-
Search Results
-
በተበባሩት መንግስታት ድርጅት ስር የሚከበረው ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን ዘንድሮ የሚከበረው ለ26ኛ ጊዜ ሲሆን የዘንድሮ ክብረ በዓል መሪ ቃልም “የአካል ጉዳተኞችን ማበረታት፣ የአካል ጉዳተኞችን ታቃፊነትና እኩልነት ማረጋገጥ” የሚል ነው።
ሀዋሳ (ሰሞነኛ ) – ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ26ኛ ጊዜ በሀዋሳ ከተማ ተከበረ።
የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበዓሉ ላይ ተገኝተው አንደገለጹት፥ አካታችነትና እኩልነትን በማስፈን የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሁሉም የህበረተሰብ ክፍል የጋራ ጉዳይ መሆን አለበት ብለዋል።
አሁን ላይ የአካል ጉዳተኞች ችግሮች ተቀርፈዋል ማለት ባይቻልም፥ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት በእየደረጃው አካታች እቅዶችን በማቀድ ለተግባራዊነታቸው እንቅሰቃሴ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
ለአካል ጉዳተኞች የተለያዩ ድጋፎች ማድረጉ የተጀመረ ሲሆን፥ ሀገር ውስጥ ዊልቼር ለማምረት መታቀዱም ነው የተገለጸው።
እንደ ፋና (ኤፍ.ቢ.ሲ.) ዘገባ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊየን ማቲያስ በበኩላቸው፥ አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ስራወች እየተከናዎኑ መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህ በፊት በክልሉ አርባ ምንጭ የአረጋውያን ማዕከል ብቻ የነበረ ሲሆን፥ አሁን ላይ በቤንች ማጅ ዞን ተጨማሪ የአረጋውያን ማዕከል ለመክፈት አየተሠራ መሆኑን ጠቁዋል።
በበዓሉ ለመታደም የተገኙት የአካል ጉዳተኞች በበኩላቸው፥ የትምህርት አገልግሎት ለማግኘት አስካሁን ድረስ ችግሮች ያሉባቸው መሆኑን ነው የተናገሩት። አገልግሎቱ የሚያገኙበት እድል ቢፈጠርም እንኳ ረጅም ርቀት መጓዝ ግድ እንደሚላቸውም አስረድተዋል። ከዚህም ሌላ የአካል ጉዳተኞችን የተመለከቱ መመሪያዎችና ደንቦች ላይ የአፈጻጸም ክፍተት የሚታይ መሆኑን አመላክተዋል። ለአብነትም አንዳንድ የሚወጡ የሥራ ማስታወቂያዎች ሙሉ ጤንነትን የሚጠይቁና የአካል ጉዳተኞችን የማይጋብዙ መሆኑን አንስተዋል።
አብዘኞቹ የአገለግሎት መስጫ ተቋማትም የአካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ አለመሆናቸውንም ገልጸዋል።
በተበባሩት መንግስታት ድርጅት ስር የሚከበረው ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን ዘንድሮ የሚከበረው ለ26ኛ ጊዜ (እ.ኤ.አ. ከ1992 ጀምሮ) ሲሆን የዘንድሮ ክብረ በዓል መሪ ቃልም “የአካል ጉዳተኞችን ማበረታት፣ የአካል ጉዳተኞችን ታቃፊነትና እኩልነት ማረጋገጥ” (“Empowering persons with disabilities and ensuring inclusiveness and equality”) የሚል ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ለአካል ጉዳት እና ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠው አመለካከት የተሳሳተ በመሆኑ ሀገሪቱ ውስጥ የአካል ጉዳተኞችን ቁጥር በትክክል ማወቅ እጅግ አዳጋች እንደሆነና፣ የሚገመተውም ቁጥር ከትክክለኛው ቁጥር ዝቅተኛ እንደሆነ (under-reported) የተለያዩ ጥናቶች ያመለታሉ።
አብዛኛው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ አካል ጉዳተኝነትን ከፈጣሪ እንደመጣ ቁጣ ወይም መርገም እንደሚመለከተውና አካል ጉዳተኛ የሆነ ሰው ያላቸው ቤተሰቦችም ይሁኑ ህብተረሰቡ ሰለአካል ጉዳተኛው፣ ስለሚያስፈልገው ነገር ብሎም እንደማንኛውም ሰው ሙሉ ፍላጎትና መብት እንዳለው በግልጽ ከመወያየት ይልቅ መደበቅና ማሸሽን ይመርጣሉ። በዚህም ምክንያት አካል ጉዳተኞች አጅግ አዳጋች የሆነ ሕይወት እንዲገፉ ይገደዳሉ።
በሀገሪቱ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ በበላይ የሚመለከተውና የሚቆጣጠረው የሠራተኛነ ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሲሆን፥ በዚህ ሚኒስቴር ስር የሚገኝው የማኅበራዊ ደህንነት ልማት ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት የአካል ጉዳነኞችን ከሥራ እና ከማኅበራዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በፌደራል ደረጃ ይመለከታል፣ ያስተባብራል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበራት ፌዴሬሽን (FENAPD) ጥላ ስር ተደራጅተው ከ አካል ጉዳተኞች ጋር በተያያዘ የሚንቀሳቀሱ ስድስት ብሔራዊ ድርጅቶች ይገኛሉ። እነሱም፦
- የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ብሔራዊ ማኅበር፣
- የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበር፣
- የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር፣
- የኢትዮጵያ ማየትና መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር፣
- የኢትዮጵያ ሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሔራዊ ማኅበር፣ እና
- የኢትዮጵያ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ብሔራዊ ማኅበር ናቸው።
ከእነዚህ ብሔራዊ ማኅበራት በተጨማሪ የአካል ጉዳተኞችን ታቃፊነትና እኩልነት በማረጋገጥ እንቅስቃሴዎች ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ጉልህ አስተዋጽዖ እያደረጉ የሚገኙ ማኅበራት ያሉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ፦
- የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ኔትዎርክ (ENDAN)፣
- የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማኅበር፣
- የትግራይ አካል ጉዳተኛ የቀድሞ ወታደሮች ማኅበር (ማኅበር ጉዱአት ኲናት ትግራይ) እና
- በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞችና ልማት ማዕከል (ECDD) ተጠቃሽ ናቸው።
ሑመራ (ኢዜአ)– በትግራይ ክልል የሰቲት ሑመራ ከተማ ነዋሪዎች የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ክልላዊና ሀገራዊ ጉዳዮችን አስመልክተው በቅርቡ ላደረጉት ንግግር ድጋፋቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ገለጹ።
ነዋሪዎቹ ለዶ/ር ደብረጽዮን ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ ትናንት በተሽከርካሪዎች የጀመሩት ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ ወጣቶችን ጨምሮ በሰቲት ሑመራ ከተማ ነዋሪዎች ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በሰልፉ ላይ የተሳተፉት ወጣቶች፣ ማኅበራትና ነዋሪዎች “የትግራይ ሕዝብ ታሪክ የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር ታሪክ የለውም! የሕግ በላይነት ይከበር! በሙስና የተጠረጠሩ በቁጥጥር መዋላቸውን ብንደግፍም በሙስናና ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ ሽፋን ብሔር ተኮር ጥቃት ይቁም! የውጭ ጣልቃ ገብነት ይቁም!” የሚሉና ሌሎች የተለያዩ መፈክሮች ይዘው ሰልፉ ላይ ታይተዋል። የትግራይ ሕዝብ ለሰላም፣ ለእኩልነት፣ ለፍትህና ለዴሞክራሲ የቆመ ነው ሲሉም ድምጻቸውን አሰምተዋል።
መንግስት የሕግ በላይነት ለማስከበር የጀመረው እንቅስቃሴ እንደሚደግፉት የገለጹት ሰላማዊ ሰልፈኞቹ፣ ሕግን የማስከበር ሥራው በሁሉም አካላትና የመሥሪያ ቤት ዘርፎች እንዲተገበር ጠይቀዋል።
በሰልፉ ላይ የተሳተፉ የቃፍታ ሑመራ ወረዳ ነዋሪ አቶ ተመስገን ካሕሳይ “የትግራይሕዝብ በእኩልነትና በፍትህ ያምናል፤ ለዓመታት የታገለውም የሕግ በላይነት እንዲረጋገጥ ነው” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
◌ የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር መስዋዕትነት የከፈለው ለህግ ልዕልና መረጋገጥ ነው – የክልሉ መንግስት
