በፊት የተረከበው 4ኛው አውሮፕላኑ ነበር።

    በተመሳሳይ ዜና ቻይናም በሀገሯ የሚገኙ ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አውሮፕላኖቿ በሙሉ ላልተወሰነ ጊዜ ከበረራ አገልግሎት እንዲወጡ መወሰኗም ተነግሯል።

    የቻይና የአቪዬሽን ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የቻይናን አየር መንገዶች ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አውሮፕላኖችን ለበረራ መጠቀም እንዲያቆሙ አስታውቋል።

    ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኘው አውሮፕላን ባለፉት አምስት ወራት የመከስከስ አደጋ ሲያጋጥመው የትናንቱ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

    ከአምስት ወራት በፊት ላዮን ኤየር የተሰኘ የኢንዶኔዢያ አየር መንገድ ንብረት የሆነ ተመሳሳይ ሞዴል አውሮፕላን ለበረራ በተነሳ በደቂቃዎች ውስጥ ተከስክሶ 189 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።

    ምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ

    Anonymous
    Inactive

    የሞጆ ሃዋሳ የፍጥነት መንገድን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው
    —–

    በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው የተጓተተውን የሞጆ ሃዋሳ የፍጥነት መንገድን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።

    ከሞጆ ተነስቶ ሀዋሳ ከተማን መዳረሻው የሚያደርገው የፈጣን መንገድ ፕሮጀክት በ2008 ዓ.ም ነበር ግንባታው የተጀመረው።

    201 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን መንገድ በፍጥነት ለማጠናቀቅም በአራት ምዕራፍ በመከፋፈል ለመገንባት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።

    ሆኖም የፍጥነት መንገዱ በተያዘለት ጊዜ ግንባታው እየተከናወነ አለመሆኑን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በተለያየ ጊዜ ባደረገው ቅኝት መታዘብ ችሏል።

    ከሞጆ መቂ፣ ከመቂ ባቱ፣ ከባቱ አርሲ ነጌሌ እና ከአርሲ ነጌሌ ሃዋሳ ለተለያዩ ተቋራጮች የተሰጠው ፕሮጀክት፥ የወሰን ማስከበር ችግር፣ በግብዓት አቅርቦትና መሰል ችግሮች ሳቢያ በፍጥነት መገንባት አለመቻሉን የባለስልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ተናግረዋል።

    የሞጆ መቂው የመንገዱ አንድ ምዕራፍ አሁን ላይ አፈጻጸሙ 70 በመቶ የደረሰ ሲሆን፥ በአንጻሩ 37 ኪሎ ሜትር ከሚረዝመው ከመቂ ባቱ መንገድ ውስጥ እስካሁን 14 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ብቻ መስራት እንደተቻለ ነው የተናገሩት።

    57 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውና ከባቱ አርሲ ነጌሌ ከሚደርሰው የፍጥነት መንገዱ አካልም ከ1 ነጥብ 5 በመቶ በላይ ስራውን ማከናወን አልተቻለም።

    በሌሎቹ የመንገዱ አካል የተስተዋለው ችግርም በባቱ አርሲ ነጌሌ መንገድ ተደግሟል የሚሉት ዳይሬክተሩ፥ የመንገዱ ግንባታ የተደቀነበት ስጋት እንዳይቀጥል መፍትሄ ተቀምጧል ብለዋል።

    ከየአካባቢው መስተዳድር ጋር ውይይት በማድረግም በቅርብ ክትትል ፈጣን መንገዱን ለማጠናቅቅ ባለስልጣኑ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

    አሁን ላይም በፕሮጀክቱ ከዚህ ቀደም ያጋጠመውን የወሰን ማስከበርና መሰል ችግሮችን በመቅረፍ ግንባታው እየተፋጠነ ይገኛልም ነው ያሉት አቶ ሳምሶን ወንድሙ።

    201 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የሞጆ – ሃዋሳ የፍጥነት መንገድ በ14 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር እየተገነባ ሲሆን በ2013 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

    የመንገዱ ግንባታ የሃገሪቱን የወጪ ንግድ ከማሳለጥ ባለፈም ቀጠናዊና አህጉራዊ ትስስርን ለመፍጠር ግብ ላላት አፍሪካ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።

    ምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ

    Semonegna
    Keymaster

    የመንገዶች የመብራት አገልግሎት አለመስጠት ምክንያቱ ኃይል ያልተለቀቀላቸው በመኖራቸው፣ መሠረተ ልማቶች ስለሚዘረፉ፣ የምሰሶና የአምፖል ማርጀት እንደሆነ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ጠቅሷል።

