-
Search Results
-
የወሎ ዩኒቨርሲቲ የሚጀምረው የግዕዝ ቋንቋ ትምህርት በቋንቋው የተጻፉ ሥራዎችን ወደ ሌሎች አገርኛ ቋንቋዎች በመተርጎም ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚያስችል በዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊና ሥነ ሰብእ ኮሌጅ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሁፍ ትምህርት ክፍል ተጠሪ ተናግረዋል።
ደሴ (ኢዜአ) – የወሎ ዩኒቨርሲቲ ከያዝነው የትምህርት ዘመን ጀምሮ የግዕዝ ቋንቋን በመጀመሪያ ዲግሪ ለማስተማር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው ትምህርቱን ለመጀመር በቀረጸው ሥርዓተ ትምህርት (curriculum) ዙሪያ ከምሁራንና ባለድርሻ አካላት ጋር መስከረም 29 ቀን 2011 ዓ.ም ተወያይቷል።
በዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊና ሥነ ሰብእ ኮሌጅ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሁፍ ትምህርት ክፍል ተጠሪ ዶክተር እንድሪስ አብይ እንዳስረዱት ግዕዝ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የላቀ ሥፍራ አለው።
ትምህርቱን ለማስጀመር አራት መምህራን የተቀጠሩ ሲሆን፣ እስከ 18 ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።
ሥርዓተ ትምህርቱ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ አገር በቀል ህክምናና መድኃኒት፣ የሥነ ከዋክብት ቀመርና የቀን አቆጣጠር፣ የባህልና የህግ ሥርዓቶች ተካተውበታል።
ትምህርቱ በቋንቋው የተጻፉ ሥራዎችን ወደ ሌሎች አገርኛ ቋንቋዎች በመተርጎም ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚያስችል ዶክተር እንድሪስ ተናግረዋል።
በቋንቋው በፍልስፍና፣ በህክምና፣ በሥነ ከዋክብትና በመሳሰሉት የዕውቀት ዘርፎች በርካታ ጽሁፎች ቢጻፉም፤ ህዝቡንም ሆነ አገሪቱን መጠቀም የሚገባቸውን ያህል አልተጠቀሙበትም። ዕውቀቱም ለሌሎች ሳይተላለፍ ለረጅም ዓመታት መቆየቱን ተጠሪው ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ትምህርት ክፍል አስተባባሪና መምህር አቶ ዘላለም ጌትነት በበኩላቸው የመጥፋት አደጋ ላይ የሚገኘውንና የዕውቀት ምንጭ የሆነውን ቋንቋ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ መስጠቱ ታሪክን ከማቆየትና እውቀትን ከማጋራት አንጻር ጠቀሜታው ጉልህ ነው ብለዋል።
ሥርዓተ ትምህርቱ በተለይ ቋንቋው ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ያለውን ቁርኝት በሚያሳይ መልኩ ቢቀረጽ የተሻለ እንደሚሆን አመልክተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል መምህርና የሥነ ጥበባት ኮሌጅ የድህረ ምረቃ ተባባሪ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ ወርቁ ”ዩኒቨርሲቲው የአገር ሃብት የሆነውን የግዕዝ ቋንቋ ለማስተማር መወሰኑ የሚያስመሰግነውና ሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ተመሳሳይ ኃላፊነት እንዲወስዱ መነቃቃትን የሚፈጥርላቸው ነው” ብለዋል።
ግዕዝ ኢትዮጵያን የምናውቅበት የዕውቀት ምንጭ መሆኑን አስታውሰው፣ ይህንን መገናኛ ብዙኃን አገራዊ ፋይዳ ያለውን የዕውቀት ዘርፍ በማስተዋወቅ ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የወሎ ዩንቨርሲቲም ተማሪዎችን ካስመረቀ በኋላ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ከባለድርሻ አካላት ጋር መምከር እንዳለበትም አቶ አሰፋ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብ ወሎ አገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ መአምራን ብርሃነሕይወት እውነቱ ቋንቋው በዩኒቨርሲቲው መሰጠቱ በርካታ አገራዊ ታሪኮች፣ ቅርሶች፣ መንፈሳዊና ዓለማዊ ሥራዎች፣ ምርምርን የሚጋብዙ ሥራዎች ለማወቅና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በአዲስ መንፈስ ለማስቀጠል ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።
