የኢህአዴግ 11ኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባዔ የአቋም መግለጫ

Home Forums Semonegna Stories የኢህአዴግ 11ኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባዔ የአቋም መግለጫ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #7907
    Semonegna
    Keymaster

    የኢህአዴግ 11ኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባዔ የአቋም መግለጫ

    የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ “ሀገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል 11ኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባዔውን በብሄር ብሄረሰቦች መዲና፣ የህብረ ብሄራዊነትና የብዝሃነት መገለጫ እና የኢትዮጵያ ተምሳሌት በሆነችው ውቢቷ ሀዋሣ ከተማ ከመስከረም 23–25 ቀን 2011 ዓ.ም ለሶስት ተከታታይ ቀናት አካሒዶ በስኬትና በድል አጠናቅቋል።

    የድርጅታችን አባላትና የትግላችን ደጋፊዎች፣ አጋሮቻችን፣ ወዳጆቻችንና መላው የአገራችን ሕዝቦች የጀመርነውን ለውጥ አጠናክረን እንድንቀጥል፣ ድርጅታችን ከምንግዜውም በላይ እንዲጠናከር እና የመሪነት ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ፣ የፈነጠቀው ተስፋ የበለጠ እየለመለመ እንዲሄድ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን አስተላልፎና አቅጣጫዎችን አስቀምጦ እንዲጠናቀቅ በጉጉት ሲጠብቁት የነበረው ታሪካዊ ጉባዔ በስኬት በማጠናቀቅ መድረኩን የሚመጥን ቁመና ተላብሰን፣ እንደ ኢህአዴግ አንድነታችንን አጠናክረን መውጣታችንን ስንገልጽ በከፍተኛ መነሳሳትና ቁርጠኝነት ነው።

    11ኛው መደበኛ ድርጅታዊ ጉባዔያችን ታሪካዊ ነው የሚያሰኙት በርካታ እውነታዎች ቢኖሩም ሁነኛ መገለጫው አገር የመበታተን፣ የአንድ አገር ሕዝብ እርስ በርስ የመተላለቅና የድርጅታችን ህልውና የማክተም አደጋ አንዣቦበት ከነበረበት ሁኔታ በማምለጥ የሰላም፣ የይቅርታ፣ የፍቅርና አንድነት ተስፋ በለመለመበት ወሳኝ ወቅት ላይ መሆኑ፤ እንዲሁም ኢህአዴግ ለውጡን በፍጥነት እና በዘለቄታ ይዞ መጓዝ የሚያስችለው ቁመና የሚያላብሱ ውሳኔዎች የተላለፉበት መሆኑ ነው።

    በ10ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ የተቀመጡ አቅጣጫዎች አፈፃፀም ሪፖርት በመገምገም፣ ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታና ለውጡን በብቃት የመምራት አስፈላጊነት ላይ በጥልቀት በመወያየት መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን እንደዚሁም የድርጅታችን የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን ሪፖርት ገምግሞ የቀጣይ ርብርብ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ ድርጅቱን እስከቀጣይ ጉባዔ የሚመሩ መሪዎችን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ መርጦ ተጠናቅቋል።
    ጉባዔያችን እንደ ድርጅት ሕዝቡ የሚጠብቀውን ለውጡን በብቃት፣ በፍጥነት እና በቁርጠኝነት በመምራት ሕዝባችንን ከስጋት ማላቀቅ የሚያስችል የሀሳብ አንድነት የፈጠርንበት፣ በችግሮቻችንና በመፍትሄ አቅጣጫዎቹ ላይ ልብ ለልብ ተገናኝተን አንድነት ፈጥረን የወጣንበት ጉባዔ ነው።
    ኢህአዴግ ባለፉት ሶስት አስርት በሚጠጉ ዓመታት ያስመዘገብናቸው ስኬቶች እንደተጠበቁ ሆነው የሕዝቡን የለውጥ ጥማት ሊያረካ የሚችል ሥራ በሚፈለገው ደረጃ ባለመሰራቱ፣ የዴሞክራሲ ባህል አለመጐልበቱ፣ ምህዳሩ እየጠበበ መምጣቱ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ በሚፈለገው ልክ አለመሠራቱ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በስፋት በመታየታቸው፣ የሕዝቡ ፍትሐዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ጐልተው በመውጣታቸው፣ የመሠረተ ልማት ተደራሽነትና ጥራት ችግሮች በመታየታቸው፣ ብልሹ አስተዳደር እየሰፋ በመሄዱ፣ የተደራጀ ሌብነት እየረቀቀና ስር እየሰደደ በመምጣቱ ምክንያት ማህበራዊ መሠረቶቻችንን ጨምሮ በሕዝቡ ዘንድ ድርጅታችን ያለው ተዓማኒነት የመሸርሸር አደጋ እንዲጋረጥበት ሆኖ ነበር። የማታ የማታ ችግሮች እየተደማመሩ መጥተው ወደ ግጭትና አለመረጋጋት ብሎም የአገራችንን ህልውና አደጋ ላይ ወደሚጥል ፖለቲካዊ ቀውስ መግባታችን ይታወቃል።

