ቦረና ዞን ውስጥ በተከሰተው ድርቅ ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች የተሟላ ድጋፍ ለማድረግ በቅንጅት እየተሠራ ነው

Home Forums Semonegna Stories ትምህርት፣ ጤና እና ሕብረተሰብ ― ሰሞነኛ ዜናዎች፣ መረጃዎች ቦረና ዞን ውስጥ በተከሰተው ድርቅ ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች የተሟላ ድጋፍ ለማድረግ በቅንጅት እየተሠራ ነው

#56088
Semonegna
Keymaster

ቦረና ዞን ውስጥ በተከሰተው ድርቅ ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች የተሟላ ድጋፍ ለማድረግ በቅንጅት እየተሠራ ነው

ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች በሚፈለገው ደረጃ ድጋፍ ማሠራጨት የሚያስችል የቅንጅት ሥራ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ። እስካሁን ከ204 ሺህ በላይ ኩንታል እህል ለተጎጂ ዜጎች መሠራጨቱም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በቦረና ዞን በድርቅ አደጋ ጉዳት ከደረሰባቸው ዜጎች ውስጥ በ13 ወረዳዎች ውስጥ ለሚገኙ ወደ 604 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የዕለት ድጋፍ ቀርቦላቸዋል። ካለፉት ሁለት ወራት በ15 ቀናት ውስጥም ለእነዚሁ ወገኖች 204 ሺህ 765 ኩንታል ምግብ ወደ አካባቢው ተልኮ ተሠራጭቷል። ከጉዳቱ አንጻርና የተጎጂዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ በመንግሥትና በአጋር አካላት ቀጣይ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል የቅንጅት ሥራ እየተሠራ ነው።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፥ ኮሚሽኑ በተለይ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡሮች፣ አጥቢ እናቶችና አቅመ ደካሞች የሚሆን 10 ኩንታል አልሚ ምግብ ወደ አካባቢው ተልኳል። ከዚህ በተጨማሪ የአካባቢው ሕብረተሰብ፣ ባለሀብቱ፣ ድጋፍ ሰጪዎችና መንግሥትም በዚሁ መልኩ ለወገኖች ሊደርስ የሚችለውን ድጋፍ እያቀረቡ ይገኛሉ።

የኦሮሚያ ክልል 800ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የዕለት ድጋፍ መጠየቁን ገልጸው፥ በዚሁ ቁጥር ልክ ድጋፉ እንዲሰጥ ከአጋር አካላት ጋር አብሮ የሚሠራ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ድርቅን በሚመለከት በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ክስተቱ እንዳለ የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ ክስተቱ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የተፈጥሮ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜም በሦስት አካላት ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመው፤ እነዚህም መንግሥት፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። እነዚህም በየአካባቢው ጉዳት ባጋጠመባቸው ስፍራዎች የየድርሻቸውን በመያዝ ምግብና ምግብ-ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ከክልል ጋር በመሆን ለሥርጭት እንዲበቃ ያደርጋሉ ነው ያሉት።

እንዲህ ዓይነት ችግሮች በሚያጋጥሙበት ጊዜ እንደ ኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የማስተባበር ሥራን በመሥራት ከሌሎች ሴክተር መሥሪያ ቤቶችና ከክልሎች ጋር አብሮ የሚሠራባቸው ስልቶች እንዳሉ ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል። ከእነዚህ ሥራዎች ውስጥም በክልል ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል ማቋቋም አንዱ እንደሆነና በዞን ደረጃ ብዙ ቁጥር ያላቸው ወገኖች ጉዳት ሲደርስባቸው የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት እንደሚቋቋም ጠቅሰዋል።

ይህም በክልል የሚመራና ኮሚሽኑ የሚደግፈው የጤና፣ የግብርና፣ የውሃ፣ የትምህርትና ሌሎች ጉዳዮች እንደመኖራቸው ሌሎች ሴክተር መሥሪያ ቤቶችን አስተባብሮ ማስኬድ የሚያስችል ድጋፍ በቅንጅት እየተሠራ እንዳለ አመላክተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ባሉ ሁኔታዎች ምክንያት በአጋር አካላት የሚደርሰው ድጋፍ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳርፉ ይችላሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፥ የተበታተነውን ሁኔታ መሰበሰብ የሚያስችል ከሀገር ቤት እስከ ውጭ ያሉ አካላት የሚሳተፉበት ተግባራትም እንዳሉ ጠቁመዋል።

አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያምን ጨምሮ በየቢሯቸው በመገኘት አጋር አካላትን፣ ኤምባሲዎችን፣ የመንግሥታቱ ኅብረት ተወካዮችን እያነጋገሩ እንዳለ ገልጸዋል። በዚህ መልክ ድጋፉ እንዲጠናከር ይደረጋል ሲሉም አስታውቀዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት፥ በሀገሪቷ ድርቅና ሌሎች ተዛማች ችግሮች አሉ። በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ለመቋቋም ከሀገር ውስጥ አቅም ባሻገር የአጋር አካላት አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው። ለዚህም አጋር አካላት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥረት እየተደረገ ነው። በአሁኑ ወቅትም ድጋፉ እየመጣ ነው፤ ለዚህም በሚፈለገው ደረጃ ማሠራጨት የሚያስችል የቅንጅት ሥራ እየተሠራ ነው።

ከመንግሥት እንቅስቃሴ በተጨማሪ የተለያዩ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያዊ ተቋማት ቦረና ዞን ውስጥ በተከሰተው ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የተለያዩ እርዳታዎችን እያሰባሰቡ ይገኛሉ። እርስዎም በዚህ ድጋፍ ለመሳተፍ የሚከተሉትን ማስፈንጠሪያዎች ይጫኑ።

  1. ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት (GARE) በጎፈንድሚ (GoFundMe) በኩል፦ GARE4Borena
  2. በሀገር ውስጥ ደግሞ የጉዞ አድዋ ማኅበር አስተባባሪ ያሬድ ሹመቴ (Yared Shumete) እና መምህር ታዬ ቦጋለ አረጋ “ዓድዋ 127 ለቦረና” በሚል እንቅስቃሴ በመጀመር የተለያዩ ድጋፎችን (ገንዘብ፣ የምግብ ምርቶችን፣ ወዘተ) እያሰባሰቡ ነው። ያግኟቸው፦ http://www.facebook.com/shumeteyared እና http://www.facebook.com/tayebogale.arega