የአብነት ተማሪዎች እንቅስቃሴ መዳከም ቋንቋውን እንዳዳከመው አውስተው፣ የወሎ ዩንቨርሲቲ የጀመረው ጥረት እንዲሳካ ቤተክርስቲያኗ ድርሻዋን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል።ከዚህ ጋር በተያያዘ በ1999 ዓ.ም. የተመሠረተው የወሎ ዩኒቨርሲቲ ዓመታዊ የቅበላ አቅም ዘንድሮ ከ20 ሺህ በላይ ደርሷል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)
የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምደባን ይፋ ከማድረጉ በፊት ኤጀንሲው የተለያዩ የማጣራት ሥራዎችን በማከናወን ሂደት ውስጥ በመቆየቱ ምክንያት ምደባው ዘገየ በማለት ቅሬታችሁን ስታሰሙ ለነበራችሁ ተማሪዎች እና የተማሪ ቤተሰቦች ከወዲሁ ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን ተማሪዎች በተመደባችሁባቸው የትምህርት ተቋማት በምትሄዱበት ወቅት የነገዋ ኢትዮጵያ በእናንተ ትከሻ ላይ መሆኗን በመገንዘብ በትምህርታችሁ ላይ ብቻ ትኩረት በመስጠት ውጤታማ በመሆን ለሀገራችን እድገት እና ልማት የበኩላችሁን አስተዋጽዖ ታበረክቱ ዘንድ ኤጀንሲው ከአደራ ጋር መልዕክቱን አስተላልፏል።
አዲስ አበባ (ኢዜአ/NEAEA)– የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምደባ ይፋ መሆኑን የሀገር አቀፍ የትምህርት ፈተናና ምዘናዎች ኤጀንሲ (NEAEA) አስታወቀ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ገብረእግዝአብሔር ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት፤ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምደባ ከዛሬ ከመስከረም 25 ቀን 2011 ዓም ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ይፋ ሆኗል።
ምደባው የተማሪዎችን ውጤት፣ የትምህርት ዓይነት፣ የዩንቨርስቲ ምርጫ፣ የዩንቨርስቲዎችን የቅበላ አቅም፣ የወንዶችና የሴቶችን ምጠና ማዕከል ባደረገ እንዲሁም የልዩ ድጋፍ ተጠቃሚዎችን ያገናዘበ መሆኑን ነው ያመላከቱት።
ዓይነ ስውራንን፣ መስማት የተሳናቸውን፣ አካል ጉዳተኞችን/ በተጨማሪም የጤና እክል ያለባቸው እና ከታወቀ የመንግስት ሆስፒታል የሜዲካል ቦርድ ማረጋገጫ ያቀረቡት ላይ የማጣራት ሥራዎችን ካካሄደ በኋላ ምደባው እንደተዘጋጀም እንዲሁ አስታውቀዋል።።
በዚሁ መሰረት በዘንድሮው የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና የማለፊያ ነጥቡን ያለፉ 138 ሺ 283 የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ሲሆኑ 75ሺ 338 የማህበራዊ ሳይንስ በድምሩ 213 ሺ 621 ናቸው።
ከነዚህም መካከል 98 ሺ 576 የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎችና 51 ሺ 229 የማህበራዊ ሳይንስ በድምሩ 149 ሺ 805 ተማሪዎች ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ባሉት የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በአጠቃላይ የሚመደቡ ይሆናል።
◌ RELATED: 35 Best Universities and Colleges Ethiopia (public and private)
ከነዚህም በኤጀንሲው በኩል በ43ቱ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት 95 ሺ 681 የተፈጥሮ ሳይንስ (natural science) እንዲሁም 51ሺ 066 የማህበራዊ ሳይንስ (social science) በድምሩ 146 ሺ 747 ተማሪዎች መመደባቸውን አስታውቀዋል።
ተማሪዎች ወደ ተመደቡበት የትምህርት ተቋማት በሚሄዱበት ወቅትም የነገዋ ኢትዮጵያ በትከሻቸው ላይ መሆኗን በመገንዘብ ለትምህርታችሁ ትኩረት እንዲሰጡም አቶ አርአያ አሳስበዋል።
ከግንቦት 27-30 ቀን 2010 ዓ.ም በተሰጠው የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና (የ12ኛ ክፍል ፈተና) 154,010 ወንዶች እንዲሁም 127,964 ሴቶች በድምሩ 281,974 ተማሪዎች የወሰዱ ሲሆን በሐምሌ 24 ቀን 2010 ዓ.ም ውጤት ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
ተማሪዎች ምደባችሁን በኤጀንሲው ድረ-ገጽ app.neaea.gov.et በመግባት ማየት እንደሚችሉም ነው የገለፁት።
ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና የሀገር አቀፍ የትምህርት ፈተናና ምዘናዎች ኤጀንሲ (NEAEA)
አዲስ አበባ (ኢ.ም.ባ.ኮ)– የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በአፍሪካ (ኢ.ም.ባ.ኮ) ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የባቡር አካዳሚ በቢሾፍቱ ከተማ ለመገንባት በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ ባቡር አካዳሚ ዘርፍ ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብይ ጌታቸው ገለፁ።
ለባቡር አካዳሚው ግንባታ የቻይና መንግስት ሳውዝዌስት ጂአኦቶንግ ዩኒቨርሲቲ (Southwest Jiaotong University) ባካሄደው አማካሪ የአዋጭነት ጥናት መነሻነት የገንዘብ ድጋፍ የፈቀደ መሆኑን የገለፁት አቶ አብይ በተጠናው የአዋጭነት ጥናትና በኮርፖሬሽኑ ፍላጎት መሠረት የትግበራ ስምምነት (Implementation Agreement) እ.ኤ.አ ታህሳስ 19 ቀን 2017 ከቻይና ኤምባሲ የንግድና ኢኮኖሚክ ካውንስለር ቢሮ፤ እንዲሁም የግንባታ ዲዛይን መነሻ ሃሳብ (Scheme design) ጥር 6 ቀን 2018 እ.ኤ.አ ከአማካሪ ድርጅቱ ጋር መፈራረማቸውን ተናግረዋል።
በግንባታው የዲዛይን መነሻ ሃሳብ መሰረትም የግንባታው የመጀመሪያ ዲዛይን (Preliminary Design) ተዘጋጅቶ በአሁኑ ወቅት በቻይና መንግስት በኩል ግንባታውን የሚያከናውን የኮንትራክተር መረጣ ሂደት ላይ መሆኑንና እስከ ቀጣይ ህዳር ወር ድረስ ኮንትራክተሩ ተለይቶ ግንባታው ከታህሳስ አጋማሽ እስከ ጥር ወር መጀመሪያ ባለው ጊዜ ሊጀመር እንደሚችልም አቶ ዓቢይ ገልፀዋል።
ግንባታውን ተቆጣጥሮ በጥራት ከመረከብ በተጨማሪ ግንባታው የሚከናወንበትን ቦታ ማዘጋጀት ከኮርፖሬሽኑ ሃላፊነቶች አንዱ ሲሆን ለአካዳሚው ግንባታ ማስፋፊያውን ጨምሮ ከሚያስፈልገው 157.7 ሄክታር መሬት ውስጥ የ62 ሄክታር መሬት ከኦሮሚያ ክልል የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ እና ከከተማ መሬት ማኔጅመንት ኤጀንሲ ጋር በመነጋገር ከክልሉ መንግስት ህጋዊ ፈቃድ ለማግኘት በሂደት ላይ መሆኑን የገለፁት አቶ ዓቢይ የመሬት ፈቃዱ እንደተገኘ ዲዛይኑ ቀርቦ ግንባታው እንደሚጀመር፤ በተጨማሪም የግንባታ ግብዓቶችን ማምረቻ ሳይቶች ለኮንትራክተሩ ማቅረብ፣ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን (ውሃ፣ መብራት…) ወደ ሳይቱ ማቅረብ የኮርፖሬሽኑ ኃላፊነት መሆኑንና ይህን ተግባር የሚያከናውን ፕሮጀክት ጽ/ቤት ተቋቁሞ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከግንባታው ጋር ተያይዞ ከሥራ ቦታቸው ለሚፈናቀሉ የአካባቢው ማህበረሰበም በካሳ ክፍያ ብቻ የሚተው ሳይሆን በጋራ የሚሠሩ ሥራዎችን በማቅረብ፣ ቴክኒካል ድጋፍ በመስጠትና የበለጠ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበት ፕሮፖዛል በማቅረብ ከክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ጋር በመሆን ህብረተሰቡን ያማከለ የተቀናጀ ልማት ፕሮፖዛል ቀርቧል ያሉት አቶ አቢይ የመሬት ፈቃዱ እንደተገኘ ወደ ሥራ እንገባለን ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ በአካዳሚ ዘርፍ የባቡር አካዳሚ ከማስገንባት ባለፈም የባቡር ዘርፉ የሚፈልገውን የሰው ኃይል ለማብቃት የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ባለሙያዎችን በተለያዩ የትምህርት መስኮች በሃገር ውስጥና በውጭ እያሰለጠ ይገኛል።
በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ከ1ኛ እስከ 4ኛ ዙር ከ400 በላይ የሚሆኑ ባለሙያዎችን በማስተርስ ፕሮግራም ያስተማረ ሲሆን የ1ኛ ዙር ተመራቂዎች ሁሉም በኮርፖሬሽኑ በስራ ላይ እንደሚገኙ የገለፁት አቶ አብይ ከ2ኛ እስከ 4ኛ ዙር የተማሩት ደግሞ ኮርፖሬሽኑ በቀጣይ የሀገራዊ ሴክተሩን አቅም በመገንባት ለሚያከናውነው የራስ ኃይል ሥራዎች በመደራጀት ላይ በሚገኙ ቢዝነስ ዩኒቶች ስር ለስድስት ወር በሥራ ላይ ስልጠና በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ ስልጠናቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ ሥራ የሚገቡ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ምንጭ፦ ኢ.ም.ባ.ኮ
በ2010 ዓ.ም ወደ ከፍትኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ 280 ኤርትራውያን ስደተኞች የመግቢያ ፈተና እንዲወስዱ መደረጉንና በአሁኑ ወቅት ፈተናውን ያለፉ 150 ተማሪዎች መለየታቸውን አስረድተዋል።
አዲስ አበባ (ኢዜአ/UNHCR)፦ በኢትዮጵያ በስደት ላይ ከሚኖሩ ኤርትራውያን መካከል 150 ተማሪዎች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብተው የመማር ዕድል እንደሚያገኙ በኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር አስታወቀ።
በተያዘው ዓመት ሌሎች ቁጥራቸው ከ11ሺህ በላይ የሆኑ ህጻናት (የስደተኛ ኤርትራውያን ልጆች የሆኑ) የቅድመ መደበኛ ትምህርት ዕድል ማግኘታቸውም ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር (Ethiopia Administration for Refugee and Returnee Affairs/ ARRA) የሰሜን ጽህፈት ቤት የትምህርት ኦፊሰር አቶ ኤፍሬም ሀጎስ ለኢዜአ እንደገለጹት ከ180 ሺህ የሚበልጡ ኤርትራውያን ስደተኞች በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ ኤርትራውያን ስደተኞች መካከል 150 ተማሪዎች ዘንድሮ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በነጻ ለመማር እድል እንደሚሰጣቸውም ተናግረዋል።
ወደ ከፍትኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ 280 ስደተኞች የመግቢያ ፈተና እንዲወስዱ መደረጉንና በአሁኑ ወቅት ፈተናውን ያለፉ 150 ተማሪዎች መለየታቸውን አስረድተዋል።
ፈተናውን ያለፉ 150 ስደተኞችም በተለያዩ የኢትዮጵያ መንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉም ነው አቶ ኤፍሬም የገለጹት።
ኤርትራውያን ስደተኛ ተማሪዎች በኢትዮጵያ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መደረጉ በሁለቱ አገራት መካከል አሁን የተጀመረውን ሰላማዊ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረውም ተናግረዋል።
◌ ቪድዮ፦ ኢትዮጵያ የቀይ ባህር እና የምጽዋ ወደቦችን ለመጠቀም ቅድመ ዝግጅቶችን እያጠናቀቀች ነው
የኢትዮጵያ መንግስት ለኤርትራውያን ስደተኞች የትምህርት ዕድል ሲሰጥ የአሁኑ ለሰባተኛ ጊዜ ሲሆን በየዓመቱ ከ100 ያላነሱ ተማሪዎችም የዕድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል።
በተመሳሳይ በትግራይ ክልል በሚገኙ አራት የኤርትራውያን ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ 11ሺህ 87 ኤርትራውያን በቅድመና በመደባኛ ትምህርት እንዲሁም በሙያ ክህሎት ማበልጸጊያ እንዲማሩ መደረጉን አቶ ኤፍሬም አክለው ተናግረዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ከአገራቸው ተሰደው ወደኢትዮጵያ ቢመጡም ልጆቻው እዚህ የትምህርት ዕድል በማግኘታቸው መደበኛ ትምህርታቸውን መቀጠላቸውን የተናገሩት ደግሞ በማይዓይኒ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙት አቶ ተስፋልደት ይህደጎ የተባሉ ስደተኛ ናቸው።
በአዲ ሓሩሽ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ሌላው ስደተኛዋ ወይዘሮ ለምለም ዘካሪያስ እንደተናገሩት በአካባቢያችን የሚገኙ ትምህርትቤቶች ለኤርትራውያን ተማሪዎች በራቸው ክፍት መሆኑ ትልቅ እድል መሆኑን ገልጸዋል።
“ልጆቻቸው ከኢትዮጵያውያን ወንደሞቻቸው ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ እንዲማሩ መደረጉ በሁለቱ አገራት ህዝቦች መካከል ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት የላቀ አስተዋፅኦ አለው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለኤርትራውያን ስደተኞች እየሰጠ ያለው የከፍተኛ የትምህርት እድል ለሌሎች አገራት በመልካም አርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለማግባት የመግቢያ ፈተና የወሰደው ተማሪ ዓንዶም ፍሳሃየ ነው።
እስከ ግንቦት ወር 2010 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በአጠቃላይ 71,833 ኤርትራውያን ስደተኞች ትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙ አራት መጠለያ ጣብያዎችና አፋር ክልል ውስጥ በሚገኙ ሁለት መጠለያ ጣብያዎች ውስጥ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) ዘግቧል።
ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR)