Search Results for 'የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን'

Home Forums Search Search Results for 'የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን'

Viewing 3 results - 1 through 3 (of 3 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    ወላይታ ዞን ውስጥ የጸጥታ ኃይሎች በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ከመጠቀም ሊቆጠቡ ይገባል!
    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)

    አዲስ አበባ (ኢሰመኮ) – ወላይታ ዞን ውስጥ በአንዳንድ ከተሞች ነሐሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በተደረጉት ተቃውሞዎች የፀጥታ ኃይሎች በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ የወሰዱት እርምጃ ተመጣጣኝነት አጠያያቂ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።

    የተለያዩ ምንጮች እንደጠቆሙት የተቃውሞ ሰልፉ የተቀሰቀሰው ሰኞ ዕለት በፌዴሬሽኑ ውስጥ አዲስ የክልል መንግሥት መመሥረትን በተናጠል ለማወጅ በፈለጉ በርካታ ከፍተኛ የዞኑ ባለስልጣናት እስርን ተከትሎ ነው። የመንግሥት ባለስልጣናት እንደሚሉት ከሆነ ግን ታሳሪዎቹ በአካባቢው አለመረጋጋት ለመፍጠር ሲያሴሩ ተይዘዋል ብለዋል።

    የኮሚሽኑ የመረጃ ምንጮች እንዳስረዱት የባለስልጣናቱን እስር ተከትሎ የተቃውሞ ሰልፈኞች በዞኑ ዙሪያ በሚገኙ በርካታ ከተሞች ወደ ጎዳናዎች የወጡ ሲሆን፥ በዞኑ ዋና ከተማ በሶዶ አንድ ሰው እንዲሁም በቦዲቲ ከተማ አምስት ሰዎች መሞታቸው ታውቋል ።

    በሰኞው እስር ወቅት በጠቅላላው 178 ሰዎች የተያዙ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ 28ቱ የዞኑ ከፍተኛ ባለስልጣናት መሆናቸው እና በወላይታ ሶዶ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ ውስጥ በቁጥጥር ስር የሚገኙ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ቃል አቀባይ አቶ አሮን ማሾ እንደገለጹት፥ “የፀጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ሰልፎችን በሚቆጣጠሩበት ወቅት የሞት አደጋን የሚያስከትል የኃይል እርምጃ ከመውሰድ ሊቆጠቡ ይገባል፤ እንደነዚህ ያሉ እርምጃዎች ቀድሞውኑን የነበረ ውጥረትን ያባብሱ እንደሆን እንጂ መፍትሔ አይሆኑም” ብለዋል።

    አቶ አሮን አያይዘውም በግጭቱ ወቅት የተከሰተው የ6 ሰልፈኞች አሟሟትን እና የጸጥታ ኃይሎች የኃይል አጠቃቀምን አስመልክቶ ፈጣን ምርመራ የሚያስፈልግ መሆኑን አስረድተዋል። እንዲሁም የታሳሪዎችን መብቶች ማክበርና በአፋጣኝ ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።

    ለስረ-ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ከመፈለግ አንጻርም የፌዴራልና የክልሉ መንግሥታት በክልሉ ውስጥ ለተነሱት የክልልነት ጥያቄዎች ወቅታዊና ሰላማዊ መፍትሔ በሥራ ላይ እንዲውል ከፍተኛ ጥረትና ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል።

    ወላይታ ዞን ውስጥ በተቀሰቀሰው ግጭት የተከሰተው ምንድን ነው?

    ባለፈው እሁድ (ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም.) ከወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄ መልስ አልተሰጠንም በሚል በተነሳ የተቃውሞ ሰልፍ፥ በነጋታው (ነሐሴ 4 ቀን) በተቃዋሚዎችና በጸጥታ ኃይሎች መካከል በተነሳ ግጭት ቢያንስ የአስር ሰዎች ሕይወት ማለፉን ሮይተርስ ዘግቧል።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል የጠቀሳቸው የቦዲቲ ከተማ የጤና ቢሮ ከፍተኛ ባለሥልጣን ተመስገን ሕሊና ነሐሴ 4 ቀን በቦዲቲ ከተማ ቢያንስ ስድስት ሰዎች የጸጥታ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ መገደላቸውን ተናግረዋል። ለሌሎችም (ለተጎዱ ሰዎች) የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና እርዳታ መስጠታቸውን የተናገሩት አቶ ተመስገን፥ የጥቃቱ ሰለባዎች ጭንቅላታቸው፣ ሆዳቸውንና ደረታቸው ላይ መመታታቸውን ገልጸዋል። ከሞቱት መካከል የ14 ዓመት ታዳጊ ወጣት እንደሚገኝበትና የቆሰሉትም በቁጥር እንደሆኑ አክለው ተናግረዋል።

    ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የጤና መኮንን ደግሞ፥ በሶዶ ከተማ አራት ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች ተተኩሶባቸው የተገደሉ ሰዎች ማየታቸውን ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    ከዚሁ ዜና ጋር በተያያዘ፥ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዱዓለም ታደሰ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ 21 ሰዎች መገደላቸውን እና ከ105 በላይ መቁሰላቸውን እንዳረጋገጡ ለዶይቼ ቬለ የአማረኛ ዝግጅት ክፍል ገልጸዋል።

    ወላይታ ዞን

    Semonegna
    Keymaster

    የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ጊዜያዊ ውጤትን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
    ህዳር 13 ቀን 2012 ዓ.ም
    ሀዋሳ

    የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ኅዳር 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የሲዳማ ዞን በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ሕዝብ ውሳኔ ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ተካሂዷል።

    የሕዝበ ወሳኔው አፈፃፀም ተአማኒ፣ ሰላማዊ እና ፍትሃዊ አንዲሆን ለማድረግ ቦርዱ እስከ ሕዝብ ውሳኔው ድምጽ መስጫ ዕለት ድረስ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። ቦርዱ የሕዝበ ውሳኔውን ጥያቄ የማስፈፀም ኃላፊነቱን መወጣት የጀመረው ሂደቱ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ እና ተአማኒ እንዲሆን እንዲሁም በሲዳማ ዞን እና በሀዋሳ ከተማ የሚኖሩ ዜጎች ያለ አድልዎ ፍላጎታቸውን የሚገልፁበት አሠራር ለመዘርጋት የሚያስችል የሲዳማ ሕዝብ ውሳኔ አፈፃፀም መመሪያ በማጽደቅ ነው።

    ከዚህ በተጓዳኝ የሕዝብ ወሳኔውን የአፈፃፀም የጊዜ ሰሌዳ በማዘጋጀት ለሚመለከታቸው የክልሉ እና የዞን መስተዳደር አካላት እንዲደርስ ለሕዝብም ይፋ እንዲሆን ተደርጓል። ቦርዱ በሕዝብ ውሳኔው እቅድ አፈፃፀም ከክልሉና የዞኑ መስተዳደር አካላት ጋር በርካታ ውይይት እና ስምምነቶችን አድርጓል። በዚህም መሠረት ለሕዝብ ውሳኔ ማስፈፀሚያ የሚያስፈለገውን በጀት በክልሉ መንግሥት እንዲፈቀድ ተደርጓል። ሕዝብ ውሳኔው በሰላማዊ ሁኔታ ለማስፈፀም አስፈላጊ ሁኔታዎችን የክልሉ ምክር ቤት አስቀድሞ እንዲፈጽም በጠየቀው መሠረት የሕዝቡ ውሳኔ የሲዳማ ዞን በክልልነት እንዲደራጅ የሚል ከሆነ በዞኑ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ብሔረሰቦች መብት ጥበቃንና አዲስ በሚፈጠረው እና ነባሩ ክልል መሃከል የሚኖረውን የሃብት ክፍፍል የሚወሰንበት አስተዳደርና በሕግ ማእቀፍ አውጥቶ አቅርቧል።

    በቅድመ ሕዝበ ውሳኔ ዝግጅት በቦርዱ ባለሞያዎች የመስክ ጥናት አካሂደው የድምፅ መስጫ ጣቢያዎችን መረጃ አደራጅተዋል። በዚህም መሠረት ለሕዝበ ውሳኔው ማስፈጸሚያ 1692 ምርጫ ጣቢያዎች የተቋቋሙ ሲሆን ከድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ በኋላ ተጨማሪ 169 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ተደራጅተዋል። የሕዝብ ወሳኔው አፈፃፀም ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲያስችል የክልሉ፣ ከዞኑ፣ ከሀዋሳ ከተማ እንዲሁም የፌደራል የጸጥታ ተቋማት እና አስተዳደር ተቋማት የሕዝበ ውሳኔው ፀጥታ ዕቅድ አዘጋጅተው አቅርበዋል። የዕቅዱንም አፈጻጸም ቦርዱ በጋራ ሲከታተል ቆይቷል። ከቅድመ ሕዝበ ውሳኔ ዝግጅት እስከ ድኅረ ሕዝበ ውሳኔ የነበረው የፀጥታና ደኅንነት ሁኔታ በዚህ ዕቅድ መሠረት በጋራ ኮሚቴ በየጊዜው እየታየ ሰላማዊ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ተችሏል።

