ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሁለተኛውን የምገባ ማዕከል ለማቋቋም የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ

Home Forums Semonegna Stories ትምህርት፣ ጤና እና ሕብረተሰብ ― ሰሞነኛ ዜናዎች፣ መረጃዎች ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሁለተኛውን የምገባ ማዕከል ለማቋቋም የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ

#48250
Semonegna
Keymaster

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሁለተኛውን የምገባ ማዕከል ለማቋቋም የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ

አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከአዲስ አበባ ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር ለድርጅቱ ሁለተኛውን የምገባ ማዕክል (ተስፋ ብርሀን አሙዲ ቁጥር 2) ለማቋቋም የስምምነት ሰነድ ሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ተፈራርሟል።

በከተማዋ የሚገኙ በቀን አንድ ጊዜ መመገብ ለማይችሉ ዜጎች ጤናውን የጠበቀ ምግብ እንዲያገኙ ስድስት የምገባ ማዕከላት መገንባታቸውን ከተማ አስተዳደሩን በመወከል የስምመነት ሰነድ የተፈራረሙት የአዲስ አበባ ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሀና የሺንጉስ ተናግረዋል።

መንግሥት ከድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር በመተባበር ስራዎች እያከናወነ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊዋ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከዳሽን ባንክ ኃ.የተ.የግ.ማ. ጋር በመተባበር ለከተማችን ሰባተኛ ለድርጅቱ ደግሞ ሁለተኛ የሆነ የምገባ ማዕከል ለማቋቋም አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል፤ ለዚህ የሚውል የ40 ሚልየን ብር ወጪ ለማድረግ የስምምነት ሰነድ መፈራረሙንም አስረድተዋል።

በሚድሮክ ኢቨስትመንት ግሩፕ የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አምባሳደር አሊ ሱለይማን በበኩላቸው ሀገራችን እያስተናገደችው ያለው ማኅበራዊ ችግር በሀገሪቷ ብሎም በከተማዋ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ቁጥር ከፍ አድርጎታል ብለዋል። ለዚህም ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለፈው ዓመት “ተስፋ ብርሀን አሙዲ” የተሰኘ የምገባ ማዕከል በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አቋቁሞ እየሠራ መሆኑን አስታውሰዋል።

በዚህ ሰዓትም ቁጥር ሁለት ተስፋ ብርሀን አሙዲ የምገባ ማዕከልን በልደታ ክፍለ ከተማ በመገንባት ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ስራ መጀመሩን ገልፀዋል።

በስምነት ሰነዱም ቢሮው የመገንቢያ ቦታ የማመቻቸት፣ ከቦታው ጋር ተያይዘው ለሚነሱ የሦስተኛ ወገን የመብት ጥያቄ ኃላፊነት ወስዶ ለማመቻቸት እና የተመጋቢ ምልመላና መረጣ የመሳሰሉ የከተማ አስተዳደሩ ኃላፊነቶችን እንደሚወጣ ተገልጿል።

ሚድሮክ የኢንቨስትመንት ግሩፕ ከዳሽን ባንክ ኃ.የተ.የግ.ማ. ጋር በመተባበር በሚገነቡበት ቦታ ላይ የሚገኙና በዝቅተኛ ኑሮ ለሚኖሩ ስምንት አባወራዎች ስምንት የመኖሪያ ቤቶች ለመገንባት እንዲሁም ባሉበት የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን 16 የሱቅ ቤቶች በመገንባት ለማስረከብ እንደሚሠራምዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በምገባ ማዕከሉ ቅጥር ግቢ ያለውን ክፍት ቦታ በከተማ ግብርና ለማልማትና የልማቱን ውጤትም ለተመጋቢዎች በምግነት እንዲጠቀሙ ለማድረግ እንደሚሠራ በሚድሮክ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት አምባሳደር አሊ አረጋግጠዋል።

በተያያዘ ዜና፥ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ (ኢትዮ አግሪ ሴፍት ኃላ/የተ/የግል ማኅበር) እና በላይነህ ክንዴ ግሩፕ (ፊቤላ ኢንዱስትሪስ ኃላ/የተ/የግል ማኅበር) በጥምረት በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ውስጥ በምትገኘው ማንኩሳ ከተማ ያስገነቡት ዘመናዊ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቆ ሥራውን ጀምሯል

ማንኩሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፥ ግንባታው ብቻ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል፤ የወጪው 75 በመቶ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ተሸፍኗል፤ ትምህርት ቤቱን ገንብቶ ለመጨረስ የወሰድው ጊዜ ስምንት ወራትን ብቻ ሲሆን፥ ትምህርት ቤቱ 36 የመማሪያ ክፍሎች፣ ዘመናዊና የተሟሉ የአስተዳደር ህንጻዎች፣ ቤተ-መጽሐፍት፣ የተሟላ ቤተ-ሙከራ፣ የመረጃና ግንኙነት ቴክኖሎጂ (ICT)፣ ንጹህ የሴትና የወንድ መፀዳጃ ቤት ህንጻዎች እና ሌሎችም የትምህርት ግብዓቶች ተሟልተውለታል።

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