Home › Forums › Semonegna Stories › የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች › ወሎ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተማሪዎች መካከል የተከሰተውን አለመግባባት በሽምግልና መፍታት መቻሉ ተገለጸ
ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተቋሙ በተከሰተ ግጭት ምክንያት ተቋሙን ለቀው የሄዱ ተማሪዎችን በድጋሚ ለመቀበል ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ሲሆን የተቋሙ መምህራንም ለተማሪዎች የማካካሻና የማካካሻ ስልጠናዎችን ለመስጠት መዘጋጀታቸው ተገልጿል።
ደሴ (ወሎ ዩኒቨርሲቲ) – የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የትርምስ ማዕከል ለማድረግ ጥቅመኞችና የፖለቲካ ቁማርተኞች ገንዘብ የጥፋት ተልዕኮ ፈጻሚ መልምለው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ይህም የጥፋት ተልዕኮ በአማራና በኦሮሚያ ክልል ያሉ ሁሉንም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለማንኳኳት ሞክሯል። ይህንኑ እኩይ ተግባር እልባት ለመስጠት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኔስተር አጀንዳና ተልዕኮ ቀርጾ በሁለቱ ክልሎች በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ አካላትን የማወያየት ሥራ ሠርቷል።
በዚሁ ውይይት በወሎ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል የተከሰተው አለመግባባት በእርቀ ሰላም ተፈቶ ወደ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ ተጀምሯል። የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን በዚህ የይቅርታና የፍቅር መድረክ ‘የሰላም መሠረቱ ይቅርታ ነው፣ በጋራ ስንሆን ብዙ ሀብት ያለን ህብር ነን፣ አባቶቻችን ቋንቋና ሀይማኖት ሳይገድቧቸው ኩርማን ዳቦ ተካፍለው ያስረከቡንን ሀገር ያልኖርንበትን ዘመን ታሪክ በመጥቀስ እርስ በርስ ከሚያጠፋፋና ሀገርን ከሚያፈርስ መጥፎ ታሪክ በመቆጠብ በይቅርታ ሀገርን የማዳን ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል’ ሲሉ ገልጸዋል። ታላላቆችን የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች ለማጋጨት ገንዘብ መድበው የሚንቀሳቀሱ አካላት ተማሪዎች መጠቀሚያ መሆን የለባቸውም ያሉት የደሴ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ ገ/መስቀል የከተማ አስተዳደሩ የውጭ ተልዕኮ አንግበው የሚቀሳቀሱ አካላትን ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጋር በመተባበር የተቋሙን ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
የፌደራል መንግሥት ተወካይ የሆኑት አቶ ብሩክ ከበደ በበኩላቸው በወቅቱ እየታየ ያለው ሁኔታ ሀገራችን ኢትዮጵያ በተስፋና በስጋት ውስጥ እንድትሆን አድርጓታል በማለት ሀገር በማፍረስ ላይ የተጠመዱ አካላት ያልኖርንበትን ዘመን ታሪክ እያመገሉ ከሚያጋጩ አካላት እኩይ ሴራ በመጠንቀቅ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የማስቀጠል ታሪካዊ ኃላፊነት እንድወጡ ለተማሪዎች ጥሪ አስተላልፈዋል። አያይዘውም አቶ ብሩክ የፌደራል መንግሥት በአማራና በኦሮሚያ ክልል ያሉ 22ቱም ዩኒቨርሲቲዎች ሰላም እንዲጠበቅና ተማሪዎች በተመደቡበት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመልሰው ገብተው እንዲማሩ እየሠራ እንደሆነ ገልጸዋል። በዚህ የእርቅ ሥነ-ሥርዓት የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተማሪዎችን ወደ አንድነት የሚያመጡ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል። ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተቋሙ በተከሰተ ግጭት ምክንያት ተቋሙን ለቀው የሄዱ ተማሪዎችን በድጋሚ ለመቀበል ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ሲሆን የተቋሙ መምህራንም ለተማሪዎች የማካካሻ (tutor) ስልጠናዎችን ለመስጠት መዘጋጀታቸው ተገልጿል።
ምንጭ፦ ወሎ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