    አዲስ አበባ (ኢዜአ)–በአዲስ አበባ ከተማ ካሉት መንገዶች ውስጥ የመብራት አገልግሎት እያገኙ ያሉት ከ40 በመቶ እንደማይበልጥ ያስታወቀው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን እስከሚቀጥለው ዓመት ዘጠና በመቶ የከተማዋ መንገዶች መብራት እንዲኖራቸው ከአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢሮ ጋር እየሠራሁ ነው ብሏል።

    የመንገዶች የመብራት አገልግሎት አለመስጠት ምክንያቱ ኃይል ያልተለቀቀላቸው በመኖራቸው፣ መሠረተ ልማቶች ስለሚዘረፉ፣ የምሰሶና የአምፖል ማርጀት እንደሆነ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ጠቅሷል።

    የመብራት ምሰሶዎች በየመንገዱ ቢተከልም ከሁለት ዓመት ወዲህ አብዛኛዎቹ አገልገሎት እንደማይሰጡ የጠቀሱት የአፍንጮ በር ነዋሪ አወል አማን፥ በምሽት ወደ መስጊድ ሲሄዱና ከሥራ አምሽቶ ወደ ቤት ለመግባት ስጋት ፈጥሮብናል ብለዋል። አክለውም ምሰሶዎችና አምፖሎች ተሰባብረው እንደሚገኙ ያነሱት ነዋሪው አገልግሎት የማይሰጡ መብራቶች እንዲጠገኑ ጠይቀዋል።

    የጉለሌ አካባቢ ነዋሪ አቶ ፀጋዬ መኩሪያ መኪና አሽከርካሪ ሲሆኑ፥ መንገዶች የምሽት መብራት ከሌላቸው ለአሽከርካሪዎች ፈታኝ በመሆኑ የትራፊክ አደጋ ይከሰታል ብለዋል። አቶ ጸጋዬ እንደሚሉት ጉለሌ አካባቢ በርካታ መኪናዎችና እግረኞች የሚተላለፉበት ቢሆንም የምሽት መብራት የላቸውም፤ ብዙዎችም አደጋ እየደረሰባቸው ነው።

    ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስም ሆነ አሮጌ መኪናዎች ከሚገባው በላይ ውድ የሆኑበት ምክንያት ምንድን ነ?

    የላዳ ታክሲ አሽከርካሪ ማቲዮስ ታምር ሥራው በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች እንዲዘዋወር ስለሚያደርገው በርካታ መንገዶችን እንዳየና መብራት እንደሌላቸው ተናግሯል። ውስጥ ለውስጥና በዋና መንገዶች መብራት በብዛት አለመኖሩ መሪን ያለ አግባብ የመጠቀም ዕድል ስለሚኖር የመጋጨት አጋጣሚውም ሰፊ ነው ብሏል።

    ከስድስት ኪሎ ሽሮ ሜዳ፣ ከሰሜን ማዘጋጃ እንጦጦ፣ ከእንቁላል ፋብሪካ ዊንጌት ባሉ መንገዶች እንደሚሰሩ የገለፁት በአዲስ አበባ የጉለሌ ክፍለ ከተማ የትራፊክ ቁጥጥር አባል ምክትል ኢንስፔክተር አያሌው በለጠ ከነዚህ መንገዶችም አብዛኛዎቹ መብራት የላቸው ብለዋል።

    መዲናዋ በተሽከርካሪዎችና በእግረኞች የተጨናነቀች በመሆኗ በጨለማ ወቅት መብራት አለመኖሩ የትራፊክ አደጋን አባብሷል ነው ያሉት ምክትል ኢንስፔክተሩ።

    መብራት ከሌለ አሽከርካሪዎች ረጅም መብራት የመጠቀም ዕድላቸው ሰፊ ነው ያሉት ረዳት ኢንስፔክተር መራጭ ድንጌቻ፤ ከፊት ለፊት የሚመጡ መኪናዎችን እይታ ሙሉ ለሙሉ በመሸፈን ለአደጋ ያጋልጣል ብለዋል።

    “ከእንቁላል ፋብርካ እስከ ዊንጌት ብዙ ሆስፒታሎች ስላሉ ህሙማንን የያዙ ተሽከርካሪዎች ቀንና ሌሊት ይመላለሳሉ፤ ባለፈው ዓመት በዚያ መንገድ በርካታ ሰዎች ተገጭተዋል” ነው ያሉት።

