የኢትዮጵያ ቡና ከመቐለ 70 እንድርታ ጋር አዳማ ላይ አልጫወትም አለ፤ በዒድ አል ፈጥር ምክንያት ጨዋታው በድጋሚ ተራዝሟል

Home Forums Semonegna Stories የኢትዮጵያ ቡና ከመቐለ 70 እንድርታ ጋር አዳማ ላይ አልጫወትም አለ፤ በዒድ አል ፈጥር ምክንያት ጨዋታው በድጋሚ ተራዝሟል

Viewing 2 posts - 1 through 2 (of 2 total)
  • Author
    Posts
  • #11031
    Semonegna
    Keymaster

    ለግንቦት 27 ቀን ተወስኖ የነበረውን የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንድርታ ጨዋታ በድጋሚ ወደ ሐሙስ ግንቦት 29 ቀን በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት በዝግ ስታድየም እንዲካሄድ ተወስኗል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– ግንቦት 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት ጨዋታ የነበራቸው ኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንድርታ ሊያካሂዱት የነበረው ጨዋታ በጸጥታ ስጋት ምክንያት (የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባደረገው ውሳኔ መሰረት) ውድድሩ ሳይካሄድ መቅረቱ ይታወቃል።

    የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህን ጨዋታ ግንቦት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት በዝግ ስታድየም እንዲካሄድ መወሰኑን አስታውቆ ነበር። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቡና ዛሬ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የላከው መግለጫ (በዋና ሥራ አስኪያጁ በተፃፈ ደብዳቤ) እንደሚያመለክተው ፌዴሬሽኑ ለግንቦት 27 ያወጣዉን ፕሮግራም እንደሚቃወመው አስታውቋል። በተጨማሪም ክለቡ ደብዳቤ ላይ በ27ኛ ሳምንት በሜዳው ከመቐለ 70 እንድርታ ጋር ያለዉን ጨዋታ በሜዳዉና በደጋፊው ፊት እንዲካሄድም ጠይቋል።

    የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውሳኔውን በዚህ ብቻ ሳያበቃ ግንቦት 26 ቀን ለመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ሆቴል ከቀኑ 9:00 ሰዓት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ክለቡ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ ስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት (Court of Arbitration for Sport) እንደሚወስደዉም ይፋ አድርጓል።

    እንደገና ግንቦት 26 ቀን የዒድ አል ፈጥር በዓል ማክሰኞ ግንቦት 27 ቀን እንደሚውል ከታወቀ በኋላ ለግንቦት 27 ቀን ተወስኖ የነበረውን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በድጋሚ ወደ ሐሙስ ግንቦት 29 ቀን በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት በዝግ ስታድየም እንዲካሄድ ተወስኗል።

    የኢትዮጵያ ቡና የጻፈው ደብዳቤ

    ጉዳዩ፦ የተላለፈብንን ውሳኔ ስለመቃወም።

    ክለባችን በ25/09/2011 ከመቀሌ 70 እንደርታ ቡድን ጋር በሊጉ 27ኛ ጨዋታ ለውድድር ተዘጋጅቶ መቅረቡ ይታወቃል።

    ሆኖም በእኛ በኩል ምንም ዓይነት ጥፋት ሳንፈጽም የዕለቱ ውድድር ሳይጀምር መሰረዙ ተገልፆልናል።

    በማግስቱ ጨዋታው በወጣበት ፕሮግራም በአስተናጋጅነታችን፣ በሜዳችን የሚካሄድበት ፕሮግራም ይላክልናል ብለን ስንጠብቅ በ26/9/2011 ዓም ውድድሩ በ27/9/2011 በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም በዝግ ስታድየም እንደሚካሔድ የሚገልፅ ደብዳቤ ደረሰን።

    ከፍተኛ ወጪ አውጥተን ወደ መቀሌ በመጓዝና በከተማችንም ቡድናችን በማዘጋጀት ያወጣነው ወጪ ከግምት ሳይገባ የዚህ ዓይነት ውሳኔ መስጠቱ በእጅጉ አሳዛኝ ነው።

    በሌላ በኩ እኛ መቀሌ ለውድድር ሄደን የደረሰብንን በደለ በቃልና በተጨማሪም በፅሁፍ 3 ጊዜ ወሳኔ እንዲሰጠን ስንጠይቅ ምንም ሳይወሰን ዛሬ በእኛ ላይ በምሽት ስብሰባ ተደርጎ የተሰጠው ወሳኔ በእጅጉ ያሳዘነነ ከመሆኑም በላይ፥ ክለባችን ከሜዳው የሚያገኘውን ገቢ በማቋረጥ፣ ወደ አዳማ ጉዞ የምናወጣው ወጪ፣ የከተማዋን ነዋሪና ደጋፊ ሞራል የሚነካ ሁኔታን በመፍጠር ተጫዋቾቻችንን ላላስፈላጊ እንግልት ከመዳረግ በተጨማሪ የሞራልና አካል ድክመት የሚፈጥር በመሆኑ ክለባችን አይቀበለውም።

    ስለሆነም በጋራ ያቋቋምነው ፌዴሬሽን ለሊግ ኮሚቴ ከተሰጠው ስልጣን ውጪ የዝግ ስታድየም ጨዋታ ውሳኔ መስጠት ያለበት የፍትህ አካል መሆኑ እየታወቀ፥ ሊግ ኮሚቴ ያሳለፈው ውሳነ ሕገ ወጥ ስለሆነ በአስቸኳይ ተሽሮ በሜዳችን፣ ለተመልካች ክፍት በሆነ ስታድየማችን እንድንጫወት ይደረግ ዘንድ እየጠየቅን፥ ከዚህ ውጭ ያለ አማራጭ ክለባችንን የሚጎዳ ስለሆነ የማንቀበለው መሆኑን እንገልፃለን።

    የክለቡ ማኅተም
    የክለቡ ሥራ አስኪያጅ ፊርማ

    የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያሳለፈው አዲስ ውሳኔ

    የ27ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንድርታ ጨዋታ ግንቦት 29/2011ዓ.ም ይካሄዳል።

    በ27ኛ ሳምንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ግንቦት 25/2011ዓ.ም ሊካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንድርታ ጨዋታ በጸጥታ ስጋት ምክንያት ጨዋታው መሰረዙ ይታወቃል፤ የሊግ ኮሚቴ ጨዋታው በጸጥታ ስጋት ምክንያት አለመካሄዱን ተከትሎ ግንቦት 27/2011ዓ.ም. በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ያለ ተመልካች /በዝግ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወቃል፤ ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ውሳኔውን በመቃወም ደብዳቤ ያስገባ ሲሆን ጉዳዩን የተመለከተው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቀደም ሲል የተሰረዘው ጨዋታ ከመንግስት ጸጥታ ኃይል በደረሰ መረጃ የደኅንነት ስጋት በስታዲየም እንዳለ በማሳወቁ በመሆኑ እና አሁንም በድጋሚ በተደረገው ውይይት ይህ ጉዳይ በጥብቅ ሊታይ የሚገባው በመሆኑ እና የመንግስት የጸጥታ ሀይልም የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ባሉበት ጨዋታው መካሄድ የሌለበት መሆኑን በጥብቅ አስገንዝቦናል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታን ግንቦት 27/2011ዓ.ም. ለማካሄድ የዒድ አል ፈጥር በዓል ስለሆነ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሐሙስ ግንቦት 29/2011ዓ.ም በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በ9 ሰዓት ያለ ተመልካች በዝግ ይካሄዳል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንድርታ ጨዋታ


    #11065
    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ተወሰነ
    —–

    የኢትዮጵያ ወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ለጊዜው እንዲቋረጥ ውሳኔ መተላለፉን ውድድሩ በበላይነት የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግንቦት 28 ቀን 2011 ዓ.ም. አስታወቀ።

    የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ግንቦት 28 ባደረጉት አስቸኳይ ስብሰባ በውድድሩ ከሚካፈሉ የእግር ኳስ ክለቡችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ፥ ውድድሮች በተገቢው መንገድ የሚካሄዱበት ዘላቂ መፍትሄ እስኪሰጥ ድረስ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ወሳኔ ላይ ደርሰዋል።

    የተደረገውን የአስቸኳይ ስብሰባ ውሳኔ ተከትሎ ግንቦት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዳማ ሊካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ ለጊዜው እንዲሰረዝም ተደርጓል። ከዚህም በተጨማሪ ለፌዴሬሽኑ የሚቀርቡ የተለያዩ ጥያቄዎች በፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን መመሪያ የውድድር ደንብ መሰረት እንዲታዩ ውሳኔ ተላልፏል።

    ምንጭ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን

Viewing 2 posts - 1 through 2 (of 2 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.