Search Results for 'የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን'

Home Forums Search Search Results for 'የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን'

Viewing 7 results - 1 through 7 (of 7 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    የሽሮ ሜዳ – ቁስቋም የአስፋልት መንገድ ግንባታ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል
    የመንገድ ፕሮጀክቱ ፊዚካል አፈፃፀም ከ85 በመቶ በላይ ደርሷል

    አዲስ አበባ (አአከመባ) – የሽሮ ሜዳ – ቁስቋም የአስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት እንደሚደረግ  የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን (አአከመባ) አስታወቀ።

    የሽሮ ሜዳ – ቁስቋም መንገድ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ገብረ እግዚአብሔር ሐጎስ እንደገለፁት፥ የመንገድ ፕሮጀክቱ የቀኝ መስመር ግንባታ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት መደረጉን ገልፀው፤ አሁን ላይ የፊዚካል አፈፃፀሙ (physical construction) ከ85 በመቶ በላይ በመድረሱ የግንባታ ሥራው የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ጠቁመዋል።

    በሌላ በኩል በመንገድ ፕሮጀክቱ የግራ መስመር ላይ 910 ሜትር የአስፋልት ንጣፍ የተከናወነ ሲሆን፤ 600 ሜትር የሚሆነው ቀሪው የግንባታ ክፍል ላይ ደግሞ የአፈር ቆረጣ፣ የቤዝ ኮርስ እና የድጋፍ ግንብ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

    ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ በቀጣይ አጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት እንደሚሆን ኢንጂነር ገብረ እግዚአብሔር ጨምረው ተናግረዋል።

    የሽሮ ሜዳ – ቁስቋም መንገድ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ክፍል 1.4 ኪ.ሜ ርዝመትና የእግረኛ መንገድን ጨምሮ 30 ሜትር የጐን ስፋት አለው። የመንገድ ፕሮጀክቱን በ160.9 ሚሊዮን ብር ወጪ ዮቴክ ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግ/ማ እየገነባው ሲሆን፤ የማማከርና የቁጥጥር ሥራው ደግሞ ቤስት ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ ኃ/የተ/የግ/ማ እያከናወነው ይገኛል።

    በተመሳሳይ ከ600 ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ሁለተኛው ክፍል በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የራስ ኃይል ተከናውኖ ለትራፊክ ክፍት የተደረገ ሲሆን፤ ለግንባታ ወጪውም ከ53.3 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦለታል። አሁን ላይ ያልተጠናቀቁ የእግረኛና የማስተካከያ ሥራዎችም እየተከናወኑ ይገኛሉ።

    ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ አጠቃላይ የመንገድ ግንባታ ሥራውን ከተያዘለት ጊዜ ቀደም ብሎ እንዲጠናቀቅና የወሰን ማስከበር ሥራዎችን እና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሲሠራ ቆይቷል።

    የመንገዱ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ለአካባቢው ነዋሪዎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ፋይዳ ከመስጠቱም ባሻገር ወደ እንጦጦ ፖርክ እና አካባቢው ለሚንቀሳቀሱ የከተማዋ ነዋሪዎችና ቱሪስቶች ምቹና የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበርክታል ተብሎ ይጠበቃል።

    አዲስ አበባ ከተማን የተመለከቱ ሰሞነኛ ዜናዎችና መረጃዎች

    ምንጭ፦ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን

    የሽሮ ሜዳ – ቁስቋም የአስፋልት መንገድ ግንባታ

    Anonymous
    Inactive

    የአዲስ አበባ የወጪና ገቢ ንግድ ማሳለጫ ኮሪደር የሆነው የቃሊቲ አደባባይ – ቱሉ ዲምቱ አደባባይ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ገፅታዎች

    አዲስ አበባ (አአመባ) – የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን (አአመባ) በሥራ ተቋራጮች ከሚያስገነባቸው ግዙፍ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው የቃሊቲ አደባባይ – ቱሉ ዲምቱ አደባባይ የመንገድ ፕሮጀክት የትራፊክ ፍሰቱን ሊያሳልጡ የሚችሉ በርካታ ገፅታዎች አሉት።

    የመንገድ ፕሮጀክቱ 11 ኪ.ሜ ርዝመትና 50 ሜትር የጎን ስፋት አለው። በመንገዱ ግራና ቀኝ መስመሮች ላይ በአንድ ጊዜ ብቻ 8 መኪናዎችን በቀላሉ ማሳለፍ የሚያስችል ነው። የመንገዱ ዋና ዋና መገጣጠሚያዎችና ማሳለጫዎች ላይ ደግሞ ከ70 እስከ 100 ሜትር የሚደርስ የጎን ስፋት ይኖረዋል።

    ከመኪና መስመር ባሻገር በግራና በቀኝ 6.5 ሜትር ስፋት ያለው የሳይክል መስመር፣ እግረኛ በሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ 9 ሜትር ድረስ ስፋት ያላቸው የእግረኛ መንገዶች፣ በመንገዱ መሀል ላይ 11 ሜትር ስፋት ያለው ለብዙሃን ትራንስፖርት ብቻ የሚያገለግል መስመር እንዲሁም በመንገዱ ግራና ቀኝ ላይ 32 የሚሆኑ የአውቶቡስ ማቆሚያዎች ይኖሩታል። እነዚህ የአውቶቡስ ማቆሚያዎች ከ40 እስከ 60 ሜትር ርዝመትና ከ3 እስከ 7 ሜትር የጎን ስፋት ይኖራቸዋል።

    የቃሊቲ አደባባይ – ቱሉ ዲምቱ አደባባይ የመንገድ ፕሮጀክት ሌላው ገፅታ ደግሞ ሦስት ዋና ዋና ማሳለጫዎች ያሉት ሲሆን የመጀመሪያው የፕሮጀክቱ መነሻ የሆነው የቃሊቲ አደባባይ ነው። ይህ ማሳለጫ በመሀላቸው ዘጠኝ ሜትር ስፋት ያላቸው 8 ስፓን እና 240 ሜትር ርዝመት ያላቸው ሁለት ድልድዮችን የያዘ ነው።

    ሁለተኛው ማሳለጫ ጥሩነሽ ቤጂንግ ማሳለጫ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፥ 100 ሜትር ርዝመት የሚጠጋ ድልድይ አለው። ይህ ማሳለጫ ወደ አቃቂ ከተማ፣ ወደ ሄኒከን ቢራ (Heineken Ethiopia)፣ ወደ ደራርቱ ት/ቤት፣ ወደ ቱሉ ድምቱ አደባባይ እና ወደ ቃሊቲ አደባባይ በድምሩ አምስት ዋና ዋና የመንገድ መጋጠሚያዎችን ለማሳለጥ የሚያገለግል ነው።

    ሦስተኛውና የመጨረሻው ማሳለጫ ቀድሞ ጋሪ ድልድይ እየተባለ የሚጠራው ሲሆን፥ በ50 ሜትር ርዝመትና በ20 ሜትር የጎን ስፋት እየተሠራ ይገኛል።

    አጠቃላይ የቃሊቲ አደባባይ – ቱሉ ዲምቱ አደባባይ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱን የቻይናው ኮሚኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ በ2 .4 ቢሊዮን ብር በጀት እያከናወነው ሲሆን፥ እስካሁን ድረስም 65 በመቶ ገደማ አፈፃፀም አስመዝግቧል። የመንገዱ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ በመንገዱ በግራ መስመር 800 ሚሊ ሜትር ውፍረት ያለው ግዙፍ የውሀ መስመርና የመብራት ፖሎች ባለመነሳታቸው እንቅፋት ፈጥረውበታል። ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት እነዚህን የወሰን ማስከበር ችግሮች ለመፍታት ከመብራት ኃይል፣ ከከተማዋ ውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን እንዲሁም ከሚመለከታቸው የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በቅርበት እየሠራ ችግሩን በመፍታት ላይ ይገኛል።

    የቃሊቲ አደባባይ – ቱሉ ዲምቱ አደባባይ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታው ሲጠናቀቅ በሀገሪቱ በምሥራቅ አቅጣጫ በኩል የሚደረገውን የወጪና ገቢ ንግድ ለማሳለጥ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል። ከዚህም በተጨማሪ የመዲናዋን ነዋሪዎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከማሻሻሉም ባሻገር የከተማዋን ገፅታ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀይራል ተብሎ ይጠበቃል።

    ምንጭ፦ አአመባ

    የቃሊቲ አደባባይ – ቱሉ ዲምቱ አደባባይ የመንገድ ፕሮጀክት

    Anonymous
    Inactive

    ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ በ3 ቢሊዮን ብር ለሚያስገነባው ገርጂ የመኖሪያ መንደር ከተቋራጮች ጋር ስምምነት ተፈራረመ

    አዲስ አበባ (ኢብኮ)፦ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ገርጂ አካባቢ በሶስት ቢሊዮን ብር ለሚያስገነባው ዘመናዊ መንደር (ገርጂ የመኖሪያ መንደር ፕሮጀክት/ Gerji Village Project) ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ተቋራጮች ጋር ነሐሴ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ስምምነት ፈፅሟል። ኮርፖሬሽኑ ስምምነቱም ያደረገው ከኮሪያ፣ ከህንድ እና ከኢትዮጵያዊያን የህንጻ ተቋራጮች መሆኑን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) ዘግቧል።

    ገርጂ የመኖሪያ መንደር ፕሮጀክትን ይፋ ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስተሩ የካቢኔ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የቦርድ ኃላፊ ወ/ሮ ደሚቱ ሐምቢሳ ናቸው።

    በስምምነቱ መሠረት ገርጂ የመኖሪያ መንደር ውስጥ በሚቀጥሉት 18 ወራት ውስጥ 510 መኖሪያ ቤቶች ይገነባሉ። የሚገነቡት መኖሪያ ቤቶች ባለ 10 ወለል የሚኖራቸው 16 ህንጻዎች መሆናቸው ተገልጿል።

    ገርጂ የመኖሪያ መንደር ሲጠናቀቅ በከተማዋ የሚታዩ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግርን በተወሰነ መልኩ የሚያቃልል መሆኑን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ረሻድ ከማል ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት ገልጸዋል።

    ግንባታው በዘመናዊ መንገድ የሚገነባ በመሆኑ የግንባታ ወጪውንም ሆነ ጊዜውን የሚያቀላጥፍ መሆኑ ተመክቷል፤ አንድ የህንጻ ወለልን በአምስት ቀናት ውስጥ ሠርቶ የሚያጠናቅቅ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ይውላል ተብሏል።

    አዲአ አበባ ውስጥ ሲ.ኤም.ሲ ከሚገኘው የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የመኖሪያ መንደር ልምድ ተወስዶ፥ በሦስት ሔክታር ላይ የሚገነባው የገርጂ የመኖሪያ መንደር ሲጠናቀቅ ዘመናዊነትን የተላበሰ የመኖሪያ መንደር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። የመኖሪያ መንደሩ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ለመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ይውሏል ተብሏል።

    የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከ28 ዓመት በኋላ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ወደ ቤቶች ግንባታ ራሱን በመመለስ፣ በተለያዩ ስምንት የግንባታ ቦታዎች ቤቶችን እየገነባ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ረሻድ ከማል በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተናግረዋል። ኮርፖሬሽኑ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ገቢውን እያሳደገ ሰፊ የቤት አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ ይሠራልም ብለዋል አቶ ረሻድ።

    ምንጭ፦ ኢብኮ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ሌሎች ዜናዎች

    ገርጂ የመኖሪያ መንደር

    Semonegna
    Keymaster

    የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በ2012 በጀት ዓመት 715 ኪ.ሜ. የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎችን ማከናወኑን አስታወቀ

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – በ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት 715 ኪ.ሜ. የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎችን ማከናወኑን፣ 21 የመንገድ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቁንና አዳዲስና ግዙፍ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ማስጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።

    ባለስልጣኑ ለአዲስ አድማስ ዕለታዊ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ በበጀት ዓመቱ 706 ኪ.ሜ. የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎችን ለማከናወን አቅዶ 715 ኪ.ሜ. በማከናወን ከዕቅድ በላይ አፈፃፀም አስመዝግቧል። በዚሁ በጀት ዓመት ከተሠራው አጠቃላይ የመንገድ ሥራ ውስጥ 167 ኪ.ሜ. አዳዲስ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 544 ኪ.ሜ. ልዩ ልዩ የመንገድ ጥገና ሥራዎች ናቸው።

    ባለስልጣኑ በግንባታ ላይ ከነበሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል 21 የሚሆኑትን በማጠናቀቅ አስመርቆ ለትራፊክ ክፍት ያደረገበት በጀት ዓመትም መሆኑን ጠቅሶ፥ በሁለት ዙር በይፋ የተመረቁት የመንገድ ግንባታዎች በድምሩ ከ33 ኪ.ሜ. በላይ ርዝመት እና የእግረኛ መንገድን ጨምሮ ከ10 እስከ 30 ሜትር የጎን ስፋት ያላቸውና ለግንባታቸውም ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሆነባቸው መሆኑን አመልክቷል።

    በ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት በዓይነታቸው ለሀገሪቱም ሆነ ለመዲናዋ አዲስና ግዙፍ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ማስጀመሩንም የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አስታውሶ፥ ከእነዚህም መካከል የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስፋፋት የተጀመረው የዊንጌት–ጀሞ ሁለት የፈጣን አውቶቡስ መንገድ እና የፑሽኪን አደባባይ–ጎተራ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች እንደሚገኙበት ገልጿል።

    በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግባቸው እና ከ90 ኪ.ሜ. በላይ ርዝመት ያላቸው 22 የመንገድ ፕሮጀክቶች መጀመራቸውንም ባለስልጣኑ ጠቅሷል። በ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት የተጀመሩት እነዚህ ታላላቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች በሁለት ዓመት ውስጥ ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሠራ እንደሚገኝም ባለስልጣኑ ጠቁሟል።

    በበጀት ዓመቱ በመንገድ መሠረተ ልማት ሀብቶች ላይ በርካታ ጉዳቶች መድረሳቸውንም አያይዞ የጠቀሰው ባለስልጣኑ፥ በ12 ወራት ውስጥ በተሽከርካሪ ግጭት ብቻ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት በመንገድ መሠረተ ልማት ሀብቶች ላይ መድረሱንና ይህም በመንገድ መሠረተ ልማት ሀብቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን እንደሚያሳይ አመልክቷል።

    በተሽከርካሪ ግጭት በብዛት ጉዳት ከደረሰባቸው የመንገድ ሀብቶች መካከል የመንገድ ዳር መብራት ምሰሶዎች፣ የትራፊክ ምልክቶች፣ የአቅጣጫና ርቀት አመላካች ሰሌዳዎች፣ የእግረኛ መከላከያ አጥሮች፣ የመንገድ ማካፈያ ግንቦች፣ ውሃ መውረጃ ቱቦዎችና ክዳኖች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ዘርዝሯል።

    የወሰን ማስከበር ችግር፣ የተቋራጮች አቅም ውስንነት፣ የገልባጭ መኪና እና ግብዓት እጥረትና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራ ወቅት የገጠሙ ዋነኛ ፈተናዎች እንደነበሩም ባለስልጣኑ አስታውሶ፥ ችግሮቹን በመፍታት በአፈፃፀም ላይ ሊያሳድሩ የነበረውን ተፅዕኖ መቀነስ መቻሉን አስታወቋል። በበጀት ዓመቱ ለመንገድ ፕሮጀክቶች እና ለመደበኛ ሥራዎች አስከአሁን ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም ባለስልጣኑ ጠቅሷል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

    የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን

    Semonegna
    Keymaster

    ከክረምቱ ወቅት መግባት ጋር ተያይዞ መንገዶች ላይ የሚደረጉ ማንኛውም ቁፋሮዎች እንደማይከናወኑ
    የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን (አአመባ) አስታወቀ

    አዲስ አበባ (አአመባ) – የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን (አአመባ) የክረምት መግባት ጋር በተያያዘ በመንገድ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚካሄዱ የቁፋሮ ሥራዎችን ከግንቦት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ማስቆሙን ገልፆ፥ ለተግባራዊነቱም የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።

    የክረምት ወራት መግባትን ተከትሎ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ከመሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማትና ግለሰቦች ለተለያዩ የልማት ሥራዎች የሚቀርቡለትን የመንገድ መሠረተ ልማት ቁፋሮ ፈቃድ ማቆሙ ይታወቃል።

    ከመንገድ መሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ የቁፋሮ ፈቃድ ይሰጥባቸው ከነበሩት ውስጥ የመጠጥ ውሃ ዝርጋታ፣ የዝናብ ውሃ ከቆሻሻ ፍሳሽ ማስወገጃ መስመር (drainage system) ጋር ይገናኝልኝ ጥያቄ፣ የፍሳሽ መስመር ለማገናኘት፣ የመግቢያ መውጫ ይከፈትልንና ከመሠረተ ልማት ዘርጊ ተቋማት የሚቀርቡ የመንገድ መቁረጥ ፈቃድ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

    የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በክረምት የሚደረጉ ቁፋሮዎች በነዋሪው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ እክል እንዳይፈጥሩ፣ ከአደጋ ለመጠበቅና የትራፊክ ፍሰት እንዳይስተጓጎል የቁፋሮና የአስፋልት መቁረጥ ፍቃድ መስጠት እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ማቆሙን አስታውቋል።

    ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት በቁጥር 443 የሚሆኑ ከተለያዩ አካላት የቀረቡለትን የመንገድ መቁረጥ ጥያቄ ፍቃድ ሰጥቷል። በተጨማሪም የመንገድ ሃብት ላይ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን በመፈጸም ጉዳት የሚያደርሱ አካላት ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የመንገድ መብት ጥሰቶችና ጉዳቶች ለመከላከል የሚያስችል አሠራርን በመዘርጋት እንቅስቃሴ እያደረግ ይገኛል።

    በመንገድ ሀብት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቅረፍና መንገዶችን ለመንከባከብ ባለስልጣኑ ከመሠረተ ልማት ቅንጅት ግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር እና ከመሠረተ ልማት ዘርጊ ተቋማትና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተናቦ በመሥራት ከፍተኛ የሕዝብ ሀብት ፈሶባቸው የተገነቡ መንገዶችን ከሚደርስባቸው የተለያዩ የመንገድ መብት ጥሰቶችና ጉዳቶች ለመከላከል ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ይህም የመንገድ መሠረተ ልማቶች በሚፈለገው መጠን ከጉዳት ተጠብቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ከማስቻሉም ባለፈ የመንገዶችን የጥገና ወጪ በመቀነስ የጎላ አስተዋፅኦ አድርጓል።

    በመጨረሻም ሕብረተሰቡ የተገነቡ እና በግንባታ ላይ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ከመንገድ መብት ጥሰቶችና ከሚፈፀሙ ሕገ-ወጥ ተግባራት በመከላከልና በመጠበቅ ከባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በጋራ እንዲሠሩ ጥሪውን ያስተላልፋል።

    ከዚሁ ዜና ጋር በተያያዘ፥ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት ከ375.2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የግንባታ ግብዓቶችን አምርቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረጉንአስታውቋል።

    ባለስልጣኑ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ በ134.9 ሚሊዮን የካባ፣ በ73.7 ሚሊዮን ብር ሲሚንቶ፣ በ166.6 ሚሊዮን ብር የሚገመት የአስፋልት ምርቶችን አምርቶ ለተለያዩ የግንባታ ሥራዎች ያሰራጨ ሲሆን፥ አጠቃላይም የዕቅዱን 89 በመቶ አፈፃፀም አስመዝግቧል።

    በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በራስ አቅም ተመርተው ሥራ ላይ ከሚውሉ የተለያዩ ምርቶች መካከል፥ ገረገንቲ፣ ቤዝ ኮርስ (base course)፣ ሰብቤዝ (subbase)፣ ጠጠር፣ ነጭ ድንጋይ፣ የተለያዩ መጠን ያላቸው ቱቦዎች፣ ሲሚንቶ ኮንክሪት፣ ከርብስቶን (curbstone)፣ የማንሆል ክዳን (manhole cover)፣ ፍርግርግ፣ ቦላርድ (bollard)፣ ታይልስ (tiles)፣ ባይንደር ሚክስ (binder mix)፣ ሰርፊስ ሚክስ (surface mix) የመሳሰሉት ይገኙበታል።

    ባለስልጣኑ የግንባታ ግብዓቶችን በራሱ አቅም ማምረት መቻሉ በራሱ አቅም እየገነባቸው ለሚገኙ የግንባታና የጥገና ሥራዎች የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በቀጣይም የግብዓት ምርቶች እጥረት እንዳይፈጠርም አሁን ላይ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ ሥራዎችን ሊሰሩ የሚችሉ በርካታ ማሽነሪዎችን በመግዛት በትጋት እየሠራ ይገኛል።

