-
Search Results
-
ከአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ
የተከበራችሁ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች !!
አገራችን ኢትዮጵያ 76 ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የሚኖሩባት ታላቅ አገር ነች። የሕዝባችን አብሮ የመኖር እሴት የሰው ልጆች መደበኛ ማኅበራዊ ግንኙነት ተሻግሮ በደም ዝምድና ተጋምዶ በባህል ተሳስሮ ላይለያይ ተቆራኝቷል። ይህ ህብረት የብሄር ማንነት እና የእምነት ልዩነት ሳይለያየው ለሺህ ዓመታት፣ ሺህ ችግሮችን ተጋፍጦ ይሄው ዛሬም ድረስ በጋራ ዘልቋል።
የዚህ አኩሪ ታሪክ ጉዞ አልጋ ባልጋ ያልነበረ ከመሆኑ ባሻገር፣ ሕዝባችን የሚያነሳቸው የፍትህ፣ የዴሞክራሲና የልማት ጥያቄዎች በተለያዩ ጊዜያት የነበሩትን መንግሥታት በመታገል ለመብቱ የተከራከረበት ወቅትም በርካታ እንደነበር የሚታወቅ ነው። በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች የተነሱት የፍትህ፣ የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የሰብዓዊ መብትና ሌሎች መሠረታዊ ጥያቄዎች ምክንያት በአገሪቱ ለውጥ አንዲመጣ አድርጓል።
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ኢትዮጵያዊንን እና ሌላውን ዓለም ያስደመሙ በርካታ የለውጥ እርምጃዎች ተወስደዋል። ከተማችንም ዘመን ተሻጋሪና ተጨባጭ ውጤቶች እየተከናወኑና ቀደም ሲል ሕዝባችን ያነሳቸው የነበሩ የፍትህ፣ የዴሞክራሲ፣ የእኩልነት፣ የልማትና መሰል አጀንዳዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ይገኛል።
በመሪ ድርጅታችን ኢህአዴግ የሚመራው የከተማችን አስተዳደር ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ መርሆዎችን ተከትሎ የአዲስ አበባ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማካሄድ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸው የከተማው ነዋሪ የሚመሰክረው ሃቅ ነው።
በሌላ በኩል የከተማችን ነዋሪዎች ሕገ-መንግሥቱ በሰጣቸው ሥልጣን መሠረት በከተማው ሕዝብ ተሳትፎ ወኪሎችን በመምረጥ ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፤ እየተከናወኑም ይገኛሉ። ይህ ሲባል ሕዝቡ ከአስፈፃሚው አካል ጐን ሆኖ ባያግዝና ባይሳተፍ ኖሮ አሁን የተገኘውን ውጤት ማስመዝገብ አይቻልም ነበር።
ስለሆነም የከተማችን ነዋሪዎች በሁሉም የሥራ መስኮች ያልተቋረጠ ድጋፍ ያደረገና እያደረገ ያለ ሲሆን በተለይም የአዲስ አበባ ሰላም ተጠብቆ እንዲቀጥል በማድረግ ለሁሉም የአገራችን አካባቢዎች ትልቅ ትልቅ ተምሳሌት ሆኖ ይገኛል። በመሆኑም ሕዝቡ ላበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ምስጋናና ዕውቅና ሊቸረው ይገባል።
ይሁንና አሁንም በከተማችን የሚስተዋሉና በልዩ ትኩረት ሊፈቱ የሚገባቸው ችግሮች እንዳሉ በመገንዘብ ችግሮችን ለመፍታት የከተማው አስተዳደር ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ እንደሆነ እና ምከር ቤቶችም የክትትል ድጋፍና ቁጥጥር ሥራችን አጠናክረን የተጠያቂነት አሠራር በጥብቅ ዲስፒሊን እየተመራ ተግባራዊ አየተደረገ ይገኛል።
ከምክርቤቱ የምርጫ ዘመንጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጥያቄዎች የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መካሄድ የነበረበትን የአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ እንዲራዘም በወሰነው መሠረት እና እንዲሁም ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. የከተማውን አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995ን ለማሻሻል ባወጣው አዋጅ ቁጥር 1094/2010 አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ጊዜ እንዲራዘም የወሰነ እና “ምርጫ ተደርጐ በምርጫው መሠረት አዲስ አስተዳደር እስኪደራጅ ድረስ በሥራ ላይ ያለው ምክር ቤቱ እና አጠቃላይ የከተማው የአስተዳደሩ በነበረበት ሁኔታ ይቀጥላል” በሚል በደነገገውና በወሰነው ውሳኔ መሠረት ህጋዋ ዕውቅና አግኝቶ የቀጠለ አስተዳደር እንደሆነ ሊታወቅ የሚገባው ሲሆን በዚሁ አዋጅ ቁጥር 1094/2010 አንቀጽ 3 ስር “ምክትል ከንቲባው ከምክር ቤት አባላት ውስጥ ወይም ከምክር ቤት አባላት ውጭ የሚሾም ሆኖ የሥራ ዘመኑ የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ይሆናል”ተብሎ በግልጽ በተደነገገው መሠረት የከተማው ምክር ቤት ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ የከተማውን ምክትል ከንቲባ ሹመት በወቅቱ በተገኙት ምክር ቤቱ አባላት በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።
ስለሆነም “የከተማውን ምክትል ከንቲባ ሹመት የነዋሪው ውክልና የለውም” ህጋዊ አይደለም በሚል የሚነሱ የተሳሳቱ አስተሰሰቦች ምንም ዓይነት ህጋዊ መሠረት የሌላቸው እና በስሜት ብቻ የሚንጸባረቁ እንዲሁም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1094/2010 የሚፃረር እና ህገወጥ እንደሆነ ሁሉም የከተማችን ነዋሪ ሊረዳው ይገባል።
ይሁንና አስተዳደሩ በከተማችን ነዋሪ ተሳትፎ ጭምር በአገር ደረጃ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል ሌት ተቀን ደፋ ቀና በሚልበትና በዕቅድ ተይዘው እየተተገበሩ ያሉ በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን ለማሳካት እየተረባረበ እና ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ ባለበት በዚህ ወቅት አንዳንድ ወገኖች በሕግ የተቋቋመውን የአስተዳደሩን ተግባራት በማደናቀፍ የሕዝብ ያልሆኑ ጥያቄዎችን የሕዝብ በማስመሰል ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል።
ስለሆነም በአገራችን ብሎም በከተማችን የመጣውን ለውጥ ለማደናቀፍ በቅርቡ በከተማችን ሰላምን ለማደፍረስ እየታዩ ያሉ ኢ-ሕገመንግሥታዊ እንቅስቃሴዎችን በትኩረት በመከታተልና ሕገወጥ እንቅስቃሴ አድራጊዎችን በሰላማዊ መንገድ በመታገል የከተማችን ነዋሪዎች እንደወትሮው ሁሉ የከተማችንን ሰላም በማስከበር የተጀመረውን ልማት በማስቀጠል የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ከከተማው አስተዳደር ጐን እንደሚቆም ያለንን ጽኑ እምነት እየገለጽን፡-
1ኛ. ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ፣ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን የሚያራግቡ፣ በህጋዊ መንገድ በተመረጠው አስተዳደር ላይ አመጽ የሚያነሳሱ ማናቸውም ድርጊቶች ለማንም የማይጠቅም ህገወጥ ድርጊት እና ፀረ-ህገመንግሥትም ስለሆነ ባስቸኳይ እንዲቆም፤
2ኛ. አሁን ያለው የከተማው አስተዳደር ህጋዊ መሠረት ያለው እና በም/ቤቱ ፀድቆ የተሾሙ በመሆኑ መላው የከተማው ነዋሪዎች ከከተማው አስተዳደር ጐን በመቆም በከተማችን ነዋሪዎች ድምፅ ውክልና የተሰጠውን ም/ቤት ሥልጣን ወደጐን በመተው እየተነሱ ያሉ የማደናገሪያ አስተሳሰቦችን አምርሮ እንዲታገል፤
3ኛ. በከተማችን ውስጥ የላቀ ልማት ለማስመዝገብ፣ ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ለማድረግ የሁሉም ወገኖች የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ በመሆኑ ለውጡን ባስተማማኝ ሁኔታ ለማስቀጠል የከተማችን ነዋሪዎች ሁሉን አቀፍ ትብብር እንዲያደርጉ እና ከከተማው አስተዳደር ጐን እንዲቆሙ ጥሪ እያቀረብን፣ የብሄርብሄረሰቦችና ሕዝቦች የቃልኪዳን ሠነድ እና የህጐች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገመንግሥት የማክበር፣ የማስከበርና የመጠበቅ ኃላፊነታችሁን በመወጣት ሕዝቡን በማደናገር የከተማችንን ሰላም ለማደፍረስ ሌት ተቀን የሚጥሩ ኃይሎችን በመታገል ከከተማ አስተዳደሩና ከምክርቤቱ ጐን በመሆን የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታደርጉ፤
4ኛ. የአዲስ አበባ ጉዳይን በተመለከተ ከተማችን የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በፍቅር፣ በመተሳሰብና በመቻቻል በአብሮነት ለሰላም ልማትና ዴሞክራሲ ዘብ የቆመ ሕዝብ የሚኖርባት የሁላችንም ከተማ የአፍሪካ መዲና፣ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች መኖሪያ መሆንዋ ታውቆ ከከተማው ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች የሕጐች ሁሉ የበላይ በሆነው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ-መንግሥት ምላሽ የሚያገኝ ስለሆነ ፍጸም የግጭት መንስኤ መሆን አይገባውም፤
5ኛ. የከተማው አስተዳደር እንደሌላው ጊዜ ሁሉ የከተማውን ሰላምና ፀጥታ ከማስከበር ባሻገር እያከናወነ ያላቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ፕሮግራሞችን አጠናክሮ እንዲቀጥል እያሳሰብን፣ እንደወትሮው ሁሉ የከተማችን ነዋሪዎችም ህግና ሥርዓት እንዲከበርከ አስተዳደሩ፣ ከሕግ እና የፀጥታ አስከባሪ አካላት ጐን በመሆን ለሰላም ዘብ በመቆም የተለመደው ትብብሩን እንዲቀጥል እንጠይቃለን።
እናመሰግናለን!
ወ/ሮ አበበች ነጋሽ
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ
አዲስ አበባ
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የሚያዘጋጀው ሽልማት ዓላማ በኢትዮጵያ አምራቾችና አገልግሎት ሰጪዎች እንዲሁም በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ለጥራት የሚያደርጉትን ሥራ ማበረታታት መሆኑ በሽልማቱ ሥነ-ሥርዓት ወቅት ተገልጿል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለሦስተኛ ጊዜ የአገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ልዩ ተሸላሚ ሆነ። ዩኒቨርሲቲው ያገኘውን ሽልማት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ደሳለኝ መንገሻ (ዶ/ር) ከፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እጅ ተቀብለዋል።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ስድስተኛ ዙር የጥራት ሽልማት ጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ምሽት በብሔራዊ ቤተ-መንግስት ተካሂዷል። በሽልማትና ዕውቅና ሥነ-ሥርዓቱ ላይ 40 ድርጅቶችና ተቋማት የምስክር ወረቀትና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በውድድሩ ላይ
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ሐረር ቢራ አክሲዮን ማኅበር እና አማራ መልሶ ማቋቋምና ልማት ድርጅት የአንደኛ ደረጃ ዋንጫ ተሸላሚ ሲሆኑ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት የጥራት ደረጃውን ጠብቆ አሸናፊ በመሆኑ የልዩ ዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።
◌ The Ethiopian Quality Award Organization
ከ336 በላይ ድርጅቶች እንዲመዘገቡ ጥሪ የተደረገ ቢሆንም የተመዘገቡት 52 ነበሩ። ከነዚህ ውስጥ 21 በአምራች፣ አምስት በአገልግሎት፣ አራት በከፍተኛ ትምህርት፣ አምስት በጤና እና አምስት በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ፤ በድምሩ 40 ተቋማት እስከመጨረሻው በውድድሩ የዘለቁ ናቸው።
የሽልማቱ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ አምራቾችና አገልግሎት ሰጪዎች እንዲሁም በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ለጥራት የሚያደርጉትን ሥራ ማበረታታት መሆኑ በሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ የሆኑት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የጥራት ጉዳይ የሥነ-ልቦናና የፈረጠመ የኢኮኖሚ የበላይነት እንዲሁም የበለፀገ ማኅበረሰብ መገለጫዎች ናቸው ብለዋል። የምርትና አገልግሎት ጥራትን ለማስጠበቅና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከደረሱበት የጥራት ደረጃ ለመድረስ ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት በ2000 ዓ.ም በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትብብር የተቋቋመ ነው። ድርጅቱ ሲመሠረት ዓላማውን መንግስት በጥራት ረገድ የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍና የጥራት ጽንሰ ሀሰብን በማኅበረሰቡ፣ በአምራቾች፣ በአገልግሎት ሰጪዎችና በግንባታ (ኮንስትራክሽን) ዘርፍ በተሰማሩ ድርጅቶችና ተቋማት ዘንድ እንዲሰርጽ ለማድረግ ነው። እስካሁን 49 ድርጅቶችና ተቋማት የድርጅቱን የልዕቀት ማዕረግ የዋንጫ ሽልማት አግኝተዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- የጎሳዬ ተስፋዬ “ሲያምሽ ያመኛል” አዲስ አልበም በገበያ ላይ ዋለ
