ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎቹን አስመረቀ፤ ለመጪው የትምህርት ዘመን የቅድመ ሥራዎች ላይ ውይይት አድርጓል።

Home Forums Semonegna Stories ሰሞነኛ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሪዎች ምርቃት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎቹን አስመረቀ፤ ለመጪው የትምህርት ዘመን የቅድመ ሥራዎች ላይ ውይይት አድርጓል።

#15243
Semonegna
Keymaster

ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎቹን አስመረቀ፤ ለመጪው የትምህርት ዘመን የቅድመ ሥራዎች ላይ ውይይት አድርጓል።

ደብረ ብርሀን (ኢዜአ/ሰሞነኛ) – ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች በ2ኛ ዲግሪ ያስተማራቸውን 61 ተማሪዎች ሐምሌ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመረቀ።

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደረጀ አንዳርጌ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፥ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት በትምህርት ዘርፉ ላይ በርካታ እንቅፋቶች አጋጥመዋል። የመማር ማስተማሩ እንዲቋረጥ በመደረጉም ተማሪዎችን አቅም በፈቀደ መንገድ በቴክኖሎጂ ለማገዝ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል። በተለይም የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በቴክኖሎጂ እንዲከታተሉ በማድረግ ለምረቃ ቀናቸው ማድረስ መቻሉን ገልፀዋል።

ዩኒቨርሲቲው በዕለቱ ያስመረቃቸው ተማሪዎችም በቀን፣ በማታ እና በሳምንታዊ የትምህርት ፕሮግራሞች ትምህርታቸውን ተከታትለው ማጠናቀቅ የቻሉ መሆናቸውን ዶ/ር ደረጀ ተናግረዋል።

ተመራቂዎቹ በጤና፣ በግብርና እና ተፈጥሮ ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ቀመር እና የቢዝነስ የትምህርት መስክን ጨምሮ በ21 የትምህርት ዘርፎች ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው ተብሏል። ዩኒቨርሲቲው ለ12ኛ ጊዜ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከልም 52ቱ ሴቶች መሆናቸውን ዶ/ር ደረጀ አስታውቀዋል።

አሁን ላይ ሀገሪቱ የተለያዩ ወቅታዊ ችግሮች ውስጥ መሆኗን አመልክተው፥ ተመራቂ ተማሪዎች ሀገሪቱ ከገጠማት ችግር ፈጥና እንድትወጣ በቆይታቸው ወቅት ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ዶ/ር ደረጀ አሳስበዋል።

በአካውንቲንግና ፋይናስ የትምህርት ዘርፍ 3.91 በማምጣት የተመረቁት አቶ ገብረሀና ደበበ በበሰጡት አስተያየት በተመረቁበት ዘርፍ ሕዝባቸውን እና ሀገራቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በእናቶች እና ሕፃናት ጤና የተመረቁት ወ/ሮ ዘነቡ አጎናፍር በበኩላቸው፥ ሕብረተሰቡን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል።

ሐምሌ 21 ቀን በተካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት በኮሮና ቨይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተወካይ ተማሪዎችና የዩኒቨርሲቲው የሴኔት አባላት ብቻ ተገኝተው የምረቃ መረሐ ግብሩን ተከታትለዋል።

ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሳንወጣ፥ ዩኒቨርሲቲው ለ2013 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ላይ ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ጋር ሰኔ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ውይይት አድርጓል።

የ2013 ዓ.ም. የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ዕቅድ በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ንጉስ ታደሰ ተዘጋጅቶ ለውይይት ቀርቦ ነበር። በፕሬዝዳንቱ የቀረበው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በ5 ዋና ዋና ዘርፎች ተከፍለዋል። በአስተዳደር፣ በፕ/ጽ/ቤት፣ በአካዳሚክ፣ በጥናትና ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት እና በቢዝነስና ልማት ዘርፍ የዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎችን በጥልቀት የመረመረ እቅድ እንደነበረ ለማየት ተችሏል።

ዶ/ር ንጉስ ታደሰ እንዳቀረቡት፥ በእያንዳንዱ የሥራ ዘርፍ የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ዝርዝር እና የአፈፃፀም የጊዜ ሰሌዳን አስቀምጠዋል። የቀጣይ የዩኒቨርሲቲው የትኩረት መስኮች ተለይተው ጥናት ተካሂዷል ብለዋል። አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲው እያከናወናቸው ያለው የግንባታ ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ እየሄዱና እያለቁ መሆናቸውንም ዶ/ር ንጉስ ገልጸዋል።

በዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎች ላይ መከናወን አለባቸው ከተባሉት ዋና ዋና ተግባራት መካከል፥ ለሀኪም ግዛው መታሰቢያ ሆስፒታልና ለአዲሱ ማስተማሪያ ካምፓስ የውስጥ ቁሳቁሶችን ማሟላት፣ የአፕላይድ ዩኒቨርሲቲ (applied university) ደረጃን መሠረት በማድረግ የዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከል (center of excellence) የሚያዘጋጅ ቡድን ማዋቀርና ወደ ሥራ ማስገባት፤ የምኒልክ የቴክኖሎጂ ካምፓስን የዲዛይን፣ የካሳ ክፍያና ሌሎች ሥራዎች መሥራት፣ የአካዳሚክ አመራሩን መገምገምና ጊዜያቸው ያጠናቀቁ አመራሮች በአዲስ መተካት፣ የተጀመሩትን የጥናትና ምርምር ሥራ ማስቀጠል፣ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የተዘጋጀውን የኮቪድ-19 ለይቶ ማቆያ በቁሳቁስና በሰው ኃይል ማሟላት እና በ2013 ዓ.ም ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል ሙሉ ዝግጅት ማድረግና የተስተጓጎለውን ትምህርት በአጭር ጊዜ ለማካካስ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል።

በመቀጠልም በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በዕቅዱ ላይ ቢካተቱ ያሏቸውን ሀሳቦችና ትኩረት የሚያሻቸውን ነጥቦች ላይ ሀሳብና አስተያየት ሰጥተዋል።

የጥናትና ምርምር ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አልማዝ አፈራ በበኩላቸው፥ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር የተያያዙ ምርምሮች እየተካሄዱ እንደሆነና የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘርን ለ3ኛ ጊዜ ለማምረት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። ቀድሞ ይከናወኑ የነበሩ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ፕሬዚዳንቷ ገልጸዋል።

የአስተዳርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደረጄ አጅቤ እንዳሉት፥ በዝግጅት ምዕራፍ እቅድ በየሥራ ዘርፉ የተዘረዘሩት ዋና ዋና ተግባራትን እያንዳንዱ የሥራ ክፍል ተወያይቶ ለተግባራዊነቱ እንዲሰራ ሁሉም አመራር የሚጠበቅበትን ድጋፍና ክትትል እንዲያደርግ አሳስበዋል።

ምንጮች፦ ኢዜአ/ ዩኒቨርሲቲው

ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