Search Results for 'ኢዜማ'

Home Forums Search Search Results for 'ኢዜማ'

Viewing 6 results - 46 through 51 (of 51 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    በየትኛውም ወገን የሚፈፀም፣ ሥርዓት አልበኝነት በቃ ለማለት ጊዜው አሁን ነው!
    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

    የኢትዮጵያውያን የፍትህ የእኩልነትና የዴሞክራሲ ጥያቄ በርካታ አስርት ዓመታትን ያስቆጠረ ብቻ ሳይሆን የአያሌ ዜጎችን ሁለንተናዊ መስዋዕትነት የወሰደ ረጅም ጉዞ ነው። በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት የሁሉንም ተሳትፎ ያማከለና አገዛዙ ከሚቋቋመው በላይ የሆነ ንቅናቄ የታየበት ትግል ተደርጓል። ውጤቱም የዛሬዋን ሁኔታ ወልዷል።

    ከበርካታ የዓለም ሀገራት ተሞክሮ እንዳየነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማዋለድ ከባድ ምጥ ያለበት የጭንቅ ጊዜ ማሳለፍ የግድ መሆኑን ነው። በኢትዮጵያችንም እያየን ያለነው ይህንኑ ነው። በእንደዚህ ዓይነት አስጨናቂ ወቅት ይህን ሂደት እንደአንድ ከባድ ታሪካዊ ኃላፊነት ወስደው የሚሠሩ የመኖራቸውን ያህል ግርግር ፈጥረውና የራሳቸውን ፍላጎት በኃይል ለመጫን የሚፍጨረጨሩ ቡድኖችና ግለሰቦች መኖራቸውን በየእለቱ በየቦታው የምናየው አሳዛኝ ክስተት ሆኗል።

    ፓርቲያችን ከተመሠረተ ጀምሮ ለሀገር ሠላምና ለሕዘብ መረጋጋት የራሱን ያልተቆጠበ አሥተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል። በእኛ ዕምነት የተያዘው የሽግግር ሂደት ለአንድ ወገን የማይተውና የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ እንደሆነ እናምናለን። ያም ሆኖ በዚህ ፈታኝ ወቅት የመንግሥት ሚና ትልቅና ከፍተኛ እንደሚሆን እንገነዘባለን።

    ፓርቲያችን በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከሠቱ ፈታኝ ሁኔታዎችንና የመንግሥትን ምላሽ በመገምገም በሚከተሉት ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን አቋም ይገልፃል።