ወጣት የዕብዮ ኃይሉ የተባለ ሌላው የወረዳው ነዋሪ በበኩሉ “እኛ ሕግ የጣሰና በሙስና የተዘፈቀ መደበቂያ አንሆንም፤ መጠየቅ ያለባቸው በትግራይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ክልሎች ያሉ በመሆኑ ሕግ የማስከበር ሥራ በሁሉም ሊተገበር ይገባል” ብሏል። የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹ ጋር ሆኖ መታገሉን ገልጾ አሁንም የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በሚደረጉ ጥረቶች ማንኛውም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን አመልክቷል።
የሰቲት ሑሞራ ከተማ ነዋሪ አቶ ሰለሞን አረጋይ በበኩላቸው “ዶ/ር ደብረጽዮን ያደረጉት ንግግር ሰላምና ልማትን የሚፈልግ ማንኛውንም ብሔር የሚመለከት በመሆኑ ድጋፌን ለመግለጽ ወጥቻለሁ” ሲሉ ገልጿል።
◌ The recent action to impose the rule of law in Ethiopia is getting political agenda – Dr. Debretsion
ወጣት መሰለ ዕቁባይ በበኩሉ ስለ ሰላም እየዘመሩ የትግራይ ሕዝብን ሰላም ለማወክ መሞከር አግባብ ያልሆነና ተቀባይነት እንደሌለው ተናግሯል። የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር ሆኖ የታገለው ሰላምና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በመሆኑ ማንኛውንም ጭቆና እንደማይሸከም አመልክቷል።
በሰልፉ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ርስቁ አለማው እንዳሉት ሰላምና የሕግ የበላይነት እንዲከበር የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወገኖቹ ጋር በመሆን መስዋዕት ከፍሏል። በአሁኑ ወቅትም ከሌሎች ሰላም ወዳድ የአገሪቱ ሕዝቦች ጋር በመሆን ሕግ ለማስከበር ድምጹን በሰላማዊ መንገድ እያሰማ መሆኑን ተናግረዋል።
“በዞናችን የማንነት ጥያቄ ባይኖርም አንዳንድ ሰላም የማይፈልጉ አካላት ሰላሙን ለመንሳት ሌት ተቀን ቢሠሩም ሕዝቡ በትዕግስት እና በሰላም ድምጹን እያሰማ ነው” ብለዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)
የትግራይ ሕዝብ ለዓመታት የከፈለው መስዋዕትነት የህግ የበላይነት እንዲከበርና በማንኛውም ወቅት ተጠያቂነት እንዲኖር ለማድረግ መሆኑን የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሰጠው መግለጫ፥ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ እንዲያተኩር ጠቁሟል።
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የትግራይ ሕዝብ ለዓመታት የከፈለው መስዋዕትነት በሃገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲከበርና በማንኛውም ወቅት ተጠያቂነት እንዲኖር መሆኑን የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ።
የክልሉ መንግስት ኅዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው መንግስት አሁን የጀመረው የህግ የበላይነትን የማስከበር ሂደት በተገቢው ጥንቃቄ ሊከናወን የሚገባው ነው በማለት አስታውቋል።
ሰብዓዊ ጥሰትና ሙስና በፈጸሙ ሰዎች ላይ በመንግስት ሰሞኑን እየተወሰደ ያለው እርምጃ የህግ ልዕልና ሳይሸራረፍ ከተጽዕኖ በጸዳ መልኩ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት መግለጫው አመልክቷል።
የትግራይ ሕዝብ ለዓመታት የከፈለው መስዋዕትነት የህግ የበላይነት እንዲከበርና በማንኛውም ወቅት ተጠያቂነት እንዲኖር ለማድረግ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ እንዲያተኩር ጠቁሟል።
በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የሙስና ችግርና ህገ-መንግስታዊ ጥሰት ውስጥ እጃቸው ያለ አመራሮችና ተቋማት ስለመኖራቸው ቀደም ሲል በተካሔዱ የኢህአዴግ መድረኮች ውይይት መደረጉንም አመልክቷል።
ችግሩ በእኩል እንዲስተናገድ ከማድረግ ባለፈ እርቅና ይቅር ባይነትን መሠረት አድርጎ የተጀመረው ሂደት ወደ ኋላ እንዳይመለስ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቅሷል።
“የህግ የበላይነትም ሳይሸራረፍ እንዲተገበር ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥናት የሚጠይቅ መሆኑንም የክልሉ መንግስት ያምናል” ብሏል መግለጫው።
