Home › Forums › Semonegna Stories › የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች › የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ቀዳሚ ተቋም ለመሆን እየሠራ ነው
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ቀዳሚ ተቋም ለመሆን እየሠራ ነው
አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ቀዳሚ ተቋም ለመሆን እየሠራ መሆኑ ተገለጸ። አስራ ሰባት (17) ችግር ፈቺ ምርምሮች ተሠርተው ወደ ግምገማ እና ትግበራ ገብተዋል።
ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ቆይታ ያደረጉት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ዘውዴ እንደተናገሩት፥ ተቋሙ በ2022 ዓ.ም ከአፍሪካ ካሉ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩቶች ቀዳሚው ለመሆን እየሠራ ነው።
በዚህም 17 የሚሆኑ ችግር ፈቺ ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑንና ከፊሉ ወደ ትግበራ ማስገባታቸውን፥ እንዲሁም የተቀሩትን ምርምሮች ወደ ትግበራ ለማስገባት በግምገማ ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ምርምሮቹም በጤና፤ በትምህርት፤ በአገልግሎት አሰጣጥና በፋይናንስ ዘርፍ ግልጋሎት እምርታዊ ለውጥ የሚያመጡ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መተግበሪያዎች መሆናቸውን አስረድተዋል። ለአብነት ያህልም በጤናው መስክ፥ የተለያዩ የሕክምና ዘርፉን ሊያዘምኑ ወይም ሊያሻሽሉ የሚችሉ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ ውስን የሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች የሚገኙባቸው ሴክተሮች ላይ ተጨባጭ ውጤት ያመጣልም ብለዋል።
የጭንቅላት እጢ፣ የጡት ካንሰር፣ የቆዳ በሽታ ልየታን ማከናወን የሚችሉ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መተግበሪያዎች መዘጋጀታቸውንም አብራርተዋል። በአዲስ አበባ ስማርት ሲቲ (smart city) ግንባታ ላይ ወሳኝ ሚና ያላቸው የስማርት ሴኩሪቲ (smart security) ግንባታዎች እየተካሄዱ እንዳሉ የገለጹት አቶ ተስፋዬ፥ በርካታ ዓለም አቀፍ ሁነቶች በሚካሄዱባት አዲስ አበባም በሺዎች የሚቆጠሩ የአርተፊሻል ኢተለጀንስ ካሜራዎች መገጠማቸውን አንስተዋል። ካሜራዎቹ የፊት ገፅታን እና የመኪና ሰሌዳ ቁጥሮችን የሚለዩ እና የሚመዘግቡ መሆናቸውን አያይዘው ጠቅሰዋል።
በፋይናንስ ሴክተር የውይይት መለዋወጫ ሮቦት (ቻትቦት/chatbot) በማዘጋጀት ዘርፉን የሚያዘምኑ ሥራዎች እየተከወኑ እንዳሉ በማብራራትም፤ ቻትቦቶቹ በተመረጡ ሀገርኛ ቋንቋዎች ጭምር ግልጋሎት ይሰጣሉ ብለዋል። የደረቅ ጭነት የተቀናጀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መተግበሪያ ደግሞ ለትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚንስቴር አበርክቶ መተግበሪያዎቹ ግልጋሎት መስጠት መጀመራውን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አትተዋል።
በትምህርቱ መስክ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመረጃ አሰጣጥ አገልግሎታቸውን ማዘመን የሚያስችል እና የሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን ማስቀረት የሚያስችል እጅግ ዘመናዊ የሆነ መተግበሪያ ለምቶ ትግበራ ላይ መዋሉንም ጨምረው ጠቅሰዋል። የተለያዩ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሥርዓቶች በቅልጥፍና እንዲሠሩ እና ለመረጃ ቋትነት ግልጋሎት የሚሰጥ ማዕከል ግንባታም በተቋሙ ውስጥ ተከናውኗል ያሉት ዳይሬክተሩ አቶ ተስፋዬ ዘውዴ፥ የመረጃ ቋት መኖሩ ለተማሪዎችም ይሁን ለመምህራን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት