Home › Forums › Semonegna Stories › የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች › የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ 2 ሺህ ተማሪዎች አስመረቀ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ 2 ሺህ ተማሪዎች አስመረቀ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በድኅረ ምረቃ የትምህርት መርሃ ግብር በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ ተማሪዎች አስመረቀ። ዩኒቨርሲቲው አሰልጥኖ ነሐሴ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ለምረቃ ካበቃቸው 2 ሺህ ተማሪዎች በዶክትሬት ዲግሪ እና በሁለተኛ (ማስተርስ) ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው።
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ጥቂት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙ ሲሆን፥ ቀሪዎቹ በቨርቹዋል (virtual) አማካይነት ምርቃታቸውን ማካሄዳቸው ታውቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ለማ ጉዲሳ፥ ተማሪዎች በተማሩት የትምህርት መስክ ሀገራቸውን በተማኝነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል። “የሲቪል ሰርቪሱን ሀገልግሎት አንድ ደረጃ ከፍ ለማድርግ በተማሩት የትምህርት መስክ የበለጠ መሥራት ይኖርባቸዋል” ሲሉም አመልክተዋል። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅትም ዩኒቨርሲቲው እንደ ኦንላይን (online) ያሉ የተለያዩ አማራጭ የማስተማሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም ምሩቃን ተማሪዎች ማሟላት ያለባቸውን እንዲያሟሉ ማድረጉንም ገልጸዋል።
ምሩቃኑ በቀጣይ ወደሥራ ሲሰማሩ ሀገራዊ ለውጡንና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ ሀገልግሎት በመስጠት ሀገራቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉም ነው ያስገነዘቡት። ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣትና ከበለጸጉ ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
ከዛሬው ተመራቂዎች መካከል ብቸኛ የዶክትሬት ተመራቂ የሆኑት ዶ/ር ሰይፉ ተሾመ በበኩላቸው፥ በተማሩት የትምህርት መስክ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በተሻለ ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። “ሁላችንም በመተባበር ለሀገራችን ብልጽግና በአንድነትና በመተባበር መሥራት አለብን” ብለዋል።
ሌላዋ ተመራቂ መሠረት መልኬ በበኩሏ፥ በምትሰማራበት የሥራ መስክ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ለሀገሪቱ እድገት የበኩሏን እንደምትወጣ ተናግራለች። በሀገሪቱ በሚደረገው የልማት እንቅስቃሴ እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የበኩሏን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኗንም ገልጻለች።
የዛሬ ምሩቃንን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ በቅድመ ምረቃ እና ድኅረ ምረቃ የትምህርት መርሃ ግብሮች ከ37 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መስኮች አሰልጥኖ ማስመረቁ ታውቋል።
ዩኒቨርሲቲው ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በሚያደርገው እንቅስቃሴም ለ300 አቅመ ደካማና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች በኮሮና ቫይረስ የሚደርስባቸውን ጉዳት ለመቀነስ የምግብ እና የዘይት ድጋፍ አድርጓል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)