-
Search Results
-
72 ኪሎ ግራም የምትመዝነው ETRSS-1 ሳተላይት በቻይና መንግሥት ድጋፍና በኢትዮጵያ መንግሥት በጀት የተገነባች ሲሆን፥ ለግብርና፣ ለማዕድን ፍለጋ፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ ክትትል/ ምርምርና ለመሳሰሉት ጥቅም ላይ ትውላለች።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. (በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር) ላይ ከቻይና ዋና ከተማ ቤይጂንግ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው የቻይና ሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ ወደ ህዋ ትመጥቃለች። ጉዳዩን በማስመልከት የኢፌዴሪ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) እና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ጀነራል ዳይሬክተር ሰለሞን በላይ (ዶ/ር) ኅዳር 12 ቀን 2012 ዓም መግለጫ ሰጥተዋል። [ከአንድ ሳምንት በፊት ይህ ዜና በተዘገበበት ጊዜ ቀኑና ሰዓቱ ታህሳስ 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ከጠዋቱ 12 ሰዓት ከ21 ደቂቃ ተብሎ የነበረ ሲሆን vኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) በትዊተር ገጻቸው ቀኑ ወደ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. መዛወሩን አስታውቀዋል]።
ETRSS-1 የተሰኘችው ይህች ሳተላይት በቻይና መንግሥት ድጋፍና በኢትዮጵያ መንግሥት በጀት የተገነባች ሲሆን፥ ከቻይና መንግሥት የጠፈር ኤጀንሲ ጋር በትብብር የማምጠቅ ሥራው ይከናወናል። 72 ኪሎ ግራም (~159 ፓውንድ) የምትመዝነው ETRSS-1 ሳተላይት ለግብርና፣ ለማዕድን ፍለጋ፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ ክትትል/ ምርምርና ለመሳሰሉት ጥቅም ላይ ትውላለች።
መግለጫ በሚሰጡበት ጊዜ፥ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) ኢትዮጵያ የመጀመሪዋን ሳተላይት ለማምጠቅ ዝግጅቷን ማጠናቀቋ ወሳኝ ጊዜ ላይ እንደምትገኝ ማሳያ ነው ብለዋል። የሳተላይቷ ቁጥጥር ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን የዘርፉ ባለሙያዎች የሚከናወን እንደሚሆን ተናግረዋል። ይህንን ለማድረግም ከአዲስ አበባ ከተማ ወጣ ብሎ በተቋቋመው እንጦጦ ኦብዘርቫቶሪና የምርምር ማዕከል (Entoto Observatory and Research Center) ቅጥር ግቢ ውስጥ የመቆጣጠሪያ ጣቢያ ግንባታው ተጠናቅቋል። ይህ ጣቢያ የሳተላይቷ ደኅንነት ክትትል የሚደረግበትና ከሳተላይቷ የሚገኙ መረጃዎች የሚሰበሰቡበት ነው።
- Also read: Ethiopian plant breeders turn to a nuclear technique to help Teff farmers adapt to climate change
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ጀነራል ዳይሬክተር ሰለሞን በላይ (ዶ/ር) በበኩላቸው በሳተላይቷ ግንባታ ከንድፍ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች መሳተፋቸውንና በሀገር ውስጥ ከሚገኙም ሆነ ከውጭ አገራት ከመጡ ምሁራን እና ባለሙያዎች መካከል የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር የተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል።
ETRSS-1 ሳተላይት ከተወነጨፈች በግማሽ ሰዓት ውስጥ ከመሬት 700 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ህዋ ላይ ቦታዋን ትይዛለች። የሳተላይቷ ግንባታ 2008 ዓ.ም. ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ የተፈረመና 2009 ዓ.ም. ላይ የተጀመረ ነው።
የሳተላይቷ መምጠቅ ኢትዮጵያ ለሳተላይት ምስል ግዢ በዓመት የምታወጣውን ከ350 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የሚያስቀር ነው።
ምንጭ፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አማካኝነት የተሠራው ለእርሻ አገልግሎት የሚውል ባለሞተር ማረሻ ተመረቀ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያን (ዶ/ር ኢንጂ.) ጨምሮ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የሮዳ ኢንጂነሪን ሠራተኞች በተገኙበት ተመርቋል።
ከዚህ ቀደም ከውጭ ሀገራት የአርሶ አደሩን ድካም ያቃልላሉ ተብለው የተገዙ ዘመናዊ የማረሻ መሣሪያዎች ከሀገራችን ድንጋያማ መሬት ጋር ባለመስማማታቸው የሚጠበቅባቸውን ጥቅም ሳይሰጡ በ አጭር ጊዜ ውስጥ ከጥቅም ውጭ ይውላሉ። ይህ በኢትዮፕያውያን ዲዛይን ተደርጎ የተሠራው ባለሞተር ማረሻ ግን ለሀገራችን መሬት ተስማሚ እንዲሆን ተደርጎ የተሠራ ነው።
ማረሻው ከተገጠመለት ሞተር ውጪ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተሠራ በመሆኑ ለጥገና፣ ማሻሻያ ለማድረግና ተጨማሪ ጥቅሞችን ለመጨመር የተመቸ መሆኑን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በቀጣይ በዚሁ ባለሞተር ማረሻ ላይ አርሶ አደሩ ተቀምጦ የሚያርስበት፣ መሬቱን ለመጎልጎል የሚያስችል፣ ምርቱን ማረሻው ላይ ለመጫን የሚያስችሉ አዳዲስ ግልጋሎቶችን እንዲሰጥ ተደርጎ እንደሚዘምን የሮዳ ኢንጂነሪን ባለቤት አቶ አክሊሉ አባተ ተናግረዋል። ማጨድና መውቃት፣ እንዲሁም ምርት መሰብሰብ የሚችል መጎታችም በቀጣይ እንደሚሠራለት ተጠቁሟል። አርሶ አደሩ በቀላሉ ነዳጅ ማግኘት እንዲችል ከእፀዋት ተረፈ ምርት መሠራት የሚችል ባዮፊዩል (biofuel) እንዲጠቀምም ይደረጋል።