- ምን ልታዘዝ ― በቀልዳ ቀልድ ለዛ የተዋበውና ፖለቲካዊ ሥላቅ ዘውግ ያለው ድራማ
- ኢትዮጵያን ለ52 ዓመታት በዲፕሎማትነት ያገለገሉት አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ እውቅና ተሰጣቸው
- ስምንተኛው ለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት በሂልተን ሆቴል ተከናወነ፤ ድምጻዊ ሮፍናን ኑሪ ሶስት ሽልማቶችን በማግኘት አውራ ሆኗል
ድምጻዊ ጎሳዬ ተስፋዬ አዲስ ያወጣው “ሲያምሽ ያመኛል” የተሰኘው የሙዚቃ አልበም አስራ አንድ ዓመታትን እንደፈጀ፤ በግጥም፣ በዜማ እና በቅንብር ከአስራ ሦስት ባለሙያዎች በላይ እንደተሣተፉበት እና ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ፈሰስ እንደተደረገበት ተዘግቧል።
አዲሰ አበባ (ሰሞነኛ) – በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የተወዳጁ ድምፃዊ ጎሳዬ ተስፋዬ አምስተኛ ሙሉ የአልበም ሥራው የሆነውና “ሲያምሽ ያመኛል” የተሰኘው የሙዚቃ አልበም ታህሳስ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያና በመላው ዓለም በገበያ ላይ ውሏል።
አራተኛ አልበሙን “ሳታመሃኝ ብላ” በሚል ርዕስ ካወጣ ከ11 ዓመታት በኋላ ለአድናቂዎቹ ያቀረበው ይህ አዲስ አልበም፥ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት አከፋፋዩ “ሪቮ ኮሚዩኒኬሽንና ኢቨንት” መግለጹን ሳምንታዊ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ ሙዚቃ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉትትና የላቀ እውቅናን ከተጎናጸፉት ድምፃዊያን አንዱ የሆነው የድምፃዊ ጎሳዬ ተስፋዬ አዲስ አልበም፣ ለረጅም ጊዜ በጉጉት ሲጠበቅ የቆየ ሲሆን፥ ደረጃውን የጠበቀና የተዋጣለት አልበም ለማድረግ ሲባል 11 ዓመታትን መፍጀቱንና ግጥምና ዜማቸው ተሠርተው ከተጠናቀቁ ከ40 በላይ ሥራዎች ውስጥ 15ቱ ተመርጠው በዚህ አልበም መካተታቸውን አከፋፋዩ ጨምሮ ገልጿል።
◌ አማርኛ ሙዚቃ፦ ድምጻዊ እሱባለው ይታየው — ዘፈን ማሞቂያ አይደለም
በዚህ አዲስ አልበም ላይ ከተሳተፉ እውቅ የሙዚቃ አቀናባሪዎች መካከል አበጋዝ ክብረወርቅ ሺዎታ፣ ካሙዙ ካሳ፣ አቤል ጳውሎስ፣ መኮንን ለማ (ዶክተሬ)፣ ሚካኤል ኃይሉ (ሚኪ ጃኖ) እና ሱልጣን ኑሪ (ሶፊ) እንደሚገኙበት የገለፀው አከፋፋዩ፥ በግጥምና ዜማውም ከዚህ ቀደም በሠሩት ሥራ አንቱታን ያተረፉት አለምፀሐይ ወዳጆ፣ ይልማ ገ/አብ፣ ሀብታሙ ቦጋለ፣ ቢኒያም መስፍን (ቢኒባና)፣ አለማየሁ ደመቀ፣ መሰለ ጌታሁን እና ራሱ ጎሳዬ ተስፋዬ ተሳትፈውበታል ተብሏል።
በአገራዊ፣ በማኅበራዊ እና በፍቅር ዙሪያ የሚያጠነጥኑ 15 ሙዚቃዎችን ያካተተው “ሲያምሽ ያመኛል” አልበም ሪከርድ የተደረገው በአሜሪካ ኒው ዮርክ ሲቲ ሲሆን ጥራትና ደረጃውን የጠበቀና ዘመኑ ያፈራው የሪከርዲንግ ቴክኖሎጂ አሻራ ያረፈበት መሆኑም ታውቋል።
ጎሳዬ ተስፋዬ ከዚህ ቀደም “ሶፊ”፣ ከሌሎች ድምፃዊያን ጋር “ቴክ ፋይቭ”፣ ከአለማየሁ ሂርጶ ጋር “ኢቫንጋዲ” እና በ1999 ዓ.ም ለብቻው የሠራውን “ሳታመሃኝ ብላ” የተሰኙ የሙዚቃ አልበሞችን ለአድናቂዎቹ ማቅረቡ ይታወሳል።
◌ ሲያምሽ ያመኛል አልበምን በዲጂታል ለመግዛት: CD Baby Siyamish Yamegnal by Gossaye Tesfaye
ምንጭ፦ አዲስ አድማስ ጋዜጣ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ተመሳሳይ ዜናዎች፦አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አፍሪካዊ የአመራር መጽሔት (African Leadership Magazine) በሚያዘጋጀው የዓመቱ ምርጥ አፍሪካዊ ምርጫ ላይ ለ2018 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ) የዓመቱ ምርጥ አፍሪካዊ መሪ ለመባል ዕጩ ሆነው ተመርጠዋል።
መጽሔቱ የዓመቱ ምርጥ ሰው ብሎ የሚመርጠው በተለያዩ ዘርፎች ለአፍሪካ እና አፍሪካውያን የላቀ አስተዋጽዖ ያበረከቱ እና እጅግ ጉልህ የሆነ ተጽዕኖ የፈጠሩ አፍሪካውያንን በማወዳደር ሲሆን፥ መጽሔቱ መታተም ከጀመረበት እ.ኤ.አ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ሽልማቱ ይሰጣል።
ዘንድሮ በእጩነት ከቀረቡት መካከል በወንድ መሪዎች ዘርፍ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በ97.25% ድምጽ በማግኘት ቀዳሚውን ቦታ ሲይዙ፣ የቀድሞው የቦትስዋና ፕሬዝደንት የሆኑት ሰረትሴ ካማ ኢያን ካማ (Serêtsê Khama Ian Khama) በ2.00% የምርጫ ድምጽ ሁለተኛ፣ የነዳጅ ላኪ ሀገራት ህብረት (Organization of the Petroleum Exporting Countries – OPEC) ጠቅላይ ሰብሳቢ የሆኑት ናይጀርያዊው መሐመድ ሳኑሲ ባርኪንዶ (Mohammed Sanusi Barkindo) በ0.75% የምርጫ ድምጽ በሦስተኝነት ይከተላሉ።
የአፍሪካዊ የአመራር መጽሔት ዋና አዘጋጅ ዶ/ር ኬን ጊያሚ (Dr. Ken Giami) እንደገለጸው የዘንድሮው ምርጫ ከሌሎች ጊዘያት በተለየ መልኩ ብዙ ሰዎች፣ ከሁሉም የ አፍሪካ አቅጣቻዎች ድምጽ የሰጡበት ሁሉም ዕጩዎች ያጋጠማቸውን ተግዳሮቶች አሸንፍው በተሠማሩባቸው መስኮች ሁሉ የሚጠበቅባቸውን በመወጣት ልቀው ሊታዩ ችለዋል ብሏል።
በሰባት የዕጩነት ቦታዎች (ስድስት ዘርፎች) በአጠቃላይ ሰላሳ (30) አፍሪካውያን ለዕጩኘት የቀረቡ ሲሆን፥ በሀገር ደረጃ በአጠቃላይ ናይጄርያ አስር (10) ዕጩዎችን በማስመረጠ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች። የሰላሳዎች ዕጩዎች ሀገራዊ ስብጥር፥ ቦትስዋና (2)፣ ኬፕ ቨርዴ (1)፣ ግብጽ (1)፣ ኢትዮጵያ (1)፣ ጋና (4)፣ ኬንያ (1)፣ ሞሮኮ (2)፣ ናይጄርያ (10)፣ ሴኔጋል (1)፣ ደቡብ አፍሪካ (5)፣ እስዋቲኒ/ስዋዚላንድ (1)፣ እና ታንዛንያ (1) መሆናቸው ታውቋል።
ከዕጩዎቹ መካከል አሸናፊዎቹን ለመለየት ማንኛውም ግለሰበ የመጽሔቱ ድረ-ገጽ ላይ ሄዶ መምረጥ (ድምጽ መስጠት) ይችላል። (ድረ-ገጹን እዚህ ጋር ያገኙታል)። በድረ-ገጽ ድምጽ የመስጠት ተግባር እ.ኤ.አ ታህሳስ 10 ቀን 2018 ዓ.ም. በመካከለኛው አፍሪካ ሰዓት እኩለ ሌሊት (10th December 2018, at midnight Central African Time.) ላይ ይጠናቀቃል ይዘጋል።
አምና እ.ኤ.አ በ2017 ዓ.ም. በተደረገው ተመሳሳይ ምርጫ የሩዋንዳው ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ (Paul Kagame) የዓመቱ ምርጥ አፍሪካዊ መሪ ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል።
አፍሪካዊ የአመራር መጽሔት (African Leadership Magazine) መቀመጫነቱን በእንግሊዝ ሀገር፣ ፖርትስማውዝ ከተማ አድርጎ አፍሪካንና አፍሪካውያንን ከተቀረው ዓለም ጋር ለማገናኘት፣ ለማቀራረብ የሚሠራ የህትመት ድርጅት ነው። በየዓመቱም በተለያዩ ዘርፎች አፍሪካና አፍሪካውያን ላይ በተለያየ መልኩ ጉልህ ሚና የተጫወቱ አፍሪካውያንን “የዓመቱ ምርጥ አፍሪካውያን” ብሉ ይመርጣል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርዱ ሰብሳቢ ተደርጋ መሾም የሀገሪቱን የምርጫ ሂደት ለማሻሻል የተገባውን ቃል ለማጠናክር እና ለ2012 ዓ.ም. ምርጫ ዝግጅት ገለልተኛ የምርጫ ቦርድን ለማጠናከር ያለውን የፓለቲካ ቁርጠኝነት ምስክር ነው ብለዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኅዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ስብሰባው ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ በአራት ተቃውሞ፣ ሦስት ድምፅ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምጽ ሾሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የዕጩዋን ሹመት ባቀረቡበት ወቅት መንግስት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢን በአዲስ መልክ ለመተካት የወሰነው የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ዳር እንዲደርስ ለማድረግ የተጀመረው የጥረት አካል መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም የዲሞክራሲ መገለጫ የሆነው ምርጫ ቦርድ ተዓማኒና ገለልተኛ ለማድረግ ተቋሙን የማዘመንና ማሻሻል ከማድረግ በተጨማሪ ብቁ የሆነ መሪ እንደሚያስፈልገው በማመን ወ/ሪት ብርቱካን ለዕጩነት ቀርበዋል ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።
ዶ/ር ዐብይ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርዶ ሰብሳቢ ተደርጋ መሾም የሀገሪቱን የምርጫ ሂደት ለማሻሻል የተገባውን ቃል ለማጠናክር እና ለ2012 ዓ.ም. ምርጫ ዝግጅት ገለልተኛ የምርጫ ቦርድን ለማጠናከር ያለውን የፓለቲካ ቁርጠኝነት ምስክር ነው ብለዋል።
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አቅራቢነት የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ሹመት የተከናወነው የቀድሞዋ ሰብሳቢ አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ በፈቃዳቸው ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ነው።
ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ማን ናቸው ?
– በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው፣
– ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ኬኔዲ ስኩል ኦፍ ገቨርንመንት የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው፣
– በፌደራል ፍርድ ቤቶች በዳኝነት ያገለገሉ፣
– የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ፣
– በውጪ ሀገር በናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዲሚክራሲ በተባለ ድርጅት ተመራማሪ ሆነው የሠሩ፣
– የፓርቲ አመራርና ተወዳዳሪ (ቅንጅት) ሆነው የሠሩ፣
– በምርጫ ሂደት ሰፊ ልምድ ያላቸው ናቸው።◌ Interview: Birtukan Mideksa, who shook Ethiopian court system, is back to Ethiopia from exile
ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በአሁኑ ሰዐት የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆኑና ገለልተኛ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ለምክር ቤት አባላት ተናግረዋል። የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑ ይታወቃል።
ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ከቀድሞ ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ (ቅንጅት) ጋር በተያያዘ ለእስራትና ለእንግልት ከተዳረጉ በኋላ ከሀገር ወጥተው በሀገረ አሜሪካ ለሰባት ዓመታት በስደት የኖሩ ሲሆን፥ በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን ሁለንተናዊ ለውጥ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባቀረቡላቸው ጥሪ መሠረት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው ይታወሳል።
PHOTO: Abebe Abebayehu
አዲስ አበባ (የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ) – የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ 34ኛውን እና የዓመቱ የመጀመሪያውን ሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት ምግብ ዋስትና በኢትዮጵያ በተሰኘ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ መስከረም 24 ቀን 2011 ዓ.ም ውይይት አካሄደ።
ገለፃውን ያቀረቡት ዶ/ር ዓለማየሁ ሥዩም (በዓለም አቀፍ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ተቋም (IFPRI) ውስጥ ከፍተኛ ተመራማሪ) ሲሆኑ፣ አቅራቢው በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና እና በምግብ እራስን መቻል መካከል ያለው ብያኔ የተዛነፈ በመሆኑ በምሁራን እና በፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ ወጥ የሆነ አረዳድ እንዳይኖር አድርጓል ብለዋል። ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ማለት በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በአገር፣ በክፍለ-ዓለምና በዓለም ደረጃ፤ ሁሉም ሰዎች፣ ዘወትር፣ በመጠኑ በቂ የሆነ፣ በጤና ላይ አደጋን የማያስከትል እና የተመጣጠነ የአመጋገብ ፍላጎትም ሆነ የአይነት ምርጫ ቁሳዊናኢኮኖሚያዊ ተደራሽነት ሲኖራቸው እንደሆነና ምንም ዓይነት ወቅታዊ መዋዠቅን፣ ያልተጠበቁ ሰው ሠራሽም ሆነ የተፈጥሮ ክስተቶችን (አደጋዎችን) መቋቋም የሚችል ማህበረሰብ ሲፈጠር እንደሆነ አቅራቢው ይገልፃሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ መካከለኛ መጠን ያላቸው ከተሞች በዓመት በአማካይ ከ5-6 በመቶ ዕድገት እያሳዩ መሆኑ እና መንግስት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማዘመን እና ምርታማነትን በመጨመር ገበያ-ተኮር ኢኮኖሚ ለመዘርጋት ጥረት እያደረገ እንደሆነ አብራርተዋል። ነገር ግን ዛሬም የግብርና ምርታማነት በጣም ዝቅተኛ መሆኑ፣ የህፃናት መቀንጨር በአማካይ 38 በመቶ መድረሱ፣ የምግብ እህል እጥረት የሚያጋጥማቸው ዜጎች ቁጥር እጅግ መጨመሩ እና ከፍተኛ የምግብ እህል/ሸቀጥ ከውጪ እንዲገባ መደረጉ “የምግብ ዋስትና ጉዳይ አሁንም እልባት ያላገኘ አገራዊ ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል” ብለዋል ዶ/ር ዓለማየሁ።
ለእንደዚህ ዓይነት የምግብ ዋስትና ስጋት ያጋልጣሉ ያሏቸውንም ምክንያቶች ዶ/ር ዓለማየሁ ዘርዝረዋል። “በገጠር የተወሳሰበ የመሬት ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ ሁኔታ (የይዞታ ባለቤትነትና አጠቃቀም ሥርዓት)፣ የእርሻ መሬት ይዞታ ማነስና መበጣጠስ፣ የመሬት ምርታማነት መቀነስ/የአፈር ለምነት መቀነስ፣ የሥራ ዕድል መጥበብ እና ወጥነት የጎደለው የፖሊሲ አፈፃፀም” ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል ዶ/ር ዓለማየሁ። ችግሩም ህፃናትን ለበሽታና ለሞት እንዲሁም ለአካልና አእምሮ ህመም ከመዳረጉ እና የመማርና የማምረት አቅምን ከማኮሰስ አልፎ ድህነት እንዲቀጥል ያደርጋል ተብሏል።
በሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት መድረኩ ከችግሩም ለመላቀቅና የተሟላ ማህበራዊ ዋስትና ለመፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየቶች ተነስተዋል። በውይይቱም ከፍተኛ የግብርና ማስፋፊያ ተግባራት በማከናወን አርሶ አደሮች የተሻለ መረጃ እንዲያገኙና የተሻሻሉ የግብርና ዘዴዎችን እንዲያላምዱ ማትጋት፤ ዘመናዊ የመሠረተ-ልማት ዝርጋታ ማድረግ፤ በትምህርትና በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በማካሄድ አማካይ በህይወት የመኖሪያ እድሜን ማሳደግ እና የምግብ ዋስትና ተጋላጭነትን እያጠኑ ስልት የሚቀይሱ ጠቃሚ ተቋማትን መፍጠር (የፖሊሲ ተቋማት፣ የንብረት ባለቤትነት መብቶች፣ የገበያ፣ የአምራቾች ማህበራት፣ የማህበራዊ ዋስትና ስልት፣ የቅድመ-ማስጠንቀቂያ ዘዴዎች) ቅድሚያ የሚፈልጉ አገራዊ ተግባራት መሆናቸው ተነስቷል።
ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪም ከ20-25 ዓመት የሚደርስ የግብርናው ዘርፍን ሊያዘምን የሚችል አሠራር በተለይ ደረቅ-አብቃይ አካባቢዎችን፣ ለድርቅ-ተጋላጭቦታዎችን እና የተጎዱ አካባቢዎችን የሚያሻሽል የተቀናጀ መርሐ-ግብር መንደፍ አስፈላጊ እንደሆነ ተሳታፊዎች አንስተዋል። እንደ ህዝብ ቁጥር መጨመርና የአየር ንብረት መለዋወጥ ያሉ አባባሽ ሁኔታዎችንም መቋቋም የሚያስችል የኢኮኖሚ ዝግጁነት መገንባት የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማስጠበቅ ይረዳልም ብለዋል።
በጥቅሉ የገለፃው አቅራቢና ተሳታፊዎች፣ ተቋማት መገንባትና በስፋትና በተፈለገው የህብረተሰብ ፍላጎት ልክ የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግር መፈጠር አለበት በማለት የዕለቱን ውይይት አጠናቀዋል።
ውይይቱን ፕሮፌሰር በላይ ካሳ (የፓን አፍሪካን ዩኒቨርሲቲ ጊዜያዊ ከፍተኛ አመራር) የመሩት ሲሆን፣ ከ110 በላይ የሚሆኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ባለሙያዎች፣ የአካዳሚው አባላትና የሚዲያ አካላት ተሳትፈውበታል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ
Topic: አገር አቀፍ የተማሪ ወላጆች ህብረት ተመሠረተ
አገር አቀፍ የተማሪ ወላጆች ህብረት ምሥረታ ላይ ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ግለሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተሳተፉበት ሲሆን ህብረቱን በሊቀመንበርነት፣ በምክትል ሊቀመንበርነት በጸሀፊነት የሚያገለግሎ ወላጆችን ምርጫ ተካሂዷል።
አዳማ (የትምህርት ሚኒስቴር) – በአገሪቱ እስከ ታኛናው መዋቅር ያሉ የትምህርትና ስልጠና ተቋማትና የተማሪ ወላጆችን ትስስር በማጠናከር በዘርፉ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ የሚያስችል አገር አቀፍ የተማሪ ወላጆች ህብረት ተመሠረተ።
ክቡር የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ አቶ መሀመድ አህመዲን በአገር አቀፍ የተማሪ ወላጆች ህብረት ምሥረታ ወቅት እንደገለጹት የህብረቱን ዓላማ በየደረጃው ባለው መዋቅር የትምህርት ተቋማትና የተማሪ ወላጆችን በማስተሳሰር በሁለንተናዊ ብቃት፣ ዕውቀት፣ ክህሎትና በስነ ምግባር የታነጸ ዜጋ ለማፍራት ረገድ የወላጆችን ሚና ለማሳደግ ነው።
በትምህርት ጥራት የማረጋገጥ ተግባር የወላጆች ሚና ማሳደግ፣ በወላጆች፣ በመምህራንና በተማሪዎች መካከል ያለውን ግንኙት ውጤታማ ማድረግ፣ ጤናማ የመማር-ማስተማር ሂደት በላቀ ደረጃ እንዲረጋገጥ የወላጆችን ተሳትፎ ማሳደግና ለትምህርት ሥራ ማጎልበት የሚያስችል አደረጃጀትና ትስስር መፍጠር የህብረቱ ቀሪ ዓላማዎች መሆናቸውን ክቡር ሚኒስትር ደኤታው አስታውቀዋል።
በህብረቱ ምሥረታ ላይ ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ547 የሚበልጡ የሀይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የተማሪ ወላጆች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተሳተፉበት ሲሆን ህብረቱን በሊቀመንበርነት፣ በምክትል ሊቀመንበርነት በጸሀፊነት የሚያገለግሎ ወላጆችን ምርጫ ተካሂዷል።
በዚህም መሠረት ኢንጅነር ጌታቸው ሠጠኝ ከአዲስ አበባ የህብረቱ ሊቀመንበር ፣ወይዘሮ መሠረት ተክሌ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ የህብረቱ ምክትል ሊቀመንበር ፣ አቶ ሀሰን በዳሶ ከኦሮሚያ የህብረቱ ጸሀፊ ሆነው ተመርጠዋል።
ህብረቱ በተጨማሪ 11 አባላት ያሉበትን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያዋቀረ ሲሆን በዚህም መሠረት ከትግራይ አቶ ጸጋዬ አለማየሁ፣ ከአፋር አቶ አሊ የጦ፣ ከአማራ አቶ አዱኛ እሸቴ፣ ከሱማሌ አቶ ኻሊድ አብዱልቃድር፣ ከደቡብ አቶ ተሻለ አየለ፣ ከጋምቤላ አቶ አእምሮ ደርበው፣ ከሐረሪ ወ/ሮ ፋጡማ አብዱ በህብረቱ ሥራ አስፈጻሚ አባልነት ተመርጠዋል።
የኢትዮጵያ የተማሪ ወላጆች ህብረት ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ኢንጂነር ጌታቸው ሰጠኝ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ህብረቱ ለትምህርቱ ሥራ ውጤታማነት በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
ክቡር የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ በበኩላቸው ህብረቱ ለፍኖተ-ካርታው መተግበር ጠቃሚ መሳሪያ መሆኑን ጠቁመው ህብረቱ ለሚያከናውነው ተግባር ውጤታማነት የትምህርት ሚኒስቴር እገዛ እንደማይለየው አስታውቀዋል።
ህብረቱ በቀጣይ በሰላምና ደህንነት፣ በመማር ማስተማር፣ በትምህርት ተቋማት ፋይናንስ አስተዳደር ጉዳዮች የሚያተኩሩ ንዑሳን ኮሚቴዎች በቀጣይ ተቋቁመው ወደሥራ እንደሚያስገባም በዚሁ ጊዜ መገለጹን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዘግቧል።
ምንጭ፦ የትምህርት ሚኒስቴር
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አድርገው መረጡ። ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር መሥራች ናቸው።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ጥቅምት 22 ቀን 2011 ዓ.ም በሚያካሂደው መደበኛ ስብሰባ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሹመትን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አድርገው መርጠዋቸዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ይካሄዳል። በስብሰባው በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 81 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርቡትን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እጩ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ሹመት መርምሮ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምርጫ ያቀረቧቸው ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ይሾማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በአሁኑ ወቅት ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው እያገለገሉ ያሉት አቶ ዳኜ መላኩ እና አቶ ጸጋዬ አስማማው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሾሙት ሰኔ 16 ቀን 2008 ዓ.ም ነበር።
ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ማን ናቸው?
ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በ1985 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ኮሚሽን የሕግ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል። በ1987 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርን (Ethiopian Women Lawyers Association/ EWLA) ከሌሎች የሕግ ባለሙያ ሴቶች ጋር በመሆን አቋቁመው በ1988 ዓ.ም. ማኅበሩ በይፋ ሥራ ጀመረ። በዚያም ጊዜ ወ/ሮ መዓዛ የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ ሆነው እስከ 1997 ዓ.ም. ድረስ ሠርተዋል።
ወ/ሮ መዓዛ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምጣኔ ሀብት ኮሚሽን ለአፍሪካ (United Nations Economic Commission for Africa) የተባለው ዓለም-አቅፍ ድርጅትን በ2003 ዓ.ም. በመቀላቀል፥ በዚሁ ድርጅት ውስጥ ከሰኔ ወር 2004 ዓ.ም. ጀምሮ የሴቶች መብት አማካሪ ሆነው ሠርተዋል።
ከሕግ ባለሙያነታቸው በተጨማሪ በ2003 ዓም ኢትዮጵያ ውስጥ በ13 ጠንካራ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ተደራጅነት የተቋቋመው እናት ባንክ (አ/ማ) ሲመሠረት ከመሥራችቹ ውስጥ ጉልህ ሚና የተጫወቱ አባል ነበሩ። ባንኩ ውስጥም ከአራት ዓመታት በላይ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሆነው አገልግለዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ለሴቶች እኩልነትና ለሴቶች መብት በመታገል ላደረጉት አንጸባራቂ ውጤት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በህዳር ወር 1996 ዓ.ም ‘የሀንገር ፕሮጀክት ሽልማት’ (Hunger Project Award) የአፍሪካ ተሸላሚ ሆነዋል። ከዚያም ቀጥሎ (ከሁለት ዓመት በኋላ) የኖቤል የሰላም ሽልማት ዕጩ ሆነው ሊቀርቡ ችለዋል።
በ2006 ዓ.ም. ዘረሰናይ ታደሰ ተደርሶ የተዘጋጀው (ዳይሬክት የተደረገው) “ድፍረት” የተሰኘውና በዓለም አቀፍ ደረጃ መልካም ተቀብይነትን ያገኘው ፊቸር ፊልም (feature film) ሂሩት አሰፋ የተባለች አንዲት የ14 ዓመት ልጃገረድ ኢፍትሀዊ በሆነ ባህል የሞት ፍርድ ተፈርዶባት ከዚያም የሕግ ባለሙያ (ጠበቃ) የሆነችውን ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊን አግኝታ የሚሆነውን የሚተርክ እንደሆነ ይታወሳል።
