-
Search Results
-
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሴቶችን ጫና በሚያቀልሉ ቴክኖሎጂዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ መሆኑን የሚኒስቴሩ የሴቶች፤ ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ገብረሥላሴ አስታውቀዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በ7 ክልሎች ውስጥ በቴክኖሎጂ ውጤቶች ሊደገፉ የሚችሉ ሴቶች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ ያሉ ሥራዎችን በጥናት ለይቷል።
ችግሮቹ የተለዩት በአፋር፤ በቤኒሻንጉል፤ በጋምቤላ፤ በደቡብ፤ በአማራ፤ በትግራይና በሶማሌ ክልል በተጠናው ጥናት መሠረት መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
በፀሐይ ኃይል የሚሠራ የምግብ ማብሰያ፤ በሬ ለምኔ ዘመናዊ ማረሻ እና የቆጮ መፋቂያ ማሽን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ተገልጿል። ዘመናዊ የበቆሎ መፈልፈያና የአፋ አሊ (የአፋር ቤት) መሥሪያ በመካከለኛ ጊዜ ወደ ሥራ ለማስገባት የታቀደ ሲሆን በመስመር መዝሪያ እና ከጉድጓድ ውሃ ማውጫ መሣሪያ ደግሞ በረጅም ጊዜ ወደ ሥራ ለማስገባት በዕቅድ ተይዟል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሴቶችን ጫና በሚያቀልሉ ቴክኖሎጂዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው። የሚኒሰቴሩ የሴቶች፤ ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ገብረሥላሴ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሴቶችን የሥራ ጫና የሚያቃልሉና ምርታማ የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎች ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ለስኬታማነቱ የሚመለከታቸው ሁሉ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉም ዳይሬክተሯ ጥሪ አቅርበዋል።
ምንጭ፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሮኒክ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ) ማዕከል ኢትዮጵያ ውስጥ ሊገነባ ነው
- ቤልካሽ ኢትዮጵያ ሄሎማርኬት እና ሄሎሾፕ የተሰኙ ሁለት የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ገፆችን ሊያስጀምር ነው
- ገበያ የተባለው የግል ድርጅት እና የኢኖቬሽንና ቴክሎጂ ሚኒስቴር ተባብረው ለመሥራት ስምምነት ተፈራረሙ
- ሁለተኛው SolveIT ሀገር አቀፍ የፈጠራ ውድድር (የኢዲስ አበባ ከተማን) በይፋ ተጀመረ ― የአሜሪካ ኢምባሲ
- ቮልስዋገን በኢትዮጵያ የመኪና መገጥጠሚያ ፋብሪካ ሊገነባ ነው፤ የጀርመን የቴክኖሎጂ ድርጅቶች በስፋት ለመግባት እያመቻቹ ነው
Topic: አድዋ – የጥቁሮች ሕዝቦች የነጻነት እርሾ
የአድዋ ድል ለኢትዮጵያ ነጻነትና ኩራትን፣ በዓለም ዙሪያ በተለይ በአሜሪካዎቹ ሰፋፊ እርሻዎች ለ500 አመታት በባርነት ለተጋዙ ጥቁር ሕዝቦች ደግሞ፥ የማንነት ማረጋገጫ፣ የዘመናት ጭቆናና የስነ-ልቦና ቁስልን አውልቆ የመጣያ የተስፋ ትንሳኤ ሆኖ ነበር።
ሰለሞን ተሰራ (ኢዜአ)
በርሊን ከተማ ውስጥ የጀርመን ግዛት አስተዳዳሪ (ቻንስለር)በነበረው ኦቶ ቫን ቢስማርክ (Otto von Bismarck) መኖርያ ሳሎን ፌሽታ በፌሽታ ሆኗል። እለቱ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር (እ.አ.አ) የካቲት 16 ቀን 1885 ሶስት ወር ሙሉ አሰልቺ ውይይት የተደረገበትና ዋና ዋናዎቹ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ተሰብስበው ”አንተ ይሄን ያዝ አንተ ያንን ያዝ” ተባብለው ከወታደራዊ ዘመቻ በፊት አፍሪካን የተቃረጡት።
በስብሰባው ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን የአፍሪካ መሬት የሃሳብ መስመር እያሰመሩ ያለከልካይ ተከፋፈሉት። ከሦስት ወራት በላይ (እ.አ.አ ከኅዳር 15 ቀን 1884 እስከ የካቲት 26 ቀን 1885) ሲካሄድ የነበረው የበርሊን ጉባዔ (Berlin Conference) መደምደሚያ የነበረው ‘የበርሊን ጉባዔ ጠቅላላ ግብአተ ሰንድ’ (በእንግሊዝኛው፥ General Act of Berlin conference) በታሪክ አጥኚዎችና ፖለቲካ ተመራማሪዎች ዘንድ በ አብዛኛው “አፍሪካን የመቀራመት ጉባዔ” (“The Division of Africa” ወይም “Scramble of Africa”) ተብሎ ይታወቃል። በጉባዔው ላይ የጀርመን፣ ኦስትሮ-ሀንጋሪ፣ ቤልጅየም፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ብሪታንያ፣ ጣልያን፣ ኔዘርላንድስና ፖርቱጋል ተወካዮች ተገኝተዋል።
አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት በበርሊን ስምምነት ሲያደርጉ፤ አፍሪካዊያን ደግሞ የውጭ ወራሪዎችን ለመከላከል ከዚህ አለፍ ሲልም እርስ-በርሳቸው መተነኳኮስ የጀመሩበት ጊዜ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። ወቅቱ በአራቱም የአህጉሪቷ አቅጣጫዎች የሚገኙ ነገስታት እና የጭፍራ አለቆች በተናጠል ከአውሮፓውያኑ ጋር በገጠሟቸው ውጊያዎች ትርጉም ያለው ስኬት ሳያገኙ፤ አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት መውደቅ የጀመሩበት ነው።
ይህን ተከትሎ ጣልያንም ኢትዮጵያን በቁጥጥሯ ስር ለማድረግ ብትነሳም እምቢተኛው ጥቁር ሕዝብ ማንነቱንና ክብሩን አሳልፎ ላለመስጠት በመወሰኑ ያልተመጣጠነ ውጊያ ቢገጥሙም አሳፍሮ መልሷታል። ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቀው የጣልያን ጦር የቅኝ ግዛት ተልእኮውን እውን ለማድረግ የተመመው በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ በአግባቡ የሰለጠኑ ወታደሮችን ይዞ ነው። ነገሩ እንደታቀደው ሳይሆን ቀርቶ የጣልያን ጦር በአድዋ ድል ተነሳ። ታሪክም ይህን ጦርነት <የአድዋ ጦርነት> (The Battle of Adwa) በማለት፣ ለጥቁር ሕዝቦች ታላቅ መነቃቃትና ተስፋ የሰጠውን የጦርነቱን ድል ደግሞ <የአድዋ ድል> (The Victory of Adwa) ብሎ ሲገዝበው ይኖራል።
