-
Search Results
-
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ ለትምህርትና ጤና አገልግሎት የሚውል ከ452 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረገ። የጃፓን መንግስት አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲው በኩል ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ አራት ፕሮጀክቶችን ለመገንባትና ለማስፋፋት ያስችላል።
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ (Daisuke Matsunaga) የፕሮጀክት ግንባታና ማስፋፊያ ከሚደረግላቸው ትምህርት ቤቶች ኃላፊዎች ጋር የድጋፍ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ፕሮጀክቶቹ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን የጉንችሬ እና እነሞር ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታና በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የሀሮ ሾጤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ናቸው።
በተጨማሪም ለሻሻመኔ ከተማ የአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች የምግባረ ሰናይ መጠለያ ግንባታና ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የዩሮሎጂ እና ድንገተኛ ክፍል የህክምና መሣሪያዎች ግዥ የሚውል ነው።
እነዚህ አራት የትምህርት እና የጤና ፕሮጀክቶች ከአራት ሺህ በላይ ህዝብ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።
አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ እንዳሉት አገራቸው ለኢትዮጵያ ልማት ተሳትፎ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች። ጃፓን በኢትዮጵያ እ.አ.አ ከ1989 ጀምሮ በተለያዩ ክልሎች ከ400 በላይ ፕሮጀክቶችን በመሥራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገች ነው።
በትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ በኢኮኖሚ ልማትና ሌሎችም መስኮች ድጋፍ ስታደርግም ቆይታለች።
በስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽነር እርስቱ ይርዳው የተደረገው ድጋፍ የዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል የትምህርት ፍላጎት ለማሟላት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ድጋፉ በተለይም ትምህርት ቤት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች መሆኑ የትምህርት ሽፋንን በማስፋት የመንግስትን ጥረት እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ የጃፓን ኤምባሲ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኘውን የራስ መኰንን አዳራሽ ለማደስ የ85 ሺሕ 679 ዶላር (2,403,500 ብር) ዕርዳታ መለገሱን ሪፖርተር ጋዜጣ በእሁድ ታህሳስ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. እትሙ ዘግቧል።
አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ እና የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር አህመድ ሐሰን (ዶ/ር) የእርዳታ ስምምነቱን የተፈራረሙ ሲሆን፣ ገንዘቡም የራስ መኰንን አዳራሽ ባህላዊና ታሪካዊ ዳራው ሳይጠፋ ለማደስ፣ የተበላሹ ክፍሎችን ለመጠገን፣ ውስጣዊ ክፍሉን ለማደስ እና አዳዲስ ቁሳቁስ ለማስገባት መሆኑ ታውቋል።
የጃፓን መንግስት ትምህርታዊ ድጋፍ ከማድረጉም በተጨማሪ የራስ መኰንን አዳራሽን ለማደስ መነሳቱ፣ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ኢትኖሎጂካል ሙዚየም በርካታ ጎብኚዎች እንዲስብ ያስችላል ተብሏል።
በሙዚየሙ ከአሥር ሺሕ በላይ የኢትዮጵያ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች የሚገለጹባቸው አልባሳትና ቁሳቁሶች አሉ፤ ይህም በአፍሪካ አንዱ ታዋቂ ሙዚየም እንዲሆን አስችሏል።
በቀድሞው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ሕንፃ ውስጥ የሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ ከ50 ዓመታት በላይ ዕድሜው በስሩ ያቀፋቸው ቤተ-መጻሕፍት፣ የኢትኖግራፊክ ሙዚየም የምርምርና የጥናት ማዕከልን ነው። በውስጡም መጻሕፍት፣ ታሪካዊ ሰነዶችና መዛግብት፣ የዳግማዊ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱን ጨምሮ የድምፅና የምስል ቅጂዎች፣ ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ የጥናት ድርሳኖች፣ ጆርናሎች፣ ረጅም ዕድሜን ያስቆጠሩ የብራና መጻሕፍትንም ይዟል።
እንዲሁም እስከ 20 ሺሕ የሚደርሱ የኅትመት ክምችቶች ከቅድመ ምረቃ እስከ ድኅረ ምረቃ ተማሪዎች፣ ለተመራማሪዎች ጥናትና ምርምር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2010 ዓ.ም. መስከረም ወር ከጃፓኑ ኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ ጋር ትምህርታዊ ልውውጥና የጥናት ትብብር ለማድረግ የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙ ይታወሳል።
ምንጭ፦ ኢዜአ እና ሪፖርተር ጋዜጣ
ዩኒሴፍ ባወጣው መግለጫ መሠረት በጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ለስደተኞች ህጻናት የሚሆኑ ሦስት ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ፣ ባለ 41 ክፍሎች ስምንት ሁለተኛ ደረጃ እና ባለ 84 ክፍሎች አራት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገነባሉ።
አዲስ አበባ (ኢዜአ)– በጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች እና ስደተኞች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች ሊገነቡ እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) አስታወቀ።
ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ኅዳር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ የሚከናወነው ”ትምህርት ቆሞ አይጠብቅም” በሚል መርህ ለትምህርት በተያዘው እና በመላው ዓለም በስደት ለሚገኙ እና ለአደጋ የተጋለጡ 12,000 የሚደርሱ ህጻናትን በትምህርት ለመደገፍ ከተያዘው የ15 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በጀት ውስጥ እንደሆነ ታውቋል።
ሦስት ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ፣ ባለ 41 ክፍሎች ስምንት ሁለተኛ ደረጃ እና ባለ 84 ክፍሎች አራት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ የሚከናወን መሆኑን መግለጫው አትቷል።
በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ጊሊያን ሜልሶፕ ”ይህ ፕሮጀክት በስደተኞች መጠለያ ጣቢያና የስደተኞች ተቀባይ ማህበረሰብን ተጠቃሚ ለማድረግ የምናደርገው ጥረት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የሚያሳይ ነው” ብለዋል።
ማንኛውም ታዳጊ በምንም አይነት ሁኔታ ቢገኝ የወደፊት ዕጣ ፈንታውን ብሩህ ከሚያደርገው ትምህርት መራቅ የሌለበት መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ 3600 ታዳጊዎችን በሁለተኛ ደረጃ፣ 8400 ታዳጊዎችን በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተቀብሎ የሚያስተናግድ ይሆናል። ትምህርት ቤቶቹ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2019 እና 2020 ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚገመት ተገልጿል። ትምህርት ቤቶቹ በቁሳቁስ፣ በላቦራቶሪ፣ በቤተመጽሐፍት፣ በመምህራን ቢሮዎችና በሌሎች አስፈላጊ ነገሮች የተሟላ እንደሚሆኑም ተነግሯል።
ዩኒሴፍ ያውጣውን መግለጫ ሙሉውን (በእንግሊዝኛ ቋንቋ) ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ተመሳሳይ ዜናዎች፦- ውጤታማ የማኅበረሰብ-አቀፍ የአኩሪ አተር የመነሻ ዘር ብዜት ሥራዎች በፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል
- የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስላለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ የሰጠው መግለጫ
- የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘላቂ የሆነ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር በአንድነት ለመሥራት ቃል ገቡ
- ሐረር የሚኖሩ የጉራጌ ህብረተሰብ አባላት በመስቃንና ማረቆ ወረዳ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ100,000 ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ
- በአገሪቱ ውስጥ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኘው የኤች አይ ቪ/ኤድስ፥ አዲስ አበባ ውስጥ በአፍላ ወጣቶች ላይ ግን ችግሩ ይከፋል
አዳማ ከተማ ውስጥ የሚገነባው የኮንፈረንስና ኮንቬንሽን ማዕከል ግንባታው ከ3 እስክ 5 ዓመት ጊዜ የሚፈጅ ሲሆን፥ የዘንድሮውን ዓመት ለዝግጅት በመያዝ በቀጣይ ወደ ግንባታ ለመግባት በትኩረት እንደሚሠራ የከተማዋ ከንቲባ አቶ መስፍን አሰፋ ገልጸዋል።
አዳማ (ኢ.ፕ.ድ./ኤፍ.ቢ.ሲ.) – አዳማ ከተማን የኮንፈረንስና እና ኮንቬንሽን ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የአዳማ ከተማ አስተዳደር ሠራ ገለጸ። የከተማ አስተዳደሩ የአዳማ ከተማ ሀገሪቱ ውስጥ ካላት መዕከላዊ አቀማመጥ እና ለዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ያላትን ቅርበት መሠረት በማድረግ ከተማዋን የኮንፈረንስ እና ኮንቬንሽን ማዕከል ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ነው የተገለፀው።
የማዕከሉ ዲዛይን ተሠርቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፥ ዲዛይኑም የአካባቢውን ማኅበረሰብ ባህል እና እሴት በጠበቀ መልኩ የተሠራ መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ አቶ መስፍን አሰፋ ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም ማዕከሉ መንግስትን እና የአካባቢውን ባለሀብቶች በማሳተፍ የሚሠራ መሆኑ ነው የተገለፀው።
ዲዛይኑ ተሠርቶ እንደተጠናቀቀም ከባለሀብቱ ጋር ወይይት ተደርጓል ያሉት ከንቲባው፥ የማዕከሉ ግንባታ ለከተማዋም ሆነ ለሀገሪቱ ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አቶ መስፍን አንስተዋል።
ግንባታው ከ3 እስክ 5 ዓመት ጊዜ የሚፈጅ ሲሆን፥ የዘንድሮውን ዓመት ለዝግጅት በመያዝ በቀጣይ ወደ ግንባታ ለመግባት በትኩረት እንሠራለን ነው ያሉት ከንቲባው። ግንባታውን አጠናቆ ለመጨረስም 2 ቢሊየን ብር ስፈልጋል ያሉት ከንቲባው፥ ለግንባታው የሚያስፈልገው የ10 ሄክታር መሬት የማዘጋጀት ሂደቱም ተጀምሯል ብለዋል።
◌ Addis-Africa International Convention and Exhibition Center (AAICEC) Share Company
በሌላ በኩል በከተማዋ ከኢንቨስትመንት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ቅሬታ መቅረፍም፥ በዚህ ዓመት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት ያለ ጉዳይ መሆኑን ነው ከንቲባው የተናገሩት።
ፋና (ኤፍ.ቢ.ሲ.) እንደዘገበው ብዙ ጊዜ የከተማዋ አቅም እና የኢንቨስትመንት አማራጭ ላይ በቂ ዝግጅት ስለማይደረግ ባለሀብቱ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ጠይቆ ምላሽ ሳያገኝ ለበርካታ ዓመታት ወደሥራ ሳይገባ መቆየቱ እና ይህም የተለያየ ቅሬታ መፍጠሩንም ከንቲባው አንስተዋል ።
የተጠራቀሙ ጥያቄዎችን ለመመለስ እና የዘርፉን ውስንነቶች ለመቅረፍም የከተማዋን አቅም እና የኢንቨስትመንት አማራጮች የመለየት ሥራ እየሠራ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ ለመሥራት ከታሰበው የኮንፈረንስና የኮንቬንሽን ማዕከል አጋዥ የሆኑ ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴሎች ለመስራት ፍቃድ የሚጠይቁ ባለሀብቶች በቅድሚያ የሚስተናገዱ መሆኑን ከንቲባው ጠቁመዋል።
በመስከረም ወር 2007 ዓ.ም. በይፋ የተመረቀው የአዲስ-አዳማ የፈጣን መንገድ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ ጀመሮ ከከተማዋ ወደ አዲስ አበባ የሚደረገውን ጉዞ በእጅጉን እንዳቃለለውና በሁለቱ ከተሞች የነበረውን የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ሁነኛ በሚባል መልኩ እንዳሻሻለው ይታወቃል። ይህ 85 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለውና ወደጎን ስድስት መኪናዎችን ማስተናገድ የሚችለው መንገድ ከተገነባ በእላ አዳማ ከተማ ውስጥ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መጨመሩን ብዙዎች ይመሰክራሉ።
ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ ፋና ብሮድካስቲንግ፣ ሰሞነኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርዱ ሰብሳቢ ተደርጋ መሾም የሀገሪቱን የምርጫ ሂደት ለማሻሻል የተገባውን ቃል ለማጠናክር እና ለ2012 ዓ.ም. ምርጫ ዝግጅት ገለልተኛ የምርጫ ቦርድን ለማጠናከር ያለውን የፓለቲካ ቁርጠኝነት ምስክር ነው ብለዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኅዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ስብሰባው ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ በአራት ተቃውሞ፣ ሦስት ድምፅ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምጽ ሾሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የዕጩዋን ሹመት ባቀረቡበት ወቅት መንግስት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢን በአዲስ መልክ ለመተካት የወሰነው የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ዳር እንዲደርስ ለማድረግ የተጀመረው የጥረት አካል መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም የዲሞክራሲ መገለጫ የሆነው ምርጫ ቦርድ ተዓማኒና ገለልተኛ ለማድረግ ተቋሙን የማዘመንና ማሻሻል ከማድረግ በተጨማሪ ብቁ የሆነ መሪ እንደሚያስፈልገው በማመን ወ/ሪት ብርቱካን ለዕጩነት ቀርበዋል ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።
ዶ/ር ዐብይ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርዶ ሰብሳቢ ተደርጋ መሾም የሀገሪቱን የምርጫ ሂደት ለማሻሻል የተገባውን ቃል ለማጠናክር እና ለ2012 ዓ.ም. ምርጫ ዝግጅት ገለልተኛ የምርጫ ቦርድን ለማጠናከር ያለውን የፓለቲካ ቁርጠኝነት ምስክር ነው ብለዋል።
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አቅራቢነት የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ሹመት የተከናወነው የቀድሞዋ ሰብሳቢ አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ በፈቃዳቸው ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ነው።
ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ማን ናቸው ?
– በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው፣
– ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ኬኔዲ ስኩል ኦፍ ገቨርንመንት የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው፣
– በፌደራል ፍርድ ቤቶች በዳኝነት ያገለገሉ፣
– የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ፣
– በውጪ ሀገር በናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዲሚክራሲ በተባለ ድርጅት ተመራማሪ ሆነው የሠሩ፣
– የፓርቲ አመራርና ተወዳዳሪ (ቅንጅት) ሆነው የሠሩ፣
– በምርጫ ሂደት ሰፊ ልምድ ያላቸው ናቸው።◌ Interview: Birtukan Mideksa, who shook Ethiopian court system, is back to Ethiopia from exile
ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በአሁኑ ሰዐት የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆኑና ገለልተኛ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ለምክር ቤት አባላት ተናግረዋል። የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑ ይታወቃል።
ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ከቀድሞ ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ (ቅንጅት) ጋር በተያያዘ ለእስራትና ለእንግልት ከተዳረጉ በኋላ ከሀገር ወጥተው በሀገረ አሜሪካ ለሰባት ዓመታት በስደት የኖሩ ሲሆን፥ በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን ሁለንተናዊ ለውጥ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባቀረቡላቸው ጥሪ መሠረት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው ይታወሳል።
PHOTO: Abebe Abebayehu
ዶ/ር ሂሩት ወልደማርያም በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በአማራ እና በኦሮሞ ብሄር ተማሪዎች መካከል በተነሳው ግጭት የሶስት ተማሪዎች ህይወት ማለፉን ገልፀው፥ የተለየ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች በተማሪዎች መካከል የብሄር ግጭት እንዲነሳ በማድረግ የመማር ማስተማር ሂደቱን ከማስተጓጎል በላይ ለስው ህይወት መጥፋት ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል።
አዲስ አበባ (የትምህርት ሚኒስቴር) – በዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር አጠቃላይ ማህበረሰቡ ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በጋራ እንዲሠራ ተጠየቀ።
በአሁኑ ወቅት በመላ ሃገሪቱ እየተካሄደ የሚገኘውን ለውጥ ለመቀልበስ የሚፈልጉ ኃይሎች ፊታቸውን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በማዞር ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን በማወክና ግጭቶች እንዲፈጠሩ በማድረግ ግጭቶቹም የብሄር ግጭት መልክ እንዲይዙ በማድርግ ከፍተኛ ሁከት እና አለመረጋጋት በዩኒቨርሲቲዎች እንዲቀሰቀስ እያደረጉ መሆኑ ተደርሶበታል።
ይህንኑ ሰሞኑን በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች የተከሰተውን አለመረጋጋትና ሁከት አስመልክቶ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ወልደማርያም ኅዳር 12 ቀን 2011 ዓ.ም በፅህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ “ዩኒቨርሲቲዎች ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የተለያየ አስተሳሰብና ክህሎት ያላቸው ወጣቶች የተሰባሰቡበት ቦታ መሆኑን ገልፀው፥ እነዚህን ወጣቶች ለተለያየ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ ለማድረግና እርስ በእርሳቸው ያለመተማመንና በመካከላቸውም የብሄር ግጭት በማስነሳት የመማር ማስተማር ሥራውን ከማስተጓጎላቸውም በላይ በግጭቱ ውድ የሆነውን የሰው ህይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሆነዋል“ ብለዋል።
ዶ/ር ሂሩት አያይዘውም ሰሞኑን በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በአማራ እና በኦሮሞ ብሄር ተማሪዎች መካከል በተነሳው ግጭት የሶስት ተማሪዎች ህይወት ማለፉን ገልፀው፥ በግጭቱ ህይወታቸውን ላጡ ውድ ተማሪዎቻችን የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልፀው ለተማሪ ቤተሰቦችና ለማህበረሰቡ መፅናናትንም ተመኝተዋል።
አሁን የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታትም ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፤ የዩኒቨርሲቲ ቦርድ አባላት፤ የሁለቱም ብሄር ተወካዮችና ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር በመሆን የዕርቅና ሰላም የማስፈን ሥራ ለመሥራት ወደ ዩኒቨርሲቲው እንደሚሄድ ሚኒስትሯ ጨምረው ገልፀዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች የዕውቀት የክህሎትና የአዳዲስ ሃሳቦች ማፍለቂያ ተቋሞች መሆናቸውን የገለፁት ሚኒስትሯ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ሙሉ ጊዜያቸውን ለትምህርትና ለምርምር በማዋል የመጡበትን ዓላማ ማሳካትና በቆይታቸውም ነገሮችን በደንብ የሚያስቡና አንዳንድ ወደ ጥፋት የሚሄዱ ተማሪዎችንም ወደ በጎነት የሚመልሱ ሊሆኑ እንደሚገባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምቹና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር የአካባቢው ማህበረሰብ የአስተዳደር አካላትና የፀጥታ አካላትም በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ በመግለጫው ተካቷል።
ምንጭ፦ የትምህርት ሚኒስቴር
ተጨማሪ ትምህርት ተኮር ዜናዎች
ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከተከፈተበት ከ1959 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋሙንም በመምራት እንዲሁም ታላላቅ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሙዚቃ ዕድገት አስተዋፅዖው የጎላ መሆኑን ለተሳታፊዎች አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት አውስቷል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)–በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥር ያለው የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ-ጥበባት ማዕከል 40ኛ የጥበብ ውሎ መድረኩን ቅዳሜ ኅዳር 8 ቀን 2011 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ አካሒዷል።
በዝግጅቱ ላይ የዕውቁ ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ሰው የፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ሕይወትና ሥራዎች ላይ ውይይት እየተደረገ ተደርጓል። ሥራዎቹን እና ሕይወቱን አስመልክቶ የሙዚቃ ባለሙያ እና በቅርቡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ሆኖ የተሾመው አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት የውይይት መነሻ ጥናት አቅርቦ በታዳሚዎች ውይይት ተካሂዶ ነበር።
“ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ <ባለዋሽንቱ እረኛ>(The Shepherd Flutist) በተሰኘ ታላቂ ሥራ የኢትዮጵያን መልክ በረቂቅ ሙዚቃ ያሳዩ ናቸው” በማለት አቶ ሠርፀ የገለጿቸው የሙዚቃውን ረቂቅነት በመጥቀስ ሲሆን፤ ፕሮፌሰር አሸናፊ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከተከፈተበት ከ1959 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋሙንም በመምራት እንዲሁም ታላላቅ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሙዚቃ ዕድገት አስተዋፅዖው የጎላ መሆኑን ለተሳታፊዎች አውስቷል።
በሙዚቃ ላይ ከሠሯቸው ከበርካታ የምርምር ሥራዎቻቸው ውስጥ “Roots of Black Music” የተሰኘው መጽሐፋቸው በብዙ የዓለማችን የሙዚቃ አጥኚዎች የተዘነጉ (የተዘለሉ) የአፍሪካ/የምሥራቁ ዓለምን የሙዚቃ ስልትና ፍልስፍናን አጉልተው ለተቀረው ዓለም ያሳዩበት እንደሆነም አቅራቢው አብራርተዋል።
በውይይቱም ከተሳታፊዎች የኢትዮጵያ ሙዚቃ በዘመናት መካከል የመድመቅና መልሶ የመደብዘዝ ችግር ከምን የመነጨ እንደሆነ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፥ “ዋናው ችግር በተለያዩ ምክንያቶች የኢትዮጵያ ሙዚቃ ተቋም ፈርሷል፤ እሱን መልሶ መገንባት የቤት ሥራችን ነው” ብለዋል አቶ ሠርፀ። አክለውም የኢትዮጵያ የሙዚቃ ትምህርት ሥርዓት ከተመሠረተበት ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከምዕራባውያን የሙዚቃ ሥርዓተ-ትምህርት ነፃ መውጣት ያለመቻሉም ሌላ ምክንያት እንደሆነ አቅራቢው ጠቅሰዋል።
ውይቱን የመሩት የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ እንዳለጌታ ከበደ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ማደግ ብርቱ ጥረት ያደረጉ የጥበብ ሰዎችን ፈለግ እና ሥራዎቻቸውን ለተተኪው ትውልድ ለማውረስ በሁሉም አካላት ጥረት መደረግ አለበት ብለዋል።
ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ አዲስ አበባ ግንቦት 8 ቀን 1930 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወለዱ። አባታቸው ግራዝማች ከበደ አድነው፣ እናታቸው ደግሞ ወ/ሮ ፋንታዬ ነከሬ ያባሉ ነበር። የሙዚቃ ፍቅርን ገና በልጅነታቸው ያሳደሩባቸው እናታቸው ቢሆኑም ታዳጊው አሸናፊ ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳሉ እናታቸውን በሞት አጥተዋል።
ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ መሠረታዊ ትምህርታቸውን በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት እና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (አሁን ኮከበ ጽባሕ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የሚባለው) ካጠናቀቁ በኋላ ከሐረር የመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጅ ተመርቀዋል። ከዚያም ወደ አሜሪካ በማቅናት ኒው ዮርክ ክፍለ-ሀገር ከሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሮቸስተር፣ ኢስትማን የሙዚቃ ትምህርት ቤት (University of Rochester’s Eastman School of Music) በ1954 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ ከተመረቁ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለሰ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትን መሥርተዋል። የትምህርት ቤቱም የመጀመሪያው ዳይሬክተር ከመሆናቸውም ባሻገር በመሆን ሙዚቃን ከማስተማሩ ባሻገር አገልግለዋል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወ.ወ.ክ.ማ.)፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የበጎ አድራጎት ድርጅት መርሓ-ዕውራን ትምህርት ቤት እና በመሳሰሉ የወጣቶች ማኅበራት እየተገኙ የሙዚቃ ትምህርት ይሰጡ ነበር።
በድጋሚ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ ተመልሰው፣ ኮነቲከት ክፍለ-ሀገር ከሚገኘው ዌስልያን ዩኒቨርሲቲ (Wesleyan University) በ1961 ዓ.ም የማስትሬት፣ እንዲሁም በ1963 ዓ.ም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ምዕራባዊ ባልሆኑ ሙዚቃዎች ምርምር (ethnomusicology) አግኝተዋል።
ከሙዚቃው መምህርነትና ተመራማሪነት ባሻገር ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ደራሲም ነበሩ። እ.ኤ.አ በ1964 ዓ.ም ኮንፌሽን (Confession)፣ እ.ኤ.አ በ1982 ዓ.ም ሩትስ ኦፍ ብላክ ሙዚክ (Roots of Black Music) የሚሉ መጻሕፍትን ያሳተሙ ሲሆን፣ በሙዚቃ ላይ ያተኮሩ በርካታ ጽሁፎችን፥ በተለይም ደግሞ በአፍሪካ-አሜሪካውያን ባህልና አኗኗር ላይ ለሚያተኩረው “The Chronicler” ለተሰኘው መጽሔት ጽፈዋል።
በአሜሪካ ፕሮፌሰር አሸናፊ ኑሯቸው ፍሎሪዳ ክፍለ ሀገር በሚገኘው ፍሎሪዳ ስቴት ዩኒቨርሲቲ (Florida State University) የሙዚቃ ኮሌጅ ውስጥ በመምህርነት የሠራ ሲሆን፣ ተቀማጭነቱን እዚያው አሜሪካ ያደረገውናታዋቂውን የኢትዮጵያ ምርምር ካውንስልን (Ethiopian Research Council) በዳይረክተርነት መርቷል።
ፕሮፌሰር አሸናፊ ከመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ባለቤታቸው (ወ/ሮ እሌኒ ገብረመስቀል) እና ሁለተኛ ባለቤታቸው (አሜሪካዊ) አራት ልጆችን (ሦስት ሴቶችና አንድ ወንድ) ልጆችን አፍርተዋል። ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ የ60ኛ የልደት በዓላቸው ዕለት በመኖሪያ ቤታቸው ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ሞተው የተገኙ ሲሆን፤ ምናልባትም የራሳቸውን ሕይወት ሳያጠፉ እንዳልቀሩ ብዙዎች ይገምታሉ።
PHOTO: Ethiopian Academy of Sciencesአዲስ አበባ (ኢ.ፕ.ድ) በአዲስ አበባ በ2010 ዓ.ም የትምህርት ጥራት ደረጃን ያላሟሉ 52 የቅድመ መደበኛ፣ የአንደኛ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ መሰናዶ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን የአዲስ አበባ አጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ብሩክነሽ አርጋው ኅዳር 7 ቀን 2011 ዓ.ም ለብዙኃን መገናኛ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ በ2010 ዓ.ም በአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን አማካኝነት ቁጥጥር ከተደረገባቸው 1 ሺህ 407 ትምህርት ቤቶች ውስጥ በቅድመ መደበኛ 26፣ በመጀመሪያ ደረጃ 22፣ በሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ አራት ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች በመሆናቸው ተዘግተዋል።
እንደ ወ/ሮ ብሩክነሽ ገለጻ፥ በቅድመ መደበኛ ትምህርት ከደረጃ በታች ሆነው የተዘጉ ትምህርት ቤቶች የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተቋም ሊኖሩት የሚገባ የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች ማሟላት አልቻሉም፤ ተመጣጣኝ የሆነ የመምህራንና የሠራተኞች የትምህርት ደረጃም የላቸውም፤ የመምህራንና ሠራተኞች ብዛት አነስተኛ ነው፤ የሕፃናት ማሸለቢያ ክፍልና የመምህራን ማረፊያ ክፍል ውስጥ ሊኖሩ የሚገባቸው ቁሳቁሶች አልተሟሉም፤ ቋሚ የውጭ መጫወቻ መሳሪያዎች የሏቸውም። የትምህርት ማበልፀጊያ ማዕከል እጥረት፣ በቂ የሰው ኃይልና ለሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት የሚያስፈልጉ የትምህርት መሳሪያዎችና የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች አለመኖርም ለትምህር ቤቶቹ መዘጋት ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።
ወ/ሮ ብሩክነሽ፥ የተዘጉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 3በ1 የሆነ ቤተ ሙከራና የማዕከል ቁሳቁስ ግብአት በተገቢው ያልተሟላላቸው፣ 3በ1 የሆነ የስፖርት ሜዳ ያላሟሉና የሰለጠነ መምህር የሌላቸው እንዲሁም የመምህራን ማረፊያ ክፍል ውስጥ ሊኖሩ የሚገባቸው ቁሳቁሶችን እንዳላሟሉ ገልጸዋል። የሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤቶችም በተመሳሳይ ለትምህርት ጥራት የተሰጠውን የመመዘኛ መስፈርት ባለማሟላታቸው እንደተዘጉ ተናግረዋል።
◌ These two Ethiopian students are working to launch their own rocket – the future Eng. Kitaw Ejigu
በቅድመ መደበኛ ከተዘጉ ትምህርት ቤቶች መካከል ቦሌ ቡልቡላ፣ ሳሊተ ምህረት፣ ቶምናጄሪ፣ ገነተ ኢየሱስ፣ አዲስ ሰው፣ ኤሎን፣ ሀመር፣ ሙሴ፣ ሜሲ ሚዶ፣ ብራስ ዩዝ፣ ንጋት፣ አሀዱ ቤተሰብ፣ ደብል፣ አፍሪካስ ድሪም፣ ባቤጅ፣ ብሪሊያንት፣ አልአፊያ ቁጥር 1፣ ጂ. ኤች፣ ኢስት አፍሪካ፣ ቅዱስ ዮሃንስ፣ አጼ ተክለጊዮርጊስ፣ ሳም ፋሚሊ፣ ኒው ዩኒክ፣ ብራይት የሚጠቀሱ ሲሆን፥ ማራናታ፣ ቦሌ ካውንት፣ ማይ ፊውቸር፣ ሰብለ መታሰቢያ፣ ጎል፣ አካዳሚ ፎር ኤክሰለንስ፣ ፎንት፣ ሰለሞን፣ አፍሪካስ ድሪም፣ ቤተሰብ፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ ብሪሊያንት፣ እየሩሳሌም፣ ስሪ ኤስ ሜርሲ ከተዘጉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪ እንጦጦ ወንጌላዊት፣ ማርክ፣ አዲስ አበባ ሉተራንና መካነ ኢየሱስ የሁለተኛ ደረጃ መሰናዶ ትምህርት ቤቶች የተዘጉ መሆናቸውንም ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል። ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በከተማዋ በ2011 ዓ.ም ፈቃድ ያገኙ 101 አዲስ ት/ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራቸውን ጀምረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአጠቃላይ ጥራትና አግባብነት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን (ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ) የሰጠው መግለጫ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአጠቃላይ ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ የ2010 ዓ.ም የትምህርት ተቋማት የኢንስፔክሽን እና የእውቅና ፍቃድ እድሳት ሪፖርትን በተመለከተ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ
- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ወ/ሪት ብሩክነሽ አረጋው በ2010 ዓ.ም ከቅድመ መደበኛ እስከ መሰናዶ ድረስ ባሉ የመንግስትና የግል ትምህርት ተቋማት በተካሄደ የኢንስፔክሽን መረጃ መሠረት ተቋማቱ ያሉበትን ደረጃ በዝርዝር አቅርበዋል። በዚሁ መሠረት በቅድመ መደበኛ ትምህርት አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት መካከል 41 ተቋማቱ ደረጃ 1፣ 560 ደረጃ 2 እንዲሁም 108 ተቋማት ደረጃ 3 እና 1 ተቋም ደረጃ 4 ላይ መሆናቸው ገልፀዋል።