አርሶ አደሮቻንን እስከ ዛሬ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ አላደርግናቸውም ያሉት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) በቀጣይ ችግሮቻቸውን የሚያቃልሉ ቴክኖሎጂዎችን ማላመድና መፍጠር ላይ በትኩረት እንሠራለን ብለዋል። አክለውም፥ ባለሞተር ማረሻውን አርሶ አደሮች የመግዛት አቅም ኖሯቸው እንዲጠቀሙበት ለማድረግም ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በትብብር ይሠራል ነው ያሉት።
ባለሞተር ማረሻውን ከማዘመንና ጠጨማሪ አገልግሎቶችን አንዲያረክት ማሻሻያዎችን ከማድረግ በተጨማሪ ዋጋውም ከጥንድ በሬዎች መግዣ ባነሰ ዋጋ አርሶ አደሩ እጅ እንዲገባ ጥረት ይደረጋል ተብሏል። ባለሞተር ማረሻው በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና በሮዳ ኢንጂነሪንግ ትብብር የተሠራ ነው።
ምንጭ፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- በአዲስ አበባ “ለሁሉ” የክፍያ ማዕከላት ተገልጋዮች መጉላላት እየገጠማቸው ነው
- የሴቶችን ጫና የሚያቃልሉ የተወሰኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባሉ
- የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሮኒክ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ) ማዕከል ኢትዮጵያ ውስጥ ሊገነባ ነው
- የወልድያ ዩኒቨርሲቲ እና ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ በትብብር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የትምህርት መስክ ሊጀምሩ ነው
- ቮልስዋገን በኢትዮጵያ የመኪና መገጥጠሚያ ፋብሪካ ሊገነባ ነው፤ የጀርመን የቴክኖሎጂ ድርጅቶች በስፋት ለመግባት እያመቻቹ ነው
የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ከስዊድኑ ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ (The University of Gothenburg) ጋር በትብብር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤን የሚመለከት ትምህርት ለመስጠት የሚያስችላቸው የመግባቢያ ሰነድ ይፈርማሉ።
በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ መስክ በሀገራችን ያለውን የባለሙያ እጥረት የሚቀርፍ መነሻ ሀሳብ ከስዊድን ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ የመጡ መምህራን ለክቡራን ሚንስትሮች ገለፃ አድርገዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ሀገራችን ኢትዮጵያ ከስዊድን መንግስት ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑ በተለይ በኪነ-ሕንፃ ትህምርት ዘርፍ ያላቸው ልምዶች ታሪካዊና ጠናካራ ግንኙነት የተፈጠረበት መሆኑ ብዙ ይወሳል።
በመሆኑም የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ስዊድን ውስጥ በትልቅነቱ ሁለተኛ ከሆነው ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ (The University of Gothenburg) ጋር በትብብር ለመክፈት ያሰበው የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ እውን እንዲሆንና የቅርስ ጥገና ተግባራዊ ትምህርት በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ እንዲሰጥ ታስቦ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በኩል ቅድመ ዝግጅት መጀመሩን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አርኪዮሎጂ (archeology) ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶ/ር መንግስቱ ጎበዜ፥ የታሰበው የትምህርት መርሀግብር ለክቡራን ሚኒስትሮች (ለፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፥ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እና ለወ/ሮ ብዙነሽ መሠረት፥ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ) የሥልጠናውን ዓላማና ግብ የሚያግባባ ገለፃና ትውውቅ አድርገውላቸዋል።
በመቀጠልም በልዑካኑ በስዊድን ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ በኩል የመጡት መምህራን ያላቸውን ዝግጁነትና ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲሁም የገጠሩ ሕዝብ ባህላዊ ሀብቱን እየተወ ወደ ከተማ ከሚኮበልል እዛው በቅርሱ ተጠቃሚ የሚሆንበት መሠረት የጣለ ልምድ መኖሩን የሚያብራራ ገለጻ በ‘Bosse Lagerqvist’ እና ‘Lars Runnquist’ የልዑኩን ቡድ ኑን በመወከል ገለፃ አደርገዋል። ተመራማሪ ፕሮፌሰሮች በነሱ በኩል ተግባራዊ ትምህርቱ ከቁሰቁስ አቅርቦት እንደሚደገፍ ጭምር በትብብር የሚሠራበት ሁኔታ ለመፍጠር በቻርትና ስዕላዊ መግለጫዎች ማብራሪያ አድርገዋል።
◌ ሰባት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና STEMpower ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ
ለመርሀግሩ ማጠቃለያ ክቡራን ሚኒስትሮችም በበኩላቸው በሁለቱም ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት መልካም በሚባል ደረጃ የደረሰ መሆኑን በማመስገን፥ ያቀረባችሁት ሀሳብ የሚጠቅመንና እንደኢትዮጵያ በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ መስክ የሚሰጡ ትምህርቶች በንድፈ-ሀሳብ ብቻ በመሆኑ በትብብር ስለምንሠራው ብዙ ባለሙያዎችን የምናፈራበት ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
የትምህርት ማስተማሪያ መርሀግብሩ የሁለተኛ ዲግሪ ለመስጠት የሚያበቃ ሲሆን፥ ለዚህ የመግባቢያ ሰነድ በቅርብ ጊዜ እንደሚፈረም እንዲሁም ተግባራዊ ትምህርቱ የሚሰጥበት ቦታ አንድ ካምፓስ በላሊበላ ቅርጫፍ የሚዘጋጅበት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
ምንጭ፦ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ልዑካን ቡድን አባላት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን በሙያቸው እንዲያግዙ ጥሪ ማቅረባቸውን ተክተሎ የመጡ ናቸው።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሲካሄድ የቆየው መንግስት ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ያለውን ዝግጁነት የሚለይና ለችግሮች የመፍትሄ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ አውደ-ጥናት ተጠናቀቀ።
በአውደ ጥናቱ የመንግስት አግልግሎት አሰጣጥ፣ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ያለው ዝግጁነት፣ የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት ክፍተት ተለይተውበታል – ሚኒስቴሩ እንደዘገበው።
የጤና አስተዳደር፣ የታክስ አሰባሰብ ስርዓት፣ የመረጃ ግንኙነት (ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን) ቴክኖሎጂ ደኅንነት፣ በባንክ አገልግሎት፣ በኢንሹራንስ አገልግሎት፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኦዲት አገልግሎት፣ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት፣ የውሃ አወጋገድ ላይ ክፍተቶች ተለይተዋል።
አሜሪካ ውስጥ ቨርጂንያ ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ (Virginia International University; Fairfax, VA) መምህር በሆኑት ዶ/ር ተፈራ በየነ የተመራው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ልዑክ ክፍተቶቹን ከለዩ በኋላ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።
◌ ከ7ሺህ 800 በላይ አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች በመላው አገሪቱ ሊቋቋሙ ነው
ባለሙያዎቹ በኢንሹራንስ፣ በህክምና ቴክኖሎጂ፣ በዲፕሎማሲ፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኑኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ በአሜሪካን ሀገር በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ኢትዮጵያዊያን ናቸው።
ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የፋይናንስ ዳይሬክተሮች እና ሌሎችም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት ከቡድኑ ጋር ለ1 ሳምንት ክፍተቶችን እና ጉድለቶችን የመለየት ሥራ ሲሠሩ ቆይተዋል።
የሚመለከታቸው አካላት በየዘርፉ የሚደረጉ ማስተካከያዎችን በኃላፊነት ወስደው ወደ ተግባር የመቀየር ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። በማጠቃለያው ላይ፥ ልዑካኑ የኢትዮጵያ መንግስት ወይም የሚመለከተው መንግስታዊ ተቋም ዕድሉን ከሰጠን የሀገራችንን ችግር ለመፍታት በቂ አቅም አለን ብለዋል። ወደፊትም በማንኛውም መልኩ ሀገራቸውን ለማገዝ ቃል ገብተዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታዎች ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) እና ጀማል በከር ልዑካኑ ሀገራቸውን ለመረዳት ያላቸውን ቁርጠኝነት በማድነቅ ምስጋና አቅርበዋል።
የልዑካን ቡድኑ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን በሙያቸው እንዲያግዙ ጥሪ ማቅረባቸውን ተክተሎ የመጡ ናቸው።
ምንጭ፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
- በዳያስፖራ ትረስት ፈንድ እስካሁን ድረስ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ተሰብስቧል
- ኢትዮጵያ በአሜሪካ ሁለተኛ ቆንስላ አጠቃላይ ጽህፈት ቤት በሚኒሶታ ግዛት ከፈተች
- የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ መቋቋሙን ተከትሎ ወደ ተግባር ለመግባት የመዋቅርና የሕግ ማዕቀፍ ሥራን አጠናቀቀ
- ሰባት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና STEMpower ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ
- ለዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥናትና ምርምር ማድረግ አስገዳጅ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ፤ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ይጀመራል
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሴቶችን ጫና በሚያቀልሉ ቴክኖሎጂዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ መሆኑን የሚኒስቴሩ የሴቶች፤ ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ገብረሥላሴ አስታውቀዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በ7 ክልሎች ውስጥ በቴክኖሎጂ ውጤቶች ሊደገፉ የሚችሉ ሴቶች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ ያሉ ሥራዎችን በጥናት ለይቷል።
ችግሮቹ የተለዩት በአፋር፤ በቤኒሻንጉል፤ በጋምቤላ፤ በደቡብ፤ በአማራ፤ በትግራይና በሶማሌ ክልል በተጠናው ጥናት መሠረት መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
በፀሐይ ኃይል የሚሠራ የምግብ ማብሰያ፤ በሬ ለምኔ ዘመናዊ ማረሻ እና የቆጮ መፋቂያ ማሽን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ተገልጿል። ዘመናዊ የበቆሎ መፈልፈያና የአፋ አሊ (የአፋር ቤት) መሥሪያ በመካከለኛ ጊዜ ወደ ሥራ ለማስገባት የታቀደ ሲሆን በመስመር መዝሪያ እና ከጉድጓድ ውሃ ማውጫ መሣሪያ ደግሞ በረጅም ጊዜ ወደ ሥራ ለማስገባት በዕቅድ ተይዟል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሴቶችን ጫና በሚያቀልሉ ቴክኖሎጂዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው። የሚኒሰቴሩ የሴቶች፤ ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ገብረሥላሴ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሴቶችን የሥራ ጫና የሚያቃልሉና ምርታማ የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎች ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ለስኬታማነቱ የሚመለከታቸው ሁሉ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉም ዳይሬክተሯ ጥሪ አቅርበዋል።
ምንጭ፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሮኒክ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ) ማዕከል ኢትዮጵያ ውስጥ ሊገነባ ነው
- ቤልካሽ ኢትዮጵያ ሄሎማርኬት እና ሄሎሾፕ የተሰኙ ሁለት የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ገፆችን ሊያስጀምር ነው
- ገበያ የተባለው የግል ድርጅት እና የኢኖቬሽንና ቴክሎጂ ሚኒስቴር ተባብረው ለመሥራት ስምምነት ተፈራረሙ
- ሁለተኛው SolveIT ሀገር አቀፍ የፈጠራ ውድድር (የኢዲስ አበባ ከተማን) በይፋ ተጀመረ ― የአሜሪካ ኢምባሲ
- ቮልስዋገን በኢትዮጵያ የመኪና መገጥጠሚያ ፋብሪካ ሊገነባ ነው፤ የጀርመን የቴክኖሎጂ ድርጅቶች በስፋት ለመግባት እያመቻቹ ነው
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አልማዝ አፈራ በዚህ ፕሮጀክት የተሳተፉ ተመራማሪዎችን ያሉትን ተግዳሮቶች ተቋቁመው ለዚህ በመብቃታቸው ምስጋና ቸረዋቸዋል።
ደብረ ብርሃን (ሰሞነኛ)– የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ከኢፌዴሪ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ ይምሎ ቀበሌ በተቀናጀ የአሳ፣ የዶሮ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ ሲያካሂድ የቆየውን የምርምር ፕሮጀክት አጠናቆ ለዞኑ አስተዳደርና ለአካበቢው ማኅበረሰብ አስረከበ።
በርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ወቅት የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ መምህርና መሪ ተመራማሪ ዶ/ር ገዛኸኝ ደግፌ እንደተናገሩት ምርምሩ በትንሽ ቦታ አሳን፣ ዶሮንና አትክልትን አቀናጅቶ ማልማት የሚያስችል የቴክኖሎጅ ዕውቀትን በመጠቀም የአሳ፣ የዶሮና የአትክልት ልማቱን አቀናጅቶ መሥራት እንደሚቻል ነው ብለዋል። በዚህም የዶሮ ኩስን ለአሳዎች ምግብ እንዲውል እንዲሁም “vermicompost” ቆሻሻን ወደ ጠቃሚ ነገርነትና ማዳበሪያነት የሚቀይሩ ትሎችን ለዶሮዎችና ለአሳ ምግብነት እንዲውል የሚያስችል እንደሆነ አብራርተዋል።
◌ በምስራቅ ጎጃም ዞን ስንዴ አምራች ወረዳዎች ለገበሬዎች የቀረቡላቸው ኮምባይነሮች በምርታቸው ላይ ጉልህ አስተዋጽዖ እያደረጉ ነው