የታሪክ ሊቃውንት እንደሚያስቀምጡት የአድዋ ጦርነት በአፍሪካ ምድርና ታሪክ ከተከናወኑት ጦርነቶች ከፍተኛውን የዋጋና የክብር ስፍራ ይዟል። የሰሜን አፍሪካን በስፋት ይገዛ የነበረው አኒባል የአልፕን ተራሮች ዞሮ የአውሮፓን ኃያል መንግሥት ካሸነፈ ወዲህ (Hannibal’s crossing of the Alps)፣ አንድ አውሮፓዊ ጦር በአፍሪካውያን ጦር ሲሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር። ስለሆነም፣ ጦርነቱ ብዙ መልክና ብዙ ቅጽል ተሰጥቶታል።
የአድዋ ድል ለኢትዮጵያ ነጻነትና ኩራትን፣ በዓለም ዙሪያ በተለይ በአሜሪካዎቹ ሰፋፊ እርሻዎች ለ500 አመታት በባርነት ለተጋዙ ጥቁር ሕዝቦች ደግሞ፥ የማንነት ማረጋገጫ፣ የዘመናት ጭቆናና የስነ-ልቦና ቁስልን አውልቆ የመጣያ የተስፋ ትንሳኤ ሆኖም ነበር።
የታሪክ ተመራማሪና ደራሲውፖል ሄንዝ በጻፉት ንብረ ጊዜ፥ የኢትዮጵያ ታሪክ (Layers of Time: A History of Ethiopia, by Paul B. Henze) በተሰኘው የታሪክ ድርሳናቸው “አውሮፓውያን የፈለጉትን ገድለዋል፣ ባሪያ ፈንግለዋል፣ አካባቢን፣ ሀብትን፣ ጉልበትን መዝብረዋል፤ ምክንያቱ በግልጽ ባይታወቅም ‘ኢትዮጵያን በጦር ከማስገበር ይልቅ እንቃረጣት ብለው’ ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይና ጣልያን የሦስትዮሽ ስምምነት (Tripartite Agreement) ተፈራርመው አጼ ምኒልክን ‘እወቁልን’ ብለው ጦማር ሰደዋል። አጼ ምኒልክም ‘ስለነገራችሁኝ አመሰግናለሁ፣ ነገር ግን እኔ በሌለሁበት የተወሰነውን አላውቅም’ በማለታቸው ጣልያን ኢትዮጵያን በወረራ ያዘች።
ወረራውን ለመቀልበስ በአጼ ምኒልክ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ሰላማዊ ትግል ቢያደርግም የወራሪዎቹ ብልጣብልጥነት ጦርነቱን አይቀሬ አደረገው። ወደ ጦርነት ተገዶ የገባው የኢትዮጵያ የጦር ኃይል በአምባላጌ፣ በመቀሌና በአድዋ በተከታታይ ባደረገው ጦርነት የበላይነት ወስዶ የካቲት 23 ቀን 1988 ዓ.ም. ላይ በአድዋ የድል ባለቤት መሆኑ ተበሰረ። የድሉ ዜና እንደናኘ በአፍሪካ ተስፋ፣ በአውሮፓ ድንጋጤ ፈጠረ። የኢትዮጵያ ድል አውሮፓውያን በዓለም የነበራቸውን ልዕለ ኃያልነት ለመጀመሪያው ጊዜ ጥያቄ ውስጥ ከቷል። ፖል ሄንዝ ”ዛሬ ላይ ሆነን ስናየው” የኢትዮጵያ ድል የአውሮፓ ተሰሚነት የቁልቁለት ጉዞ መነሻ ነበር” ሲሉ በጽሁፍ አስፍረዋል።
ድሉ ታላቋ ብሪታንያን ኢትዮጵያን በእኩል ዓይን ዓይታ ”የምስራቁን የደቡቡን የምእራቡን ድንበራችንን እንካለል” ብላ በፊርማ እንድታጸድቅ አስገድዷታል። ከዚህ በተጨማሪ በአውሮፓ ቅኝ ግዛት መዳፍ ስር ሲማቅቁ የነበሩትን አፍሪካውያን እና ካሪቢያን ጥቁሮች ለነፃነታቸው እንዲታገሉ ብርታት እና ምሳሌ ሆኗቸዋል። ለጥቁር አሜሪካውያን ምሁራን ከፍተኛ የመንፈስ መነቃቃት እንዲያገኙ አድርጓል።
የአድዋ ድል (ማለትም፥ በአውሮፓውያን ዘንድ የአድዋ ጦርነት ሽንፈት) በተሸናፊ የአውሮፓ ገዢዎች ዘንድ ቁጭት ፈጥሮ ከ30 ዓመት በኋላ ፋሺዝም በጣልያን ውስጥ ስር እንዲሰድ እና መሪ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም (አይዲዮሎጂ) እንዲሆን ምክንያት ሆኗል። ለኢትዮጵያ ደግሞ የተረጋጋ መንግስታዊ አስተዳደር አስገኝቷል። በዚህ የከሸፈ የቅኝ-ግዛት ዕቅድና የአውሮፓውያን ተስፋፊነት የተደሰቱ ሶሻሊስት አመለካከት ያላቸው ወገኖች በጣልያን፣ በብሪታንያና በፈረንሣይም ነበሩ።
ዕውቁ የታሪክ ተመራማሪና የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ፕሮፌሰር የነበሩት ሪቻርድ ፓንክረስት እና ሌላው ኢትዮጵያዊ የታሪክ ተማራማሪ ዶ/ር አብዱልሳማድ አህመድ በጋራ በጻፉት ስለ አድዋ ድል በጻፉት መጽሐፍ (Adwa Victory Centenary Conference, 26 February – 2 March 1996) ውስጥ እንዳሰፈሩት የኢጣሊያኑ ክሪቲካ ሶሻሌ (Critica Sociale) ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ፊሊፖ ቱራቲ (Filippo Turati) በወኔና በምልዓት ለእውነት ስለእውነት ጻፈ። “ጣልያን ወደ አድዋና ወደ ሌሎችም ከኢትዮጵያ ጋር ወደ ተደረጉት ጦርነቶች የገባችው፣ ለእንግሊዛውያን አገልጋይና አሽከር ሆና ነው። በዚህም የተነሳ የጣሊያናውያን ሀብትና ደም ያላግባብ ፈሰሰ” ሲል ወረራውን በማውገዝ ድፍረት የተሞላበት ጽሁፉን ማስነበቡን ይገልጻሉ።
ጋዜጠኛው በጽሁፉ “የጣልያንና የእንግሊዝ መንግሥታት በአፍሪካ ስለተቀዳጁት የቅኝ-ግዛትና የተስፋፊነት ድል እንደጽጌረዳ የፈካ ውሸት እየፈበረኩ ይመጻደቁ እንጂ፣ በእርግጥ ኢትዮጵያ ድል አድርጋለች… ቪቫ ምኒልክ! ቪቫ ኢትዮጵያ!” ሲል አወድሷል።
በአጼ ምኒልክ መሪነት የኢትዮጵያ ኃይል በጣልያን ወራሪ ኃይል ላይ በአድዋ የተቀዳጀው ድል ድልድይ ሆኖ የጥንታዊቷን ኢትዮጵያ የታላቅነት ክብር ከዘመናዊ ዓለም ጋር ያገናኘ ድልድይ ሆኗል። ታዲያ ይህ ድልድይ በ1890ዎቹ ግንባታው የተጀመረው የተቀረው የአፍሪካ ክፍል በውጭ ኃይሎች አገዛዝ ቀንበር ስር ሲወድቅ ኢትዮጵያውያን ብቻ በተከታታይ የተሰነዘረባቸውን ወረራ በድል ሲመልሱ ነበር።
በዚያው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያውያን ለውጭ ወራሪዎች የማይንበረከኩ መሆናቸውን ማሳየታቸውን ማስታወስ ይቻላል። በ1870ዎቹ የግብፃውያንን፣ በ1880ዎቹ የመሃዲስቶችን ተደጋጋሚ ጥቃቶች መክተው መልሰዋል። የአድዋ ድል ደግሞ ይህን የነፃነት ቀናዒነት ይበልጥ ከማድመቅ አልፎ የዓለምን ትኩረት ስቧል።
የአውሮፓ መንግሥታት ዲፕሎማቶቻቸውን ወደአዲስ አበባ እንዲልኩ፣ ከኢትዮጵያ ጋር 19 ድንበርን የሚመለከቱ ስምምነቶችን እንዲፈራረሙ አደረጋቸው ። በአርነት ትግሉ መስክ በቅኝ ግዛት ሥር ለነበሩት እህት የአፍሪካ አገሮች ታጋዮችም ኢትዮጵያ ፋና ወጊ መብራታቸውና የራዕይ ምንጫቸው ነበረች።
የአድዋ ድል የፓን አፍሪካን ንቅናቄ መሠረት መሆኑን የኢትዮጵያውያንን የአድዋ ውሎ ከዘከሩ የታሪክ ጠበብት መካከል የዋሽንግተኑ የታሪክ ሊቅ ፕሮፌሰር ራየሞንድ ጆናስ፥ “የአድዋ ጦርነት – የአፍሪካውያን ድል በዘመነ ግዛት” (The Battle of Adwa: African Victory in the Age of Empire, by Raymond Jonas” በሚለው መጽሐፋቸው አስፍረዋል፡፡ በዚህ ጽሁፋቸው “የአድዋ ድል ለአፍሪካውያን ቅኝ አገዛዝን ታግሎ መጣል እንደሚቻል ያሳየ፣ የኢትዮጵያንም ታላቅነት ያስመሰከረ” ስለመሆኑ ደጋግመው አውስተዋል።
ለዚህም ነው የናይጄሪያ ድኀረ ነፃነት የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶ/ር ናምዲ አዚኪዊ (Nnamdi Azikiwe) “ኢትዮጵያ ጥቁር ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርባት አገር ነች። በዚህ ክፍለ አህጉር ላይ የአፍሪካ ቀደምት አባቶች የመሠረቱት መንግሥት የታሪክ ዋቢ ነች። ኢትዮጵያ ከዘመን ወደ ዘመን እየተሸጋገረች ህልውናዋን ጠብቃ መኖሯ የሚደነቅና መደነቅም ያለበት ነው” በማለት የተናገሩት።
ከአድዋው ድል አርባ ዓመት በኋላ ጣልያን ቂሟን ልትወጣ ወረራ ስታካሂድ በግልጽም ይሁን በተዘዋዋሪ የአውሮፓና የአሜሪካ መንግሥታት ከእሷ ጎን ቆመዋል። በተቃራኒው ድሉ በአፍሪካም ይሁን በተቀረው ዓለም የተቀጣጠለውን የአፍሪካዊነት የትግል ስሜት አነሳስቷል፤ እልህ አጭሯል። በአጠቃላይ መላው ጥቁር ሕዝብ፣ በቁጥር አነስተኛ ቢሆኑም ለፍትህ የታመኑ አውሮፓዊያን ነጮችም ለኢትዮጵያ ያላቸውን ወገናዊነት እንዲያጠናክሩ ጥርጊያውን አመቻችቷል። የነኝህም ጥረት በውጭ የነበረውን ሕዝባዊ ድጋፍ ወደ ኢትዮጵያ ያደላ እንዲሆን አድርጎታል። ባህላዊ እሴቶቻቸውን ያልጣሉ የአፍሪካ ምሁራን ከነበሩባቸው የአህጉሩ ከተሞች፣ ከካርቢያን ደሴቶች፣ ከጥቁር አሜሪካዊያን በኩል ተሰባስበው ወረራው ያጫረባቸውን የመጠቃት ስሜት በይፋ አንጸባርቀዋል።
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ለነበሩት የአፍቃሪ ኢትዮጵያዊነት እንቅስቃሴ መሪዎችም የአድዋው ድል የሞራል እርሾ ሆኗቸዋል። ከእንቅስቃሴው ግንባር ቀደም መሪዎች አንዱ ጀምስ ድዋኔ (James Mata Dwane) ግብጽና ሱዳን ውስጥ ያሉትን ክርስቲያን አፍሪካዊያን ሁኔታ ትኩረት ሰጥተው መፍትሄ ይፈልጉለት ዘንድ ለአጼ ምኒልክ ደብዳቤ የፃፉት የአድዋውን ድል ተከትሎ ነበር።
ስለአድዋ ድል የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዊንስተን ቸርችል “የካቲት 23 ቀን 1888 የአድዋ ጦርነት ተካሂዶ፥ ጣልያን በኢትዮጵያውያን የደረሰባት ሽንፈት ደረሰባት። (ይህም) ሌሎች ሕዝቦችን የሚነካ ሁለት ውጤቶች አስከተለ፤ አንደኛ፥ ሰሜን አፍሪካ ላይ አውሮፓዊ ክብርን ትልቅ ምች መታው። ሁለተኛ፥ በአውሮፓ ፖለቲካ ማንነት ረገድ የኢጣልያ ዋጋ ወደታች ወረደ” ብለው ጽፈዋል።
ዊንስተን ቸርችል ስለ ኢጣልያ ሽንፈትና ውጤቱ ከመጻፍ ይልቅ ስለ ኢትዮጵያ ድልና በአፍሪካና በሌሎቹ ጭቁን አገሮች ዘንድ የኢትዮጵያን ማንነት ሽቅብ መናሩን መግለጽ አልፈለጉም። ይህ ሊሆን የቻለው ምናልባትም አድዋ ላይ የተገኘው ድል ለጥቁር ሕዝቦች ከነጻነት ለመውጣት የተስፋ እርሹ በመሆኑ፣ ለአውሮፓውያኑ የቅኝ ግዛቶቻቸውን ሊያጡ የሚችሉበት ጅምር በመሆኑ ሊሆን ይችላል።
የሆነ ሆኖ አድዋ ላይ የተለኮሰው የድል ችቦ በቅኝ ግዛት ስር ለነበሩት የአፍሪካ አገሮች ቀንዲል ሆኗል። ለዚህም ክብር ለመስጠት 17 የአፍሪካ አገሮች የሰንደቅ ዓላማ ቀለማቸውን ከኢትዮጵያ ወስደዋል። አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የሆነው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለም ማሊ፣ ጋና፣ ካሜሩን … አገሮች በተለያየ ቅርጽ የአገራቸው መለያ ሰንደቅ አላማ እንዲሆን አድርገዋል።
Pankhurst, Richard. “”Viva Menelik!”: The Reactions of Critica Sociale to the Battle and to Italian Colonialism” In Adwa Victory Centenary Conference, 26 February – 2 March 1996, edited by Abdussamad Ahmad and Richard Pankhurst, 517-548. Addis Ababa: Institute of Ethiopian Studies, Addis Ababa University, 1998.
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ዘመን ባንክ እንደ ይሁዳ – (ኤርሚያስ አመልጋ – ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት)
(አጽንቼ ያቆምኩትን ባለውለታውን ዞሮ የወጋው ዘመን ባንክ)ከ20 ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ወደ አገር ቤት ተመልሼ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ስሥራ እንደመቆየቴ፣ የሥራዬ ባህሪ ከባንኮች ጋር ያገናኘኝ ነበርና አዘውትሬ ወደተለያዩ የአገሪቱ ባንኮች እሄድ ነበር። ሁሉም ባንኮች ግን፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የማይጠቀምና የደንበኞችን ፍላጐት በተቀላጠፈ መልኩ የማያረካ፣ ኋላቀር የባንክ አሠራር ይዘው ነበር የማገኛቸው።
በ2001 ዓ.ም. በባንኩ ዘርፍ ላይ ጥናት ካደረግኩ በኋላ፣ በወቅቱ በተለያዩ የአገሪቱ ባንኮች የሚታየውን ኋላቀር የባንክ አሠራር ወደ ጐን በመተው፣ ለአገሪቱ አዲስ የሆነና ባደጉት አገራት የሚሠራበት ዘመናዊ አሠራር የሚከተል በአይነቱ የተለየ ባንክ ለማቋቋም ወሰንኩ።
የማቋቁመው ባንክ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ የነበሩ ባንኮች ከሚሰጡት የተለየ ቀልጣፋና ዘመናዊ አሠራር የሚከተል እንዲሆን በማሰብም፣ አቅም ላላቸው ደንበኞች ብቻ ትኩረት በመስጠት፣ ከዚህ በፊት በአገሪቱ ባልተለመደ መልኩ በአንድ ቅርንጫፍ ብቻ አገልግሎት መስጠት የሚቻልበት አዲስ የባንክ አሠራር ቀየስኩ። ባንኩ በአንድ ቅርንጫፍ ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ቢሆንም፣ የባንኩ ባለሙያዎች ደምበኞች ያሉበት ቦታ ድረስ ሄደው የሚያገለግሉበትና ተደራሽነት ያለው አዲስ አሠራር እንዲኖር በማድረግ አገልግሎቱ በቅርንጫፍ እጥረት እንዳይስተጓጎል ተጨማሪ በቴክኖሎጂ የታገዙ የአገልግሎት አሰጣጥ ዘዴዎችን ተግባራዊ አደረግኩ።
◌ ዘመን ባንክ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 1.1 ቢልዮን ብር ማትረፉንና ይህም ከባለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ15.3 መቶ ብልጫ እንዳለው አስታወቀ
ወደ አክሲዮን ሽያጭና ባንኩን ወደማቋቋም ገባሁ። የአክሲዮን ሽያጩን በአግባቡ ለማከናወንና የሚፈለገውን ያህል ገንዘብ ለመሰብሰብ የባንኩን አጠቃላይ አደረጃጀት፣ የአገልገሎት አሰጣጥና የሥራ ዕቅድ በተመለከተ ለባለሃብቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በተደጋጋሚ በማዘጋጀት ሰፊ ማብራሪያ በመስጠት በከፍተኛ ጥረትና መስዋዕትነት ከ3 ሺህ በላይ ከሚሆኑ ባለአክሲዮኖች 150 ሚሊዮን ብር ያህል አሰባሰብኩ።
ዘመን ባንክን ለማቋቋም የጀመርኩት ጥረት በተለይ በብሔራዊ ባንክ ተደጋጋሚ እንቅፋቶች ገጥመውት ነበር። ያም ሆኖ ግን፣ በከፍተኛ መስዋዕትነት ፈተናዎችን ሁሉ ለማለፍ ተጋሁ። ከእልህ አስጨራሽ ቢሮክራሲና ኢፍትሃዊ ጣልቃገብነት በኋላም፣ ተሳካልኝና ዘመን ባንክን ወደ ሥራ አስገባሁት።
