Home › Forums › Semonegna Stories › ሰሞነኛ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሪዎች ምርቃት › ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 4,700 ተማሪዎችን ዛሬ አስመረቀ
ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 4,700 ተማሪዎችን ዛሬ አስመረቀ
ሐዋሳ (ኢዜአ/HU) – ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በበይነ-መረብ (virtual) ትምህርታቸውን እንዲጨርሱ ያስቻለቸውን የድኅረ ምረቃ (ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ) ተማሪዎች እንዲሁም ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በፊት በእንስሳት ሕክምና እና በሌሎች መርሀ-ግብሮች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ የመጀመሪያ ዲግሪ 4,780 ተማሪዎችን ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም አስመረቀ።
ዩኒቨርሲቲው ለ21ኛ ጊዜ ካስመረቃቸው መካከል 2,866 በመጀመሪያ፣ 1,900 በሁለተኛ እና 12 ደግሞ በሦስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸው መሆናቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ገልጸዋል።
ተማሪቂዎችና ቤተሰቦቻቸው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) ምክንያት የተፈጠረውን አስቸጋሪ ሁኔታ ተቋቁመው ለመመረቅ በመብቃታቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው ወረርሽኙን ከመከላከሉ ሥራ በተጓዳኝ ችግር ፈቺ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች ላይ ትኩረት በመስጠት እና የመንግሥትን የልማት እንቅስቃሴ በጥናት ለመደገፍ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ወረርሽኙን እየተከላከሉ መደበኛ የትምህርት ሥራቸውን ለመጀመር እየተዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል።
ዶ/ር አያኖ በአዲሱ ፍኖተ-ካርታ መሠረት የምርምር ዩኒቨርሲቲ (Research University) ለመሆን ከሚጠበቁት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በቀዳሚነት ለማሰለፍ በቁርጠኝነት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ምክትል ቦርድ ሰብሳቢና የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው ተመራቂዎች የቀሰሙትን ዕውቀት በተግባር በማዋል የሀገሪቱን ዕድገት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። ተቋሙ በተደራረበ ጫና ውስጥ እያለ ተማሪዎችን ማስመረቁ፥ ምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን አጠናክሮ መቀጠሉ የአመራሩንና የሠራተኞችን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በእንስሳት ሕክምና ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የተመረቀው ዶ/ር ግርማ በዳዳ በሰጠው አስተያየት፥ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ጫና በመቋቋምና ጥናቱ ላይ በመትጋት ለምርቃ መብቃቱን ተናግሯል። ለዚህም ዩኒቨርሲቲውን አመሰግኗል።
ሌላዋ በሶሻል ሣይኮሎጂ የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂ ማርታ ማጋ በበኩሏ፥ ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት የክፍል ትምህርት ማጠናቀቃቸውን ጠቅሳ፤ የምርምር ሥራዋን ከዩኒቨርሲቲው ውጭ በማካሄድ ለመመረቅ እንደበቃች ገልጻለች።
ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና ተከታታይ የትምህርት መርሀ-ግብር የሚያስተምራቸው ከ43,000 በላይ ተማሪዎች እንዳሉት ከዩኒቨርሲቲው ድረ-ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ዩኒቨርሲቲው በአጠቃላይ ከ7,000 በላይ ሠራተኞች (staff)፣ ሰባት ካምፓሶች፣ ስምንት ኮሌጆችና ሁለት ተቋማት (institutes)፣ እና ከ200 በላይ የትምህርት መርሀ ግብራት (programs) እንዳሉት ድረ-ገጹ ያሳያል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)/ ዩኒቨርሲቲው (HU)