-
Search Results
-
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የወሰናቸውን ኢ-ፍትሃዊ እርምጃዎችን እንዲመረምር እና ያላአግባብ የተወሰነበትን ፎርፌ እንዲያነሳ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የጠየቀ ሲሆን፥ ያቀረባቸው ቅሬታዎች ምላሽ እስከሚያገኙ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮች ራሱን ማግለሉን አስታውቋል።
አዲስ አበባ – የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ላቀረባቸው ጥያቄዎች ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮቸ ራሱን ማግለሉን አስታወቀ።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሊግ ኮሚቴ የቅዱስ ጊዮርጊስን የሜዳ ተጠቃሚነት ለማሳጣት ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ሊያደርገው የነበረን ጨዋታ በዝግ ወይም አዳማ ከተማ ላይ ተጫወቱ በማለት ሁለት ጊዜ እንዲቋረጥ አድርጎል ብሏል።
ይህን ጨዋታ ከዚህ በፊት የተቋረጡ የሌሎች ክለቦች ጨዋታወችን ባስተናገደበት ሁኔታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን አላስተናገደም ሲል በፌዴሬሽኑ ላይ ቅሬታውን አቅርቧል።
እንዲሁም በ29ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ለፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ የተሰጠው ፎርፌ አግባብነት የሌለውና አድሏዊ መሆኑንም ነው በመግለጫው ያመላከተው።
አዲስ ከመጡት የፌዴሬሽኑ አመራሮች ጋር በመተባበር፣ በመቻቻል እና በመተጋገዝ ለመሥራት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ ቆይቷልም ነው ያለው።
በመሆኑም ፌዴሬሽኑ የወሰናቸውን ኢ-ፍትሃዊ እርምጃዎችን እንዲመረምር እና ያላአግባብ የተወሰነበትን ፎርፌ እንዲያነሳ የጠየቀ ሲሆን፥ ያቀረባቸው ቅሬታዎች ምላሽ እስከሚያገኙ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮች ራሱን ማግለሉን አስታውቋል።
ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ. / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
—–
ተመሳሳይ ዜናዎች፦- ኢትዮጵያ ቡና የአዲስ አበባ ዋንጫ አሸናፊ ሆነ
- ከመጣንበት መንገድ በላይ የሚቀረን ይከብዳል!! (ለኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች)
- የኢትዮጵያ ቡና ከመቐለ 70 እንድርታ ጋር አዳማ ላይ አልጫወትም አለ፤ በዒድ አል ፈጥር ምክንያት ጨዋታው በድጋሚ ተራዝሟል
ለግንቦት 27 ቀን ተወስኖ የነበረውን የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንድርታ ጨዋታ በድጋሚ ወደ ሐሙስ ግንቦት 29 ቀን በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት በዝግ ስታድየም እንዲካሄድ ተወስኗል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– ግንቦት 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት ጨዋታ የነበራቸው ኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንድርታ ሊያካሂዱት የነበረው ጨዋታ በጸጥታ ስጋት ምክንያት (የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባደረገው ውሳኔ መሰረት) ውድድሩ ሳይካሄድ መቅረቱ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህን ጨዋታ ግንቦት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት በዝግ ስታድየም እንዲካሄድ መወሰኑን አስታውቆ ነበር። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቡና ዛሬ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የላከው መግለጫ (በዋና ሥራ አስኪያጁ በተፃፈ ደብዳቤ) እንደሚያመለክተው ፌዴሬሽኑ ለግንቦት 27 ያወጣዉን ፕሮግራም እንደሚቃወመው አስታውቋል። በተጨማሪም ክለቡ ደብዳቤ ላይ በ27ኛ ሳምንት በሜዳው ከመቐለ 70 እንድርታ ጋር ያለዉን ጨዋታ በሜዳዉና በደጋፊው ፊት እንዲካሄድም ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውሳኔውን በዚህ ብቻ ሳያበቃ ግንቦት 26 ቀን ለመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ሆቴል ከቀኑ 9:00 ሰዓት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ክለቡ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ ስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት (Court of Arbitration for Sport) እንደሚወስደዉም ይፋ አድርጓል።
እንደገና ግንቦት 26 ቀን የዒድ አል ፈጥር በዓል ማክሰኞ ግንቦት 27 ቀን እንደሚውል ከታወቀ በኋላ ለግንቦት 27 ቀን ተወስኖ የነበረውን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በድጋሚ ወደ ሐሙስ ግንቦት 29 ቀን በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት በዝግ ስታድየም እንዲካሄድ ተወስኗል።
የኢትዮጵያ ቡና የጻፈው ደብዳቤ
ጉዳዩ፦ የተላለፈብንን ውሳኔ ስለመቃወም።
ክለባችን በ25/09/2011 ከመቀሌ 70 እንደርታ ቡድን ጋር በሊጉ 27ኛ ጨዋታ ለውድድር ተዘጋጅቶ መቅረቡ ይታወቃል።
ሆኖም በእኛ በኩል ምንም ዓይነት ጥፋት ሳንፈጽም የዕለቱ ውድድር ሳይጀምር መሰረዙ ተገልፆልናል።
በማግስቱ ጨዋታው በወጣበት ፕሮግራም በአስተናጋጅነታችን፣ በሜዳችን የሚካሄድበት ፕሮግራም ይላክልናል ብለን ስንጠብቅ በ26/9/2011 ዓም ውድድሩ በ27/9/2011 በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም በዝግ ስታድየም እንደሚካሔድ የሚገልፅ ደብዳቤ ደረሰን።
ከፍተኛ ወጪ አውጥተን ወደ መቀሌ በመጓዝና በከተማችንም ቡድናችን በማዘጋጀት ያወጣነው ወጪ ከግምት ሳይገባ የዚህ ዓይነት ውሳኔ መስጠቱ በእጅጉ አሳዛኝ ነው።
በሌላ በኩ እኛ መቀሌ ለውድድር ሄደን የደረሰብንን በደለ በቃልና በተጨማሪም በፅሁፍ 3 ጊዜ ወሳኔ እንዲሰጠን ስንጠይቅ ምንም ሳይወሰን ዛሬ በእኛ ላይ በምሽት ስብሰባ ተደርጎ የተሰጠው ወሳኔ በእጅጉ ያሳዘነነ ከመሆኑም በላይ፥ ክለባችን ከሜዳው የሚያገኘውን ገቢ በማቋረጥ፣ ወደ አዳማ ጉዞ የምናወጣው ወጪ፣ የከተማዋን ነዋሪና ደጋፊ ሞራል የሚነካ ሁኔታን በመፍጠር ተጫዋቾቻችንን ላላስፈላጊ እንግልት ከመዳረግ በተጨማሪ የሞራልና አካል ድክመት የሚፈጥር በመሆኑ ክለባችን አይቀበለውም።
ስለሆነም በጋራ ያቋቋምነው ፌዴሬሽን ለሊግ ኮሚቴ ከተሰጠው ስልጣን ውጪ የዝግ ስታድየም ጨዋታ ውሳኔ መስጠት ያለበት የፍትህ አካል መሆኑ እየታወቀ፥ ሊግ ኮሚቴ ያሳለፈው ውሳነ ሕገ ወጥ ስለሆነ በአስቸኳይ ተሽሮ በሜዳችን፣ ለተመልካች ክፍት በሆነ ስታድየማችን እንድንጫወት ይደረግ ዘንድ እየጠየቅን፥ ከዚህ ውጭ ያለ አማራጭ ክለባችንን የሚጎዳ ስለሆነ የማንቀበለው መሆኑን እንገልፃለን።
የክለቡ ማኅተም
የክለቡ ሥራ አስኪያጅ ፊርማየኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያሳለፈው አዲስ ውሳኔ
የ27ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንድርታ ጨዋታ ግንቦት 29/2011ዓ.ም ይካሄዳል።
በ27ኛ ሳምንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ግንቦት 25/2011ዓ.ም ሊካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንድርታ ጨዋታ በጸጥታ ስጋት ምክንያት ጨዋታው መሰረዙ ይታወቃል፤ የሊግ ኮሚቴ ጨዋታው በጸጥታ ስጋት ምክንያት አለመካሄዱን ተከትሎ ግንቦት 27/2011ዓ.ም. በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ያለ ተመልካች /በዝግ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወቃል፤ ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ውሳኔውን በመቃወም ደብዳቤ ያስገባ ሲሆን ጉዳዩን የተመለከተው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቀደም ሲል የተሰረዘው ጨዋታ ከመንግስት ጸጥታ ኃይል በደረሰ መረጃ የደኅንነት ስጋት በስታዲየም እንዳለ በማሳወቁ በመሆኑ እና አሁንም በድጋሚ በተደረገው ውይይት ይህ ጉዳይ በጥብቅ ሊታይ የሚገባው በመሆኑ እና የመንግስት የጸጥታ ሀይልም የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ባሉበት ጨዋታው መካሄድ የሌለበት መሆኑን በጥብቅ አስገንዝቦናል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታን ግንቦት 27/2011ዓ.ም. ለማካሄድ የዒድ አል ፈጥር በዓል ስለሆነ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሐሙስ ግንቦት 29/2011ዓ.ም በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በ9 ሰዓት ያለ ተመልካች በዝግ ይካሄዳል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከፍተኛ አመራሮች አሜሪካ ውስጥ በካሊፎርንያ ግዛት ሎስ አንጀለስ ከተማ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር አዲስ በተቋቋመው ፓርቲ አጠቃላይ ሁኔታና የሀገራችን ኢትዮጵያን (የፖለቲካ) ነባራዊ ሁኔታን በተመለከተ ተወያዩ።
የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የሕዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ናትናኤል ፈለቀ በሰሜን አሜሪካ በሚገኙ ሦስት ከተሞች ከሚያደርጉት ውይይቶች የመጀመሪያው በሆነው የሎስ አንጀለስ ውይይት፣ የፓርቲው አመሠራረት፣ ለመሥራት የታቀዱ ሥራዎች እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በፓርቲው እና በአጠቃላይ ሀገሪቷ ውስጥ እንዲገነባ የሚፈለገው የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እንዴት ማገዝ እንደሚችሉ ውይይት ተደርጓል። በቪዛ መዘግየት ምክንያት ለስብሰባው መድረስ ያልቻሉት የኢዜማ ምክትል መሪ አቶ አንዱዓለም አራጌ የመክፈቻ የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኢዜማ ባደረገው በዚህ ውይይት፥ የሀገራችንን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እና የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችም የውይይቱ አካል ነበሩ። ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣውን ለውጥ “ሁለንተናዊ መሻሻል” ተብሎ የሚፈረጅ (reform) እንጂ አብዮት (revolution) አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክት ያስተላለፉት የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ ለውጡ ያልገባቸው (የሚያስጨንቃቸው) የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚፈጥሩት እንቅፋት፣ በየክልሉ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች እና ብዛት ያለው ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ቁጥር የለውጡ ከፍተኛ ተግዳሮቶች እንደሆኑ እና በየደረጃው መፍትሄ መስጠት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በኢዜማ እንቅስቃሴዎች ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን የሚችሉበት አደረጃጀት (ቻፕተሮች) በሁሉም የዓለማችን አካባቢዎች የሚዋቀሩ ሲሆን በሀገራችን ዜግነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲፈጠር እና ማኅበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን የሚፈልጉ በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በነዚህ መዋቅሮች ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ተላልፏል።
ከፓርቲው ዜና ጋር በተያያዘ፥ የኢዜማ ግብረ-ኃይል በአምስት አቅጣጫ ተንቀሳቅሷል። ከአዲስ አበባ በመነሳት በአምስት አቅጣጫ መዳረሻውን ያደረገ ግብረ-ኃይል ግንቦት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. እንቅስቃሴ ጀምሯል።
መነሻውን ከመስቀል አደባባይ ያደረገው ግብረ-ኃይል የኢዜማ ምክትል የፓርቲ መሪ አቶ አንዱዓለም አራጌና የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች በተገኙበት መሸኛ ተደርጎለታል።
ግንቦት 24 ቀንጉዞውን የጀመረው ግብረ ኃይል፣ በኢዜማ ለተደራጁ ለ216 የምርጫ ወረዳዎች ጊዚያዊ የእውቅና ደብዳቤ፣ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ደረሰኝ፣ የአባላት ፎርም እና የድርጅት ጉዳይ መመሪያዎቹን ተደራሽ ለማድረግ በአምስት አቅጣጫዎች ጉዞ ጀምሯል። በየመጀመሪያው ዙር ጉዞ ተደራሽ የሚደረግባቸው፡-
1. ከአዲስ አበባ – ደብረ ብርሃን፣ ደሴ፣ ወልዲያ መዳረሻውን ሰቆጣ
2. ከአዲስ አበባ – ፍቼ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ባህር ዳር አድርጎ መዳረሻውን ጎንደር
3. ከአዲስ አበባ – ሻሸመኔ፣ ሀዋሳ፣ ጌድኦ፣ አለታ፣ መዳረሻውን አዶላ (ክብረ መንግስት)
4. ከአዲስ አበባ – አምቦ፣ ነቀምት፣ ጊምቢ፣ ጅማ፣ መዳረሻውን ቤንች ማጂ
5. ከአዲስ አበባ – አዳማ፣ አሰላ፣ ወላይታ፣ ሀዲያ፣ ዳውሮ፣ ወልቂጤ፣ መዳረሻውን ጉራጌ በማድረግ ሲሆን በቀጣይም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሌሎች አዳዲስ ቦታዎችንና ከተማዎችን ተደራሽ የሚያደርግ ጉዞ እንደሚኖር ታውቋል።የሀገር መረጋጋትን ቀዳሚ ዓላማ አድርጎ የሚሠራው ኢዜማ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ አባላቱና ደጋፊዎቹ ይህንኑ ዓላማ ተፈፃሚ ለማድረግ እንዲሠሩ በሁሉም አቅጣጫ የሚጓዙት የግብረ ኃይሉ አባላት አፅዕንዎት ሰጥተው የሚያስገነዝቡ ይሆናል። በየአካባቢው የሚገኙ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም የየአካባቢው ሕዝብ ለግብረ -ኃይሉ አባላት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉላቸው ጥሪ ተላልፏል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
መንግስት በሀገር ውስጥ የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን በማስፋፋት ለሥራ ፈላጊ ዜጎች አስፈላጊውን ጥቅም ለማዳረስ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። መሥራት ለሚችሉ ዜጎች ሁሉ በሀገር ውስጥ ላሉ የሥራ ዕድሎች ቅድሚያ በመስጠት ሠርተው የሚለወጡበትን ሁኔታዎች በማመቻቸት ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሠርቶ ለመኖር በርካታ መልካም አጋጣሚዎች አሉ። ለዚህም ምሳሌ የሚሆኑ በሀገራቸው ሠርተው የተለወጡ በርካታ ወጣቶችን መጥቀስ ይቻላል።
ከዚህ ባለፈ ወደ ውጭ ሀገራት ለሥራ መሄድ የሚያስቡ ዜጎች እራሳቸውን ከአቻ ግፊትና ከሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሊጠብቁ ይገባል። ዜጎች ስለሚሄዱበት ሀገር ስላለው እውነታ ያላቸው ግንዛቤና መረጃ ውስንና የተዛባ በመሆኑ ከመሄዳቸው በፊት ስለሚሄዱበት ሀገር ባህል፣ ወግና ልማድ መረዳትና እና የዜጎችን መብት ደህንነትና ክብር ለማስጠበቅ ሲባል በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 923/2008 ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል።
ለጉዞ ከመነሳታችን በፊት ምን ማወቅ ይጠበቅብናል?
ወደ ውጭ ሀገር ሄደን ለመሥራት በምናስብበት ወቅት ጊዜ ሰጥቶ ማሰብ ይገባል። ለምን እንደምንሄድ፣ ከሄድን በኋላ የሚያጋጥሙንን መልካምና መጥፎ አጋጣሚዎች እንዴት መቋቋምና ማለፍ እንደሚገባን፣ የምንሄድበትን ሀገር ባህል፣ ወግ፣ ልማድና ስርዓት እንዴት ተላምደን መኖር እንደምንችል፣ የሠራንበትን ገንዘብ ወደ ሀገራች እንዴት መላክና መቆጠብ እንደምንችል፣ ኮንትራታችንን ጨርሰን መቼ ወደ ሀገራችን መመለስ እንዳለብን አስቀድመን ማቀድ ያስፈልጋል።
በአዋጅ ቁጥር 923/2008 መሠረት በውጭ አገር ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች እድሜያቸው ከ18 አመት በላይ የሆኑ፣ 8ኛ ክፍል ያጠናቀቁ (ወደ 9ኛ ክፍል የተዛወሩ)፣ በሚሄዱበት የሥራ መስክ ስልጠና ወስደው የብቃት ማረጋገጫ ያገኙ፣ የቅድመ ጉዞ ስልጠና ወስደው ሰርተፊኬት የያዙ፣ የጤና ኢንሹራንስ የተገባላቸው፣ ሙሉ የጤና ምርምራ ያደረጉና ከወንጀል ነጻ ሊሆኑ ይገባል።
ይህን ያሟሉ ዜጎች በአስቀጣሪ ኤጀንሲ በኩል ወይም በራሳቸው አማካኝነት ሥራውን በማፈላለግ ማለትም በቀጥታ ቅጥር አስፈላጊውን የቅጥር ፎርማሊቲ በማሟላት ቪዛውን አግኝተው መሄድ ይችላሉ። ብዙ ጊዜ በቀጥታ ቅጥር የሚጓዙ ሠራተኞች መደበኛ ስልጠና የወሰዱና ከቤት ሠራተኝነት ውጭ በልዩ ልዩ ሙያዎች የሰለጠኑ ሲሆን የሚሠሩትም በካምፓኒና በልዩ ልዩ አነስተኛ የቢዝነስ ተቋማት ውስጥ ነው። ከዚህ በፊት በውጭ ሀገር ሠርተው የተመለሱ ልምድ ይኖራቸዋል ተብሎ ስለሚታሰብ መረጃ ማቅረብ የሚችሉ ከሆነ ስልጠናውን መውሰድ ግዴታ ባይሆንም የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማቅረብ ይኖርባቸዋል።
ለሥራ የት ሀገር ነው መሄድ የሚቻለው?
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በቤት ሠራተኝነት የሚሄድ ከሆነ ሊጓዝ የሚችለው በኤጀንሲዎች አማካኝነት ብቻ መሆኑን ሊረዳ ይገባል። የሥራ ስምሪት ማድረግ የሚችለውም አገሪቷ የሁለትዮሽ ስምምነት ወደተፈራረመችባቸው ሀገራት ብቻ ነው። የሁለትዮሽ ስምምነት የተፈፀመባቸው መዳረሻ ሀገራት ለጊዜው ሳውዲ አረቢያ፣ ኳታርና ጆርዳን ሲሆኑ ከሌሎች አገሮች ጋር የሚደረገው ስምምነትም በሂደት ይቀጥላል።
ስምምነት በተፈፀመባቸው ሀገሮች የደመወዝ መጠን ስንመለከት ከኳታር መንግስት 1200 ለቤት ሠራተኛና 1300 ለእንክብካቤ (care giver) የኳታር ሪያል፣ ከጆርዳን መንግስት ለጀማሪ 225 ዶላር፣ ልምድ ላላው 250 ዶላር፣ ከሳውዲ አረቢያ መንግሰት ጋር 1000 የሳውዲ ሪያል እንዲሆን ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በሠራተኞችና በአሠሪዎች የሚሸፈኑ ወጪዎች
አንድ ሠራተኛ በሥራ ለመሰማራት አስፈላጊውን መስፈርት ካሟላና ብቁ ከሆነ በአዋጁ የተደነገጉ የቅጥርና ምልመላ መንገዶችን በመከተል አስፈላጊውን መፈጸም እና ወጪዎችን መሸፈን ይገባል።
- አሠሪው ወይንም ኤጀንሲው የሚሸፍናቸው ወጪዎች
በአሠሪው የሚሸፈኑ ወጪዎች ሠራተኛውን ወደ ተቀባይ አገር ለማድረስ፣ በተቀባይ አገር ያለችግር እንዲቆይና እንዲሠራ ለማድረግ፣ እንዲሁም በሥራ ላይ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የሚወጡ ወጪዎች ናቸው።
እነርሱም የተቀባይ አገር የመግቢያ ቪዛ፣ የደርሶ መልስ መጓጓዣ፣ የሥራ ፍቃድ፣ የመኖሪያ ፍቃድ፣ የሥራ ውል ማጽደቂያ ክፍያዎች፣ የመድህን ዋስትና ሽፋን እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኝ የተቀባይ አገር ኤምባሲ ወይም ቆንስላ ጽህፈት ቤት የሚከፈል ከቪዛና ከሰነድ ማረጋገጥ ጋር የተያያዘ ማናቸውም ወጪዎች ናቸው።
- በሠራተኛው የሚሸፈኑ ወጪዎች
አንድ ሠራተኛ ለሥራ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በሚጓዝበት ወቅት የሚያወጣው ወጪ በአብዛኛው በህይወት ዘመኑና በማህበራዊ ህይወቱ ውስጥ የትኛውም ሰው ስለሚጠቀምባቸው የሚያወጣቸው ወጪዎች ናቸው።
እነርሱም ለልደት ሰርተፊኬት፣ ለፓስፖርት፣ ለክትባት፣ ለህክምና ምርመራ፣ ለሙያ ብቃት ማረጋገጫ፣ ከወንጀል ነፃ ማስረጃ ማረጋገጫ ወጪዎች ናቸው። እነኝህ ክፍያዎች በሙሉ አገልግሎቱን ለሰጡ ሌሎች መሥሪያ ቤቶችና ተቋማት የሚከፈል እንጂ ምልመላውን ለሚያከናውነው ኤጀንሲ የሚከፈል አይደለም። ኤጀንሲው ምንም አይነት ክፍያ ከሠራተኛው ቢጠይቅ ህገወጥ ያደርገዋል።
ይሁን እንጂ ለሥራ ወደ ውጭ አገር ለመሄድ አስፈላጊ ሁኔታዎች ተጠናቀው ያለበቂ ምክንያት ሠራተኛው ወደ ሥራ ባይሰማራ ከቅጥሩ ጋር በተያያዘ አሠሪው ያወጣውን ወጪ ሠራተኛው እንዲከፍለው ሊጠይቅ ይችላል። በተመሳሳይ መንገድ በተራ ቁጥር 2 ላይ የተጠቀሱትን ወጪዎች ሠራተኛው አውጥቶ በራሱ ጉድለት ባልሆነ ምክንያት በሥራ ላይ ካልተሰማራ ኤጀንሲው ወይም አሠሪው የሠራተኛውን ወጪ የመተካት ግዴታ ይኖርበታል።
ለውጭ አገር ለሥራ ስምሪት የሚሰጡ ስልጠናዎችና ማሰልጠኛ ተቋማቱ
ለውጭ አገር ሥራ ስምሪት የሚሰጡ ስልጠናዎች ሶስት ሲሆኑ እነሱም በቤት አያያዝ (Household Service) በቤት ውስጥ ሥራ (Domestic Help) እና በእንክብካቤ ሥራ (Care Giving) ናቸው።
የእነዚህ ሙያዎች የስልጠና መሳሪያዎች፣ የሙያ ደረጃ፤ ሥርዓተ ትምህርት እና የብቃት ማረጋገጫ ምዘና መሳሪያዎች ሲዘጋጁ ለማንኛውም ዜጋ እንዲያገለግል ሲሆን ወንድም ሆነ ሴት በፍላጎቱ ሊሰለጥን ይችላል። ሠልጣኞች ስልጠናውን በግላቸው ሊሠሩበት፣ በአገር ውስጥ ሊቀጠሩበት እንዲሁም ወደውጭ አገር ሊሰማሩበት እንደሚችሉ ሊገነዘቡና በምልመላ ወቅትም ሊነገራቸው ይገባል። በተጨማሪም በስልጠናው የተሳተፈ ሁሉ የብቃት ምዘናውን ያልፋል ማለት አይደለም፣ የብቃት ምዘናውን ያለፈ ሁሉ ቀጣሪ ያገኛል ማለትም አይደለም። በመሆኑም በተጠቀሱት ሙያ እንዲሰለጥኑ የተደረጉ ሁሉ ወደአረብ ሀገር መሄድን እንደመብት ሊያዩት አይገባም።
ይሁን እንጂ ወደአረብ አገር መሄድ የሚፈልጉ ሰልጣኞች ከላይ በተጠቀሱት ሦስት ሙያዎች ከሰለጠኑ በኋላም የብቃት ምዘና ማረጋገጫ ተፈትነው ማለፍና ሰርተፊኬት መያዝ ይኖርባቸዋል። ስልጠናው በየክልላቸውና በአቅራቢያቸው በሚገኙ በተመረጡ ማሰልጠኛ ተቋማት ይሰጣል። ስልጠናው በየክልላቸውና አቅራቢያቸው የመሰጠቱ ጠቀሜታም የሠራተኞች ምልመላ በየክልላቸው የሚካሄድ በመሆኑ፣ አስፈላጊ መረጃዎችን ለማጣራትና ለማረጋገጥ፣ የዜጎችን ደህንነትና ክብር በቅርብ ለመከታተል እና ከስልጠና፣ ከምልመላ ጋር ተያይዞ ለአላስፈላጊ ወጪና የመብት ጥሰቶች እንዳይጋለጡ ያግዛል።
ስልጠናን በተመለከተም፣ የመንግስት ማሰልጠኛ ተቋማት ትምህርቱን በነፃ የሚሰጡ ሲሆን ማንኛውም ሰልጣኝ በክልሉ በሚገኝ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ወይም በየዞኑና ክፍለ ከተማው ወይም ወረዳዎች በሚገኙ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤቶች በመመዝገብ ለየማሰልጠኛዎቹ በመላክ እንዲሰለጥኑ ይደረጋል።
በተጨማሪም የመንግስት ማሰልጠኛ ተቋማት የተደራሽነትና የአቅም ውስንነት ስላለባቸው በፌደራልና በክልል በሚገኙት የቴ/ሙ/ት/ስ/ኤጀንሲ ቢሮዎች ለግል ማሰልጠኛ ተቋማት ፍቃድ በመስጠት በማሰልጠን ሥራው እንዲሳተፉ ተደርጓል። በመሆኑም የግል ማሰልጠኛ ተቋማት የስልጠና ጥራታቸው ላይ ጥንቃቄ በማድረግና አስፈላጊ የስልጠና ቁሳቁሶችን በማሟላት የትምህርቱን ጥራት እንዲጠብቁ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። ፍቃድ ሰጪ አካላትም የጀመሩትን ክትትል፣ ቁጥጥርና ድጋፍ በማጠናከር እገዛ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን።
በየክልሉ የተመረጡ የመንግስት ማሰልጠኛ ተቋማት ዝርዝር
በመንግስት የተመረጡ 66 ማሰልጠኛ ተቋማት ሲሆኑ ስልጠናውም በሁሉም ክልል በነፃ ይሰጣል።
የማሰልጠኛ ተቋማት ዝርዝር በየክልሉ፡-
አማራ ክልል
- ባህርዳር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ወልድያ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ደሴ ወ/ሮ ስህን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ከሚሴ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ
- ደ/ብርሃን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ጎንደር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- እንጂባራ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ቡሬ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ
- ደብረታቦር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ደብረ ማርቆስ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ሠቆጣ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ
ደቡብ ክልል
- አዋሳ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- አርባ ምንጭ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ሶዶ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ዱራሜ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
- ሆሳዕና ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ወራቤ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
- ወልቂጤ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ቡታጅራ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
- ሀላባ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
- ይርጋለም ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
- ዲላ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
ትግራይ ክልል
- መቀሌ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ዶ/ር ተወልደ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ
- አክሱም ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- ዶ/ር አርዕያ ካሳ ኮሌጅ
- ውቅሮ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
- (ማይጨው) ጥላሁን ይግዛው ፖሊቴክኒክ
- አላማጣ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ
አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
- እንጦጦ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና (ቴ/ሙ/ት/ስልጠና) ኮሌጅ
- ጄነራል ዊንጌት ቴ/ሙ/ት/ስልጠና ኮሌጅ
- ንፋስ ስልክ ቴ/ሙ/ት/ስልጠና ኮሌጅ
- ምሥራቅ አጠቃላይ ቴ/ሙ/ት/ስልጠና ኮሌጅ
- የካ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
- ልደታ ማኒፋክቸሪንግ ኮሌጅ
- አዲስ ከተማ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ
- ቂርቆስ ማኒፋክቸሪንግ ኮሌጅ
- አቃቂ ቴ/ሙ/ት/ስልጠና ኮሌጅ
ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር
- መለስ ዜናዊ ቴ/ሙ/ት/ስልጠና ኮሌጅ
ኦሮሚያ ክልል
- ሀሮማያ ቴክኒክና ሙያ
- አሰላ ቴክኒክና ሙያ
- ሻሸመኔ ቴክኒክና ሙያ
- መርቲ ፖሊ ቴክኒክ
- ቢሾፍቱ ቴክኒክና ሙያ
- ጂማ ቴክኒክና ሙያ
- መቱ ቴክኒክና ሙያ
- መቱ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ
- ነቀምት ቴክኒክና ሙያ
- ነቀምት ጤና ሳይንስ ኮሌጅ
- ባቱ ተራራ ቴክኒክና ሙያ
- ዶና ባርበር ቴክኒክና ሙያ
- ፍቼ ቴክኒክና ሙያ
- መርቲ ፖሊ ቴክኒክ
- አዳማ ፖሊ ቴክኒክ
- አብቦ ፖሊ ቴክኒክ
- ሰበታ ፖሊ ቴክኒክ
- ወሊሶ ፖሊ ቴክኒክ
- አጋሮ ፖሊ ቴክኒከ
- አደላ ፖሊ ቴክኒክ
- ቡሌ ሆራ ፖሊ ቴክኒክ
- ጨርጭር ፖሊ ቴክኒክ
- ደደር ፖሊ ቴክኒክ
- አርሲ ነገሌ ፖሊ ቴክኒክ
- ሀሰሳ ፖሊ ቴክኒክ
- ጊምቢ ፖሊ ቴክኒክ
- ወንጂ ፖሊ ቴክኒክ
ምንጭ፦ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ግንባታው በሦስት ዓመት የጊዜ ገደብ ውስጥ የሚጠናቀቀው የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ከኦጋዴን ኢላላና ካሉብ (ሶማሊ ክልል) ተነስቶ ጅቡቲ ወደብ የሚደርስ ሲሆን ጅቡቲ ላይ ነዳጁ ይቀነባበራል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ኢትዮጵያ ለምትገነባው የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ከጅቡቲ ጋር ስምምነት ተፈራረመች።
በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መንግስታት መካከል የተፈረመው ስምምነት ኢትዮጵያ ለምትገነባው የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ በጅቡቲ ምድር ለማቀነባባሪያ የሚሆን መሬት ለማግኘትና ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችል ነው።
ስምምነቱን የፈረሙት በኢትዮጵያ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ሳሙኤል ኡርካቶ (ዶ/ር) ና በጅቡቲ የነዳጅና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትር ሚስተር ዮኒስ አሊ ጒዲ ናቸው።
760 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ማስተላለፊያ ቧንቧ ግንባታው 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጅ ሲሆን 700 ኪሎ ሜትር በኢትዮጵያ፣ 60 ኪሎ ሜትሩ ደግሞ በጅቡቲ ምድር የሚያልፍ ነው።
◌ ALSO: Ethiopia is ready to use Red Sea Ports of Assab and Massawa of Eritrea
ግንባታው በሦስት ዓመት የጊዜ ገደብ ውስጥ የሚጠናቀቀው የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ከኦጋዴን ኢላላና ካሉብ (ሶማሊ ክልል) ተነስቶ ጅቡቲ ወደብ የሚደርስ ሲሆን ጅቡቲ ላይ ነዳጁ ይቀነባበራል።
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ዶ/ር ሳሙኤል ኡርካቶ ስምምነቱ የሁለቱን አገራት የረጅም ጊዜ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ግንኙነት እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል። ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው የተፈጥሮ ሃብት መጠቀሚያ መሠረተ ልማት የአገራቱን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያጠናክር ነው ብለዋል። በከፍተኛ ድርድር ውሳኔ ያገኘው ይህ ስምምነት ዓለም አቀፍ መስፈርት ያሟላ መሆኑንም ዶ/ር ሳሙኤል አክለዋል።
የጅቡቲው የነዳጅና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትር በበኩላቸው ስምምነቱ የሁለቱን ወንድማማች አገራት የጋራ ተጠቃሚነት ስለሚያጎለብት ጅቡቲ ጥበቃውን ታጠናክራለች ነው ያሉት። የመሠረተ ልማት ግንባታው በጅቡቲ በማለፉ ከምታገኘው ጥቅም ባሻገር በርካታ ዜጎቿን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧውን መቀመጫውን ሆንግ ኮንግ ከተማ ያደረገው ያቻይናው GCL-Poly ኩባንያ እንደሚገነባው ተጠቁሟል። GCL-Poly ኩባንያ የተቋቋመው እ.ኤ.አ በ1996 ሲሆን፥ በተለያዩ የኃይል ማመንጫ ግንባታዎች ላይ የተሰማራው ጎልደን ኮንኮርድ ሆልዲንግስ ሊሚትድ (Golden Concord Group Limited) የተባለው ግዙፍ ድርጅት ቅርንጫፍ (subsidiary) ነው።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦
- የጊዳቦ ግድብ ሥራ ፕሮጀክት በዚህ ወር ይመረቃል
- ባለፉት 6 ወራት ለኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 484 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡ ተገለጸ
- የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሮኒክ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ) ማዕከል ኢትዮጵያ ውስጥ ሊገነባ ነው
- አዳማ ከተማ ውስጥ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው እና ጥቅም ላይ የማይውሉ መድኃኒቶችን ማስወገጃ ማዕከል ተገነባ
- ቮልስዋገን በኢትዮጵያ የመኪና መገጥጠሚያ ፋብሪካ ሊገነባ ነው፤ የጀርመን የቴክኖሎጂ ድርጅቶች በስፋት ለመግባት እያመቻቹ ነው
[caption id="attachment_9717" align="aligncenter" width="600"] PHOTO: Ethiopian Broadcasting Corporation[/caption]
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና የውጪ ምንዛሬ እጥረት ለሀገር በቀል የመድኃኒት እና የሕክምና መገልገያ አምራቾች እውነተኛ ፈተና መሆን አለመሆናቸው በገለልተኛ አካል ሊጠና ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ባለድርሻ አካላት ተናገሩ።
ጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም ከሀገር ውስጥ አምራቾች በተደረገው ውይይት የ6 ወር የመድኃኒት አቅርቦት አፈፃፀም 25% መሆኑን ተከትሎ ለአቅርቦቱ ዝቅተኛ አፈፃፀም በተደጋጋሚ በምክንያትነት የሚሰጡት የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በገለልተኛ አካል ተጠንቶ ድጋፍ የሚያስፈልገውን በመደገፍ የሚያጭበረብረውን በማጣራት እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል ሲሉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ገልፀዋል።
ኤጀንሲው ለሀገር ውስጥ አምራቾች በቅድሚያ ክፍያ እንዲሁም 25 በመቶ ጨረታ ላይ እንዲወዳደሩ እንደሚደግፉ የተጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ አሁንም አምራቾች መድኃኒቶችን በበቂ መጠን ጥራት ማቅረብ አለመቻላቸው አጠራጣሪ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
◌ News: Humanwell Healthcare Group inaugurates Humanwell Pharmaceutical Ethiopia PLC in Chacha town
እንደአስተያት ሰጪዎች ገለጻ ሀገር በቀል አምራቾች ኤጀንሲው የሚሰጣቸው የቅድሚያ ክፍያ ሒሳብ በአግባቡ ቃላቸውን ለመተግበር እያዋሉት መሆኑ ወይም ሌላ ዓላማ መዋሉ ሊጠና ይገባል ብለዋል። አክለውም የሚሰጠውን ገንዘብ ለሌላ የግል ንግድ እየተጠቀሙበት መሆኑን ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜና የቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች በአዳማ ከተማ የግማሽ ዓመት አቅድ አፈጻጸም ላይ እንዳሉት ሀገር በቀል የመድኃኒት አምራቾች ኤጀንሲው በሚያቀርበው ገንዝብ ለግል አቅራቢዎች ትርፍ ለማሳደድ እንደሚያውሉት መረጃ አለ ሲሉ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም የሚደረገው ድጋፍ በአግባቡ የመያጠቀሙበት ከሆነ በሂደት እየለዩ እርምጃ ለወሰድ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚሁ ውይይት በተጨማሪ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ የጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል አቅርቦቱን የበለጠ ለማሻሻል ብቻውን መስራቱ ውጤታማ ሊያደርገው እንደማይችል የኤጀንሲው የግዥ ትንበያና ገበያ ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብይ ክፍሎም አብራርተው የሀገር ውስጥ አምራቾቹ ሊያስቡበት እንደሚገባም አቶ አብይ አክለው ገልፀዋል።
◌ News: SanSheng Pharmaceutical PLC inaugurated in the Eastern Industry Zone in Dukem, Ethiopia
የአገር ውስጥ አምራቾች አፈፃፀማቸውን መፈተሽ እንዳለባቸውና አፈፃፀማቸው ዝቅ ባለ ቁጥር በመድኃኒት እጦት የሚያልፈውን የሰው ሕይወት ሊያስቡ እንደሚገባ የመድኃኒትና የህክምና መሣርያዎች ግዢ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ጎይቶም ጊጋር ገልፀዋል።
የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ሣሙኤል ኃይሉ በበኩላቸው በአሁኑ ሠዓት የመድኃኒት እጥረት እንደ ቀልድ የሚታይ ጉዳይ አይደለም ብለዋል።
አቅርቦቱ ዝቅ እንዲል ካደረጉ ምክንያቶች መካከል የውጭ ምንዛሬና የመብራት መቆራረጥ በዋናነት በውይይቱ የተጠቀሱ ሲሆን ኤጀንሲው ይህን ለማስተካከል አፈፃፀማቸውን ለመለካት የሚያስችል ነጥቦችን የያዘ ረቂቅ ሰነድ (KPI) ቀርቦ የጋራ ማድረግ ተችሏል።
በመጨረሻም ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ ባንክ፣ የኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት መገኘታቸው በቀጣይ ችግሩን በመቅረፍ የሕብረተሠቡን የመድኃኒት ፍላጎት ለማሟላት ያስችላል ብለዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
“በርቱ! ባየሁት ነገር ተደስቻለሁ… የሥራ ፍላጎት ተነሳሽነት ለለውጥ ወሳኝ መሆኑን ከጴጥሮስ መረዳት እንችላለን” – የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ የካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገኘተው የሥራ እንቅስቃሴን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በቆይታቸውም የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በጋራ ያስገነቡትን የልብ ህክምና ማዕከል፣ በሀገሪቱ ብቸኛና የመጀመሪያ የሆነውን የተመረዙ ሰዎች የሚታከሙበት የቶክሲኮሎጂ ህክምና ማዕከል እንዲሁም የእናቶችና ህጻናት የህክምና ከፍልን ዋና ዳይሬክተሩ ጎብኝተዋል።
በሆስፒታሉ ፈጣን እድገት ተደስቻለሁ ያሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የልብ ህክምና አገልግሎት መስጠት መጀመሩና በሀገሪቱ ካለው የህክምና እጥረት አኳያ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸው ብዙም ትኩረት ያልተሰጠበት የመመረዝ ህክምና በሆስፒታሉ መሰጠቱም ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።
◌ ቪዲዮ፦ የኢትዮጵያዊያን-አሜሪካዊያን ዶክተሮች ቡድን እያስገነባ ያለው ግዙፉ ዓለምአቀፋዊ ሆስፒታል በአዲስ አበባ
ሆስፒታሉ የሰሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) ህክምና ብቻ ይሰጥ እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር ቴዎድሮስ በአሁኑ ሰዓት አጠቃላይ መሠረታዊ የሆስፒታል አገልግሎቶችን መስጠት መጀመሩና የተወሰኑ የህክምና አገልግሎቶች ላይም የበለጠ ስፔሻላይዝድ ለማድረግ መሥራቱ በጣም እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
ከዚህ ሌላም የሆስፒታሉ ሰራተኞች የሥራ ተነሳሽነትም በጣም እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል። ለሆስፒታሉ ፈጣን ዕድገትም ሁሉም የሆስፒታሉ ሠራተኞች ዋና ተዋናይ መሆናቸውን እንዳዩ ገልጸው በዚህም የሥራ ፍላጎት መኖር ለለውጥ ወሳኝ መሆኑን ከጴጥሮስ መረዳት እንችላለን ብለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በዚሁ ዕለት የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ከመጎብኘታቸው በተጨማሪም ከየኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) የጤና ሚኒስትር አሚር አማን (ዶ/ር) እንዲሁም ከኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር ተገናኝትው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ከሰኔ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀን ጀምሮ ዋና መቀመጫው ጄነቭ፣ ስዊዘርላንድ የሆነውን የዓለም ጤና ድርጅትን (WHO) በዋና ዳይረክተርነት የሚመሩት ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከዚህ ስልጣናቸው በፊት ከ ከኅዳር 20 ቀን 2005 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ከጥቅምት 2 ቀን 1998ዓ.ም. እስከ ኅዳር 19 ቀን 2005 ዓ.ም. ደግሞ የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።
ምንጭ፦ የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- የካንሰር ህክምና አገልግሎት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል
- የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የካንሰርና የልብ ህክምና ማዕከል ግንባታ 56 በመቶ ደርሷል
- ከሆዱ 120 ሚስማር የወጣለት ታካሚ መዳኑ ተገለጸ ― የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል
- የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የፎረንሲክ ምርመራ በጋራ ለማከናወን ተስማሙ
- አዳማ ከተማ ውስጥ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው እና ጥቅም ላይ የማይውሉ መድኃኒቶችን ማስወገጃ ማዕከል ተገነባ
አዲስ አበባ (ዋልታ)– ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ድርጅቶች የሚመረቱ የታሸጉ ውሃዎች ላይ ሁነኛ የሆነ የጥራት ችግር እንዳለ ተገለፀ።
በአገሪቱ ለመጠጥ ውሃ የሚውሉት የታሸጉ ውሃዎች ላይ በሚታየው የጥራት መጓደል ምክንያትም በኅብረተሰቡ ላይ አሉታዊ የጤና ችግር መንስዔ ከመሆናቸው ባሻገር አገሪቱ ማግኘት ያለባትን ገቢ አለማግኘቷም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ በውሃ ምርቶች ላይ የሚስተዋሉትን ችግሮችና የጥራት ማስጠበቅ ሥራዎች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ጥር 23 ቀን 2011 ዓ.ም. አካሄዷል።
◌ ቪዲዮ፦ የታሸጉ ውሃዎች በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣው ፍላጎት እና የውሃዎቹ ያልተመጣጠነ ዋጋ
በመጠጥ ውሃ የፕላስቲክ ማሻጊያዎቹ ክዳን ላይ የሚለጠፉትና ከፍተኛ የውጭ ምናዛሬን የሚጠይቁ ግብዓቶች ተመሳስለው በሀገር ውስጥ የሚሠሩ በመሆኑ የማሸጊያዎችም የምርት ጥራት ላይ ችግር እየተስተዋለ በመሆኑ ይህን ለማስቀረት እየተሠራ ይገኛል።
በሀገሪቱ እየተስፋፉ ያሉ የውሃ ማምረቻ ተቋማት ንፁ ውሃን በማቅረብ እና ኢኮኖሚውን ከመደገፍ አንጻር አበረታታች ሥራ ቢሠሩም አሁንም ግን ዘርፉ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚንስትር ዴኤታ አቶ እሸቱ አስፋው ተናግረዋል።
በርካታ በሀገሪቱ የሚኖሩ ኤምባሲዎችና የውጭ ኮሚኒቲ አካላት የታሸጉ ውሃዎችን ወደ አገር ውስጥ እያስገቡ በመሆኑ፤ በዘርፉ ያለውን የጥራት ችግር ያሳያል።
የምርቶቹን የጥራት ደረጃ በማሻሻል ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ ሀገሪቱን ከዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማሳደግ መሥራት እንደሚገባ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
የምርቶችን የአመራረት፣ የአስተሻሸግ፣፤ የማጓጓዝ እና የአቀማመጥ ሆነ ለገበያ በሚቀርቡበት ጊዜ ያለው አያያዝ ችግር ምርቶቹን በከፍተኛ ሁኔታ የጥራት ችግር እንዲጋለጡ ማድረጉን ሚኒስትር ዲኤታው አክለው ገልጸዋል።
አሁን በሥራ ላይ የሚገኙ ከ 65 በላይ የታሸጉ ውሃ አምራቾች አለም አቀፉን የጥራት ደረጃ በጠበቀ መልኩ እንዲያመርቱ እየተሠራ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ይልማ መንግስቱ ተናግረዋል።
ምንጭ፦ ዋልታ ሚዲያ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- ባለፉት 6 ወራት 7ሺህ 8 መቶ ባለቤት አልባ ውሾችን ማስወገዱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ
- አዳማ ከተማ ውስጥ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው እና ጥቅም ላይ የማይውሉ መድኃኒቶችን ማስወገጃ ማዕከል ተገነባ
- ኬር ኢትዮጵያ በ7 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ወጭ ያስገነባውን የምርምርና የስልጠና ማዕከል ለሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አስረከበ
- “ከተሽከርካሪ ፍሰት ነፃ የሆኑ መንገዶች ቀን” – መንገዶችን በወር አንድ ቀን የእግር ጉዞና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጊያ
- ደኅንነታቸውና ያልተረጋገጠ የስፈተ ወሲብና ጸጉርን ለማሳድግ የሚረዱ እና የከንሰር መድኃኒቶች በህገወጥ መንገድ ሊገቡ ሲሉ ተያዙ
አዳማ (ኢዜአ)–የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒት እና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን 22 ነጥብ 78 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ህገ-ወጥ መድኃኒቶች እንዲወገዱ ማድረጉን አስታወቀ።
ባለፉት ስድስት ወራት በጤና አገልግሎት ግብአቶች ላይ ቁጥጥርና ፍተሻ ተደርጎ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ መድኃኒትና የህክምና መገልገያ መሣርያዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉም ተመልክቷል።
በባለስልጡኑ የፕሮጀክትና ፕላን ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ወ/ሮ ዓለም እሸቴ እንዳሉት መስፈርቱን ያላሟሉና ህገ ወጥ የሆኑ መድኃኒቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉና በአግባቡ እንዲወገዱ የተደረገው ባለፉት ስድስት ወራት ነው። መደኃኒቶቹ የተያዙት በመውጫና መግቢያ ኬላዎች ላይ በተደረገ የቤተ-ሙከራ ፍተሻ እንዲሁም በኦዲቲንግ ኢንስፔክሽን ወቅት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከውጭ ሀገር የሚገቡ መድኃኒቶችን ጥራት፣ ደኅንነትና ፈዋሽነታቸውን ለማረጋገጥ ባለስልጣኑ ከዓለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅትና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካለት ጋር በመተባበር የቁጥጥር ሥራ ማከናወኑንም ገልጸዋል። በቶጎ ውጫሌ፣ ሞያሌ፣ ቃሊቲ፣ መተማና ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ባለስልጣኑ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ወ/ሮ ዓለም አንዳሉት በግማሽ በጀት ዓመቱ የምግብ ጥራትና ደህንነት ቁጥጥር ውጤታማነትን ለማሻሻል በተደረገው እንቅስቃሴም 2ሺህ 389 ሜትሪክ ቶን ዱቄት፣ ሩዝ፣ አኩሪ አተርና የምግብ ጥሬ እቃ ተይዟል።
“በተደረገ ፍተሻም ምግብና ጥሬ እቃው የመጠቀሚያ ጊዜው በመቃረቡ፣ አምራች ካምፓኒው ባለመታወቁ፣ በጉዞ ወቅት በደረሰ ጉዳትና በነቀዝ በመባላቱ ምክንያት ወደመጣበት አገር እንዲመለስ ተደርጓል” ብለዋል።
በተጨማሪም ከ200 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው ፓስታ፣ ዱቄት፣ ዘይት፣ ብስኩት፣ ጁስ፣ ሩዝ፣ ወተት፣ ፍራፍሬና የምግብ ጥሬ እቃዎች በተለያየ ምክንያት በመበላሸታቸውና አስፈላጊውን መስፈርት ያላሟሉ ሆነው በመገኘታቸው ከንግድ ተቋማት ውስጥ ተሰብስበው እንዲወገዱ መደረጉን ነው ያስረዱት።
ዘይት፣ ጨው፣ የዱቄት ወተት፣ ጁስና ሌሎች 15 አይነት የምግብ ናሙናዎች ላይ በተካሄደ የቤተሙከራ ምርመራ ሰባቱ መስፈርቱን ሳያማሉ በመቅረታቸው ምርቱ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ መደረጉን አስረድተዋል።
“በመንፈቅ ዓመቱ በጤና አገልግሎት ግብአቶች ላይ ቁጥጥርና ፍተሻ ተደርጎም 4 ነጥብ 23 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው መድኃኒትና የህክምና መገልገያ መሣሪያዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርጋል” ብለዋል። ዋጋቸው ከ457 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የውበትና የንጽህና መጠበቅያ ምርቶችም ቁጥጥርና ፍተሻ ተደርጎላቸው ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን አስረድተዋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት ሄራን ገርባ በበኩላቸው ህገ-ወጥ የጤና አገልግሎትና ግብአቶችን ለመቆጣጠር ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በስሩ ስድስት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችንና 17 የመውጫና መግቢያ ኬላዎችን በማደራጀት እየሠራ ይገኛል።
በየደረጃው በሚደረጉ የቁጥጥር ሥራዎች ህዝቡን ተሳታፊ ለማድረግ በተለያዩ የህዝብ ንቅናቄ መድረኮች ላይ ህዝብን የማስገንዘብ ሥራ መሠራቱን ወ/ሪት ሄራን ገልጸዋል። በእዚህም ህገ ወጥ የምግብና የመድኃኒት ንግድን እንዴት መከላከል እንደሚቻልና በዘርፉ ቁጥጥር አለማድረግም በሀገር ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ህብረተሰቡ እንዲገነዘበው የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አመለክተዋል።
ዳይሬክተሯ እንዳሉት በቁጥጥር ሥራው ካጋጠሙ ችግሮች መካከል የምግብ ቤተሙከራ አለመጠናከር፣ የባለሙያዎች አቅም ውስንነት፣ የባለድርሻ አካላትና የህዝብ ክንፉ ተሳትፎ የተደራጀና የተቀናጀ አለመሆን ይጠቀሳሉ። ይህንን ችግር ለማቃለል የባለስልጣኑን አዋጅ የመከለስ ሥራ እየተጠናቀቀ ሲሆን ከምግብና መድኃኒት ጋር የተጣጣመ የአደረጃጀት ትግበራ፣ የሰው ኃይል ድልድልና የህግ ማዕቀፎች ዝግጀት መደረጉንም አመልክተዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የአሜሪካ ኢምባሲ 2ኛውን ‹‹SolveIT›› የተሰኘ ሀገር አቀፍ የፈጠራ ውድድርን የኢዲስ አበባ ከተማን በይፋ አስጀመረ። ኢምባሲው ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከጃፓን ዓለማቀፋዊ ኮኦፐሬቲቭ ኤጀንሲ (Japan International Cooperation Agency – JICA) እና ከአይኮግ ላብስ (iCog Labs) ጋር በመተባር ነው ውድድሩን ይፋ ያደረገው።
ፕሮጀክቱ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 15 ከተሞች የሚካሄድ ሲሆን ቴክኖሎጂ ነክ የፈጠራ ሥራዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው።
ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂ ነክ የፈጠራ ሰራዎች ያሏቸው ወጣቶች የሚሳተፉበት ይህ ውድድር የፈጠራ ባላሙያዎቹ ሥራዎቻቸውን ሊያዳብር የሚችል ስልጠና በየከተሞቹ ይሰጣቸዋል።SolveIT ሀገር አቀፍ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድርን የአሜሪካ ኢምባሲና የጃፓን ዓለማቀፋዊ ኮኦፐሬቲቭ ኤጀንሲ ፕሮጀክቱን በገንዘብ ይደግፉታል። ተመሳሳይ ፕሮግራሞች በየከተሞቹ የሚዘጋጁ ሲሆን የተመረጡ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎች ለሽልማት ይበቃሉ ተብሏል።
◌ VIDEO: These two Ethiopian students are working to launch their own rocket – the future Eng. Kitaw Ejigu
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽን ልማትና ምርምርና ዘርፍ ዳይሬክተር ጀነራል ካህሊድ አህመድ (ዶ/ር) በፕሮጀክቱ ተመርጠው የመጡ የፈጠራ ሥራዎች ገበያውን እንዲቀላቀሉ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
ተጨማሪ ስልጠና የሚያስፈልጋቸውን በቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ማዕከላት በማስገባትና የሥራ ማስጀመሪያ ገንዘብ በመደጎም ጭምር ድጋፍ እንደሚያደረግ አረጋግጠዋል።
የአሜሪካ ኤምባሲ በኢትዮጵያ በዋናነት ስፖንሰር የሚያደርገው SolveIT ውድድር በወጣት ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የኢንጂነሪንግ፣ የአርት እና የሒሳብ (STEAM) በወጣቶች ዘንድ ይበልጥ እንዲጎለብቱ የሚያበረታታ ውድድር ሲሆን ፥ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ለሚኖሩበት ህብረተሰብ፣ ብሎም ለሀገራቸው ችግር ፈቺ የሆኑ የቴክኖሎጂ፣ የሶፍትዌርና የሀርድዌር ፈጠራዎችን በመፍጠር እንዲሳተፉ ያደርጋል።
ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 28 ዓመት የሆነ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በሚኖሩበት ከተማ ሆነው ህብረተሰባቸው የሚያጋጥመውን ችግር ሊፈታ የሚፍል ፈጠራ ለመፍጠር ለዘጠኝ ወራት ያህል ጊዜ ተሰጥቷቸው ይሠራሉ። በዚህም ጊዜ ከአወዳዳሪዎች በተመደቡላቸው ባለሙያዎች ስልጠና ይሰጣቸዋል። ፈጠራዎቻቸው ከሞባይ አፕ (mobile app) ጀምሮ እስከ ከፍ ያለ የኮምፒዩተር ሶፍትዌር ሊሆን ይችላል። በከተሞቻቸው (በክሎቻቸው) አሸናፊ የሆኑ ተወዳዳሪዎች ከፍ ወዳለው (የፌደራል) ውድድር ያልፋሉ፤ በዚያም ለሳምንት ያህል በዳኞች ና በከፈተኛ ኤክስፐሮች እየተዳኙ ይወዳደራሉ። በዚህም የመጨረሻዎቹ አሸናፊዎች ይለያሉ።
በአሁኑ ጊዜ ተወዳዳሪዎችን እየተቀበለ ይገኛል። የበለጠ መረጃ የአይኮግ ላብስ (iCog Labs) ድረ ገጽ ላይ ማግኘት ሲችሉ (እዚህ ጋር ይጫኑ)፥ መመዝገቢያውን ደግሞ እዚህ ጋር ያገኙታል (Register)።
ምንጭ፦ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለተወሰነ ጊዜ ተዘጋ
- ራይድ የተባለዉ የታክሲ አገልግሎት ድርጅት የስም ማጥፋት ዘመቻ እና ጥቃት ደርሶብኛል በማለት ወቀሰ
- ቤልካሽ ኢትዮጵያ ሄሎማርኬት እና ሄሎሾፕ የተሰኙ ሁለት የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ገፆችን ሊያስጀምር ነው
- ገበያ የተባለው የግል ድርጅት እና የኢኖቬሽንና ቴክሎጂ ሚኒስቴር ተባብረው ለመሥራት ስምምነት ተፈራረሙ
- ኬር ኢትዮጵያ በ7 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ወጭ ያስገነባውን የምርምርና የስልጠና ማዕከል ለሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አስረከበ
ዓባይ ኢንዱስትሪያል የልማት አክስዮን ማኅበር ደጀን ከተማ ውስጥ (አማራ ክልል) የሚያስገነባው ሲሚንቶ ፋብሪካ አጠቃላይ ወጪው 8.8 ቢልዮን ብር እንደሆነና ግንባታው በ24 ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተጠቁሟል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– ዓባይ ኢንዱስትሪያል የልማት አክስዮን ማኅበር በአማራ ክልል ደጀን ከተማ ላይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ለመገንባት ከሁለት የውጭ ሀገር ድርጅቶች ጋር የሦስትዮሽ የሥራ ስምምነት ተፈራረመ።
አክስዮን ማኅበሩ አክስዮን ማኅበሩ ስምምነቱን የተፈራረመው መቀመጫውን ኮፐንሃገን ከተማ (ዴንማር) ያደረገውና ዓለምአቀፍ የምህንድስና (ግሎባል ኢንጂነሪንግ) ኩባንያ ከሆነው “FLSmidth & Co. A/S” እና መቀመጫውን ያንግጆ ከተማ፣ ቻይና (Yangzhou, China) ያደረገው ሌላው ዓለምአቀፍ የምህንድስና ኩባንያ “Hengyuan Group” ጋር አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሸራተን አዲስ ሆቴል ውስጥ ነው ነው። በስምምነቱ መሠረት “FLSmidth & Co. A/S” የግንባታ መሣሪያዎችን ሲያቀርብ፣ “Hengyuan Group” ደግሞ የግንባታውን ሥራ ያከናውናል። የፋብሪካው ግንባታ አጠቃላይ ወጪውም 8.8 ቢልዮን ብር እንደሆነና ግንባታው በ24 ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተጠቁሟል።
◌ ቪድዮ፦ በ8.8 ቢልዮን ብር በደጀን ከተማ (አማራ ክልል) የሲሚንቶ ፋብሪካ ሊገነባ ነው።
የዓባይ ኢንዱስትሪያል የልማት አክስዮን ማኅበር ለሚገነባው ፋብሪካ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውንም የአክስዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ መላኩ አለበል ጠቁመዋል።
በስምምነቱ ወቅት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝደንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፦ “ይሄ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለክልሉ ልማት ትልቅ አጋዥ ይሆናል የሚል እምነት አለን፤ ስለዚህ ገንቢዎቹም፣ አቅራቢዎቹም፣ ሁላችሁም ደጀን ላይ ይህንን ሲሚንቶ ፋብሪካ ለማፋጠን በምታደርጉት ጥረት የአማራ ክልል ሕዝብና መንግስት ሁልጊዜም ቢሆን ከጎናችሁ ይሆናል” በማለት የክልሉን መንግስት ደጋፍ አረጋግጠዋል።
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም በበኩላቸው የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ብቻ ትርጉም እንደሌለውና፣ ይልቁንም በፍጥነት ተገንብተው ወደማምረት ሥራና ለኅብረተሰቡ የሥራ ዕድል ፈጠራ መግባት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የሲሚንቶ ፋብሪካው ወደ ሥራ ሲገባ በቀን 5 ሺህ ቶን ክሊንከር እና በዓመት 2.25 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ እንዲያመርት፣ ለዚህም 655 ሰዎችን በቋሚነት የሚቀጥር ሲሆን፥ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር ደግሞ የሠራተኞቹን ቁጥር ወደ 1,500 ለማሳደግ ታቅዶ እንደሚገነባ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ዓባይ ኢንዱስትሪያል የልማት አክስዮን ማኅበር በህዝብና በግል ባለሀብቶች ባለቤትነት በአክስዮን የተቋቋመ የንግድ ድርጅት ነው። ዋና መሥሪያ ቤቱም የአማራ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ በሆነችው ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ነው።
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ተመሳሳይ ዜናዎች፦- የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የካንሰርና የልብ ህክምና ማዕከል ግንባታ 56 በመቶ ደርሷል
- የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሮኒክ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ) ማዕከል ኢትዮጵያ ውስጥ ሊገነባ ነው
- ቤልካሽ ኢትዮጵያ ሄሎማርኬት እና ሄሎሾፕ የተሰኙ ሁለት የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ገፆችን ሊያስጀምር ነው
- የጣልያን መንግስት አዲስ አበባን ከምፅዋ የሚያገናኘውን የባቡር ምስመር ፕሮጀክት ጥናት ወጪ ለመሸፈን ተስማማ
- አዳማ ከተማ ውስጥ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው እና ጥቅም ላይ የማይውሉ መድኃኒቶችን ማስወገጃ ማዕከል ተገነባ