    1. የየትኛውም በኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ግዛት ውስጥ የሚንቀሳቀስ ቡድንም ሆነ ግለሰብ ተግባር የሀገራችን ሕጎ እና ሀገራችን ያፀደቀቻቸውንና የተቀበለቻቸውን ድንጋጌዎች ባከበረ መልኩ ብቻ እንዲሆን ማድረግ የሚገባን ዛሬ ነው። ዜጎች በሕግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ካልተረጋገጠላቸው እና ከሕግ በታች መሆናቸውን ካልተረዱ ማንም እየተነሳ የፈለገውን አድርጎ “አልጠየቅም” የሚል ማንአለብኝነት ከሠፈነ መቼም ማቆሚያ ወደማይኖረው የሁከት ዓለም ጅው ብሎ እንዳይገባ ያሠጋል።
    2. የሁሉም የፖለቲካ አስተሳሰቦችን በነፃነት እና በሠለጠነ መንገድ መግለፅ፣ በሥልጣን ላይ ያለውንም ሆነ ሌሎች ፓርቲዎችን መተቸት፣ ማጋለጥ አልፎም በምርጫ ከሥልጣን ማውረድ የተለመደና ተገቢም ሊሆን ይችላል። ሀገርን የሚያዋርድ ተግባር መፈፀም ግን ለማንም ያልተፈቀደ የሀገር ከህደት ወንጀል መሆኑ በግልፅ ሊታወቅ ይገባል። በሕዝብ፣ በሃይማኖቶች፣ በብሔረሰቦች፣ በሰንደቅ ዓለማና በመሳሰሉት የአገር መገለጫዎች ላይ የሚፈፀም ማንኛውም የነውር ተግባር አስተማሪ የሆነ ቅጣት የሚያስከትል መሆን አለበት።
    3. ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሚሠጠው ትኩረት ከዚህ በፊት ከነበረው የተለየና ከወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት የሚጠብቃቸው መሆን እደሚገባው እናምናለን። በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ባሉ ዩኒቨርስቲ ግቢዎች የተከሠቱ ችግሮች የሕዝባችንን ልብ ሰብረው ያለፉ ክስተቶች ናቸው። ከሁሉም በላይ በደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ላይ የተደረገው እገታ ውሉ የጠፋና የመንግሥትን የተማሪዎችን ህይወት የመጠበቅ ኃላፊነት አለመወጣት ያጋለጠ ነው። ከዚህ ቀደም መንግሥት ስለለተማሪዎቹ እገታ ወቅቱን የጠበቀ እና ትክክለኛ መረጃ ለተማሪዎቹ ቤተሰቦች እና ለሕዝብ እንዲሰጥ ኢዜማ መጠየቁ ይታወሳል። ሆኖም መንግሥት ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃ የመስጠት ከፍተኛ ክፍተት ታይቶበታል። ከዚህ አንጻር መንግሥት ተማሪዎቹን ከእገታ የማስለቀቁን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ እና የሕዝብን ልብ እንዲያሳርፍ አበክረን እንጠይቃለን።
    4. በየትኛውም አካባቢ የሚፈጸም ግፍ ለየትኛውም አካባቢ ለሚገኝ ሰላም ጠንቅ ነው” እንዲሉ፥ ለተማሪዎቻችን የመቆም ጉዳይ የአንድ ወገን ወይም የአንድ ክልል ጉዳይ ሊሆን አይገባውም። የሁላችንንም ተናብቦ መሥራት ግድ ይላል። ከዚህ አንጻር የታገቱ ልጆቻችንን በሰላም ለማስለቀቅ ሕግ እና ሥርዓትን በተከተለ መልኩ በሀገራችን በሁሉም አካባቢዎች በሕዝባችን የሚደረጉ ሀቀኛ ጥረቶችን እንደግፋለን።
    5. ሀገርን እና ሕዝብን የማወክ አንድ አካል የሆነው የሞጣ መስጂዶችን የማቃጠል ድርጊት በአጥፊዎቹ ላይ አስተማሪ ርምጃ ተወስዶ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ፤ መስጂዶቹን አድሶና ምዕመናኑን ክሶ ወደቀድሞው ሰላማዊ አገልግሎት ለመመለስ የሚደረጉትን የአብሮነት እንቅስቃሴዎችን እንደግፋለን።
    6. በቅርቡ የጥምቀት በዓል አከባበር ወቅት በተወሰኑት አካባቢዎች በተለይም በአቦምሳ የከተራ በዓል ሳይከበር የቀረበትን ሁኔታ ታዝበናል። የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዳይከበር እንቅፋት የሆኑ አካላትም ለሕግ እንዲቀርቡና ተገቢ ቅጣት እንዲያገኙ እንጠይቃለን።
    7. ኢዜማ የምርጫ ወረዳዎችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እንደዚሁም ሕዝባዊ ውይይቶች በሚያካሄድበት ጊዜ ጥቂት ሥርዓት አልበኞች የሚፈጥሩት ግርግር ሕዝብን የሚወክል እንዳልሆነ ብንረዳም በአጠቃላይ የፖለቲካ ድባቡ ላይ የሚፈጠረው የስሜት መሻከር ያሳስበናል። በተለይም ወደምርጫ ለመግባት ዝግጅት እያደረግን ነው በሚባልበት በዚህ ወቅት ሕዝቡ ሕገመንግሥታዊ የሆነውን የመሰብሰብ መብቱን መጠቀም የማይችልበት ሁኔታ ይታያል። ባሳለፍነው ሳምንት በተከሠቱ በተለይ የጎንደር እና የሸዋሮቢት ድርጊቶችን ተከታትሎ አጥፊዎችን እንዲቀጣ አቤቱታችንን ለመንግሥት አቅርበናል። ኢዜማ ላይ የሚከሠቱ ችግሮች ሁለት ገጽ አላቸው አንደኛው ከመንግስት መዋቅር የሚመጣ ሲሆን ሁለተኛው ከዚያ ውጭ የሆኑ ሥርዓት አልበኞች የሚፈጥሩት ነው። “ባለጌና ጨዋ በተጣሉ ጊዜ ለጊዜውም ቢሆን ባለጌ ያሸነፈ ይመስላል” የሚል የቆየ የሀገራችን ብሂል አለ። ይህም ጨዋው በሕግ ስለሚያምንና የሕግ አስከባሪ ባለጌውን ይቀጣል፤ ብሎ በማመን ነው። በእኛ መዋቅርም የሚታየው ይሄው ሕግን የማክበር ጉዳይ ነው፤ ይህም ቢሆን ልክ አለው፤ ከገደብ ያለፈ ነውር ሲፈፀም አመራሩም፣ አባሉም፣ ደጋፊውም ራሱን፣ ፓርቲውንና ሀገሩን የመጠበቅ ተፈጥሯዊ መብት አለው። ኢዜማ ሀገርንና ሕዝብን ለድርድር አያቀርብም። ይህንንም ደግመን ደጋግመን ተናግረናል! መንግሥት በራሱ ውስጥም ሆነ ከራሱ ውጭ ያሉትን ሥርዓት አልበኞች በሕግ ሊቀጣ ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ሕዝቡ ራሱን ወደመከላከልና ሰላሙን ወደ ማስጠበቅ ሊገፋ ይችላል። ይህም በየትኛውም መመዘኛ ስህተት ሊሆን አይችልም።