    በዚህም ምክንያት በተፈጠሩ ግጭቶች የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ የዜጐች አካል ተጐድቷል፣ የመንግስትና ሕዝብ ንብረት ወድሟል። የችግሮቹ ምንጮቹም በዋናነት ከእኛ የመሪነት ጉድለት ጋር እንደሚያያዙ ጉባዔው በአጽንዖት ገምግሟል።

    ድርጅታችን የተስተዋሉበትን ድክመቶች ለማረምና ሀገራችንን ከጥፋት ለማዳን በሕዝቡ ግፊት ከውስጥ የመነጨ የጥልቅ ተሀድሶ ንቅናቄ ጀምሮ አሁን የምንገኝበት ተሰፋ ሰጪ የለውጥ ምህዋር ውስጥ ገብተናል።

    እኛ የ11ኛ የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ ተሳታፊዎች እንደ ድርጅት የመጣንበት መንገድ፣ አሁን የምንገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ በጥልቀት በመገምገም በሀገራችን ሕዝቦች፣ በአጐራባች ሀገሮች እና በመላው ዓለም ዕውቅና የተቸረው የሀገራችን ጅምር የለውጥ እንቅስቃሴ ጐልብቶ ወደማይቀለበስበት ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል ይህንን ባለ 7 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል።

    1. በሀገራችን ሕዝቦች አነሳሽነት እና በኢህአዴግ መሪነት ሀገራችን ወደ ተስፋ ሰጪ የለውጥ ምዕራፍ ገብታለች። ይህ የለውጥ ምዕራፍ የፈነጠቀው የተስፋ ብርሃን በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ መነቃቃትን ከመፍጠሩም ባሻገር ለዘመናት ተኮራርፈው የዘለቁ ወገኖች እንዲታረቁ፣ የታሰሩ እንዲፈቱና የተለያዩ እንዲገናኙ በማድረግ ብሄራዊ መግባባት ከፍ እንዲል ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳበረከተ በጉባዔያችን ታይቷል።

    በመሆኑም በሀገራችን እየተመዘገበ ያለው ለውጥ ሕዝባዊ፣ ህገ መንግስታዊ እና ኢህአዴጋዊ መሆኑ ላይ በመተማመን ለውጡ እንዳይቀለበስ የጉባዔው ተሳታፊዎች የየራሳችንን ታሪካዊ ኃላፊነት መወጣት እንዳለብን የጋራ አቋም ወስደናል። ኢህአዴግ እንደ ግንባር ጠንካራ የአስተሳሰብ አንድነት በመያዝ፣ ከአሰራር፣ ከአደረጃጀት እና ከአመራር ግንባታ አንፃር ያሉበትን ጉድለቶች ፈትሾ በማስተካከል እንዲሁም ጥናት ላይ በመመስረት የርዕዮተ -ዓለም ማልማትና ማሻሻልን ከግምት በማስገባት ድርጅቱ ለውጡን በብቃትና በሚፈለገው ፍጥነት መርተን ወደ ግቡ ለማድረስ በጋራ እንሠራለን።

    1. በሀገራችን የፖለቲካ ምህዳሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ በመምጣቱ ምክንያት የሀሳብ ብዙሃነትን በብቃት ያለማስተናገድ፣ የሀሳብና የፖለቲካ አቋም ልዩነቶች በጠላትነት የሚፈረጁበት፣ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች እየሰፉ የመጡበት አገራዊ ሁኔታ ውስጥ የነበርን መሆናችንን የገመገምን ሲሆን ዴሞክራሲን በማስፋት ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ችግሮቻችንን በሰለጠነ መንገድ ተወያይተን ለመፍታት የሚያስችሉ ጅምር እርምጃዎች ተወስደዋል፤ እየተወሰዱም ይገኛሉ። በተለያዩ ምክንያቶች ተፈርዶባቸው ማረሚያ ቤት የነበሩ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች፣ ጋዜጠኞችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በይቅርታና በምህረት እንዲፈቱ መደረጉ፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩ ላይ ጥያቄ የሚያስነሱ እና መሻሻል የሚገባቸው ህጐች እንዲሻሻሉ አቅጣጫ መቀመጡ፣ የትጥቅ ትግልን እንደ አመራጭ ወስደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ቡድኖች ወደ ሠላማዊ ትግል መድረክ መመለስ መጀመራቸው ይበል የሚያሰኝ ተግባር መሆኑን ገምግመናል።

    በመሆኑም የዴሞክራሲ ምህዳሩን የበለጠ ማስፋት፣ ዜጐች በያዙት የተለየ የፖለቲካ ሀሳብ እና አመለካከት የማይገፉበትና በጠላትነት የማይታዩበት ሀገራዊ ሁኔታ እንዲፈጠር፣ የግልና የቡድን መብቶች በተሟላ መልኩ የሚከበሩበትን ሁኔታ በማመቻቸት፣ በሀገራችን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እየተጠናከረ እንዲሄድ በጽናት እንታገላለን።

    1. ህብረ – ብሄራዊ ፌደራላዊ ሥርዓቱ ባልተማከለ አስተዳደር ብሔር – ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ዕድል የሰጠ፣ ሕዝቦች በሀገሪቷ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ያስቻለ፣ የሀገራችንን አንድነት በጽኑ መሠረት ለመገንባት ብቸኛው አማራጭ እንደሆና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ሀገራዊ አንድነትን ለመፍጠር ወሳኝ ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኝ ተገምግሟል።ይሁን እንጂ የፌደራል ሥርዓት ግንባታችን በጅምር ደረጃ ላይ ያለ እንደመሆኑ መጠን የወሰን አከላለል ጥያቄዎች፣ ማንነትን መነሻ ያደረጉ ግጭቶች፣ የዜጐች ሞትና መፈናቀል፣ እንዲሁም ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ በነፃነት የመሥራት ህገ – መንግስታዊ መብት ጥሰቶች ይስተዋላሉ።

    በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ከሥረ – መሠረታቸው መነቅል የሚገባቸው ችግሮች በመሆናቸው የማንነትም ይሁን የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች የሚመለከታቸውን ሕዝቦች ነፃ ፍላጐት ከግምት ውስጥ ባስገባ፣ በህገ-መንግስታዊ እና ዴሞክራሲያዊ አግባብ እንዲፈቱ፣ የዜጐች የትም ቦታ ተዘዋውሮ የመኖር፣ የመሥራት፣ በቋንቋቸው የመማር፣ የመዳኘት፣ ወግና ባህላቸውን የማሳደግ፣ ተገቢውን ዕውቅናና ውክልና የማግኘት፣ ሀብት የማፍራት፣ ህገ – መንግስታዊ መብቶቻቸው እንዲከበር እንዲሁም ብሄራዊ ማንነት እና ሃገራዊ አንድነት ሳይነጣጠሉ እንዲጐለብቱ አበክረን እንሰራለን።