    ምክትል ኢንስፔክተር አያሌው “ከዚህ ቀደም በአዲሱ ገበያ ዊንጌት በሚወስደው መንገድ አንዲት ሴት ተገጭታ መብራት ባለመኖሩ ምክንያት ሌሊቱን ሙሉ መኪና ሲመላለስባት አድሮ የገላዋ ዱቄት ነው የተነሳው” ሲሉ ያጋጠማቸውን አሳዛኝ ክስተት ነግረውናል።

    በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ መብራት ክትትል ባለሙያ ኢንጅነር ደረጀ ኃይሉ የከተማዋ መንገዶች አንዳንዶቹ የመብራት አገልግሎት እንደሌላቸው ገልጸው “ከጉርድ ሾላ ኦቨር ፓስ፣ መገናኛ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ከስድስት ወር በፊት ተጠይቆ የዋጋ ግምት አልተመለሰልንም” ነው ያሉት።

    የቦሌ አራብሳ መንገድ ከሁለት ዓመት በፊት ለአገልገሎት ክፍት ሆኖ የመብራት ምሰሶ ቢተከልም መብራት እንዳልተለቀቀ የገለጹት ኢንጅነር ደረጀ ከስድስት ኪሎ ፈረንሳይ ጉራራ ኪዳነምኅረት የምሰሶ ተከላና የገመድ ዝርጋታ የማሟላት ሥራ ተከናውኖ የኃይል ዋጋ ግምት እንዲላክለት ከአንድ ወር ወዲህ መጠየቁን ተናግረዋል።

    በባለስልጣኑ የድንገተኛና አንሰለሪ ጉዳዮች ቡድን መሪ አቶ ዘውዱ ባይህ በበኩላቸው መብራት ተቋርጦባቸው የነበሩ 37 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የቀለበት መንገዶች ባለፈው ዓመት ተጠግነው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

    ጨለማን ተገን አድርገው ዝርፊያ የሚፈጽሙ አካላት የመብራት ቁሳቁሶችን ከአገልግሎት ውጪ እያደረጉና እየዘረፉ መሆኑን የተናገሩት አቶ ዘውዱ ከዮሴፍ-ቦሌ ሚካኤል፣ ከአየር መንገድ አደባባይ-ኢምፔሪያል፣ ሸጎሌ ከጎጃም በር-እስከ ዊንጌት እንዲሁም 18 ማዞሪያ፣ ከ3 ቁጥር ማዞሪያ-አለርት ቁሳቁሶቹ በየጊዜው እየጠፉ ተቸግረናል በማለት አስረድተዋል።

    የተበላሹትን ወደ አገልገሎት ለመመለስ በራስ ኃይልና በጨረታ እየተጠገኑ መሆኑን ያነሱት ቡድን መሪው አሮጌ መብራቶችን ደረጃቸውን የጠበቁ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

    በከተማዋ መንገዶች ከ40 በመቶ የማይበልጡ የመብራት አገልግሎት ያላቸው ሲሆን ባለሥልጣኑ 25 ሚሊዮን ብር በመመደብ ጥገና እየሠራ ነው፤ በዚህ በጀት ዓመትም ሽፋኑን 90 በመቶ ለማድረስ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

    የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ክፍሌ በበኩላቸው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ባለው ውል መሠረት ቆጣሪና ትራንስፎርመር እየገጠምን ነው ብለዋል።

    ሆኖም የሲቪል ሥራዎች በመንገዶች ባለስልጣን በኩል ባለመጠናቀቃቸውና የመንገድ ርክክብ ባለማድረጋቸው ምክንያት መብራት የማያገኙ መንገዶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

    “የካ አባዶ አንድ መንገድ፣ ከስድስት ኪሎ ፈረንሳይ ጉራራ መንገድ ተገምቷል፣ ቦሌ አራብሳ እየተገመተ ነው፣ ጎሮ ቱሉ ዲምቱ ትራንስፎርመርና ቆጣሪ ተገጥሟል፣ ከሲኤምሲ አደባባይ እስከ ካራ ትራንስፎርመርና ቆጣሪ ቢገጠምም መንገዱን ርክክብ አላደረጉም፣ ከዊንጌት አደባባይ እስከራስ ደስታ ሆስፒታል ላለው መንገዶች ባለስልጣን ግምት አላመጣም፣ ዓለም ባንክ ቤቴል አየር ጤና ፍርድ ቤት ያሉት ያልተጠናቀቁ የሲቪል ሥራዎች ሲጠናቀቁ ኃይል ይለቀቅላቸዋል” ብለዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን

    Semonegna
    Keymaster

    ጅማ (ኢ.መ.ባ.)– የጅማ – አጋሮ – ዲዴሳ ወንዝ ድልድይ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዓብይ አህመድ በተገኙበት በይፋ መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን (ኢ.መ.ባ) አስታወቀ።

    የአንድን ሀገር ልማት በማፋጠን ረገድ ጉልህ ሚና ካላቸው የመሠረተ ልማት ዘርፎች አንዱ መንገድ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት እና በነደፈው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት የዘርፉ ዋነኛ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ለተግባራዊ እንቅሰቃሴው ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።

    የጅማ – አጋሮ – ዲዴሳ ወንዝ ድልድይ የመንገድ ፕሮጀክት ነባሩ መንገድ ገፅታ

    • በጠባብ የአስፋልት መንገድ ደረጃ የነበረ፣
    • የ50 ዓመት አገልግሎት የሰጠ፣
    • በ5 ሜትር ስፋት እጅግ አስቸጋሪ የነበረው፣ እና
    • ለትራፊክ እንቅስቃሴዎች ምቹ ባለመሆኑ ለአደጋ ሲያጋለጥ የነበረ መንገድ ነው።

    የጅማ – አጋሮ – ዲዴሣ ወንዝ ድልድይ የመንገድ ፕሮጀክት አዲሱ መንገድ ገፅታ

    • የ2ኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመንገድ ዘርፍ ልማት መርሃ ግብር አንድ አካል ነው፤
    • የአገሪቱን ደቡብ አና ሰሜን ምዕራብ ክፍሎች ደረጃውን በጠበቀ የመንገድ መሠረተ ልማት ያስተሳስራል።

    መገኛ፦ ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት – ጅማ ዞን ጅማ ከአዲስ አበባ ምዕራባዊ – ደቡብ አቅጣጫ ወሊሶን አቋርጦ በሚያልፈው አስፋልት ኮንክሪት መንገድ 360 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ናት።

    መነሻ እና መድረሻ ፕሮጀክቱ የሚጀመረው ጅማ ከተማ ከሚገኘው “ሃኒላንድ ሆቴል” በመነሳት በዋናነት በጅማ ሰሜን – ምዕራብ አቅጣጫ አድርጐ ወደ አጋሮ እና ዴዴሣ ወንዝ ድልድይ ድረስ የሚዘልቅ ነው። ከዚያም ከወንዙ እስከ መቱ ከተማ በሚዘልቀው በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ ተገንብቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሚገኘው መንገድ ጋር ያገናኛል።

    የጅማ – አጋሮ – ዲዴሳ ወንዝ ድልድይ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ኮንትራት እና ውል

    የሥራ ተቋራጭ፦ ቻይና ሬል ዌይ 21ኛ ቢሮ ግሩፕ የተባለ አለም አቀፍ ድርጅት
    አማካሪ ድርጅት፦ ኦሜጋ ኮንሰልቲንግ ኢንጂነሪንግ እና ፕሮሜ ኮንሰልታንትስ በጋራ
    የግንባታ ወጪ፦ ከ1.3 ቢሊዩን ብር በላይ
    የግንባታ ጊዜ፦ 41 ወራት
    የግንባታ ወጪ ሽፋን፦ የኢትዮጵያ መንግስት

    የጅማ – አጋሮ – ዲዴሳ ወንዝ ድልድይ የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክት ሁለንተናዊ ፋይዳ

    ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤
    የተሽከርካሪ የጉዞ ወጪና ጊዜ ይቀንሳል፤
    የምርት እና የሸቀጥ ልውውጥን ያቀላጥፋል፤
    የግብርና ምርቶችን ወደ ገበያ በማውጣት የገበያ ተደራሽነትን ያቀላጥፋል፤
    የከተሞች የእርስ በርስ ትስስር ይፈጥራል፤
    የጤና ፣ የትራንስፖርት እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችን ተደራሽነት ያጠናክራል፤
    የማኅበረሰቡን ኑሮና በኢኮኖሚው ዕድገት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል፤
    ቡናን ጨምሮ በግብርና ምርቶችና በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገውን አካባቢ ተጠቃሚ ያደርጋል።