አቶ ተፈራ ወንድማገኘሁ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳደሪ እንዳሉት ይህ ለምርቃት የበቃው የምርምር ሥራ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በዞኑ ከሚያከናውናቸው ምርምሮች አንዱ ሲሆን ፣ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፈጻሚነትና በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የገንዘብ ድጋፍ የተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ዋና አስተዳዳሪው አክለው እንዳስታወቁት ይህንን ምርምር በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ለማስፋፋት ትልቅ ኃላፊነትና አደራ የተጣለባቸው መሆኑን አውስተው ለተግባራዊነቱም እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ ባደረጉት ንግግር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ከሚደግፋቸው በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በሚባል ደረጃ ከ60 በላይ ምርምሮች መካከል የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ አንዱና ውጤታማው በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ በሚችሉ ትናንሽ ፕሮጀክቶች በመደገፍ የሀገራችንን ልማት ማረጋገጥ ይኖርብናል ብለዋል። ይህን ፕሮጀከት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች እንዲተላለፍ ማኑዋልና ስታንዳርድ ተዘጋጅቷል። የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደርም በአማራ ክልል ለሚገኙ ሁሉም ዞኖች እንዲያደርስ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሲሆን በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሰራጭ አናደርጋለን ብለዋል።
ዶ/ር አልማዝ አፈራ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት በበኩላቸው በዚህ ፕሮጀክት የተሳተፉ ተመራማሪዎችን ያሉትን ተግዳሮቶች ተቋቁመው ለዚህ በመብቃታቸው ምስጋና ቸረዋቸዋል። እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለፃ፥ በሀገራችን እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ሥራ-አጥ ወጣቶች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን እንደነዚህ ዓይነት የምርምር ሥራዎች ደግሞ ወጣቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ በማድረግ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል። ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲም ብዙ የምርምር ውጤቶች ያሉት ሲሆን እነዚህን ምርምሮች ወደ ፕሮጀክት መቀየር የሚያስችል ተሞክሮ ስለሆነ ይህ ትልቅ ማሳያ ይሆነናል ብለዋል። በመጨረሻም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርንና የኤፍራታና ግድም ወረዳ አስተዳደርን ላደረጉት ድጋፍና ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።
ምንጭ፦ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በ”ለሁሉ” የተለያዩ የክፍያ ማዕከላት የውሃ፣ መብራትና ስልክ ክፍያ ለመፈጸም ሄደው መጉላላት እየገጠማቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪች ገለጹ።
በአዲስ አበባ 34 የሚሆኑ የውሃ፣ የመብራት፣ የስልክና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ “ለሁሉ” ማዕከላት ያሉ ቢሆንም ሰሞኑን በአገልግሎት ፈላጊዎች ወረፋ ተጨናንቀዋል። ተገልጋዮቹ የወርሃዊ ክፍያቸውን ለመፈጸም ረዥም ሰልፍ በመያዝ እንግልትና መስተጓጎል እየገጠማቸው መሆኑንም ገልፀዋል።
የኢዜአ ጋዜጠኛም ከ”ለሁሉ” አገልግሎት መስጫ ማዕከላት መካከል በፒያሳ ጊዮርጊስ፣ በአራት ኪሎና ለገሃር አካባቢ በሚገኙ የክፍያ ማዕከላት ተዘዋውሮ ችግሩ መኖሩን ተመልክቷል።
አራት ኪሎ በሚገኘው የክፍያ ማዕከል የተገኙት ወይዘሮ አስካለ ኃይሌ እንደሚሉት ከተወሰኑ ወራት ወዲህ በከተማዋ ባሉ ብዙ የክፍያ ማዕከላት ወረፋና መጉላላት ተባብሷል።
◌ VIDEO: The newly established i-Pro Mobile Assembly Company in Dessie struggling to get building
በአራት ኪሎ የ”ለሁሉ” የክፍያ ማዕከል ክፍያ ለመፈጸም የተገኙት ወ/ሮ ኤልሳቤት ግርማም በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እንዳላቸው ነግረውናል።
በአራዳ ክፍለ ከተማ ኢትዮ-ቴሌኮም ጊቢ ውስጥ በሚገኘው “ለሁሉ” የክፍያ ማዕከል ክፍያ ለመፈጸም የተገኙ ተገልጋዮችም በመስተጓጎላቸው ምሬታቸውን ገልፀውልናል።
ከጉለሌ ክፍለ ከተማ የመጡት ወ/ሮ ብስኩት ይጥና እና አቶ መስፍን ተገነውም የውሃና መብራት ክፍያ ለመፈጸም ማልደው ቢገኙም አገልግሎቱን ማግኘት እንዳልቻሉ ገልፀውልናል።
አገልግሎት የሚሰጡ ሰራተኞች በቁጥር ጥቂት መሆናቸውና “ሲስተም የለም በማለት”፣ ከፍተኛ መጨናነቅ እየተፈጠረ መሆኑንም ጭምር ተገልጋዮቹ ገልፀዋል።
በመሆኑም “ክፍያውን የሚያስፈጽሙልን አካላት ከቴክኖሎጂ ጋር በተጣመረ ቅልጥፍና ሊያስተናግዱን ይገባል” በማለትም ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
ካነጋገርናቸው ተገልጋዮች መካከል ለሦስት ቀናትና ከዚያ በላይ ክፍያ ለመፈጸም እንደተመላለሱ ጠቅሰው ለችግሩ የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሄ እንዲያበጅላቸው የጠየቁም አሉ።
በፒያሳ ጊዮርጊስ አካባቢ የሚገኘው “ለሁሉ” ማዕከል ኃላፊ ወ/ሮ ጽዮን ዮሃንስን እንዲሁም የአራት ኪሎ ክፍያ ማዕከል ሃላፊ ወ/ሮ ወይንሸት ገብረጻዲቅ ችግሩ መኖሩን አምነዋል። ወ/ሮ ጽዮን እንደሚሉት ችግሩ የተፈጠረው ሌላኛው የአራዳ የክፍያ ማዕከል ዝግ በመሆኑ ነው።
