የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች

Home Forums Semonegna Stories የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች

Viewing 15 posts - 1 through 15 (of 56 total)
  • Author
    Posts
  • #12008
    Semonegna
    Keymaster

    በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሥር ከሚገኙት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የጎንደር ዩንቨርሲቲ በርካታ ቁሳዊና መንፈሳዊ እሴት የያዙ መጻህፍት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ለማድረግ ሥርዓተ ትምህርት (curriculum) ተቀርጾና መምህራን ተቀጥረው የግእዝ ቋንቋን ለማስተማር መዘጋጀቱን አስታውቋል።

    ጎንደር ዩንቨርሲቲ የግእዝ ቋንቋ በመጀመሪያ ዲግሪ መስጠት ሊጀምር ነው

    ጎንደር (ኢዜአ) – ጎንደር ዩንቨርሲቲ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበትን የግእዝ ቋንቋ ለመታደግ በአዲሱ የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ ዲግሪ የቋንቋ ትምህርት ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ።

    የጎንደር ዩንቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዘዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የግእዝ ቋንቋ ባለቤት ብትሆንም ለቋንቋው ማደግና መስፋፋት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው። “በዚህም ሳቢያ ቋንቋው የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበት ከመሆኑም በላይ በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ በርካታ የብራና መጻፍትን ለጥናትና ምርምር ስራ ለማዋል አልተቻለም “ብለዋል።

    ዘመናት የተሻገሩና በቋንቋው የተጻፉ ለዘመናዊ ሕክምና ሙያ የሚያግዙ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ፋይዳ ያላቸው በርካታ መጻሕፍት በኃይማኖት ተቋማትና ገዳማት ተወስነው መኖራቸውን አመልክተዋል።

    ዩንቨርሲቲው እነዚህን ቁሳዊና መንፈሳዊ እሴት የያዙ መጻህፍት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ለማድረግ ሥርዓተ ትምህርት (curriculum) ተቀርጾና መምህራን ተቀጥረው የግእዝ ቋንቋን ለማስተማር መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

    በትምህርት ዘመኑ 50 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት መደረጉን ያመለከቱት ዶክተር ካሳሁን፥ ትምህርቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጠውም በኤክስቴንሽንና በክረምት መርሃ ግብሮች መሆኑን አስረድተዋል። ትምህርቱ ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ ሲሄድ መደበኛ ተማሪዎችን ጭምር በቀጣይ በግእዝ ቋንቋ አሰልጥኖ ለማስመረቅ መታቀዱን አመልክተዋል።

    በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሥር ከሚገኙት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የጎንደር ዩንቨርሲቲ፥ በአጠቃላይ 87 የመጀመሪያ ዲግሪ፤ 158 ሁለተኛ ዲግሪና 29 የሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞች እንዳሉት ተገልጿል። በመደበኛ፣ በተከታታይና በክረምት መርሃ ግብሮች ትምህርታቸውን የሚከታታሉ ከ45ሺ በላይ ተማሪዎች በዩንቨርሲቲው ይገኛሉ።

    ምንጭ፦ ኢዜአ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    —–
    ተመሳሳይ ዜናዎች

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች


    #12013
    Anonymous
    Inactive

    ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ተጠሪነቱ ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሆን ተወሰነ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ሲመራ የነበረው ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ተጠሪነቱ ለፌዴራል የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ጳጉሜን 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው 29ኛ መደበኛ ስብሰባ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።

    በተለያዩ የትምህርት መስኮች የሚያስተምሩ መምህራንና የስፖርትና የሰውነት ማጎልመሻ ባለሙያዎችን በብቸኝነት በማፍራት ይታወቅ የነበረው የዛሬው ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ሥራውን የጀመረው በ1951 ዓ.ም. በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ነው፡፡
    በኋላም የአዲስ አበባ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ በሚል ስያሜ ሜክሲኮ አካባቢ ባሁኑ ተግባረ ዕድ ግቢ በርካታ መምህራንን በማሰልጠን ለመላው ሀገሪቱ ትምህርት ቤቶቸ አበርክቷል። በ1967 ዓ.ም. አሁን ወደሚገኝበት ኮተቤ ተዛውሮ ‘ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ’ በሚል ስያሜ ሲሠራ ከቆየ በኋላ በ1990 ዓ.ም. ተጠሪነቱ ከትምህርት ሚኒስቴር ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሆኖ ለከተማው ትምህርት ቤቶች መምህራንን ሲያሰጥን ቆይቷል፡፡ ከዘጠኝ ዓመታት ቆይታ በኋላ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ባሁኑ ወቅት በመምህራን ስልጠናና ሌሎችም መስኮች ከ14 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ይገኛል። ተቋሙ ስር ሦስት ኮሌጆች እና አራት ፋኩልቲዎች እንዲሁም 26 የትምህርት ክፍሎች አሉት።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    #12020
    Anonymous
    Inactive

    አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2012 የትምህርት ዘመንን ሠላማዊ ለማድረግ የሠላም ጥምር ግብረ ኃይል አቋቁሞ እንደሚሠራ ገለፀ

    አርባ ምንጭ (ሰሞነኛ)– አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2012 የትምህርት ዘመንን ሠላማዊ ለማድረግ የሠላም ጥምር ግብረ ኃይል አቋቁሞ እንደሚሠራ ገለፀ። ዩኒቨርሲቲው በ2012 የትምህርት ዘመን ሠላማዊ መማር ማስተማር ለማረጋገጥ በተዘጋጀ የሠላም ጥምር ግብረ ኃይል መሪ ዕቅድ ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ጋር ጳጉሜ 2/2011 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል።

    ጥምር ግብረ ኃይሉ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ በማዕከል እንዲሁም በየካምፓሱ የሚቋቋም ሲሆን ዓላማውም የትምህርት ዘመኑ በተሻለ ሁኔታ ውጤታማና ሠላመዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ማድረግ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ተናግረዋል። ጥምር ግብረ ኃይሉ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ባሻገር የተማሪዎች ኅብረት ተወካዮችን፣ የሠላም ፎረም አመራሮችን፣ የዞንና የከተማ የሥራ ኃላፊዎችንና ፀጥታ አካላትን ያካተተ መሆኑንም ፕሬዝደንቱ ገልፀዋል።

    ጥምር ግብረ ኃይሉ በዋናነት ከታች እስከ ላይ ባለው የዩኒቨርሲቲው መዋቅር መማር ማስተማሩን ሊያውኩ የሚችሉ ጉዳዮችን በየጊዜው እየተከታተለና እየገመገመ መፍትሔና ማስተካከያ የሚሰጥ መሆኑን ዶ/ር ዳምጠው ገልፀዋል። ጥምር ግብረ ኃይሉ በውስጥና በውጪ ጭምር የሚዋቀር መሆኑን የተናገሩት ፕሬዝደንቱ መዋቅሩ ከዩኒቨርሲቲው ባሻገር ከማህበረሰቡ ጋር በጋራ ይሠራል ብለዋል።