    ምንጭ፦ ኢ.መ.ባ. | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የጅማ–አጋሮ–ዲዴሳ መንገድ ግንባታ

    Semonegna
    Keymaster

    በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ፋግታ ለኮማ ወረዳ በደረሰ የመኪና አደጋ የ14 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት (አብመድ) እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የዞኑ ፖሊስ መምሪያን በመጥቀስ ዘግበዋል።

    የመምሪያው የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ባለሙያ ዋና ኢንስፔክተር ወርቅነህ ስዩም በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ይህ የመኪና አደጋ የደረሰው ጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓ.ም፣ ከጠዋቱ 3፡00 አካባቢ ሲሆን፥ ቦታው ደግሞ በወረዳው “ሉሊስታ” በተባለ ቀበሌ ነው። ከዳንግላ ወደ ኮሶበር እየሔደ የነበረ 16 ሰው የመጫን አቅም ያለው የህዝብ ማመላለሻ መኪና (የሰሌዳ ቁጥሩ፦ 3-20705-አማ) እና ወደ ባህር ዳር አቅጣጫ እየሄደ ከነበረ የመከላከያ ሠራዊት ከባድ የጭነት መኪና (የሰሌዳ ቁጥሩ፦ መከ-01335) ክፉኛ በመጋጨታቸው የ1 ሰዎች ሕይወት የቀጠፈው አደጋ ሊደርስ ችሏል።

    ዋና ኢንስፔክተር ወርቅነህ በገለጻቸው “የህዝብ ማመላለሻ መኪናው ከዳንግላ ወደ ኮሶበር በመጓዝ ላይ ሳለ በተቃራኒ አቅጣጫ ወደ ባህር ዳር ይመጣ ከነበረው ከባድ የጭነት መኪና ጋር በመጋጨታቸው አደጋው ሊከሰት ችሏል” ሲሉ፥ በተከሰተው አደጋ 14 ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ ሌሎች 12 ሰዎች በጽኑ ቆስለዋል በማለት አክለው ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ አደጋው በደረሰበት ወቅት 15 ሰው ብቻ መጫን የነበረበት የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪው 25 ሰዎችን ጭኖ እንደነበር ዋና ኢንስፔክተር ወርቅነህ አያይዘው ገልጸዋል።

    በፋግታ ለኮማ ወረዳ የትራፊክ ተቆጣጣሪ ሳጅን መልካሙ ልየው ለአብመድ ሕይወታቸው ስላለፈው ሰዎች ሲያብራሩ፥ በአደጋው ሹፌሩን እና ረዳቱን ጨምሮ የ14 ሰዎች ሕይወት አልፏል ብለዋል።

    የቆሰሉት ሰዎች በዳንግላና እንጅባራ ሆስፒታሎች ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሁለት ተጨማሪ ሰዎች ደግሞ በአዲስ ቅዳም ጤና ጣቢያ ሕክምና ተደርጎላቸው ወደ ቤተሰቦቻቸው ተልከዋል።

    የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የስምንት መንገዶች ግንባታ ሥራ የኮንትራቶችን ከተለያዩ ተቋራጮች ጋር ተፈራረመ

    ከሟቾች መካከል ከሕጻን ልጃቸው ጋር ሕይወታቸው ያለፈው አንዲት እናት እንደሚገኙበት ያስታወቁት ኢንስፔክተሩ፣ የ13ቱ ሟቾች አስክሬን ወደቤተሰቦቻቸው የተላከ ሲሆን ለቀሪው የአንዲት ሴት አስከሬን ቤተሰቦቿን የማፈላለግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ዋና ኢንስፔክተር ወርቅነህ ስዩም ጠቁመዋል።

    ዋና ኢንስፔክተሩ እንዳስታወቁት በአሁኑ ወቅት የአደጋው መንስዔ እየተጣራ መሆኑን አመልክተው፣ የከባድ መኪናው አሽከርካሪ አደጋው ከደረሰ በኋላ በመሰወሩ በቁጥጥር ስር ለማዋል በፖሊስ በኩል ክትትል እየተደረገ ሲሆን፤ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድርስ አልተያዘም። በየቀኑ እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ አሽከርካሪዎች የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ህጉን አክብረው ሊያሽከረክሩ እንደሚገባም ኢንስፔክተሩ አሳስበዋል።

    ከዚህ ጋር በተያያዘ ባለፈው ዓመት ሀምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም የሀገሪቱ ትራንስፖርት ባለስልጣን ባወጣው በ2010 ዓ.ም የበጀት ዓመት ብቻ 5,118 ሰዎች በተሽከርካሪ አደጋ ሕይወታቸው እንዳለፈ፣ ይህም ከ2009 ዓ.ም የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር 13.7 በመቶ እንደጨመረ ያስረዳል። የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ባወጣው በዚሁ መግለጫ ላይ በ2010 ዓ.ም የበጀት ዓመት በተሽከርካሪ አደጋ 7,754 ሰዎች ላይ የከባድ፣ 7,775 ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል የመቁሰል አደጋ ደርሷል። በዚሁ የበጀት ዓመት የደረሰው የመኪና አደጋ (የተሽከርካሪ አደጋ) በቁጥር 41,000 ሲሆን ይህም በ2009 ዓ.ም የበጀት ዓመት ከደረሰው የተሽከርካሪ አደጋ ጋር ሲነጻጸር በመቶ እድገት አሳይቷል። ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካሉ ሀገራት በተሽከርካሪ ብዛት ዝቅተኛ ከሚባሉ ሀገራት ብትመደብም በተሽከርካሪ ምክንያት በሰው ላይ በሚደርስ አደጋ ግን አውራ ቦታ ከያዙት ሀገራት ውስጥ ትመደባለች።

    ምንጮች፦ Xinhua፣ አብመድ እና ኢዜአ

    የመኪና አደጋ

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ኢመባ) – የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን (ኢመባ) 600 ኪ.ሜ ርዝመት የሚሸፍኑ የስምንት መንገዶች ግንባታ ሥራ የኮንትራት ስምምነት ከ13.8 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ተቋራጮች ጋር ተፈራረመ።

    የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን አካል የሆኑና 600 ኪ.ሜ ርዝመት የሚሸፍኑ የስምንት መንገዶች የመንገድ ግንባታ ሥራዎች የኮንትራት ስምምነት ከብር 13.8 ቢሊዮን በላይ በሆነ ወጪ ጥቅምት 14 ቀን 2011 ዓ.ም በሒልተን ሆቴል ተፈራርሟል። የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ዝርዝር መረጃ የሚከተለውን ይመስላል።

    1. ጣርማበር–መለያ–ሰፈሜዳ መገንጠያ 1 መለያ–ሞላሌ–መገንጠያ 2 ሞላሌ–ወገሬ መንገድ (ርዝመት 118.87 ኪ.ሜ)

    o የገንዘቡ መጠን፦ 1,906,200,296.75 ብር
    o የግንባታ ጊዜ ሚፈጀው፦ 36 ወራት
    o ኮንትራክተር፦ መከላከያ ኮንስትራክሽን

    2. ጂማ–አጋሮ–ዴዴሳ ወንዝ መንገድ (ርዝመት 79.07 ኪ.ሜ)

    o የገንዘቡ መጠን፦ 1,306,509,305.57 ብር
    o የግንባታ ጊዜ ሚፈጀው፦ 42 ወራት
    o ኮንትራክተር፦ ቻይና ሬል ዌይ 21ኛ ቢሮ ግሩኘ
    o ቀድሞ የነበረው የመንገዱ ደረጃ፦ አስፋልት

    3. መሰል/ሞሲሊ–ኮራ/ቆሪ–84.2 ኪ.ሜ /ኮንት 1/ መንገድ (ርዝመት 84.2 ኪ.ሜ)

    o የገንዘቡ መጠን፦ 1,536,235,563.54 ብር
    o የግንባታ ጊዜ ሚፈጀው፦ 42 ወራት
    o ኮንትራክተር፦ ቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮ. ሊሚትድ

    4. መሰል/ሞሲሊ–ኮራ/ቆሪ–84.2–ጠሩ ኪ.ሜ /ኮንት 2/ መንገድ (ርዝመት 73.34 ኪ.ሜ)

    o የገንዘቡ መጠን፦ 1,502,371,329.85 ብር
    o የግንባታ ጊዜ ሚፈጀው፦ 42 ወራት
    o ኮንትራክተር፦ ቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮ. ሊሚትድ

    5. አርሲ–ሮቤ–አጋርፋ–አሊ ኮንትራት 1 አሊ ከተማ-ዋቤ ድልድይ መንገድ (ርዝመት 53.5 ኪ.ሜ)

    o የገንዘቡ መጠን፦ 2,153,060,671.98 ብር
    o የግንባታ ጊዜ ሚፈጀው፦ 36 ወራት
    o ኮንትራክተር፦ ቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ (ሲሲሲሲ)

    6. አዲአርቃይ–ጠለምት መንገድ (ርዝመት 76.6 ኪ.ሜ)

    o የገንዘቡ መጠን፦ 1,981,378,049.64 ብር
    o የግንባታ ጊዜ ሚፈጀው፦ 36 ወራት
    o ኮንትራክተር፦ የንኮማድ ኮንስትራክሽን

    7. እስቴ–ስማዳ መንገድ (ርዝመት 53.08 ኪ.ሜ)

    o የገንዘቡ መጠን፦ 1,925,451,264.41ብር
    o የግንባታ ጊዜ ሚፈጀው፦ 36 ወራት
    o ኮንትራክተር፦ ቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ (ሲሲሲሲ)

    8. ውቅሮ–አጽቢ–ኮነባ መንገድ (ርዝመት 63 ኪ.ሜ)

    o የገንዘቡ መጠን፦ 1,745,722,493.86 ብር
    o የግንባታ ጊዜ ሚፈጀው፦ 42 ወራት
    o ኮንትራክተር፦ ሱር ኮንስትራክሽን

    የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በመግለጫው እንዳስታወቀው መንገዶቹ ከዚህ በፊት በጠጠር ደረጃ የነበሩ ሲሆን አሁን ግን በአስፋልት ደረጃ የሚገነቡ ይሆናሉ። ለነዚህም ግንባታ ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ይሆናል።

    የመንገዶቹ ግንባታ በሚጠናቀቅበት ወቅት እንደ ጤፍ፣ ማር እና ፍየል እንዲሁም ሌሎች የግብርና ምርቶችንም ሆነ ሌሎች ምርቶችን ካለምንም ችግር ወደ ገበያ ለማውጣት ያስችላሉ። በተጨማሪም ከዚህ በፊት በአካባቢው የነበረውን የተቀላጠፈ የትራንስፖርት ችግር በመቅረፍ የአካባቢው ህብረተሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ ወደ ፈለገው ቦታ የሚንቀሳቀስበትን ሁኔታ ያመቻቻሉ።

    እነዚህ መንገዶች በአገሪቱ ካለው ማ ኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲሁም መንግሥት ከያዘው የድህነትና የኋላቀርነት ቅነሳ ስትራቴጂ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክቱ ይታመናል። የመንገዶቹ ግንባታ በሚጠናቀቅበት ወቅት ከዚህ በፊት በአካባቢው የነበረውን የትራንስፖርት ችግር በመቅረፍ የአካባቢው ህብረተሰብ በቀላሉ ወደ ፈለገው ቦታ የሚንቀሳቀስበትን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር ፣ በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች ያመረቱትን ምርት ወደ ገበያ ለማውጣት እንዲችሉና ሌሎች ባለሃብቶችም በአካባቢው ኢንቨስት ለማድረግ ተነሳሽነትን ከመፍጠር አኳያ የዚህ መንገድ መገንባት ጉልህ ሚና ይጫወታል።

    ከዚህም በተጨማሪ በአካባቢው የስራ ዕድል እንዲፈጠር በማስቻል ፣ በአካባቢው የሚገኙ ትንንሽ መንደሮች በከተማ ደረጃ እንዲስፋፉና እንዲያድጉ ከማድረግ እንዲሁም የጤና ፣ የትምህርት እና ሌሎች የማህበራዊ አገልግሎት ተቋማት በሰፊው እንዲስፋፉ ከማድረግ አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ ተብሎ ይታመናል። ስለሆነም የመንገድ ኘሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ በአካባቢው የሚገኙ የመስተዳድር አካላትና፣ የክልሉ ነዋሪዎች ከፍተኛ ትብብር እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ያሳስባል።

    የኮንትራት ስምምነቱን የፈረሙት በኢመባ በኩል አቶ ሃብታሙ ተገኝ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሲሆኑ በተቋራጮቹ የሥራ ተቋራጮቹ ሥራ አስኪያጆች እና ተወካዮቻቸው ናቸው።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን (ኢመባ)

    የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን

Viewing 9 results - 1 through 9 (of 9 total)