    ሕዝበ ውሳኔውን በገለልተኝነትና በሕግ መሠረት የሚያስፈፅሙ 6843 አስፈፃሚዎችን ከአዲስ አበባ ከተማ እና ኦሮሚያ ክልል አከባቢዎች በመመልመል በዞኑ ያሰማራ ሲሆን ሁሉም አስፈጻሚዎች ሕዝበ ውሳኔውን እንዴት እንደሚያስፈጽሙ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። ስልጠናውም ቀድመው የአሰልጣኞች ስልጠና በወሰዱ 20 አሰልጣኞች ለ5 ቀናት የተከናወነ ሲሆን ሁሉም አስፈጻሚዎች የታተመ የማስፈጸሚያ መመሪያ (manual) እንዲኖራቸው ተደርጓል።

    የመራጮች ምዝገባ በዞኑ እና በሀዋሳ ከተማ መስተዳድር ለሚኖሩ ማንኛውም ሕጋዊ መስፈርቱን ለሚያሟሉ ዜጎች ክፍት ሆኖ ከጥቅምት 27 እስከ ህዳር 06 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ምዝገባው ተካሂዶ 2,280,147 ድምጽ ሰጪዎች ተመዝግበዋል።

    የድምጽ ሰጪዎች ሕዝበ ውሳኔው ድምጻቸውን ለመስጠት እንዲመዘገቡ ለመቀስቀስ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የተለያዩ የምዝገባ መስፈርቶችን የሚገልጹ እንዲሁም ስለድምጽ አሰጣጡ የሚያብራሩ መልእክቶች ተላልፈዋል። በድምጽ ሰጪዎች ምዝገባና ድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ የዜጎች መብት እንዳይገደብ እና የሂደቱን ሰላማዊነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል። ከነዚህም መካከል የመጀመሪያው የቦርዱ አመራር አባላት በሀዋሳበይርጋለም፣ በወንዶ ገነት፣ በበሌላ፣ በመዘዋወር የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባና ድምጽ ሰጪዎች ድምጽ አሰጣጥ ሂደት ክትትል በማድረግ የታዩ ጉድለቶች እና የአሠራር ዝንፈቶች እንዲስተካከሉ ያደረጉ ሲሆን፣ በተጨማሪም ዜጎች በድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ እንዲሁም በድምጽ መስጠት ሂደቱ የታዘቧቸውን ግድፈቶች በቀጥታ ለቦርዱ ለማሳወቅ እንዲችሉ የቀጥታ የስልክ መስመሮች ተዘጋጅተው ለመገናኛ ብዙኃን እና ማኅበራዊ ሚዲያ ይፋ ተደርጓል። በደረሱት ጥቆማዎችም መሠረት የተለያዩ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲሁም መረጃዎች ሲሰጡ ቆይተዋል።

    በቦርዱ አባላት በተደረጉ ጉብኝቶች እና ቀደም ብሎ ከዞኑ እና ከክልል መስተዳድር ተቋማት ጋር በተደረጉ ተከታታይ ግንኙነቶች በሕዝበ ውሳኔው ሂደት በርካታ ማስተካከያዎች የተደረጉ ሲሆን ከነዚህም ጥቂቶቹ፦

    • የአካባቢ ሚሊሻ አባላት የምርጫ ጣቢያዎችን ጸጥታ አጠባበቅ ምንም አይነት ሚና እንዳይኖራቸው ተደርጓል፤
    • በሕዝበ ውሳኔው አፈጻጸም ያልተገባ ጣልቃ ገብነት የፈጸሙ ሰዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፤
    • በሕዝበ ውሳኔው መራጮች ምዝገባ እና ድምጽ መስጠት ሂደት ሁለቱም አማራጮችን የሚወክሉ ወኪሎች አንዲገኙ ጥረት ተደርጓል፤
    • የተጓደሉ የሕዝበ ውሳኔ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶች በፍጥነት እንዲሟሉ ተደርጓል።

