Search Results for 'አዲስ አበባ'

Home Forums Search Search Results for 'አዲስ አበባ'

Viewing 15 results - 151 through 165 (of 495 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳይ የተሰጠ መግለጫ ― በድር ኢትዮጵያ

    ለረጅም ዘመናት በታሪክ እንደምንረዳዉ በኢትዮጵያ ሕብረተሰቡ በጥሩ ማኅበራዊ ሁኔታ በመቀራረብ፣ በመተሳሰብ፣ በመቻቻል እና በመሳሰሉ ሁኔታዎች ተሳስሮ በጋራ ይኖር እንደነበር በሰፊዉ ሲተረክ ይታወሳል። ይኸዉ ማኅበራዊ ኑሮአቸዉንም ሀይማኖት፣ ዘር፣ ቋንቋ፣ አካባቢና መሰል ጉዳዮች ሳይገድባቸዉ ሕዝቦች አንድነታቸዉን ጠብቀዉ ኖረዋል፤ ምንም እንኳን በነበሩ መንግሥታት በኩል ይደረጉ የነበሩ ልዩነቶች፣ ጫናዎች፣ ጭቆናዎች እንደተጠበቁ ሆነዉ ማለታችን ነዉ።

    ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን የተለያዩ የልዩነት ክስተቶች ቢንጸባረቁም ሕዝቡ ግን ችግሮቹን ወደ ጎን በማድረግ ከሀይማኖት ዉጭ እንዲሆኑ ትግል ሲያደርግ ቢቆይም፥ በአሁኑ ወቅት ግን ይዘቱን ቀይሮ የመጣዉ ለችግሮች ሁሉ መነሻዉ ሀይማኖት እንደሆነ የሚዘምሩ አካላት እየተበራከቱ ይገኛል።

    የታዋቂዉ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ በግፍ መገደልን ተከትሎ በሀገሪቱ በተከሰተዉ አለመግባባትና ብጥብጥ የበርካታ ንጹሀን ዜጎች ህይወት እጅግ አሰቃቂ በሆነ መልኩ አልፏል። ለሟቾች ነብስ ይማር እያልን ለቤተሰቦቻቸዉና ለመላዉ ኢትዮጵያዉያን መጽናናትን እንመኛለን። በሌላ መልኩ ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸዉ ንጹሀን ዜጎች እንዲሁም የወደመዉ የሀገር ንብረት ቁጥሩ እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር የጉዳዩ አስከፊነት ስፋቱን ይጠቁማል።

    መንግሥት ባለበት ሀገር እንደዚህ አይነት ልቅ የሆነ ሥርዓተ-አልበኝነት ሲፈጠር መንግሥት አለን? ያስብላል። መንግሥት ሆይ የታሰሩ አካላት ፈጣን ፍትህ እንዲያገኙና መፈታት ያለባቸዉ አካላትም ያለምንም መጉላላት በሕግ የበላይነት መፍትሄ ሊቸራቸዉ ይገባልም እያልን፥ በሌላ መልኩም የጥላቻ ንግግር የሚያስተጋቡ አካላትን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ የማስቆም ኃላፊነቱን እንዲወጣ አደራ እንላለን።

    ችግሩ የተከሰተበትን መንስኤ በማጥናት መፍትሄ መሻት ሲገባ፥ አንዳንድ የግል ዓላማ ያላቸውና እስላም-ጠል የሆኑ ጽንፈኛ አካላት የጉዳዩን አቅጣጫ ለማስቀየር የተለያዩ የዜና ማሰራጫ ዘዴዎችን በመጠቀም ጸረ-ሰላም ብሎም ጸረ-ኢስላም የሆነ ፕሮፓጋንዳቸዉን በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ። በእምነት ተቃርኖ የማያዉቀዉ የሀገራችን አማኞች በእምነታቸዉ ከተመጣባቸዉ ሁሌም ቢሆን ወደ ኋላ የማይሉ እንደሆነ ስለሚያዉቁ በሌሎች ነገሮች ሁሉ ሞክረዉ አልሳካ ቢላቸዉ መጨረሻ ላይ ሕዝቡን በእምነት ለማጋጨት ሌት ተቀን እየዳከሩ ይገኛሉ።

    በድር ኢትዮጵያ የማንኛዉም ቤተ-እምነት ወይም ተቋም ሲደፈር በጽኑ ተቃዉሞዉን ያሰማል። የእምነት ተቋማት ሊከበሩ ስለሚገባም ጭምር ነዉ። አንዱ ተቋም ከአንዱ አይበልጥም፤ የትኛዉም ተቋም ከማንኛዉም አያንስም፤ በእምነት ተቋምነታቸዉ ሁሉም እኩል ናቸዉ። ይህንን መገንዘብ የተሳናቸዉ የጽንፍ አራማጆች ግን በእምነቶች መካከል ጣልቃ በመግባት እኔ አዉቅልሀለሁ አባዜያቸዉን በመንዛት ሙስሊሙን ማኅበረሰብ ለማሸማቀቅ በሚያስችል ደረጃ የችግሩ አካል ለማድረግ ብዙ ለፍተዋል፤ ሆኖም ግን አይሳካላቸዉም። ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የማንም አካል ተቀጥላ ሆኖም አያዉቅም፤ መብቱን ለማስከበር ደግሞ ማንም ሊነግረዉ አይችልም፤ በቂ ተሞክሮም አለዉ።

    በሀገሪቱ የመጣዉን አንጻራዊ ለዉጥ ያልተዋጠላቸዉ ለዉጡን  ለመቀልበስና ዳግም ላይመለስ ያከተመዉን የአጼዎችን ስርዓት ለማንገስ ለሚድሁ ያለን ምክረ-ሀሳብ ሀገራችን በተያያዘችዉ የለዉጥ ጎዳና የሚያራምዳት እንጂ ለነዉጥ የሚዳርጋትን ስለማትሻ ከእኩይ ተግባራችሁ እንድትቆጠቡ እያልን የሰላም ሰባኪ በመምሰል በሕዝቡ መካከል አሉባልታ የሚነዙና ጽንፈኝነትን የሚያራምዱ አካላት ከሚያስቡት ባልታሰበ መልኩ በተቃራኒዉ ብዙ አላስፈላጊ ዋጋ ሊያስከፍላቸዉ ይችላልና ለሀገሪቱ ሉዓላዊነት ለሕዝቦቿ አንድነት እንዲሁም ለሰላም ሲባል ቆም ብላችሁ እንድታስቡ መልካም መሆኑን ለመጠቆም እንወዳለን።

    በአማራ ክልል በሞጣ የሚገኙ አራት መስጂዶችን አቃጥሎ የሙስሊም ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በመለየት በማዉደምና ንብረታቸዉን በመዝረፍ እሳት እየሞቁ ይጨፍሩ የነበሩትን የሥነ ምግባር ሞራል የጎደላቸዉን ኢስላም-ጠል ጽንፈኞችን ለመገሰጽ እንኳ የሞራል ብቃት ያጡ አካላት አሁን በሀገሪቱ በተከሰተዉ ብጥብጥ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በሞተበትና ንብረቱ የወደመበት ሆኖ ሳለ የግል ድብቅ አጀንዳቸዉን ለማሳካት በበሬ ወለደ ትርክታቸዉ የእምነት ጥቃት አድርጎ ክፍፍልን መዝራት ፍጹም ተቀባይነት የሌለዉ እኩይ ተግባር ነዉ።

    ስለዚህ እየተካሄደ ያለዉ አላስፈላጊ ቅስቀሳ ሕዝቡን ከማበጣበጥ፣ ሀገር ከማፈራረስ እና በሕዝቦች መካከል ሊፈታ የማይችል ጠባሳ ከማኖር ውጭ እንደ ሀገር እና ሕዝብ የማያስተሳስር ለሰላምና ፍትህ ያልቆመ መሆኑ ብቻ ሳይሆን እንደ እምነትም ቢሆን በየትኛዉም የእምነት አስተምህሮት የማይደገፍ አጸያፊ ተግባር መሆኑን በመረዳት ሁሉም ሊገነዘበዉ የሚገባና ማንኛዉም አካል  ከዚህ መሰል ሂደት ጥፋትን እንጂ ትርፋማነትን ማሰብ እንደማይገባ በቅጡ መገንዘብ ያሻል።

    በመጨረሻም ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ የምናስተላልፈዉ መልእክት ኢስላም ሰላም እንደመሆኑ መጠን፥ ለሰላም መከፈል የሚገባዉ ዋጋም እንደተጠበቀ ሆኖ፥ በሁለንተናዊ መልኩ ተጠናክሮ መገኘት እና በጽንፈኞች ለሚሰነዘሩብን የዉሸት ፕሮፓጋንዳ ለኛ አዲስ ባለመሆኑ ትኩረት ባለመስጠት የሚቃጣብንን በጥበብ፣ በሰከነ መንፈስ እንደ ሀገር በማሰብ የመመከት ኃይል ማዳበር ለሰላም ዘብ መቆም ግድ ይላል እንላለን።

    ሀገራችንን ፈጣሪ  አላህ (ሱ.ወ) በሰላም ይጠብቅልን።

    በድር ኢትዮጵያ
    ሰሜን አሜሪካ
    24 ጁላይ 2020

    በድር ኢትዮጵያ

    Semonegna
    Keymaster

    ከ200 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ እየተገነባ ያለው መርካቶ የአውቶቡስ ተርሚናል እየተጠናቀቀ ነው

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ከ200 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ እየተገነባ ያለው መርካቶ የአውቶቡስ ተርሚናል በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሥራ እንደሚጀምር የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ። በቀጣዩ ዓመት ተጨማሪ 3 ሺህ የከተማ አውቶቡሶችን ለማሰማራት የግዥ ሂደት ላይ መሆኑንም የትራንስፖርት ቢሮው አክሎ አስታውቋል።

    በቢሮው የፕሮጀክቱ አስተባባሪ መሀንዲስ ኢ/ር ናትናኤል ጫላ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደጠቆሙት፥ መንግሥት በመደበው ከፍተኛ በጀት መርካቶ የአውቶቡስ ተርሚናል ግንባታው ከነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በመከናወን ላይ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት ግንባታው ከ87 በመቶ በላይ መድረሱንም ኢ/ር ናትናኤል አመልክተዋል።

    በዘመናዊ መልኩ እየተገነባ ያለው መርካቶ የአውቶቡስ ተርሚናል የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ያሉት መሆኑንም ኢ/ር ናትናኤል ጨምረው ጠቅሰዋል። ከነዚሁ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት መካከል ዘመናዊ የትኬት መቁረጫ፣ የደህንነት መቆጣጠሪያ፣ የተገልጋይ ማረፊያ፣ ለአቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች አገልግሎት የሚውል ዘመናዊ አሳንሰር፣ የመረጃ ማዕከልእና የተገልጋይ መጸዳጃ ቤቶች ይገኙበታል።

    በመሀል ገበያ 4 ሺህ ካሬ ስፋት ባለው ቦታ ላይ የሚገነባው የአውቶቡስ ተርሚናል ባለ ሁለት ወለል ከፍታ ያለው መሆኑን ኢ/ር ናትናኤል አስረድተዋል። በአፍሪካ ትልቁ ክፍት የገበያ ማዕከል በሆነው መርካቶ በአንድ ቀን ብቻ ከ50,000 እስከ 80,000 ገበያተኛ ሕዝብ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግበት የሚገመት ሲሆን የአውቶቡስ ተርሚናሉ በዚህ የገበያ ማዕከል አቅራቢያ መገንባቱ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል።

    በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባብሪያ ጽሕፈት ቤት በከተማዋ ውስጥ አራት (ማለትም፥ መርካቶ፣ ፒያሳ፣ ሰሚት እና መገናኛ አካባቢዎች) ዘመናዊ የአውቶቡስ ተርሚናሎችን ለመገንባት ከ2008 ዓም ጀምሮ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል።

    ከሚገነቡት ተርሚናሎች ውስጥ አስተዳደሩ በ2013 ዓ.ም በመገናኛ አካባቢ ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ አንድ ዘመናዊ የብዙኃን ትራንስፖርት ተርሚናል ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ኢ/ር ናትናኤል ጠቁመዋል። ይህ የአውቶቡስ ተርሚናል ተገንብቶ ሲጠናቀቅዘመናዊ ተርሚናሉ የአንበሳ አውቶቡስ፣ ሸገር ባስንና ታክሲዎችን ጨምሮ የተለያዩ የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎቶችን በማጣመር በአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የሚያደርግ መሆኑንም አስረድተዋል።

    ኢ/ር ናትናኤል እንዳሉት የመገናኛው የአውቶቡስ ተርሚናል በአንድ ሄክታር ቦታ ላይ የሚገነና እና ባለስምንት ወለል ሲሆን አራቱ ወለሎች የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥበት ነው። በተጨማሪም የፈጣን አውቶቡስ፣ የታክሲ እና የቀላል ባቡር አገልግሎቶች በጣምራ የሚሰጥበት መሆኑንም አብራርተዋል።

    ፕሮጀክቱ ለእግረኞች አገልግሎት የሚውል አንድ ዘመናዊ ድልድይና 200 መኪኖችን በአንድ ቦታ ለማስቆም በሚያስችል የመኪና ማቆሚያ ቦታ (ፓርኪንግ) እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።

    የብዙኃን ትራንስፖርትን ለማሻሻል በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የጠቀሱት ኢንጅነር ናትናኤል፥ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን የፈጣን አውቶቡስ አገልግሎት ግንባታን ለአብነት ጠቅሰዋል።

    ከእነዚህ ሥራዎች ጎን ለጎን በከተማዋ አሁን በሥራ ላይ ያሉትን 1 ሺህ የከተማ አውቶቡሶች ቁጥር ለማሳደግ በቀጣዩ ዓመት 3 ሺህ አውቶቡሶችን ግዥ ለመፈጸም እተሠራ መሆኑንም ኢ/ር ናትናኤል ጨምረው ገልጸዋል።

    ምንጭ፦ ኢዜአ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    መርካቶ የአውቶቡስ ተርሚናል

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ከ10,900 በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ

    አዲስ አበባ/ ጎንደር (ሰሞነኛ) – አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎችና መርሃግብሮች ያስተማራቸውን ተማሪዎች ሐምሌ 18፣ 2012 ቀን አስመርቋል።

    ዩኒቨርሲቲው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ በክብር እንግድነት በተገኙበት 5,642 ተማሪዎችን በቨርቹዋል አስመርቋል። ፕሬዝዳንቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ (COVID-19) ምክንያት ምርቃቱን በተንጣለለ አዳራሽ ማከናወን ባይቻልም ተመራቂ ተማሪዎች ትምህርታችሁን በማጠናቀቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

    ተመራቂዎች ቀጣዩ የሕይወት ምዕራፍ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት፣ ለሕዝብ እና ለሀገር ለውጥ ለማምጣት የሚተጉበት መሆኑን አመላክተው ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ እንዲከላከሉና ጥንቃቄ እንዳያጓድሉ እንዲሁም ችግር ፈቺ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ አሳስበዋል።

    የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና ዩኒቨርሲቲው ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 2,270 የሚሆኑት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የገፅ-ለገፅ ትምህርት (in-class and face-to-face education) ከመቋረጡ በፊት ጥናታቸውን ያቀረቡ ሲሆን 3,372 ተማሪዎች ደግሞ በትምህርት ዓመቱ መጨረሻ ማቅረባቸውን ገልፀዋል።

    ተመራቂዎቹ ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትና ወደሀገራችን መግባት በፊት በገፅ-ለገፅ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች፣ እና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የገፅ-ለገፅ ትምህርት ከተቋረጠ በኃላ በኦንላይን (online) ያስተማራቸው የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ናቸው።

    የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በዩኒቨርሲቲው 6 ኪሎ ግቢ ራስ መኮንን አዳራሽ የተከናወነ ሲሆን፥ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቀጥታ በማስተላለፍ ተመራቂ ተማሪዎች ከቤታቸው ሆነው በሥነ ሥርዓቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ መመቻቸቱ ተገልጿል።

    ቀደም ብሎ ከሁለት ሳምንታት በፊት (ሐምሌ 4 ቀን 2012 ዓ.ም.) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በዩኒቨርሲቲው የሳይንስ አምባ መሰብሰቢያ አዳራሽ 5,315 ተማሪዎችን አስመርቋል። ከተመራቂዎቹ መካከል ቀደም ብለው ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ለመመረቅ እየተጠባበቁ የነበሩ እንዲሁም ኤክስተርንሽፕ እና ፕሮጀክት ላይ የነበሩ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችና በኦንላይን ትምህርታቸውን የተከታተሉ የሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ይገኙበታል። ተመራቂዎቹ በየቤታቸው ሆነው የምረቃ ሥነ ሥርዓቱን በአማራ ቴሌቪዥን እንዲሳተፉ መደረጉን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን ገልፀዋል።

    የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተመራቂ ተማሪዎችን እንኳን ደስ አላችሁ እያለ የአገራችንና ሕዝባችንን ኑሮ የሚያሻሽሉ፣ ለወገን ፍቅር የሚሰጡ፣ ከድህነት የሚያላቅቁና ወደ ብልፅግና የሚያሻግሩ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ መልዕክቱን አስተላልፏል።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ

    Anonymous
    Inactive

    ሂሩት ክፍሌ ማን ናቸው?

    አዲስ አበባ (ኢዜማ) – ሂሩት ክፍሌ በ1967 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ ነው የተወለዱት። ትውልዳችው ጎንደር ቢሆንም እድገታቸው ግን በአዲስ አበባ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ከተማ በቀድሞ እቴጌ መነን የአሁኑ የካቲት 12 ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።

    ሂሩት የፖለቲካ ተሳትፎ አሀዱ ብለው የጀመሩት በአስራት ወልደየስ (ፕሮፌሰር) አማካኝነት በተመሠረተው የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአህድ) መሥራች አባል በመሆን ነበር። ይህ የፖለቲካ ተሳፏቸው መአህድ ወደ መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ከተለወጠ በኋላ የቀጠለ ሲሆን መኢአድ ቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ (ቅንጅት) ጋር ከተጣመረ በኋላ በቅንጅት ውስጥም በአባልነት ተሳትፎ አድርገዋል። በ1998 ዓ.ም. የቅንጅቱ አመራሮች ወደ ወህኒ ሲጋዙ ከቅንጅት አመራሮች ጋር ወደ ወህኒ ከወረዱት አባላት መካከል አንዷ የነበሩ ሲሆን ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ›› የሚል ክስ ቀርቦባቸው 18 ዓመት ተፈርዶባቸው ነበር። ሁለት ዓመት ለተጠጋ ጊዜ ከሌሎች የቅንጅት አመራር እና አባላት ጋር ከታሰሩ በኋላ ‹‹በምኅረት›› በሚል በ2000 ዓ.ም. የአዲስ ዓመት ዋዜማ ከእስር ተለቀው ነበር። ከቅንጅቱ እስር ከተለቀቁ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በ2003 ዓ.ም. በድጋሚ በእነ ኤልያስ ክፍሌ መዝገብ ‹‹በሽብር›› ተከሰው 19 ዓመታት ተፈርዶባቸው ነበር። በዚህ ክስ 6 ዓመታት ከታሰሩ በኋላም በ2009 ዓ.ም. ከእስር ‹‹በምኅረት›› ሊለቀቁ ችለው ነበር።

    ሂሩት ከእስር ከተለቀቁ በኋላ በ2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሲመሠረት መሥራች አባል ከመሆናቸውም በተጨማሪ የፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የሙያ ማኅበራት ተጠሪ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።

    ሂሩት ክፍሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ፣ ለውጥ እንዲመጣና አምባገነኑ የህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ከፌደራል መንግሥትነት ሥልጣኑ እንዲወገድ ከፍተኛ ዋጋ ከከፈሉ ዜጎች መካከል በግምባር ቀደምነት የሚነሱ ኢትዮጵያዊት ናቸው። እጅግ በጣም ጥቂት እንስቶች በሚሳተፉበት የኢትዮጵያ ተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ በመሳተፍም የፅናት ምሳሌ የሆኑ ዜጋ ናቸው። በሥልጣን ላይ የነበረው የህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝም ለሁለት ጊዜያት ያህል አስሯቸው በድምሩ ለ9 ዓመታት በፖለቲካ እስረኝነት አሳልፈዋል። ለውጥ መጣ በሚባልበት ጊዜም የበኩሌን አስተዋፅኦ ልወጣ በማለት ኢዜማን በመመሥረት ፓርቲውን በከፍተኛ ኃላፊነት እያገለገሉ ይገኛሉ።

    መረጃ ― የመሥራች አባል ሂሩት ክፍሌ መታሰር እና አሁን ያሉበት ሁኔታ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሥራ አስፈጻሚ አባል እና የሙያ ማኅበራት ተጠሪ ሂሩት ክፍሌ ማክሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ከመኖሪያ ቤታቸው በፖሊስ ተወስደው መታሰራቸው ይታወሳል። በተመሳሳይ ቀን ፖሊስ የፍርድቤት ማዘዣ በመያዝ መኖሪያ ቤታቸውን የፈተሸ ሲሆን ሦስት የተንቀሳቃሽ ስልክ ቀፎዎች፣ ልጃቸው የሚገለገልበት ከሚሠራበት ድርጅት የተሰጠው ላፕቶፕ ኮምፒውተር እና የቤተሰብ ዝግጅት የተቀዳበት የቪዲዮ ካሴት ከመኖሪያ ቤታቸው ተወስዷል።

    ሐምሌ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሰዓት የኢዜማ ጠበቃ ሂሩትን አግኝተው የተያዙበትን ሁኔታ እና የተጠረጠሩበት ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል። ሐሙስ ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ከጠበቃቸው ጋር የቀረቡ ሲሆን ፖሊስ «ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ ሁከት እንዲነሳ አስተባብረዋል» ብዬ ጠርጥሬያቸዋለሁ ብሏል። ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ 14 ቀን ጠይቆ የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ 10 ቀን ፈቅዷል። ፍርድ ቤቱ በቤተሰብ የመጎብኘት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲከበር ሂሩት ያቀረቡትን አቤቱታ ተንተርሶ በቤተሰብ እንዲጎበኙ እንዲሁም አልባሳት እና ምግብ እንዲገባላቸው ለፖሊስ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። ፖሊስ ትዕዛዙን እስከ አርብ ሐምሌ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሰዓት ድረስ ሳያከብር የቆየ ቢሆንም ከአርብ ከሰዓት በኋላ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ በመቀበል ለሂሩት አልባሳት እና ምግብ እንዲገባላቸው ፈቅዷል።

    ኢዜማ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ያሉት የሥራ አስፈጻሚ አባል ሂሩት ክፍሌ እና ሌሎችም ዜጎች በሕገ መንግሥት እውቅና የተሰጠው የሰብዓዊ እና የተያዙ ዜጎች መብቶቻቸው ምንም ሳይሸራረፍ እንዲከበርላቸው እና የተፋጠነ ፍትህ እንዲያገኙ ባሳለፍነው ሳምንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ማሳሰቡ ይታወሳል።

    ምንጭ፦ ኢዜማ

    ሂሩት ክፍሌ

    Anonymous
    Inactive

    በኦሮሚያ ክልል፣ አዲስ አበባ፣ ሐረር እና ድሬ ዳዋ ከተሞች በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. የተፈጸመውን ፍጅት ለመጣራት መረጃ ለመሰብሰብ የተላለፈ ጥሪ

    ሰላም ኢትዮጵያውያን ወገኖች፥

    በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመሠረተው የኢትዮጵያውያን ለሰላም፣ ለፍትህና፣ ለአንድነት ኔትወርክ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የሕግ ባለሞያዎች ቡድን የራሱን መግለጫ እንደሚያወጣ በገለጸው መሠረት፥ የሕግ ባለሞያዎች የሚገኙበት ቡድን በኦሮሚያ ክልል፣ አዲስ አበባ፣ ሐረር እና ድሬ ዳዋ ከተሞች በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. የተፈጸመውን ፍጅት ለመጣራት መረጃ ለመሰብሰብ የተላለፈ ጥሪ እቅርቧል። ይህን ጥሪ ሀገር ቤት ለሚገኙ ወገኖች በማስተላለፍ ሁሉም ዜጎች እንዲተባበሩ ጥሪውን ያስተላልፋል።

    በኦሮሚያ ክልል፣ አዲስ አበባ፣ ሐረር እና ድሬ ዳዋ ከተሞች በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. የተፈጸመውን ፍጅት
    ለመጣራት መረጃ ለመሰብሰብ የተላለፈ ጥሪ

    በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. የተፈጸመውን የሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል፣ አዲስ አበባ፣ ሐረር እና ድሬ ዳዋ ከተሞች ሰፊ ተቃውሞ መቀስቀሱ ይታወሳል። እነዚህ ተቃውሞዎች በአብዛኛው በታዋቂው የባህልና የፖለቲካ ትግል ፋና ወጊ በነበረው ሃጫሉ ግድያ የሕብረተሰቡን ድንጋጤ ያንጸባረቁና ሰላማዊ ነበሩ። ሆኖም በተወሰኑ አካባቢዎች፣ የተወሰኑ ቡድኖች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የኃይል እርምጃ ወስደዋል። በዚህ እርምጃም የተወሰኑ የብሔርና የሃይማኖት ቡድን አባላት እና ጎረቤቶቻቸውን ለማዳን የተንቀሳቀሱ ንጹሃን የኦሮሞ ተወላጆች ላይ የሕይወት መጥፋት፣ አካል መጉደልና ንብረት ውድመት ደርሷል። የተለያዩ የዜና ማስራጫ ዘገባዎች እንድሚያስረዱት የኃይል እርምጃው በድንገት በተወሰኑ ቦታዎች ብቻ የተፈጸሙ እርምጃዎች አለመሆናቸውን ነው። ጥቃቶቹ በመረጃ፣ በሰው ኃይልና በገንዘብ በቂ ዝግጅት ተደርጎባቸው በእቅድ፣ በመዋቅርና በሰፊው በኦሮሚያ ክልል ነዋሪ በሆኑ የተወሰኑ የብሔርና የሃይማኖት ቡድኖች አባላት ላይ ያነጣጠሩ ይመስላሉ። የእነዚህ ጥቃቶች እጅግ አሳሳቢ የሚያደርጋቸው ነገር ውሰጥ አንዱ በመንግሥት የጸጥታ ኃይልና አስተዳደራዊ መዋቅር ድጋፍ የተፈጸሙ መሆናቸው ነው።

    ስለሆነም የእነዚህ ጥቃቶች ሁኔታና ያደረሱት የጉዳት ዓይነትና መጠን እውነቱ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ነው። እንደዚህ ያለ ፍጅት እንዳይደገም እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል። በዚህ ድርጊት የተሳተፈ ወይም ድርጊቱ እንዲፈጸም ያደራጀ፣ የቀሰቀሰ፣ በገንዘብ የደገፈ ማንኛውም ሰው ተጠያቂ መሆን ይኖርበታል። በወንጀሎቹ ጉዳት ደረሰባቸውን ወገኖች የፍትሕ ጥያቄ በከንቱ እንዳይቀር ወንጀለኞቹን ተጠያቂ ማድረግ፤ እንዲሁም ተጎጂዎቹን መልሶ ለማቋቋም አስፈላጊ ነው።

    እውነትን የማግኝትና ፍትሕን የማረጋገጥ ጉዳይ ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም። እነዚህን አሰቃቂ ወንጀሎችን የመመርመርና የመሰነድ ሥራ ሙያዊና ተዓማኝነት ባለው መለኩ መከናወን አስፈላጊነቱ የሚያጠያይቅ አይደለም።

    እነዚህን ጉዳዮች ከግምት በማስገባት፥ በሰሜን አሜሪካ በጥብቅና (ሕግ) ሙያ በተሰማሩ ባለሙያዎች የሚመራ የበጎ ፋቃደኞች ቡድን የሰኔውን ጥፋቶች (ፍጅት) በሚመለከት መረጃ በማሰባሰብ የተሟላ ሪፖርት ለማዘጋጀት ተቋቁሟል። ይህ ሪፖርት ለወንጀሎቹ ተጠያቂ የሆኑ ሰዎች፣ ቡድኖች ተቋማት ከፍትህ እንዳያመልጡ ለሚደረገው ጥረት ይረዳል።

    የዚህ ቡድን አባላት ከማንኛውም ድርጅት ጋር ንክኪ ያለን አለመሆኑን እየገለጽን፥ የዓላማችን ደጋፊ ከሆኑ ግለሰቦችና ተቋማት ድጋፍ ለመቀበል ግን ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን።

    በዚህም መሠረት፥ ማንኛውም ወንጀሎቹን በቀጥታ የተመለከተ ወይም ስለወንጀሎቹ አስተማማኝ መረጃ ያለው ሰው ምስክርነት እንድትሰጠን(ጭን) ወይም የሰነድ ወይም የኦዶቪዡዋል ማስረጃዎችን እንድትልክልን(ኪልን) ጥሪ እናቀርባለን። ምስክርነት የሚሰጠን ወይም ሌሎች ዓይነት ማስረጃዎችን የሚሰጠን ሰው ራሱ(ሷ) ተጎጂ የሆነ(ች) ወይም የተጎጂው(ዋ) የቤተሰብ አባል፣ ዘመድ፣ ጓዳኛ፣ ጎረቤት ወይም መንደርተኛ የሆነ(ች) መሆን አለበት(ባት)። የምስክሮችን ማንነት በሚስጥር የሚያዝ ሆኖ፥ በሪፖርቱ ላይ ሊጠቀስ የሚችለው በግልጽ በተሰጠ የምስክሩ ፈቃድ ብቻ ይሆናል።

    ምስክርነት ለመሰጠት በቡድናችን የኢሜል አድራሻ forallethiopia@gmail.com ያሳውቁን። ከቡድናችን አንዱ አባል በስልክ ወይም እርስዎ በሚመርጡት የመገናኛ መንገድ ግንኙነት በማድረግ የምስክርነት ቃልዎን እንቀበላለን።

    በተጨማሪም የፎቶና የቪዲዮ ማስረጃዎችንም በኢሜል አድራሻችን forallethiopia@gmail.com የምንቀበል መሆኑን እንገልጻለን። ማንኛውም የምንሰበስበው ማስረጃ እውነተኝነትና አስተማማኝነትን የምናጣራ መሆናችንን እንገልጻለን።

    ይህንን መልዕክት በእንግሊዝኛ ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ

    በኦሮሚያ ክልልና አዲስ አበባ ከተማ በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም.  የተፈጸመውን ፍጅትን የሚያጣራ – በሰሜን አሜሪካ የሕግ ባለሙያዎች ቡድን
    ሐምሌ 11 ቀን፥ 2012 ዓ.ም.

    [caption id="attachment_15116" align="aligncenter" width="600"]Call for evidence regarding June/July 2020 massacre in Oromia, Addis Ababa, Harar and Dire Dawa በኦሮሚያ ክልል፣ አዲስ አበባ፣ ሐረር እና ድሬዳዋ ከተሞች የተፈጸመውን ፍጅት ለመጣራት መረጃ ለመሰብሰብ የተላለፈ ጥሪ Call for evidence regarding June/July 2020 massacre in Oromia, Addis Ababa, Harar and Dire Dawa[/caption]

    Anonymous
    Inactive

    በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለቱሪስት ብቻ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች ሄሎ ታክሲ በተባለ ድርጅት አማካኝነት በይፋ ተመርቀው ሥራ ጀመሩ

    አዲስ አበባ (ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር) – ኦክሎክ ጄነራል ትሬዲንግ የሚገጣጥማቸውና በሄሎ ታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ታክሲዎች በሸራተን አዲስ ሆቴል በኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ሒሩት ካሳው በይፋ ተመርቀዋል።

    የኦክሎክ ጄነራል ትሬዲንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሶሎሞን ሙሉጌታ፥ “ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ የቱሪዝም ሀብት ያላትና የተስፋ ምድር በመሆኗ ለቱሪስት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎችን ቀድመን ለማዘጋጀት ችለናል” ብለዋል።

    የሄሎ ታክሲ መሥራችና ባለቤት አቶ ዳንኤል ዮሐንስ በበኩላቸው፥ “ሄሎ ታክሲ በቀጣይም ቱሪስቱን በአውሮፕላን ወደ ቱሪስት መዳረሻዎች ለማድረስና አመርቂ አገልግሎት ለመስጠት 50% ዝግጅቱን አጠናቋል” ብለዋል።

    ሄሎ ታክሲ ከዚህ ቀደም 40 ታክሲዎችን አስመርቆ በይፋ ሥራ ያስጀመረ ሲሆን፥ አሁን ደግሞ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የቱሪስት ታክሲ ወደ አገልግሎት በማስገባት ሥራውን ጀምሯል። ሄሎ ታክሲ ከዚህ ቀደም በታክሲ አገልግሎት ተሰማርተው መኪኖቻቸው አሮጌ በመሆናቸው ከአገልግሎት ውጭ ለሆኑባቸው አሮጌውን መኪና በመቀበልና በአዲስ በመተካት የታክሲ ባለቤቶችን እየታደገ ያለ ድርጅት መሆኑም ተገልጿል። የተሰበሰቡ አሮጌ ታክሲዎችም ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመንጃ ፍቃድና ተግባራዊ የመኪና ጥገና መማሪያ እንዲሆኑ፤ ከዚያም ሲያልፍ የዋጋ ተመን ወጥቶላቸው ወደ ማቅለጫ ገብተውና ለውጭ ገበያ ተሽጠው ገቢ እንዲያስገኙ ሥራ እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል።

    የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስተር ክብርት ዶ/ር ሒሩት ካሳው፥ “መንግሥት የታክሲ ሞተሮች ከቀረጥ ነጻ ሆነው ወደ ሀገራችን እንዲገቡ የወሰነው ግብር መሰብሰብ አቅቶት ሳይሆን፥ አሮጌ መኪኖችን በአዲስ ተተክተው የአየር ብክለት እንዲቀንስ፣ ሀገር ውስጥ ሲገጣጠሙም ተጨማሪ የሥራ ዕድል ስለሚፈጥሩ፣ ዜጎቻችንም በሀገራቸው ሠርተው እንዲከብሩ፣ ስርቆት የሚፀየፍ ጥሩ አገልጋይ እንድትሆኑ ነው” ብለዋል።

    ሚኒስትሯ አክለውም፥ ታክሲዎችን በአዲስ እንደቀየራችሁ ሁሉ አስተሳሰባችሁንና ሕይወታችሁን በመቀየር ለቱሪስቶቻችንም ቀድሞ መረጃ በመስጠት ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ የሀገራችንን ገፅታ እንድትገነቡ አሳስባለሁ ብለዋል።

    የክህሎትና የአገልግሎት አሰጣጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ለታክሲ ሹፌሮች ይሰጣል ያሉት ሚኒስትሯ፥ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሕጋዊ አሠራርን መከተል እና ለረዥም ዓመታት በአሮጌ መኪና ጭስ የተበከለችውን ሀገራችንን በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብራችን ችግኝ በመትከልና በማልማት ማኅበራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ አደራ እላለሁ ብለዋል።

    በመጨረሻም ክብርት ወ/ሮ ቡዜና አልኸድር የኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ፥ ለታክሲ አገልግሎት ማኅበራቱ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንዲሳተፉ የችግኝ ስጦታ ያበረከቱ ሲሆን፥ ከሄሎ ታክሲ ድርጅት ጋርም በቱሪስት የታክሲ አገልግሎት ዙሪያ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

    የኦክሎክ ጄነራል ትሬዲንግ ተወካይ አቶ ሸምሰዲን አብዱራህማን በኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በኩል ተደራሽ የሚሆኑ ለ110 ሥራ አጥ ወጣቶች በ100% ብድር የሚሰጡ ሄሎ ታክሲዎችን፣ አስር የቱሪስት አምቡላንሶችን፣ በ59 ቋንቋዎች የማስተርጎም ሥራ የሚሠሩ ሃምሳ ማሽኖችን ለክብርት ዶ/ር ሒሩት ካሳው አስረክበዋል።

    የሄሎ ታክሲ ባለቤት አቶ ዳንኤል ዮሐንስ በኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በኩል ተደራሽ የሚሆኑ ለ250 ሰዎች አሮጌ ታክሲያቸውን ብቻ ሰጥተው አዲስ ታክሲ እንዲረከቡ የሚያስችል ስጦታ ያቀረቡ ሲሆን፥ የታክሲ ማኅበራትም ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የምስጋና ስጦታ ለክብርት ዶ/ር ሒሩት ካሳው አበርክተዋል።

    ምንጭ፦ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ሄሎ ታክሲ ኦክሎክ ጄነራል ትሬዲንግ

    Anonymous
    Inactive

    የሕግ የበላይነትን ማስከበር እና የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ የሀገር ህልውና መሠረት ነው!
    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ ምግለጫ

    በቅርቡ በልጃችን አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ እና ይህን ተከትሎ በሀገራችን በደረሰው የንፁሃን ዜጎች ሞትና የንብረት ውድመት የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለፅን ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በድጋሚ መፅናናትን እንመኛለን።

    በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት ምክንያት ሁላችንም ሀዘን እና የልብ ስብራት ውስጥ እንዳለን፥ ግድያውን ተከትሎ የደረሰው የበርካታ ዜጎቻችን ሞትና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ሀዘናችንን እጅግ መራር አድርጎታል። የአርቲስቱ ግድያ እና እሱን ተከትሎ በብዙ ዜጎች ሕይወት እና ንብረት ላይ የደረሰው ጥፋት እጅግ አሳሳቢ፣ አሳፋሪ እንዲሁም በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የተወገዘ እና በሀገራችን በምንም ዓይነት ሊደገም የማይገባው ድርጊት ነው።

    ኢትዮጵያውያን ከአምባገነናዊ አገዛዝ ነፃ ለመውጣትና የሚመጥነንን ሕዝባዊ አስተዳደር ለመትከል ረጅም ጊዜያትን በትግል አሳልፈናል፣ ብዙ ዋጋም ተከፍሏል። ዋጋ የተከፈለባቸው ሙከራዎች የከሸፉ ቢሆኑም በዚህ ሁሉ የታሪክ ውጣ ውረድ ግን የሀገር ህልውና በዚህ መልኩ ተፈትኖ አያውቅም።

    ሀገራችን ከነችግሮቿ ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ያላት፣ የምናወሳቸው እና የምንዘክራቸው ዛሬ ላለው ትውልድ መኩሪያ እና መመኪያ የሆኑ የማንነታችን መገለጫዎች የሞሉባት ሀገር ናት። በአንድ ወቅት አርቲስ ሃጫሉ እንደተናገረው ኢትዮጵያችን በብዙ የማንነት ቀለማት ኅብር የተዋበች ሀገር ናት። ኢትዮጵያዊነታችን በልዩነት ውስጥ የተጋመደ አንድነት መሆኑ ሃቅ ሆኖ እያለ የዘውግ ማንነት እና የቋንቋ ልዩነቶችን እየመዘዙ በሀገር አንድነት ላይ አደጋ መጣል ማንም አሸናፊ ወደማይሆንበት የቀውስ አዙሪት ውስጥ እንደሚከተን ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን ግልፅ ሆኗል።

    ሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት አስርተ ዓመታት በተለይም በሕወሃት/ኢህአዴግ ከፋፋይ አገዛዝ ስር ያሳለፈችው የፖለቲካ ትርክት ምን ያህል አደገኛ እንደነበር በግልፅ አይተናል። የህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ምንም እንኳን ያረጀና በሕዝብ ትግል የተሸነፈ ቢሆንም፤ የተከላቸው መርዘኛ ቅራኔዎች በአጭር ጊዜ የሚነቀሉ አልሆኑም። እያየን ያለነው የንፁሃን ዜጎች ሕይወት መቀጠፍ እና በረጅም ጊዜ ድካም የተገነቡ ሀብቶች ውድመት የዚሁ አገዛዝ ቅሪቶች እንጂ የኢትዮጵያዊያን እሴቶች አለመሆናቸውን እንገነዘባለን።

    በሰሞነኛው ብጥብጥ የደረሰው የበርካታ ዜጎች ሕይወት መቀጠፍና ከፍተኛ የንብረት ውድመት እጅግ አስከፊና የትውልዱ ማፈሪያ ከመሆኑ በተጨማሪ በዘውግ ማንነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ አካሄድ ወደ መቀመቅ እየወሰደን እንደሆነ ሕዝብና መንግሥት ከበቂ በላይ ትምህርት አግኝተዋል ብለን እናምናለን። በኢዜማ እምነት እውነተኛ ፌዴራሊዝም ሁሉም ራሱን በራሱ የማስተዳደር እና በመረጠው የመተዳደር መብት እንደሆነ እያስረገጥን ፖለቲካችን ከዘውግ እና ከሃይማኖት ካልተላቀቀ በስተቀር መጨረሻችን እጅግ አደገኛ እንደሚሆን በተደጋጋሚ ስንገልፅ ነበር። በዘውግ እና በሃይማኖት ልዩነት ላይ የተንጠለጠለ የፖለቲካ አካሄድ ወደ መጠፋፋት እየወሰደን መሆኑን በመገንዝብ በማስተዋል እና በመረጋጋት እንድንጓዝ፤ በአንድ ሀገር ለውጥን ማዋለድ ብዙ ትግልና መስዋትነትን የሚጠይቅ እንደዚሁም ከፍተኛ ትዕግስትና ማስተዋል የሚሻ መሆኑን በተደጋጋሚ ስንገልፅ ብንቆይም ይህ አቋማችን ባንዳንድ ወገኖች እንደመለሳለስ ሲቆጠር ቆይቷል።

    ሰሞኑን በተከሰተው ቅስም-ሰባሪ ጥፋት በሀገራችን ፖለቲካ የሚከተሉትን አበይት ነጥቦች በተለየ እንድንታዘብ አስገድዶናል። እነዚህም፦

    • በድንገት የሚፈጠር ነውጥ ሀገራችንን ከማትወጣው የከፋ አዘቅት ውስጥ ሊያስገባት እንደሚችል፣
    • በዘውግ እና በሃይማኖት ላይ የሚሰበክ የፖለቲካ ትርክት፤ ከዚህ ትርክት ተነስቶ የሚቆሠቆሰው ፍጹም ስሜታዊ ጥላቻ እና ጥላቻው የሚቀሰቅሰው የደቦ እንቅስቃሴ፤ የሰውን ልጅ ከሰብዓዊነት ማማ አውርዶ ወደ አውሬነት ሊቀይረው እንደሚችል ተገንዝበናል። በሌላ መልኩ ደግሞ በዚህ ዓይነት ፍጹም ስሜታዊ ሁኔታም ውስጥ ብሔራቸውን እና ሃይማኖታቸውን ተሻግረው፤ ለሰብዓዊነት እና ለጋራ ህልውናችን ዘብ ቆመው፤ በሁከቱ ምክንያት ለችግር የተዳረጉ ዜጎችን በመሸሸግ እና በማስጠለል የንፁሀንን ነፍስ የታደጉ የምንኮራባቸው ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን፣ ይህንን የመሰለው ዘመን ተሻጋሪ የኢትዮጵያዊያን እሴት ቢፈተንም በዚህ ዘመንም መቀጠሉን፣
    • ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጭምር እንደገለፁት፥ ችግር ፈጣሪዎች በመንግሥት አስተዳደር መዋቅሮች ውስጥ የሚገኙ ኃይሎች ጭምር መሆናቸውን፤
    • ችግሩ በተከሰተበት ጊዜ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች በአንዳንድ አካባቢዎች የዜጎች ሕይወት በአደባባይ ሲቀጠፍ፣ የሀገር ሃብት ሲወድም አይተው እንዳላዩ የማለፍ ሁኔታ እንደነበር፤ የዚያኑ ያክል ደግሞ የሕግና የሞራል ኃላፊነታችውን በመወጣት እየሞቱና እየቆሰሉ ማኅበረሰቡን ከጥቃት የተከላከሉ ብዙ የጸጥታ ኃይሎችን ያየንበት መሆኑ፣
    • በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ በወታደራዊው የደርግ አገዛዝ ውድቀት ማግስት የፀጥታ ኃይሎች ባልተደራጁበት እና ከፍተኛ የመንግሥት አስተዳደር ክፍተት በነበረበት ወቅት ነዋሪው ለሰላምና መረጋጋት አኩሪ አሰተዋፅኦ እንዳበረከተ ሁሉ፥ ዛሬም ሕዝባችን በመኖሪያ ቀዬው ራሱን በማደራጀት ራሱን፣ ቤተሰቡን፣ ንብረቱን እና አካባቢውን ለመጠበቅ ያሳየው ቁርጠኝነት እጅግ የሚመሰገን ተግባር ሆኖ ጎልቶ መታየቱ፤

    ከሰኔ 22 በኋላ በጉልህ የታዘብናቸው ክስተቶች ነበሩ።

    በቅርቡ የተከሰተው እና የሀገርን አንድነት የተፈታተነው አውዳሚ ክስተት ለጊዜውም ቢሆን መክሸፉ ችግሩ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ አግኝቷል ማለት አይደለም። የሀገራችንን አንድነት የሚፈታተኑ ብዙ ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። በዚህ ጊዜ እንደ ተፎካካሪ ድርጅቶችም ሆነ እንደ ዜጎች ያለብን ኃላፊነት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ማወቅና በተግባር ለማሳየት መዘጋጀት ይጠበቅብናል። የሀገርን አንድነት እና ሰላም ባጭር ጊዜ፤ ለዘላቂው ደግሞ ለዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ምሥረታ፤ ከምሩ የቆመ መንግሥት እስካለን ድረስ (በተለያዩ የፖለቲካ እና የፖሊሲ አመለካከት የምናምን የፖለቲካ ድርጅቶችና ዜጎች ብንሆንም እንኳን) ይህን ማዕከላዊ መንግሥት ለማዳከም፤ በዚህም የተለያዩ የጦር አበጋዞች የሚርመሰመሱበት የእርስበርስ ግጭት ውስጥ ሊዳርጉን የሚፈልጉ ኃይሎች የሚያደርጉትን ዘመቻ በማስቆም በኩል ሙሉ ትብብር ማድረግ እንዳለብን ልናውቅ ይገባል። በእነኝህ አንኳር ጉዳዮች ላይ የምንስማማ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆነ ሌሎች የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት እና አባላት ለሀገራችን መኖር እና ለሕዝቧ ሰላም ባንድነት በተግባር መቆም እንደሚኖርብን መገንዘብ ያለብን ጊዜ ላይ ደርሰናል።

    ኢዜማ በሀገር አንድነትና በማኅበረሰባችን ሰላም ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ድርድር መኖር የለበትም ብሎ ያምናል። እነኝህን ሁለት መሠረታዊ እሴቶች በዋናነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት ደግሞ ሀገራዊ መንግሥቱ ነው። ያለ ሀገር ፖለቲካም ሆነ ዴሞክራሲ ትርጉም የላቸውም። ለዘላቂው የሀገር አንድነት እና ሰላም ከዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ መኖር፤ ከፍትህ መኖር፤ ከዜጎች እኩልነት መረጋገጥ ወዘተ… ጋር በጥብቅ የተቆራኙ መሆናቸውን እናምናለን። ስለሆነም ሁሉም የሀገራችን ዜጎች ይህን ፈታኝ ጊዜ በትግስት፣ በማስተዋልና በጥንቃቄ እንዲሻገሩት እና የሀገራችንን አንድነት እና ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ሁላችንም ያለብንን ኃላፊነትና ድርሻ የመወጣት ግዴታ እንዳለብን በማሰብ ኢዜማ በሚከተሉት ወሳኝ ነጠቦች ላይ በድርጅታችን መርሆዎች ላይ የተመሠረተ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፤

    1. የሰው ልጅ ማኅበራዊ ፍጥረት በመሆኑ በተለይም ፈታኝ ጊዜያትን ያሳለፈው፣ ከፍጥረታት ልቆ የቆየው እና ተፈጥሮን ገርቶ ትውልድን ማስቀጠል የቻለው በተለያዩ ማኅበራዊ አደረጃጀቶች አቅም ፈጥሮ በመተጋገዝ ነው። በአደረጃጀቱ አያሌ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ተቋቁሞ አሳልፏል፤ ከእነዚህም አደረጃጀቶች መካከል «መንግሥት» ትልቁ የሰው ልጅ አደረጃጀት ሲሆን በውስጡ በርካታ አደረጃጀቶችን እንደያዘ ግልፅ ነው።

    የእነዚህ አደረጃጀቶች ዋና መሠረት ደግሞ የቆየው ማኅበራዊ አደረጃጀት ነው። በሀገራችንም በርካታ የቆዩ የአደረጃጀት ዓይነቶች አሉ። ይህንን ማጠናከር የሀገርን ህልውና እና የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ በእጅጉ ይረዳል የሚል እምነት አለን። ማኅበራዊ ፍትህ በነገሰባቸው በርካታ ሀገራት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ነፃ ማኅበራዊ አደረጃጀቶች አሉ። እኛም ሀገር ሰሞኑን በተፈጠረው ችግር ሕዝቡ በየመኖሪያ ቀዬው ተደራጅቶ ሰላሙን ሲያስከብር ተመልክተናል። በተለይም በአዲስ አበባ እና በአንዳንድ ከተሞች የታየው አደረጃጀት ትልቅ ትምህርት ሰጪ ነበር። አዲስ አበባ ከተማ ሁሉንም የሀገራችንን ማኅበረሰቦች አቅፋ የምትኖር፤ በዓለማችን በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ የዲፕሎማቲክ ከተሞች አንዷ እንደመሆንዋ በውስጧ ያቀፈቻቸው ዜጎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱባትና ልዩልዩ አስተሳሰቦችና እምነቶች ተከባብረው የሚኖሩባት ከተማ ናት። ይህን መሰሉ ማኅበራዊ እሴት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እናምናለን። ይሁን እንጂ ሰሞነኛው ክስተት እንደሀገር ለከፍተኛ ውርደት የዳረገን የታሪካችን ማፈሪያ ሆኖ አልፏል። በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ሕዝብ ዘመኑን በሚመጥን እና በሠለጠነ መንገድ በዘውግ ማንነት፣ በሃይማኖት ወይም በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳያደርግ በመደራጅት ቤተሰቡን እና አካባቢውን ከጥፋት ከመከላከሉም ባሻገር ከተማዋን እጅግ ከከፋ ውድመት ታድጓታል። ለዚህም አክብሮት እና ምስጋናችንን ለማቅረብ እንወዳለን።

    ይህን ዓይነቱ መሰባሰብ ለወቅታዊ ችግሮች ብቻ ሳይሆን ለዘላቂውም ጭምር ጠቀሜታው የጎላ ስለሆነ የማኅበረሰቡ የቆዩ አደረጃጀቶች እንዲበረታቱ መሥራት ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር አሁን እየታዩ ያሉ አደረጃጀቶችን በየአካባቢው በሕዝብ በሚመረጡ አካላት ማጠናከር፣ እውቅና መስጠት እና የፀጥታ ጉዳይን በሚመለከት አደራጃጀቶቹን ከማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ እና የመንግሥት የጸጥታ አካላት ጋር የማጣመሩን ተግባር መንግሥት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተቻለ ፍጥነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን። አደረጃጀቶቹ የጋራ ደኅንነትን ከመጠበቅ በተጨማሪ የከተማዋ ምልክት የሆነውን ሁሉም ዓይነት ማንነቶች ተከብረውባት፣ ዜጎች ተጋግዘው እና ተባብረው የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን በቀጣይነት ለማረጋገጥም የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አደራ እንላለን።

    እነዚህ አደረጃጀቶች በሌሎች ኃይሎች እንዳይጠለፉ እና ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ ደኅንነታቸውን ከመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች ጋር እንዲያስጠብቁ ከማስቻል ያፈነገጠ ዓላማ ማስፈፀሚያ መሣሪያ እንዳይሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንደሚገባም ልናሳስብ እንወዳለን።

    1. የደኅንነት እና የፀጥታ ተቋማት ዋና ተግባር የሀገርን ደኅንነት እና የሕዝብን ሰላም ማስጠበቅ ነው። ሰሞኑን ሀገራችን በገባችበት ችግር ዙሪያ ማብራሪያ ሲሰጡ የነበሩ የፀጥታ ተቋማት ኃላፊዎች ችግሩ እዚህ ደረጃ እስኪደርስ የዘገዩት በሆደ-ሰፊነት የፖለቲካውን ምህዳር ለማስፋት መንግሥት በያዘው አቋም ምክንያት መሆኑን ሲገልፁ ሰምተናል። ይህ ተቋማዊ ኃላፊነታቸውን የዘነጋ አካሄድ እና አገላለፅ በቶሎ ሊታረም ይገባል። የዜጎችን ሕይወት እና ንብረት ለከፋ አደጋ ዳርጎ ሆደ-ሰፊነት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ መነገር የለበትም። ይህንን የማድረግ መብትም ሆነ የሕግ ድጋፍም የላቸውም። የፀጥታ ተቋማት በየደረጃው ተቀናጅተው በመሥራት እና ሀገርን እና ዜጎችን ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጥቃት መታደግ ነው ዋና ተልዕኳቸው። በተለይም በእንደዚህ ዓይነት ወቅት ሕዝብን በማስተባበር አደጋ ከመድረሱ ቀድሞ የማክሸፍ ሥራ በመሥራት፤ አንዴ ከተፈጠረ ደግሞ በፍጹም ቁርጠኝነት ሀገርን እና ሰላማዊ ሕዝብን ከጥቃት መከላከል የፀጥታ አካላት ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባ ተግባር እንደሆነ በአንክሮ እንገልፃለን።
    2. ለዘመናት የታገልንለት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እና የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ሀገርን እና ሕዝብን ለአደጋ እስከሚያጋልጥ ልቅነት ድረስ መሆን እንደሌለበት ደጋግመን ስንገልጽ ቆይተናል። አሁን እንደምናየው የግል የብዙሃን መገናኛዎች የተወሰኑት በፓርቲ ልሳንነት፣ የተወሰኑት ደግሞ በጥቅም አሳዳጅነት ሀገርን እና ዜጎችን አደጋ ላይ ሲጥሉ ሥልጣን የተሰጠው አካል አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ነበረበት፤ አለበትም። ከዚህ አንፃር የግል ብዙሃን መገናኛዎች የሀገሪቱን ሕግና የሙያውን ሥነ-ምግባር ጠብቅው እንዲሠሩ ጥሪ እናቀርባለን። በሌላ በኩል የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ደግሞ ሚዛናዊነት በጎደለው መልኩ በተለይም የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ቃለመጠይቆችን ብቻ በማስተናገድ መሪ አዘጋገብ እና ፍረጃ ውስጥ መግባታቸው የዜጎችን በፍርድ ቤት ጥፋተኛነታቸው እስኪረጋገጥ ድረስ እንደነፃ የመታየት መብት የሚጋፋ እና የፍትህ ተቋማቱን አካሄድ የሚያዛባ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲያርሙት እናሳስባለን። የመገናኛ ብዙሃን እንዲመሠረት የምንፈልገውን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መርህ የተከተሉ፣ የሕዝብ መረጃ ማሳወቂያ፣ ማስተማሪያ እና ማረጋጊያ መሆን እንሚገባቸውም በአፅንዖት እንገልፃለን። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የብዙሃን መገናኛ ተቋማትን በቅርበት እየተከታተለ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድም አበክረን እናሳስባለን።
    3. የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመሥረት ለዘላቂ ሀገራዊ መረጋጋት መሠረት መሆኑን እናምናለን። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚመሠረተውም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማለትም በእውነተኛ ውይይትና ድርድር ብቻ ነው።

    ይህንን ለማድረግም ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ዘመናዊ፣ የሠለጠነ ፖለቲካ እና የጨዋታ ሜዳውን ሕግ ያከበረ አካሄድ መከተል ይገባናል። ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደምም ሆነ ሰሞኑን የተከሰተው የመገዳደልና የመጠፋፋት ፖለቲካ ወደ ሰለጠነ ፖለቲካ የሚወስደን ሳይሆን ከዚህ ቀደም ዋጋ ወደከፍልንባቸው የተወሳሰቡ ችግሮች ውስጥ መልሶ የሚዘፍቀን አካሄድ ነው። በዚህ ረገድ የሁሉም ድርሻ አስፈላጊ ቢሆንም በሀገር አንድነት፣ በሰላማዊ እና በሠለጠነ የፖለቲካ ትግል እንዲሁም ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረግ ሽግግርን ከሚያምኑ ወገኖች ጋር ለሚደረግ ውይይት ገዢው ፓርቲ ወሳኝ ድርሻ አለው። በአንድ በኩል የሀገርን ህልውና እና የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቁን አጠናክሮ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበትን ሽግግር እውን ለማድረግ የሚያስችል እና ለሁሉም ተሰፋ የሚሰጥ የባለድርሻዎች ውይይት ሳይውል ሳያድር እንዲጀመር እንጠይቃለን።

    1. የሙያ እና የሲቪክ ማኅበራት በአጠቃላይ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፤ በተለይ ደግሞ እንደኛ ሀገር ፖለቲካችንን ሰቅዞ ከያዘው የዘውግ ፖለቲካ ወደ ጤናማ የሀሳብ ፖለቲካ በማሸጋገር እንቅስቃሴ ውስጥ የሚኖራቸው ሚና እጅግ የጎላ እና ሚዛንን ማስጠበቅ የሚያስችል እንደሚሆን ይታመናል። ባለፉት 27 ዓመታት በሀገራችን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሙያ ማኅበራት በገዢው ፓርቲ ተፅዕኖ ስር የወደቁ እና ተዳክመው የቆዩ መሆናቸውን እንረዳለን።

    ረጅም ጊዜ ከቆየ አምባገነናዊ ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረግ ሽግግር ውስጥ ለረጅም ጊዜ የተጠራቀሙ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሁሉ በቶሎ እንዲፈቱ መጓጓት እና ዜጎች ጥያቄዎቻቸውን እና ፍላጎቶቻቸውን የሚያቀርቡበት እና እንዲመለስላቸው ጫና ለማሳደር ኃይልን የቀላቀለ መንገድ መከተላቸው ትልቅ ተግዳሮት ይፈጥራል። የሙያ እና የሲቪክ ማኅበራት ራሳቸውን ከነበረባቸው ጭቆና ነፃ አውጥተው እና ተጠናክረው የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር እና ተደራሽ የሆኑ ብዙሃን መገናኛዎችን በመጠቀም ስለ ሰላማዊ ተቃውሞን የማሰሚያና ጫና የማሳደሪያ መንገዶች በሰፊው በማስተማር ከሕዝብና ከእውነት ጎን ቆመው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና ለሀገር መረጋጋት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ እናቀርባለን።

    1. በሀገራችን በተደጋጋሚ ጊዜ ፖለቲካዊ ሽፋን እየተሰጣቸው ከተነሱ ረብሻዎች ጋር በተያያዘ በርካታ የንፁሃን ዜጎች ሕይወት በከንቱ ሲቀጠፍ እና የግል ባለሃብቶችም ንብረት በሚያሳዝን ሁኔታ ሲወድም እየተመለከትን ነው። እነዚህ ረብሻዎች እንዳይከሰቱ፣ ከተከሰቱም የሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ አደጋ እንዳያደርሱ መቆጣጠር እና የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ዋነኛ የመንግሥት ሥራ በመሆኑ፣ መንግሥት ይህን ኃላፊነቱን በሚገባ ሳይወጣ ቀርቶ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በይፋ ወጥቶ ይቅርታ መጠየቅ እና ከዚህ በኋላ እንደዚህ ዓይነት ጥፋት በፍፁም እንደማይደገም ቃል ሊገባ እና ሊያረጋግጥ ይገባዋል።

    መንግሥት የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ እና የአርቲስቱን ሞት ተከትሎ ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ጉዳይ ባስቸኳይ አጣርቶ ፍትህ እንዲያገኙ ሊያደርግ ይገባል። እንደዚሁም የሀገራችን ኢኮኖሚ ዳዴ በሚልበት በዚህ ፈታኝ ወቅት ባለሀብቶች አንጡራ ሃብታቸውን አፍስሰው የገነቧቸው መሠረተ ልማቶች እንደዘበት ወድመው፣ ተቃጥለው እና ሠራተኞች ተበትነው ማየቱ እጅግ ያሳዝናል። በቀጣይም ሃብታቸውን አፍስስው ሊያለሙ የሚችሉ ባለሃበቶችም ዋስትና ስለማይኖራቸው መዋዕለ ንዋያቸውን ከማፍሰስ ይታቀባሉ። ከዚህ አንፃር በሰሞኑ ክስተት ቤት ንብረታቸውና ትልልቅ የንግድ ተቋሞቻቸው ለወደመባቸው ዜጎች መንግሥት ተገቢውን ካሳ ከፍሎ እንዲያቋቁማቸው አበክረን እንጠይቃለን።

    በመጨረሻም አሁን ያለንበት ሁኔታ ለሀገራችን እጅግ ፈታኝ መሆኑ ግልፅ ነው። ዓለም አቀፍ ስጋት የሆነው የኮቪድ-19 ወረርሺኝ ከዕለት ዕለት እየተስፋፋ መጥቷል። ከአባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀም በተለይም ከህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ ግብፅ የፈጠረችው እሰጥአገባ ያመጣው ጫና ከሀገራችን አልፎ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ መነጋገሪያ ሆኗል። ኢትዮጵያውያንም በእነዚህ አንገብጋቢ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከምንግዜውም በላይ በጋራ መቆም የሚገባን ትክክለኛው ሰዓት ላይ እንገኛለን።

    በመሆኑም የውስጥ ልዩነቶቻችንን በሰለጠነ ፖለቲካ አሰታርቀን እንደሀገር የተደቀኑብንን ተደራራቢ ፈተናችዎች በፅናት ማለፍ ካልቻልን ለትውልድ የምትሆን ሀገር ማሻገር ይቅርና እኛ ራሳችን ከማንወጣው የከፋ አዘቅት ውስጥ ገብተን እንደምንዳክር መረዳት ይኖርብናል። ስለሆነም የሕግ የበላይነትን በማክበር፣ በወንድማማችነትና በእህትማማችነት በመተባበር እና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት አሁን ካለንበት ውስብስብ ችግር ወጥተን ሀገራችንን ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በጋራ እንድናሻግር ለኢትዮጵያውያን በሙሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
    ሐምሌ 6 ቀን 2012 ዓ.ም.

    የሕግ የበላይነትን ማስከበር እና የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ የሀገር ህልውና መሠረት ነው

    Anonymous
    Inactive

    አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን በመግደል የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ተያዙ፤ ኦነግ ሸኔ ከተባለው ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን በመግደል ዋነኛ የተባሉ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ሐምሌ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. አስታውቋል። ሦስተኛው ተጠርጣሪ ደግሞ እየተፈተለገ ነው ብሏል።

    ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክብርት አዳነች አቤቤ ሐምሌ 3 ቀን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አንደኛው ተጠርጣሪ ጥላሁን ያኒ የተባለ ሃጫሉ የተገደለበት ገላን የተባለዉ የአዲስ አበባ አካባቢ ነዋሪ እንደሆነ አስታዉቀዋል። በግድያው ተባባሪ የተባለዉ ሁለተኛ ተጠርጣሪ አብዲ ዓለማየሁም በቁጥጥር ስር መዋሉን ክብርት አዳነች ተናግረዋል።

    ዋነኛ የተባለው ተጠርጣሪ ጥላሁን ያኒ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል መሣሪያውን የተኮሰው እሱ መሆኑን እና ተልዕኮውንም ከኦነግ ሸኔ መቀበሉን ማመኑ ተገልጿል። ጥላሁን ያኒ ለፖሊስ በሰጠው የእምነት ቃል ድርጊቱን የፈፀመው “ኦነግ ሸኔ” ከተባለው ክንፍ በተሰጠው ተልኮ መሆኑን መግለፁን፤ ተልኮውን የሰጡት ግለሰቦችም ሁለት መሆናቸውን አምኖ መቀበሉን ክብርት አዳነች አስረድተዋል።

    ጠቅላይ ዐቃቤ ክብርት ሕግ አዳነች አቤቤ አያይዘው እንደገለጹትም ከበደ ገመቹ የተባለ ሦስተኛ ተጠርጣሪ እስካሁን በቁጥጥር ስር እንዳልዋለ እና በፖሊስ እየተፈለገ ነው።

    የኢትዮጵያ መንግሥት ኦነግ ሸኔ እያለ የሚጠራቸውና ራሱን “የኦሮሞ ነፃነት ጦር” ብለው በሎ የሚጠራው (ከዋናው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተከፍሎ ጫካ የቀረው) ቡድን ሀገር ወስጥ በተደጓጋሚ ጥቃት እያደረሰ ለንጹሃን ዜጎች ሞት፤ መቁሰል እና ለንብረት መጥፋት ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል። ለምሳሌ የካቲት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል የቡራዩ ከተማ ፖሊስ አዛዥን የገደለውና የካቲት 15 ቀን 2012 ዓ.ም. በአምቦ ከተማ ውስጥ ለድጋፍ ሰላማዊ ሠልፍ በወጡ ነዋሪዎች ላይ ቦምብ በመወርወር የአካል ጉዳት ያደረሰው ኦነግ ሸኔ የተባለው ቡድን መሆኑን የኦሮሚያ ክልል አስታውቆ ነበር።

    በታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም. ደግሞ የቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ሠራተኛ የነበሩት አቶ አብዱላሂ ሳጆር ከአሶሳ ወደ ነቀምት ለሥራ ጉዳይ በመሄድ ላይ እያሉ ዛሬ በታጣቂዎች መገደላቸውን፤ ጥቃቱንም የፈጸመው ትጥቅ ያልፈታው ኦነግ ሸኔ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ጽ/ቤት አስታውቆ ነበር።

    በምዕራብ ኦሮሚያ በተለያዩ ዞኖች በመንቀሳቀስ የሰላማዊ ሰዎችን ኖሮ እና እንቅስቃሴ የሚያውከውን የኦነግ ሸኔ ቡድን ድርጊት በማውገዝ የቄለም ወለጋ፣ የምዕራብና ምስራቅ ወለጋ እንዲሁም ቡሎ በደሌ የተለያዩ ወረዳዎች ነዋሪዎች ሰኔ 19 ቀን 2011 ዓም የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደው ነበር። በሰላማዊ ሰልፉም ላይ ነዋሪዎቹ ኦነግ ሸኔ የተባለው ቡድን እንደማይወክላቸው፣ ይልቁንም የሕዝቡን ሰላም እያደፈረሰ መሆኑን ገልጸው ነበር።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ገዳዮች ኦነግ ሸኔ ከተባለው ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው

    Anonymous
    Inactive

    በኦሮሚያ ክልል “ከአንድ ብሔር ተወላጅ ናቸው” በተባሉ ዜጎች ላይ ዘግናኝ ጥቃት መድረሱን ነዋሪዎች ተናገሩ ― የአሜሪካ ድምፅ

    በኢትዮጵያ የአንድ ብሔር ተወላጅ ናቸው በተባሉ ዜጎች ላይ በተነጣጠረ ጥቃት ቁጥራቸው ለጊዜው ያልታወቁ ኢትዮጵያውያን በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ (ቪኦኤ) ገልፀዋል።

    በሌላ በኩል ጥቃቱ የተፈፀመው “ከአንድ ብሔር የመጡ ናቸው” የሚሉ ሰዎች ላይ በማነጣጠር ቢሆንም፥ ሕብረተሰቡ የተጋባና የተዋለደ በመሆኑ ተጎጂ ከሆኑት ውስጥ ከተለያየ ብሔር የተወጣጡ ሰዎች መሆናቸውን ነዋሪዎችም፣ የዞኑ አስተዳዳሪም ተናግረዋል።

    ሰኞ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት በአዲስ አበባ ገላን ኮንደሚኒየም አካባቢ ባልታወቁ ሰዎች የተገደለውን ዝነኛውን የኦሮሚኛ ቋንቋ ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች እጅግ አሰቃቂ በሆኑ ሁኔታዎች የተፈጸሙ ግድያዎች፣ አካል ማጉደል፣ ዘረፋና በከፍተኛ ሁኔታ ንብረት ማቃጠል መከሰቱንም ተጎጂዎችና የዓይን እማኝ መሆናቸውን የተናገሩ ለአሜሪካ ድምፅ (ቪኦኤ) ገልፀዋል።

    አንዳንዶቹ ግድያዎች በደቦ የተፈፀሙ ሲሆኑ፥ አንዳንዶቹ ግን በሰለጠኑ እና ተኩሰው በማይስቱ ታጣቂዎች የተፈፀሙ መሆናቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። የአሜሪካ ድምፅ ቤተሰቦቻቸው ፊት ለፊታቸው እደተገደሉባቸው የሚናገሩ፣ ንብረታቸው እንደተቃጠለባቸውና ያለ መጠለያ መቅረታቸውን የሚገልፁ በተለያዩ ከተማ የሚገኙ ወደ 20 የሚጠጉ ሰዎችን ያነጋገረ ሲሆን፥ በዛሬው ዕለት (ሰኔ 29 ቀን) በአርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ ዴራ ከተማ እና አካባቢው የሚገኙ ከጥቃት ከተረፉት መካከል የተወሰኑትን አስደምጧል።

    በሌላ በኩል የአርሲ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ጀማል አልዩ በአርሲ ዞን ውስጥ እርሳቸው ከሚያስተዳድሯቸው 25 ወረዳዎችና ሦስት ከተሞች መካከል በስድስቱ ውስጥ በተፈፀሙ አሰቃቂ ግድያዎች የ34 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገፀዋል። ድርጊቱ በአካባቢው ከነበረው ፖሊስ አቅም በላይ እንደነበርና የፀጥታ አባል ጭምር መገደሉን አረጋግጠዋል። የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በተለያዩ ከተሞች ጥቃቶቹ መፈፀማቸውን አምነዋል።

    ድርጊቱ የተፈፀመው በሁለት ብሔሮች መካከል የተካረረ ፀብና ግጭት በመቀስቀስ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዓላማቸው ባደረጉ አካላት ነው ሲሉም ከግጭቱ ጀርባ ሌሎች ቡድኖች እንዳሉ ጥቆማ ሰጥተዋል። መንግሥት ይህንን በአስቸኳይ በመረዳት የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት አባላቱን ከክልል የፀጥታ ጥበቃ አባላት ጋር በማዋቀር የመከላከል ሥራ በመሥራቱ እንጂ ከዚህም የባሰ ጥቃት ይደርስ ነበር ሲል መንግሥት መግለጫ ሰጥቷል።

    የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር ግርማ ገላን እስካሁን የ145 ሰላማዊ ዜጎች እና የ11 የፀጥታ ኃይሎች ሕይወት በድምሩ የ156 ዜጎች ሕይወት ማለፉን አረጋግጠዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ደግሞ በአዲስ አበባ የሁለት የፀጥታ ኃይሎችና የስምንት ሲቪሎች በድምሩ የ10 ሰዎች ሕይወት ማለፉን አረግጋጠዋል። በአጠቃላይ ከመንግሥት የተገኘው መረጃ 166 ሰዎች በቦምብ፣ በጥይት፣ በድንጋይና በመሳሰሉት ሕይወታቸው ማለፉ ይጠቁማል።

    (ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ)

    ምንጭ፦ የአሜሪካ ድምፅ

    ከአንድ ብሔር ተወላጅ ናቸው በተባሉ ዜጎች ላይ ዘግናኝ ጥቃት

    Anonymous
    Inactive

    ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በአፋጣኝ ይቁም!!

    (ያሬድ ኃይለማርያም*)

    በ1994 እ.ኤ.አ. ሩዋንዳ ውስጥ የተከሰተውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በዋናነት የመሩት ሁለት ሬድዮ ጣቢያዎች ነበሩ። አንዱ በመንግሥት ስር የነበረው ሬድዮ ሩዋንዳ (Radio Rwanda) የሚባለው ሲሆን ሁለተኛው እና ዋናው የእልቂቱ አነሳሽና ቀስቃሽ የነበረው Radio Télévision des Milles Collines (RTLM) ተብሎ የሚጠራው ጣቢያ ነበር። ይህ ጣቢያ በወቅቱ በወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበረው ስለነበር በሀገሪቱ ውስጥ የነበሩ ሥራ አጥ ወጣቶችን እና የቀኝ አክራርሪ የሆኑትን የሁቱ ኢንተርሃሞይ ሚሊሻዎችን (Interahamwe militia) በቀላሉ ወደ ጥላቻ በመንዳት በመምራት እና እልቂት እንዲፈጽሙም በማነሳሳት ትልቅ ሥራ ሠርቷል። ይህ ጣቢያ ከእልቂቱም በፊት ቢያንስ ለአንድ ዓመት ያህል ጥላቻን ሲሰብክ ቆይቷል።

    ዛሬ ደግሞ ተራው የእኛ በሚመስል ሁኔታ እጅግ ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ለዓመታት ጥላቻን ለኦሮሞ ወጣቶች እና ለኦነግ ሽኔ ታጣቂዎች ሲሰብክ የነበረው OMN የተባለው ሚዲያ የወንድማችንን ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ባስተላለፋቸው ተከታታይ የአመጽ እና የእልቂት ጥሪዎች እና ቅስቀሳዎች ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በዘር ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ምክንያት ሆኗል። ይህ የቴሌቪዥን ጣቢያ ልክ የሩዋንዳው RTLM እንዳደረገው ሁሉ ጥሪው ክልሉ ውስጥ ላሉ ሥራ-አጥ ወጣቶች እና በሽኔ ስም ለሚጠሩት ሚሊሺያዎች ነበር። በዚህም እጅግ ለመስማትና ለማየት የሚሰቀጥጡ ዘር ተኮር ጭፍጨፋዎች በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች እንዲፈጸሙ ተደርጓል። ሰዎች እቤታቸው ውስጥ እንዳሉ ከነቤተሰቦቻቸው በእሳት ጋይተዋል፤ ህጻናት፣ ሴቶች እና ሽማግሌዎች ሳይቀሩ በስለት እና በቆንጨራ ተቆራርጠው ተገድለዋል፤ እናት ከህጻን ልጇ ጋር በአንድ ገመድ ታንቃ ተገድላለች፤ ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት ወድሟል፤ ብዙዎች ከቤታቸው ሸሽተው በተለያዩ ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ ተደብቀዋል።

    አንዳንድ እማኞች በመገናኛ ብዙኃን ምስክርነታቸውን እንደሰጡት እና እኛም ማረጋገጥ እንደቻልነው ለጥቃት የተሰማሩት ኃይሎች በቂ ዝግጅት ያደረጉ፣ የተለያዩ የጥቃት መሣሪያዎችን የያዙ እና የጥቃት ዒላማ የሆኑ ሰዎችን ስም እና አድራሻም ይዘው እንደሚንቀሳቀሱ ለማወቅ ተችሏል። ነገሩን እጅግ አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ በክልሉ ውስጥ ያሉ የክልሉ ታጣቂ ኃይሎች ይህ ሁሉ እልቂት ሲፈጸም ድርጊቱን ለማቆም አፋጣኝ እርምጃ አለመውሰዳቸው ነው። በአሜሪካ ድምጽ (ቬኦኤ) እና አንዳንድ ሚዲያዎች እንደተዘገበውም በተወሰኑ ቦታዎች የመንግሥቱ ታጣቂዎች ትዕዛዝ አልተሰጠንም በሚል ጥቃት ሲፈጸም እያዩ ዝምታን መርጠው መቆየታቸው ነው። በሩዋንዳም የዘር ማጥፋት ጥቃት ሲፈጸም የሆነው ይሄው ነበር። እነዚህ ኃይሎች በምንም መልኩ የኦሮሞን ሕዝብ አይወክሉም። በኦሮሞ ሕዝብ መሃል የበቀሉ እንክርዳዶች ናቸው። በመሆኑም እንዲህ ያሉ እኩይ ተግባር የሚፈጽሙ ቡድኖችን እና ነገሩን በቸልታ ሲያዩ በነበሩ የክልሉ ኃላፊዎች ላይ በቂ ምርመራ ሊካሔድ እና በሕግ ሊጠየቁ ይገባል።

    OMN አዲስ አበባ ያለው ጽሕፈት ቤቱ ቢዘጋም ተመሳሳይ የእልቂት ጥሪዎችን ከሀገር ውጭ ባሉ ባልደረቦቹ በኩል ሲያስተላልፍ ቆይቷል። ዛሬ ደግሞ ይህ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከግጭቱ ጋር ተያይዞ አየር ላይ ያዋላቸውን እና በዩቲዩብ (YouTube) የተላለፉ ዝግጅቶቹን ከአየር ላይ እያወረደ እና መረጃዎችን ለማጥፋት ጥረት እየተደረገ ነው። ይሁንና ለማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት፦

    (ኛ) የእነዚህ የእልቂት ጥሪዎች ቅጂዎቻቸው ጣቢያው በመንግሥት ቁጥጥር ስር ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ በመንግሥት እጅ ስለሚገኙ እና የብሮድካስቲንግ ኤጀንሲውም የእነዚህ ቅስቀሳዎች ቅጂ እንዳለው ባለሥልጣኑ ስለተናገሩ ጣቢያው መረጃ ለማጥፋት እያደረገ ያለው ጥረት ይሳካል ብዬ አላምንም። ነገር ግን እነዚህ መረጃዎች በመንግሥት በኩል በቂ ጥበቃ ተደርጎላቸው በክልሉ ውስጥ ለተፈጸመው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ያላቸው አስተዋጽኦ በአግባቡ ሊመረመር ይገባል፤

    (ኛ) በOMN የተላለፉ የዘር ተኮር ቅስቀሳ ቪዲዮዎች እና ዘገባዎች በእጃችው ላይ የሚገኝ እና ጉዳዩ የሚያሳስባችው ግለሰቦች፤ እንዲሁም በተለያዩ የክልሉ ከተሞች እና አንዳን አካባቢዎች የተፈጸሙ ዘር ተኮር የሆኑ ጥቃቶችን የሚያሳዩ የፎቶ ግራፍ፣ የቪዲዮ እና ሌሎች ዝርዝር መረጃዎች ያላችሁ ሰዎች በዚህ የኢሜል አድራሻ end.empunity.eth@gmail.com እንድታቀብሉን በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።

    ዘር ተኮር ጥቃት ይቁም!

    አቶ ያሬድ ኃይለማርያም መቀመጫውን ጄኔቭ ከተማ፥ ስዊዘርላንድ ያደረገ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ (Association for Human Rights in Ethiopia) የተባለ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ናቸው።

    ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በአፋጣኝ ይቁም

    Anonymous
    Inactive

    የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን አስመልክቶ የኦሮሚያ ክልል መሪ አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያስተላለፉት መልዕክት

    አዲአ አበባ (EBC) – የታዋቂዉና ተዋዳጁ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ አስመልክቶ ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስትዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሀዘናቸውን ገለፁ።

    በአዲስ አበባ ከተማ በአቃቂ ክፍለ ከተማ ጀግናችን፣ የቅርብ አካላችን የትግልና የለዉጥ ምልክት የሆነዉ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ በጥይት መመታቱን ሰምቻለሁ ሲሉ አሳዛኙ ዜና እንዴት እንደደረሳቸው አስረድተዋል። ሕይወቱንም ለማትረፍ ጥረት ቢደረግም ሕይወቱ ሊተርፍ አለመቻሉንም ነው ያስታወቁት።

    በአርቲስቱ ህልፈተ ሕይወት እንደ ግለሰብና እንደ አብሮ አደግ አብሮም እንደኖረ ሰዉ እንደ ታጋይና የትግል አጋር እንደ የችግር ጊዜ ጀግና ትልቅ ሀዘን ተሰምቶኛል ብለዋል ርዕሰ መስተዳደሩ።

    ሃጫሉ ሁንዴሳ አርቲስት ብቻ ሳይሆን ታጋይም ነዉ ያሉት ርዕሰ መስትዳደሩ፥ ለእኔ ደግሞ ወንድሜም መካሪዬም ነዉ።  ይህንን ጀግና ነዉ ያጣነዉ ብለዋል አቶ ሽመልስ።

    የዚህ ጀግና ግድያም እንደቀላል እና ለቀላል ነገር የተፈጸመ ወንጀል አይደለም። ታስቦበት እና ታቅዶበት የተፈጸመ ድርጊት ነዉ። ይሄ ምንም ጥርጥር የለዉም ሲሉም ነው አቶ ሽመለስ የገለጹት። በዚህ ወንጀል የተጠረጠሩ የተወሰኑት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የገለጹት ርዕሰ መስትዳደሩ፥ ምርመራም እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።

    የጸጥታ አካላት በሁሉም አቅጣጫ ተሰማርቷል። የዚህ ግድያ ዓላማም ሕዝብና ሕዝብን በማጋጨት፣ ሀገር ለማፍረስ፣ ሲዝቱ የነበሩ ኃይሎች ድርጊት ነው ብለዋል።

    ከለዉጡ ወዲህ እንደዚህ ዓይነት ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል። አብዛኛዎቹን በማክሸፍ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ብሔር ብሔረሰቦች አንድ ላይ ቆመዋል። አሁን ያለዉን ለዉጥ ለማደናቀፍ ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል ሲሉ አስረድተዋል። ርዕሰ መስተዳደሩ እንደገለጹት፥ ይህንን ለማክሸፍ የኦሮሚያ ፖሊስና የሀገሪቱ የጸጥታ ኃይሎችም ትልቅ ሥራ ሠርተዋል ብለዋል። ዛሬ ደግሞ ይህንን የግድያ ወንጀል በመፈጸም ብሄር ብሄረሰቦችን ለማጋጨት ሀገር ለማፍረስ፣ አቅደዉ እንደተነሱ ጥርጥር የለዉም ነው ያሉት። ለዚህ ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች እርስ በርስ በመደማመጥ፣ አንድላይ በመቆም ጀግናችን የከፈለለትን መስዋዕትነት፣ ይህ ለዉጥ እንዲሳካ እጅ ለእጅ ተያይዘን ሁሉም ሰዉ በእርጋታ ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ እንድንሻገር ጥሪ አቅርበዋል።

    መንግሥታዊ መዋቅሩም ይህንን አደጋ ለመታደግ በአንድነት ሊቆም ይገባል ብለዋል አቶ ሽመልስ አብዲሳ። ለቤተሰቦቹ ፣ ለኦሮሞ ሕዝብና ለመላዉ የሀገራችን ሕዝቦች መጽናናትን እንደሚመኙ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገልጸዋል።

    ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በተወዳጁና ጀግናው አርቲስት ሃጫሉ ሞት የተሰማቸውን ከባድ ሀዘን ገልፀዋል።

    ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፥ “ሃጫሉ ቢሞትም መሞት የማይችል ሥራ ሠርቷል። ማንም ይሁን ማን ሃጫሉን የገደለው ሰው ከሕግ ማምለጥ አይችልም። የእኩይ እና አስነዋሪ ሥራውን ዋጋ በሕግ ያገኛል። የአርቲስት ሃጫሉን ነብስ ፈጣሪ በገነት ያኑር! ለቤተሰቡና ለመላው ሕዝባችን ፈጣሪ ትዕግስቱን፣ ብርታትና መጽናናትን ይስጠን!” ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባስተላለፉት የሐዘን መልእክት ደግሞ፥ “ለመላው የሀገራችን ሕዝቦች፥ ውድ ሕይወት አጥተናል። የዚህ ድንቅና አንፀባራቂ ወጣት አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሕይወት መቀጠፍ ከተሰማ ጀምሮ በከባድ ሀዘን ውስጥ ለምንገኝ ሁሉ መፅናናትን እመኛለሁ ። የዚህን ክፉ ድርጊት ሙሉ የፖሊስ ምርመራ ሪፖርት እየተጠባበቅን እንገኛለን። የድርጊቱን መጠን በመረዳት በሀገራችን ውስጥ ስለሚከናወኑ እንቅስቃሴዎች ትኩረት ሰጥተን የምንከታተልበት ወቅት ላይ ነን። ሀዘናችንን ራሳችንን በመጠበቅ እና ተጨማሪ ወንጀልን በመከላከል እንግለፅ” ብለዋል።

    ሃጫሉ ሁንዴሳ

    Anonymous
    Inactive

    የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባባር ኢትዮጵያን ማስቻል (Enabling Ethiopia) የተባለ የ5 ዓመት ፕሮጀክት ጀመረ

    አዲስ አበባ – የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኢትዮጵያን ማስቻል (Enabling Ethiopia) የተባለ የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባባር ጀመረ። የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽንና ማስተርካርድ ፋውንዴሽን በጋራ የጀመሩት የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ፈጠራን በማበረታታት፣ አካታችና አነቃቂነትን መሠረት በማድረግ ፖሊሲዎችን በማሻሻል በኢትዮጵያ የተጀመረውን የሥራ ፈጠራ እንቅስቃሴ የሚደግፍ ነው። ለዚህ ፕሮጀክት ማስተርካርድ ፋውንዴሽን የ11.8 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

    “ኢትዮጵያን ማስቻል” (Enabling Ethiopia) ፕሮጀክት ሲቀረጽ የሀገሪቱን የ5 ዓመት የሥራ ፈጠራ መሪ ዕቅድ ለማሳካት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ታምኖበት ነው። ፕሮጀክቱ ሀገሪቱን የሥራ ፈጠራ አጀንዳ እና የኮሚሽኑን አምስት ዓመት ስትራቴጂ ለመተግበር እንዲያግዝ ሆኖ የተቀረጸ ነው። እ.ኤ.አ በኦክቶበር 2019 የተጀመረው የኮሚሽኑ የአምስት ዓመት የሥራ ዕድል ፈጠራ መሪ ዕቅድ በግል ዘርፉና በፌደራል እንዲሁም በክልሎች ደረጃ ያሉ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በተናበበ መልኩ አስፈላጊውን ግብዓት በማቅረብ፣ ኢንቨስትመንትን በማመቻቸት በ 2015 (እ.ኤ.አ) 14 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ያለመ ነው።

    በዚህ ፕሮጀክት የረጅም ጊዜ ዕቅድ ለሥራ ፈጠራ ምቹ ምህዳር መፍጠር፣ አስፈላጊ የሰው ኃይል ካፒታልን ማዳበር እና ማክሮ ፖሊሲዎች ሥራ ፈጠራን እንዲያበረታቱ ማስቻል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራባቸዋል።

    ኢትዮጵያን ማስቻል ለ50 ሺህ ሴቶችና ወጣቶች በሚቀጥሉት 5 ዓመታት የሥራ ዕድል በማመቻቸት የመሪ ዕቅዱን አፈጻጸም ያግዛል። በተጨማሪም ለሥራ ዕድል ፈጠራ ተገቢውን ትኩረት የሚሰጡ ማክሮ ፖሊሲዎች እንዲቀረጹና አፈጻጸማቸውም ቀልጣፋ እንዲሆን የአቅም ግንባታ እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ፣ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ግንባታውን በማገዝ እንዲሁም ሃብት በማሰባሰብ ሥራዎች ላይ የበኩሉን ድርሻ ያበረክታል።

    ኢትዮጵያን ማስቻል ትኩረት ላልተሰጣቸው የማኅበረሰብ አካላት ማለትም የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ለሚሠሩት ሥራ ክፍያ የማያገኙ በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች፣ ስደተኞችና አካል ጉዳተኞችን ለመርዳት ዓላማ ያደረገ ነው። ፕሮጀክቱ የወጣቶችን ክህሎት ከማዳበር በተጨማሪ 200 ለሚሆኑ እምቅ ኃይል ያላቸው ሥራ ፈጣሪዎች ህልማቸውን እንዲያሳኩ ድጋፍ ያደርጋል።

    “ኢትዮጵያን ማስቻል ስሙም እንደሚያመለክተው ለበርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች መልካም አጋጣሚ ነው። በተለይም ትኩረት ያልተደረገባቸው ነገር ግን ለኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሥራ እንዲኖራቸውና ገቢ እንዲያገኙም ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው። በተጨማሪም ፕሮጀክቱ አዳዲስ ዕድሎችን ለማመቻቸት እና ለሥራ ፈጣሪዎች ፣ ለድርጅቶችና ለግሉ ሴክተር እንቅፋቶችን ለማስወገድ ትኩረት ፈጠራ ትብብርና ልህቀትን በመጠቀም ለሴቶችና ለወጣቶች ደህንነቱ የተጠበቀ ፣ የተከበረ እና አስደሳች የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ይተጋል” በማለት ዶ/ር ኤፍሬም ተክሌ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር የፕሮጀክቱን አስፈላጊነት ገልጽዋል።

    ፕሮጀክቱ የሚተገበረው በሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን መሪነት ሲሆን የፌዴራልና የክልል መንግሥታት፣ የኢንተርፕራይዝ ልማት አካላት እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ ተቋማትና የግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር ነው።

    “ይህ ፕሮጀክት በ2030 (እ.ኤ.አ) ለ10 ሚሊዮን ወጣቶች የተከበሩና አስደሳች የሥራ ዕድሎችን ለማመቻቸት ከተቀረጸው የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ወጣት አፍሪካ በሥራ ላይ ፕሮጀክት ጋር አብሮ የሚሄድ ሲሆን፥ ከኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ጋር ባለን ትብብር የኢትዮጵያ ወጣቶች እድገት እንዲያስመዘግቡና የሚያደርጉት አስተዋጽኦ በጉልህ እንዲታይላቸው የሚያደርግ ነው” በማለት አቶ አለማየሁ ኮንዴ ኮይራ፣ የማስተርካርድ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ገልጸዋል።

    • ኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን
      የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን እ.ኤ.አ በ2018 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት በጸደቀው ደንብ ቁጥር 435/2011 መሠረት ተጠሪነቱ ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆኖ የተቋቋመ መንግሥታዊ ተቋም ነው። ኮሚሽኑ በሁሉም የሥራ ዘርፎች የሥራ ዕድል ፈጠራ አጀንዳን የማስተዳደር ፣ የማቀናጀት እና የመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን በዚህም በመላ ሀገሪቱ የሚፈጠሩ ሥራዎች ዘለቄታ ያላቸው እንዲሆኑ እ.ኤ.አ በ2020 ዓ.ም ሦስት ሚሊዮን ፣ በ2025 ዓ.ም 14 ሚሊዮን ፣ በ 2030 ደግሞ 20 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ በማመቻቸትና ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም በፖሊሲና ስትራቴጂ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ ክትትል እና አቅም ግንባታ፣ በትብብርና ኢንቨስትመንት፣ በኢኖቬሽንና በመረጃ ትንተና እና ሥርዓት ማበልጸግ ላይ ትኩረት በማድረግ እስከ ሚያዝያ 2012 (እ.ኢ.አ) ድረስ 2.4 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ አድርጓል።

    ስለ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን የበለጠ መረጃ ለማግኘት ድረ-ገጹንና ማኅበራዊ ሚድያዎቹን ይጎብኙ፦
    https://www.jobscommission.gov.et
    https://twitter.com/Jobs_FDRE
    https://www.facebook.com/JobsCommissionFDRE/

    • ማስተርካርድ ፋውንዴሽን
      ማስተርካርድ ፋውንዴሽን (Mastercard Foundation) ሁሉም ሰው የመማር እና የመበልፀግ ዕድል ሊያገኝ የሚችልበት ዓለም እንዲኖር ይመኛል። ለዚህም ፋውንዴሽኑን ዋነኛ ተልዕኮውን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉ ሰዎች የትምህርት ልህቀት እና የፋይናንስ አካታችነትን ማሻሻል ነው። በዓለማችን ካሉ ታላላቅ ፋውንዴሽኖች መሐከል አንዱ የሆነው የማስተርካርድ ፋውንዴሽን አፍሪካ ላይ ዋነኛ ትኩረቱን ያደርጋል። እ.ኤ.አ በ2006 በማስተርካርድ ኢንተርናሽናል አማካኝነት ቢመሠረትም በአሁኑ ወቅት ራሱን በቻለ የቦርድ አመራር ስር ይተዳደራል። ማስተርካርድ ፋውንዴሽን በቶሮንቶ፥ ካናዳ እንዲሁም በኪጋሊ፥ ሩዋንዳ  ፅሕፈት ቤቶች አሉት።

    ስለ ማስተርካርድ ፋውንዴሽን የበለጠ መረጃ ለማግኘት ድረገጹንና ማህበራዊ ሚድያዎቹን ይጎብኙ፦
    http://www.mastercardfdn.org
    http://twitter.com/MastercardFdn

    ምንጭ፦ ማስተርካርድ ፋውንዴሽን

    ኢትዮጵያን ማስቻል (Enabling Ethiopia)

    Anonymous
    Inactive

    አዲስ አበባ ― ዳቦ፣ የመኖሪያ ቤት፣ መብራት እና ውሃ፣ የመሬት ቅርምት፣ ተረኝነተ፣ ሙስና፣ ግፍ፣ ወዘተ…

    (ያሬድ ኃይለማርያም)

    አዲስ አበባ ብዙ ስር የሰደዱ እና ውስብስብ ችግሮችን በጉያዋ የያዘች ጉደኛ ከተማ ነች። ልክ እንደ ከተማዋም አዲስ አበቤዎችም እንዲሁ ከዳቦ አንስቶ እጅግ ብዙ እና ውስብስብ የመብት እና የጥቅም ጥያቄዎች እንዳረገዙ ከዚህ ሁሉ ጭንቅ የሚገላግላቸው አስተዳደር ሲናፍቁ ዘመናት ተቆጥረዋል። ይህ ችግር በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ምን ያህል ሊከፋ እንደሚችል መገመት ይቻላል።

    የኋላውን ትተን ባለፉት ሁለት ዓመታት [የአዲስ አበበባ ከተማ መስተዳድር] እና የፌደራል መንግሥቱ ከተማዋን ለማዘመን በሚል አዳዲስ ዕቅዶችን ይዘው እና አንዳንዱንም ጀምረው የከተሜውን ቀልብ ለመግዛት ጥረዋል። እነዚህ የተጀመሩ አንዳንድ የልማት ዕቅዶች በእርግጥም ከተማዋን ለማዘመን ይረዱ ይሆናል። ነገር ግን የከተማዋን ሕዝብ የቆዩ እና ውስብስብ ችግሮች የሚፈቱ ስለመሆናቸው በቂ ጥናት መደረጉን የሚያሳዩ ነገሮች አይታዩም።

    አብዛኛዎቹ የመስተዳድሩ እንቅስቃሴዎች ገጽታ እና ምርጫ ተኮር ስለሆኑ የከተማዋን ገበና በእነዚህ ትላልቅ እና ከፍተኛ ገንዘብ በሚወስዱ ፕሮጀክቶች ለመሸፈን ጥድፊያም ላይ ያሉ ይመስላል። በሌላው ጎን ከንቲባው በአደባባይ የታሙባቸው እና ጠያቂ ቢኖር በሕግ በሚያስጠይቁ ተግባራት በማኅበረ ድኅረ ገጾች (social media) እና በሚዲያ ሲብጠለጠሉ ቆይተዋል። ከዚህ በሚከተሉት ጉዳዮች መስተዳድሩ አንድም ጊዜ አጥጋቢ ምላሽ ሲሰጥ አልተስተዋለም፤

    • በሕገ-ወጥ መንገድ ዘር-ተኮር የነዋሪነት መታወቂያ ማደል፣
    • በአንድ ሰው መኖሪያ ቤት ባለቤቱ ሳያውቅ ለበርካታ ሰዎች ዘር-ተኮር የመታወቂያ እና የቁጠባ ብድር መስጠት፣
    • በከተማዋ ፕላን መሠረት በየአካባቢው ለልጆች መጫወቻ እና ለልማት የተተው ክፍት ስፍራዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ እና ዘር-ተኮር በሆነ መንገድ በግለሰቦች እጅ እንዲገቡ ማድረግ፣
    • ሕገ-ወጥ መኖሪያዎች በሚል የሚደረጉ ዘር-ተኮር የቤት ማፍረስ እርምጃዎች፣
    • የከተማዋ ነዋሪ ከዕለት ጉርሱ ቆጥቦ የሠራቸውን የመኖሪያ ቤቶች [የኮንዶሚኒየም ቤቶች] አሁንም ዘር-ተኮር በሆነ መንገድ ለሌሎች አሳልፎ መስጠት፣
    • በከተማዋ መስተዳድር ውስጥ ዘር-ተኮር የሆነ የሠራተኞች ድልድልና ሽግሽግ ማድረግ እና በሌሎች ተመሳሳይ ጥፋቶች በአደባባይ መስተዳድሩ እየተወነጀለ ነው።

    እነዚህ ክሶች እውነት ተደርገው ከሆነ ሁለት ዋና የጥፋት ዓይነቶችን የያዙ ናቸው። አንደኛው ድርጊቶቹ ለማንም ጥቅም ተብሎ ይፈጸሙ የሀገሪቱን እና የከተማዋን ሕግ የጣሱ ናቸው። ሁለተኛው ጥፋት እያንዳንዱ ድርጊት ዘር-ተኮር መሆኑ ነው። ሌሎቸን የሕብረተሰብ ክፍሎች ለመጉዳት ሆን ተብሎ የተፈጸሙ ነው ባይባልም እንኳ አንድን ዘር ባልተገባ መልኩ፣ ስልጣንን ከለላ በማድረግ እና ሕግን በተላለፈ መልኩ ለመጥቀም የተፈጸሙ ናቸው መባሉ ነው።

    በእነዚህ ክሶች ላይ መስተዳድሩ በድፍኑ አልፈጸምኩም ከማለት ባለፈ ወቀሳዎቹን በዝርዝር እና በማስረጃ ሲያስተባብል አይታይም። የእነዚህን ጉዳዮች ክብደት ከግምት በማስገባት የፌዴራል መንግሥቱ በጉዳዩ ውስጥ ጣልቃ መግባት እና ገለልተኛ አጣሪ አካል መድቦ ለእነዚህ የሕዝብ ብሶቶች በአፋጣኝ ምላሽ ቢሰጥ ጥሩ ነው። ይህን ቸል ማለት ድርጊቶቹ የፌደራል መንግሥቱን ድጋፍ የተቸሩ ያስመስላቸዋል። እነዚህን የሕዝብ ጥያቄዎች ወደ ጎን ለመግፋትም ሆነ በዳቦና በዘይት እደላ ለመሸፈን ከተሞከረ ግን ሌላ የፖለቲካ ቀውስ ማስከተሉ አይቀርም። አዲስ አበቤዎችም ያቄሙበትን ፖርቲ እንዴት መቅጣት እንደሚችሉ የሚያውቁበት መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ምርጫ 97ን ማስታወሱ በቂ ነው።

    አቶ ያሬድ ኃይለማርያም መቀመጫውን ጄኔቭ ከተማ፥ ስዊዘርላንድ ያደረገ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ (Association for Human Rights in Ethiopia) የተባለ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ናቸው።

    አዲስ አበባ

    Anonymous
    Inactive

    ኢትዮጵያ ውስጥ በግዙፍነቱ ቀዳሚ የሆነው ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ

    አዲስ አበባ (ፋና) – በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባውና በሰዓት 80 ሺህ ዳቦ የሚያመርተው ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ። በፋብሪካው ምርቃ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በምረቃው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ፋብሪካው የዳቦ ፋብሪካ ብቻ ሳይሆን በምግብ ራሳችንን የመቻል ፍላጎታችንን፣ ከድህነት የመውጣት ጥማትን እና የብልፅግና ጎዳናን አመላካች ነው ብለዋል።

    በኢትዮጵያ በ10 ወራት ፋብሪካ ገንብቶ ማጠናቀቅ የሚታሰብ አልነበረም፤ በተለይም ለሚድሮክ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፥ ሚድሮክ ከነበረበት ድክመት ተላቆ ፋብሪካውን በዚህ ፍጥነት ማጠናቀቅ መቻሉ ለሌሎችም ትምህርት የሚሆን ነው ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አክለውም መንግሥት በቀጣይ ሁለት ዓመታት ስንዴን ከውጭ ማስገባት የማቆም ፍላጎት እንዳለው በመግለጽ፤ ለዚህም የሙከራ ምርቶች መጀመራቸውን አስታውቅዋል። ስንዴ ማምረት ብቻ ሳይሆን ምርቶቹን ወደ አግሮ ኢንዱስትሪ መቀየር አስፈላጊ መሆኑንም የገለፁ ሲሆን፥ ለዚህም ለግሉ ዘርፍ ጥሪ መቅረቡን አስታውቅዋል።

    መንግሥት ላቀረበው ጥሪ ሼክ መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ፈጣን ምላሽ መስጠታቸውን በመግለፅ፥ ሸገር ዳቦ ፋብሪካ እውን እንዲሆን በማድረጋቸውም ምስጋናቸውን ያቀረቡላቸው ሲሆን፥ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሌም ከጎናቸው እንደሆነ አረጋግጠዋል።

    መሰል የዳቦ ማምረቻዎችን ከአዲስ አበባ ውጪ በክልል ከተሞችም ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑን እና ለዚህም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሌሎች ከተሞች መሰል መለስተኛ የዳቦ ፋብሪካዎችን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሯን አስታውቀዋል። በተጨማሪም የዱባይ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ዛይድ አልናህያንም ከፍ ያለ ፋብሪካ ቃል መግባታቸውን እና ይህም በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገባ መሆኑንም ነው ያስታወቁት።

    እነዚህ አሁን የተገነቡ እና ወደ ፊት የሚገነቡ ፋብሪካዎች በቀን ዳቦ ለማግኘት ለሚያዳግታቸው ሕፃናት ዳቦ እንዲያገኙ የሚያስችሉ መሆናቸውን ነው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ።

    “አዲስ አበባን፣ ክልሎችን፣ ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን እንለውጣለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፥ “ኢትዮጵያ የጀመረችውን በሙሉ ታጠናቅቃለች፤ ይህም በየአደባባዩ እየጮኸች ሳይሆን ሪቫን እየቆረጠች ነው” ብለዋል።

    ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማም፥ ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተገንብቶ እውን እንዲሆን ለተሳተፉ አካላት መስጋና አቅርበዋል። የሸገር ዳቦ ፋብሪካ መገንባት የከተማውን ነዋሪዎች የኑሮ ጫና ይቀንሳል ያሉት ኢ/ር ታከለ፥ በቀጣይም የከተማዋ ነዋሪዎችን ጥያቄ የሚመልሱ ሥራዎችን በማቀድ ወደ ሥራ መገባቱብንም አስታውቅዋል።

    የሚድሮክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብነት ገብረ መስቀል በበኩላቸው፥ ሜድሮክ ኢትዮጵያ ለአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ነዋሪ ሕዝብ በከፍተኛ ጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ዳቦ አምርቶ ማቅረብ እንዲቻል ሸገር ዳቦ ፋብሪካን ገንብቶ ለፍሬ አብቅቷል ብለዋል።

    በ41 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ፋብሪካው፥ የዳቦ እና የዱቄት ፋብሪካ፣ የሻይ ቅጠል ማቀነባበሪያ እና 120 ሺህ ኩንታል ስንዴ ማከማቸት የሚያስችል 4 ጎተራ እንዳለው አስታውቀዋል። በ6 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው የዳቦ መጋገሪያ ፋብሪካው በሰዓት 80 ሺህ ዳቦ የሚያመርት መሆኑን እና በቀን በሶስት ፈረቃ እስከ 2 ሚሊየን ዳቦ የሚያመርት መሆኑ ገልፀዋል።

    ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ግንባታው በአጠቃላይ በ900 ሚሊዮን ብር ወጪ መከናወኑን ያስታወቁት አቶ አብነት፥ አጠቃላይ ወጪውም በሚድሮክ እህት ኩባንያዎች የተሸፈነ መሆኑንም አስታውቅዋል። ፋብሪካው ከምርት እስከ ማከፋፈል ሂደት ቁጥራቸው 3 ሺህ 400 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልፀዋል።

    ምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት

    ሸገር ዳቦ ፋብሪካ

    Anonymous
    Inactive

    ኢትዮጵያ ውስጥ በግዙፍነቱ ቀዳሚ የሆነው ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ

    አዲስ አበባ (ፋና) – በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባውና በሰዓት 80 ሺህ ዳቦ የሚያመርተው ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ። በፋብሪካው ምርቃ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በምረቃው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ፋብሪካው የዳቦ ፋብሪካ ብቻ ሳይሆን በምግብ ራሳችንን የመቻል ፍላጎታችንን፣ ከድህነት የመውጣት ጥማትን እና የብልፅግና ጎዳናን አመላካች ነው ብለዋል።

    በኢትዮጵያ በ10 ወራት ፋብሪካ ገንብቶ ማጠናቀቅ የሚታሰብ አልነበረም፤ በተለይም ለሚድሮክ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፥ ሚድሮክ ከነበረበት ድክመት ተላቆ ፋብሪካውን በዚህ ፍጥነት ማጠናቀቅ መቻሉ ለሌሎችም ትምህርት የሚሆን ነው ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አክለውም መንግሥት በቀጣይ ሁለት ዓመታት ስንዴን ከውጭ ማስገባት የማቆም ፍላጎት እንዳለው በመግለጽ፤ ለዚህም የሙከራ ምርቶች መጀመራቸውን አስታውቅዋል። ስንዴ ማምረት ብቻ ሳይሆን ምርቶቹን ወደ አግሮ ኢንዱስትሪ መቀየር አስፈላጊ መሆኑንም የገለፁ ሲሆን፥ ለዚህም ለግሉ ዘርፍ ጥሪ መቅረቡን አስታውቅዋል።

    መንግሥት ላቀረበው ጥሪ ሼክ መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ፈጣን ምላሽ መስጠታቸውን በመግለፅ፥ ሸገር ዳቦ ፋብሪካ እውን እንዲሆን በማድረጋቸውም ምስጋናቸውን ያቀረቡላቸው ሲሆን፥ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሌም ከጎናቸው እንደሆነ አረጋግጠዋል።

    መሰል የዳቦ ማምረቻዎችን ከአዲስ አበባ ውጪ በክልል ከተሞችም ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑን እና ለዚህም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሌሎች ከተሞች መሰል መለስተኛ የዳቦ ፋብሪካዎችን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሯን አስታውቀዋል። በተጨማሪም የዱባይ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ዛይድ አልናህያንም ከፍ ያለ ፋብሪካ ቃል መግባታቸውን እና ይህም በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገባ መሆኑንም ነው ያስታወቁት።

    እነዚህ አሁን የተገነቡ እና ወደ ፊት የሚገነቡ ፋብሪካዎች በቀን ዳቦ ለማግኘት ለሚያዳግታቸው ሕፃናት ዳቦ እንዲያገኙ የሚያስችሉ መሆናቸውን ነው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ።

    “አዲስ አበባን፣ ክልሎችን፣ ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን እንለውጣለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፥ “ኢትዮጵያ የጀመረችውን በሙሉ ታጠናቅቃለች፤ ይህም በየአደባባዩ እየጮኸች ሳይሆን ሪቫን እየቆረጠች ነው” ብለዋል።

    ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማም፥ ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተገንብቶ እውን እንዲሆን ለተሳተፉ አካላት መስጋና አቅርበዋል። የሸገር ዳቦ ፋብሪካ መገንባት የከተማውን ነዋሪዎች የኑሮ ጫና ይቀንሳል ያሉት ኢ/ር ታከለ፥ በቀጣይም የከተማዋ ነዋሪዎችን ጥያቄ የሚመልሱ ሥራዎችን በማቀድ ወደ ሥራ መገባቱብንም አስታውቅዋል።

    የሚድሮክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብነት ገብረ መስቀል በበኩላቸው፥ ሜድሮክ ኢትዮጵያ ለአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ነዋሪ ሕዝብ በከፍተኛ ጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ዳቦ አምርቶ ማቅረብ እንዲቻል ሸገር ዳቦ ፋብሪካን ገንብቶ ለፍሬ አብቅቷል ብለዋል።

    በ41 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ፋብሪካው፥ የዳቦ እና የዱቄት ፋብሪካ፣ የሻይ ቅጠል ማቀነባበሪያ እና 120 ሺህ ኩንታል ስንዴ ማከማቸት የሚያስችል 4 ጎተራ እንዳለው አስታውቀዋል። በ6 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው የዳቦ መጋገሪያ ፋብሪካው በሰዓት 80 ሺህ ዳቦ የሚያመርት መሆኑን እና በቀን በሶስት ፈረቃ እስከ 2 ሚሊየን ዳቦ የሚያመርት መሆኑ ገልፀዋል።

    ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ግንባታው በአጠቃላይ በ900 ሚሊዮን ብር ወጪ መከናወኑን ያስታወቁት አቶ አብነት፥ አጠቃላይ ወጪውም በሚድሮክ እህት ኩባንያዎች የተሸፈነ መሆኑንም አስታውቅዋል። ፋብሪካው ከምርት እስከ ማከፋፈል ሂደት ቁጥራቸው 3 ሺህ 400 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልፀዋል።

    ምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት

    ሸገር ዳቦ ፋብሪካ

Viewing 15 results - 151 through 165 (of 495 total)