    1. የምንገኝበት ወቅት የ2ኛው የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዳችንን ማጠናቀቂያ ዋዜማ እንደመሆኑ በኢኮኖሚው ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግር ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችሉ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ለገበያ የሚያመርቱ አርብቶ እና አርሶ አደሮችና በመደገፍ፣ የመስኖ እና መሰል የግብርና ልማት ሥራዎችን በማፋጠን፣ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማትን በመደገፍ፣ በንግድ እና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት፣ ገቢ የመሰብሰብ አቅማችንን በማጠናከር የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ መፍጠር አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑ በጉባዔያችን ላይ በዝርዝር ታይቷል።

    በመሆኑም በገጠርም ሆነ በከተማ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ፣ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን የሚያጠናክሩ፣ የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር የሚያስችሉ፣ የመላውን ሕዝብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ዕውን የሚያደርጉ፣ በተለይም የወጣቶችንና የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ለመንቀሳቀስ ቃል እንገባለን።

    1. የቀሰቀስነው ለውጥ ተስፋ ሰጪ ውጤት እያስመዘገበ ያለው በሀገር ውስጥ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በውጭ ዲፕሎማሲ ዘርፍም ጭምር መሆኑን በዝርዝር የገመገምን ሲሆን ከጐረቤት ሀገሮች፤ በተለይም ከቀይ ባህር አካባቢ አገራት ጋር የፈጠርነው ትስስር ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበትና በምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር ሁነኛ ሚና የሚጫወት የሰላም፣ የትብብርና የአንድነት ተስፋ የፈጠረ ግንኙነት መሆኑ በዝርዝር የገመገምን ሲሆን የኢትዮ – ኤርትራ ግንኙነት መታደስ በቅድሚያ ሊጠቀስ የሚገባው መሆኑን፤ እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ተዘርግቶ የነበረው ጥቁር መጋረጃ መቀደዱን ስኬታማ የዲፕለማሲ ሥራ ውጤት መሆኑን እና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገምግመናል።

    በመሆኑም ከሁሉም አጐራባች ሀገራት የሚኖረን ግንኙነት የጋራ ጥቅሞቻችን እና የሕዝቦቻችን አንድነት የሚያጠናክሩ እንዲሆኑ በተለይም በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የሁለቱን ሀገራት ድንበር በተመለከተ መርህን በተከተለ፣ የሕዝባችንን አንድነት በማያናጋ እና መልካም ጉርብትናን አጠናክሮ ማስቀጠል በሚያስችል መልኩ እልባት እንዲያገኝ እንሰራለን።

    1. በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች አውዳሚ ግጭቶች፣ ሥርዓት አልበኝነት እና የህግ የበላይነትን የሚጥሱ ተግባራት ሲፈፀሙ ይስተዋላል። በስርዓተ አልበኝነት እና በመንጋ ፍትህ ምክንያት የዜጐች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚጣሱበት ነባራዊ ሁኔታ መኖሩን ጉባዔተኛው ገምግሟል።

    በመሆኑም ከዚህ ታሪካዊ ጉባዔ በኋላ ሃገራችን ሠላም የሠፈነባት፣ ዜጐች በነፃነት ተንቀሳቅሰው ያለ ስጋት የሚኖሩባት፣ የህግ የበላይነት የተከበረባት እንድትሆን፤ እንዲሁም ነፃነት ከህግ የበላይነት ውጪ ባርነት መሆኑን በመገንዘብ መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታውንም ጠንቅቆ የሚያውቅ ህብረተሰብ ለመገንባት በትጋት እንሠራለን።

    1. በአገር ደረጃ የተለኮሰው የተሃድሦ እንቅስቃሴ የበለጠ እየጠራ እንዲሄድ፣ መሪው ድርጅታችን ኢህአዴግ ብቃት ያለው አመራር መሥጠት አለበት። ስለሆነም ድርጅታችን መሠረታዊ ባህሪውን ጠብቆ በውስጡ ያለውን ችግር በሚገባ አጥርቶ እንዲወጣ የተለየ ትኩረት ሰጥቶት መሠራት እንደሚገባውም ተገምግሟል። ከዚህ አኳያ የኢህአዴግ አባል ብሔራዊ ድርጅቶች ባካሄዱት ጉባዔ አዳዲስ ምሁራን፣ ወጣቶችና ሴቶችን ወደ አመራር ቋት ማስገባት መቻላቸውም በጥንካሬ ተገምግሟል። ይህ የተጀመረው ድርጅታችንን የማጠናከር ሥራ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በብቃት ለመምራትና ሕዝቡን ለመካስ ቃል እንገባለን።

    የተከበራችሁ የድርጅታችን አባላት፦
    ድርጅታችሁ ኢህአዴግ በዚህ ታሪካዊ ጉባዔ ያለፉትን ድክመቶችን በዝርዝር ገምግሞና ፈትሾ የእርምት ዕርምጃ ለመውሰድና ጥንካሬዎቻችንን እንዲጐለብቱ ለማድረግ ያስችል ዘንድ የጀመርነው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና እንዳይቀለበስ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል። ስለሆነም በመላው ሀገራችን ተስፋ የተጣለበት ለውጥ እንዲቀጥልና የበለጠ እንዲጠናከር ግንባር ቀደም ሚና የመጫወት ታሪካዊ ኃላፊነት በትከሻችሁ ላይ የወደቀ መሆኑን በመገንዘብ ግንባር ቀደም ሚናችሁን እንድትጫወቱ ጥሪ እናቀርብላችኋለን።

    የተከበራችሁ የሀገራችን ወጣቶችና ሴቶች፦
    ድርጅታችን ኢህአዴግ የሀገራችን ወጣቶችና ሴቶች ለሰላም ለልማትና ለዴሞክራሲ መረጋገጥ ያላችሁ ሚና ተኪ የሌለው መሆኑን ከማመኑም በላይ ለውጡ የእናንተ መሆኑን ይገነዘባል። ኢህአዴግ የዛሬ ብቻ ሳይሆን የነገ ድርጅት በመሆኑ የጓጓችሁለትና መስዋዕትነት የከፈላችሁለት ለውጥ በአስተማማኝ ሁኔታ እውን እንዲሆን በማድረግ ለውጥ ለማምጣት ካደረጋችሁት ትግል እና ከከፈላችሁት መስዋዕትነት ባሻገር ለውጡን የመንከባከብና የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለባችሁ በመገንዘብ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ አስተዋይነትና ብልህነት በተላበሰ ሁኔታ እንድትንቀሳቀሱ ጥሪ እናስተላልፈላችኋለን።

    የተከበራችሁ የሀገራችን ምሁራን
    አሁን ሀገራችን የደረሰችበት የለውጥ ደረጃ የእናንተን ዕውቀት፣ ልምድና ችሎታ በከፍተኛ ሁኔታ ይፈልጋል። በመሆኑም የጀመርነው ለውጥ እንዲቀጥልና እንዲሳካ ጥናትና ምርምር በማድረግ እና ሳይንሳዊ ትንታኔ በመስጠት ያላችሁን ልምድ፣ ብቃት እና ተነሳሽነት ለወገናችሁ እንድታበረክቱ ጥሪ እናስተላልፍላችኋለን።

    የተከበራችሁ የአጋር ድርጅቶች
    በጉባዔያችን መክፈቻ ስነ – ስርዓት ላይ እንዳስተላለፋችሁት መልዕክት ሁሉ ኢህአዴግም ከእናንተ ጋር በመዋሀድ አንድ ሀገራዊ ፓርቲ በመሆን ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት እና የሚታገሉበት የጋራ መድረክ ይሆን ዘንድ የጥናት ሥራዎችን ተጀምረዋል። በመሆኑም እንደ አንድ ህብረ ብሄራዊና ሀገራዊ ድርጅት ለመንቀሳቀስ በሚያስችለን ህሊናዊና ነባራዊ ሁኔታ ላይ መሆናችንን እየገለጽን ለዚህ ዓላማ ስኬት ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