በኢትዮጵያውያን የኪነ ጥበብ አድናቂዎች ዘንድ ተወዳጅነት እያተረፈ የመጣው ለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት ዘንድሮ ለስምንተኛ ጊዜ ጥቅምት 13 ቀን 2011 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል፣ አዲስ አበባ፣ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ተከናውኗል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – በሀገራችን የሙዚቃ ታሪክ እጅግ መቀዛቀዝ፣ የሙዚቃ አልበምም ህትመት መፍዘዝ፣ ፊልም ሠሪዎችም ሥራዎቻችውን ተመልካቾች ፊታቸውን ባዞሩባቸው በዚያ ወቅት እንደ አንድ የኪነጥበብ አባልና የሚዲያ ባለሙያ አቅማቸው በፈቀደ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ለማበርከት፣ እንዲሁም አድማጭ ተመልካቹን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለማነቃቃት በማሰብ ነበር ጋዜጠኛ ብርሀኑ ድጋፌ እና ባልደረቦቹ በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ሬድዮ ላይ “ለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት” ሥነ ስርዓትን የየጀመሩት።
በእርግጥ ኪነ ጥበብና ኢትዮጵያ ሀገራችን በባህላዊውም ሆነ በዘመናዊው መንገድ እጅግ ብዙ ዓመታትን ያስቆጠረ ቁርኝት ቢኖራቸውም ቅሉ የኪነ ጥበብ ሙያዉን እንደተከበረ ሙያ ባለሙያዉንም የተከበረ ሙያ እንዳለው ቆጥሮ ወቅት ጠብቆ በተገደበ የጊዜ ኡደት ለሙያውና ለባለሙያው ተገቢውን ዕውቅና፣ ብሎም ክብር የሚሰጥ ቋሚ ተቋም ባለመኖሩ ያለመኖሩን በማስገንዘብ የሥነ ስርዓቱ ሀሳብ ጠንሳሾች “ለምን እኛ የቻልነውን አናደርግም?” በሚል ነበር የኪነ ጥበብ ሰዎችን በዓመት አንድ ጊዜ እያሰባሰቡ ለማወያየት፣ በዓመቱ በሙያውና በሙያቸው ጉልህ አስተዋጽዖ ያደረጉትን “በጎ ሥራ ሠርታችኋል! ይበል!” ለማለት ለዛ የኤድማጮች ምርጫ ሽልማትን በ2003 ዓ.ም የጀመሩት።
በ2003 ዓ.ም በተደረገው የመጀመሪያ ሽልማት ‘የዓመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማ’፣ ‘ምርጥ ተዋናይት’፣ ‘የዓመቱ ምርጥ ተዋናይ’፣ ‘የዓመቱ ምርጥ ፊልም’ እና ‘የዓመቱ ምርጥ አልበም’ በሚሉ አምስት ዘርፎች (ዘውጎች) ኢትዮጵያውያን የኪነ ጠበብ ሰዎች ተመርጠው የተሸለሙ ሲሆን ሽልማቱም ያገኙትም ከያኒት ዘሪቱ ከበደ “አርቴፍሻል” በሚለው ነጠላ ሙዚቃዋ፣ ተዋናይት ሰሃር አብዱልከሪም “ያንቺው ሌባ” በተሰኘ ፊቸር ፊልም ላይ ባሳየችው ትወና፣ ጋሽ አበበ ባልቻ “ሄሮሺማ” በተሰኘ ፊቸር ፊልም ላይ ባሳየው ትወና፣ “ሄሮሺማ” ፊቸር ፊልም በምርጥ በፊልምነት፣ እንዲሁም ከያኒ ናትናኤል አያሌው (ናቲ ማን) በመጀመሪያው አልበሙ በአምስቱ የተዘረዘሩት ዘርፎች አሸናፊዎች ሆነው የሥነ ስርዓቱ የበኩር ተሸላሚዎች ሆኑ።
በዚህ መልኩ የተጀመረው ለዛ የአድማጮች ምርጫ በየዓመቱ ከጥቅምት ወር ጀምሮ እስከ ሃምሌ ድረስ የሚወጡ የኪነ ጥበብ ሰዎችንና ሥራዎችን በአድማጮች ምርጫ አወዳድሮ ዕውቅና እየሰጠ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተሳታፊዎችን እያበዛ፣ በባለሙያዉም፣ በመራጭነት በሚሳተፈውም ይሁን በየበይ ተመልካችነት በሚከታተለው ኢትዮጵያዊ ዘንድም ተወዳጅነት እያተረፈ ዘንድሮ ለስምንተኛ ጊዜ ጥቅምት 13 ቀን 2011 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል፣ አዲስ አበባ፣ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ተከናውኗል። ከሁለት ወራት በፊት በተካሔደው ዘጠነኛው አዲስ የሙዚቃ ፌቲቫል ላይ የዓመቱ ምርጥ አርቲስት ተብሎ የተሸለመው ድምጻዊ ሮፍናን ኑሪ በዚህ ሥነ ስርዓትም ላይ ተመሳሳይ ሽልማት፣ ሌሎች ሁለት ሽልማቶችን ጨምሮ አሸንፏል። በስምንተኛው ለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት፦
● ምርጥ ነጠላ ዜማ፦ “ጨረቃ” (ሮፍናን ኑሪ)፣
● ምርጥ አዲስ ድምፃዊ፦ ሮፍናን ኑሪ (“ነፀብራቅ” በተባለው የሙዚቃ አልበሙ)
● ምርጥ የሙዚቃ አልበም፦ ነፀብራቅ (ሮፍናን ኑሪ)
● ምርጥ የሙዚቃ ክሊፕ፦- የመጀመርያዬ (ናትናኤል አያሌው/ናቲ ማን):-
● ምርጥ ተዋናይት፦ አዚዛ አህመድ “ትህትና” በተሰኘ ፊቸር ፊልም ላይ ባሳየችው ትወና፣
● ምርጥ ተዋናይ፦ አለማየው ታደሰ “ድንግሉ” በተሰኘ ፊቸር ፊልም ላይ ባሳየው ትወና፣
● ምርጥ ፊልም፦ “ድንግሉ”
● ምርጥ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ፦ ምን ልታዘዝ?አሸናፊ ሆነው ተሸልመዋል። በዚህ ሥነ ስርዓት ላይ እጅግ ለበርካታ ሙዚቀኞች የዘፈን ግጥም በመስጠት በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ስሙ እጅጉን ጎልቶ የሚታወቀው የሙዚቃ ግጥም ገጣሚ (lyricist) ይልማ ገብረአብ “የ2010 ዓ.ም የኪነ ጥበባ በለውለታ” ሆኖ ልዩ የክብር ሽልማት ተሸልሟል። ገጣሚ ይልማ ገብረ አብ ከአንድ ሺህ በላይ የሙዚቃ ግጥሞችን ጽፎ ለተለያዩ ድምጻውያን አበርክቷል።
የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምደባን ይፋ ከማድረጉ በፊት ኤጀንሲው የተለያዩ የማጣራት ሥራዎችን በማከናወን ሂደት ውስጥ በመቆየቱ ምክንያት ምደባው ዘገየ በማለት ቅሬታችሁን ስታሰሙ ለነበራችሁ ተማሪዎች እና የተማሪ ቤተሰቦች ከወዲሁ ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን ተማሪዎች በተመደባችሁባቸው የትምህርት ተቋማት በምትሄዱበት ወቅት የነገዋ ኢትዮጵያ በእናንተ ትከሻ ላይ መሆኗን በመገንዘብ በትምህርታችሁ ላይ ብቻ ትኩረት በመስጠት ውጤታማ በመሆን ለሀገራችን እድገት እና ልማት የበኩላችሁን አስተዋጽዖ ታበረክቱ ዘንድ ኤጀንሲው ከአደራ ጋር መልዕክቱን አስተላልፏል።
አዲስ አበባ (ኢዜአ/NEAEA)– የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምደባ ይፋ መሆኑን የሀገር አቀፍ የትምህርት ፈተናና ምዘናዎች ኤጀንሲ (NEAEA) አስታወቀ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ገብረእግዝአብሔር ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት፤ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምደባ ከዛሬ ከመስከረም 25 ቀን 2011 ዓም ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ይፋ ሆኗል።
ምደባው የተማሪዎችን ውጤት፣ የትምህርት ዓይነት፣ የዩንቨርስቲ ምርጫ፣ የዩንቨርስቲዎችን የቅበላ አቅም፣ የወንዶችና የሴቶችን ምጠና ማዕከል ባደረገ እንዲሁም የልዩ ድጋፍ ተጠቃሚዎችን ያገናዘበ መሆኑን ነው ያመላከቱት።
ዓይነ ስውራንን፣ መስማት የተሳናቸውን፣ አካል ጉዳተኞችን/ በተጨማሪም የጤና እክል ያለባቸው እና ከታወቀ የመንግስት ሆስፒታል የሜዲካል ቦርድ ማረጋገጫ ያቀረቡት ላይ የማጣራት ሥራዎችን ካካሄደ በኋላ ምደባው እንደተዘጋጀም እንዲሁ አስታውቀዋል።።
