ኢሰመኮ – በወላይታ ዞን የተቃውሞ ሰልፍ ያደርጉ የነበሩ ስዎች ላይ የጸጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ተጠቅሟል

Home Forums Semonegna Stories የሰብዓዊ መብቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ ኢሰመኮ – በወላይታ ዞን የተቃውሞ ሰልፍ ያደርጉ የነበሩ ስዎች ላይ የጸጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ተጠቅሟል

#15371
Anonymous
Inactive

ወላይታ ዞን ውስጥ የጸጥታ ኃይሎች በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ከመጠቀም ሊቆጠቡ ይገባል!
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)

አዲስ አበባ (ኢሰመኮ) – ወላይታ ዞን ውስጥ በአንዳንድ ከተሞች ነሐሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በተደረጉት ተቃውሞዎች የፀጥታ ኃይሎች በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ የወሰዱት እርምጃ ተመጣጣኝነት አጠያያቂ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።

የተለያዩ ምንጮች እንደጠቆሙት የተቃውሞ ሰልፉ የተቀሰቀሰው ሰኞ ዕለት በፌዴሬሽኑ ውስጥ አዲስ የክልል መንግሥት መመሥረትን በተናጠል ለማወጅ በፈለጉ በርካታ ከፍተኛ የዞኑ ባለስልጣናት እስርን ተከትሎ ነው። የመንግሥት ባለስልጣናት እንደሚሉት ከሆነ ግን ታሳሪዎቹ በአካባቢው አለመረጋጋት ለመፍጠር ሲያሴሩ ተይዘዋል ብለዋል።

የኮሚሽኑ የመረጃ ምንጮች እንዳስረዱት የባለስልጣናቱን እስር ተከትሎ የተቃውሞ ሰልፈኞች በዞኑ ዙሪያ በሚገኙ በርካታ ከተሞች ወደ ጎዳናዎች የወጡ ሲሆን፥ በዞኑ ዋና ከተማ በሶዶ አንድ ሰው እንዲሁም በቦዲቲ ከተማ አምስት ሰዎች መሞታቸው ታውቋል ።

በሰኞው እስር ወቅት በጠቅላላው 178 ሰዎች የተያዙ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ 28ቱ የዞኑ ከፍተኛ ባለስልጣናት መሆናቸው እና በወላይታ ሶዶ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ ውስጥ በቁጥጥር ስር የሚገኙ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ቃል አቀባይ አቶ አሮን ማሾ እንደገለጹት፥ “የፀጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ሰልፎችን በሚቆጣጠሩበት ወቅት የሞት አደጋን የሚያስከትል የኃይል እርምጃ ከመውሰድ ሊቆጠቡ ይገባል፤ እንደነዚህ ያሉ እርምጃዎች ቀድሞውኑን የነበረ ውጥረትን ያባብሱ እንደሆን እንጂ መፍትሔ አይሆኑም” ብለዋል።

አቶ አሮን አያይዘውም በግጭቱ ወቅት የተከሰተው የ6 ሰልፈኞች አሟሟትን እና የጸጥታ ኃይሎች የኃይል አጠቃቀምን አስመልክቶ ፈጣን ምርመራ የሚያስፈልግ መሆኑን አስረድተዋል። እንዲሁም የታሳሪዎችን መብቶች ማክበርና በአፋጣኝ ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።

ለስረ-ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ከመፈለግ አንጻርም የፌዴራልና የክልሉ መንግሥታት በክልሉ ውስጥ ለተነሱት የክልልነት ጥያቄዎች ወቅታዊና ሰላማዊ መፍትሔ በሥራ ላይ እንዲውል ከፍተኛ ጥረትና ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል።

ወላይታ ዞን ውስጥ በተቀሰቀሰው ግጭት የተከሰተው ምንድን ነው?

ባለፈው እሁድ (ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም.) ከወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄ መልስ አልተሰጠንም በሚል በተነሳ የተቃውሞ ሰልፍ፥ በነጋታው (ነሐሴ 4 ቀን) በተቃዋሚዎችና በጸጥታ ኃይሎች መካከል በተነሳ ግጭት ቢያንስ የአስር ሰዎች ሕይወት ማለፉን ሮይተርስ ዘግቧል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የጠቀሳቸው የቦዲቲ ከተማ የጤና ቢሮ ከፍተኛ ባለሥልጣን ተመስገን ሕሊና ነሐሴ 4 ቀን በቦዲቲ ከተማ ቢያንስ ስድስት ሰዎች የጸጥታ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ መገደላቸውን ተናግረዋል። ለሌሎችም (ለተጎዱ ሰዎች) የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና እርዳታ መስጠታቸውን የተናገሩት አቶ ተመስገን፥ የጥቃቱ ሰለባዎች ጭንቅላታቸው፣ ሆዳቸውንና ደረታቸው ላይ መመታታቸውን ገልጸዋል። ከሞቱት መካከል የ14 ዓመት ታዳጊ ወጣት እንደሚገኝበትና የቆሰሉትም በቁጥር እንደሆኑ አክለው ተናግረዋል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የጤና መኮንን ደግሞ፥ በሶዶ ከተማ አራት ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች ተተኩሶባቸው የተገደሉ ሰዎች ማየታቸውን ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ከዚሁ ዜና ጋር በተያያዘ፥ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዱዓለም ታደሰ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ 21 ሰዎች መገደላቸውን እና ከ105 በላይ መቁሰላቸውን እንዳረጋገጡ ለዶይቼ ቬለ የአማረኛ ዝግጅት ክፍል ገልጸዋል።

ወላይታ ዞን