    በትምህርት ዘመኑ ለተማሪዎች ቅበላ ይረዳ ዘንድ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እቀድ ተዘጋጅቶ እየተሠራ ሲሆን በቅርቡም አፈፃፀሙን በተመለከተ በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች የሚመራ ልዑክ ወደየካምፓሱ በመሄድ ምልከታ እንደሚያደርግና ሥራው ያለበትን ደረጃ በመገምገም አቅጣጫ እንደሚሰጥ ዶ/ር ዳምጠው ተናግረዋል።

    ሠላማዊ የመማር ማስተማሩ ሥራ ካለ ህብረተሰቡ ተሳትፎ ስኬታማ መሆን ስለማይችል መስከረም መጀመሪያ አካባቢ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሀይማኖት አባቶችና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ውይይት ይደረጋል ብለዋል።

    ምንጭ፦ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    #12024
    Anonymous
    Inactive

    ተማሪዎች ውጤታቸውን መሠረት በማድረግ የዩኒቨርሲቲ ምርጫቸውን ማስተካከል እንደሚችሉ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በ2012 የትምህርት ዘመን የሚካሄደው የተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ምደባ ተማሪዎች ውጤታቸውን መሠረት በማድረግ የዩኒቨርሲቲ ምርጫቸውን መቀየር እንሚችሉ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

    የዘንድሮ ምደባ በተፈጥሮ ሳይንስ፣ በማኅበራዊ ሳይንስ እና በመምህርነት የሚካሔድ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

    ተማሪዎች ከተፈጥሮ ሳይንስ ወደ ማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት መስክ መቀየር እንሚችሉ ገለፀው ተቋሙ ከተፈጥሮ ሳይንስ ወደ ማኅበራዊ ሳይንስ መቀየር የሚቻለው ለተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች የተዘጋጀውን ማለፊያ ነጥብ ለሚያሟሉ ተማሪዎች ብቻ መሆኑን አስታውቋል።

    የትምህርት መስክ ምርጫ በተመለከተም ለተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች፣ ተፈጥሮ ሳይንስና መምህርነት፣ ለማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ደግሞ ማኅበራዊ ሳይንስና እና መምህርነት ብቻ እንደሚሆንም ነው የገለፀው።

    ተማሪዎች ውጤታቸውን መሠረት በማድረግ የዩኒቨርሲቲ ምርጫቸውን መቀየር እንሚችሉም ተገልጿል።

    የዩኒቨርሲቲ ምርጫን ማስተካከልም ሆነ የትምህርት መስክ መቀየር (ከተፈጥሮ ሳይንስ ወደ ማኅበራዊ ሳይንስ) የሚቻለው ተማሪዎች ትምህርታቸዉን በተከታታሉበት ትምህርት ቤት ወይም ፈተና በወሰዱበት የፈተና ጣቢያ ነው ተብሏል።

    የዩኒቨርሲቲ ምርጫ ማስተካከያና የፊልድ መቀየሪያ ቀናት እስከ መስከረም 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ብቻ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር በድረ ገፁ አስነብቧል።

    ምንጭ፡- ኢቢሲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    #12037
    Anonymous
    Inactive

    የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ቅበላ ጊዜ ይፋ ተደረገ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ቅበላ ጊዜን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ይፋ አደረገ። ሚኒስቴሩ በ2012 የትምህርት ዘመን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሠላማዊ የመማር ማስተማር እንዲኖር የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን እንዳደረገ መግለጫ ሰጥቷል።

    በተከለሰው አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሠረትም የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች የመጀመሪያ ሴሚስተር በአራት ቅበላ ዓይነቶች እንደሚሆን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።

    በተፈጥሮ ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ሳይንስ በመምህርነት፣ በማኅበራዊ ሳይንስና በማህበራዊ ሳይንስ በመምህርነት የቅበላ ክፍል በመምህርነት የተከፈለ ነው ብለዋል።

    በሁለተኛው ወሰነ ትምህርት ደግሞ የመጀመሪያውን ሴሚስተር ውጤት መሠረት በማድረግ በአምስት የሙያ መስኮች ማለትም በሕግ፣ ሕክምናና የጥርስ ሕክምና፣ ፋርማሲ፣ የእንስሳት ሕክምና እና ምሕንድስና ናቸው።

    ሌሎቹ የትምህርት መስኮች ምደባ የሚደረገው ከአንድ ዓመት የትምህርት ቆይታ በኋላ ነው። በ‹ቪዲዮ ኮንፈረንስ› ዝግጅት ግምገማ በማድረግ የመምህራን ቅጥር እንደሚካሄድም ተጠቅሷል።

    አዳዲስ ፟ዩኒቨርሲቲዎችም ለተማሪ ቅበላ ዝግጁ እንደሆኑ ተጠቁሟል። የቅበላው ጊዜም ለነባር ተማሪዎች ከመስከረም 5 እስከ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. እየተካሄደ ይገኛል ነው የተባለው። አዲስ ለሚገቡ ተማሪዎች ከመስከረም 25 እስከ 29 ቅበላው ይካሄዳል ተብሏል። ጥቅምት 03 ቀን 2012 ዓ.ም. ደግሞ ሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት የሚያስጀምሩ ይሆናል ነው የተባለው።

    አዲስ ተማሪዎች በክልሉ ወይም በየወረዳው ስለመብቶቻቸውና ግዴታዎቻቸው ስልጠና ይሰጣቸዋል። ወላጆችና ተማሪዎች በሚፈርሙት ውል መሠረት ወደ ዩኒቨርሲቲ ይገባሉ።

    142 ሺህ 943 ተማሪዎችን የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ተቀብለው እንደሚያስተምሩና የሴት ተማሪዎች ብዛት 43 ከመቶ እንደሆነ ተገልጿል።

    የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ዝውውር የሚጠይቁት በጤና እክል ምክንያት ብቻ እንደሆነም ተጠቁሟል።

    ከተፈጥሮ ሳይንስ ወደ ማኅበራዊ ሳይንስና ከማኅበራዊ ሳይንስ ወደ ተፈጥሮ ሳይንስ ዝውውር ማድረግ ይቻላል፤ ዝውውር ማድረግ የሚቻለው ግን የየመስኮቹን የማለፊያ ውጤት ሲያሟሉ እንደሆነ ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ተናግረዋል።

    ምንጭ፦ ዋልታ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    #12196
    Semonegna
    Keymaster

    በተማሪዎች አቀባበል ዙሪያ ከባሕር ዳር ከተማ ወጣት ማህበራት ጋር ምክክር ተደረገ

    ባህር ዳር (ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ) – የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች በ2012 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ወደ ዩኒቨርሲቲው ለሚመጡ ተማሪዎች አቀባበል በማድረግ ዙሪያ ከዘጠኝ በላይ ከሚሆኑ የባህር ዳር ከተማ ወጣት ማኅበራት ጋር በዩኒቨርሲቲው የጥበብ ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ምክክር አደረጉ።

    የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽን ስትራቴጂክ ኮምንኬሽ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ እንዲሁም የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ገድፍ የባህር ዳር ወጣቶች በዩኒቨርሲቲው ፀጥታ ጉዳይና የተማሪዎችን ደህንነት ከመጠበቅ አንፃር እያበረከቱት ያለውን አስተዋፅኦ አድንቀዋል። አቶ ብርሃኑ አክለውም ዩኒቨርሲቲውም የሥራ ዕድሎችን በመፍጠርና የወጣቶችን አቅም በመገንባት የሚጠበቅበትን እንደሚያደርግ ጠቁመው ወጣቶችም የባህር ዳር ከተማና የዩኒቨርሲቲው ስም በበጎ እዲነሳ አሁንም ከዚህ ቀደም ሲያደርጉት የነበረውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አደራ ብለዋል።

    ከባህር ዳር ከተማ የተወጣጡ የወጣት ማኅበራት ተወካዮች እንደገለጹት፥ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሞባይልና የላፕቶፕ ዘረፋዎች የሚደርስባቸው ተብለው የተለዩ ዋና ዋና የሚባሉ መስመሮች የመንገድ መብራቶቻቸው የጠፉ እና አንዳንዶችም መስመር ሊዘረጋላቸው የሚገባ ስለሆነ ዩኒቨርሲቲው ከመብራት ኃይል እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንዲሠራ ጠይቀዋል። አክለውም፥ ወጣቶቹ በባህር ዳር ከተማም ሆነ በዩኒቨርሲቲው ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር እንዳይኖር ተግተው እንደሚሠሩ ተናግረዋል። በመጨረሻም፥ በተማሪዎች አቀባበል ዙሪያ ለተነሱት ጥያቄዎች በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች መላሽ ተሰጥቷል።

    ምንጭ፦ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    #12232
    Semonegna
    Keymaster

    ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የፈረንሳይኛ ቋንቋ አስተምሮ በዲፕሎማ ፕሮግራም ተቀብሎ ለማሰልጠን ተቀማጭነቱ አዲስ አበባ ውስጥ ከሆነው የፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን ዩኒቨርስቲው አስታወቋል።
    —–

    ጎንደር (ኢዜአ) – ጎንደር ዩንቨርሲቲ የፈረንሳይኛ ቋንቋ የስልጠና ማእከል ለመክፈት ከፈረንሳይ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ጋር ስምምነት መድረሱን አስታወቀ።

    ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ተማሪዎችን በዲፕሎማ ፕሮግራም ተቀብሎ ለማሰልጠን ተቀማጭነቱ አዲስ አበባ ውስጥ ከሆነው የፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን ዩኒቨርስቲው አስታወቋል።

    የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት በበኩሉ የስልጠና ማዕከሉ መከፈት ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ቱሪስቶችን በቋንቋቸው ለማስጎብኘትም ሆነ በሆቴሎችና በመዝናኛ ስፍራዎች ቀልጣፋ የቱሪስት መስተንግዶ ለመስጠት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብሏል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንዳስታወቁት፥ የትምህርት ስልጠናው የሚሰጠው ከኢምባሲው ጋር በመተባበር ነው። ስልጠናውን በተቀናጅ አግባብ ለመስራት ማዕከል ይቋቋማል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ማዕከሉን ለመክፈት የሚያስችለው ስምምነት ከኤምባሲው ጋር ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ይፈራረማል።

    በሚደረገው ስምምነቱም የፈረንሳይኛ ቋንቋ አስተማሪዎችን ከመመደብ ጀምሮ የማስተማሪያ ግብአቶችን በራሱ ወጪ ለዩኒቨርሲቲው እንደሚያሟላ ገልፀዋል። የማዕከሉ መከፈት ዋና ዓላማ በፈረንሳይኛ ቋንቋ የሰለጠኑ አስጎብኚዎችና የሆቴል አስተናጋጆችን እጥረት ለመቅረፍ እንዲያስችል የታሰበ መሆኑን ተናግረዋል።

    ዩኒቨርሲቲው ከቱሪዝም ትምህርት ክፍሉ ጋር በመቀናጀት ከዚህ ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ቋንቋውን በሰርተፊኬትና በዲፕሎማ ደረጃ ለመስጠት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል። ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ከ100 ዓመታት በላይ የዘለቀ ዲፖሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው ያሉት ፕሬዘዳንቱ፥ በአፍሪካም ከ20 በላይ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሀገሮች መኖራቸውን አመልክተዋል።

    የጎንደር ከተማ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ የአጼ ፋሲል ቤተ-መንግስትና የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ መዳረሻ በመሆኑ በርካታ ቁጥር ያላቸው የፈረንሳይ ቱሪሰቶች ለጉብኝት እንደሚመጡ ተናግረዋል።

    የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጽህፈት ቤት የህብረተሰብና ቱሪዝም ሃላፊ አቶ ታደሰ ይግዛው እንዳሉት ከሆነ በአካባቢው ካሉት 80 አስጎብኚዎች መካከል የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ከ2 አይበልጡም።

    በርካታ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ፓርኩን ለመጎብኘት እንደሚመጡ የተናገሩት ኃላፊው፥ ዩኒቨርሲቲው ለመክፈት ያሰበው የፈረንሳይኛ ቋንቋ ማሰልጠኛ የፓርኩን የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ አስጎብኚ እጥረት እንደሚያቃልል ተናግረዋል።

    የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከፈረንሳይኛ ቋንቋ በተጨማሪ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበትን የግእዝ ቋንቋ ለመታደግ በዚህ ዓመት የግእዝ ቋንቋ ትምህርት ቤት ለመክፈት መዘጋጀቱ በቅርቡ መገለጹ የሚታወስ ነው።

    ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    #12296
    Anonymous
    Inactive

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርሲቲ ስለሚገቡ አዲስ ተማሪዎች እና የሚደረግላቸውን አቀባበል በተመለከተ የሰጠው መግለጫ
    —–

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በ2011 ዓ.ም. በመላ አገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ከወሰዱት ተማሪዎች ውስጥ 142,840 ተማሪዎች በመደበኛ መርሀ ግብር (regular program) በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በኩል በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበዋል። ምደባቸውም የተማሪዎቹን የትምህርት መስክና የተቋም ምርጫ፣ የተማሪዎቹን ውጤት እና የዩኒቨርሲቲዎችን የቅበላ አቅም ባገናዘበ መልኩ የተካሄደ ነው።

    በዚሁም መሠረት አብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ተቀብለዋል። ቀሪዎቹም እየተቀበሉ ይገኛሉ። በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ አብዛኞቹ አዲስ ገቢ ተማሪዎች በተመደቡበት በመገኘት ትምህርታቸውን መከታተል ጀምረዋል። ነባር ተማሪዎችም ትምህርታቸውን መከታተል ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

    ከዚህ ጋር ተያይዞም የ2012 ዓ.ም. የመማር-ማስተማር ሰላማዊ እንዲሆን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። ከነዚህም መካከል አንዱ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ደኅንነታቸውን ለማስጠበቅ የሚረዳ ወላጆችን እና ሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የኃላፊነት መውሰጃ የስምምነት ውል እንዲገቡ መደረጉ አንዱ ነው። በዚህም ላይ ተማሪዎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል አዲስ ተማሪዎች ወደተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ከመግባታው ቀድም ብሎ እንዲሁም ከገቡ በኃላ፣ ነባር ተማሪዎችም ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት የግንዛቤ ማዳበሪያ ስልጠናዊ ውይይቶች እንዲካሄዱ ተደርጓል። በተጨማሪም በያዝነው ዓመትም አዲስ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች የሥነ-ምግባር መመሪያ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ተደርጓል።

    የመማር-ማስተማር ሥራው የግብዓትም ሆነ ሌሎች ችግሮች እንዳያጋጥሙትም ዩኒቨርሲቲዎቹ ያሉበትን አቋም እና ተማሪዎችን ለመቀበል ያደረጉትን ቅድመ-ዝግጅት ለመገምገም ያገዙ ከፍተኛ አመራሮች ጭምር የተሳተፉባቸው የመስክ ጉብኝቶች ተካሂደዋል። በቪዲዮ ኮንፈረነስም ከዩኒቨርሲቲ አመራሮች ጋር ተከታታይ ውይይቶችና የደረሱበትን የዝግጅት ደረጃ የመገምገም እና የማረጋገጥ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። በውጤቱም ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ የ2012 የትምህርት ዘመንን ሰላማዊ ለማድረግ ሊሠሩ የሚገባቸው አስፈላጊ ቅድመ-ዝግጅቶችን ማካሄዳቸው ተረጋግጧል።

    ከተማሪዎች ቅበላ ጋር ተያይዞም በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን (ሚዲያዎች) ሲታይ እንደነበረው ዩኒቨርሲቲዎቹ ያሉበት አከባቢ ማኅበረሰብ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮችና የአከባቢው የጸጥታ ኃላፊዎች ጋር በመተባበር ፍፁም ኢትዮጵያዊነትን የሚገልፁ ቤተሰባዊ አቀባበሎችን ሲያደርጉ ታይቷል፤ እያደረጉም ይገኛሉ። ይህ በዝግጅት ምዕራፍ ወቅት ከተካሄዱ ተከታታይ ማኅበረሰብ አቀፍ ውይይቶች በኋላ የተገኘ ውጤት ነው።
    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ምደባውን ተግባራዊ ሲያደርግ የተማሪዎችን ምርጫ፣ ውጤት እና የየተቋማቱን የቅበላ አቅም ከማገናዘብ ጎን ለጎን ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት የሚያስችሉ አካሄዶችንም ተከትሏል። ይሄው ታውቆ የክልል መንግስታት፣ የዩኒቨርሲቲ ቦርዶችና አመራሮች እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ማኅበረሰቡ እና የሚመለከታቸው አካላት በጠቅላላ የተቀመጠውን የቅበላና ድልደላ መርህ ተገንዝበው ለአፈፃፀሙ ሁሉም የድርሻቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ እንተማመናለን።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    #12297
    Anonymous
    Inactive

    የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ አዲስ ገቢ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ወደ አማራ ክልል አንደማይልክ አስታወቀ
    —–

    መቐለ (ቢቢሲ አማርኛ) – የትግራይ ክልል አዲስ ገቢ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አማራ ክልል ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንደማይልክ አስታውቋል።

    የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ገብረመስቀል ካሕሳይ ጥቅምት 7 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ “ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ወደ ሚሰነዘሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎች እና ኃላፊነት ወደማይወስድ ክልል አዲስ ተማሪዎችን ላለመላክ የክልሉ አቋም ነው” ብለዋል።

    “አማራ ክልል የተመደቡት 600 ተማሪዎች እንደማይሄዱ ለሚመለከተው የፌደራል መንግሥት አሳውቀናል። ይህ የክልሉ አቋም ነው” ሲሉ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

    ዘንድሮ፤ በትግራይ ክልል የዩኒቨሲቲ መግብያ ፈተና ወስደው ማለፍ የቻሉ የተማሪዎች ቁጥር ከ9000 በላይ መሆኑን የጠቀሱ ኃላፊው፤ ወደ አማራ ክልል ተመድበው የነበሩ ተማሪዎች ከ2000 በላይ እንደነበረ እና ከሚመለከታቸው የፌደራል መንግስት አካላት ጋር በተደረገው ውይይት ወደ 600 ዝቅ እንዲል መደረጉን ተናግረዋል።

    “ከአንድ ወር ተኩል በላይ የክልሉ መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሲወያይ ቆይቷል። የተቀሩ 600 ተማሪዎችን ሌላ ቦታ እንዲመደቡ ይሠራል። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን የትግራይ ክልል ሌላ አማራጭ ይፈልጋል እንጂ ተማሪዎቹን ወደዚያ አይልክም” ብለዋል።

    ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲ አመዳደብ ሥርዓት መሠረት ከአንድ ክልል አጠቃላይ ተማሪዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት በክልላቸው የተቀሩት 60 በመቶ ደግሞ ሌላ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ይመደቡ እንደነበረ የሚያስታውሱት ኃላፊው፤ “ብሔርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በበዙበት ወቅት ይህ ተቀይሮ 10 በመቶ በክልላቸው 90 በመቶ ደግሞ ወደ ሌላ ክልል እንዲላኩ መደረጉ አግባብ አይደለም” ብለዋል በሰጡት መግለጫ።

    ይህ እንዲስተካከል ከፌደራል እና ከሌሎች አካላት ጋር ውይይት መደረጉን እና 20 በመቶ በክልላቸው 80 በመቶ ደግሞ ከክልል ውጪ እንዲመደቡ መወሰኑን ጨምረው ተናግረዋል።

    የትምህርት ቢሮው ኃላፊ ገብረመስቀል ካሕሳይ ትግራይ ክልል ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው የሚመጡ ተማሪዎች “ምንም አይነት የደህንነት ችግር አይገጥማቸውም” ብለዋል።