- በመጀመሪያ ደረጃ በሚገኙ የትምህርት ተቋማት በተደረገ ኢንስፔክሽን 10 ተቋማት በደረጃ 1፣ 409 ተቋማት ደረጃ 2፣ 125 ደረጃ 3፣ እና 1 ተቋም ብቻ ደረጃ 4 ላይ እንደሚገኝ የተጠቆመ ሲሆን በሁለተኛና መሰናዶ ተቋማት ላይ በተካሄደ ኢንስፔክሽን ደግሞ 6 ተቋማት ደረጃ 1፣ 80 ተቋማት ደረጃ 2፣ 66 ተቋማት ደረጃ 3 ላይ ሲገኙ አንድም ተቋም ደረጃ 4 ላይ አለመገኘቱን ነው ዳይሬክተሯ ገልፀዋል።
- በሌላ በኩል ባለስልጣኑ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመሆን በአዲስ አበባ ደረጃ የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና የተማሪዎች ውጤት ዝቅተኛ የሚሆንበትን ምክንያት በተለመከተ ጥናት ማድረጉ በመግለጫው ከመገለፁ ባሻገር የጥናቱን ውጤትም የኮተቤ ሜትፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዘዳንት ዶ/ር ኤላዛር ታደሰ ያቀረቡ ሲሆን ለ8ኛ ክፍል ውጤት ማሽቆልቆል በዋናነት ከተለዩ ምክንያቶች መካከል ተማሪዎች ለትምህርት ያላቸው አሉታዊ አመለካከት፣ የመምህራን ለደረጃው ብቁ አለመሆን እንዲሁም በየትምህርት ተቋማቱ የሚደረገው (የማስተባበርና መቆጣጠር (የሱፐርቪዥንና ኢንስፔክሽን) አሠራር በቂ አለመሆን እንደምክንያት ተጠቁሟል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ
አቶ ሽመልስ አብዲሳ ኡፍታላ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሲሾሙ፥ ወይዘሮ ቢልለኔ ስዩም ወልደየስ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ሆነው ተሹመዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – አቶ ሽመልስ አብዲሳ ኡፍታላ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው በዛሬው ዕለት (ጥቅምት 26 ቀን 2011 ዓ.ም) ተሾሙ።
አቶ ሽመልስ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩትን አቶ ፍጹም አረጋ ተክተው ነው የተሾሙት። በዚህም አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተሰጣቸው ኃላፊነት መሠረት የፕሬስ ሴክቴሪያት ጽህፈት ቤት፣ የብቃትና ፖሊሲ ምዘና ጽህፈት ቤት፣ የአገር ደህንነት ጉዳይ አማካሪ ጽህፈት ቤትና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትን ይመራሉ ተብሏል።
ከዚህ በፊት የነበሩት አቶ ፍጹም አረጋ ወደ ቀድሞ ቦታቸው፥ ማለትም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ተመልሰዋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚነት የነበሩት በላቸው መኩሪያ (ዶ/ር) በመስከረም ወር መጀመሪያ ሳምንት “የግል/ የቤተሰብ ጉዳይ” በሚል ምክንያት ኃላፊነታቸውን (ብሎም ከኮሚሽኑ በአጠቃላይ) መልቀቃቸው ይታወሳል።
I wanted to announce that I will be moving back to Ethiopian Investment Commission—as a Commissioner. I have enjoyed my time immensely as a Chief of Staff serving a historic Prime Minister who will no doubt transform the country for the better. #Ethiopia
— Fitsum Arega (@fitsumaregaa) November 5, 2018
አቶ ሽመልስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰብአዊ መብት የማስትሬት ዲግሪ፣ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ አፍሪካ (UNISA) ደግሞ በፖለቲካል ፍልስፍና ሁለተኛ የማስተሬት ድግሪ አግኝተዋል።
በተያያዘ ዜና፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ስር የፕሬስ ሴክሬታሪ ጽህፈት ቤት የተቋቋመ ሲሆን ወይዘሮ ቢልለኔ ስዩም ኃላፊ ተደርገው ተሹመዋል። ወይዘሮ እና ቢልለኔ ስዩም ስነ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጸሐፊ/ደራሲ ሲሆኑ፣ የሴቶች መብት ላይ እና በጾታ እኩልነት ላይ የሚሠራ ዕሩያን ሶሉሽንስ (Earuyan Solutions) የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት መሥራችና ኃላፊ ነበሩ። በትምህርታቸውም የማስተርስ ዲግሪ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፒስ-ኮስታሪካ፣ ሌላ የማስተርስ ዲግሪ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኢንስብሩክ (ኦስትርያ) እና የባችለርስ ዲግሪ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ብሪቲሽ ኮለምብያ (ካናዳ) አላቸው።
አዲስ አበባ (የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ) – የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ 34ኛውን እና የዓመቱ የመጀመሪያውን ሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት ምግብ ዋስትና በኢትዮጵያ በተሰኘ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ መስከረም 24 ቀን 2011 ዓ.ም ውይይት አካሄደ።
ገለፃውን ያቀረቡት ዶ/ር ዓለማየሁ ሥዩም (በዓለም አቀፍ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ተቋም (IFPRI) ውስጥ ከፍተኛ ተመራማሪ) ሲሆኑ፣ አቅራቢው በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና እና በምግብ እራስን መቻል መካከል ያለው ብያኔ የተዛነፈ በመሆኑ በምሁራን እና በፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ ወጥ የሆነ አረዳድ እንዳይኖር አድርጓል ብለዋል። ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ማለት በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በአገር፣ በክፍለ-ዓለምና በዓለም ደረጃ፤ ሁሉም ሰዎች፣ ዘወትር፣ በመጠኑ በቂ የሆነ፣ በጤና ላይ አደጋን የማያስከትል እና የተመጣጠነ የአመጋገብ ፍላጎትም ሆነ የአይነት ምርጫ ቁሳዊናኢኮኖሚያዊ ተደራሽነት ሲኖራቸው እንደሆነና ምንም ዓይነት ወቅታዊ መዋዠቅን፣ ያልተጠበቁ ሰው ሠራሽም ሆነ የተፈጥሮ ክስተቶችን (አደጋዎችን) መቋቋም የሚችል ማህበረሰብ ሲፈጠር እንደሆነ አቅራቢው ይገልፃሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ መካከለኛ መጠን ያላቸው ከተሞች በዓመት በአማካይ ከ5-6 በመቶ ዕድገት እያሳዩ መሆኑ እና መንግስት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማዘመን እና ምርታማነትን በመጨመር ገበያ-ተኮር ኢኮኖሚ ለመዘርጋት ጥረት እያደረገ እንደሆነ አብራርተዋል። ነገር ግን ዛሬም የግብርና ምርታማነት በጣም ዝቅተኛ መሆኑ፣ የህፃናት መቀንጨር በአማካይ 38 በመቶ መድረሱ፣ የምግብ እህል እጥረት የሚያጋጥማቸው ዜጎች ቁጥር እጅግ መጨመሩ እና ከፍተኛ የምግብ እህል/ሸቀጥ ከውጪ እንዲገባ መደረጉ “የምግብ ዋስትና ጉዳይ አሁንም እልባት ያላገኘ አገራዊ ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል” ብለዋል ዶ/ር ዓለማየሁ።
ለእንደዚህ ዓይነት የምግብ ዋስትና ስጋት ያጋልጣሉ ያሏቸውንም ምክንያቶች ዶ/ር ዓለማየሁ ዘርዝረዋል። “በገጠር የተወሳሰበ የመሬት ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ ሁኔታ (የይዞታ ባለቤትነትና አጠቃቀም ሥርዓት)፣ የእርሻ መሬት ይዞታ ማነስና መበጣጠስ፣ የመሬት ምርታማነት መቀነስ/የአፈር ለምነት መቀነስ፣ የሥራ ዕድል መጥበብ እና ወጥነት የጎደለው የፖሊሲ አፈፃፀም” ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል ዶ/ር ዓለማየሁ። ችግሩም ህፃናትን ለበሽታና ለሞት እንዲሁም ለአካልና አእምሮ ህመም ከመዳረጉ እና የመማርና የማምረት አቅምን ከማኮሰስ አልፎ ድህነት እንዲቀጥል ያደርጋል ተብሏል።
በሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት መድረኩ ከችግሩም ለመላቀቅና የተሟላ ማህበራዊ ዋስትና ለመፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየቶች ተነስተዋል። በውይይቱም ከፍተኛ የግብርና ማስፋፊያ ተግባራት በማከናወን አርሶ አደሮች የተሻለ መረጃ እንዲያገኙና የተሻሻሉ የግብርና ዘዴዎችን እንዲያላምዱ ማትጋት፤ ዘመናዊ የመሠረተ-ልማት ዝርጋታ ማድረግ፤ በትምህርትና በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በማካሄድ አማካይ በህይወት የመኖሪያ እድሜን ማሳደግ እና የምግብ ዋስትና ተጋላጭነትን እያጠኑ ስልት የሚቀይሱ ጠቃሚ ተቋማትን መፍጠር (የፖሊሲ ተቋማት፣ የንብረት ባለቤትነት መብቶች፣ የገበያ፣ የአምራቾች ማህበራት፣ የማህበራዊ ዋስትና ስልት፣ የቅድመ-ማስጠንቀቂያ ዘዴዎች) ቅድሚያ የሚፈልጉ አገራዊ ተግባራት መሆናቸው ተነስቷል።
ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪም ከ20-25 ዓመት የሚደርስ የግብርናው ዘርፍን ሊያዘምን የሚችል አሠራር በተለይ ደረቅ-አብቃይ አካባቢዎችን፣ ለድርቅ-ተጋላጭቦታዎችን እና የተጎዱ አካባቢዎችን የሚያሻሽል የተቀናጀ መርሐ-ግብር መንደፍ አስፈላጊ እንደሆነ ተሳታፊዎች አንስተዋል። እንደ ህዝብ ቁጥር መጨመርና የአየር ንብረት መለዋወጥ ያሉ አባባሽ ሁኔታዎችንም መቋቋም የሚያስችል የኢኮኖሚ ዝግጁነት መገንባት የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማስጠበቅ ይረዳልም ብለዋል።
በጥቅሉ የገለፃው አቅራቢና ተሳታፊዎች፣ ተቋማት መገንባትና በስፋትና በተፈለገው የህብረተሰብ ፍላጎት ልክ የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግር መፈጠር አለበት በማለት የዕለቱን ውይይት አጠናቀዋል።
ውይይቱን ፕሮፌሰር በላይ ካሳ (የፓን አፍሪካን ዩኒቨርሲቲ ጊዜያዊ ከፍተኛ አመራር) የመሩት ሲሆን፣ ከ110 በላይ የሚሆኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ባለሙያዎች፣ የአካዳሚው አባላትና የሚዲያ አካላት ተሳትፈውበታል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ
በአገሪቱ ከ7 ሺህ 800 በላይ አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች እንደሚቋቋሙ የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።
አዳማ (ኢዜአ)– በመላ አገሪቱ በዚህ አመት ከ7 ሺህ 800 በላይ አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች እንደሚቋቋሙ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ስር የሚገኘው የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ (Federal Small and Medium Manufacturing Industry Development Agency) አስታወቀ።
አዳዲስ ኢንዱስትሪዎቹን ለማቋቋም፣ ነባሮችን ለማጠናከርና በቁሳቁስ ለማደራጀት 14 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ኤጀንሲው አስታውቋል።
የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት የ2010 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ አፈጻጸምን የሚገመግምና በ2011 ዕቅድ ላይ የሚመክር የሁለት ቀን መድረክ ጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓም በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።
በኤጀንሲው የፖሊሲ ዕቅድና ፕሮጀክት ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ገነት አረጋዊ በወቅቱ እንደገለጹት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለሚደረገው መዋቅራዊ ሽግግር አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን መገንባት አስፈልጓል። ነባሮችንም የማጠናከር ሥራ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ነው የገለጹት።
ለእዚህም በበጀት ዓመቱ 7 ሺህ 860 አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን የማቋቋምና 2 ሺህ 924 ነባር ኢንዱስትሪዎች የማጠናከር ሥራ እንደሚከናወን አመልክተዋል።
“አዳዲስ ኢንዱስትሪዎቹን ለማቋቋም፣ ነባሮቹን ለማጠናከርና ለእቃ አቅርቦት የሚያስፈልገው 14 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ለሁሉም ክልሎች፣ ለአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ መስተዳድሮች በብድር ይቀርባል” ብለዋል ወ/ሮ ገነት።
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጥን ፕሬዝደንት አድርጎ መርጧል
አዲስ ከሚቋቋሙት የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች መካከል የብረታ ብረትና እንጨት ሥራ፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያዎች፣ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችና ጌጣ ጌጥ ማምረቻዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ዳይሬክተሯ እንዳሉት በሚቋቋሙት ኢንዲስትሪዎች ከ195 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል። አያይዘውም “ኢንዱስትሪዎቹን ውጤታማ ለማድረግ በሀገር ውስጥ የ2 ቢሊዮን ብርና በውጭ አገራት የ194 ነጠብ 5 ሚሊዮን ዶላር የገበያ ትስስር ይመቻቻል” ብለዋል።
ዘርፉን ለማሳደግ ለባለሀብቶች፣ ለዩኒቨርሲቲ ምሩቃን፣ ለሞዴል አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች እንዲሁም ለሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እንደሚሰጥ ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ በበኩላቸው “የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት የትራንስፎርሜሽኑ መሰረት ስለሆነ በእያንዳንዱ ወረዳ ሊቋቋም ይገባል” ብለዋል።
ባለድርሻ አካላትን በልዩ ትኩረት በመሳተፍ ዕቅዱን እውን ለማድረግ ኤጀንሲው ከሁሉም ክልሎችና ከሁለት የከተማ መስተዳድሮች ጋር ጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓ.ም የስምምነት ሰነድ መፈራረሙንም አቶ አስፋው አመልክተዋል።
የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥና ብልጽግና እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር ያለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዕድገትና ተወዳዳሪነት ሊመጣ ስለማይችል ሁሉም አካላት ለተፈጻሚነቱ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል ።
የቀረበው አመላካች ዕቅድ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ-መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚደረገውን ግብ ለማሳካት ወሳኝ ስለመሆኑ ከመድረኩ ተሳታፊዎች ተገልጿል።
ለኢንዱስትሪው ልማት ማነቆ የሆኑ በሊዝ፣ በብድር ገንዘብና በኤሌክትሪክ አቅርቦት የሚስተዋሉ እጥረቶችና የተንዛዙ አሠራሮች ሊፈቱ እንደሚገባም በተሳታፊዎቹ ጥያቄ ቀርቧል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)
አዲስ ዓለም ከተማ የሞቱት ሁለቱ ተመራማሪዎች ወሰን ታፈረ እና ማንደፍሮ አብዲ የሚባሉ ሲሆን፥ ከባድ የመቁሰል አደጋ የደረሰበት የሜጫ ወረዳ ጤና መኮንን (የላቦራቶሪ ባለሙያ) የሆነው ኃይለየሱስ ሙሉ ይባላል።
አዲስ ዓለም፣ አማራ ክልል – በምዕራብ ጎጃም ዞን ጎንጂ ቆለላ ወረዳ ለምርምር ወደ አዲስ ዓለም ከተማ የሄዱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሶስተኛ (ዶክትሬት) ዲግሪ ተማሪዎች እና የሜጫ ወረዳ ጤና መኮንን በከተማው የሚኖሩ ግለሰቦች ባደረሱባቸው ጥቃት ሁለቱ ህይወታቸው ሲያልፍ፣ አንዱ ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደርሶበታል። ሁለቱ የሞቱት ተመራማሪዎች ወሰን ታፈረ እና ማንደፍሮ አብዲ የሚባሉ ሲሆን፥ ከባድ የመቁሰል አደጋ የደረሰበት የሜጫ ወረዳ ጤና መኮንን (የላቦራቶሪ ባለሙያ) የሆነው ኃይለየሱስ ሙሉ ይባላል።
የዶክትሬት ተማሪዎቹ አዲስ ዓለም ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ለምርምር የሚሆን የሽንትና የዓይነ ምድር ናሙና እየሰበሰቡ ባሉበት ወቅት ከዕለቱ ቀደም ብሎ በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያዎች “ሦስት ተማሪዎች ሞቱ” በሚል በተነዛው ወሬ ተቆጥተው በመጡ የአካባቢው ወጣቶች በደረሰባቸው ከፍተኛ ጥቃት ሕይወታቸው ማለፉን የምዕራብ ጎጃም ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ አንማው ዳኛቸው ለአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ ዝግጅት ክፍል ተናግረዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቢቢሲ አማርኛ የጎንጂ ቆለላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ደመቀ መላኩን ጠቅሶ እንደዘገበው “በተሳሳተ መልኩ ልጆቻችን የጤና ክትባት እየተሰጣቸው ነው፤ እየተመረዙብን ነው፤ ሊገደሉብን ነው” በሚል የተቆጡ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የአካባቢው ግለሰቦች የዶክትሬት ተማሪዎቹ (ተመራማሪዎቹን) ወደነብሩበት የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ሄደዋል። የትምህርት ቤቱ የጥበቃ ሠራተኞች ሁኔታው ከአቅማቸው በለይ ሲሆን በአካባቢው በነበሩ ጥቂት የጽጥታ አስከባሪ አካላት (ፖሊሶች) ታግዘው ተመራማሪዎቹን ወደ ፖሊስ ጣቢያ እየወሰዷቸው ሳለ፥ በከተማው መናኸሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጥቃቱ እንደደረሰባቸው ቢቢሲ አማርኛ ጨምሮ ዘግቧል።
ግለሰቦቹ ያደረሱት ጥቃት በተማራማሪዎቹ ላይ ብቻ ሳይገታ ሁኔታው በፈጠረው ግርግር ለቤተ ክርስቲያን ህንፃ ግንባታ ግልጋሎት የሚውል ሲሚንቶ በራሳቸው መኪና ጭነው ወደ አካባቢው ተጉዘው የነበሩ ጥንዶች ንብረትም መቃጠሉን የአሜሪካ ድምፅ አቶ አንማው ዳኛቸውን ጠቅሶ ዘግቧል። አቶ አንማው ለአሜሪካ ድምፅ አክለው በሰጡት ማብራሪያ በዚህ ድርጊት ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩ 30 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን፣ ብሎም በተፈፀመው ድርጊት የአካባቢው ማኅበረሰብም ሆነ መንግሥት ማዘኑን እና በድርጊቱ ተሳትፈዋል የተባሉትን እየፈለጉ በቁጥጥር ስር የማዋሉ ሥራ መቀጠሉን ጠቁመዋል።
ከቢቢሲ አማርኛ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የጎንጂ ቆለላ ወረዳ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አንተነህ በላይ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በክልሉ ዋና ከተማ ባህር ዳር ውስጥ ለህፃናት ክትባት ሲሰጡ ሞቱ በሚል በተናፈሰ ወሬ ምክንያት መኪና መሰባበር፣ እንዲሁም በአንዳንድ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት (መቁሰል) መድረሱን አስታውሰው አካባቢው ለባህር ዳር ከተማ ቅርብ በመሆኑ ይሄው መረጃ በመናፈሱ ጥቃቱ ሊፈፀም እንደቻለ አስረድተዋል። አቶ አንተነህ አክለው እንደተናገሩ ጥቃቱን ያደረሱት የ አካባቢ ተወላጆች መሆናቸውና አገር ሊጠቅሙ ምሁራን በራሳቸው ወገኖች በመገደላቸው የ አካባቢው ማኅበረሰብ መፀፀቱን፣ በድርጊቱ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን አጋልጦ መስጠት የጀመረውም ራሱ ህብረተሰቡ እንደሆነ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ ዝግጅት ክፍል ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ ከምዕራብ ጎጃም ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ አንማው ዳኛቸው ጋር ያደረገችውን ቃለ ምልልስ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
የአሜሪካ ድምፅ ለባለሞያዎቹ ሥልጠና ሲሰጥ ያገር ውስጥ ጋዜጠኞችንም ቢያካትት ፍላጎታቸው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስልጠና ለመስጠት አዲስ አበባ ከሚገኙ የአሜሪካ ድምጽ ጋዜጠኞች ጋር በተገናኙበት ጊዜ አስታውቀዋል።
አዲስ አበባ – የአሜሪካ ድምፅ ለባለሞያዎቹ ሥልጠና ሲሰጥ ያገር ውስጥ ጋዜጠኞችንም ቢያካትት ፍላጎታቸው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የአሜሪካ ድምፅ የአፍሪካ ዲቪዥን ዳይሬክተር አቶ ንጉሤ መንገሻን እና የአፍሪካ ቀንድ ማኔጂንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ ትዝታ በላቸውን በቢሯቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
የአሜሪካ ድምፅ በኢትዮጵያና በጎረቤት ሃገሮች ለሚገኙ ዘጋቢዎቹ እስካለፈው ዓርብ የቆየ የአንድ ሣምንት ሥልጠና አዲስ አበባ ላይ ሰጥቷል።
በኢሕአዴግ መንግሥትና በአሜሪካ ድምፅ መካከል ላለፉት 27 ዓመታት ከዘለቀ ውጣ ውረድ ያልተለየው ግንኙነት በኋላ አንድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የጣቢያውን ኃላፊዎች ተቀብሎ ሲያነጋግር ይህ የመጀመሪያው ነው።
ለተጨማሪ መረጃ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ። ዘጋቢ እስክንድር ፍሬው ለአሜሪካ ድምጽ የአማርኛ ዝግጅት ክፍል
ጋዜጠኛ ንጉሤ መንገሻ
ትውልደ ኢትዮጵያዊው ንጉሤ መንገሻ ከ2014 (እ.ኤ.አ) ጀምሮ የአሜሪካ ድምጽ የአፍሪካ ዲቪዥን ዳይሬክተር (Africa Division Director) ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ጋዜጠኛ ንጉሤ ወደ አሜሪካ የመጣው እ.ኤ.አ በ1981 ዓም ሲሆን በ1982 የአሜሪካ ድምጽን በሲኒየር ኤዲተርነት ተቀላቅሏል። ቀጠሎም የአሜሪካ ድምጽ የመካከለኛው አፍሪካ ሰርቪስ ቺፍ (Service Chief)፣ የአፍሪካ ዲቪዥን ፕሮግራም ማናጀር (Africa Division Program Manager)፣ አሁን ደግሞ ሆኖ የአፍሪካ ዲቪዥን ዳይሬክተር አገልግሏል/እያገለገለ ይገኛል።ጋዜጠኛ ትዝታ በላቸው
በ ኤሉባቡር ዞን (የቀድሞው ኤሉባቡር ክፍለሀገር) ያዮ ወረዳ ውስጥ የተወለደችው ጋዜጠኛ ትዝታ በላቸው ወደ አሜሪካ የመጣችው እ.ኤ.አ በ1973 ሲሆን፥ ትምህርቷን ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ (Howard University) ተከታትላ የአሜሪካ ድምጽን የተቀላቀለችው የአማርኛ ዝግጅት ክፍሉ በተመሠረተ በሁለት ዓመቱ (እ.ኤ.አ በ1984) ነበር። በአሜሪካ ድምጽ (የአማርኛ ዝግጅት ክፍሉን ጨምሮ) በተለያዩ የጋዜጠኝነት ሙያ እርከኖች ያገለገለች ሲሆን በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ቀንድ ማኔጂንግ ኤዲተር (Horn of Africa Managing Director) ሆና እየሠራች ነው።ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ለ13ኛ ጊዜ በሚያካሂደው ዓመታዊ የኪነ ህንጻ አውደ ርዕይ “ኪነ ህንጻና የከተማ ፕላን” በሚል መሪ ሀሳብ ከጥቅምት 8 ቀን እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓ.ም በብሔራዊ ቲያትር ይካሄዳል።
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በየዓመቱ የሚያካሂደው ዓመታዊ የኪነ ህንጻ አውደ ርዕይ ጥቅምት 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ይጀመራል።
ለ13ኛ ጊዜ በሚካሄደው አውደ ርዕዩ “ኪነ ህንጻና የከተማ ፕላን” በሚል መሪ ሀሳብ በብሔራዊ ቲያትር ይካሄዳል።
የዩኒቨርሲቲው የኪነ ህንጻና የከተማ ፕላን የትምህርት ክፍል ሃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ገብረጻዲቅ ለኢዜአ እንደገለጹት አውደ ርዕዩ የትምህርት ክፍሉ ተማሪዎች የሥራ ውጤቶቻቸውን የሚያቀርቡበት ነው።አውደ ርዕዩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደ ዘርፉ ኢንዱስትሪ ከመቀላቀላቸው በፊት ሥራዎቻቸውን ለኅብረተሰቡ፣ ለመንግስት ተቋማትና ለዘርፉ ባለድርሻ አካላት በማቅረብ ልምድ የሚቀስሙበት እንደሚሆን አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ተማሪዎቹ እርስ በእርስ እንዲማማሩም መልካም አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል።
የተሻለ አቅም ያላቸው ተማሪዎች ወደ ሥራ ዓለም ሲገቡ በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት ከመቅረፍ አንጻር አስተዋጽዖ እንደሚያበረክቱም ነው አቶ ቴዎድሮስ ያስረዱት።
አውደ ርዕዩ በየዓመቱ ሲካሄድ በአማካይ እስከ ሁለት ሺህ ሰው እንደሚጎበኘውና ዘንድሮም ከአንድ ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚጎበኙት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
በአውደ ርዕዩ የዩኒቨርሲቲው የዘንድሮ የትምህርት ክፍሉ 60 ተማሪዎች የሥራ ፕሮጀክቶቻቸውን እንደሚያቀርቡና የተሻለ ሥራ ያቀረቡ ተማሪዎች የኢትዮጵያ የኪነ ህንጻ ባለሙያዎች ማኅበር (Association of Ethiopian Architects) በሚያዘጋጀው ዓመታዊ ውድድር እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል።
በዚህ አውደ ርዕይ ሌሎች የመንግስትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንደሚሳተፉም ተናግረዋል።
በብሔራዊ ቲአትር አዳራሽ የሚካሔደው አውደ ርዕይ ከጥቅምት 8 ቀን እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል።
ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ከሚሰጣቸው የትምህርት ዘርፎች አንዱ “ኪነ ህንጻና የከተማ ፕላን” ሲሆን በዚሁ ትምህርት ዘርፍ ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ (bachelors degree) አስተምሮ ያስመርቃል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአገር ውስጥ ሰላም እና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን በሕዝቡ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ የሰላም ሚኒስቴር እንዲቋቋም ተወስኗል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የሚኒስትሮች ምክር ቤት መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የፌደራል መንግሥትን አስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በተዘጋጀ ረቀቅ አዋጅ ላይ መክሮ እንዲጸድቅ ለተወካዮች ምክር ቤት እንዲላክ ወስኗል።
በውይይቱ ላይ የአስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን ያስፈለገበት ዋና ዋና ምክንያቶች እንደሚከተለው ቀርቧል፦
- የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በቀሪው ጊዜ ያልተጠናቀቁ ሥራዎችን አካክሶ ለመፈጸም የሚያስችል አደረጃጀት በማስፈለጉ፤
- አገራችን የተያያዘችውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠልና የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ለማድረስ የሚያስችል አደረጃጀትን መከተል በማስፈለጉ፤
- የአስፈጻሚ አካላትን ቁጥር ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ ለማድረግ በማስፈለጉ፤
- ተደራራቢና ድግግሞሽ ሥልጣንና ተግባር የያዙ የመንግሥት ተቋማትን መቀነስ ወይም ለሥራቸው ቅርብ ከሆነ ሌላ የመንግሥት ተቋም ጋር እንዲዋሃዱ ማድረግ በማስፈለጉ፤
እንደሆነ በስብሰባው ላይ ተብራርቷል።
በምክር ቤቱም ውሳኔ የካቢኔ አባላት ቁጥር ከ28 ወደ 20 እንዲቀንስ ተደርጓል፤ ዋና ዋናዎቹ ለውጦችም:-
- የንግድ ሚኒስቴር እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተዋህደው – የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲሆን ፤
- በየሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተዋህደው – የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሆን ፤
- የከተማ ልማት ሚኒስቴር እና የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ተዋህደው – የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እንዲሆን
ወስኗል።
ሌሎች ተጠሪ ተቋማትም በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲዋሃዱ ውሳኔ የተሰጠባቸው ይገኛሉ።
ሌላው ቁልፍ ውሳኔ በአገር ውስጥ ሰላም እና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን በሕዝቡ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ የሰላም ሚኒስቴር እንዲቋቋም ተወስኗል።
ከትምህርት ሚንስቴር ሁሉንም ዩኒቨርሲቲዎች እና የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በመውሰድ እንዲሁም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ስር የሚገኙት ሁለቱን ዩኒቨርሲቲዎች በመጨመር “የከፍተኛ ትምህርትና የሳይንስ ሚንስቴር” ተብሎ እንዲደራጅ ተወስኗል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የገቢዎች ሚኒስቴር እና ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጠሪ የሆነ የጉምሩክ ኮሚሽን በመሆን ሁለት ተቋማት ሆነው እንዲደራጁ ተወስኗል።
በአዲሱ አደረጃጀት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚንስቴር ቀርቶ በቀጣይነት የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ለማስተዳደር መሠረታዊ ሚናቸው ንግድ የሆኑትን በመለየት የመንግስትን የባለቤትነት ሚና በተገቢው ሁኔታ የሚያስተዳደር “የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ” በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር እንዲቋቋም ተወስኗል። ይህም የመንግሥት ቁልፍ ሚና የሆነው ቁጥጥር (regulation) በልማት ድርጅቶች ላይ ካለው የባለቤትነት ሚና ተለይቶ እንዲታይ እንደሚያግዝ ታምኖበታል።
ረቂቅ አዋጁ ሌሎች መለስትኛ ለውጦችንም የያዘ ሲሆን፥ በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ የፌስቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአገር ውስጥ ሰላም እና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን በሕዝቡ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ የሰላም ሚኒስቴር እንዲቋቋም ተወስኗል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የሚኒስትሮች ምክር ቤት መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የፌደራል መንግሥትን አስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በተዘጋጀ ረቀቅ አዋጅ ላይ መክሮ እንዲጸድቅ ለተወካዮች ምክር ቤት እንዲላክ ወስኗል።
በውይይቱ ላይ የአስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን ያስፈለገበት ዋና ዋና ምክንያቶች እንደሚከተለው ቀርቧል፦
- የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በቀሪው ጊዜ ያልተጠናቀቁ ሥራዎችን አካክሶ ለመፈጸም የሚያስችል አደረጃጀት በማስፈለጉ፤
- አገራችን የተያያዘችውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠልና የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ለማድረስ የሚያስችል አደረጃጀትን መከተል በማስፈለጉ፤
- የአስፈጻሚ አካላትን ቁጥር ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ ለማድረግ በማስፈለጉ፤
- ተደራራቢና ድግግሞሽ ሥልጣንና ተግባር የያዙ የመንግሥት ተቋማትን መቀነስ ወይም ለሥራቸው ቅርብ ከሆነ ሌላ የመንግሥት ተቋም ጋር እንዲዋሃዱ ማድረግ በማስፈለጉ፤
እንደሆነ በስብሰባው ላይ ተብራርቷል።
በምክር ቤቱም ውሳኔ የካቢኔ አባላት ቁጥር ከ28 ወደ 20 እንዲቀንስ ተደርጓል፤ ዋና ዋናዎቹ ለውጦችም:-
- የንግድ ሚኒስቴር እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተዋህደው – የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲሆን ፤
- በየሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተዋህደው – የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሆን ፤
- የከተማ ልማት ሚኒስቴር እና የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ተዋህደው – የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እንዲሆን
ወስኗል።
ሌሎች ተጠሪ ተቋማትም በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲዋሃዱ ውሳኔ የተሰጠባቸው ይገኛሉ።
ሌላው ቁልፍ ውሳኔ በአገር ውስጥ ሰላም እና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን በሕዝቡ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ የሰላም ሚኒስቴር እንዲቋቋም ተወስኗል።
ከትምህርት ሚንስቴር ሁሉንም ዩኒቨርሲቲዎች እና የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በመውሰድ እንዲሁም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ስር የሚገኙት ሁለቱን ዩኒቨርሲቲዎች በመጨመር “የከፍተኛ ትምህርትና የሳይንስ ሚንስቴር” ተብሎ እንዲደራጅ ተወስኗል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የገቢዎች ሚኒስቴር እና ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጠሪ የሆነ የጉምሩክ ኮሚሽን በመሆን ሁለት ተቋማት ሆነው እንዲደራጁ ተወስኗል።
በአዲሱ አደረጃጀት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚንስቴር ቀርቶ በቀጣይነት የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ለማስተዳደር መሠረታዊ ሚናቸው ንግድ የሆኑትን በመለየት የመንግስትን የባለቤትነት ሚና በተገቢው ሁኔታ የሚያስተዳደር “የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ” በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር እንዲቋቋም ተወስኗል። ይህም የመንግሥት ቁልፍ ሚና የሆነው ቁጥጥር (regulation) በልማት ድርጅቶች ላይ ካለው የባለቤትነት ሚና ተለይቶ እንዲታይ እንደሚያግዝ ታምኖበታል።
ረቂቅ አዋጁ ሌሎች መለስትኛ ለውጦችንም የያዘ ሲሆን፥ በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ የፌስቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።