የትግራይ ክልል ሕዝብ ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር በመሆን የከፈለው መስዋዕትነት የዜጎች እኩልነትና ሰብዓዊ መብት እንዲከበር እንጂ በማንም አካል እንዲጣስ እንዳልሆነ መግለጫው አመልክቷል።
ባለፉት ዓመታት ይታዩ የነበሩት የፍትህና የዲሞክራሲ መጓደሎች እንዲስተካከሉ ሕዝቡ በጽናት እየታገለ መምጣቱንም መግለጫው አስታውሶ በጥልቅ ተሀድሶ ወቅት ህዝቡ ያሳየው ተሳትፎ አንዱ ማሳያ መሆኑን አስረድቷል።
ከሰብአዊ መብት አያያዝና ከሙስና ጉዳዮች ጋር በተያያዘ እየታየ ላለው ሁኔታ ተጠያቂዎቹ እጃቸው ያለበት አመራሮችና ተቋማት መሆናቸውንም መግለጫው አመልክቷል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)ሰሞነኛ ኢትዮጵያ |
የማህፀን በር ካንሰር ክትባት መሰጠት ያለበት ከ9 ዓመት ጀምሮ ላሉ ልጃገረዶች ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ባጋጠመው ክትባት እጥረት ምክንያት ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሆኑ ብቻ እንደሚሰጥ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
አዲስ አበባ (የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር) – ከመጪው ህዳር ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ የማህፀን በር ካንሰር ቅድመ መከላከያ ክትባት በአገር አቀፍ ደረጃ መሰጠት ሊጀመር መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ክትባቱ ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ልጃገረዶች በጤና ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶችና በጊዜያዊ የክትባት ማዕከሎች ይሰጣል። የማህፀን በር ካንሰር ክትባት በሙከራ ደረጃ በትግራይና ኦሮሚያ በተመረጡ ወረዳዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሰጥ ቆይቷል።
በሚኒስቴሩ የክትባት ባለሙያ አቶ ጌትነት ባየ እንዳሉት፥ ክትባቱን ለማስጀመር በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ለሚገኙ ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና ይሰጣል።
“ከመጪው ህዳር ወር ጀምሮም በአገር አቀፍ ደረጃ ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ልጃገረዶች ክትባቱ መሰጠት ይጀምራል” ብለዋል አቶ ጌትነት ።
የማህፀን በር ካንሰር ክትባት መሰጠት ያለበት ከ9 ዓመት ጀምሮ ላሉ ልጃገረዶች ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ባጋጠመው ክትባት እጥረት ምክንያት ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሆኑ ብቻ ነው የሚሰጠው።
የማህፀን በር ካንሰር መንስኤው “ሂውማን ፓፒሎማቫይረስ” (Human papillomavirus) በሚባል ኢንፌክሽን የሚመጣ ሲሆን፥ የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) እንደሚያስታውቀው አግባብ የሆነ በሽታን የመከላከል አቅም ያላቸው ሴቶች (women with normal immune systems) በቫይረሱ ከተጠቁ በኋላ የማህፀን በር ካንሰር ምልክት ሳይታይባቸው ከ15 እስከ 20 ዓመታት ሊቆዩ እንደሚችሉ፣ ደካማ የሆነ በሽታን የመከላከል አቅም ያላቸው ሴቶች (women with weak immune systems) ደግሞ ምልክቱ ሳይታይባቸው ከ5 እስከ 10 ዓመታት ሊቆዩ እንደሚችሉ ያትታል።
ለበሽታው ከሚያጋልጡት ምክንያቶች ውስጥ ዋነኞቹ ልጃገረዶች በለጋነት እድሜያቸው የግብረ ስጋ ግንኙነት መጀመርና ከተለያዩ ሰዎች ጋር ፆታዊ ግንኙነት ማድረግ ሲሆኑ፥ ሲጋራ ማጨስም ሌላው ምክንያት ነው።
ከ30 እስከ 45 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ እና ወደ ህክምና ተቋማት መጥተው ምርመራ በማድረግ ራሳቸውን ከበሽታው መጠበቅ እንደሚኖርባቸው ይመከራል።