    በመጨረሻም የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱን መጠበቅ ለሁላችንም የሚጠቅም ሀገር እና ሕዝብን የሚታደግ ብቸኛው መንገድ መሆኑን አውቀን እንድንጓዝበት መልዕክታችንን እያስተላለፍን ሥርዓት አልበኝነትን በጋራ በቃ የምንልበት ጊዜው ዛሬ መሆኑን በአፅንኦት እንገልፃለን።

    ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!
    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
    ጥር 22 ቀን 2012 ዓ.ም
    አዲስ አበባ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

    Semonegna
    Keymaster

    ሀገር የማዳን ጥሪ
    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሕዝብ ግንኙነት

    ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ በሥርዓት አልበኞች በተወሰደ የጥፋት እርምጃ የማይተካ የዜጎቻችንን ሕይወት አጥተናል፣ የብዙዎች አካል ጎድሏል፣ ዜጎች ለፍተው ያፈሩት ንብረት ወድሟል እዲሁም በተዘጉ መንገዶች ምክንያት ዜጎች ተንገላተዋል፤ የሀገሪቷ የኢኮኖሚ እቅስቃሴም ተስተጓጉሏል።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በዜጎች ሕይወት ላይ በደረሰው ጥፋት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ይገልጻል። ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ቤተሰቦች እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን ይመኛል። የተፈጸመውን ሕገ ወጥ እና አሳፋሪ ተግባር አጥብቆ ያወግዛል!

    የፖለቲካ ፍላጎትን በኃይል ለመጫን የሚደረጉ የሥርዓት አልበኞች ሙከራዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሱ መጥቷል። የመንግሥት እነዚህን ሙከራዎች አስቀድሞ የመተንበይ፣ ሲከሰቱም አፋጣኝ እና ተገቢውን ምላሽ የመስጠት አቅሙ ከጊዜ ወደጊዜ መሻሻል እየታየበት አይደለም። በዚህም ምክንያት የዜጎች ሕይወት በተደጋጋሚ አደጋ ላይ ወድቋል፤ አሁንም እየወደቀ ይገኛል። በቁጥር ቀላል የማይባሉ ዜጎች በሀገራቸው ደኅንነታቸው ተጠብቆ በነጻነት የመንቀሳቀስ፣ የመሥራት እና የመኖር መብታቸውን መጠቀም የማይችሉበት ብቻ ሳይሆን በማያቋርጥ ስጋት እና ጭንቀት ውስጥ ሕይወታቸውን እንዲመሩ የተገደዱበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ከዚህም አልፎ በዕምነት ተቋማት እና ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ደግሞ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለመተማመን ክፍተት እንዲፈጠር ምክንያት እየሆነ ነው። ይህ ጉዳይ በአስቸኳይ የማይታረም ከሆነ የሽግግር ሂደቱ ተጨናግፎ ወደማንወጣው ቀውስ ውስጥ ሊከተን ይችላል።

    መንግሥት የችግሩን ጥልቀት እና ሕግ የማስከበር ድክመቱን በሚገባ ፈትሾ በአስቸኳይ ክፍተቶቹን እንዲያስተካክል እና የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት የማስጠበቅ እና ጥፋተኞችን ሕግ ፊት የማቅረብ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ከመቼውም ጊዜ በላይ አጥብቀን እናሳስባለን።

    መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ የጋራ ሀገራችንን ከጥፋት አፋፍ ለማዳን የምንችለውን ሁሉ ማድረግ የሚገባን ወቅት ላይ መሆናችንን ተገንዝበን ልዩነቶቻችንን አቻችለን በአንድነት እንድንቆም እና ሀገራችን ከተደቀነባት ከባድ አደጋ እንድንታደግ ከአደራ ጭምር ጥሪ እናስተላልፋለን።

    የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት

    ምንጭ፦ ኢዜማ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    —–
    ተመሳሳይ ዜናዎች፦

    ሀገር የማዳን ጥሪ

    Semonegna
    Keymaster

    ባንዲራ ይዛችሁ ወጥታችኋል በማለት ክርስቲያኖችን የሚያዋክቡ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተጠየቀ
    ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚሞክሩ ጽንፈኞች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ፣ በቤተ ክርስቲያን እና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ እንዲቆም የሚያግዝ እና ጥፋት ከመፈጸሙ በፊት ሙያዊ ትንተና የሚያቀርብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ጉባኤው ጠይቋል።

    —–

    አዲስ አበባ (ማኅበረ ቅዱሳን) – የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ዓርማ አድርጋ ስትጠቀምበት የኖረችውን እና አሁንም የምትጠቀምበትን ባንዲራ ለበዓል ይዛችሁ ወጥታችኋል፤ በቤተ ክርስቲያን ጣሪያ እና ጉልላት ላይ ቀብታችኋል በማለት ምእመናንን የሚያዋክቡ፣ ወጣት ክርስቲያኖችን የሚያስሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተጠየቀ።

    በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያንን ተቀማጭ ገንዘብ ከንግድ ባንክ አውጥታችሁ እኛ በምንፈልገው ባንክ አስቀምጡ በማለት የሚያስገድዱ በአንዳንድ አህጉረ ስብከት የሚገኙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ያስጠነቀቀው 38ኛው የመንበረ ፓትርያርክ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ቅዳሜ ጥቅምት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በተጠናቀቀበት ዕለት ነው።

    ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት ርዕዮተ ዓለም ቀርጸው፣ የሐሰት ታሪክ ፈጥረው በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሚነዙ አቀጣጣዮችን (‘አክቲቪስት’/ ‘activist’ ነን ባዮች) እና ፖለቲከኞችን እኩይ ድርጊት መቃወም እንደሚገባ ጉባኤው በመግለጫ አሳውቋል።

    ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚሞክሩ ጽንፈኞች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ፣ በቤተ ክርስቲያን እና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ እንዲቆም የሚያግዝ እና ጥፋት ከመፈጸሙ በፊት ሙያዊ ትንተና የሚያቀርብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ጉባኤው ጠይቋል።

    የሕግ ባለሙያዎች የተካተቱበት ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚደርስ ኮሚቴ በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቋቋም ጉባኤው አሳስቦ አገራዊ ለውጡ ተስፋ የሰጠ ቢሆንም በቤተ ክርስቲያን እና በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለው እኩይ ተግባር ቤተ ክርስቲያንን እያሳዘናት እና እያሳሰባት መሆኑንም አስገንዝቧል።

    በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፈጸመውን ጥፋት በሰላማዊ መንገድ በሽምግልና እና በውይይት ለመፍታት ጥረት ማድረግ የሚገባ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ መደረግ እንደሚኖርበትም አሳስቧል።

    የጥምቀት እና የመስቀል በዓላት ማክበሪያ ቦታዎችን ሙሉ በሙሉ ነጥቀው፣ አንዳንድ ጊዜም ቆርሰው ለሌሎች የሚሰጡ አካላትን እኩይ ድርጊት አጥብቆ የተቃወመው መግለጫው በአገር ውስጥም በውጭም የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለመፈታተን የሚሞክሩ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን እኩይ ድርጊት ቅዱስ ሲኖዶስ በጥበብ እና በትዕግሥት ማሳለፉ የሚያስደንቅ መሆኑን ገልጧል።

    ምንጭ፦ ማኅበረ ቅዱሳን / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ባንዲራ ይዛችሁ ወጥታችኋል

    Semonegna
    Keymaster

    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ
    የኢትዮጵያ ሕዝብ የፍትህ እና ነፃነት ጥያቄ በግድየለሽነት በሚንቀሳቀሱ ሰዎችና ተግባራቸው እንዳይጠለፍ ሁሉም ዘብ ሊቆም ይገባል!

    የኢትዮጵያ ሕዝብ የዴሞክራሲ ሥርዓት ይገባናል በሚል ሁሉንም አገዛዞች ሲታገል የቆየ ሕዝብ መሆኑ ሃቅ ነው። በዘመናዊት ኢትዮጵያ እንኳን ፍትሃዊ እና የሁሉንም ዜጎች ነፃነት የሚያከብር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመትከል በትግል የተገኙ አራት ዕድሎች መክነውብናል። ይህ የአምባገነን ሥርዓቶች እና የዜጎች አልገዛም ባይነት እና እምቢተኝነት ትንቅንቅ የሚቋጨው ሕዝብ እውነተኛ የሥልጣን ምንጭ ሆኖ የሚመርጠው እና የሚቆጣጠረው መንግሥት ሲኖር ብቻ ነው።

    የሩቁን ትተን በ2007 ዓ.ም. እንኳን ብናይ፣ በሙሉ ድምጽ ተመርጫለሁ ብሎ ፓርላማውን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረዉ ገዢ ቡድን በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ስብርብሩ የወጣው በዜጎች የጋለ የዴሞክራሲ ጥያቄ እና የተባበረ ትግል ነው።

    ይህ በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተባበረ ክንድ የተሰበረ አምባገነናዊ አሠራርና አስተሳሰብ መልክ እና ቅርፁን በመቀያየር የተገኘውን የለውጥ ጭላንጭል ድርግም አድርጎ በማጥፋት ጥለነዉ ወደመጣነዉ ጨለማና ወደራሱ የአገዛዝ አቅጣጫ ሊጠልፈው እንደተዘጋጀ ከበቂ በላይ ምልክቶችን አይተናል።የኢትዮጵያን ሕዝብ ትዕግስት፣ አስተዋይነት እና አርቆ አሳቢነት የመረዳት ችሎታ ያነሳቸው ጥቂት ፅንፈኞች ሀገራችን የምትጠብቀውን ተስፋ ሊነጥቋትና እነሱም አጥፍተው ሊጠፉ የተዘጋጁ ይመስላል። በእንደዚህ ዓይነት አቅላቸውን በሳቱ የአገዛዝ ቡድኖች እጅ መውደቅ ለአገራችን የመጀመሪያ ባይሆንም ይህ አሁን የገጠመን አጅግ በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት መቆምን እና መታገልን የሚያሻ መሆኑን ማሳሰብ እንወዳለን። በተደጋጋሚ እንዳልነው አሁን ያገኘነውን ዕድል በአግባቡ ተጠቅመን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥረት ሀገራዊ መረጋጋት በእጅጉ የሚያስፈልገን ወቅት ላይ እንገኛለን። ከዚህ በተፃራሪ የአንድ ወገን አሸናፊነት ተረክ መፍጠር ያገኘነውን ዕድል አደጋ ላይ የሚጥል እና ለማንም የማይጠቅም ኃላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑን መረዳት ይገባል።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምንሸጋገርበትን መደላድል ለመፍጠር ሰላም እና መረጋት ለማስፈንና ተቋማትን ነጻ እና ገለልተኛ ለማድረግ የበኩሉን እየተወጣ ቢሆንም በገዢው ፓርቲ ውስጥም ይሁን ከዚያ ውጪ ለውጡ የጋራ ትግል ውጤት መሆኑን የዘነጉ ቡድኖች የሚሠሩትን ነውረኛ አካሄድ በማየት በሚከተሉት 7 ነጥቦች ላይ ያለውን አቋም ይገልጻል።

    1. የአማራ እና የቅማንት ሕዝብ ብዙ መከራዎችን በጋራ ያሳለፈ ድንበር የሌለው አንድ ሕዝብ ዛሬ በአስተዳደር ወሰን እና በማንነት ጉዳዮች የሚነሱ ደም አፋሳሽ ግጭቶችን የሚያስተናግደው በክፋት በተዋቀረው ፌደራላዊ አሠራር መሆኑን ተገንዝበን ለዘላቂ ሰላም እና ለሕዝብ አብሮ መኖር በትዕግስት እንድንሠራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። ግጭቶች ባሉበት አካባቢ የሚኖረውም ሕዝብ፤ በመሀከሉ ያለውን ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ እና ሰላሙን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ እኩይ ኃይሎች ሰለባ እንዳይሆን በሕዝባችን አንድነት ስም እንማጸናለን።
    2. ኢሕአዴግ በጌታ እና ሎሌ አደረጃጀት የተዋቀረ ከዚህም ሲያልፍ መንግሥትነት የሚያስገኘውን የሥልጣን ጥቅም በመቀራመት ጎን ለጎን ሲጓተቱ የነበሩ ቡድኖች ስብስብ መሆኑን ለምናውቅ ሁሉ የዛሬው እሽኮለሌ አያስደንቀንም። ሆኖም ግን ሕዝባችንን በእነሱ ጦስ ወደእልቂት ለመክተት የሚያደርጉትን የትንኮሳ አካሄድ እንዲያቆሙ በኢሕአዴግ ውስጥ የተሰባሰቡ የብሔር ድርጅቶችን በጥብቅ እናሳስባለን።
    3. የተቋማትን መኖር እና መጠንከር አስፈላጊ ከሚያደርጉት ጉዳዮች ውስጥ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክንውኖች ከፖለቲካ ነጻ መሆናቸውን ማረጋገጥ ቢሆንም ከሰሞኑ በተለይም የኦዴፓ አደረጃጀት የሰላም፣ የይቅርታ እና የምስጋና ታላቅ በዓል የሆነውን ኢሬቻን መጥለፉ ሳያንስ የተለመደውን የ100/150 ዓመት የሠባሪ/ተሠባሪ ትርክት ማቀንቀኑ ሀገሪቱን ወደ አንድነት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ወደኋላ የሚጎትት እና የሚበርዝ በመሆኑ እንዲህ ዓይነትቱ ትርክት በአስቸኳይ እንዲታረም አንጠይቃለን። የሀገር አንድነትንና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማምጣት ሂደት የምንጠቀምበት ቋንቋ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ እናሳስባለን።

    በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ የአዲስ አበባ ሕዝብ አዲስ አበባ ለተከበረው ኢሬቻ በዓል ከየቦታው የመጡ የበዓሉ ታዳሚ ኢትዮጵያዊያንን በመንከባከብ ላሳየው አብሮነት እና ወገናዊ ፍቅር እንዲሁም በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ላሳየው ትዕግስት ያለንን አክብሮት እና ምስጋና እየገለጽን ወደፊትም ለሀገር ሰላም እና መረጋጋት እጅ ለእጅ ተያይዞ እንዲታገል የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡

    1. የአዲስ አበባ ሕዝብ እየደረሰበት ያለውን አፈና እስካሁን በሆደሰፊነት ማለፉ ሊያስመሰግነው ቢገባም ይህን ያልተረዱ ወገኖች ትዕግስቱን እንደፍርሀት፤ ጨዋነቱን እንደ የዋህነት እየወሰዱ ማኅበረሰቡን መተንኮስ እየተለመደ መጥቷል። ይህ የሀገራችንን ሁሉንም ሕዝብ አቅፎ የያዘ፤ ከዚያም በላይ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማእከል የሆነና ለፌደራል መንግሥቱም ከፍተኛ የሆነ የግብር ገቢ የሚያስገኝ ከተማን በጥንቃቄና በአክብሮት፤ የሚገባውን መብት አክብሮ መያዝ ይገባል። የከተማው ሕዝብ ተፈጥሮአዊ የሆነና በሕገ መንግሥቱም እውቅና የተሰጠውን ራሱን የማስተዳደር መብት ለመሸርሸር የሚደረግ ምንም ዓይነት አካሄድን አይቀበልም። ይህንን መብቱን በዘላቂነት ለማስጠበቅም ራሱን ከቀበሌ ጀምሮ በሁሉም ያስተዳደር እርከን በጠንካራ ሁኔታ አደራጅቶ የራሱን መብት ለማስከበርና የራሱን መሪዎች ለመምረጥ መዘጋጀት ይጠበቅበታል። ኢዜማ ይህንን ራስን የማስተዳደር እንቅስቃሴውን እውን ለማድረግ ከከተማው ሕዝብ ጋር አብሮ ይሠራል፤ የከተማውን ሕዝብም ዘርና ሃይማኖት ሳይለይ በዜግነቱና በከተማ ነዋሪነቱ ያደራጃል። ከዚህም በተጨማሪ የሚደርስበትን የመብት ጥሰት ለመቃወምና ተቃውሞውንም በሰላማዊ መንገድ ለመግለጽ የሚያደርጋቸውን ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች እንደግፋለን፤ በሥነ ሥርዓት እና ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን በጠበቀና ሀገራዊ አንድነታችንን በሚያጎለብት ሁኔታ እንዲካሄድም ጥሪ እናስተላልፋለን።
    2. በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ያስተዋወቀው አዲስ የደንብ ልብስ ለከተማ የፖሊስ አገልግሎት የሚመች ባለመሆኑ ጥቅም ላይ እንዳይውል አጥብቀን እናሳስባለን። የከተማዋ ፖሊስ በክፍለ ከተማ፣ በወረዳ እንዲሁም በኮሚኒቲ ፖሊስ ደረጃ የተዋቀረ አደረጃጀት እያለው እና የፌደራል ፖሊስ ኃይል በቋሚነት በሚገኝበት ከተማ ውስጥ ተጨማሪ ቋሚ ተወርዋሪ ኃይል ማቋቋም ተቀባይነት የለውም። ይልቁንም የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ከፖለቲካ ወገንተኝነት በጸዳ መልኩ የከተማዋን ኅብረተሰብ ደኅንነት ማስጠበቅ እና አባላቱ የሚፈጽሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማስቆም ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል። በክልሎች የተደራጀው ልዩ ኃይል እና አዲስ አበባ አስተዳደር አቋቋምኩት ያለው ቋሚ ተወርዋሪ ኃይል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ለሚደረገው ትግል ትልቅ ተግዳሮቶች ናቸው። ከዚህ ቀደም እንደገለጽነው እነዚህ አደረጃጀቶች ፈርሰው ወደመደበኛ ፖሊስ እና መከላከያ ሠራዊት እንዲካተቱ በድጋሚ ጥሪ እናስተላልፋለን።
    3. በአማራ ክልል የተከሰቱ የወንድማማች ሕዝብ ግጭቶች ተከትሎ ሁኔታው እንዲረጋጋና ሰላም እንዲሰፍን ከመስበክ ይልቅ ሥራዬ ብለው ወሬ እየፈበረኩ ግጭቶችን በሚያዋልዱ ሚዲያዎች ላይ የብሮድካስት ባለሥልጣን በአስቸኳይ አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድባቸው እናሳስባለን።
    4. ላለፉት 27 አመታት ሲሰራበት የቆየው ሀገርን እና ሕዝብን ሆን ብሎ የሚከፋፍልና የሚበትን የዘረኝነት አሠራር ለመጨረሻ ጊዜ ማቆም የሚቻለው ፖለቲካችንን በማዘመንና በመግራት፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ ተደራጅቶ በመታገል በመሆኑ፤ ሌሎች ያደርጉልናል ብሎ ከመጠበቅ ዜጎች በተለይም ለዘብተኛ አመለካከት ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ በጋራ እንድናልፍ ባላችሁ አቅም ሁሉ በሀገራችሁ ጉዳይ ሙሉ ተሳታፊ እንድትሆኑ የዘወትር ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

    በአጠቃላይ ሰላምን፤ ሀገራዊ አንድነትንና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የሚያይ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሀገራችን እንዲገነባ ሕዝባችን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ባሉ የኢዜማ አደረጃጀቶች በመግባት የጀመረውን የሰላምና የዴሞክራሲ ጉዞ ከዳር እንዲያደርስ ጥሪያችንን እያቀረብን ሌሎች የማኅበረሰብ መሪዎች ለሀገር ሰላም እና ለሕዝብ መረጋጋት ዘብ መቆም የሚገባቸው ጊዜ ዛሬ መሆኑን በአጽንዖት እንገልጻለን።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሀገር አንድነትን ማስቀጠል እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምስረታ ከሁሉ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው። አሁን ያለንበት የሽግግር ወቅት የሀገር አንድነትን እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረትን እንዲያረጋግጥ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እንደምናደርግ እና አስፈላጊውን መስዕዋትነት ለመክፈልም ወደኋላ እንደማንል በድጋሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን። የኢትዮጵያ ሕዝብም ከጎናችን እንደሚቆም አንጠራጠርም።

    ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
    መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ
    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)


    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በግንቦት ወር በይፋ ተመሥርቶ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመሥራት በሩ ክፍት መሆኑን ከገለፀ በኋላ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ፥ የከምባታ ሕዝብ ኮንግረስ (ከሕኮ) ተከትሎ ራሱን አክስሞ ኢዜማን የተቀላቀለ ሁለተኛ ፓርቲ ሆኗል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ከተመሠረተ 11 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ መክሰሙን አስታወቀ።

    ኢራፓ ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. በራስ ሆቴል ባካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ መክሰሙንና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህን (ኢዜማ) መቀላቀሉን የኢራፓ ፕሬዝዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ አስታውቀዋል። ፓርቲው በጠቅላላ ጉባዔው ላይ 8 ነጥቦችን የያዘ የአቋም መግለጫውም ይፋ አድርጓል።

    ኢራፓ በአቋም መግለጫው፥ ኢትዮጵያ ያለችበትን ችግር ለመፍታትና ከምንጩ ለማድረቅ መንግሥት፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መላው የሀገሪቱ ሕዝቦች በመቻቻል፣ በትዕግስትና በአብሮነት መሥራት እንዳለባቸው ገልጿል። “ጣት መቀሳሰሩን ወደ ጎን በመተው የምክክርና የድርድር መድረኮች ተዘጋጅተው ተቀራርቦ መነጋገር ይገባል” ሲል ፓርቲው ጥሪውን አቅርቧል።

    ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄን ሕዝበ ውሳኔ አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

    በጠቅላላ ጉባኤው መገባደጃ ላይ ኢዜማን በመወከል ንግግር ያደረጉት የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፣ ኢዜማ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ይፈጥሯቸው ከነበሩ ህብረቶች በተለየ መልኩ ራሳቸውን ያከሰሙ ድርጅቶች በምርጫ ወረዳ የተዘረጉ መዋቅሮችን በመቀላቀል እንደአዲስ ፓርቲ የተመሠረተ ፓርቲ መሆኑን አስታውሰው፤ “ትንሽ ፓርቲ ውስጥ ትልቅ ከመሆን ትልቅ ፓርቲ ውስጥ ትንሽ ሰው መሆን ይሻላል” ሲሉ በመሠረታዊ መርኾች የተስማሙ የፖለቲካ ድርጅቶች አንድ ላይ ሆነው ሰፊ ድንኳን ያለው ጠንካራ ድርጅት የማቆምን አስፈላጊነትን አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ አባላት በሚኖሩበት አካባቢ በተደራጁ የኢዜማ ምርጫ ወረዳ መዋቅሮች ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ያደረጉት የኢዜማ መሪ፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሰከነ ውይይት እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመፍታት ባሕል አዳብረን ኢዜማን ታሪክ የሚሠራ ድርጅት እናደርገዋለን ብለዋል።

    የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ለአማራ ሕዝብ ህልውና እና ለሀገር እንድነት አስፈላጊውን መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ገለፀ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ግንቦት 1 እና 2 ቀን 2011 ዓ.ም. በይፋ ተመሥርቶ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመሥራት በሩ ክፍት መሆኑን ከገለፀ በኋላ ኢራፓ፣ የከምባታ ሕዝብ ኮንግረስ (ከሕኮ) ተከትሎ ራሱን አክስሞ ኢዜማን የተቀላቀለ ሁለተኛ ፓርቲ ሆኗል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)


    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከፍተኛ አመራሮች አሜሪካ ውስጥ በካሊፎርንያ ግዛት ሎስ አንጀለስ ከተማ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር አዲስ በተቋቋመው ፓርቲ አጠቃላይ ሁኔታና የሀገራችን ኢትዮጵያን (የፖለቲካ) ነባራዊ ሁኔታን በተመለከተ ተወያዩ።

    የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የሕዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ናትናኤል ፈለቀ በሰሜን አሜሪካ በሚገኙ ሦስት ከተሞች ከሚያደርጉት ውይይቶች የመጀመሪያው በሆነው የሎስ አንጀለስ ውይይት፣ የፓርቲው አመሠራረት፣ ለመሥራት የታቀዱ ሥራዎች እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በፓርቲው እና በአጠቃላይ ሀገሪቷ ውስጥ እንዲገነባ የሚፈለገው የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እንዴት ማገዝ እንደሚችሉ ውይይት ተደርጓል። በቪዛ መዘግየት ምክንያት ለስብሰባው መድረስ ያልቻሉት የኢዜማ ምክትል መሪ አቶ አንዱዓለም አራጌ የመክፈቻ የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ኢዜማ ባደረገው በዚህ ውይይት፥ የሀገራችንን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እና የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችም የውይይቱ አካል ነበሩ። ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣውን ለውጥ “ሁለንተናዊ መሻሻል” ተብሎ የሚፈረጅ (reform) እንጂ አብዮት (revolution) አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክት ያስተላለፉት የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ ለውጡ ያልገባቸው (የሚያስጨንቃቸው) የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚፈጥሩት እንቅፋት፣ በየክልሉ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች እና ብዛት ያለው ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ቁጥር የለውጡ ከፍተኛ ተግዳሮቶች እንደሆኑ እና በየደረጃው መፍትሄ መስጠት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

    በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በኢዜማ እንቅስቃሴዎች ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን የሚችሉበት አደረጃጀት (ቻፕተሮች) በሁሉም የዓለማችን አካባቢዎች የሚዋቀሩ ሲሆን በሀገራችን ዜግነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲፈጠር እና ማኅበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን የሚፈልጉ በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በነዚህ መዋቅሮች ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ተላልፏል።

    ከፓርቲው ዜና ጋር በተያያዘ፥ የኢዜማ ግብረ-ኃይል በአምስት አቅጣጫ ተንቀሳቅሷል። ከአዲስ አበባ በመነሳት በአምስት አቅጣጫ መዳረሻውን ያደረገ ግብረ-ኃይል ግንቦት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. እንቅስቃሴ ጀምሯል።

    መነሻውን ከመስቀል አደባባይ ያደረገው ግብረ-ኃይል የኢዜማ ምክትል የፓርቲ መሪ አቶ አንዱዓለም አራጌና የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች በተገኙበት መሸኛ ተደርጎለታል።

    ግንቦት 24 ቀንጉዞውን የጀመረው ግብረ ኃይል፣ በኢዜማ ለተደራጁ ለ216 የምርጫ ወረዳዎች ጊዚያዊ የእውቅና ደብዳቤ፣ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ደረሰኝ፣ የአባላት ፎርም እና የድርጅት ጉዳይ መመሪያዎቹን ተደራሽ ለማድረግ በአምስት አቅጣጫዎች ጉዞ ጀምሯል። በየመጀመሪያው ዙር ጉዞ ተደራሽ የሚደረግባቸው፡-
    1. ከአዲስ አበባ – ደብረ ብርሃን፣ ደሴ፣ ወልዲያ መዳረሻውን ሰቆጣ
    2. ከአዲስ አበባ – ፍቼ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ባህር ዳር አድርጎ መዳረሻውን ጎንደር
    3. ከአዲስ አበባ – ሻሸመኔ፣ ሀዋሳ፣ ጌድኦ፣ አለታ፣ መዳረሻውን አዶላ (ክብረ መንግስት)
    4. ከአዲስ አበባ – አምቦ፣ ነቀምት፣ ጊምቢ፣ ጅማ፣ መዳረሻውን ቤንች ማጂ
    5. ከአዲስ አበባ – አዳማ፣ አሰላ፣ ወላይታ፣ ሀዲያ፣ ዳውሮ፣ ወልቂጤ፣ መዳረሻውን ጉራጌ በማድረግ ሲሆን በቀጣይም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሌሎች አዳዲስ ቦታዎችንና ከተማዎችን ተደራሽ የሚያደርግ ጉዞ እንደሚኖር ታውቋል።

    የሀገር መረጋጋትን ቀዳሚ ዓላማ አድርጎ የሚሠራው ኢዜማ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ አባላቱና ደጋፊዎቹ ይህንኑ ዓላማ ተፈፃሚ ለማድረግ እንዲሠሩ በሁሉም አቅጣጫ የሚጓዙት የግብረ ኃይሉ አባላት አፅዕንዎት ሰጥተው የሚያስገነዝቡ ይሆናል። በየአካባቢው የሚገኙ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም የየአካባቢው ሕዝብ ለግብረ -ኃይሉ አባላት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉላቸው ጥሪ ተላልፏል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ኢዜማ


Viewing 6 results - 46 through 51 (of 51 total)