ዘመን ባንክ በአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ የራሱን አዎታዊ ተፅዕኖ የፈጠረ ስኬታማ ባንክ ለመሆን ቻለ። ይዟቸው በመጣቸው አዳዲስ የባንክ አሠራሮች ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ዘመን ባንክ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው የብዙዎችን ቀልብ መሳብና በርካታ ደንበኖችን ማፍራት እንዲሁም ትርፋማ መሆን የቻለው። ለረጅም አመታት አገልግሎት በመስጠት ከሚታወቁት ሌሎች ነባር ባንኮች ተርታ ለመሰለፍ ጊዜ አልወሰደበትም። በአንድ ቅርንጫፍ ብቻ በዓመት ከታክስ ውጭ 120 ሚሊዮን ብር አትርፏል። ዘመን ባንክ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተጐናፀፈው ተጨባጭ ስኬት ብዙዎችን ማስገረሙን ቀጥሏል።
ዘመን ባንክ በተቋቋመ በሦስተኛው ዓመት…
በዘመን ባንክ የመመሥረቻ ጽሁፍና የመተዳደሪያ ደንብ ላይ፣ ከባንኩ ዘጠኝ የቦርድ አባላት መካከል ስድስቱ በየሶስት አመቱ መቀየር እንዳለባቸው በግልጽ ተቀምጧል። በዚህም መሰረት በሦስተኛው ዓመት ላይ፣ ከነባር የቦርድ አባላት ስድስቱን ለመቀየር ዝግጅት ማድረግ ጀመርን። እኔም የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ እንደመሆኔ፣ መቀየር አለባቸው ብዬ ያሰብኳቸውን ስድስት የቦርዱ አባላት መርጬ፣ ደንቡና አሠራሩ በሚፈቅደው መሰረት ለባለአክስዮኖች እንዲያጸድቁት አቀረብኩ። የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤም፣ ግለሰቦቹ ከቦርድ አባልነታቸው እንዲነሱ ወሰኑ።
◌ ብርሃን ባንክ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 410 ሚልዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ
ይሄን ተከትሎ ነው ነገር መበላሸት የጀመረው። በእኔ ጠቋሚነት ከቦርድ አባልነታቸው ከተነሱት ስድስት ሰዎች መካከል ሁለቱ ከአባልነታቸው በመነሳታቸው እጅግ በጣም ተበሳጩ። ከእነዚህ ግለሰቦች በተጨማሪ ለችግሩ መፈጠርና መባባስ መሪ ተዋናይ የሆነ አንድ ልዩ ቂም ያለውና የ500 ሺህ ብር አክሲዮን የገዛ ባለአክሲዮንና ተወካዩ ተጨመሩበት። ይህ ግለሰብ በዘመን ባንክ የምስረታ ዘመን፣ የግሉን ህንጻ እጅግ በተጋነነ ዋጋ ለባንኩ ለማከራየትና 36 ሚሊዮን ብር ያለአግባብ ወደ ኪሱ ሊያስገባ ሲሞክር፣ ዕቅዱን ስላከሸፍኩበት ቂም ይዞ ሊያጠቃኝ ደፋ ቀና ሲልና ባንኩን ሲበጠብጥ የኖረ ሰው ነው። ሌሎቹ ሁለቱም፣ በባንኩ የቦርድ አባልነታቸው የሚያገኙትን ጥቅማጥቅም በማጣታቸው ክፉኛ የተናደዱ ናቸው። እነዚህ ሰዎች በባንኩ ምስረታ ወቅት ስለተፈጸሙ ነገሮች የሚያውቁትን መረጃ መሰረት በማድረግ ነው ሊያጠቁኝ የተዘጋጁት።
ነገሩ እንዲህ ነው…
በአገሪቱ ሕግ መሰረት፣ አንድን ባንክ ለማቋቋም ከባለአክሲዮኖች የሚሰበሰበው ገንዘብ በቀጥታ በዝግ የባንክ አካውንት ውስጥ ነው የሚቀመጠው። የተሰበሰበውን ገንዘብ ማንቀሳቀስና ባንኩን ለማደራጀት በሚያስፈልጉ ሥራዎች ላይ ማዋል የሚቻለው፣ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ከሰጠ በኋላ ብቻ ነው። ፈቃድ እስኪሰጥ ድረስ ምንም መሥራት አይቻልም። ገንዘቡ እስኪለቀቅ ጠብቆ መደበኛ የባንክ ሥራ ለመጀመር ደግሞ፣ ቢያንስ ተጨማሪ የሁለት ዓመት ጊዜ ይፈጃል። እኔ ግን ብሔራዊ ባንክ ለዘመን ባንክ ፈቃድ እስኪሰጥና በዝግ ሂሳብ የተጠራቀመው የባንኩ ገንዘብ እስከሚለቀቅ ድረስ ሥራዎች እንዲጓተቱ አልፈለግኩም። በመሆኑም ለባንኩ ምስረታው የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ከራሴ ገንዘብ ለመሸፈን ወስኜ፣ አርባ ሚሊዮን ብር የሚደርስ ገንዘብ ከራሴ ወጪ በማድረግ፣ አጠቃላይ ባንኩን በቁሳቁስና በሰው ሃይል የማደራጀት ሥራ ሠራሁ። ብሔራዊ ባንክ ብዙ ጊዜ ፈጅቶ ፈቃድ በሰጠን በቀናት ውስጥ ነበር፣ ዘመን ባንክን በቀጥታ ወደ ሥራ ያስገባሁት። ይህን በማድረጌም የዘመን ባንክ ባለአክሲዮኖች ሌላ የማንም ባንክ ባለአክሲዮን ያላገኘውን የሁለት ዓመት ትርፍ ጥቅም አስገኝቻለሁ።
ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፣ በቅን ልቦና ተነሳስቼ በዘመን ባንክ ምስረታ ወቅት የራሴን ገንዘብ እያወጣሁ ሥራዎችን ስሠራ እንደነበር የሚያውቁትና በእኔ ጠቋሚነትና በጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ ከቦርድ አባልነታቸው የተሰናበቱት ግለሰቦች እና ተባባሪያቸው ከአመታት በኋላ ይህን ሁኔታ መሰረት አድርገው የግሌን ጥቅም ለማሳደድ ያደረግኩት ነገር አስመስለው ብሔራዊ ባንክ ሄደው በመክሰስ ሊበቀሉኝ ወሰኑ። በባንኩ ምስረታ ወቅት ህጋዊ አካሄድን ባልተከተለ መልኩ የተለያዩ ሥራዎችን ስሠራ እንደነበርና በሕግ ልጠየቅ እንደሚገባ ለብሔራዊ ባንክ አመለከቱ።
◌ ወጋገን ባንክ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት አንድ ቢልዮን ብር ማትረፉንና ይህም ከባለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ49 መቶ ብልጫ እንዳለው አስታወቀ
‘አቶ ኤርሚያስ ዘመን ባንክን ሲያቋቁም የግል ገንዘቡን ተጠቅሟል። የተለያዩ የባንኩ ሥራዎችን ያሠራ የነበረው ጨረታ ሳያወጣና የጥቅም ግጭት በሚያስከትል መልኩ ነበር። የአክሰስ ካፒታልም የዘመን ባንክም ሃላፊ ከመሆኑ ጋር በተያያዘም፣ የጥቅም ግጭት የሚያስከትል አሠራር ይከተል ነበር ወዘተ…’ የሚሉ ውንጀላዎችን በዝርዝር በመግለጽ፣ ጉዳዩ ተጣርቶ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድብኝ የሚጠይቅ ማመልከቻ ለብሔራዊ ባንክ አስገቡ።
የግለሰቦቹ አቤቱታ ለብሔራዊ ባንክ ትልቅ አጋጣሚ ሆነለት። ዱሮም በሄድኩበት ሁሉ እየተከተለ እንቅፋት ሲፈጥርብኝ የኖረውና እንቅስቃሴዬን ለመግታት ሰበብ ሲፈልግ የነበረው ብሔራዊ ባንክ፣ የግለሰቦቹን ማመልከቻ በደስታ ነበር የተቀበለው። ይህን ተከትሎም፣ መጋቢት 6 ቀን 2003 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ በዘመን ባንክ የምስረታ ወቅት አንዳንድ ወጪዎች የተደረጉት የጥቅም ግጭት በሚያስከትል መልኩ እንደነበር የሚጠቁሙ ምልክቶች ስለተገኙ በወቅቱ የተደረጉ የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች በሙሉ በባንኩ በሚሾም ኦዲተር እንዲመረመር መወሰኑን ገለጸ። ይህም ብቻ አይደለም፤ ጉዳዩ ተጣርቶ እስኪጠናቀቅ ድረስም፣ እኔን ከዘመን ባንክ የቦርድ አባልነቴ በጊዚያዊነት እንዳገደኝ አሳወቀኝ።