    የሕዝበ ውሳኔውን ሂደት ሰላማዊ ፣ ፍትሃዊነት እና ግልጽነቱን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም ለወደፊት መሻሻል ላለባቸው አሠራሮች ትምህርት ለመውሰድ ለ128 የሲቪል ማኅበራት ታዛቢዎች እና 74 የአገር ውስጥና የውጪ ሚዲያ ጋዜጠኞች ሂደቱን እንዲታዘቡና እንዲዘግቡ የሚያስችል እውቅና ተሰጥቷል። በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመነጋገር የኮሚሽኑ 20 ታዛቢዎች ሕዝበ ውሳኔውን እንዲታዘቡ ተደርጓል። በኢትዮጵያ መንግሥት ሕዝበ ውሳኔውን እንዲታዘቡ ፍቃድ የተሰጣቸው የአሜሪካን መንግሥት ወኪሎችና ዲፕሎማቶች ሕዝበ ውሳኔን እንዲታዘቡ አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጓል።

    የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ ከተጠናቀቀበት እስከ ድምጽ መስጫው ቀን ባሉት ጥቂት ቀናት ቦርዱ የድምጽ መስጫ ቁሳቁሶችን ያሰራጨ ሲሆን በዚህም ሂደት 3000 የድምጽ መስጫ ሳጥኖች እና 2.5 ሚሊዮን በላይ (መጠባበቂያን ጨምሮ) የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እንዲሁም የተለያዩ ቅጾችና ቁሳቁሶች ስርጭት ተከናውኗል።

    በሕዝበ ውሳኔው ሂደት ጸጥታ እና ደኅንነት አስመልክቶ ቦርዱ ሂደቱን በሚመራበት ወቅት የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም መረጃ በመሰብሰብ፣ በሀዋሳ ከተማ እንዲሁም በሌሎች ወረዳዎች የሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች የመስክ ጉብኝት አድርጓል። ከአስተዳደር ወሰን ጋር በተያያዘ እና ቀድሞ ግጭት በነበረባቸው የተወሰኑ ቀበሌዎች ከማኅበረሰብ ክፍሎች የቀረቡ አቤቱታዎችን በማዳመጥ የቦርድ አመራር አባላት በቦታው በመገኘት የመስክ ቅኝቶችን አድርገው ከቀበሌ አስተዳደሮች ጋርም ውይይት አድርገዋል። ከውይይቱም በተጨማሪ የሲዳማ ዞን እና የደቡብ ክልል የጸጥታ አካላት፣ የፌደራል ፓሊስ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊትን ያካተተ የፀጥታ ችግሮችን በጋራ የሚያይ መድረክ በማቋቋም ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን ተደርጓል።

    ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. የተከናወነው የድምጽ መስጠት ሂደት ሰላማዊ እና ጉልህ የሎጄስቲክስ ችግር ያልታያበት ሲሆን አንዳንድ ቦታዎች ላይ የመራጮች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ሰልፎች ከመኖራቸው በስተቀር በታቀደበት ሁኔታ ተጠናቋል። በዕለቱ የቦርድ አመራር አባላት የመስክ ጉብኝቶችን ያካሄዱ ሲሆን የምርጫ ቆጠራውም በዕለቱ ተጠናቆ በየምርጫ ጣቢያዎቹ ተለጥፏል። በዕለቱ ከመራጮች የሚመጡ ጥቆማዎችንም መሠረት በማድረግ የተለያዩ እርምት እርምጃዎች ሲከናወኑ ውለዋል።

    በዚህም መሠረት በአጠቃላይ ከተመዘገበው 2,280,147 መራጭ 2,277,063 ሰው ድምጹን ሰጥቷል። ይህም የምርጫ ቀን የድምጽ መስጠት ተሳትፎ (voter turnout) 99.86 በመቶ መሆኑን ያሳያል። ሲዳማ በነባሩ ክልል ውስጥ እንዲደራጅ ጎጆ ምልክትን የመረጠ ሰው ብዛት 33,463 ሲሆን የሲዳማ በክልልነት መደራጀትን ሻፌታን የመረጠ ሰው ብዛት 2,225,249 ነው። በውጤቱም ሻፌታ የመረጠው 98.51 % ሲሆን ጎጆን የመረጠው 1.48 % ነው። ። በሂደቱ የዋጋ አልባ ድምጽ ቁጥር 18,351(0.01%) ነው። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 47/2/ እና /3/ ማንኛውም ብሄር ብሄረሰብ ወይም ሕዝብ የራሱ ክልል የመቋቋም መብት አለው በማለት በሚደነግገው መሠረት፥ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ተፈጽሟል። የዞኑ ነዋሪዎች በነፃ ፈቃዳቸው በሰጡት ውሣኔ መሠረት ሲዳማ ክልል ሆኖ መደራጀት የሚያስችለውን ድምፅም በዚህ ውሳኔ አግኝቷል።

    የሕዝበ ውሳኔው ሂደት ሰላማዊና ተአማኒ እንዲሁም ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ የታየበት ነው። ሕዝበ ውሳኔው ዜጎች መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ ተግባራዊ ያደረጉበት እና በሀገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አንድ እርምጃ ነው ብሎ ቦርዱ ያምናል። በውጤቱ መሠረትም በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 47/3/መ ላይ እንደተጠቀሰው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት እና በሲዳማ ዞን አስተዳደር የሕዝቡን ድምጽ ባከበረ፣ ሰላማዊ እና ግልጽ በሆነ መልኩ እንዲሁም ሽግግሩን ጊዜን በጠበቀ ሁኔታ በማከናወን የስልጣን ርክክቡን በአግባቡ አከናውነው ይህንን ሕዝበ ውሳኔ ውጤት እንደሚያስፈጽሙ ቦርዱ የጸና እምነት አለው።

    ያጋጠሙ ተግዳሮቶች
    የሕዝበ ውሳኔው አፈፃፀም ሰላማዊና ሕጋዊ መሆኑ በዚህ ሂደት የተገኘ በጎ ውጤት ሲሆን፥ ለዝግጅት ከነበረው አጭር ጊዜም አንጻር የቦርዱ አፈጻጸም የተሳካ ነው ብሎ ያምናል። የአፈፃፀም ሂደቱ ጠቃሚ ትምህርት የተገኘበት መሆኑን ያህል ተግዳሮቶች የነበሩበት በመሆኑ ለቀጣይ ትምህርት ይሆን ዘንድ የሚከተሉትን ማንሳት ተገቢ ይሆናል፤

    • የሕግ ማዕቀፍ እንዲወጣ (የአነስተኛ ቡድኖች መብት ጥበቃ፤ የሀብት ክፍፍል) በቦርዱ የቀረበው ጥያቄ በክልሉ ምክር ቤት የተሰጠው ምላሽ መዘግየት፤
    • የሕዝበ ውሳኔው ቅስቀሳ ሂደት የአንድን ወገን አማራጭ ብቻ የቀረበበት መሆኑ እና የሕዝበ ውሳኔውን ሂደት እንዲታዘቡ የክልሉ መንግሥት ወኪሎች እንዲመድብ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብለትም አለመመደቡ፤
    • የድምጽ መስጫ ጣቢያዎችን ለመወሰን የሚያስፈልገው የሕዝብ ቁጥር የተሟላ መረጃ አለመኖር፤
    • በተወሰኑ የሀዋሳ ከተማን የገጠር አካባቢ ድምፅ መስጫ ጣቢያዎች የማይመለከታቸው ሰዎች መገኘት፣ በድምፅ ሰጪዎች ላይ በአንዳንድ ጣቢያዎች ተፅእኖ የማሳደር ሁኔታ መታየት፤
    • በአንዳንድ ቦታዎች በድምፅ ሰጪዎች ብዛት ምክንያት የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች መጨናነቅ መከሰቱ፤
    • በሕዝበ ውሳኔው ውጤት አገላለጽ ላይ ከሀዋሳ ከተማና ከዞኑ መስተዳድር ተቋማት ኃላፊዎች በቦርዱ ይፋዊ መግለጫ ከመሰጠቱ በፊት አስቀድሞ የመገመት (projection) እና የመግለጽ ችግር መታየቱ፤
    • በአንዳንድ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች በሕግ የተቀመጠን የምርጫ ጣቢያ መክፈቻ እና መዝጊያ ሰዓት አለመጠበቅ እንደዋና ተግዳሮት የሚጠቀሱ ሲሆን (ማለትም የክልሉ የጸጥታ ተቋማት፣ የደቡብ እዝ የአገር መከላከያ ሠራዊት) የሕዝበ ውሳኔ ቁሳቁስ ማጓጓዝ፣ የአካባቢ ጸጥታ እና ደኅንነትን በመጠበቅ፣ የአስፈጻሚዎች ስምሪትን እንዲሁም ድምጽ የተሰጠባቸውን ሰነዶችን ጥበቃ በማድረግ እጅግ የሚመሰገን ድጋፍ ማድረጋቸው እና በሕዝበ ውሳኔው ሂደት ከፍተኛ ቅንጅት መኖሩ እንደትልቅ ስኬት የሚነሳ ነው።