    ምንጭ፦ አአመባ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን

    Semonegna
    Keymaster

    የመንገዶች የመብራት አገልግሎት አለመስጠት ምክንያቱ ኃይል ያልተለቀቀላቸው በመኖራቸው፣ መሠረተ ልማቶች ስለሚዘረፉ፣ የምሰሶና የአምፖል ማርጀት እንደሆነ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ጠቅሷል።

    አዲስ አበባ (ኢዜአ)–በአዲስ አበባ ከተማ ካሉት መንገዶች ውስጥ የመብራት አገልግሎት እያገኙ ያሉት ከ40 በመቶ እንደማይበልጥ ያስታወቀው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን እስከሚቀጥለው ዓመት ዘጠና በመቶ የከተማዋ መንገዶች መብራት እንዲኖራቸው ከአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢሮ ጋር እየሠራሁ ነው ብሏል።

    የመንገዶች የመብራት አገልግሎት አለመስጠት ምክንያቱ ኃይል ያልተለቀቀላቸው በመኖራቸው፣ መሠረተ ልማቶች ስለሚዘረፉ፣ የምሰሶና የአምፖል ማርጀት እንደሆነ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ጠቅሷል።

    የመብራት ምሰሶዎች በየመንገዱ ቢተከልም ከሁለት ዓመት ወዲህ አብዛኛዎቹ አገልገሎት እንደማይሰጡ የጠቀሱት የአፍንጮ በር ነዋሪ አወል አማን፥ በምሽት ወደ መስጊድ ሲሄዱና ከሥራ አምሽቶ ወደ ቤት ለመግባት ስጋት ፈጥሮብናል ብለዋል። አክለውም ምሰሶዎችና አምፖሎች ተሰባብረው እንደሚገኙ ያነሱት ነዋሪው አገልግሎት የማይሰጡ መብራቶች እንዲጠገኑ ጠይቀዋል።

    የጉለሌ አካባቢ ነዋሪ አቶ ፀጋዬ መኩሪያ መኪና አሽከርካሪ ሲሆኑ፥ መንገዶች የምሽት መብራት ከሌላቸው ለአሽከርካሪዎች ፈታኝ በመሆኑ የትራፊክ አደጋ ይከሰታል ብለዋል። አቶ ጸጋዬ እንደሚሉት ጉለሌ አካባቢ በርካታ መኪናዎችና እግረኞች የሚተላለፉበት ቢሆንም የምሽት መብራት የላቸውም፤ ብዙዎችም አደጋ እየደረሰባቸው ነው።

    ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስም ሆነ አሮጌ መኪናዎች ከሚገባው በላይ ውድ የሆኑበት ምክንያት ምንድን ነ?

    የላዳ ታክሲ አሽከርካሪ ማቲዮስ ታምር ሥራው በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች እንዲዘዋወር ስለሚያደርገው በርካታ መንገዶችን እንዳየና መብራት እንደሌላቸው ተናግሯል። ውስጥ ለውስጥና በዋና መንገዶች መብራት በብዛት አለመኖሩ መሪን ያለ አግባብ የመጠቀም ዕድል ስለሚኖር የመጋጨት አጋጣሚውም ሰፊ ነው ብሏል።

    ከስድስት ኪሎ ሽሮ ሜዳ፣ ከሰሜን ማዘጋጃ እንጦጦ፣ ከእንቁላል ፋብሪካ ዊንጌት ባሉ መንገዶች እንደሚሰሩ የገለፁት በአዲስ አበባ የጉለሌ ክፍለ ከተማ የትራፊክ ቁጥጥር አባል ምክትል ኢንስፔክተር አያሌው በለጠ ከነዚህ መንገዶችም አብዛኛዎቹ መብራት የላቸው ብለዋል።

    መዲናዋ በተሽከርካሪዎችና በእግረኞች የተጨናነቀች በመሆኗ በጨለማ ወቅት መብራት አለመኖሩ የትራፊክ አደጋን አባብሷል ነው ያሉት ምክትል ኢንስፔክተሩ።

    መብራት ከሌለ አሽከርካሪዎች ረጅም መብራት የመጠቀም ዕድላቸው ሰፊ ነው ያሉት ረዳት ኢንስፔክተር መራጭ ድንጌቻ፤ ከፊት ለፊት የሚመጡ መኪናዎችን እይታ ሙሉ ለሙሉ በመሸፈን ለአደጋ ያጋልጣል ብለዋል።

    “ከእንቁላል ፋብርካ እስከ ዊንጌት ብዙ ሆስፒታሎች ስላሉ ህሙማንን የያዙ ተሽከርካሪዎች ቀንና ሌሊት ይመላለሳሉ፤ ባለፈው ዓመት በዚያ መንገድ በርካታ ሰዎች ተገጭተዋል” ነው ያሉት።

    ምክትል ኢንስፔክተር አያሌው “ከዚህ ቀደም በአዲሱ ገበያ ዊንጌት በሚወስደው መንገድ አንዲት ሴት ተገጭታ መብራት ባለመኖሩ ምክንያት ሌሊቱን ሙሉ መኪና ሲመላለስባት አድሮ የገላዋ ዱቄት ነው የተነሳው” ሲሉ ያጋጠማቸውን አሳዛኝ ክስተት ነግረውናል።

    በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ መብራት ክትትል ባለሙያ ኢንጅነር ደረጀ ኃይሉ የከተማዋ መንገዶች አንዳንዶቹ የመብራት አገልግሎት እንደሌላቸው ገልጸው “ከጉርድ ሾላ ኦቨር ፓስ፣ መገናኛ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ከስድስት ወር በፊት ተጠይቆ የዋጋ ግምት አልተመለሰልንም” ነው ያሉት።

    የቦሌ አራብሳ መንገድ ከሁለት ዓመት በፊት ለአገልገሎት ክፍት ሆኖ የመብራት ምሰሶ ቢተከልም መብራት እንዳልተለቀቀ የገለጹት ኢንጅነር ደረጀ ከስድስት ኪሎ ፈረንሳይ ጉራራ ኪዳነምኅረት የምሰሶ ተከላና የገመድ ዝርጋታ የማሟላት ሥራ ተከናውኖ የኃይል ዋጋ ግምት እንዲላክለት ከአንድ ወር ወዲህ መጠየቁን ተናግረዋል።

    በባለስልጣኑ የድንገተኛና አንሰለሪ ጉዳዮች ቡድን መሪ አቶ ዘውዱ ባይህ በበኩላቸው መብራት ተቋርጦባቸው የነበሩ 37 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የቀለበት መንገዶች ባለፈው ዓመት ተጠግነው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

    ጨለማን ተገን አድርገው ዝርፊያ የሚፈጽሙ አካላት የመብራት ቁሳቁሶችን ከአገልግሎት ውጪ እያደረጉና እየዘረፉ መሆኑን የተናገሩት አቶ ዘውዱ ከዮሴፍ-ቦሌ ሚካኤል፣ ከአየር መንገድ አደባባይ-ኢምፔሪያል፣ ሸጎሌ ከጎጃም በር-እስከ ዊንጌት እንዲሁም 18 ማዞሪያ፣ ከ3 ቁጥር ማዞሪያ-አለርት ቁሳቁሶቹ በየጊዜው እየጠፉ ተቸግረናል በማለት አስረድተዋል።

    የተበላሹትን ወደ አገልገሎት ለመመለስ በራስ ኃይልና በጨረታ እየተጠገኑ መሆኑን ያነሱት ቡድን መሪው አሮጌ መብራቶችን ደረጃቸውን የጠበቁ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

    በከተማዋ መንገዶች ከ40 በመቶ የማይበልጡ የመብራት አገልግሎት ያላቸው ሲሆን ባለሥልጣኑ 25 ሚሊዮን ብር በመመደብ ጥገና እየሠራ ነው፤ በዚህ በጀት ዓመትም ሽፋኑን 90 በመቶ ለማድረስ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

    የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ክፍሌ በበኩላቸው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ባለው ውል መሠረት ቆጣሪና ትራንስፎርመር እየገጠምን ነው ብለዋል።

    ሆኖም የሲቪል ሥራዎች በመንገዶች ባለስልጣን በኩል ባለመጠናቀቃቸውና የመንገድ ርክክብ ባለማድረጋቸው ምክንያት መብራት የማያገኙ መንገዶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