ብሔራዊ ባንክ ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት የተጀመረውና አንድ ዓመት ያህል ፈጅቶ የተጠናቀቀው የኦዲት ምርመራ ሪፖርት ግን፣ በዘመን ባንክ ምስረታ ወቅት ያከናወንኩት ሥራ እንደተባለው የጥቅም ግጭት የሚያስከትል እንዳልነበር አረጋገጠ። የግል ገንዘቤን ወጪ አድርጌ ባንኩን ሳቋቁም፣ የግሌን ተጠቃሚነት ለማስጠበቅ ያከናወንኩትና በሕግ የሚያስጠይቀኝ ምንም አይነት ወንጀል እንዳልሠራሁ መሰከረ።
◌ ደቡብ ግሎባል ባንክ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 142 ሚልዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ
የኦዲት ሪፖርቱ በባንኩ ምስረታ ወቅት ተጠያቂ የሚያደርገኝ ህገወጥ ተግባር እንዳልፈጸምኩ ቢያረጋግጥልኝም፣ ብሄራዊ ባንክ ግን ከዘመን ባንክ አመራርነቴ በጊዚያዊነት እንድነሳ የጣለብኝን እገዳ ሊያነሳልኝ አልፈቀደም። የግለሰቦችን ውንጀላ መሰረት አድርጎ የወሰደብኝ እርምጃ አግባብነት የሌለው መሆኑን የሚያሳይና በአፋጣኝ ወደ ሥራዬ እንድመለስ የሚጠይቅና “የዘገየ ፍትህ እንደተነፈገ ይቆጠራል” የሚል ርዕስ ያለው ጽሁፍ አዘጋጅቼ በፎርቹን ጋዜጣ ላይ አወጣሁ። ጽሁፉ በጋዜጣው ላይ በወጣ በሁለተኛው ቀን ግን፣ ከዘመን ባንክ አመራርነት ብቻም ሳይሆን ከማንኛውም የአገሪቱ ባንክ የቦርድ አባልነት እስከመጨረሻው መታገዴን የሚገልጽ ደብዳቤ ከብሔራዊ ባንክ ደረሰኝ።
40 ሚሊዮን ብር ያህል ገንዘብ ከግሌ ወጪ አድርጌ ባንኩን በማቋቋሜ፣ ወንጀል ሠራህ ተባልኩ። የሠራሁት ወንጀል መኖሩ በገለልተኛ አካል በኦዲት እንዲጣራ ተደረገ፣ የኦዲት ምርመራው ውጤት ወንጀል አለመሥራቴን አረጋገጠ። ብሔራዊ ባንክ ግን፣ ወንጀል አለመሥራቴን ቢያረጋግጥም እኔን ከመቅጣት ወደኋላ አላለም። ራሱ ከሳሽ ራሱ ፈራጅ የሆነውን፣ ባለሙሉ ስልጣኑን ብሔራዊ ባንክ በፍርድ ቤት ለመክሰስና መብትን ለማስከበር ህጉ አይፈቅድልኝም። ስለዚህ ብሔራዊ ባንክን ከስሼ መብቴን ለማስከበር ከመሞከር ይልቅ፣ የደረሰብኝን ግልጽ በደል ለመንግስት ማሳወቅ እንዳለብኝ ተሰማኝ። የተፈጠረውን ነገር በሙሉ በዝርዝር ገልጬ፣ አቤቱታዬን በደብዳቤ መልክ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ላክሁ።
ደብዳቤውን ከላክሁ ከቀናት በኋላ፣ በወቅቱ በጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ የመንግስት ተቋማት ድጋፍና ክትትል ሃላፊ የነበሩ ግለሰብ፣ በጉዳዩ ዙሪያ ሊያወያዩኝ እንደሚፈልጉ በመግለጽ ወደቢሯቸው አስጠሩኝ። ደስተኛ ሆኜ ወደቢሯቸው ሄድኩ። ጉዳዩን ከስር መሰረቱ አብራራሁላቸው፤ ዘመን ባንክን ለመመስረት ካሰብኩበት ጊዜ ጀምሮ ብሔራዊ ባንክ የፈጠረብኝን ችግሮች፣ ያደረሰብኝን በደልና በተደጋጋሚ ያስተላለፈብኝን ኢፍትሃዊ ውሳኔዎች በዝርዝር አቀረብኩላቸው። ከሰውዬው ጋር ሰዓታትን የፈጀ ውይይት ካደረግኩ በኋላ ግን፣ ፍትህን ፍለጋ ወደቢሯቸው መምጣቴ ከንቱ ድካም መሆኑን የሚያሳይ ምላሽ ሰጡኝ።
“አቶ ኤርሚያስ በሆነው ነገር ሁሉ እናዝናለን። አንተን ለማጥቃት ተብሎ የተደረገ ነገር የለም። አንተ የምትሠራቸው ሥራዎች ለአገር ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳላቸውና ፈር ቀዳጅ እንደሆኑ እናውቃለን። አንተ ተራ ነጋዴ እንዳልሆንክም እናውቃለን። ተቋማትን ነው የምትገነባው። ሥራዎችህን እና ጥረትህንም እንደግፋለን። ያው እንደምታውቀው ግን፤ ታዳጊ አገር ውስጥ ነው ያለነው። አንዳንዴ መሆን የሌለባቸው ነገሮች ይሆናሉ። በአንተ ላይ የተፈጸመው ነገር ትክክል እንዳልሆነ ይገባናል። ችግሩ በጊዜ ሂደት ይፈታል ብለን እናምናለን። ስሜትህ ሳይነካ፣ ጠንክረህ ሥራህን እንድትቀጥል ነው የምንፈልገው። ከዚህ ውጭ ግን፣ በብሔራዊ ባንክ ስልጣንና ሃላፊነት ውስጥ ጣልቃ ገብተን አስተያየት ለመስጠትም ሆነ ውሳኔውን ለማስቀየር ይከብደናል” የሚል ምላሽ ሰጡኝ።
◌ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 658.7 ሚልዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ
ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍዬ ካቋቋምኩትና ወደትርፋማነት ካሸጋገርኩት ዘመን ባንክም ሆነ፣ አዳዲስ አሠራሮችን አስተዋውቄ ተጨባጭ ለውጥ ከፈጠርኩበት የአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ በዚህ መልኩ ያለአግባብ ተገፍቼ እንድወጣ ተደረግኩ። ከዘመን ባንክ አመራርነቴም ከባንኩ ዘርፍም እንድወጣ የተላለፈብኝ ውሳኔ ቢያሳዝነኝም፣ ሌላ የተሻለ ሥራ እንደምጀምርና ነባር ሥራዎችን አጠናክሬ እንደምቀጥል ስለማውቅ ብዙም ትኩረት አልሰጠሁትም – ፊቴን ወደሌሎች ሥራዎች አዞርኩ።
በዘመን ባንክ መሥራችነቴ ማግኘት የሚገባኝን ጥቅም አለማግኘቴን ያስታወስኩት እንኳን፣ ባንኩ ሥራ በጀመረ በሶስተኛው ዓመት ላይ ነበር። በዘመን ባንክ የመመስረቻ ጽሁፍ አንቀጽ 7 ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው፣ የባንኩ መሥራቾችና አደራጆች በመጀመሪያዎቹ 3 አመታት ባንኩ ከሚያገኘው የተጣራ ትርፍ 10 በመቶ የመሥራችነትና የአደራጅነት ጥቅም ያገኛሉ። እኔም የባንኩ መሥራች እንደመሆኔ ከሶስቱ አመታት ትርፍ ይህን ድርሻ ማግኘት ይገባኝ ነበር። በወቅቱ ዋነኛ ትኩረቴ የነበረው ባንኩን ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንጂ የግል ገንዘብ በማሳደድ ላይ ስላልነበር፣ ከመጀመሪያውም ሆነ ከሁለተኛው ዓመት የባንኩ ትርፍ ላይ የመሥራችነት ድርሻዬን ተከታትዬ አልተቀበልኩም። ሶስተኛው ዓመት ላይ ግን፣ ቢያንስ ያለፉትን ሁለት አመታት የመሥራችነት የትርፍ ድርሻ አስልቶ እንዲከፍለኝ ለባንኩ ጥያቄ አቀረብኩ።
ዘመን ባንክ በ2002 ዓ/ም በ2003 ዓ/ም በድምሩ ብር 92,634,690.00 /ዘጠኛ ሁለት ሚሊዩን ስድስት መቶ ሰላሳ አራት ሺ ስድስት መቶ ዘጠና/ ማትረፉ በውጭ ኦዲተሮች በተረጋገጠው መሰረት፣ የዚህ ገንዘብ አስር በመቶ እና የውጭ ኦዲተሮች ባንኩ ማትረፉን ካረጋገጡበት ቀን ጀምሮ ከሚታሰብ ዘጠኝ መቶ ወለድ ጋር በድምሩ 10,359,105.69 /አስር ሚሊዩን ሶስት መቶ ሃምሳ ዘጠኝ ሺ አንድ መቶ አምስት ብር ከ69/100/ እንዲከፈለኝ ነበር የጠየቅኩት። የወቅቱ የዘመን ባንክ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤና ቦርድ፣ ይህ ክፍያ እንዲፈጸምልኝ ወሰነ። የሚገርመው ነገር ግን፣ አሁንም የብሔራዊ ባንክ ኢፍትሃዊ በደል አልቀረልኝም። ብሔራዊ ባንክ ለኤርሚያስ ይከፈል ያላችሁትን ክፍያ አልቀበለውም፤ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤና የቦርድ ውሳኔ የተላለፈበትን ቃለ-ጉባኤም አላጸድቅም አለ። ዘመን ባንክም ይህን የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ መሰረት በማድረግ ክፍያውን እንደማይፈጽምልኝ አስታወቀኝ።
እዚህ ላይ ዝም ማለት አልፈለግኩም። ዘመን ባንክን በፍርድ ቤት ለመክሰስና በመሥራችነቴ ማግኘት የሚገባኝን ክፍያ በሕግ ለማግኘት ወስኜ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መሰረትኩ። የከፍተኘው ፍርድ ቤት ግን ግንቦት 3 ቀን 2009 ዓ/ም ክሱን ውድቅ አደረገው። ይህን ውሳኔ በመቃዎም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠየቅኩ። ፍርድ ቤቱም የከፍተኛው ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመሻር የሚገባኝ ገንዘብ እንዲከፈለኝ መጋቢት 18 ቀን 2009 ዓ/ም ወሰነልኝ። ዘመን ባንክ በዚህ ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል በማለት የሰበር አቤቱታ ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ቢያቀርብም፣ ፍርድ ቤቱ ግን የተፈጸመ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለም ሲል ውድቅ አደረገው።
◌ ዳሽን ባንክ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 1.14 ቢልዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ
በፍርዱ መሰረት ክፍያው እንዲፈጸምልኝ ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የአፈጻጸም አቤቱታ ባቀረብኩት መሰረት ባንኩ ክፍያውን እንዲፈጽም ሲጠየቅ ግን፣ ክፍያውን ሊፈጽምልኝ አልፈለገም። ይልቁንም የተለያዩ ምክንያቶችን እየደረደረና ሌሎች የጥቅም ግጭት ጥያቄዎችን እያነሳ፣ አዳዲስ ክርክሮችን መፍጠሩን ተያያዘው። አልፎ ተርፎም በእኔ ላይ አዲስ የወንጀል ክስ በመመስረት የተወሰነው ገንዘብ እንዲታገድና እንዳይከፈለኝ አደረገ። ባንኩ የመሰረተብኝ አዲሱ ክስ አሁንም ተጨማሪ የጥቅም ግጭት ነበረ የሚል ክስ ነበር። የቀረበብኝ ክስ የወንጀል ክስ መሆኑ ደግሞ እጅግ በጣም የሚገርምም የሚያሳዝንም ነበር።
የራሴን ገንዘብ አውጥቼ፣ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍዬ፣ ብዙ ፈተናዎችንና እንቅፋቶችን አልፌ ያቋቋምኩትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርፋማ ያደረግኩት ዘመን ባንክ፣ ለውለታዬ እውቅና መስጠትና ስሜን በክብር ማውሳት ባይሆንለት የሚገባኝን ጥቅም ለመከልከል በእኔ ላይ ያልተገባ ክስ መመስረቱ በእጅጉ አሳዝኖኛል።
የአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ለዘመናት ከኖረበት ኋላቀር አሠራር ተላቅቆ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አሠራር እንዲዘረጋ በማስቻል ረገድ ፈር ቀዳጅ ሥራ ሰርቻለሁ። ለዘመን ባንክ እዚህ ደረጃ መድረስ ቁልፍ ሚና ተጫውቻለሁ። ገንዘቤን፣ እውቀቴንና ልምዴን ሳልሰስት በመገበር፣ ባንኩንም ባለአክሲዮኖችንም በተለየ ሁኔታ ትርፋማ አድርጊያለሁ። የባንኩ ኢንዱስትሪ ተዋንያንም ሆኑ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ውለታዬን ሲዘክሩት ይኖራሉ። የዘመን ባንክ ባለአክሲዮኖችም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለሠራሁት ሥራ እውቅና ሲሰጡኝ ኖረዋል። በቅርቡ አዲስ አበባ ውስጥ ያጋጠመኝ ድንገተኛ ነገር ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል።
አንድ ማለዳ ከወዳጄ ጋር ወደነበረኝ ቀጠሮ እየሄድኩ እያለ፣ መንገድ ላይ አንድ የማላውቀው ሰው ስሜን ጠርቶ አስቆመኝ። ሰላምታ እንኳን ሳይሰጠኝ፣ በደስታ ስሜት ውስጥ ሆኖ አቀፈኝ። በግለሰቡ ድርጊት እየተገረምኩ እያለ፣ በስሜት ተውጦ ምክንያቱን ነገረኝ። ‘አቶ ኤርሚያስ… አንተ አታውቀኝም፤ ከአመታት በፊት ዘመን ባንክን ስታቋቁም ተገናኝተን ነበር። ስለምታቋቁመው ባንክ ማብራሪያ ስትሰጥ ሰምቼ፣ ባንኩ አትራፊ እንደሚሆን በመተማመን በ50 ሺህ ብር አክሲዮን ገዛሁ። ያኔ በ50ሺ ብር የገዛኋት የዘመን ባንክ አክሲዮን፣ ዛሬ ሚሊዬነር አድርጋኛለች… አንተ ባታውቀኝም፣ ባለሃብት ያደረግከኝ ባለውለታዬ ነህ! …’ እያለ ደጋግሞ አመሰገነኝ። ከዘመን ባንክ ያተረፍኩት ነገር፣ በሄድኩበት ሁሉ የሚያጋጥመኝ ይህን መሰሉ የሰዎች ፍቅርና አድናቆት ነው።
◌ አዋሽ ባንክ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 1.96 ቢልዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ
ለአመታት ብዙ ነገር የከፈልኩለት ዘመን ባንክ ግን፣ የከፈልኩለትን መስዋዕትነት ከንቱ ሊያስቀረውና የሚገባኝን ጥቅም ሊያሳጣኝ አሁንም ቆርጦ ቆሟል። ወርቅ ያበረከትኩለት ዘመን ባንክ፣ ጠጠር ሊመልስልኝ ደፍሯል። በቅንነት የፈጸምኩትን ተግባር የግል ጥቅሜን ለማሳደድ ያደረግኩት ዝርፊያ በማስመሰል፣ ያለሥራዬ የወንጀል ክስ መስርቶብኛል። ከአገር እንዳልወጣ ሳይቀር አሳግዶኛል። ፍርድ ቤት የዘመን ባንክን መሰረተቢስ ክስ ተቀብሎ የሚያስተላልፈው ውሳኔ ምንም ይሁን ምን፣ ዘመን ባንክ ግን ትልቅ ክህደት እንደፈጸመብኝ ህዝቡ ሊያውቀው ይገባል።
ዘመን ባንክ የፈጸመብኝን ክህደት በአደባባይ ላወጣው የወሰንኩት፣ የሚገባኝን ጥቅም አለማግኘቴ አንገብግቦኝ አይደለም። የእኔ ጥያቄ የገንዘብ አይደለም – የፍትህ እንጂ። ህይወቴ በዘመን ባንክ 10 ሚሊዮን ብር የታጠረች አይደለችም። እጄ ላይ ያሉት ጅምር ሥራዎችና የሚያንቀሳቅሱት ገንዘብ፣ ከዘመን ባንክና ከነፈገኝ 10 ሚሊዮን ብር ጋር የሚወዳደሩ አይደሉም። ሰበብ እየፈለገ ሲያስረኝና ሲፈታኝ የኖረው መንግስት፣ ባልተሳተፍኩበት አስቂኝ የሙስና ወንጀል እጄን ይዞ ወደ ቂሊንጦ ላከኝ እንጂ፣ በረቀቀ ቴክኖሎጂ የሚከወንና ለአገሪቱ አዲስ የሆነ ግዙፍ ቢዝነስና ኢንቨስትመንት ወደ አገሪቱ ለማስገባት መንገድ ላይ ነኝ።
በስተመጨረሻም፣ መላው ህዝብ ዘመን ባንክ በእኔ ላይ የሠራውን ግፍና በደል እንዲያውቅልኝ ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ጥሪዬን እያስተላለፍኩ፤ ባንኩ የመሰረተብኝን ሃሰተኛ የወንጀል ክስ አንስቶ የሚገባኝን የመሥራችነት መብት እንዲያከብርልኝ ለማስቻል በማደርገው ጥረት ውስጥ ሁሉም ከጎኔ እንዲቆም እጠይቃለሁ!
ከከበረ ሰላምታ ጋር።
ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ
(የዘመን ባንክ መሥራችና የቀድሞ የቦርድ ሊቀመንበር)
የካቲት 7 ቀን 2011 ዓ.ም.
ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት
አዲስ አበባ
ወላይታ ሶዶ (ሰሞነኛ)– የወላይታ ልማት ማህበር ለሰው ሀብት ልማት ልዩ የትኩረት ሰጥቶ በሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል በትምህርትና ስልጠና በዕውቀትና ክህሎት የበለጸጉ ዜጎችን ማፍራት ዓላማው አድርጎ የራሱን ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ለዚህም ዓለማ የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት በማቋቋም፣ በዞኑ ውስጥ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ በማድረግ፣ በትምህርት ጥራት ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት፣ የቅድመ መደበኛ ትምህርት በማስፋፋትና ዕድሜያቸው ለትምህርት ደርሶ በድህነት ምክንያት በትምህርት ገበታ ላይ መገኘት ያልቻሉ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት በማስገባት ሙሉ የትምህርት ቁሳቁሶችን በማሟላት ከእኩዮቻቸው ጋር እኩል ለማድረግ በአንድ ዓመት ከአንደኛ ክፍል እስከ ሦስተኛ ክፍል በማስተማር በዓመቱ መጨረሻ በየወረዳው ትምህርት ጽ/ቤቶች የሚዘጋጀውን ፈተና ተፈትነው ሲያልፉ ወደ መደበኛው አራተኛ ክፍል ተዛውረው ትምህርታቸውን የሚቀጥሉበት ወደ አራተኛ ክፍል በማዛወር የተፋጠነ ትምህርት ለአፍሪካ በተሰኘ ፕሮጀክት እየተገበረ ይገኛል።
◌ ቪዲዮ፦ ደቡብ ግሎባል ባንክ ባለፈው የበጀት ዓመት ከታክስ በፊት ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ
የወላይታ ልማት ማህበር በሰው ሀብት ልማት ዘርፍ ከሚተገብራቸው ፕሮጀክቶች አንዱ ጀኔቫ ግሎባል ከተባለ ግብረሰናይ ድርጅት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚያከናውነው የተፋጠነ ትምህርት ፕሮጀክት ነው። ይህ ፕሮጀክት ከ2013 እ.ኤ.አ. ጀምሮ በወላይታ ዞን ውስጥ ከ13,500 በላይ በድህነት ምክንያት ወደ ትምህርት ቤት መግባት ያልቻሉ ህጻናትን ተጠቃሚ አድርጓል።
ፕሮጀክቱ ከትናንትናው ዕለት ጥር 29 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለፕሮጀክቱ አመቻች የአንደኛ ደረጃ መምህራን፣ ከዳሞት ሶሬ ወረዳ ለተወጣጡ መምህራንና ርዕሰ መምህራን በተግባር ተኮር የመማር ማስተማር ስነዘዴ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ ሲሆን ስልጠናው አስከ የካቲት 2 ቀን 2011 ዓ.ም.. እንደሚቆይ በልማት ማህበሩ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ቆርጋ ላምቤቦ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በተያዘው በጀት ዓመት በዳሞት ሶሬ ወረዳ አስር ትምህርት ቤቶች በ3 ሚሊዮን ብር በ30 የመማሪያ ክፍሎች ለ900 ህጻናት ሙሉ የትምህርት ቁሳቁሶችን በማሟላት አመርቂ ሥራ እየሠራ ይገኛል።
ከዚህ ጎን ለጎን የእነዚህን ተማሪዎች እናቶች በራስ አገዝ ማህበራት በማደራጀት በመረጡት የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ በየሳምንቱ ገንዘብ በማስቆጠብና ከራሱ መጠነኛ ድጎማ በማድረግ ገቢያቸውን እንዲያሻሽሉና ወደ ፊት ልጆቻቸው ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ በማድረግ፣ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች አቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠትና የህጻን ለህጻን ትምህርትን በማጎልበት እንደሚሠራ ከፕሮግራም ኦፕሬሽን ዳይሬክቶሬት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ምንጭ፦ የወላይታ ልማት ማህበር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
የጊዳቦ ግድብ ሥራ ፕሮጀክት በ258 ሚሊዮን ብር በጀት የተጀመረ ቢሆንም ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቁ እና የዲዛይን ለውጥ በመደረጉ አጠቃላይ የግንባታ ወጭው 1.66 ቢሊዮን ብር መድረሱን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አስታውቀዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢ.ኮ.ሥ.ኮ) በውሃ መሠረተ ልማት ኮንስትራክሽን ዘርፍ እየተገነባ የሚገኘው የጊዳቦ ግድብ ሥራ ፕሮጀክት መቶ በመቶ መጠናቀቁን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።
የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አብዱልፈታህ ታጁ በታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም. ፕሮጀክቱን ለጎበኙ በኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ባለሙያዎች እንደገለጹት የጊዳቦ ዋና ግድብ ሥራ መቶ በመቶ ተጠናቆ በጥር ወር 2011 ዓ.ም እንደሚመረቅ ገልጸዋል።
የጊዳቦ ግድብ ሥራ ፕሮጀክት በ258 ሚሊዮን ብር በጀት የተጀመረ ቢሆንም ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቁ እና የዲዛይን ለውጥ በመደረጉ አጠቃላይ የግንባታ ወጭው 1.66 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቀዋል።
የግድቡን ዲዛይንና የቁጥጥር ሥራውን ያካሄደው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን ሲሆን፣ ግንባታውን ደግሞ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አከናውኖታል።
የኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎችን በመስኖ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቀው የጊዳቦ ግድብ በአጠቃላይ 63.5 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እና 13,425 ሔክታር መሬት ማልማት ያስችላል የተባለው ይህ የጊዳቦ መስኖ ልማት ግድብ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሳይጠናቀቅ የዘገየው እና የፕሮጀክቱ የገንዘብ መጠኑ የጨመረው ውሉ ከተፈረመ ከሁለት ዓመታት በኋላ ግንባታው መጀመሩ፣ የዲዛይን ለውጥ መደረጉ፣ በአካባቢው የካሳ ክፍያ የሚጠይቁ ሥራዎች መኖራቸው፣ የባለድርሻ አካላት ችግር፣ በግንባታ ዕቃዎች አቅርቦት እጥረት ምክንያት ነው። ግድቡ የተጀመረው በ2002 ዓ.ም. ሲሆን፥ ሲጀመር ይጠናቀቃል ተብሎ የታቀደው በ2004 ዓም ነብር።
ግድቡ ሲጀመር ተይዞ የነበረው 16 ሜትር ከፍታ ሲሆን አሁን ላይ ወደ 22.5 ሜትር ከፍታ፣ 315 ሜትር ርዝመትና፣ 7.16 ኪ.ሎ ሜትር ርዝመት ያለው በግድቡ ግራ እና ቀኝ የዋና ቦይ ግንባታ ሥራዎችን መሠራቱ እና በአንድ ሺህ አምሳ ሄክታር መሬት ላይ ውሃ እንዳጠራቀመ (ሰው ሠራሽ ሀይቅ እንደሚኖረው) ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ግንባታው ሙሉ በሙሉ በመጠናቀቁ በሚቀጥለው በያዝነው ወር የፌዴራል፣ የደቡብ እና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ይመረቃል ተብሎ መርሐ ግብር ተይዟል።
ምንጭ፦ ኢ.ኮ.ሥ.ኮ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የካንሰርና የልብ ህክምና ማዕከል ግንባታ 56 በመቶ ደርሷል
- አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገነባው የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ በተያዘለት ጊዜ አይጠናቀቅም
- አዳማ ከተማ ውስጥ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው እና ጥቅም ላይ የማይውሉ መድኃኒቶችን ማስወገጃ ማዕከል ተገነባ
- የጅማ–አጋሮ–ዲዴሳ ወንዝ ድልድይ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በተገኙበት በይፋ ተጀመረ
- ኬር ኢትዮጵያ በ7 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ወጭ ያስገነባውን የምርምርና የስልጠና ማዕከል ለሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አስረከበ
ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ለተለያዩ ትምህርት ቤቶች ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪም በሌሎች የማኅበረሰብ-አቀፍ አገልግሎቶች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው አቅዶ እየሠራ መሆኑን ተገልጿል።