በታዳጊ ሀገራት የማህፀን በር ካንሰር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ የካንሰር ዓይነቶች በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጧል። ከዚህ በተጨማሪ በዓለም ላይ እጅግ በብዛት ከሚታይባቸው ሀያ አገራት ውስጥ አስራ ዘጠኙ የአፍሪካ አገራት እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
HPV Information Centre የሚባለው ድርጅት እ.ኤ.አ በሀምሌ ወር በ2017 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ ውስጥ በየ ዓመቱ 7,095 ሴቶች ማህፀን በር ካንሰር የሚጠቁ ሲሆን፣ በየዓመቱም 4,732 ሴቶች በዚሁ ካንሰር ምክንያት ለሞት እንደሚዳረጉ ዘግቧል።
ምንጭ፦ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) እና የዓለም የካንሰር ምርምር ፈንድ (WCRF)
በመቀሌ ከተማ በ147 ሚሊዮን ብር ካፒታል ሙሉ ብርሃን ኢንዱስቱሪና ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ያቋቋመው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
መቀሌ (ኢዜአ) – በ147 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ገመድ ተሸካሚ የኮንክሪት ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካ ምርት ማከፋፈል መጀመሩን አስታወቀ።
“ሙሉ ብርሃን ኢንዱስቱሪና ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር” በሚል የተቋቋመው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ አቶ እሥራኤል ብርሃኑ ለኢዜአ እንደገለጹት ፋብሪካው በአገር አቀፍ ደራጃ ያለውን የኮንክሪት ምሶሶ ችግር ለመፍታት ታሳቢ ተደርጎ የተቋቋመ ነው።
ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት በቀን እስከ 90 የሚደርስ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ ምሶሶዎችን በማምረት ላይ ሲሆን በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር በቀን እስከ 300 የተለያዩ ደረጃ ያላቸው ምሶሶዎችን የማምረት አቅም እንደሚኖረው ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመነጋገር ፋብሪካው ምርቶቹን ለትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች ማከፋፈል መጀመሩን አቶ እሥራኤል አስታውቀዋል።
ፋብሪካው ከአገር ውስጥ ስሚንቶ፣ አሸዋና ጠጠር የሚጠቀም ሲሆን ለምሶሶው መሥሪያ የሚውሉ ብረቶችን ከውጭ በማስገባት ለአገልግሎት ያውላል።
ፋብሪካው በሚያመርተው ምርት መንግስት በከተማና በገጠር የኤሌክትሪክ ሽፋን ለማዳረስ እያከናወነ ላለው ሥራ አጋዥ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት በቦታ አቅርቦትና ብድር በማመቻቸት እገዛ እንዳደረገላቸው የገለጹት አቶ እሥራኤል ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት እንዲችል ከውጭ ለሚመጡ ጥሬ ዕቃዎች መግዣ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የትግራይ ቅርንጫፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ገብረመድህን የኮንክሪት ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ምርቶች ማምረት መጀመሩን ተናግረዋል።
የኮንክሪት ምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካው በመቀሌ ማምረት መጀመሩ ከአሁን ቀደም ከአዲስ አበባ ለማጓጓዝ ለትራንስፖርት ይወጣ የነበረውን ወጪ ይቀንሳል ብለዋል።
ከፍትኛ የኤሌክትሪክ ምሶሶዎች ለ20 ዓመታት ዋስትና ያላቸው መሆኑን የገለጹት ሥራ አስፈፃሚው ካሁን በፊት ለአገልግሎት ይውሉ የነበሩ የባህርዛፍ ምሶሶዎች በጉዳት ምክንያት ያደርሱ የነበሩትን አደጋና የኤሌክትሪክ መቆራረጥ የሚቀንስ ነው።
የትግራይ ክልል ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሃፍቶም ፋንታሁን እንደገለጹት የምሶሶ ማምረቻ ፋብሪካው በመቀሌ ከተማ ለተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ቦታ ከተሰጣቸው ባለሀብቶች መካከል በፍጥነት ወደ ማምረት ሥራ መሸጋገር መቻሉ በአርያነቱ እንዲቀመጥ የሚያደርገው ነው።