    የትምህርት ቢሮ ኃላፊው ሁለተኛ ዓመት እና ከዚያ በላይ በሆኑ ተማሪዎች ዙሪያ ያሉት ነገር የለም።

    ምንጭ፦ ቢቢሲ አማርኛ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    #12309
    Semonegna
    Keymaster

    ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የ2012 ዓ.ም. የመማር ማሰተማር ሥራውን በይፋ ጀመረ
    —–

    ቦንጋ ከተማ፣ ከፋ ዞን (ሰሞነኛ) – ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ከመስከረም 24 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ነባር ተማሪዎችን ተቀብሎ የምዝገባ ሂደቱን ካጠናቀቀ በኋላ ጥቅምት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ለ2ኛ እና 3ኛ ዓመት ተማሪዎች የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ትምህርትን (first day, first class) በይፋ መስጠት ጀምሯል። በዕለቱም የዩኒቨርሲቲው የመ/ማ/ም/ፕሬዝዳንት በመማሪያ ክፍል አካባቢ በመገኘት የመማር ማስተማር ሥራው በአግባቡ መጀመሩን ዞረው የጎበኙ ሲሆን ለተማሪዎችም መልካም የትምህርት ዘመን እንዲሆንላቸው በመግለፅ የመማር ማስተማሩም ተግባር በተያዘለት የጊዜ ገደብ መሠረት እንዲጀምር አስተዋፅኦ ላበረከቱ ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና ባለድርሻ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

    ከዚሁ ጋር በተያያዘ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት አባላት በ2012 ዓ.ም. የመጀመሪያውን ውይይት አማድረጋቸውን ዩኒቨርሲቲውስ አስታውቋል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት የሴኔት አባላትን በማሰባሰብ የ2012 ዓ.ም. የአንደኛ ሩብ አመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ፣ ከተማሪዎችና ከትምህርት ክፍል ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ በአካዳሚክ ዘርፍ ያለውን መዋቅር ማስፋትን እና የአዲስ ተማሪዎች ቅበላ ዝግጅትን በተመለከተ በሚሉ አጀንዳዎች ላይ ውይይት አድርገዋል።

    በመድረኩም በያዝነው የትምህርት ዘመን ከተማሪዎች ቁጥር እና የትምህርት ክፍል መጨመር ጋር በተያያዘ የአካዳሚክ ዘርፍ መዋቅርን ማስፋት በሚለው አጀንዳ ላይ በመወያየት የየዘርፉን ሥራ ለማሳለጥ የመዋቅሩ መስፋት አስፈላጊ መሆኑን በጋራ በመስማማት ለአምሰቱም ኮሌጆች በምክትል ዲን ማዕረግ የሚሠራ፣ በጥናትና ምርምር ዘርፍና በትምህርት ጥራት ዘርፍም በምክትል ዲን ማዕረግ የየኮሌጆች አስተባባሪ በመሆን እና በሬጅስትራር ዘርፍም በተባባሪ ሬጅስትራር ማዕረግ ተጨማሪ ሰው በመሰየም ሥራው በአግባቡ እንዲሠራ ተወስኗል።

    በመጨረሻም አዲስ የሚመጡ የመደበኛ መርሀ ግብር ተማሪዎችን (freshman students of the regular program) ቅበላ ዝግጅትን አስመልክቶ በቀረበው አጀንዳ ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ እንደተለመደው የተዋጣለትን አቀባበል ለማድረግ የተዋቀሩ ኮሚቴዎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።

    ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች የምዝገባ ጊዜ ከጥቅምት 8 እስከ ጥቅምት 10 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ድረስ እምደሆነ አስታውቋል።

    * Bonga University is one of the Public Higher Education Institution in Ethiopia. It is established with its own legal personality by the Proclamation No. 349/2015 of the Council of Ministers of the Federal Democratic Republic of Ethiopia. It is found in the South Western part of Ethiopia, in the Southern Nations, Nationalities and Peoples (SNNP) region.

    #12557
    Anonymous
    Inactive

    አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከአፍረካ ምርጥ 10 ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ መሆን የቻለው ባሳየው ጥረትና መሻሻል ነው- ፕ/ር ጣሰው

    አዲስ አበባ (ኤፍ.ቢ.ሲ) – አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከአፍረካ ምርጥ 10 ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ መሆን የቻለው በየጊዜው ባሳየው ጥረት እና መሻሻል መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ገለፁ።

    አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአሜሪካው ግዙፍ የሚዲያ ድርጅት “U.S. News & World Report” ባወጣው ዘገባ  በአፍረካ ካሉ ምርጥ 10 ዓለማቀፋዊ ዩኒቨርሲቲዎች (Best Global Universities in Africa) አንዱ ሆኖ መመረጡን ተከትሎ ጥቅምት 27 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. መግለጫ ሰጥቷል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በመግለጫው፥ ዩኒቨርሲቲው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1950 ዓ.ም. መቋቋሙን ገልፀዋል። ዩኒቨርሲቲው ሲመሠረት የመቀበል አቅሙ 33 ተማሪዎችን ብቻ ሲሆን፥ ዛሬ ላይ የቅበላ አቅሙን እስከ 50 ሺህ ማድረሱን አስታውቀዋል።

    እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው 13 ካምፓሶች፣ 10 ኮሌጆች፣ 2 የቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩቶች፣ 12 የምርምር ኢንስቲቲዩቶች እና 2 የማስተማሪያና የከፍተኛ ሕክምና መስጫ ሆስፒታሎችን በመያዝ በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች ማለትም በ73 የትምህርት መስኮች የመጀመሪያ ዲግሪ መርሃ ግብር፣ በ345 የድኅረ ምረቃ መርሃ ግብሮች፣ በ90 የጥናትና ምርምር መስኮች የዶክትሬት መርሃ ግብሮችን እያከናወነ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

    ይህንን ተከትሎም ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ እውቅናዎችን እና ደረጃዎችን አግኝቷል ያሉት ፕሮፌሰር ጣሰው፥ ከነዚህም የቅርብ የሆኑት በአውሮፓውያኑ በ2014 ከአፍሪካ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች 18ኛ ደረጃ፣ በ2015 ከአፍሪካ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች የ16ኛ ደረጃን እግኝቶ ነበር ብለዋል።

    በያዝነው በአውሮፓውያኑ በ2019 ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከአፍሪካ ምርጥ ዓለማቀፋዊ ዩኒቨርሲቲዎች በ10ኛ ደረጃ ሆኖ ሊመዘገብ መቻሉንም ነው ፕሮፌሰር ጣሰው የገለፁት።

    አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እዚህ ደረጃ የደረሰው በየጊዜው ባሳየው ጥረት እና መሻሻል እንዲሁም በሚያደርገው ጥናትና ምርምር ኢትዮጵያ ከምትፈልገው የተማረ የሰው ኃይል ፍላጎት ጋር ለማጣጣም በተደረገው ጥረት መሆኑንም አስታውቀዋል።

    አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ኩራት ነው ያሉት ፕሮፌሰር ጣሰው፥ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትንሿ ኢትዮጵያ ነው፤ ዩኒቨርሲቲው ሌሎች ኢትዮጵያውያን ዩኒቨርስቲዎችን በያዘው የእድገት እና የመሻሻል ጉዞ ላይ የመውሰድ ግዴታ አለበትም ብለዋል።

    የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአድሚኒስትሬሽን እና የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ማቲዎስ ኢንሰርሙ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ካስመዘገበችው እድገት በተጨማሪ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እዚህ ደረጃ የደረሰው ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ባለው ተልኮ ነው ብለዋል።

    አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ምርጥ ዓለማቀፋዊ ዩኒቨርሲቲዎችን ደረጃ እና ዝርዝር ለማየት እዚህ ጋር ይጫኑ

    ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ. / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

     አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከአፍረካ ምርጥ 10 ዩኒቨርሲቲዎች


    #12575
    Anonymous
    Inactive

    ጎንደር (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጥቅምት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. 251 የህክምና ዶክተሮችን አስመርቋል። በዚሁ ዕለት ዩኒቨርሲቲው ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ዘርፍ እያደረገ ያለው ምርምር አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገቡን አስታውቋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በህክምናው ዘርፍ ከአጋር አካላት ጋር በተባበር በአባላዘር፤ በወባ በሽታ፤ በሳንባ ምች እና ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች (communicable and noncommunicable diseases) ዙሪያ ምርምሮችን በማካሄድ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች አስመዝግቧል። የምርምር ውጤቶቹም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲሠራባቸው የቆዩ የህክምና መመሪያዎችን እስከ ማስቀየር የደረሱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆን መብቃታቸውንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

    “የምርምር ውጤቶቹ የህክምና ጊዜን በማሳጠር በመርፌ ይሰጡ የነበሩ ህክምናዎችን በአፍ በሚሰወዱ መድኃኒቶች በመተካትና የህሙማንን ስቃይ፤ እንግልትና የህክምና ወጪንም ለመቀነስ አስችለዋል” ብለዋል ዶ/ር አስራት።

    በየዓመቱም በጤናው ዘርፍ ብቻ ከ150 በላይ የምርምር ውጤቶች በታወቁ ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ጭምር ለህትመት የበቁበት ሁኔታን መፍጠር እንደተቻለ ተናግረዋል።

    ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ለ36ኛ ጊዜ በህክምናው ዘርፍ ካስመረቃቸው 251 ዶክተሮች መካከልም 64ቱ ሴቶች መሆናቸውን ገልጸው፥ ምሩቃኑ በህክምናውና በምርምሩ ዘርፍ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል። የዕለቱ ተመራቂዎች ለሙያቸውና ለገቡት ቃል-ኪዳን ታማኝ በመሆን ከግል ጥቅም ይልቅ ሕዝብን በማገልገል ፍጹም አዛኝና ሩህሩህ በመሆን ለህክምናው ሥነ-ምግባር ተገዥነታቸውን በተግባር እንዲያረጋግጡም መክረዋል።

    የዕለቱ የክብር እንግዳ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው “የህክምና ሳይንስ ትምህርት ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት የሚታደግ የተከበረ ሙያ ነው” ብለዋል። “ተማራቂዎች ለዚህ የደስታ ቀን ትደርሱ ዘንድ እውቀት ላቀበሏችሁ መምህራን፤ ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና ለወላጆቻችሁ ብሎም ከእናንተ ብዙ ለምትጠብቀው ውድ ሀገራችሁ ድርብ ኃላፊነት አለባችሁ” ሲሉ አሳስበዋል።

    “ትምህርት የሁሉም መሠረት በመሆኑ ሀገርንና ወገንን ወደ እድገት ለማሻገር በተማርኩት ሙያ ለማገልገል ዝግኙ ነኝ” ያለችው ከዕለቱ ተመራቂዎች መካካል በከፍተኛ ማዕረግ የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ የሆነችው ዕ ዶክተር ነጻነት ሃይሉ ነች። የሀገሪቱን ስር የሰደዱ የጤና ችግሮች ለመፍታት በጤናው ዘርፍ ምርምሮችን በማካሄድ የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማድረግ የረጅም ጊዜ ህልሟ መሆኑንም ተናግራለች።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በዩኒቨርሲቲው በምርምርና በህክምናው ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሀኪሞችና ተመራማሪዎች የእውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

    የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በአሁኑ ወቅት በጤናው ዘርፍ 26 የመጀመሪያ፤ 37 የሁለተኛና 6 የሦስተኛ ዲግሪ እንዲሁም 10 የስፔሻሊቲ የትምህርት ፕሮግራሞች ሲኖሩት፤ ዩኒቨርሲቲው በጠቅላላው (በአምስቱ ካምፓሶቹ) 87 የመጀመሪያ፤ 137 የሁለተኛና 29 የሦስተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች አሉት። በጠቅላላው ከ45,000 በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ ሲሆን፣ 8,300 ሠራተኞች አሉት።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ጎንደር ዩኒቨርሲቲ

    #13133
    Semonegna
    Keymaster

    ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተቋሙ በተከሰተ ግጭት ምክንያት ተቋሙን ለቀው የሄዱ ተማሪዎችን በድጋሚ ለመቀበል ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ሲሆን የተቋሙ መምህራንም ለተማሪዎች የማካካሻና የማካካሻ ስልጠናዎችን ለመስጠት መዘጋጀታቸው ተገልጿል።

    ደሴ (ወሎ ዩኒቨርሲቲ) – የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የትርምስ ማዕከል ለማድረግ ጥቅመኞችና የፖለቲካ ቁማርተኞች ገንዘብ የጥፋት ተልዕኮ ፈጻሚ መልምለው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ይህም የጥፋት ተልዕኮ በአማራና በኦሮሚያ ክልል ያሉ ሁሉንም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለማንኳኳት ሞክሯል። ይህንኑ እኩይ ተግባር እልባት ለመስጠት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኔስተር አጀንዳና ተልዕኮ ቀርጾ በሁለቱ ክልሎች በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ አካላትን የማወያየት ሥራ ሠርቷል።

    በዚሁ ውይይት በወሎ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል የተከሰተው አለመግባባት በእርቀ ሰላም ተፈቶ ወደ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ ተጀምሯል። የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን በዚህ የይቅርታና የፍቅር መድረክ ‘የሰላም መሠረቱ ይቅርታ ነው፣ በጋራ ስንሆን ብዙ ሀብት ያለን ህብር ነን፣ አባቶቻችን ቋንቋና ሀይማኖት ሳይገድቧቸው ኩርማን ዳቦ ተካፍለው ያስረከቡንን ሀገር ያልኖርንበትን ዘመን ታሪክ በመጥቀስ እርስ በርስ ከሚያጠፋፋና ሀገርን ከሚያፈርስ መጥፎ ታሪክ በመቆጠብ በይቅርታ ሀገርን የማዳን ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል’ ሲሉ ገልጸዋል። ታላላቆችን የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች ለማጋጨት ገንዘብ መድበው የሚንቀሳቀሱ አካላት ተማሪዎች መጠቀሚያ መሆን የለባቸውም ያሉት የደሴ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ ገ/መስቀል የከተማ አስተዳደሩ የውጭ ተልዕኮ አንግበው የሚቀሳቀሱ አካላትን ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጋር በመተባበር የተቋሙን ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

    የፌደራል መንግሥት ተወካይ የሆኑት አቶ ብሩክ ከበደ በበኩላቸው በወቅቱ እየታየ ያለው ሁኔታ ሀገራችን ኢትዮጵያ በተስፋና በስጋት ውስጥ እንድትሆን አድርጓታል በማለት ሀገር በማፍረስ ላይ የተጠመዱ አካላት ያልኖርንበትን ዘመን ታሪክ እያመገሉ ከሚያጋጩ አካላት እኩይ ሴራ በመጠንቀቅ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የማስቀጠል ታሪካዊ ኃላፊነት እንድወጡ ለተማሪዎች ጥሪ አስተላልፈዋል። አያይዘውም አቶ ብሩክ የፌደራል መንግሥት በአማራና በኦሮሚያ ክልል ያሉ 22ቱም ዩኒቨርሲቲዎች ሰላም እንዲጠበቅና ተማሪዎች በተመደቡበት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመልሰው ገብተው እንዲማሩ እየሠራ እንደሆነ ገልጸዋል። በዚህ የእርቅ ሥነ-ሥርዓት የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተማሪዎችን ወደ አንድነት የሚያመጡ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል። ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተቋሙ በተከሰተ ግጭት ምክንያት ተቋሙን ለቀው የሄዱ ተማሪዎችን በድጋሚ ለመቀበል ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ሲሆን የተቋሙ መምህራንም ለተማሪዎች የማካካሻ (tutor) ስልጠናዎችን ለመስጠት መዘጋጀታቸው ተገልጿል።

    ምንጭ፦ ወሎ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ወሎ ዩኒቨርሲቲ

    #13178
    Anonymous
    Inactive

    ጎንደር (ሰሞነኛ) – ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተከሰተው አለመርጋጋት በተለያየ ደረጃ ተሳታፊ ሆነው በተገኙ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞች እና የጤና ባለሙያ ከቀላል እስከ ከባድ እርምጃ ወሰደ።

    ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተከሰተው አለመረጋጋት የመማር ማስተማር ሂደቱ ሲቆራረጥ መቆየቱ ይታወቃል። በዚህም መሠረት በዩኒቨርሲቲው ሰላም እንዲሰፍን፣ ዩኒቨርሲቲው ሲሠራቸው ከቆየው ሰፊ ተግባራት በተጨማሪ ከፌደራል መንግሥት የተላኩ ልዑካን በዩኒቨርሲቲያችን ውስጥ ከሚገኙ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የአስተዳደር ሠራተኞች፣ የፀጥታ አካላት እንዲሁም ከከተማው ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ሰፊ ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

    በእነዚህ ውይይቶችም አንዳንድ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የአስተዳደር ሠራተኞች እና የጤና ባለሙያ የተከሰተውን ሁከት በማነሳሳት፣ የሕይወት እና የአካል ጉዳት እንዲደርስ በተለያዩ ደረጃዎች አሉታዊ አስተዋፅኦ በማድረግ በተደጋጋሚ ምክር ቢሰጣቸውም ችላ በማለት ተማሪዎች ክፍል እንዳይገቡ ክልከላ በማድረግ እና ትምህርት እንዳይጀመር ተማሪዎችን እና መምህራንን በማስፈራራት፣ ስለት ነገሮችን ግቢ ውስጥ ይዘው በመገኘት፣ አደንዛዥ እፆችን በመጠቀም እና ይዘው በመገኘት፣ ኃላፊነትን ባለመወጣት በሥራ ቦታቸው ላይ ባለመገኘት እና ችግሩ ሲከሰት ሪፖርት ባለማድረግ ሁከት እንዲስፋፋ በማሰብ ሠራተኞችን በማነሳሳት እና ቀስቃሽ መልእክቶችን በመበተን ተሳታፊ ሲሆኑ መቆየታቸውን መረዳት ተችሏል።

    በመሆኑም ታህሳስ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በተለያየ ደረጃ ተሳታፊ ሆነው በተገኙ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞች እና የጤና ባለሙያ ከቀላል የፅሁፍ ማሰጠንቀቂያ እስከ ሙሉ በሙሉ ከሥራ እና ከትምህርት የማሰናበት እርምጃ ወስዷል።

    በዚህም 2 የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች አንድ ዓመት ከትምህትር ገበታቸው እንዲታገዱ፣ 39 ተማሪዎች ለሁለት ዓመት ከትምህርት ገበታቸው እንዲታገዱ እንዲሁም 11 ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ከትምህርት ገበታቸው (ከዩኒቨርሲቲው) እንዲሰናበቱ ሴኔቱ ወስኗል።

    ከዚህም በተጨማሪ ለ7 የዩኒቨርሲቲው መምህራን ቀላል የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ ለ3 መምህራን የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ ለ3 መምህራን እና ለ8 የአስተዳደር ሠራተኞች እንዲሁም የጤና ባለሙያ ሙሉ በሙሉ ከሥራ እንዲሰናበቱ ሴኔቱ ወስኗል።

    ወደፊትም ትምህርት የመማር ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች መብት ለማስጠበቅ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲውንም ሆነ የጎንደር ከተማን ማኅበረሰብ ሰላም ለማስከበር በመሰል ድርጊቶች ሲሳተፉ በሚገኙ ተማሪዎች፤ የአስተዳደር ሠራተኞች፣ መምህራን እና የጤና ባለሙያዎች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወስድ ሴኔቱ በጥብቅ አሳስቧል።

    ጎንደር ዩኒቨርሲቲ

    ምንጭ፦ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    #13208
    Anonymous
    Inactive
    • ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በዩኒቨርሲቲው የጸጥታ ችግር የተሳተፉ ተማሪዎች ላይ እርምጃ ወሰደ
    • ወሎ ዩኒቨርሲቲ በ335 ተማሪዎች፣ ሁለት የአስተዳደር ሠራተኞች እና አንድ መምህር ላይ እርምጃ ወሰደ
    • የጋምቤላ፣ ቦንጋ እና አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች ጥያቄዎች በተለያዩ ሀይሎች ሴራ እንዳይጠመዘዝ አስቀድመው በመሥራታቸው የመማር ማስተማር ሂደቱ በሰላማዊ ሁኔታ መቀጠሉን አስታወቁ

    የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ታህሳስ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በ2012 ዓ.ም. በተደጋጋሚ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የተለያየ ተሳትፎ በነበራቸው ተማሪዎች ላይ የሚከተሉትን ውሳኔዎች ወስኗል።

    1. ሁለት (2) ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ከትምህርት ገበታቸው እንዲሰናበቱ፣
    2. ሰባት (7) ተማሪዎች እያንዳንዳቸው ለሦስት (3) ዓመት ከትምህርት ገበታቸው እንዲታገዱ፣
    3. ስምንት (8) ተማሪዎች እያንዳንዳቸው ለሁለት (2) ዓመት ከትምህርት ገበታቸው እንዲታገዱ፣
    4. አንድ (1) ተባሮ የነበረ (በወቅቱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪ ያልነበረ) ነገር ግን በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ውስጥ ተሳታፊ የነበረ ዩኒቨርሲቲው ክስ መስርቶ ግለሰቡን በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ፤

    በመጨረሻም በወቅቱ ለሴኔቱ ውሳኔ ለቀረበ ተጨማሪ ስልሳ ዘጠኝ (69) ተማሪዎች ዲሲፕሊን ጉዳይ ላይ ተወያይቶ ጥፋታቸው በሂደት ተጣርቶ ወደ ፊት እርምጃ እንደሚወሰድባቸው እንዲሁም በቀጣይ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በተለያየ መልኩ ተሳታፊ የነበሩ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ላይ እንደየጥፋታቸው እርምጃ እንደሚወሰድ አቅጣጫ ተቀምጧል።

    በተያያዘ ዜና የጋምቤላ፣ ቦንጋ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች ጥያቄዎች በተለያዩ ሀይሎች ሴራ እንዳይጠመዘዝ አስቀድመው በመሥራታቸው የመማር ማስተማር ሂደቱ በሰላማዊ ሁኔታ መቀጠሉን አስታወቁ።

    ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሃይማኖትና የብሄር ተኮር ግጭቶች ማዕከል ሆነው እና የጸጥታ ችግር ተጋርጦባቸው ጥቂት የማይባሉ ዩኒቨርሲቲዎችም በተደጋጋሚ ትምህርት ለማቆም ተገደዋል፤ በተማሪዎች ላይም ጉዳት አጋጥሟል። የግጭት መንስኤዎች የተለያዩ ሲሆን አንዳንዶቹ ከአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ጋር የተያያዙ ናቸው።

    ወሎ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራውን አውከዋል ያላቸውን 332 ተማሪዎች፣ ሁለት የአስተዳደር ሠራተኞች እና አንድ መምህር ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቋል።

    ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመሆን ባለፉት ሁለት ወራት ችግር ፈጣሪዎችን ለመለየት በተከናወነው ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራው እንዳይቀጥል ፍላጎት ባላቸው 332 ተማሪዎች፣ ሁለት የአስተዳደር ሠራተኞች እና አንድ መምህር ላይ እርምጃ መወሰዱን ዩኒቨርስቲው አስታውቋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን ለ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ ተመራጭ እና ተምሳሌት ሆኖ ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በብሔር እና በሀይማኖት ሽፋን በተፈጠረ አለመረጋጋት የመማር ማስተማር ሥራው ባለፉት ወራት ውስጥ ለሦስት ጊዜ መቋረጡን አውስተዋል።

    በዚህም የሁለት ተማሪዎች ሕይወት ማለፉንና በተወሰኑት ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት መድረሱን ጠቅሰው፣ ይህም ከአንድ የእውቀት ምንጭ ተቋም የማይጠበቅ አሳፋሪ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

    የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ ግን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የሚታዩት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ለግድያ የሚያደርሱ እንዳልሆኑ ይናገራሉ። አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ሰላም ወዳድ መሆናቸውን የሚገልጸው ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማሩን ለማወክ የሞከሩ ጥቂት ተማሪዎች እንዳልተሳካላቸው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ገልፀዋል።

    ከ4 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስተናገደ የሚገኘው ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲም ሁነኛ የጸጥታ ችግር ሳያጋጥመው የመማር ማስተማሩ ሂደት በሰላማዊ ሁኔታ ከቀጠለባቸው ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ተጠቃሹ ነው። ዩኒቨርሲቲው ባወጣው መርሃ ግብር መሠረት የአንደኛ መንፈቅ ዓመት ትምህርትን ወደማገባደድ መቃረቡን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኡጁሉ ኦካክ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

    የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛም የመማር ማስተማር ሂደቱ በሰላማዊ ሁኔታ መቀጠሉን አንስተዋል። ዩኒቨርሲቲዎቹ በተለይም ተማሪዎች በተደጋጋሚ የሚያነሷቸውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ ካልተቻለም ለማሻሻል ጥረት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

    ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተናገድ ከጀመሩ በኋላ የሚነሱ ቅሬታዎችን በአጭሩ ለመፍታትም ከተማሪዎች ጋር የሰከነ እና የሰለጠነ ውይይት ማድረጋቸውን የአርባምንጭ እና ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ገልፀዋል። ለዚህም ተማሪዎች እያንዳንዱ ጥያቄ በሂደት እንደሚፈታ ማመናቸውና አርቆ ተመልካችነታቸው ሰላማዊ ሁኔታው እንዲቀጥል ትልቁን ድርሻ እንደተወጣም ተጠቁሟል።

    የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙባቸው አካባቢዎች የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት መሪዎች እና ወጣቶች በሰላማዊ የመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ መደረጉንም ዩኒቨርሲቲዎቹ የገለጹት።

    የዩኒቨርሲቲዎቹ ባለቤት የሆነው ማኅበረሰብ ተማሪዎቹን እንደ ራሱ ልጆች ተመልክቶ እንዲጠብቃቸው የተሰራው ሥራም ውጤታማ እንደነበር ነው ፕሬዚዳንቶቹ የገለጹት።

    ተማሪዎችም በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የታዩ አሰቃቂ ተግባራት እንዳይደገሙ በጋራ መሥራት አለባቸው፤ ከስሜታዊ ድርጊትም ሊታቀቡ ይገባልም ነው ያሉት። የብዙሃኑን ሰላም ለመጠበቅ ጥቂት በጥባጮችን አደብ ማስገዛት ይገባል ብለዋል በመልዕክታቸው።

    ምንጮች፦ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ / የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    በዩኒቨርሲቲዎች የጸጥታ ችግር

Viewing 15 posts - 1 through 15 (of 56 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.