    ምስጋና
    በሲዳማ የክልልነት የመደራጀት ሕዝበ ውሳኔ እስካሁን በአገራችን ከነበረው ልምድ የተለየ እና መጀመሪያው ቢሆንም ሰላማዊ እና ሕጋዊ በሆነ ሁኔታ ሊፈጸም ችሏል። ይህንን ሕዝበ ውሳኔ ስኬታማ ለማድረግ ቦርዱ ከተለያዩ አካላት፣ ተቋማት እና ግለሰቦች ድጋፍ አግኝቷል። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሚከተሉት ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋናውን ያቀርባል።

    • በሕዝበ ውሳኔው በሰላማዊ እና ሥነ ሥርዓት ባለው ሁኔታ ለተሳተፉት የሲዳማ ዞን ነዋሪዎች በሙሉ፣
    • ከመኖሪያ አካባቢያቸው ርቀው በመሄድ ባልተሟላ አንዳንዴም በአስቸጋሪ ሁኔታ ሕዝበ ውሳኔውን ላስፈጻሙ የሕዝበ ውሳኔው አስፈጻሚዎች እና ሥራውን በማስተባበር ለደከሙ የቦርዱ ሠራተኞች፣
    • ለሕዝበ ውሳኔው አስፈጻሚዎች ምልመላ ድጋፍ ያደረጉልን፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከንቲባ ፣ ለአዲስ አበባ ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ፣ ለኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ
    • ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት፣ ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስዳድር እና የርዕሰ መስተዳድሩ ሕህፈት ቤት፣
    • ለሲዳማ ዞን ምክር ቤት፣
    • ለሲዳማ ዞን አስተዳደር፣
    • ለሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣
    • ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሃገር መከላከያ ሠራዊትና ለአገር መከላከያ ሠራዊት ደቡብ እዝ፣
    • ለፌደራል ፓሊስ፣
    • ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፓሊስ ኮሚሽን፣
    • ለሲዳማ ዞን ፓሊስ፣
    • ለሀዋሳ ከተማ ፓሊስ፣
    • ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን
    • ሕዝበ ውሳኔውን ለመታዘብ ለተሳተፉ ሲቪል ማኅበራት፣
    • የተለያዩ እገዛዎችንን ላደረጉልን የአሜሪካን የልማት ድርጅት (USAID/IFES) እና የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (UNDP)፣
    • ለአዲስ ፓርክ

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ

    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን ጋዜጣዊ መግለጫ

    አዲስ አበባ፥ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም.
    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሸነር የእስረኞች ጉብኝት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን።

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በፌዴራል ፖሊስ ተይዘው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሸን ስር በአደራ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ተጠርጣሪ ታሳሪዎችን ጥቅምት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ጐብኝተዋል።

    ዋና ኮሚሸነሩ በዚህ ጉብኝታቸው ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህር ዳር እና በአዲስ አበባ ከተማ ከተከሰተው የፖለቲካ ግድያ ጋር በተያያዘ እና በሌሎችም ተዛማጅ ጉዳዮች በቁጥጥር ስር ከሚገኙ እስረኞች ውስጥ፥ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራር እና አባሎች ውስጥ እነ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ አቶ በለጠ ካሳን፤ ከባልደራስ ባለአደራ ምክር ቤት ንቅናቄ አባሎች ውስጥ እነ አቶ ኤልያስ ገብሩ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኰል እና አቶ መርከብ ኃይሌን፤ ከኢትዮጵስ ጋዜጣ ባልደረቦች አቶ ምሥጋና ጌታቸው እና አቶ አዳሙ ሁጁራን (አቶ አዳሙ በተጨማሪም የባልደራስ ባለአደራ ም/ቤት ንቅናቄም አባል ናቸው)፤ እንዲሁም «የተጠለፈው ትግል›› ከሚለው መጽሐፍ ሕትመት ጋር በተያያዘም በእስር የሚገኙትን አቶ ፍሬው በቀለ፣ አቶ ሳሙኤል በቀለ፣ አቶ መለሰ ማሩ፣ አቶ ጋዲሳ ዳንኤል እና አቶ አማረ ተፈራን፤ በተጨማሪም የሟች ብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌን ባለቤት ወ/ሮ ደስታ አሰፋንና ሌሎች በርካታ ታሳሪዎችን በማነጋገር ጉዳያቸው ያለበትን ደረጃ እና የእስር ሆኔታቸውንም ተመልክተዋል።

    ዋና ኮሚሸነሩ ‹‹የሴቶች እስር ክፍሉ በአንፃራዊነት የተሻለ እና የጽዳት ደረጃው የተጠበቀ ሲሆን በሌላ በኩል ከ300 በላይ ታሳሪዎችን የያዘው የወንዶች እስር ቦታ እጅግ የተጨናነቀ፣ በውሃ መቋራረጥ እና በታሳሪው ብዛትም የጽዳት ደረጃው ዝቅተኛ ነው» ያሉ ሲሆን ታሳሪዎቹ በየእለቱ ከቤተሰብ፣ ወዳጅ እና የሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘት እንደሚችሉም ለማወቅ ችለዋል።

    በሌላ በኩል “ታሳሪዎቹ ከ 3–4 ወር ያህል የፖሊስ ምርመራን ለማጠናቀቅ በሚል በእስር የቆዩና በአሁኑ ወቅት በሕግ የሚፈቀደው የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ በአብዛኛው የተጠናቀቀ እና ቀሪውም በመጠናቀቅ ላይ ያለ በመሆኑ ከዚህ በላይ ታሳሪዎቹ በእስር ሊቆዩ ስለማይገባ እንደየአግባቡ በዋስ ወይም ያለዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ ወይም ተዓማኒ የሆነ ክስ በመደበኛው የወንጀል ሕግ መሰርት ሊቀርብ ይገባል” በማለት ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

    “ከአንድ መጽሐፍ ሕትመት ጋር በተያያዘ የመጽሐፉ ፀሐፊ ነው ተብሎ ከተጠረጠረ ግለሰብ አንስቶ፣ የማታሚያ ቤቱ ባለቤት፣ የመጽሐፉ የፊት ገጽ ዲዛይን የሰራ ግለሰብ፣ የመጽሐፉ አከፋፋይ እና የመጽሐፉ የጐዳና ላይ ቸርቻሪ ሻጭ ሳይቀር እንዲሆም ሌሎች ታሳሪዎች ፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ጌዜ ፎቶ አንስተሃል በሚል የተያዘ ጋዜጠኛ ጭምር ለዚህን ያህል ጊዜ በእስር መቆየታቸው አሳሳቢ ሁኔታ በመሆኑ አፋጣኝ እልባት እና የዋስትና መብት መከበር ያስፈልገዋል” በማለት ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

    ክቡር ዋና ኮሚሽነሩ በተጨማሪም ለጉዳዮቹ ሁሉ ሕጋዊ እልባት ለማግኘት ከሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች ጋር በመነጋገር ኮሚሽኑ ክትትሉን እየቀጠለ መሆኑን አሳውቀዋል።

    ጉብኝቱ በዓለም ዓቀፍ የእስር ቤቶች ጉብኝት ደረጃ መሠረት ያለ ቅድሚያ ማስታወቂያ የተደረገ ሲሆን የፖሊስ ኮሚሸኑ አመራሮች እና የጥበቃ ክፍል ኃላፊዎች ለዋና ኮሚሸነሩ ጉብኝቱ በማመቻቸት ኃላፊነታቸውን በመወጣታቸው ዋና ኮሚሸነሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

    ምንጭ፦ የኮሚሽኑ ፌስቡክ ገጽ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን

Viewing 3 results - 1 through 3 (of 3 total)