በዚሁ መሰረት በዘንድሮው የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና የማለፊያ ነጥቡን ያለፉ 138 ሺ 283 የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ሲሆኑ 75ሺ 338 የማህበራዊ ሳይንስ በድምሩ 213 ሺ 621 ናቸው።
ከነዚህም መካከል 98 ሺ 576 የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎችና 51 ሺ 229 የማህበራዊ ሳይንስ በድምሩ 149 ሺ 805 ተማሪዎች ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ባሉት የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በአጠቃላይ የሚመደቡ ይሆናል።
◌ RELATED: 35 Best Universities and Colleges Ethiopia (public and private)
ከነዚህም በኤጀንሲው በኩል በ43ቱ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት 95 ሺ 681 የተፈጥሮ ሳይንስ (natural science) እንዲሁም 51ሺ 066 የማህበራዊ ሳይንስ (social science) በድምሩ 146 ሺ 747 ተማሪዎች መመደባቸውን አስታውቀዋል።
ተማሪዎች ወደ ተመደቡበት የትምህርት ተቋማት በሚሄዱበት ወቅትም የነገዋ ኢትዮጵያ በትከሻቸው ላይ መሆኗን በመገንዘብ ለትምህርታችሁ ትኩረት እንዲሰጡም አቶ አርአያ አሳስበዋል።
ከግንቦት 27-30 ቀን 2010 ዓ.ም በተሰጠው የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና (የ12ኛ ክፍል ፈተና) 154,010 ወንዶች እንዲሁም 127,964 ሴቶች በድምሩ 281,974 ተማሪዎች የወሰዱ ሲሆን በሐምሌ 24 ቀን 2010 ዓ.ም ውጤት ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
ተማሪዎች ምደባችሁን በኤጀንሲው ድረ-ገጽ app.neaea.gov.et በመግባት ማየት እንደሚችሉም ነው የገለፁት።
ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና የሀገር አቀፍ የትምህርት ፈተናና ምዘናዎች ኤጀንሲ (NEAEA)
በተደረገው ምርጫ በጠቅላላው 177 ሰዎች ድምጽ የሰጡ ሲሆን ዶ/ር አብይ አህመድ 176 ድምጽ በማግኘት የሊቀ መንበርነቱን ሹመት ሲያገኙ አቶ ደመቀ መኮንን ደግም 149 ድምጽ አግኝተው ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተሹመዋል።
ሀዋሳ (ኢዜአ/ፋና)፦ ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ ሲካሔድ የነበረው የኢህአዴግ 11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ሰባት የአቋም መግለጫዎችን በማውጣት አርብ መስከረም 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ማምሻውን ተጠናቋል፡፡ በጉባዔው ማጠቃለያም ዶ/ር አብይ አህመድ እና አቶ ደመቀ መኮንን በድጋሚ የግንባሩ ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል።
በምስጢር በተደረገው ምርጫ በጠቅላላው 177 ሰዎች ድምጽ የሰጡ ሲሆን ዶ/ር አብይ አህመድ 176 ድምጽ በማግኘት የሊቀ መንበርነቱን ሹመት ሲያገኙ አቶ ደመቀ መኮንን ደግም 149 ድምጽ አግኝተው ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተሹመዋል።
ዶ/ር አብይ አህመድ (በግራ) እና አቶ ደመቀ መኮንን (በቀኝ)
ግንባሩ ባወጣው የማጠቃለያ መግለጫ ኢህአዴግ እንደ ግንባር ጠንካራ የአስተሳሰብ አንድነት በመያዝ ከአሰራር፣ ከአደረጃጀትና ከአመራር ግንባታ አንጻር ያሉበትን ጉድለቶች ፈትሾ በማስተካከል እንዲሁም ጥናት ላይ በመመሥረት የርዕዮተ ዓለም ማልማትና ማሻሻል ሥራን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለውጡን በሚፈለገው ፍጥነት መርተን ከግብ ለማድረስ በጋራ እንደሚሠራ ሲል በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
የዴሞክራሲ ምህዳሩን የበለጠ ማስፋት፣ ዜጎች በያዙት የተለየ የፖለቲካ ሀሳብና አመለካከት የማይገፉበትና በጠላትነት የማይታዩበት ሀገራዊ ሁኔታ እንዲፈጠር የግልና የቡድን መብቶች በተሟላ መልኩ የሚከበሩበትን ሁኔታ በማመቻቸት በሀገራችን የመድበለ ፓርቲ ስርዓት እየተጠናከረ እንዲሄድ በፅናት እንደሚታገሉ መግለጫው አትቷል፡፡
የማንነትም ይሁን የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች የሚመለከታቸውን ሕዝቦች ነጻ ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት በሕገ-መንግሰታዊና ዴሞክራሲያዊ አግባብ እንዲፈቱ፣ የዜጎች የትም ቦታ ተዘዋውሮ የመሥራት የመኖር፣ በቋንቋቸው የመማርና የመዳኘት፣ ወግና ባህላቸውን የማሳደግ፣ ተገቢውን እውቅናና ውክልና የማግኘት፣ ሃብት የማፍራት ሕገ-መንግሰታዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩ፣ ብሔራዊ ማንነትና ሀገራዊ አንድነት ሳይነጣጠሉ እንዲከበሩ በትኩረት እነደሚሠራም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
በገጠርም ሆነ በከተማ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የኢንቨስትመንት ፍሰቶችን የሚያጠናክሩ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር የሚያስችሉ የመላውን ህዝብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እውን የሚያደርግ በተለይም የወጣቶችና የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ በላቀ ሁኔታ ለመንቀሳቀስ ቃል ገብቷል።
ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት አንድነትና መልካም ጉርብትናን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሠራም በመግለጫው ተመልክቷል።
ሀገራችን ሰላም የሰፈነባት፣ ዜጎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው ያለስጋት የሚኖሩባት የህግ የበላይነት የተከበረባት፣ ነጻነት ከህግ የበላይነት ውጭ ባርነት መሆኑን በመገንዘብ መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታን ጠንቅቆ የሚያውቅ ህብረተሰብ ለመገንባት በትጋት እንደሚሠራ በመግለጫው ተጠቁሟል።ድርጅታችንን የማጠናከር ስራ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በብቃት ለመምራትና ህዝቡን ለመካስ ቃል ገብቷል።
ምንጭ፦ ኢዜአ/ፋና