እንደ ወ/ሮ ወይንሸት ገለፃ ህብረተሰቡ በጊዜ የመክፈል ልማድ ስለሌለው ወደ መጨረሻው ቀን ክፍያው በሚፈጽምበት ወቅት አንዲህ ያለው መጨናነቅ ይፈጠራል ብለዋል።
ኢዜአ በ”ለሁሉ” የክፍያ መፈጸሚያ ዋና መሥሪያ ቤት በመገኘት ከኃላፊዎች ምላሽ ለማግኘት ቢሞክርም “ከቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ፍቃድ ያስፈልጋል” በማለት መላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሮኒክ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ) ማዕከል ኢትዮጵያ ውስጥ ሊገነባ ነው
- ቤልካሽ ኢትዮጵያ ሄሎማርኬት እና ሄሎሾፕ የተሰኙ ሁለት የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ገፆችን ሊያስጀምር ነው
- ገበያ የተባለው የግል ድርጅት እና የኢኖቬሽንና ቴክሎጂ ሚኒስቴር ተባብረው ለመሥራት ስምምነት ተፈራረሙ
- ሁለተኛው SolveIT ሀገር አቀፍ የፈጠራ ውድድር (የኢዲስ አበባ ከተማን) በይፋ ተጀመረ ― የአሜሪካ ኢምባሲ
- ቮልስዋገን በኢትዮጵያ የመኪና መገጥጠሚያ ፋብሪካ ሊገነባ ነው፤ የጀርመን የቴክኖሎጂ ድርጅቶች በስፋት ለመግባት እያመቻቹ ነው
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የአሜሪካ ኢምባሲ 2ኛውን ‹‹SolveIT›› የተሰኘ ሀገር አቀፍ የፈጠራ ውድድርን የኢዲስ አበባ ከተማን በይፋ አስጀመረ። ኢምባሲው ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከጃፓን ዓለማቀፋዊ ኮኦፐሬቲቭ ኤጀንሲ (Japan International Cooperation Agency – JICA) እና ከአይኮግ ላብስ (iCog Labs) ጋር በመተባር ነው ውድድሩን ይፋ ያደረገው።
ፕሮጀክቱ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 15 ከተሞች የሚካሄድ ሲሆን ቴክኖሎጂ ነክ የፈጠራ ሥራዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው።
ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂ ነክ የፈጠራ ሰራዎች ያሏቸው ወጣቶች የሚሳተፉበት ይህ ውድድር የፈጠራ ባላሙያዎቹ ሥራዎቻቸውን ሊያዳብር የሚችል ስልጠና በየከተሞቹ ይሰጣቸዋል።SolveIT ሀገር አቀፍ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድርን የአሜሪካ ኢምባሲና የጃፓን ዓለማቀፋዊ ኮኦፐሬቲቭ ኤጀንሲ ፕሮጀክቱን በገንዘብ ይደግፉታል። ተመሳሳይ ፕሮግራሞች በየከተሞቹ የሚዘጋጁ ሲሆን የተመረጡ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎች ለሽልማት ይበቃሉ ተብሏል።
◌ VIDEO: These two Ethiopian students are working to launch their own rocket – the future Eng. Kitaw Ejigu
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽን ልማትና ምርምርና ዘርፍ ዳይሬክተር ጀነራል ካህሊድ አህመድ (ዶ/ር) በፕሮጀክቱ ተመርጠው የመጡ የፈጠራ ሥራዎች ገበያውን እንዲቀላቀሉ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
ተጨማሪ ስልጠና የሚያስፈልጋቸውን በቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ማዕከላት በማስገባትና የሥራ ማስጀመሪያ ገንዘብ በመደጎም ጭምር ድጋፍ እንደሚያደረግ አረጋግጠዋል።
የአሜሪካ ኤምባሲ በኢትዮጵያ በዋናነት ስፖንሰር የሚያደርገው SolveIT ውድድር በወጣት ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የኢንጂነሪንግ፣ የአርት እና የሒሳብ (STEAM) በወጣቶች ዘንድ ይበልጥ እንዲጎለብቱ የሚያበረታታ ውድድር ሲሆን ፥ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ለሚኖሩበት ህብረተሰብ፣ ብሎም ለሀገራቸው ችግር ፈቺ የሆኑ የቴክኖሎጂ፣ የሶፍትዌርና የሀርድዌር ፈጠራዎችን በመፍጠር እንዲሳተፉ ያደርጋል።
ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 28 ዓመት የሆነ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በሚኖሩበት ከተማ ሆነው ህብረተሰባቸው የሚያጋጥመውን ችግር ሊፈታ የሚፍል ፈጠራ ለመፍጠር ለዘጠኝ ወራት ያህል ጊዜ ተሰጥቷቸው ይሠራሉ። በዚህም ጊዜ ከአወዳዳሪዎች በተመደቡላቸው ባለሙያዎች ስልጠና ይሰጣቸዋል። ፈጠራዎቻቸው ከሞባይ አፕ (mobile app) ጀምሮ እስከ ከፍ ያለ የኮምፒዩተር ሶፍትዌር ሊሆን ይችላል። በከተሞቻቸው (በክሎቻቸው) አሸናፊ የሆኑ ተወዳዳሪዎች ከፍ ወዳለው (የፌደራል) ውድድር ያልፋሉ፤ በዚያም ለሳምንት ያህል በዳኞች ና በከፈተኛ ኤክስፐሮች እየተዳኙ ይወዳደራሉ። በዚህም የመጨረሻዎቹ አሸናፊዎች ይለያሉ።
በአሁኑ ጊዜ ተወዳዳሪዎችን እየተቀበለ ይገኛል። የበለጠ መረጃ የአይኮግ ላብስ (iCog Labs) ድረ ገጽ ላይ ማግኘት ሲችሉ (እዚህ ጋር ይጫኑ)፥ መመዝገቢያውን ደግሞ እዚህ ጋር ያገኙታል (Register)።
ምንጭ፦ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለተወሰነ ጊዜ ተዘጋ
- ራይድ የተባለዉ የታክሲ አገልግሎት ድርጅት የስም ማጥፋት ዘመቻ እና ጥቃት ደርሶብኛል በማለት ወቀሰ
- ቤልካሽ ኢትዮጵያ ሄሎማርኬት እና ሄሎሾፕ የተሰኙ ሁለት የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ገፆችን ሊያስጀምር ነው
- ገበያ የተባለው የግል ድርጅት እና የኢኖቬሽንና ቴክሎጂ ሚኒስቴር ተባብረው ለመሥራት ስምምነት ተፈራረሙ
- ኬር ኢትዮጵያ በ7 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ወጭ ያስገነባውን የምርምርና የስልጠና ማዕከል ለሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አስረከበ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– ግዙፉ የመኪና አምራች የሆነው የጀርመኑ ኩባንያ ቮልስዋገን በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ፈረመ። ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አበባ አበባየሁ እና ከሰሃራ በታች የኩባንያው የአፍሪካ ቀጣና ሥራ አስፈጻሚ ቶማስ ሻፈር ተፈራርመዋል። በስምምነቱ መሠረትም ኩባንያው የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ መክፈት፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫ ዕቃዎችን ማቅረብ፣ የስልጠና ማዕከል መክፈት እና ተጓዳኝ ሥራዎችን ይሠራል።
በስምምነቱ ላይ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ላይ የሚገኙት የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ዋልተር ስታይንማየር እና የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ተገኝተዋል።
ቮልስዋገን ኩባንያ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት መካከል ኢትዮጵያን የማስፋፊያ ማዕከሉ አድርጎ ሲመርጥ፣ ከኩባንያው ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈረም ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ኢትዮጵያ ሦስተኛዋ አገር (ከጋና እና ናይጄሪያ ቀጥሎ) ሆናለች።
◌ VIDEO: የጀርመኑ ግዙፍ የመኪና አምራች ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊ ኢንቨስትመንት ለመጀመር እየተንቀሳቀሰ ነው
ኩባንያው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለመሥራት መስማማቱ በቀጥታ የእሴት ሰንሰለት የተቀናጀ የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ክላስተር ለመፍጠር ወሳኝ ምዕራፍ ይከፍታል ነው የተባለው።
ኮሚሽነር አበበ አበባየሁ በፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት መንግሥት አገሪቷን ቀዳሚ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ነው።
”በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪው መስክ ልዩ ክላስተር እንዲመሠረት መንግሥት ያለሰለሰ ጥረት ያደርጋል” ያሉት ኮሚሽነሩ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ቮልስዋገንን ጨምሮ ፍላጎት ካላቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ‘ዝግጁ ነው’ ብለዋል።
◌ VIDEO: German companies including Volkswagen and Siemens embarking to invest in Ethiopia
የኩባንያው የአፍሪካ ቀጣና ሥራ አስፈጻሚ ቶማስ ሻፈር በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ለአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪው እድገት ትኩረት መስጠቱ ‘የሚደነቅ ነው’ ሲሉ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ቶማስ ሻፈር ‘ኢትዮጵያ ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ላይ ያለች እና በሕዝብ ብዛትም ከ አህሪካ አገራት በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠች በመሆኗ፥ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ለመስፋፋት በምናደርገው ጥረት ኢትዮጵያን ሁነኛ ተመራጭ አገር አድርገናታል፤ በተጨማሪም ቮልስዋገን ኩባንያ ሀገሪቱ ያላትን የስትራቴጂ ጥቅም ከግምት በማስገባት በ አውቶሞቲቭ ዘርፍ ከፍትኛ እድገት እንድታስመዘግብ ይተጋል’ ብለዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የጀርመን የቢዝነስ ልኡካን ቡድን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሥራ ሃላፊዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ በሚሰማሩበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
ሲመንስ የተሰኘው በግዙግነቱ ከአውሮፓ ኩባንያዎች ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው የጀርመን የቴክኖሎጂ ኩባንያ በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ሲሠራቸው ከነበሩ የቴክሎጂ ዘርፍ ሥራዎች በተጨማሪ በተጠናከረ መልኩ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አሳውቋል።
◌ NEWS: German automaker Volkswagen develops automotive industry in Ethiopia
የጀርመን የቴክኖሎጂ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ማኅበርም ቢሮውን አዲስ አበባ በመክፈት ወደ ሥራ ለመግባት ፍቃደኛ መሆኑን አሳውቋል። ማኅበሩ ጀርመን ውስጥ ያሉ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ማኅበር እንደመሆኑ ድርጅቶቹ በመስኩ ለመሰማራት የሚያስችላቸውን ሁኔታ ለማመቻቸት መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥር ይታመናል።
በኢትዮጵያ መንግስት በኩል በጊዜያዊነት በነፃ ቢሮ በመስጠት ጭምር ማንኛውንም እገዛ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑንም ተገልጿል።
የልኡካን ቡድኑ አባላት በኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ድርጅቶች ከምንዛሬ እጥረት፣ በደላላ ምክንንያት ምርቶቻቸው ተጠቃሚው ጋር በተጋነነ ዋጋ መድረስ የመሳሰሉ ችግሮች እንደገጠሟቸው ተናግረዋል።የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ለመጀመር ሥራዎች እየተሰሩ በመሆኑ ወደ ሥራ ሲገባ ችግሩ እንደሚቀረፍ ተናግረዋል።
ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ቤልካሽ ኢትዮጵያ የሚያስጀምራቸው ሄሎማርኬት እና ሄሎሾፕ የተሰኙ ሁለት የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ገፆች በኢትዮጵያ ውስጥ እና ከኢትዮጵያ ውጪ ለሚገኙ ተገልጋዮች ኢንተርኔት አማካኝነት ግብይት መፈም የሚችሉባቸው ናቸው።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ቤልካሽ ኢትዮጵያ ተጠቃሚዎች በበይነመረብ (ኢንተርኔት) አማካኝነት ግብይት መፈም የሚችሉባቸው ሁለት የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ገፆችን በቅርቡ እንደሚያስጀምር አስታወቀ።
ሄሎማርኬት (Hellomarket) የተሰኘው ገፅ በዋነኛነት በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ተገልጋዮቹ ብቻ ካሉበት ቦታ ሆነው ቁሳቁሶችን የሚሸምቱበት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በበይነመረብ አማካኝነት የግዥ ትዕዛዝ እና ክፍያ የተፈፀመባቸው ቁሳቁሶቹን ወደ ደምበኞች ለማጓጓዝም ከ ዓለምአቀፉ ዲኤችኤል (DHL) ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።
◌ The dispute between RIDE Taxi, Ethiopian-kind of Uber, and Addis Ababa Transport Authority continues
ተቋሙ በመጀመርያው ምዕራፍ ወደ 2,500 የሚጠጉ ሴት ኢትዮጵያውያን በባለቤትነት በሚያስተዳድሩዋቸው የተለያዩ ድርጅቶች የተመረቱ ምርቶችን ለማሻሻጥ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቋል።
በተመሳሰይ ቤልካሽ ከኢትዮጵያ ውጭ ሆነው የኤሌክትሮኒክ ግብይት መፈፀም ለሚፈልጉ ደንበኞቹ አገልግሎት የሚሰጥ ሄሎሾፕ (Helloshop) የተሰኘ ሌላ ገፅ ያዘጋጀ ሲሆን የክፍያ ስርዓቱም በማስተር ካርድ አማካኝነት አንደሚከወን ለማወቅ ተችሏል።
◌ Ethiopia – blueMoon Incubator and Addis Garage co-working space for startups in Ethiopia
ቤልካሽ ኢትዮጵያ መቀመጫውን ኔዘርላንድ ባደረገው እና ቤልካሽ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን (Belcash Technology Solutions) የተሰኘ በኤሌክትሮኒክ ክፍያ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ የተሰማራ ድርጅት እህት ኩባንያ ሲሆን እ.ኤ.አ ከ2011 ጀምሮ በኢትዮጵያ በተለይም በሞባይል ክፍያ እና የገንዘብ ማስተላለፍ ዘርፎች ላይ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ከኩባንያው ድረገፅ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ሥርዓት በተገቢው አለመስፋፋት እና በዚህ ዘርፍ ላይ ግልፅ የሆኑ ፖሊሲዎችን አለመኖራቸው በኢትዮጵያ መሰል የኤሌክተሮኒክ ግብይት ተቋማት እንዳይስፋፉ እንቅፋት መሆኑን ባለሞያተኞች ይገልፃሉ።
ከዚህ ዜና ጋር በተመሳሳይ የቻይናው ግዙፉ የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ (e-commerce) አሊባባ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ ለመሥራት ፍላጎት እንዳለውና ከኢትዮጵያ ባላስልጣናት ጋር (የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ) መወያየቱን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዘግቦ ነበር።
ምንጭ፦ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ / አዲስ ፎርቹን
——
ሌሎች ዜናዎች፦- የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሮኒክ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ) ማዕከል ኢትዮጵያ ውስጥ ሊገነባ ነው
- ራይድ የተባለዉ የታክሲ አገልግሎት ድርጅት የስም ማጥፋት ዘመቻ እና ጥቃት ደርሶብኛል በማለት ወቀሰ
- ገበያ የተባለው የግል ድርጅት እና የኢኖቬሽንና ቴክሎጂ ሚኒስቴር ተባብረው ለመሥራት ስምምነት ተፈራረሙ
- ከ7ሺህ 800 በላይ አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች በመላው አገሪቱ ሊቋቋሙ ነው
- የዱባይ አቡዳቢው ኤግል ሒልስ በአዲስ አበባ ለገሀር የተቀናጀ የመኖሪያ፣ አገልግሎት መስጫና የመዝናኛ ስፍራ ሥራውን ጀመረ