-
Search Results
-
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) የአማራ ክልል የልማትና ኢንቨስትመንት ድርጅት በሆነው ጥረት ኮርፖሬት ላይ ከደረሰ የሀብት ብክነት ወንጀል ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአማራ ክልላዊ መንግስት ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።
የአማራ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ዝግአለ ገበየሁ አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ (“ተጠርጣሪዎች”) በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ባህር ዳር መወሰዳቸውን ለመገናኛ ብዙኃንና ለጋዜጠኞች አስታውቀዋል። እንደ አቶ ዝግአለ ገለጻ፥ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ከፍተኛ በሆነ የሀብት ብክነት ምክንያት ጥረት ኮርፖሬትን ለኪሳራ ዳርገዋል፤ ይህም በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ምክንያት እንደሆነና የተጠረጠሩበት ወንጀል የተፈፀመው በክልሉ በመሆኑ ጉዳያቸው በክልሉ ፍርድ ቤት የሚታይ ይሆናል።
የክልሉ ፀረ ሙስና ኮሚሽን በእስካሁኑ የመረጃና ማስረጃ ማሰባሰብ ሂደት በሁለቱ ግለሰቦች ላይ ተገቢውን ክስ ለመመሥረት የሚያስችለውን በቂ መረጃ/ማስረጃ መሰበሰቡንም አስታውቋል።
◌ አባይ የህትመትና የወረቀት ፓኬጂን ፋብሪካ ባህር ዳር ከተማ ውስጥ ሥራ ጀመረ
አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕድን)እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መሥራቾች ከመሆናቸው በተጨማሪ በፌደራልና በክልል መንግስታዊ ቦታውች ለረዥም ጊዜ ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በጥረት ኮርፖሬት ውስጥ ደግሞ አቶ ታደሰ ካሳ በዋና ሥራ አስፈፃሚነት አቶ በረከት ስምኦን ደግሞ በቦርድ ሰብሳቢነት ለበርካታ ዓመታት መሥራታቸው ተጠቁሟል።
አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳን በቁጥጥር ስር ለመዋል ያበቃቸውና ጥረት ኮርፖሬት ላይ የተፈጸመው የሀብት ብክነት ምንድን ነው?
የጥረት ኮርፖሬት የሀብት፣ እንዲሁም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የገንዘብ ብክነት ተፈጽሞብኛል ያላቸው ዝርዝሮች፦
- የኮርፖሬቱ ንብረት የሆኑ አምስት ኩባንያዎች ከ ክስዮን መሸጥ/ግዢ ጋር በተያያዘ ለሀብት ብክነት የዳረገ ብልሹ አሠራር በኦዲት ተደርሶበታል፤
- ሌሎች ሁለት እህት ኩባንያዎች ላይ ተመሳሳይ የኦዲት ሥራ እየተሠራ ነው፤
- ተጠርጣሪዎቹ በኮርፖሬቱ ውስጥ በስልጣን ላይ እያሉ የተመሠረቱ ስድስት እህት ኩባንያዎች፥ ከመመሥረታቸው በፊት አስፈላጊውን የአዋጭነት ጥናት ሳይደረግ ለእነዚህ ኩባንያዎች መመሠረቻ/ ግዢ ወደ ሚሊዮን ብር ወጪ ወጥቷል፤
- እነዚህ ስድስት እህት ኩባንያዎች ከተመሠረቱ/ ከተገዙ በኋላ በጊዜው ወደሥራ ባለመግባታቸው ኮርፖሬቱን ለተጨማሪ ወጪ/ ኪሳራ ዳርገውታል፤
- ጥረት ኮርፖሬሽን በአጋርነት ከሚሠራቸው ኩባንያዎች ጋርም ከኮርፖሬቱ የፋይናንስ አሠራርና ሕግ ውጪ 7 ሚሊየን ብር ለሁለት ኩባንያዎች ተሰጥቷል፤
- በሦስት ግለሰቦች ለሚተዳደር አንድ የማዕድን ኩባንያ ላወጣው የእያንዳንዱ አክሲዮን ዋጋ 1,000 ብር ሲሆን፥ ጥረት ኮርፖሬት በአንጻሩ የእያንዳንዱን አክሲዮን ዋጋ በ2,200 ብር እንዲገዛ ተደርጓል። በዚህም ሦስቱ ባለሀብቶች የ4 ሚሊየን 320 ሺህ ብር ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆኑ፥ ጥረት ኮርፖሬት ግን ለኪሳራ ተዳርጓል፤
- ባለሙያን ያላካተተ የአክስዮን መግዛትና መሸጥ ሥራ በኮርፖሬቱ ውስጥ ይተገበር ነበር፤ ይህም ለሀብት ብክነት ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል፤
- ለካፒታል ዕድገት ለሀገር ውስጥ ገቢ መክፈል የነበረበትን 1 ሚሊዮን 296 ሺህ ብር ባለመክፈሉ ጥረት ኮርፖሬት ባለዕዳ አድርጎታል፤
- ለፋብሪካ ይገነባል በሚል የ17 ሚሊየን ብር ግብዓት ተገዝቶ እስካሁን ምንም ዓይነት ሥራላ በለመዋሉ ኮርፖሬቱን ለሌላ የሀብት ብክነት ዳርጎታል።
በስተመጨረሻም አቶ ዝግአለ እንዳስታወቁት የአቶ በረከት ስምኦን እና የአቶ ታደሰ ካሳ በቁጥጥር ስር መዋል መጀመሪያ እንደሆነና፥ ሌሎችም በእንዲህ ዓይነት ወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ይውላሉ።
ቀድሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን)፣ በመሀል ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን)፣ አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) የተባለው የአማራ ሕዝብ ፓርቲ ያቋቋመው ጥረት ኮርፖሬት በአምራችነት ዘርፍ፣ በአገልግሎት መሰጠት ዘርፍ፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ እና በ አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የአስራ ዘጠኝ ኩባንያዎች ባለቤት መሆኑን የኮርፖሬቱ ድረ ገጽ ያሳያል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– አዲስ አበባን ከኤርትራዋ ምጽዋ ጋር ለሚያገናኘው የባቡር መስመር ፕሮጀክት ጥናት ወጪ ለመሸፈን የጣሊያን መንግስት መስማማቱን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
በጣሊያን ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጣሊያን አቻቸው ጁሴፔ ኮንቴ ጋር ተወያይተዋል። መሪዎቹ ከውይይቱ በኋላ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ጣልያን አዲስ አበባን ከምፅዋ ለሚያገናኘው የባቡር መስመር ፕሮጀክት የመጀመሪያ ጥናት ወጪ ለመሸፈን ተስማምታለች።
ከጥናቱም በኋላ በሚገኘው ውጤት በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላት ጁሴፔ ኮንቴ እንደገለጹላቸውና ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ምስጋናውን እንደሚያቀርብ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናግረዋል።
አዲስ አበባ እንደ ስሟ እንድትሆንና ነዋሪዎች ወጥተው ሲገቡ የሚዝናኑበትን ቦታ ከመፈለግ አንጻር በአዲስ አበባ በሚገኙ ኤምባሲዎች የተወሰነ ቦታቸውን ለህዝብ መዝናኛ ፓርክ እንዲያውሉ ጥያቄ ቀርቧል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የጣልያን መንግስትም ለዚህ ቅን ምላሽ መስጠቱን ተናግረዋል።
◌ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከጣሊያን አቻቸው ጁሴፔ ኮንቴ የሰጡት የጋራ መግለጫ
የኢትዮጵያ መንግስት የብሔራዊ ቤተ መንግስቱን ግማሽ የህዝብ መዝናኛ ፓርክ ለማድረግ እየሠራ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጠቅሰዋል። በአዲስ አበባ ለተቸገሩ ወገኖች ምግብ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት ጣልያን በመዲናዋ የዳቦ መጋገሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ፍላጎት እንዳላትም አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጣልያን ቆይታቸው ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በልማትና በሰላም ውይይቶች እንዳደረጉና ከአቻቸው ጁሴፔ ኮንቴ ጋር ያደረጉት ሁለገብ ምክክርም የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማሳደግ ፈር ቀዳጅ እንደሆነ ተናግረዋል።
በምስራቅ አፍሪካ ሰላም፣ ልማትና አንድነት እንዲረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የጣሊያን መንግስት ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ዶ/ር አብይ አመልክተዋል።
በኢትዮጵያና በጣልያን መካከል የተደረገው ውይይት ፍሬያማ እንዲሆን በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚካሄዱ የሁለትዮሽ ውይይቶች አገራቱ በሰላም፣ በልማትና በቱሪዝም ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባም አንስተዋል። አገራቱ ለጋራ እድገትና ሰላም በጋራ እንሥራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በአጠቃላይ ከልዑካን ቡድኑ ጋር በጣልያን የነበራቸው ቆይታ ስኬታማ እንደነበረ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት። “እንደ ወንድም አገርና እንደ ጠንካራ ወዳጅ ከምናያት ከጣልያን የምንፈልገውን ነገር አግኝተናል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
◌ የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ምርቱን ለመጨመር እና የኤክስፖርት መጠኑን ለማሳደግ እየሠራ ነው
የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጄሴፔ ኮንቴ በበኩላቸው ሁለቱ አገራት ታሪካዊ የሚባል ግንኙነት እንዳላቸውና በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራና በትብብር ለመሥራት መግባባታቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው የልማት ሥራዎች የጣሊያን መንግስት የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ቃል ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በጣልያን ጉብኝት ያደረጉት የጣሊያኑ አቻቸው ጁሴፔ ኮንቴ በ2011 ዓ.ም መጀመሪያ በኢትዮጵያ ጉብኝት ባረደጉበት ወቅት ባቀረቡላቸው ግብዣ መሠረት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጣሊያን ቆይታቸው ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ፣ ከዓለም የምግብ ድርጅት ዋና ዳሬክተር ዴቪድ ቤዝሊ፣ ከተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆዜ ግራዚያኖ ዳ ሲልቫና ከግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ፈንድ ፕሬዝዳንት ጊልበርት ሆዉንግቦ ጋር ተወያይተዋል።
በሌላ በኩል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተጓዘው የልዑካን ቡድን በሮም ከጣሊያን ባለሃብቶች ጋር ውይይት አካሂዷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ አምባሳደር ፍጹም አረጋ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አበበ አበባየሁን ያካተተው የልዑካን ቡድን ለባለሃብቶቹ ሃገሪቱ ስላላት የተለያዩ የኢንቨሰትመንት ዘርፎችና አማራጮች ማብራሪያ መስጠታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
◌ በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ምርታቸውን ወደውጭ ሀገራት መላክ ጀምረዋል
ካርቪኮ ግሩፕ በአሁኑ ሰዓት በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ23 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ ግንባታውን እያጠናቀቀ ሲሆን፥ በጣሊያንና በቬትናም በሚገኙ ፋብሪካዎች የሠራተኛ ስልጠና በማድረግ ዝግጅቱን ለመጀመር በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
በውይይቱ የተገኙት ሌሎች ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በመድኃኒት፣ በግንባታ፣ በግብርና ማቀነባበርያ እና አልባሳት ዘርፍ በስፋት ለመሰማራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ተብሏል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራው የልዑካን ቡድን ከጣልያን ቆይታው በኋላ በስዊዘርላንድ ዳቮስ ከተማ በሚካሄደው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ለመሳተፍ ወደ ስፍራው ያቀናል ተብሎ ይጠበቃል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አቶ ሽመልስ አብዲሳ ኡፍታላ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሲሾሙ፥ ወይዘሮ ቢልለኔ ስዩም ወልደየስ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ሆነው ተሹመዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – አቶ ሽመልስ አብዲሳ ኡፍታላ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው በዛሬው ዕለት (ጥቅምት 26 ቀን 2011 ዓ.ም) ተሾሙ።
አቶ ሽመልስ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩትን አቶ ፍጹም አረጋ ተክተው ነው የተሾሙት። በዚህም አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተሰጣቸው ኃላፊነት መሠረት የፕሬስ ሴክቴሪያት ጽህፈት ቤት፣ የብቃትና ፖሊሲ ምዘና ጽህፈት ቤት፣ የአገር ደህንነት ጉዳይ አማካሪ ጽህፈት ቤትና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትን ይመራሉ ተብሏል።
ከዚህ በፊት የነበሩት አቶ ፍጹም አረጋ ወደ ቀድሞ ቦታቸው፥ ማለትም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ተመልሰዋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚነት የነበሩት በላቸው መኩሪያ (ዶ/ር) በመስከረም ወር መጀመሪያ ሳምንት “የግል/ የቤተሰብ ጉዳይ” በሚል ምክንያት ኃላፊነታቸውን (ብሎም ከኮሚሽኑ በአጠቃላይ) መልቀቃቸው ይታወሳል።
I wanted to announce that I will be moving back to Ethiopian Investment Commission—as a Commissioner. I have enjoyed my time immensely as a Chief of Staff serving a historic Prime Minister who will no doubt transform the country for the better. #Ethiopia
— Fitsum Arega (@fitsumaregaa) November 5, 2018
አቶ ሽመልስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰብአዊ መብት የማስትሬት ዲግሪ፣ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ አፍሪካ (UNISA) ደግሞ በፖለቲካል ፍልስፍና ሁለተኛ የማስተሬት ድግሪ አግኝተዋል።
በተያያዘ ዜና፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ስር የፕሬስ ሴክሬታሪ ጽህፈት ቤት የተቋቋመ ሲሆን ወይዘሮ ቢልለኔ ስዩም ኃላፊ ተደርገው ተሹመዋል። ወይዘሮ እና ቢልለኔ ስዩም ስነ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጸሐፊ/ደራሲ ሲሆኑ፣ የሴቶች መብት ላይ እና በጾታ እኩልነት ላይ የሚሠራ ዕሩያን ሶሉሽንስ (Earuyan Solutions) የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት መሥራችና ኃላፊ ነበሩ። በትምህርታቸውም የማስተርስ ዲግሪ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፒስ-ኮስታሪካ፣ ሌላ የማስተርስ ዲግሪ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኢንስብሩክ (ኦስትርያ) እና የባችለርስ ዲግሪ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ብሪቲሽ ኮለምብያ (ካናዳ) አላቸው።
የኢህአዴግ 11ኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባዔ የአቋም መግለጫ
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ “ሀገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል 11ኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባዔውን በብሄር ብሄረሰቦች መዲና፣ የህብረ ብሄራዊነትና የብዝሃነት መገለጫ እና የኢትዮጵያ ተምሳሌት በሆነችው ውቢቷ ሀዋሣ ከተማ ከመስከረም 23–25 ቀን 2011 ዓ.ም ለሶስት ተከታታይ ቀናት አካሒዶ በስኬትና በድል አጠናቅቋል።
የድርጅታችን አባላትና የትግላችን ደጋፊዎች፣ አጋሮቻችን፣ ወዳጆቻችንና መላው የአገራችን ሕዝቦች የጀመርነውን ለውጥ አጠናክረን እንድንቀጥል፣ ድርጅታችን ከምንግዜውም በላይ እንዲጠናከር እና የመሪነት ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ፣ የፈነጠቀው ተስፋ የበለጠ እየለመለመ እንዲሄድ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን አስተላልፎና አቅጣጫዎችን አስቀምጦ እንዲጠናቀቅ በጉጉት ሲጠብቁት የነበረው ታሪካዊ ጉባዔ በስኬት በማጠናቀቅ መድረኩን የሚመጥን ቁመና ተላብሰን፣ እንደ ኢህአዴግ አንድነታችንን አጠናክረን መውጣታችንን ስንገልጽ በከፍተኛ መነሳሳትና ቁርጠኝነት ነው።
11ኛው መደበኛ ድርጅታዊ ጉባዔያችን ታሪካዊ ነው የሚያሰኙት በርካታ እውነታዎች ቢኖሩም ሁነኛ መገለጫው አገር የመበታተን፣ የአንድ አገር ሕዝብ እርስ በርስ የመተላለቅና የድርጅታችን ህልውና የማክተም አደጋ አንዣቦበት ከነበረበት ሁኔታ በማምለጥ የሰላም፣ የይቅርታ፣ የፍቅርና አንድነት ተስፋ በለመለመበት ወሳኝ ወቅት ላይ መሆኑ፤ እንዲሁም ኢህአዴግ ለውጡን በፍጥነት እና በዘለቄታ ይዞ መጓዝ የሚያስችለው ቁመና የሚያላብሱ ውሳኔዎች የተላለፉበት መሆኑ ነው።
በ10ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ የተቀመጡ አቅጣጫዎች አፈፃፀም ሪፖርት በመገምገም፣ ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታና ለውጡን በብቃት የመምራት አስፈላጊነት ላይ በጥልቀት በመወያየት መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን እንደዚሁም የድርጅታችን የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን ሪፖርት ገምግሞ የቀጣይ ርብርብ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ ድርጅቱን እስከቀጣይ ጉባዔ የሚመሩ መሪዎችን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ መርጦ ተጠናቅቋል።
ጉባዔያችን እንደ ድርጅት ሕዝቡ የሚጠብቀውን ለውጡን በብቃት፣ በፍጥነት እና በቁርጠኝነት በመምራት ሕዝባችንን ከስጋት ማላቀቅ የሚያስችል የሀሳብ አንድነት የፈጠርንበት፣ በችግሮቻችንና በመፍትሄ አቅጣጫዎቹ ላይ ልብ ለልብ ተገናኝተን አንድነት ፈጥረን የወጣንበት ጉባዔ ነው።
ኢህአዴግ ባለፉት ሶስት አስርት በሚጠጉ ዓመታት ያስመዘገብናቸው ስኬቶች እንደተጠበቁ ሆነው የሕዝቡን የለውጥ ጥማት ሊያረካ የሚችል ሥራ በሚፈለገው ደረጃ ባለመሰራቱ፣ የዴሞክራሲ ባህል አለመጐልበቱ፣ ምህዳሩ እየጠበበ መምጣቱ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ በሚፈለገው ልክ አለመሠራቱ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በስፋት በመታየታቸው፣ የሕዝቡ ፍትሐዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ጐልተው በመውጣታቸው፣ የመሠረተ ልማት ተደራሽነትና ጥራት ችግሮች በመታየታቸው፣ ብልሹ አስተዳደር እየሰፋ በመሄዱ፣ የተደራጀ ሌብነት እየረቀቀና ስር እየሰደደ በመምጣቱ ምክንያት ማህበራዊ መሠረቶቻችንን ጨምሮ በሕዝቡ ዘንድ ድርጅታችን ያለው ተዓማኒነት የመሸርሸር አደጋ እንዲጋረጥበት ሆኖ ነበር። የማታ የማታ ችግሮች እየተደማመሩ መጥተው ወደ ግጭትና አለመረጋጋት ብሎም የአገራችንን ህልውና አደጋ ላይ ወደሚጥል ፖለቲካዊ ቀውስ መግባታችን ይታወቃል።በዚህም ምክንያት በተፈጠሩ ግጭቶች የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ የዜጐች አካል ተጐድቷል፣ የመንግስትና ሕዝብ ንብረት ወድሟል። የችግሮቹ ምንጮቹም በዋናነት ከእኛ የመሪነት ጉድለት ጋር እንደሚያያዙ ጉባዔው በአጽንዖት ገምግሟል።
ድርጅታችን የተስተዋሉበትን ድክመቶች ለማረምና ሀገራችንን ከጥፋት ለማዳን በሕዝቡ ግፊት ከውስጥ የመነጨ የጥልቅ ተሀድሶ ንቅናቄ ጀምሮ አሁን የምንገኝበት ተሰፋ ሰጪ የለውጥ ምህዋር ውስጥ ገብተናል።
እኛ የ11ኛ የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ ተሳታፊዎች እንደ ድርጅት የመጣንበት መንገድ፣ አሁን የምንገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ በጥልቀት በመገምገም በሀገራችን ሕዝቦች፣ በአጐራባች ሀገሮች እና በመላው ዓለም ዕውቅና የተቸረው የሀገራችን ጅምር የለውጥ እንቅስቃሴ ጐልብቶ ወደማይቀለበስበት ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል ይህንን ባለ 7 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል።
- በሀገራችን ሕዝቦች አነሳሽነት እና በኢህአዴግ መሪነት ሀገራችን ወደ ተስፋ ሰጪ የለውጥ ምዕራፍ ገብታለች። ይህ የለውጥ ምዕራፍ የፈነጠቀው የተስፋ ብርሃን በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ መነቃቃትን ከመፍጠሩም ባሻገር ለዘመናት ተኮራርፈው የዘለቁ ወገኖች እንዲታረቁ፣ የታሰሩ እንዲፈቱና የተለያዩ እንዲገናኙ በማድረግ ብሄራዊ መግባባት ከፍ እንዲል ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳበረከተ በጉባዔያችን ታይቷል።
በመሆኑም በሀገራችን እየተመዘገበ ያለው ለውጥ ሕዝባዊ፣ ህገ መንግስታዊ እና ኢህአዴጋዊ መሆኑ ላይ በመተማመን ለውጡ እንዳይቀለበስ የጉባዔው ተሳታፊዎች የየራሳችንን ታሪካዊ ኃላፊነት መወጣት እንዳለብን የጋራ አቋም ወስደናል። ኢህአዴግ እንደ ግንባር ጠንካራ የአስተሳሰብ አንድነት በመያዝ፣ ከአሰራር፣ ከአደረጃጀት እና ከአመራር ግንባታ አንፃር ያሉበትን ጉድለቶች ፈትሾ በማስተካከል እንዲሁም ጥናት ላይ በመመስረት የርዕዮተ -ዓለም ማልማትና ማሻሻልን ከግምት በማስገባት ድርጅቱ ለውጡን በብቃትና በሚፈለገው ፍጥነት መርተን ወደ ግቡ ለማድረስ በጋራ እንሠራለን።
- በሀገራችን የፖለቲካ ምህዳሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ በመምጣቱ ምክንያት የሀሳብ ብዙሃነትን በብቃት ያለማስተናገድ፣ የሀሳብና የፖለቲካ አቋም ልዩነቶች በጠላትነት የሚፈረጁበት፣ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች እየሰፉ የመጡበት አገራዊ ሁኔታ ውስጥ የነበርን መሆናችንን የገመገምን ሲሆን ዴሞክራሲን በማስፋት ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ችግሮቻችንን በሰለጠነ መንገድ ተወያይተን ለመፍታት የሚያስችሉ ጅምር እርምጃዎች ተወስደዋል፤ እየተወሰዱም ይገኛሉ። በተለያዩ ምክንያቶች ተፈርዶባቸው ማረሚያ ቤት የነበሩ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች፣ ጋዜጠኞችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በይቅርታና በምህረት እንዲፈቱ መደረጉ፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩ ላይ ጥያቄ የሚያስነሱ እና መሻሻል የሚገባቸው ህጐች እንዲሻሻሉ አቅጣጫ መቀመጡ፣ የትጥቅ ትግልን እንደ አመራጭ ወስደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ቡድኖች ወደ ሠላማዊ ትግል መድረክ መመለስ መጀመራቸው ይበል የሚያሰኝ ተግባር መሆኑን ገምግመናል።
በመሆኑም የዴሞክራሲ ምህዳሩን የበለጠ ማስፋት፣ ዜጐች በያዙት የተለየ የፖለቲካ ሀሳብ እና አመለካከት የማይገፉበትና በጠላትነት የማይታዩበት ሀገራዊ ሁኔታ እንዲፈጠር፣ የግልና የቡድን መብቶች በተሟላ መልኩ የሚከበሩበትን ሁኔታ በማመቻቸት፣ በሀገራችን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እየተጠናከረ እንዲሄድ በጽናት እንታገላለን።
- ህብረ – ብሄራዊ ፌደራላዊ ሥርዓቱ ባልተማከለ አስተዳደር ብሔር – ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ዕድል የሰጠ፣ ሕዝቦች በሀገሪቷ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ያስቻለ፣ የሀገራችንን አንድነት በጽኑ መሠረት ለመገንባት ብቸኛው አማራጭ እንደሆና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ሀገራዊ አንድነትን ለመፍጠር ወሳኝ ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኝ ተገምግሟል።ይሁን እንጂ የፌደራል ሥርዓት ግንባታችን በጅምር ደረጃ ላይ ያለ እንደመሆኑ መጠን የወሰን አከላለል ጥያቄዎች፣ ማንነትን መነሻ ያደረጉ ግጭቶች፣ የዜጐች ሞትና መፈናቀል፣ እንዲሁም ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ በነፃነት የመሥራት ህገ – መንግስታዊ መብት ጥሰቶች ይስተዋላሉ።
በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ከሥረ – መሠረታቸው መነቅል የሚገባቸው ችግሮች በመሆናቸው የማንነትም ይሁን የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች የሚመለከታቸውን ሕዝቦች ነፃ ፍላጐት ከግምት ውስጥ ባስገባ፣ በህገ-መንግስታዊ እና ዴሞክራሲያዊ አግባብ እንዲፈቱ፣ የዜጐች የትም ቦታ ተዘዋውሮ የመኖር፣ የመሥራት፣ በቋንቋቸው የመማር፣ የመዳኘት፣ ወግና ባህላቸውን የማሳደግ፣ ተገቢውን ዕውቅናና ውክልና የማግኘት፣ ሀብት የማፍራት፣ ህገ – መንግስታዊ መብቶቻቸው እንዲከበር እንዲሁም ብሄራዊ ማንነት እና ሃገራዊ አንድነት ሳይነጣጠሉ እንዲጐለብቱ አበክረን እንሰራለን።
- የምንገኝበት ወቅት የ2ኛው የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዳችንን ማጠናቀቂያ ዋዜማ እንደመሆኑ በኢኮኖሚው ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግር ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችሉ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ለገበያ የሚያመርቱ አርብቶ እና አርሶ አደሮችና በመደገፍ፣ የመስኖ እና መሰል የግብርና ልማት ሥራዎችን በማፋጠን፣ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማትን በመደገፍ፣ በንግድ እና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት፣ ገቢ የመሰብሰብ አቅማችንን በማጠናከር የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ መፍጠር አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑ በጉባዔያችን ላይ በዝርዝር ታይቷል።
በመሆኑም በገጠርም ሆነ በከተማ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ፣ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን የሚያጠናክሩ፣ የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር የሚያስችሉ፣ የመላውን ሕዝብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ዕውን የሚያደርጉ፣ በተለይም የወጣቶችንና የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ለመንቀሳቀስ ቃል እንገባለን።
- የቀሰቀስነው ለውጥ ተስፋ ሰጪ ውጤት እያስመዘገበ ያለው በሀገር ውስጥ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በውጭ ዲፕሎማሲ ዘርፍም ጭምር መሆኑን በዝርዝር የገመገምን ሲሆን ከጐረቤት ሀገሮች፤ በተለይም ከቀይ ባህር አካባቢ አገራት ጋር የፈጠርነው ትስስር ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበትና በምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር ሁነኛ ሚና የሚጫወት የሰላም፣ የትብብርና የአንድነት ተስፋ የፈጠረ ግንኙነት መሆኑ በዝርዝር የገመገምን ሲሆን የኢትዮ – ኤርትራ ግንኙነት መታደስ በቅድሚያ ሊጠቀስ የሚገባው መሆኑን፤ እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ተዘርግቶ የነበረው ጥቁር መጋረጃ መቀደዱን ስኬታማ የዲፕለማሲ ሥራ ውጤት መሆኑን እና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገምግመናል።
በመሆኑም ከሁሉም አጐራባች ሀገራት የሚኖረን ግንኙነት የጋራ ጥቅሞቻችን እና የሕዝቦቻችን አንድነት የሚያጠናክሩ እንዲሆኑ በተለይም በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የሁለቱን ሀገራት ድንበር በተመለከተ መርህን በተከተለ፣ የሕዝባችንን አንድነት በማያናጋ እና መልካም ጉርብትናን አጠናክሮ ማስቀጠል በሚያስችል መልኩ እልባት እንዲያገኝ እንሰራለን።
- በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች አውዳሚ ግጭቶች፣ ሥርዓት አልበኝነት እና የህግ የበላይነትን የሚጥሱ ተግባራት ሲፈፀሙ ይስተዋላል። በስርዓተ አልበኝነት እና በመንጋ ፍትህ ምክንያት የዜጐች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚጣሱበት ነባራዊ ሁኔታ መኖሩን ጉባዔተኛው ገምግሟል።
በመሆኑም ከዚህ ታሪካዊ ጉባዔ በኋላ ሃገራችን ሠላም የሠፈነባት፣ ዜጐች በነፃነት ተንቀሳቅሰው ያለ ስጋት የሚኖሩባት፣ የህግ የበላይነት የተከበረባት እንድትሆን፤ እንዲሁም ነፃነት ከህግ የበላይነት ውጪ ባርነት መሆኑን በመገንዘብ መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታውንም ጠንቅቆ የሚያውቅ ህብረተሰብ ለመገንባት በትጋት እንሠራለን።
- በአገር ደረጃ የተለኮሰው የተሃድሦ እንቅስቃሴ የበለጠ እየጠራ እንዲሄድ፣ መሪው ድርጅታችን ኢህአዴግ ብቃት ያለው አመራር መሥጠት አለበት። ስለሆነም ድርጅታችን መሠረታዊ ባህሪውን ጠብቆ በውስጡ ያለውን ችግር በሚገባ አጥርቶ እንዲወጣ የተለየ ትኩረት ሰጥቶት መሠራት እንደሚገባውም ተገምግሟል። ከዚህ አኳያ የኢህአዴግ አባል ብሔራዊ ድርጅቶች ባካሄዱት ጉባዔ አዳዲስ ምሁራን፣ ወጣቶችና ሴቶችን ወደ አመራር ቋት ማስገባት መቻላቸውም በጥንካሬ ተገምግሟል። ይህ የተጀመረው ድርጅታችንን የማጠናከር ሥራ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በብቃት ለመምራትና ሕዝቡን ለመካስ ቃል እንገባለን።
የተከበራችሁ የድርጅታችን አባላት፦
ድርጅታችሁ ኢህአዴግ በዚህ ታሪካዊ ጉባዔ ያለፉትን ድክመቶችን በዝርዝር ገምግሞና ፈትሾ የእርምት ዕርምጃ ለመውሰድና ጥንካሬዎቻችንን እንዲጐለብቱ ለማድረግ ያስችል ዘንድ የጀመርነው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና እንዳይቀለበስ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል። ስለሆነም በመላው ሀገራችን ተስፋ የተጣለበት ለውጥ እንዲቀጥልና የበለጠ እንዲጠናከር ግንባር ቀደም ሚና የመጫወት ታሪካዊ ኃላፊነት በትከሻችሁ ላይ የወደቀ መሆኑን በመገንዘብ ግንባር ቀደም ሚናችሁን እንድትጫወቱ ጥሪ እናቀርብላችኋለን።የተከበራችሁ የሀገራችን ወጣቶችና ሴቶች፦
ድርጅታችን ኢህአዴግ የሀገራችን ወጣቶችና ሴቶች ለሰላም ለልማትና ለዴሞክራሲ መረጋገጥ ያላችሁ ሚና ተኪ የሌለው መሆኑን ከማመኑም በላይ ለውጡ የእናንተ መሆኑን ይገነዘባል። ኢህአዴግ የዛሬ ብቻ ሳይሆን የነገ ድርጅት በመሆኑ የጓጓችሁለትና መስዋዕትነት የከፈላችሁለት ለውጥ በአስተማማኝ ሁኔታ እውን እንዲሆን በማድረግ ለውጥ ለማምጣት ካደረጋችሁት ትግል እና ከከፈላችሁት መስዋዕትነት ባሻገር ለውጡን የመንከባከብና የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለባችሁ በመገንዘብ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ አስተዋይነትና ብልህነት በተላበሰ ሁኔታ እንድትንቀሳቀሱ ጥሪ እናስተላልፈላችኋለን።የተከበራችሁ የሀገራችን ምሁራን
አሁን ሀገራችን የደረሰችበት የለውጥ ደረጃ የእናንተን ዕውቀት፣ ልምድና ችሎታ በከፍተኛ ሁኔታ ይፈልጋል። በመሆኑም የጀመርነው ለውጥ እንዲቀጥልና እንዲሳካ ጥናትና ምርምር በማድረግ እና ሳይንሳዊ ትንታኔ በመስጠት ያላችሁን ልምድ፣ ብቃት እና ተነሳሽነት ለወገናችሁ እንድታበረክቱ ጥሪ እናስተላልፍላችኋለን።የተከበራችሁ የአጋር ድርጅቶች
በጉባዔያችን መክፈቻ ስነ – ስርዓት ላይ እንዳስተላለፋችሁት መልዕክት ሁሉ ኢህአዴግም ከእናንተ ጋር በመዋሀድ አንድ ሀገራዊ ፓርቲ በመሆን ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት እና የሚታገሉበት የጋራ መድረክ ይሆን ዘንድ የጥናት ሥራዎችን ተጀምረዋል። በመሆኑም እንደ አንድ ህብረ ብሄራዊና ሀገራዊ ድርጅት ለመንቀሳቀስ በሚያስችለን ህሊናዊና ነባራዊ ሁኔታ ላይ መሆናችንን እየገለጽን ለዚህ ዓላማ ስኬት ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።የተከበራችሁ የተፎካካሪ ፓርቲዎች
ምንም እንኳን የተለያየ የፖለቲካ አቋም ቢኖረንም የሀገራችን ሕዝቦች የመልማት፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ማረጋገጥ የጋራ አጀንዳዎቻችን መሆናቸውን በውል እንገነዘባለን። እስከ አሁን ባለው ጊዜ በጥላቻ እና በመጠፋፋት ፖለቲካ በመጠመዳችን እና በጠላትነት በመተያየታችን ብዙ ዕድሎች አምልጠውናል። ስለሆነም ወቅቱ የሚጠይቀውን የአንድነትና የአብሮነት መንፈስ በመተጋገዝ እና በመርህ ላይ የተመሠረተ ትግል በማድረግ ሀገራዊ ለውጡን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በሚደርገው ጥረት የበኩላችሁን ገንቢ ሚና እንድትጫወቱ ጥሪያችንን በአክብሮት ስናቀርብላችሁ የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያሰፉ ተቋማትን፣ አሠራሮችን እና አደረጃጀቶችን በማሻሻል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በቁርጠኝነት ለመሥራት የተዘጋጀን መሆናችንን እንገልፃለን።የተከበራችሁ የመንግስት ሠራተኞች
የመንግስት ሠራተኛው አገልግሎታችንን የሚፈልገውን ህብረተሰብ በተገቢው ሁኔታ በማገልገል እርካታ ሊፈጥር የሚችል ታላቅ ኃይል መሆኑን እናምናለን። በመሆኑም የህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ እና ዕርካታ እንዲረጋገጥ በቅንነት፣ በታማኝነት እና በውጤታማነት በማገልገል ለውጡን ለማስቀጠል የበኩላችሁን ሚና እንድትወጡ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ እናስተላልፍላችኋለን።የተከበራችሁ የሀገራችን የፀጥታ አካላት፦
የሀገራችንን ሕዝቦች ሰላምና ፀጥታ እንዲሁም ደህንነት ለማስከበር እስከአሁን ለሰራችሁት ሥራ እና ለከፈላችሁት መስዋዕትነት ታላቅ አክብሮት ያለን መሆኑን እየገለጽን ሀገራዊ ለውጡ በስኬት ግቡን እንዲመታ የሕዝቦችን ሰላምና የሕግ የበላይነትን የማስከበር ህገ-መንግስታዊ ግዴታችሁን በጽናት እንድትወጡ በአክብሮት ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች፦
ኢህአዴግ በ11ኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባዔው ባለፉት ዓመታት ያስመዘገብናቸው ስኬቶች እንደተጠበቁ ሆነው ባላሟላናቸው ድክመቶች ምክንያት ቅሬታ የፈጠረባችሁና በዚህም ምክንያት በድርጅታችን ላይ ያላችሁ እምነት እየተሸረሸረ መምጣቱን ገምግሞ በእናንተ ቀስቃሽነትና በድርጅቱ መሪነት ተስፋ ሰጪ ለውጥ ላይ የምንገኝ መሆኑን በመገምገም ለውጡን ወደማይቀበለስበት ደረጃ የሚያደርሱ ታሪካዊ ውሳኔዎችን አስተላልፏል። ለሀገራዊ አንድነት፣ ለጋራ ብልጽግና፣ ለዘላቂ ሠላም መረጋገጥና የመደመር መርህዎችንና እሴቶችን ይዘን በጉባዔያችን ያስተላለፍናቸው ውሳኔዎች ዕውን እንዲሆኑ ሁለንተናዊ ተሳትፎአችሁና ድጋፋችሁ እንዳይለየን በታላቅ አክብሮት ጥሪአችንን እናስተላልፍላችኋለን።ሀገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና !!!
ዘላለማዊ ክብር ለትግሉ ሰማዕታት!!
መስከረም 25/2011
ሐዋሳ
Search Results for 'የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን'
Viewing 7 results - 1 through 7 (of 7 total)
Viewing 7 results - 1 through 7 (of 7 total)