የትግራይ ክልል የተረጋጋ ሰላም ያለው በመሆኑ በርካታ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች እየተሳተፉ መሆናቸውን የጽህፈት ቤት ኃላፊው ገልጸዋል።
በመካኒካል ምህንድስና የተመረቀው ወጣት አማኑኤል ሀይሉ በፋብሪካው በመቀጠር በወር 6ሺህ ብር የወር ደሞዝ እየተከፈለው ይሠራል። በፋብሪካው የሥራ እድል በማግኘቱ ደስተኛ መሆኑን የሚናገረው ወጣት አማኑኤል ገቢ ማግኘት መጀመሩ ከቤተሰብ ጥገኝነት ወጥቶ የራሱን ቤተሰብ ለመመስረት መቻሉን ገልጿል።
ወጣት ዙፋን ኪዳኑ በበኩሏ “ማኅበሩ በዘርፉ ኢንቨስት በማድረጉ የአካባቢውን ወጣቶች የሥራ አድል ተጠቃሚ አድርጎናል” ብላለች።
በትግራይ ክልል በ2010 ዓ.ም 24 ቢልዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 1ሺህ 328 ባለሀብቶች በሥራ እንዳሉ ከክልሉ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመልክታል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)
ኢህአዴግ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን በሀዋሳ ከተማ ጀመረ
ሀዋሳ ከተማ፣ ደቡብ (ኢዜአ) – የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ለሶስት ቀናት የሚዘልቀውን ጉባዔውን የደቡብ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው ሀዋሳ ማካሄድ ጀምሯል።
በጉባዔው ቀደም ብለው ድርጅታዊ ጉባዔያቸውን ያጠናቀቁት የኢህአዴግ አራቱ እህት ድርጅቶች (የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ እና የሕዝበ ወያኔ ሀርነት ትግራይ) እና አጋር ፓርቲዎችም ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
በዚህ ጉባዔ ላይ 2 ሺህ የሚጠጉ ተሳፊዎች ታዳሚ ሆነዋል። ከነዚህም 1 ሺህ ያህሉ ተሳፊዎች በድምፅ የሚሳተፉ ናቸው።
———————————————-
———————————————-
የውጭ አገራት ወዳጅ ፓርቲዎችን ጨምሮ፣ በአገር ውስጥ ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራትና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶችም ከዛሬ ጅምሮ በሚካሔደው ጉባዔ ላይ የሚካፈሉ ይሆናል።
የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) 11ኛውን ድርጅታዊ ጉባዔ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ በዋናነት በ10ኛው ጉባኤ መግባባት የተደረሰባቸውን አቅጣጫዎች አፈጻጸምን በተመለከተ የበላይ አመራሩ ግምገማ ለጉባኤ ተሳታፊ አባላት የሚቀርብበትና ከዚያም በመነሳት በቀጣይ ሁለት አመታት ተግባራዊ ሊደረጉ የሚገባቸውን ጉዳዮች አቅጣጫ የሚያስቀምጥበት ይሆናል ብለዋል።
ጉባዔተኛው ከበላይ አመራሩ የሚቅርብለትን መነሻ በመያዝ ባለፉት 27 ዓመታት እንደ ድርጅት ያካሄደውን ጉዞ በመገምገም አገራችን የምትገኝበትን የትግል መድረክ ከግምት ውስጥ በማስገባት ኢትዮጵያ ወደ አዲስ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት አቅጣጫ ሊያሸጋግር እንደሚችል በታመነበት አቅጣጫ ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃልም ብለዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵይ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)
ቪድዮ፦ The Oromo Democratic Party (ODP) is the new OPDO, with Abiy Ahmed and Lemma Megersa as its leaders
በ2010 ዓ.ም ወደ ከፍትኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ 280 ኤርትራውያን ስደተኞች የመግቢያ ፈተና እንዲወስዱ መደረጉንና በአሁኑ ወቅት ፈተናውን ያለፉ 150 ተማሪዎች መለየታቸውን አስረድተዋል።
አዲስ አበባ (ኢዜአ/UNHCR)፦ በኢትዮጵያ በስደት ላይ ከሚኖሩ ኤርትራውያን መካከል 150 ተማሪዎች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብተው የመማር ዕድል እንደሚያገኙ በኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር አስታወቀ።
በተያዘው ዓመት ሌሎች ቁጥራቸው ከ11ሺህ በላይ የሆኑ ህጻናት (የስደተኛ ኤርትራውያን ልጆች የሆኑ) የቅድመ መደበኛ ትምህርት ዕድል ማግኘታቸውም ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር (Ethiopia Administration for Refugee and Returnee Affairs/ ARRA) የሰሜን ጽህፈት ቤት የትምህርት ኦፊሰር አቶ ኤፍሬም ሀጎስ ለኢዜአ እንደገለጹት ከ180 ሺህ የሚበልጡ ኤርትራውያን ስደተኞች በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ ኤርትራውያን ስደተኞች መካከል 150 ተማሪዎች ዘንድሮ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በነጻ ለመማር እድል እንደሚሰጣቸውም ተናግረዋል።
ወደ ከፍትኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ 280 ስደተኞች የመግቢያ ፈተና እንዲወስዱ መደረጉንና በአሁኑ ወቅት ፈተናውን ያለፉ 150 ተማሪዎች መለየታቸውን አስረድተዋል።
ፈተናውን ያለፉ 150 ስደተኞችም በተለያዩ የኢትዮጵያ መንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉም ነው አቶ ኤፍሬም የገለጹት።
ኤርትራውያን ስደተኛ ተማሪዎች በኢትዮጵያ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መደረጉ በሁለቱ አገራት መካከል አሁን የተጀመረውን ሰላማዊ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረውም ተናግረዋል።
◌ ቪድዮ፦ ኢትዮጵያ የቀይ ባህር እና የምጽዋ ወደቦችን ለመጠቀም ቅድመ ዝግጅቶችን እያጠናቀቀች ነው
የኢትዮጵያ መንግስት ለኤርትራውያን ስደተኞች የትምህርት ዕድል ሲሰጥ የአሁኑ ለሰባተኛ ጊዜ ሲሆን በየዓመቱ ከ100 ያላነሱ ተማሪዎችም የዕድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል።
በተመሳሳይ በትግራይ ክልል በሚገኙ አራት የኤርትራውያን ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ 11ሺህ 87 ኤርትራውያን በቅድመና በመደባኛ ትምህርት እንዲሁም በሙያ ክህሎት ማበልጸጊያ እንዲማሩ መደረጉን አቶ ኤፍሬም አክለው ተናግረዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ከአገራቸው ተሰደው ወደኢትዮጵያ ቢመጡም ልጆቻው እዚህ የትምህርት ዕድል በማግኘታቸው መደበኛ ትምህርታቸውን መቀጠላቸውን የተናገሩት ደግሞ በማይዓይኒ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙት አቶ ተስፋልደት ይህደጎ የተባሉ ስደተኛ ናቸው።
በአዲ ሓሩሽ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ሌላው ስደተኛዋ ወይዘሮ ለምለም ዘካሪያስ እንደተናገሩት በአካባቢያችን የሚገኙ ትምህርትቤቶች ለኤርትራውያን ተማሪዎች በራቸው ክፍት መሆኑ ትልቅ እድል መሆኑን ገልጸዋል።
“ልጆቻቸው ከኢትዮጵያውያን ወንደሞቻቸው ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ እንዲማሩ መደረጉ በሁለቱ አገራት ህዝቦች መካከል ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት የላቀ አስተዋፅኦ አለው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለኤርትራውያን ስደተኞች እየሰጠ ያለው የከፍተኛ የትምህርት እድል ለሌሎች አገራት በመልካም አርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለማግባት የመግቢያ ፈተና የወሰደው ተማሪ ዓንዶም ፍሳሃየ ነው።
እስከ ግንቦት ወር 2010 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በአጠቃላይ 71,833 ኤርትራውያን ስደተኞች ትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙ አራት መጠለያ ጣብያዎችና አፋር ክልል ውስጥ በሚገኙ ሁለት መጠለያ ጣብያዎች ውስጥ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) ዘግቧል።
ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR)