Search Results for 'አዲስ አበባ'

Home Forums Search Search Results for 'አዲስ አበባ'

Viewing 15 results - 451 through 465 (of 495 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ድረስ የካንሰር ህክምና አገልግሎት በብቸኝነት ሲሰጥ የነበረው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንደነበረና የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ይህን አገልግሎት መጀመሩ ለታካሚዎች ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል።

    አዲስ አባባ (ዋልታ/ ሰሞነኛ) – የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ከመስከረም 2 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የካንሰር ህክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቋል። ሆስፒታሉ ህክምናውን ከጀመረበት ቀን አንስቶ እስካሁን ድረስ ከ300 በላይ የካንሰር ታማሚዎችን በተመላላሽ ማከሙንም ገልጿል።

    በሆስፒታሉ የካንሰር ህክምና ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አብዲ አደም የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ይህንን ህክምና መጀመሩ ከዚህ በፊት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በቦታ ጥበት ምክንያት በወረፋ ለሚንገላቱ ታካሚዎች መፍትሔ ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል።

    እስካሁን በተመላላሽ ህክምና ለታካሚዎች አገልግሎት ሲሠጥ መቆየቱን የገለጹት ዶ/ር አብዲ በቅርቡ አስተኝቶ ማከም የሚያስችል ወደ 350 የሚጠጋ አልጋ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል።

    ዋልታ ያነጋገራቸው በሆስፒታሉ የካንሰር ታካሚዎች እንደገለጹት ከዚህ በፊት ህክምናውን ለማግኘት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እስከ ስድስት ወር እንደሚወስድ ገልጸው አሁን ግን በቅዱስ ጳውሎስ አገልግሎት መጀመሩ ያለምንም ወረፋ ህክምናን ለማግኘት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

    Ethiopia: Are Ethiopian hospitals constructed in environment-suitable and climate-friendly way?

    በኢትዮጵያ የተደራጀ የጥናት ውጤት ባይኖርም በግምት በዓመት ከ160 ሺህ በላይ የካንሰር ተጠቂዎች እንደሚኖሩ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። እ.ኤ.አ በ2012 በተደረገ ጥናት ኢትዮጵያ ውስጥ በዓመት ውስጥ ከሚሞቱ ሰዎች ውስጥ 5.8 በመቶ የሚሆኑት በካንሰር ምክንያት እንደሚሞቱ ይጠቁማል። በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስር የብሔራዊ የካንሰር ቁጥጥር ፕላን ባወጣው በዚህ ጥናት ምንም እንኳን ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ አጠቃላይ የሕዝብ ቆጠራን ተገን ያደረገ አሀዝ (population-based data) ባይኖርም ኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ 60,960 ሰዎች በተለያዩ ዓይነት የካንሰር በሽታዎች እንደሚጠቁና 44,000 ሰዎች ደግሞ በካንሰር ምክንያት እንደሚሞቱ ያትታል። በዚህም የካንሰር በሽታ በከፍተኛ ቁጥር ሰዎችን ከሚያጠቁ አራት ተለላፊ ካልሆኑ በሽታዎች [non-communicable diseases] ውስጥ ከልብ በሽታ ቀጥሎ ሁለተኛው ነው። (እነዚህ አራቱ ተለላፊ ከሆኑ በሽታዎች የልብ በሽታ፣ ካንሰር፣ የስኳር በሽታ እና የሳንባ በሽታ ሲሆኑ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎ ከሚሞቱት ሰዎች ቁጥር 80 በመቶ የሚሆነው ከእነዚህ በሽታዎች በአንዱ ምክንያት የሚሞት ነው።) ኢትዮጵያ ውስጥ ወንዶች ላይ የደምየ አንጀት ካንሰሮች፣ ሴቶች ላይ ደግሞ የጡት ካንሰር በከፍተኛ መጠን እንደሚታይ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ሪፖርት ያሳያል።

    የዓለም ጤና ድርጅት ለአንድ ሚሊዮን ሰዎች አንድ የካንሰር ህክምና ተቋም ሊኖር እንደሚገባ ቢመክርም በኢትዮጵያ ግን ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በብቸኝነት የህክምናውን አገልግሎት ይሰጥ እንደነበርና እ. ኤ.አ በ2017 በወጣ አሃዝ ከ6,000 በላይ የካንሰር ታካሚዎችን እያከመ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የስዊዘርላንዱ መድኃኒት አምራች ግዙፍ ኩባንያ ኖቫትሪስ (Novartis) እ.ኤ.አ በ2017 ባወጣው ዘገባ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ በቁጥር ስምንት ኦንኮሎጂስቶች (የካንሰር ሀኪሞች) ብቻ እንዳላት አስታውቋል። ሌላ ተመሳስይ ጥናት ደግሞ ብቸኛው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ካሉት 627 ነርሶች ውስጥ 26ቱ ብቻ የካንሰር ህክምና ነርሶች እንደሆነ ይጠቁማል።

    ዋልታ | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል

    Semonegna
    Keymaster

    አቶ ሽመልስ አብዲሳ ኡፍታላ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሲሾሙ፥ ወይዘሮ ቢልለኔ ስዩም ወልደየስ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ሆነው ተሹመዋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – አቶ ሽመልስ አብዲሳ ኡፍታላ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው በዛሬው ዕለት (ጥቅምት 26 ቀን 2011 ዓ.ም) ተሾሙ።

    አቶ ሽመልስ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩትን አቶ ፍጹም አረጋ ተክተው ነው የተሾሙት። በዚህም አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተሰጣቸው ኃላፊነት መሠረት የፕሬስ ሴክቴሪያት ጽህፈት ቤት፣ የብቃትና ፖሊሲ ምዘና ጽህፈት ቤት፣ የአገር ደህንነት ጉዳይ አማካሪ ጽህፈት ቤትና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትን ይመራሉ ተብሏል።

    ከዚህ በፊት የነበሩት አቶ ፍጹም አረጋ ወደ ቀድሞ ቦታቸው፥ ማለትም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ተመልሰዋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚነት የነበሩት በላቸው መኩሪያ (ዶ/ር) በመስከረም ወር መጀመሪያ ሳምንት “የግል/ የቤተሰብ ጉዳይ” በሚል ምክንያት ኃላፊነታቸውን (ብሎም ከኮሚሽኑ በአጠቃላይ) መልቀቃቸው ይታወሳል።

    አቶ ሽመልስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰብአዊ መብት የማስትሬት ዲግሪ፣ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ አፍሪካ (UNISA) ደግሞ በፖለቲካል ፍልስፍና ሁለተኛ የማስተሬት ድግሪ አግኝተዋል።

    በተያያዘ ዜና፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ስር የፕሬስ ሴክሬታሪ ጽህፈት ቤት የተቋቋመ ሲሆን ወይዘሮ ቢልለኔ ስዩም ኃላፊ ተደርገው ተሹመዋል። ወይዘሮ እና ቢልለኔ ስዩም ስነ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጸሐፊ/ደራሲ ሲሆኑ፣ የሴቶች መብት ላይ እና በጾታ እኩልነት ላይ የሚሠራ ዕሩያን ሶሉሽንስ (Earuyan Solutions) የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት መሥራችና ኃላፊ ነበሩ። በትምህርታቸውም የማስተርስ ዲግሪ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፒስ-ኮስታሪካ፣ ሌላ የማስተርስ ዲግሪ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኢንስብሩክ (ኦስትርያ) እና የባችለርስ ዲግሪ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ብሪቲሽ ኮለምብያ (ካናዳ) አላቸው።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ሽመልስ አብዲሳ

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ) – የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ 34ኛውን እና የዓመቱ የመጀመሪያውን ሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት ምግብ ዋስትና በኢትዮጵያ በተሰኘ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ መስከረም 24 ቀን 2011 ዓ.ም ውይይት አካሄደ።

    ገለፃውን ያቀረቡት ዶ/ር ዓለማየሁ ሥዩም (በዓለም አቀፍ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ተቋም (IFPRI) ውስጥ ከፍተኛ ተመራማሪ) ሲሆኑ፣ አቅራቢው በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና እና በምግብ እራስን መቻል መካከል ያለው ብያኔ የተዛነፈ በመሆኑ በምሁራን እና በፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ ወጥ የሆነ አረዳድ እንዳይኖር አድርጓል ብለዋል። ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ማለት በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በአገር፣ በክፍለ-ዓለምና በዓለም ደረጃ፤ ሁሉም ሰዎች፣ ዘወትር፣ በመጠኑ በቂ የሆነ፣ በጤና ላይ አደጋን የማያስከትል እና የተመጣጠነ የአመጋገብ ፍላጎትም ሆነ የአይነት ምርጫ ቁሳዊናኢኮኖሚያዊ ተደራሽነት ሲኖራቸው እንደሆነና ምንም ዓይነት ወቅታዊ መዋዠቅን፣ ያልተጠበቁ ሰው ሠራሽም ሆነ የተፈጥሮ ክስተቶችን (አደጋዎችን) መቋቋም የሚችል ማህበረሰብ ሲፈጠር እንደሆነ አቅራቢው ይገልፃሉ።

    ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ መካከለኛ መጠን ያላቸው ከተሞች በዓመት በአማካይ ከ5-6 በመቶ ዕድገት እያሳዩ መሆኑ እና መንግስት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማዘመን እና ምርታማነትን በመጨመር ገበያ-ተኮር ኢኮኖሚ ለመዘርጋት ጥረት እያደረገ እንደሆነ አብራርተዋል። ነገር ግን ዛሬም የግብርና ምርታማነት በጣም ዝቅተኛ መሆኑ፣ የህፃናት መቀንጨር በአማካይ 38 በመቶ መድረሱ፣ የምግብ እህል እጥረት የሚያጋጥማቸው ዜጎች ቁጥር እጅግ መጨመሩ እና ከፍተኛ የምግብ እህል/ሸቀጥ ከውጪ እንዲገባ መደረጉ “የምግብ ዋስትና ጉዳይ አሁንም እልባት ያላገኘ አገራዊ ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል” ብለዋል ዶ/ር ዓለማየሁ።

    ለእንደዚህ ዓይነት የምግብ ዋስትና ስጋት ያጋልጣሉ ያሏቸውንም ምክንያቶች ዶ/ር ዓለማየሁ ዘርዝረዋል። “በገጠር የተወሳሰበ የመሬት ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ ሁኔታ (የይዞታ ባለቤትነትና አጠቃቀም ሥርዓት)፣ የእርሻ መሬት ይዞታ ማነስና መበጣጠስ፣ የመሬት ምርታማነት መቀነስ/የአፈር ለምነት መቀነስ፣ የሥራ ዕድል መጥበብ እና ወጥነት የጎደለው የፖሊሲ አፈፃፀም” ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል ዶ/ር ዓለማየሁ። ችግሩም ህፃናትን ለበሽታና ለሞት እንዲሁም ለአካልና አእምሮ ህመም ከመዳረጉ እና የመማርና የማምረት አቅምን ከማኮሰስ አልፎ ድህነት እንዲቀጥል ያደርጋል ተብሏል።

    በሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት መድረኩ ከችግሩም ለመላቀቅና የተሟላ ማህበራዊ ዋስትና ለመፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየቶች ተነስተዋል። በውይይቱም ከፍተኛ የግብርና ማስፋፊያ ተግባራት በማከናወን አርሶ አደሮች የተሻለ መረጃ እንዲያገኙና የተሻሻሉ የግብርና ዘዴዎችን እንዲያላምዱ ማትጋት፤ ዘመናዊ የመሠረተ-ልማት ዝርጋታ ማድረግ፤ በትምህርትና በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በማካሄድ አማካይ በህይወት የመኖሪያ እድሜን ማሳደግ እና የምግብ ዋስትና ተጋላጭነትን እያጠኑ ስልት የሚቀይሱ ጠቃሚ ተቋማትን መፍጠር (የፖሊሲ ተቋማት፣ የንብረት ባለቤትነት መብቶች፣ የገበያ፣ የአምራቾች ማህበራት፣ የማህበራዊ ዋስትና ስልት፣ የቅድመ-ማስጠንቀቂያ ዘዴዎች) ቅድሚያ የሚፈልጉ አገራዊ ተግባራት መሆናቸው ተነስቷል።

    ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪም ከ20-25 ዓመት የሚደርስ የግብርናው ዘርፍን ሊያዘምን የሚችል አሠራር በተለይ ደረቅ-አብቃይ አካባቢዎችን፣ ለድርቅ-ተጋላጭቦታዎችን እና የተጎዱ አካባቢዎችን የሚያሻሽል የተቀናጀ መርሐ-ግብር መንደፍ አስፈላጊ እንደሆነ ተሳታፊዎች አንስተዋል። እንደ ህዝብ ቁጥር መጨመርና የአየር ንብረት መለዋወጥ ያሉ አባባሽ ሁኔታዎችንም መቋቋም የሚያስችል የኢኮኖሚ ዝግጁነት መገንባት የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማስጠበቅ ይረዳልም ብለዋል።

    በጥቅሉ የገለፃው አቅራቢና ተሳታፊዎች፣ ተቋማት መገንባትና በስፋትና በተፈለገው የህብረተሰብ ፍላጎት ልክ የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግር መፈጠር አለበት በማለት የዕለቱን ውይይት አጠናቀዋል።

    ውይይቱን ፕሮፌሰር በላይ ካሳ (የፓን አፍሪካን ዩኒቨርሲቲ ጊዜያዊ ከፍተኛ አመራር) የመሩት ሲሆን፣ ከ110 በላይ የሚሆኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ባለሙያዎች፣ የአካዳሚው አባላትና የሚዲያ አካላት ተሳትፈውበታል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ

    የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ

    Semonegna
    Keymaster

    ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ከሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የመቄዶንያ የአረጋውያንና አእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከልን ከጎበኙ በኋላ የ15 ዘመናዊ ባለሞተር ዊልቸሮችን ድጋፍ አድርገዋል።

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታየቸው ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የአካል ጉዳተኞች መንቀሳቀሻ ወንበር (ዊልቸር/wheelchair) ድጋፍ አደረጉ።

    ቀዳማዊ እመቤቷ የ2011 ዓ.ም አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በማዕከሉ ለሚገኙ አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን የምሳ ግብዣ ባደረጉበት ወቅት ባለቤታቸው ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ማዕከሉን እንደሚጎበኙ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።

    በመሆኑም ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ከሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ማዕከሉን ከጎበኙ በኋላ የ15 ዘመናዊ ባለሞተር ዊልቸሮችን ድጋፍ አድርገዋል። ድጋፉ የሚውለውም በማዕከሉ በከፋ የእንቅስቃሴ እክል ውስጥ ለሚገኙ አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መሆኑ ተገልጿል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በችግር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ወገን ሲደገፉ ማየት ጥልቅ ሞራልና ተስፋ እንደሚሰጥ ገልጸዋል። እውነተኛው አክሊል የሚገኘውም እንደዚህ ዓይነቱን ተግባር በመፈጸም ነው ሲሉም አሳስበዋል።

    “መናገር የማይችሉ እራሳቸውን መቆጣጠር የማይችሉ ሰዎችን የሚያየን ያየናል ብለው በንጹህ ልቦና ማገልገል መታደል ነው። እውነተኛው አክሊል የሚገኘው ከእንደዚህ አይነት ስፍራ ነው።እውነተኛውን የሚሹ ሰዎች ዝቅ ብለው መደገፍ የሚገባቸውን ሲደግፉ ሲያግዙ ማየት በኢትዮጵያ እንደዚህም አይነት ስራ የሚሰሩ ግለሰቦችን ማየት ጥልቅ ሞራል ተስፋ የሚሰጥ ነው።” በማለት ተናግረዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

    የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግና ሩህሩህ በመሆኑ ማዕከሉን በቀጣይነት እንደሚደግፍ እምነት እንዳላቸው የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፥ እርሳቸውም በተቻላቸው አቅም በማዕከሉ ያሉ አረጋውያንንና የአእምሮ ህሙማንን ለመጎብኘት ቃል ገብተዋል።

    “እኔ ልነግራችሁ የምፈልገው ነገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግ ህዝብ ነው። የማየት እድል ካገኘ ይህን የተቀደሰ ዓላማና ተግባር በመደገፍ ከጎናችሁ ሆኖ አልባሌ ቦታ የሚባክን ጉልበትና ሃብት ሰብስቦ እናንተን በማገዝ ከጎናችሁ በመሆን ቤተሰብ መሆኑን እንደሚያረጋግጥ ሙሉ እምነት አለኝ ፤እኔም አቅሜ በፈቀደ መጠን እናንተን በመጎብኘት ከጎናችሁ እንደምሆን ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ።” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

    የማዕከሉ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ብንያም በለጠ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን በተለይም ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች የጠቅላይ ሚንስትሩን አርአያ በመከተል በማዕከሉ የሚገኙ ወገኖቻቸውን እንድጎበኙ ጥሪ አቅርቧል።

    ለመልካም ሥራ ጊዜ መስጠት እንደሚያስፈልግ በመጠቆም አቶ ብንያም፥ “የዶክተር አብይን አርአያ ተከትለን ዛሬ መጥተው በመጎብኘታቸው ማንም ሰው ከፈለገ ጊዜ እንዳለውና ለእግዚአብሔር ሥራ ጊዜ ሊያንሰው እንደማይገባ ስለአስተማሩን፤ ከእርሳቸው የበለጠ ጊዜ የሌለው ሰው የለም፤ ኢትዮጵያን የሚያህል አገር እየመሩ ጊዜ የለኝም ቢሉ ተቀባይነት አለው። እና ሁላችሁም የመንግስት ሠራተኞችም ብትሆኑ፣ ሚንስትሮችም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችም የእርሳቸውን አርአያ በመከተል ሰዎችን በመርዳት ከእግዚአብሔር ዋጋ እንድናገኝና በዚህ ውሸት በሞላበት ዓለም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለመግለጽ እወዳለሁ።” ብሏል።

    ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታየቸው ያደረጉት ድጋፍም ለማዕከሉ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም አቶ ብንያም አክሎ ተናግሯል።

    የመቄዶንያ የአረጋውያንና አእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል አርባ አረጋውያንና አእምሮ ህሙማን በመያዝ የተቋቋመ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን፤ ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት ወደ ሁለት ሺህ ለሚጠጉ ወገኖች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታየቸው

    Semonegna
    Keymaster

    ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በሒሳብ ዓመት ያስመዘገበው የተጣራ ትርፍ 728 ሚሊዮን ብር እንደሆነ የባንኩ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ይፋ ባደረገው ሪፖርት የተመለከተ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ145 በመቶ ብልጫ አለው።

    አዲስ አበባ (ኦኢባ) – ከተመሠረተ አሥረኛ ዓመቱን የያዘው ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በታሪኩ ከፍተኛ የትርፍ ዕድገት በማስመዝገብ በ2010 ዓ.ም የሒሳብ ዓመት (fiscal year) ከታክስ በፊት 938 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ።

    ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ቅዳሜ ጥቅምት 24 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ይፋ እንዳደረገው፣ የባንኩ የ2010 ዓ.ም የሒሳብ ዓመት የትርፍ መጠን ከቀድሞው የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከ140 በመቶ በላይ ዕድገት አሳይቷል።

    በቀደመው ዓመት ባንኩ ከታክስ በፊት 391 ሚሊዮን ብር ያስመዘገበ ሲሆን፣ የባንኩ ትርፍ በአንድ ዓመት ልዩነት የ547 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለውን ትርፍ ማስመዝገቡ የባንኩን የ2010 የሒሳብ ዓመት የትርፍ መጠን የተለየ አድርጎታል።

    ባንኩ በሒሳብ ዓመት ያስመዘገበው የተጣራ ትርፍ 728 ሚሊዮን ብር እንደሆነ የባንኩ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ይፋ ባደረገው ሪፖርት የተመለከተ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ145 በመቶ ብልጫ አለው።

    ኢትዮጵያ ውስጥ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ገንዘብን በሞባይል ስልክ ለማንቀስቀስ የሚያስችሉት ሲቢኢ ብር እና አሞሌ

    ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ያስመዘገበው የትርፍ ዕድገት ምጣኔ በባንክ ኢንዱስትሪው ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በዚህም ምክንያት የባንኩ የትርፍ ክፍፍል ወደ 54 በመቶ ከፍ ብሏል፡።

    የ2010 ዓ.ም በሒሳብ ዓመት በአብዛኛው ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት ሲሆን፣ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 19.9 ቢሊዮን ብር እንደደረሰና ጠቅላላ ሀብቱም 23.8 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተመልክቷል።

    መስከረም 11 ቀን 2001 ዓ.ም ተመሥርቶ ጥቅምት 15 ቀን 2001 ዓ.ም የመጀመሪያ ቅርንጫፉን አዲስ አበባ ውስጥ ደንበል ሲቲ ሴንተር ላይ ከፍቶ ሥራ የጀመረው ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በአሁኑ ወቅት በመላው ሀገሪቱ ከ200 በላይ ቅርንጫፎች አሉት።

    ምንጭ፦ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል (ኦኢባ)

    ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ

    Semonegna
    Keymaster

    የማህፀን በር ካንሰር ክትባት መሰጠት ያለበት ከ9 ዓመት ጀምሮ ላሉ ልጃገረዶች ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ባጋጠመው ክትባት እጥረት ምክንያት ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሆኑ ብቻ እንደሚሰጥ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

    አዲስ አበባ (የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር) – ከመጪው ህዳር ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ የማህፀን በር ካንሰር ቅድመ መከላከያ ክትባት በአገር አቀፍ ደረጃ መሰጠት ሊጀመር መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ክትባቱ ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ልጃገረዶች በጤና ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶችና በጊዜያዊ የክትባት ማዕከሎች ይሰጣል። የማህፀን በር ካንሰር ክትባት በሙከራ ደረጃ በትግራይና ኦሮሚያ በተመረጡ ወረዳዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሰጥ ቆይቷል።

    በሚኒስቴሩ የክትባት ባለሙያ አቶ ጌትነት ባየ እንዳሉት፥ ክትባቱን ለማስጀመር በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ለሚገኙ ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና ይሰጣል።

    “ከመጪው ህዳር ወር ጀምሮም በአገር አቀፍ ደረጃ ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ልጃገረዶች ክትባቱ መሰጠት ይጀምራል” ብለዋል አቶ ጌትነት ።

    የማህፀን በር ካንሰር ክትባት መሰጠት ያለበት ከ9 ዓመት ጀምሮ ላሉ ልጃገረዶች ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ባጋጠመው ክትባት እጥረት ምክንያት ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሆኑ ብቻ ነው የሚሰጠው።

    የማህፀን በር ካንሰር መንስኤው “ሂውማን ፓፒሎማቫይረስ” (Human papillomavirus) በሚባል ኢንፌክሽን የሚመጣ ሲሆን፥ የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) እንደሚያስታውቀው አግባብ የሆነ በሽታን የመከላከል አቅም ያላቸው ሴቶች (women with normal immune systems) በቫይረሱ ከተጠቁ በኋላ የማህፀን በር ካንሰር ምልክት ሳይታይባቸው ከ15 እስከ 20 ዓመታት ሊቆዩ እንደሚችሉ፣ ደካማ የሆነ በሽታን የመከላከል አቅም ያላቸው ሴቶች (women with weak immune systems) ደግሞ ምልክቱ ሳይታይባቸው ከ5 እስከ 10 ዓመታት ሊቆዩ እንደሚችሉ ያትታል።

    ለበሽታው ከሚያጋልጡት ምክንያቶች ውስጥ ዋነኞቹ ልጃገረዶች በለጋነት እድሜያቸው የግብረ ስጋ ግንኙነት መጀመርና ከተለያዩ ሰዎች ጋር ፆታዊ ግንኙነት ማድረግ ሲሆኑ፥ ሲጋራ ማጨስም ሌላው ምክንያት ነው።

    ከ30 እስከ 45 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ እና ወደ ህክምና ተቋማት መጥተው ምርመራ በማድረግ ራሳቸውን ከበሽታው መጠበቅ እንደሚኖርባቸው ይመከራል።

    በታዳጊ ሀገራት የማህፀን በር ካንሰር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ የካንሰር ዓይነቶች በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጧል። ከዚህ በተጨማሪ በዓለም ላይ እጅግ በብዛት ከሚታይባቸው ሀያ አገራት ውስጥ አስራ ዘጠኙ የአፍሪካ አገራት እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

    HPV Information Centre የሚባለው ድርጅት እ.ኤ.አ በሀምሌ ወር በ2017 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ ውስጥ በየ ዓመቱ 7,095 ሴቶች ማህፀን በር ካንሰር የሚጠቁ ሲሆን፣ በየዓመቱም 4,732 ሴቶች በዚሁ ካንሰር ምክንያት ለሞት እንደሚዳረጉ ዘግቧል።

    ምንጭ፦ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) እና የዓለም የካንሰር ምርምር ፈንድ (WCRF)

    የማህፀን በር ካንሰር

    Semonegna
    Keymaster

    አገር አቀፍ የተማሪ ወላጆች ህብረት ምሥረታ ላይ ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ግለሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተሳተፉበት ሲሆን ህብረቱን በሊቀመንበርነት፣ በምክትል ሊቀመንበርነት በጸሀፊነት የሚያገለግሎ ወላጆችን ምርጫ ተካሂዷል።

    አዳማ (የትምህርት ሚኒስቴር) – በአገሪቱ እስከ ታኛናው መዋቅር ያሉ የትምህርትና ስልጠና ተቋማትና የተማሪ ወላጆችን ትስስር በማጠናከር በዘርፉ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ የሚያስችል አገር አቀፍ የተማሪ ወላጆች ህብረት ተመሠረተ።

    ክቡር የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ አቶ መሀመድ አህመዲን በአገር አቀፍ የተማሪ ወላጆች ህብረት ምሥረታ ወቅት እንደገለጹት የህብረቱን ዓላማ በየደረጃው ባለው መዋቅር የትምህርት ተቋማትና የተማሪ ወላጆችን በማስተሳሰር በሁለንተናዊ ብቃት፣ ዕውቀት፣ ክህሎትና በስነ ምግባር የታነጸ ዜጋ ለማፍራት ረገድ የወላጆችን ሚና ለማሳደግ ነው።

    በትምህርት ጥራት የማረጋገጥ ተግባር የወላጆች ሚና ማሳደግ፣ በወላጆች፣ በመምህራንና በተማሪዎች መካከል ያለውን ግንኙት ውጤታማ ማድረግ፣ ጤናማ የመማር-ማስተማር ሂደት በላቀ ደረጃ እንዲረጋገጥ የወላጆችን ተሳትፎ ማሳደግና ለትምህርት ሥራ ማጎልበት የሚያስችል አደረጃጀትና ትስስር መፍጠር የህብረቱ ቀሪ ዓላማዎች መሆናቸውን ክቡር ሚኒስትር ደኤታው አስታውቀዋል።

    በህብረቱ ምሥረታ ላይ ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ547 የሚበልጡ የሀይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የተማሪ ወላጆች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተሳተፉበት ሲሆን ህብረቱን በሊቀመንበርነት፣ በምክትል ሊቀመንበርነት በጸሀፊነት የሚያገለግሎ ወላጆችን ምርጫ ተካሂዷል።

    በዚህም መሠረት ኢንጅነር ጌታቸው ሠጠኝ ከአዲስ አበባ የህብረቱ ሊቀመንበር ፣ወይዘሮ መሠረት ተክሌ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ የህብረቱ ምክትል ሊቀመንበር ፣ አቶ ሀሰን በዳሶ ከኦሮሚያ የህብረቱ ጸሀፊ ሆነው ተመርጠዋል።

    ህብረቱ በተጨማሪ 11 አባላት ያሉበትን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያዋቀረ ሲሆን በዚህም መሠረት ከትግራይ አቶ ጸጋዬ አለማየሁ፣ ከአፋር አቶ አሊ የጦ፣ ከአማራ አቶ አዱኛ እሸቴ፣ ከሱማሌ አቶ ኻሊድ አብዱልቃድር፣ ከደቡብ አቶ ተሻለ አየለ፣ ከጋምቤላ አቶ አእምሮ ደርበው፣ ከሐረሪ ወ/ሮ ፋጡማ አብዱ በህብረቱ ሥራ አስፈጻሚ አባልነት ተመርጠዋል።

    የኢትዮጵያ የተማሪ ወላጆች ህብረት ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ኢንጂነር ጌታቸው ሰጠኝ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ህብረቱ ለትምህርቱ ሥራ ውጤታማነት በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

    ክቡር የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ በበኩላቸው ህብረቱ ለፍኖተ-ካርታው መተግበር ጠቃሚ መሳሪያ መሆኑን ጠቁመው ህብረቱ ለሚያከናውነው ተግባር ውጤታማነት የትምህርት ሚኒስቴር እገዛ እንደማይለየው አስታውቀዋል።

    ህብረቱ በቀጣይ በሰላምና ደህንነት፣ በመማር ማስተማር፣ በትምህርት ተቋማት ፋይናንስ አስተዳደር ጉዳዮች የሚያተኩሩ ንዑሳን ኮሚቴዎች በቀጣይ ተቋቁመው ወደሥራ እንደሚያስገባም በዚሁ ጊዜ መገለጹን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዘግቧል።

    ምንጭ፦ የትምህርት ሚኒስቴር

    አገር አቀፍ የተማሪ ወላጆች ህብረት

    Semonegna
    Keymaster

    አንበሳ የከተማ አውቶቡስ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አሠራሩን በማሻሻል ቀልጣፋና ዘመናዊ አሠራርን መሰረት ያደረገ አገልግሎት በመስጠት ፋንታ አንዳንድ የአገልግሎት መስመሮቹን መዝጋቱ ተገቢ አለመሆኑን ተገልጋዮች ጠቁመዋል።

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – በአዲስ አበባ ከተማና በዙሪያዋ በረጅም ዘመን አገልግሎቱ የሚታወቀው አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት በተወሰኑ አካባቢዎች አገልግሎቱን በማቋረጡ ለትራንስፖርት እጥረት መጋለጣቸውን ተገልጋዮች ተናገሩ።

    የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ሪፖርተር በኮልፌ ቀራንዮ፣ ቀጨኔ፣ ሚኪሊላንድና መሰል አካባቢዎች ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ተገልጋዮች እንዳሉት አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት በእነዚህ አካባቢዎች ሲሰጥ የነበረውን አገልግሎት በማቋረጡ ለችግር ተዳርገዋል።

    የቀጨኔ አካባቢ ነዋሪዋ ወ/ሮ ባዩሽ ለማ ከሰፈራቸው እስከ መርካቶ በሁለት ብር የምታደርሳቸው ስምንት ቁጥር አውቶቡስ አገልግሎት በማቋረጧ ለተጨማሪ ወጪና እንግልት መዳረጋቸውን ተናግረዋል።

    በሚኪሊላንድ የጋራ መኖሪያ ቤት የሚኖሩት መምህር በላቸው አንዳርጌም ከሚኖሩበት አካባቢ ተነስተው ወደ መርካቶ እና ፒያሳ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ አውቶቡሶች አገልግሎት በማቋረጣቸው ህብረተሰቡ ለችግር መዳረጉን ገልጸዋል።

    መምህር በላቸው እንዳሉት አገልግሎቱ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከሚሰጠው የተመጣጠነ አገልግሎት በተጨማሪ ለተማሪዎችና መንግስት ሠራተኞችም የጎላ አስተዋጽዖ አለው።

    አንበሳ የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አሠራሩን በማሻሻል ቀልጣፋና ዘመናዊ አሠራርን መሰረት ያደረገ አገልግሎት በመስጠት ፋንታ የአገልግሎት መስመሮቹን መዝጋቱ ተገቢ አለመሆኑንም ጠቁመዋል።

    በአስኮ የአዲስ ሰፈር ነዋሪው ወጣት ሳሙኤል መንገሻ በአካባቢው በተለይ ጠዋትና ማታ ህብረተሰቡ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት እየተቸገረ መሆኑን ገልጾ ከአስኮ አዲስ ሰፈር አገልግሎት ለመስጠት የተመደበችው አውቶቡስ ስራ ማቆሟ ችግሩን እንደሚያባብሰው ተናግሯል።

    ከስድስት ኪሎ በሩፋዔል አስኮ እንዲሁም ከስድስት ኪሎ በሜክሲኮ ቄራ ይመላለሱ የነበሩትን አውቶብሶች ለማግኘት መቸገሩን የተናገረው ደግሞ ተማሪ ያለው ደምሴ ነው። ይህም በተለይ የማታ ትምህርት ለመከታተተል የትራንስፖርት እጥረቱን እንዳባባሰው ነው የተናገረው።

    በአንበሳ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የብዙሃን ትራንስፖርት ዋና ሥራ ሂደት ተጠባባቂ ሃላፊ አቶ መላኩ ካሳዬ የነዋሪዎቹ ጥያቄ ትክክለኛ መሆኑን አምነዋል።

    ይሁን እንጂ ችግሩ የተፈጠረው የአገልግሎት መስመሮች በመታጠፋቸው ሳይሆን በርካታ አውቶብሶች በእርጅና ምክንያት ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው መሆኑን አብራርተዋል።

    ችግሩን ለመፍታ ድርጅቱ ሰባት መቶ አውቶብሶችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው ከመጪው ሰኞ ጀምሮ አዳዲስ አውቶብሶችን እንደሚረከብም ገልጸዋል። አሁን ያሉትን አውቶብሶች በአግባቡ በመጠቀም ችግሩን ለማቃለል ጥረት እደሚደረግም ነው ኃላፊው የተናሩት።

    አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት በአሁኑ ወቅት 444 አውቶብሶችን በየቀኑ እያሰማራ ቢሆንም ከ20 በላይ የሚሆኑት አውቶቢሶች በብልሽትና በቴክኒክ ጉድለት ሳቢያ በየቀኑ በአግባቡ አገልግሎት እንደማይሰጡ አስታውቀዋል።

    በ1935 ዓ.ም በአራት ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት መስጠት የጀመረው አንበሳ የከተማ አውቶቡስ ድርጅት በ1967 ዓ.ም ወደ መንግስት ይዞታነት ተሸጋግሮ እስካሁን ድረስ ቆይቷል። በተለያዩ የሥራ መስኮችም ከሰባት ሺህ አምስት መቶ በላይ ሠራተኞች አሉት።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

    አንበሳ የከተማ አውቶቡስ

    Semonegna
    Keymaster

    የስንፈተ ወሲብ መድኃኒቶች እንደአግባቡ ከሆነ በሀኪም ትዕዛዝ የሚሰጡ መሆናቸውን በመግለጽ፥ ነገር ግን በሕገ-ወጥ መንገድ ያለሀኪም ትዕዛዝ ለኅብረተሰቡ የሚያሰራጩ ሕገ-ወጥ የመድኃኒት ተቋማት እንዳሉ ተጠቅሟል።

    አዲስ አበባ – የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ፈዋሽነቱና ደኅንነቱ ያልተረጋገጠ በንግድ ስሙ “ቪጋ፣” “ቪጎ” እና “ፊካ” (ቪጎ 50፣ ቪጎ 100/ Vigo50/100፣ ቬጋ 50፣ ቬጋ 100/Vega 50/100፣ ፊካ 50፣ ፊካ 100/Fika 50/100) የተሰኙ የወሲብ ማነቃቂያ መድኃኒቶች (የስንፈተ ወሲብ መድኃኒቶች) በሕገ-ወጥ መንገድ በሀገር ውስጥ መሰራጨታቸውንና በተጠቃሚዎች ላይም የጤና እና የኢኮኖሚ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን አስታወቀ።

    ባስልጣን መሥሪያ ቤቱ ጥቅምት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተገለጸው በድህረ-ገበያ ቅኝት በተደረገው የቁጥጥር ሥራ ለማወቅ እንደተቻለው በተቋሙ ያልተመዘገቡና ጥራት እና ደኅንነነታቸው ያልተረጋገጡ እንዲሁም በሕገ-ወጥ መንገድ ወደሀገር ውስጥ የገቡት የስንፈተ ወሲብ (የወሲብ ማነቃቂያ) መድኃኒቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመገኘታቸው ህብረተሰቡ ምርቶቹን ከመጠቀም ራሱን እንዲቆጥብና ጥንቃቄ እንዲያደርግ ባለስልጣን መስሪያቤቱ አሳስቧል።

    ከዚህ በተጨማሪ ችግሩን የከፋ የሚያደርገው የስንፈተ ወሲብ መድኃኒቶች እንደአግባቡ ከሆነ በሀኪም ትዕዛዝ የሚሰጡ መሆናቸውን በመግለጽ፥ ነገር ግን በሕገ-ወጥ መንገድ ያለሀኪም ትዕዛዝ ለኅብረተሰቡ የሚያሰራጩ ሕገ-ወጥ የመድኃኒት ተቋማት እንዳሉ የተደረሰበት ስለሆነ ህብረተሰቡ መሰል ተግባር ሲፈጸም ከተመለከተ በነጻ የስልክ መስመር 8482 በመደወል ለባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ እንዲያሳውቅ አስገንዝቧል።

    የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱን መግለጫ በመጥቀስ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደዘገበው ከላይ የተጠቀሱት ሕገ-ወጥ መድኃኒቶች ለስንፈተ ወሲብ (ፈዋሽነት (በሌላ አባባል፥ ለወሲብ ማነቃቂያነት) ጥቅም ላይ እየዋሉ ሲሆን፥ በአዲስ አበባ፣ በዲላ፣ በወላይታ፣ በወራቤ፣ በሆሳዕና፣ በሀዋሳ፣ በደሴ፣ በኮምቦልቻ እና በጎንደር በስፋት እየተሰራጩ ነው። እነዚህ ሕገ-ወጥ መድኃኒቶች በህብረተሰቡ ላይ እይሳደሩ ያለው ዘርፈ ብዙ ጫና እና ተጽዕኖዎች ከፍተኛ ነው። እንደዘገባው ከሆነ ይህ እጅግ አሳሳቢ ችግር በስፋት ከተከሰተ ሁለት ዓመትና ከዚያ በላይ ቢሆነውም በአሁኑ ጊዜ የተጠቃሚው ቁጥር እየጨመረና እያስከተለ ያለውም ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። መግለጫውን መስጠት ያስፈለገውም ስርጭቱ በመስፋፋቱ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ እና በድርጊቱ ላይ የሚሳተፉም ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ለማሳሰብ ነው።

    በባለስልጣኑ የመድኃኒት ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ እንዳለ እንደገለጹት፤ ባለስልጣኑ ባከናወነው የክትትልና ቁጥጥር ስራ በደቡብ ክልል ‹‹ቪጋ› እና ‹‹ቪጎ›› የተባለውን ጨምሮ በህገወጥ መንገድ የገቡ መድኃኒቶች ሲሸጡ የተደረሰባቸው ከ30 በላይ የሚሆኑ የግል መድኃኒት ቤቶች የክልሉ ተቆጣጣሪ አካል እርምጃ እንዲወስድ ስም ዝርዝራቸውን አሳውቋል። በከሚሴና በደሴም በተመሳሳይ የተሰማሩ ወደ 20 ድርጅቶች እርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረጉን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

    ባለስልጣኑ በተለያየ ጊዜ በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ መድኃኒቶችን ከፍትህ አካላትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመውጫ በሮች ላይ ቁጥጥር በማድረግ ህገወጦችን በመከላከል ረገድ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ቢሆንም የህብረተሰብ ተሳትፎ መኖር እንዳለበት አመልክተዋል። ህብረተሰቡ ያለ ሀኪም ትዕዛዝ ከመውሰድ እንዲቆጠብና ህገወጥነትንም እንዲከላከል ጥሪ አቅርበዋል።

    በባለስልጣኑ የመድኃኒት ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብደላ ቃሶ ባለስልጣኑ ፈዋሽነታቸውና ጥራታቸው የተረጋገጠ መድኃኒቶችን ህብረተሰቡ በቀላሉ የሚለይበትን አሠራር ዘርግቶ ችግሩን ለመቅረፍ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል። ተገልጋዮች ከዚህ በኋላ ሕጋዊና ሕጋዊ ያልሆኑ መድኃኒቶችን በባለስልጣኑ ድረ-ገጽ (http://www.mris.fmhaca.gov.et) ማየት እንደሚችሉና በድረ-ገጹ ላይም ስለመድኃኒቱ ዝርዝር የሆነ መረጃ እንደሚያገኝ አመልክተዋል። ቀደም ሲል እስከ አንድ ዓመት ጊዜ ይወስድ የነበረውን መድኃኒቶችን በዓይነትና በብዛት የመመዝገብ ሥራም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

    የስንፈተ ወሲብ መድኃኒቶች

    Semonegna
    Keymaster

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አድርገው መረጡ። ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር መሥራች ናቸው።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ጥቅምት 22 ቀን 2011 ዓ.ም በሚያካሂደው መደበኛ ስብሰባ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሹመትን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አድርገው መርጠዋቸዋል።

    የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ይካሄዳል። በስብሰባው በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 81 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርቡትን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እጩ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ሹመት መርምሮ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምርጫ ያቀረቧቸው ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ይሾማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    በአሁኑ ወቅት ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው እያገለገሉ ያሉት አቶ ዳኜ መላኩ እና አቶ ጸጋዬ አስማማው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሾሙት ሰኔ 16 ቀን 2008 ዓ.ም ነበር።

    ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ማን ናቸው?

    ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ  በ1985 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ኮሚሽን የሕግ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል። በ1987 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርን (Ethiopian Women Lawyers Association/ EWLA) ከሌሎች የሕግ ባለሙያ ሴቶች ጋር በመሆን አቋቁመው በ1988 ዓ.ም. ማኅበሩ በይፋ ሥራ ጀመረ። በዚያም ጊዜ ወ/ሮ መዓዛ የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ ሆነው እስከ 1997 ዓ.ም. ድረስ ሠርተዋል።

    ወ/ሮ መዓዛ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምጣኔ ሀብት ኮሚሽን ለአፍሪካ (United Nations Economic Commission for Africa) የተባለው ዓለም-አቅፍ ድርጅትን በ2003 ዓ.ም. በመቀላቀል፥ በዚሁ ድርጅት ውስጥ ከሰኔ ወር 2004 ዓ.ም. ጀምሮ የሴቶች መብት አማካሪ ሆነው ሠርተዋል።

    ከሕግ ባለሙያነታቸው በተጨማሪ በ2003 ዓም ኢትዮጵያ ውስጥ በ13 ጠንካራ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ተደራጅነት የተቋቋመው እናት ባንክ (አ/ማ) ሲመሠረት ከመሥራችቹ ውስጥ ጉልህ ሚና የተጫወቱ አባል ነበሩ። ባንኩ ውስጥም ከአራት ዓመታት በላይ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሆነው አገልግለዋል።

    ኢትዮጵያ ውስጥ ለሴቶች እኩልነትና ለሴቶች መብት በመታገል ላደረጉት አንጸባራቂ ውጤት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በህዳር ወር 1996 ዓ.ም ‘የሀንገር ፕሮጀክት ሽልማት’ (Hunger Project Award) የአፍሪካ ተሸላሚ ሆነዋል። ከዚያም ቀጥሎ (ከሁለት ዓመት በኋላ) የኖቤል የሰላም ሽልማት ዕጩ ሆነው ሊቀርቡ ችለዋል።

    በ2006 ዓ.ም. ዘረሰናይ ታደሰ ተደርሶ የተዘጋጀው (ዳይሬክት የተደረገው) “ድፍረት” የተሰኘውና በዓለም አቀፍ ደረጃ መልካም ተቀብይነትን ያገኘው ፊቸር ፊልም (feature film) ሂሩት አሰፋ የተባለች አንዲት የ14 ዓመት ልጃገረድ ኢፍትሀዊ በሆነ ባህል የሞት ፍርድ ተፈርዶባት ከዚያም የሕግ ባለሙያ (ጠበቃ) የሆነችውን ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊን አግኝታ የሚሆነውን የሚተርክ እንደሆነ ይታወሳል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    መዓዛ አሸናፊ

    Semonegna
    Keymaster

    የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር በበጎ ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያን ሴቶች የተቋቋመውን ጀግኒት የተሰኘ የማህበረሰብ ንቅናቄ በይፋ ለመመሥረት እና አገር አቀፍ የሴቶች የሰላም ጉባዔ ለማካሔድ ዝግጅት መጀመሩን አስታውቋል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – ጀግኒት ንቅናቄ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር “ጀግኒት ዓለመች፣አቀደች፣ አሳካች” በሚል መሪ ቃል የሚያዘጋጁትን አገር አቀፍ ጉባዔ አስመልክቶ ዘጠኙ ሴት ሚኒስትሮች፣ እንዲሁም የሁለቱ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔና ምክትል አፈ ጉባዔ በተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ መሰጠቱን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዘግቧል።

    ከዘጠኙ ክልሎች እና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ሴቶች የሚሳተፉበት አገር አቀፍ የሴቶች የሰላም ጉባዔ የፊታችን ጥቅምት 26 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚካሄድም በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ይፋ ተደርጓል።

    በመግለጫው ላይ ንግግር ያደረጉት የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወ/ሮ ያለም-ፀጋይ አስፋው፥ “ጅግኒት ዓለመች፣ አቀደች፣ አሳካች” በሚል መሪ ቃል የሚደረገው አገር አቀፍ ጉባዔ በሀገሪቱ ውስጥ ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ፤ የሴቶችና ሕፃናትን የአደጋ ተጋላጭነት በመቀነስ መብትና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እና ሴቶች ሰላም በአጠቃላይ መከበር ላይ ያላቸውን አስተዋጽዖና ግብዓት ለማሳደግ ነው ብለዋል። እንዲሁም የሴቶችና ሕፃናትን ደኅንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ በየአከባቢው ሴቶች ለሰላማቸው ጠንክረው እንዲሠሩ ለማድረግም ነው በማለት አክለዋል።

    ጀግኒት የተሰኘው የማህበረሰብ ንቅናቄ በአገሪቱ የሴቶችን ጥንካሬ ከተተኪነት በላይ ራሳቸው ለተሻለ ነገር የሚያበቁ እና ብቁ ትውልድ የሚያፈሩ መሆናቸውን ለማሳየት ያስችላል ተብሏል። በአሁን ሰዓት ሴቶች በአገሪቱ ልማትና እድገት ላይ በየደረጃው እየተወጡ ያለው ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በማሳወቅና በማሳየት ክብርና ዕውቅና ማግኘት እንዲችሉ ያደርጋል ተብሎ ተብራርቷል።

    ከንቅናቄው በኋላ የሴቶች የልማት ጥምረት ይመሰረታል የተባለ ሲሆን፥ ይህም በሴቶችና ህፃናት ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ አካላት ለማጠናከር፣ በዘላቂ ሰላም ማረጋግጥና ሴቶች በልማቱ ያላቸው ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ዙሪያ የራሱ ድርሻ እንደሚኖረው ተጠቁሟል።

    ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ውስጥ ከጾታ እኩልነት ጀምሮ እስከ አጠቃላይ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፥ ከቅርብ ወራት ወዲህ በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ለማፋጠንም ንቅናቄው አስተዋፅኦው የጎላ ይሆናል ተብሏል።

    በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ለሚኒስትሮቹ አሁን ያለውን የሴት ሚኒስትሮች ቁጥር ለማስቀጠልም ሆነ በአጠቃላይ በፖለቲካ ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ ለማጎልበት ምን ታስቧል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፥ ብዙ አቅም ያላቸው ሴቶች እንዳሉና ንቅናቄው እስከ ወረዳ ድረስ የሚካሄድ በመሆኑ አቅም ያላቸውን ሴቶች ወደ ከፍተኛ የስልጣን እርከኖች ማምጣት ይቻላል ብለዋል።

    ጀግኒት ንቅናቄን ለመቀላቀል ወይም ደግሞ ስለንቅናቄው የበለጠ ለመረዳት በፌስቡክ ገጻቸው (Jegnit) ወይም በትዊተር አድራሻቸው (@jegnit) ያግኟቸው።

    ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ እና የጀግኒት ንቅናቄ ማኅበራዊ ገጾች

    ጀግኒት ንቅናቄ

    Semonegna
    Keymaster

    የፈረንሳይ መንግስት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥያቄ መሰረት፥ ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን እድሳት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል፤ የኢትዮጵያ መከላከያን ለማዘመን ተስማምቷል፤ ለአየር መንገድ ከ100 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ድጋፍ ያደርጋል።

    ፓሪስ፥ ፈረንሳይ – የፈርንሳይ መንግስት ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን ድጋፍ እንዲያደርግ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) የቀረበለትን ጥያቄ በፕሬዝዳንቱ ኢማኑኤል ማክሮን (Emmanuel Macron) በኩል ተቀብሎ ተስማምቷል።

    በፈረንሳይ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፥ ትናንት ምሽት ነው በፓሪስ ኢልዚ ቤተ መንግስት (Élysée Palace) ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኢትዮጵያ በባህል፣ በእምነትና በቋንቋ ከፈረንሳይ ጋር የነበራትን ወዳጅነት እንድታጠናክር የፈረንሳይ የመጀመሪያ ሥራ በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን የደረሰውን ችግር መቅረፍ ሊሆን እንደሚገባ ለፕሬዝዳንት ማክሮን ጥያቄ አቅርበው አዎንታዊ ምላሽ መገኘቱን ሁለቱ መሪዎች በጋራ በስጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቀዋል።

    መሪዎቹ በሰላም፣ በዴሞክራሲና በልማት ዙሪያ ዝርዝር ውይይት ማድረጋቸውን የጠቀሱት ዶ/ር አብይ፥ ፈረንሳይ የሀገር መከላከያን ለማዘመን የሰው ኃይል ለማሰልጠን መስማማቷንም  አስታውቀዋል።

    መሪዎቹ በኢኮኖሚው መስክ ባደረጉት ውይይትም ፈረንሳይ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለማዘመን ከ100 ሚሊዮን ዩሮ በላይ በማውጣት የአዲስ አበባ ኤርፖርትን ለመሥራት፣ እንዲሁም የፈረንሳይ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ከስምምነት መድረሳቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

    ኢትዮጵያ የጀመረችውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ከማገዝ አንጻርም ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ (ኤ.ኤፍ.ዲ)፣ ከአለም ባንክ እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) ከምታገኘው የበጀት ድጋፍ በተጨማሪ የፈረንሳይ መንግስት የቀጥታ ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ዝግጁነት ፕሬዝዳንት ማክሮን መግለፃቸውን ዶ/ር አብይ አስታውቀዋል።

    የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት እ.ኤ.አ በመጋቢት ወር 2019 ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

    በአፍሪካ ቀንድ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የመጣውን ሰላም በማስቀጠል በኤርትራና በጅቡቲ መካከል ሰላም እንዲጠናከር ለማድረግ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውንም አስታውቀዋል በማለት ኤፍ.ቢ.ሲ ዘግቧል።

    ፕሬዚዳንት ማክሮን ኢትዮጵያን የሚጎበኙት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በቀረበላቸው ግብዣ መሰረት መሆኑም ታውቋል። ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከውይይቱ በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር በሰጡት የጋራ መግለጫ፥ የፊታችን መጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ላይ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ አስታውቀዋል።

    የፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ (ኤ.ኤፍ.ዲ) እ.ኤ.አ በመስከረም ወር 2017 ዓም የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅትን ለማሻሻልና በአዲስ ቦታ ለማደራጀት ከ70 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ድጋፍ ማድረጉን፣ እ.ኤ.አ በሰኔ ወር 2018 ደግሞ ለከተማ ልማት እና የጂኦተርማል ኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀችት 18 ሚሊዮን ዩሮ ለመደገፍ ከኢፌዴሪ የፋይናንስና ገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ስምምነቶችን መፈራረሙን መዘገባችን ይታወሳል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 

    የፈረንሳይ መንግስት


    Semonegna
    Keymaster

    በአገሪቱ ከ7 ሺህ 800 በላይ አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች እንደሚቋቋሙ የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።

    አዳማ (ኢዜአ)– በመላ አገሪቱ በዚህ አመት ከ7 ሺህ 800 በላይ አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች እንደሚቋቋሙ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ስር የሚገኘው የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ (Federal Small and Medium Manufacturing Industry Development Agency) አስታወቀ።

    አዳዲስ ኢንዱስትሪዎቹን ለማቋቋም፣ ነባሮችን ለማጠናከርና በቁሳቁስ ለማደራጀት 14 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ኤጀንሲው አስታውቋል።

    የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት የ2010 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ አፈጻጸምን የሚገመግምና በ2011 ዕቅድ ላይ የሚመክር የሁለት ቀን መድረክ ጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓም በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

    በኤጀንሲው የፖሊሲ ዕቅድና ፕሮጀክት ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ገነት አረጋዊ በወቅቱ እንደገለጹት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለሚደረገው መዋቅራዊ ሽግግር አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን መገንባት አስፈልጓል። ነባሮችንም የማጠናከር ሥራ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ነው የገለጹት።

    ለእዚህም በበጀት ዓመቱ 7 ሺህ 860 አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን የማቋቋምና 2 ሺህ 924 ነባር ኢንዱስትሪዎች የማጠናከር ሥራ እንደሚከናወን አመልክተዋል።

    “አዳዲስ ኢንዱስትሪዎቹን ለማቋቋም፣ ነባሮቹን ለማጠናከርና ለእቃ አቅርቦት የሚያስፈልገው 14 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ለሁሉም ክልሎች፣ ለአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ መስተዳድሮች በብድር ይቀርባል” ብለዋል ወ/ሮ ገነት።

    የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጥን ፕሬዝደንት አድርጎ መርጧል

    አዲስ ከሚቋቋሙት የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች መካከል የብረታ ብረትና እንጨት ሥራ፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያዎች፣ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችና ጌጣ ጌጥ ማምረቻዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

    ዳይሬክተሯ እንዳሉት በሚቋቋሙት ኢንዲስትሪዎች ከ195 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል። አያይዘውም “ኢንዱስትሪዎቹን ውጤታማ ለማድረግ በሀገር ውስጥ የ2 ቢሊዮን ብርና በውጭ አገራት የ194 ነጠብ 5 ሚሊዮን ዶላር የገበያ ትስስር ይመቻቻል” ብለዋል።

    ዘርፉን ለማሳደግ ለባለሀብቶች፣ ለዩኒቨርሲቲ ምሩቃን፣ ለሞዴል አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች እንዲሁም ለሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እንደሚሰጥ ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል ።

    የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ በበኩላቸው “የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት የትራንስፎርሜሽኑ መሰረት ስለሆነ በእያንዳንዱ ወረዳ ሊቋቋም ይገባል” ብለዋል።

    ባለድርሻ አካላትን በልዩ ትኩረት በመሳተፍ ዕቅዱን እውን ለማድረግ ኤጀንሲው ከሁሉም ክልሎችና ከሁለት የከተማ መስተዳድሮች ጋር ጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓ.ም የስምምነት ሰነድ መፈራረሙንም አቶ አስፋው አመልክተዋል።

    የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥና ብልጽግና እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር ያለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዕድገትና ተወዳዳሪነት ሊመጣ ስለማይችል ሁሉም አካላት ለተፈጻሚነቱ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል ።

    የቀረበው አመላካች ዕቅድ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ-መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚደረገውን ግብ ለማሳካት ወሳኝ ስለመሆኑ ከመድረኩ ተሳታፊዎች ተገልጿል።

    ለኢንዱስትሪው ልማት ማነቆ የሆኑ በሊዝ፣ በብድር ገንዘብና በኤሌክትሪክ አቅርቦት የሚስተዋሉ እጥረቶችና የተንዛዙ አሠራሮች ሊፈቱ እንደሚገባም በተሳታፊዎቹ ጥያቄ ቀርቧል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    መካከለኛ የማኑፋክቸሪንግ

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ ዓለም ከተማ የሞቱት ሁለቱ ተመራማሪዎች ወሰን ታፈረ እና ማንደፍሮ አብዲ የሚባሉ ሲሆን፥ ከባድ የመቁሰል አደጋ የደረሰበት የሜጫ ወረዳ ጤና መኮንን (የላቦራቶሪ ባለሙያ) የሆነው ኃይለየሱስ ሙሉ ይባላል።

    አዲስ ዓለም፣ አማራ ክልል – በምዕራብ ጎጃም ዞን ጎንጂ ቆለላ ወረዳ ለምርምር ወደ አዲስ ዓለም ከተማ የሄዱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሶስተኛ (ዶክትሬት) ዲግሪ ተማሪዎች እና የሜጫ ወረዳ ጤና መኮንን በከተማው የሚኖሩ ግለሰቦች ባደረሱባቸው ጥቃት ሁለቱ ህይወታቸው ሲያልፍ፣ አንዱ ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደርሶበታል። ሁለቱ የሞቱት ተመራማሪዎች ወሰን ታፈረ እና ማንደፍሮ አብዲ የሚባሉ ሲሆን፥ ከባድ የመቁሰል አደጋ የደረሰበት የሜጫ ወረዳ ጤና መኮንን (የላቦራቶሪ ባለሙያ) የሆነው ኃይለየሱስ ሙሉ ይባላል።

    የዶክትሬት ተማሪዎቹ አዲስ ዓለም ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ለምርምር የሚሆን የሽንትና የዓይነ ምድር ናሙና እየሰበሰቡ ባሉበት ወቅት ከዕለቱ ቀደም ብሎ በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያዎች “ሦስት ተማሪዎች ሞቱ” በሚል በተነዛው ወሬ ተቆጥተው በመጡ የአካባቢው ወጣቶች በደረሰባቸው ከፍተኛ ጥቃት ሕይወታቸው ማለፉን የምዕራብ ጎጃም ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ አንማው ዳኛቸው ለአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ ዝግጅት ክፍል ተናግረዋል።

    ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቢቢሲ አማርኛ የጎንጂ ቆለላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ደመቀ መላኩን ጠቅሶ እንደዘገበው “በተሳሳተ መልኩ ልጆቻችን የጤና ክትባት እየተሰጣቸው ነው፤ እየተመረዙብን ነው፤ ሊገደሉብን ነው” በሚል የተቆጡ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የአካባቢው ግለሰቦች የዶክትሬት ተማሪዎቹ (ተመራማሪዎቹን) ወደነብሩበት የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ሄደዋል። የትምህርት ቤቱ የጥበቃ ሠራተኞች ሁኔታው ከአቅማቸው በለይ ሲሆን በአካባቢው በነበሩ ጥቂት የጽጥታ አስከባሪ አካላት (ፖሊሶች) ታግዘው ተመራማሪዎቹን ወደ ፖሊስ ጣቢያ እየወሰዷቸው ሳለ፥ በከተማው መናኸሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጥቃቱ እንደደረሰባቸው ቢቢሲ አማርኛ ጨምሮ ዘግቧል።

    አዲስ ዓለም

    ግለሰቦቹ ያደረሱት ጥቃት በተማራማሪዎቹ ላይ ብቻ ሳይገታ ሁኔታው በፈጠረው ግርግር ለቤተ ክርስቲያን ህንፃ ግንባታ ግልጋሎት የሚውል ሲሚንቶ በራሳቸው መኪና ጭነው ወደ አካባቢው ተጉዘው የነበሩ ጥንዶች ንብረትም መቃጠሉን የአሜሪካ ድምፅ አቶ አንማው ዳኛቸውን ጠቅሶ ዘግቧል። አቶ አንማው ለአሜሪካ ድምፅ አክለው በሰጡት ማብራሪያ በዚህ ድርጊት ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩ 30 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን፣ ብሎም በተፈፀመው ድርጊት የአካባቢው ማኅበረሰብም ሆነ መንግሥት ማዘኑን እና በድርጊቱ ተሳትፈዋል የተባሉትን እየፈለጉ በቁጥጥር ስር የማዋሉ ሥራ መቀጠሉን ጠቁመዋል።

    ከቢቢሲ አማርኛ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የጎንጂ ቆለላ ወረዳ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አንተነህ በላይ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በክልሉ ዋና ከተማ ባህር ዳር ውስጥ ለህፃናት ክትባት ሲሰጡ ሞቱ በሚል በተናፈሰ ወሬ ምክንያት መኪና መሰባበር፣ እንዲሁም በአንዳንድ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት (መቁሰል) መድረሱን አስታውሰው አካባቢው ለባህር ዳር ከተማ ቅርብ በመሆኑ ይሄው መረጃ በመናፈሱ ጥቃቱ ሊፈፀም እንደቻለ አስረድተዋል። አቶ አንተነህ አክለው እንደተናገሩ ጥቃቱን ያደረሱት የ አካባቢ ተወላጆች መሆናቸውና አገር ሊጠቅሙ ምሁራን በራሳቸው ወገኖች በመገደላቸው የ አካባቢው ማኅበረሰብ መፀፀቱን፣ በድርጊቱ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን አጋልጦ መስጠት የጀመረውም ራሱ ህብረተሰቡ እንደሆነ ተናግረዋል።

    የአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ ዝግጅት ክፍል ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ ከምዕራብ ጎጃም ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ አንማው ዳኛቸው ጋር ያደረገችውን ቃለ ምልልስ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄዱት ልዩ ስብሰባቸው አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን 4ኛው የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሄር (ፕሬዝዳንት) አድርጎ በሙሉ ድምፅ መርጧል።

    ፕሬዝዳት ሳህለወርቅ ዘውዴ ቃለ መሃላ ፈፅመው ኃላፈነታቸውን በትጋትና በታኝነት አገርና ህዝብን ለማገልገል ቃል ገብተዋል።

    አምባሳደር ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ላለፉት አመስት ዓመታት በፕሬዝዳንትነት ላይ የነበሩትን ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን በመተካት አገሪቱን በፕሬዝዳንትነት የሚመሩ ይሆናል። ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመም ከተመራጯ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር የስልጣን ርክክብ አድርገዋል።

    አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ማን ናቸው?

    ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሲሆን የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ነው። አራት ሴት ልጆች ለነበሯቸው ወላጆቻቸው የመጀመሪያ ልጅ የሆኑት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገና በ17 ዓመታቸው ነጻ የትምህርት ዕደል አግኝትው ወደ ፈረንሳይ በማቅናት ሞንትፔልየር (Montpellier) በምትባለው የፈረንሳይ ከተማ በሚገኘው ዮኒቨርሲቲ ኦፍ ሞንትፔልየር (University of Montpellier) የተፈጥሮ ሳይንስን አጥንተዋል። በሀገረ ፈረንሳይ ለዘጠኝ ዓመታት ከቆዩ በኋላ ወደ ኢትዮጵይ በመመለስ በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ የሕዝብ ግንኙነት ክፍልን ማገልገል ጀመሩ። ቆይተውም የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉን በበላይነት መርተዋል። ከዚያም ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመዘዋወር በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች አገልግለዋል።

    ወሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ በአምባሳደርነት ለመሾም ከአምባሳደር ዮዲት እምሩ ቀጥሎ ሁለተኛዋ እንስት ናቸው። በመጀመሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙትም ሴኔጋል ሲሆን የአምባሳደርነት ስልጣናቸውም ሴኔጋልን ጨምሮ ማሊን፣ ኬፕ ቨርዴን፣ ጊዚ ቢሳውን፣ ጋምብያን እና ጊኒን (እ.ኤ.አ 1989–1993) ያጠቃልል ነበር። ቀጥሎም እ.ኤ.አ 1983–2002 በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደርና በኢጋድ (IGAD) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል። እ.ኤ.አ ከ2002 ጀምሮ እስከ 2006 ድረሰ በፈረንሳይ (ሞሮኮን ጨምሮ) የኢትዮጵያ አምባሳደርና በዩኔስኮ (UNESCO) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል። እ.ኤ.አ ከ2006 ጀምሮ እስከ 2009 ድረስ በአፍሪካ ህብረት (AU) እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው ሀገራቸውን አገልግለዋል።

    ከሀያ ዓመታት በላይ በተለያዩ ሀገራትና ዓለማቀፋዊ ድርጅቶች የኢትዮጵያ አምባሳደርና ተጠሪ በመሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን ያገለገሉት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ እ.ኤ.አ በ2009 የተበባሩት መንግስታት ድርጅትን (ተመድ) በመቀላቀል የድርጅቱ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ የተቀናጀ ሰላም ግንባታ መሪ (Head BINUCA) በመሆን ማገልገል ጀመሩ። ይህ አገልግሎታቸውም ወደ ሚቀጥለው ኃላፊነት አሸጋግሯቸው እ.ኤ.አ በ2011 ዓም የዚያን ጊዜ የተመድ ጠቅላይ-ጸሀፊ ባን ኪ-ሙን (Ban Ki-moon) አዲስ ለተቋቃመው በናይሮቢ የተመድ ጽህፈት ቤት (UNON) የመጀመሪያዋ ጠቅላይ-መሪ አድርገው ሾማቸው። በዚያም ለሰባት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ እ.ኤ.አ በሰኔ ወር 2010 የአሁኑ የተመድ ጠቅላይ-ጸሀፊ አንቶንዮ ጉቴሬስ (António Guterres) አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን በተመድ ጠቅላይ-መሪ ስር (Under-Secretary-General) የአፍሪካ ህብረት ልዩ ተጠሪ (UN’s Special Representative to the AU) እና በአፍሪካ ህብረት ውስጥ የተመድ ጽህፈት ቤት ዋና ኃላፊ (Head of UNOAU) አድርገው ሾሟቸው እስካሁን ድረስ በዚሁ ሹመታቸው እያገለገሉ ይገኛሉ።

    አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ባለትዳርና የሁለት ወንድ ልጆች እናት ናቸው።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ሳህለወርቅ ዘውዴ


Viewing 15 results - 451 through 465 (of 495 total)