    የተከበራችሁ የተፎካካሪ ፓርቲዎች
    ምንም እንኳን የተለያየ የፖለቲካ አቋም ቢኖረንም የሀገራችን ሕዝቦች የመልማት፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ማረጋገጥ የጋራ አጀንዳዎቻችን መሆናቸውን በውል እንገነዘባለን። እስከ አሁን ባለው ጊዜ በጥላቻ እና በመጠፋፋት ፖለቲካ በመጠመዳችን እና በጠላትነት በመተያየታችን ብዙ ዕድሎች አምልጠውናል። ስለሆነም ወቅቱ የሚጠይቀውን የአንድነትና የአብሮነት መንፈስ በመተጋገዝ እና በመርህ ላይ የተመሠረተ ትግል በማድረግ ሀገራዊ ለውጡን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በሚደርገው ጥረት የበኩላችሁን ገንቢ ሚና እንድትጫወቱ ጥሪያችንን በአክብሮት ስናቀርብላችሁ የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያሰፉ ተቋማትን፣ አሠራሮችን እና አደረጃጀቶችን በማሻሻል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በቁርጠኝነት ለመሥራት የተዘጋጀን መሆናችንን እንገልፃለን።

    የተከበራችሁ የመንግስት ሠራተኞች
    የመንግስት ሠራተኛው አገልግሎታችንን የሚፈልገውን ህብረተሰብ በተገቢው ሁኔታ በማገልገል እርካታ ሊፈጥር የሚችል ታላቅ ኃይል መሆኑን እናምናለን። በመሆኑም የህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ እና ዕርካታ እንዲረጋገጥ በቅንነት፣ በታማኝነት እና በውጤታማነት በማገልገል ለውጡን ለማስቀጠል የበኩላችሁን ሚና እንድትወጡ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ እናስተላልፍላችኋለን።

    የተከበራችሁ የሀገራችን የፀጥታ አካላት፦
    የሀገራችንን ሕዝቦች ሰላምና ፀጥታ እንዲሁም ደህንነት ለማስከበር እስከአሁን ለሰራችሁት ሥራ እና ለከፈላችሁት መስዋዕትነት ታላቅ አክብሮት ያለን መሆኑን እየገለጽን ሀገራዊ ለውጡ በስኬት ግቡን እንዲመታ የሕዝቦችን ሰላምና የሕግ የበላይነትን የማስከበር ህገ-መንግስታዊ ግዴታችሁን በጽናት እንድትወጡ በአክብሮት ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

    የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች፦
    ኢህአዴግ በ11ኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባዔው ባለፉት ዓመታት ያስመዘገብናቸው ስኬቶች እንደተጠበቁ ሆነው ባላሟላናቸው ድክመቶች ምክንያት ቅሬታ የፈጠረባችሁና በዚህም ምክንያት በድርጅታችን ላይ ያላችሁ እምነት እየተሸረሸረ መምጣቱን ገምግሞ በእናንተ ቀስቃሽነትና በድርጅቱ መሪነት ተስፋ ሰጪ ለውጥ ላይ የምንገኝ መሆኑን በመገምገም ለውጡን ወደማይቀበለስበት ደረጃ የሚያደርሱ ታሪካዊ ውሳኔዎችን አስተላልፏል። ለሀገራዊ አንድነት፣ ለጋራ ብልጽግና፣ ለዘላቂ ሠላም መረጋገጥና የመደመር መርህዎችንና እሴቶችን ይዘን በጉባዔያችን ያስተላለፍናቸው ውሳኔዎች ዕውን እንዲሆኑ ሁለንተናዊ ተሳትፎአችሁና ድጋፋችሁ እንዳይለየን በታላቅ አክብሮት ጥሪአችንን እናስተላልፍላችኋለን።

    ሀገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና !!!
    ዘላለማዊ ክብር ለትግሉ ሰማዕታት!!
    መስከረም 25/2011
    ሐዋሳ

    የ11ኛ የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.