    “የካ አባዶ አንድ መንገድ፣ ከስድስት ኪሎ ፈረንሳይ ጉራራ መንገድ ተገምቷል፣ ቦሌ አራብሳ እየተገመተ ነው፣ ጎሮ ቱሉ ዲምቱ ትራንስፎርመርና ቆጣሪ ተገጥሟል፣ ከሲኤምሲ አደባባይ እስከ ካራ ትራንስፎርመርና ቆጣሪ ቢገጠምም መንገዱን ርክክብ አላደረጉም፣ ከዊንጌት አደባባይ እስከራስ ደስታ ሆስፒታል ላለው መንገዶች ባለስልጣን ግምት አላመጣም፣ ዓለም ባንክ ቤቴል አየር ጤና ፍርድ ቤት ያሉት ያልተጠናቀቁ የሲቪል ሥራዎች ሲጠናቀቁ ኃይል ይለቀቅላቸዋል” ብለዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን

    Semonegna
    Keymaster

    የዘንድሮው የፀረ-ሙስና ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ለ14 ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ የተከበረ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበርያ ጽህፈት ቤት ዘግቧል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በአዲስ አበባ ከተማ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ እና በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ትብብር የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ዓመታዊ የፀረ-ሙስና ቀን “ሁለንተናዊ ሰላማችንና እድገታችንን ለማረጋገጥ በሙስና ላይ በጋራ እንዝመት፤ ጊዜው የተግባር ነው” በሚል መሪ-ቃል በፓናል ውይይት እሁድ ኅዳር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ተከብሮ ውሏል።

    በዕለቱም የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታከለ ሉሊና ሙስና ተሸሞንሙኖ የሚጠራ ሳይሆን ሌብነት እንደሆነ ሁሉም ዜጎች ተገንዝበው መታገል እና ሙስና በዓይነቱም የተለያየ እንደሆነ በመግለፅ ሁላችንም ተረባርበን መከላከል አለብን ብለዋል።

    አቶ ታከለ አያይዘውም ከትንሽ ከህዝብና መንግስት ሰዓትና ንብረት ጀምሮ ትኩረት በመስጠት ያለአግባብ እናዳይባክኑ በቀጣይነትም ልንሠራ ይገባል፤ ለዚህም ሁላችንም የበኩላችንን ሚና መወጣት አለብን ብለዋል።

    በዓሉን አስመልክቶ በተዘጋው የፓናል መወያያ መነሻ ሃሳብ ላይም የኢፌዲሪ ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የአዲስ አበባ ማስተባበሪ ቅርንጫፍ የሕግ ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ከፋለ እንደተናሩት በርካታ የሙስና መገለጫዎች አሉ እነዚህንም እንደየዓይነታቸው ነጣጥለን መከላከል ያስፈልጋል፤ ህብረተሰቡም ሊያግዝ ይገባል በጉዳዩም ላይ ባለቤት ነኝ ይመለከተኛል ማለት ይገባል ብለዋል።

    ሙስና በአሠራር፣ በአስተሳሰብ፣ በአመለካከት፣ በጥቅም ትስስር፣ በዝምድናና በመሳሰሉት የሚፈፀም በረቀቀና ሚስጢራዊ በሆነ መንገድ የሚከወን በመሆኑ የኮሚሽኑን ስራም በተገቢው እንዳይወጣ ሲያደርግ እንደነበርም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

    የአዲስ አበባ ከተማ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ችግሯን ለመፍታት አማራጮች እየተፈለጉ ነው

    አክለውም ሙስና ለአገር ዕድገት ፀር፣ ለዲሞክራሲ ጋንግሪን እንደሆነ በማስታወስ ለአንዲት አገር ህዝብ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ውድቀት የሚያስከትል በመሆኑ ሁሉም ዜጋ እንደሚመለከተው በማብራራት ይህን ለመከላከል ሁሉም ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል።

    በመጨረሻም እንደአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ያለው የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ በመሆኑና ብዙውን ጊዜ ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚታዩ የሙስና ወንጀሎችን ለመቀነስ በትኩረት መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

    የዘንድሮው የፀረ-ሙስና ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ለ14 ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ የተከበረ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበርያ ጽህፈት ቤት (TPMO) ዘግቧል።

    የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሙስናን ለመዋጋት የተደረገው ስምምነት (United Nations Convention Against Corruption) እ.ኤ.አ ጥቅምት 31 ቀን 2003 ቀን መጽደቁን ተከትሎ በየዓመቱ ኅዳር 30 ቀን  “የፀረ-ሙስና ቀን” ሆኖ እንዲከበር ተወስኗል።

    ምንጭ፦ TPMO | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የፀረ-ሙስና ቀን

Viewing 7 results - 1 through 7 (of 7 total)