ጂንካ ከተማ፣ ደቡብ ኦሞ ዞን (ሰሞነኛ) – ጂንካ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ተገንብተው በ2010 ዓ.ም. ወደ ሥራ ከገቡት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንዱ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው ምንም እንኳን ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆንም የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ-አቀፍ አገልግሎት (community-based service) በደቡብ ኦሞ ዞን ውስጥ ለሚገኙ 18 ሁለተኛ ደረጃ እና አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በጥቅሉ ለ19 ትምህርት ቤቶች 510 ኮምፒዩተሮችን ከአንድ ደርጅት እንዲሁም በውጭ ሀገር ከሚኖር አንድ የአካባቢው ተወላጅ ጋር በመተባበር ለእያንዳንዳቸው ሃያ አምስት፣ ሃያ አምስት ኮምቲዩተሮችን ለትምህርት ቤቶቹ የሰጠ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕ/ር ገብሬ ይንቲሶ ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም እነዚህ ኮምፒዩተሮች ተማሪዎቹ ከቴክኖሎጂ ጋር እንዲተዋወቁ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ በሁሉም ኮምፒዩተሮች ላይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር የሚያዘጋጃቸው የመማሪያ መጽሐፍት እና ሌሎች አጋዥ ሊሆኑ የሚችሉ ሶፍትዌሮች የተጫኑባቸው በመሆኑ ተማሪዎቹ በቀላሉ የሚፈልጉትን ለማግኘት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ለICT (information, communication and technology) እና ሂሳብ መምህራን በICT አጠቃቀም ዙሪያ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል ፕሬዚዳንቱ ።
ድጋፍ የተደረገላቸው ትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራን በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው አዲስ የተከፈተ ቢሆንም ለየትምህርት ቤቶቹ የተደረገው ድጋፍ የመማር ማስተማር ሂደቱን ከማሳለጥ አንፃር ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ያሉ ሲሆን፥ በቀጣይ ትምህርት ቤቶችን በመደገፍ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ ዩኒቨርሲቲው የራሱን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት ቤቶች ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪም በሌሎች የማኅበረሰብ-አቀፍ አገልግሎቶች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው አቅዶ እየሠራ መሆኑን የገለፁት የዩኒቨርሲቲው ቢዝነስ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ነፃነት ይርጉ ሲሆኑ ከብት በማደለብ፣ በከብቶች ህክምና፣ በዶሮ እርባታ፣ በንብ እርባታ፣ በአሳ እርባታ በመሳሰሉት ውጤታማ ሥራዎችን ለመሥራት አቅዶ በተግባር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተዋል።
ምንጭ፦ የትምህርት ሚኒስቴር
——
See also:- የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ አዲስ ተማሪዎችን ተቀበለ
- አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ41 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ መዘጋጀቱን አስታወቀ
- የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሠራ ነው
- የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አዲሱ ካምፓስ (በንሳ ዳዬ ካምፓስ) ተማሪዎችን በመቀበል በይፋ ሥራ ጀመረ
- ጂንካ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን 1ሺህ 500 ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረገ ነው
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ ለትምህርትና ጤና አገልግሎት የሚውል ከ452 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረገ። የጃፓን መንግስት አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲው በኩል ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ አራት ፕሮጀክቶችን ለመገንባትና ለማስፋፋት ያስችላል።
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ (Daisuke Matsunaga) የፕሮጀክት ግንባታና ማስፋፊያ ከሚደረግላቸው ትምህርት ቤቶች ኃላፊዎች ጋር የድጋፍ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ፕሮጀክቶቹ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን የጉንችሬ እና እነሞር ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታና በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የሀሮ ሾጤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ናቸው።
በተጨማሪም ለሻሻመኔ ከተማ የአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች የምግባረ ሰናይ መጠለያ ግንባታና ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የዩሮሎጂ እና ድንገተኛ ክፍል የህክምና መሣሪያዎች ግዥ የሚውል ነው።
እነዚህ አራት የትምህርት እና የጤና ፕሮጀክቶች ከአራት ሺህ በላይ ህዝብ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።
አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ እንዳሉት አገራቸው ለኢትዮጵያ ልማት ተሳትፎ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች። ጃፓን በኢትዮጵያ እ.አ.አ ከ1989 ጀምሮ በተለያዩ ክልሎች ከ400 በላይ ፕሮጀክቶችን በመሥራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገች ነው።
በትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ በኢኮኖሚ ልማትና ሌሎችም መስኮች ድጋፍ ስታደርግም ቆይታለች።
በስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽነር እርስቱ ይርዳው የተደረገው ድጋፍ የዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል የትምህርት ፍላጎት ለማሟላት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ድጋፉ በተለይም ትምህርት ቤት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች መሆኑ የትምህርት ሽፋንን በማስፋት የመንግስትን ጥረት እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ የጃፓን ኤምባሲ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኘውን የራስ መኰንን አዳራሽ ለማደስ የ85 ሺሕ 679 ዶላር (2,403,500 ብር) ዕርዳታ መለገሱን ሪፖርተር ጋዜጣ በእሁድ ታህሳስ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. እትሙ ዘግቧል።
አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ እና የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር አህመድ ሐሰን (ዶ/ር) የእርዳታ ስምምነቱን የተፈራረሙ ሲሆን፣ ገንዘቡም የራስ መኰንን አዳራሽ ባህላዊና ታሪካዊ ዳራው ሳይጠፋ ለማደስ፣ የተበላሹ ክፍሎችን ለመጠገን፣ ውስጣዊ ክፍሉን ለማደስ እና አዳዲስ ቁሳቁስ ለማስገባት መሆኑ ታውቋል።
የጃፓን መንግስት ትምህርታዊ ድጋፍ ከማድረጉም በተጨማሪ የራስ መኰንን አዳራሽን ለማደስ መነሳቱ፣ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ኢትኖሎጂካል ሙዚየም በርካታ ጎብኚዎች እንዲስብ ያስችላል ተብሏል።
በሙዚየሙ ከአሥር ሺሕ በላይ የኢትዮጵያ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች የሚገለጹባቸው አልባሳትና ቁሳቁሶች አሉ፤ ይህም በአፍሪካ አንዱ ታዋቂ ሙዚየም እንዲሆን አስችሏል።
በቀድሞው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ሕንፃ ውስጥ የሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ ከ50 ዓመታት በላይ ዕድሜው በስሩ ያቀፋቸው ቤተ-መጻሕፍት፣ የኢትኖግራፊክ ሙዚየም የምርምርና የጥናት ማዕከልን ነው። በውስጡም መጻሕፍት፣ ታሪካዊ ሰነዶችና መዛግብት፣ የዳግማዊ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱን ጨምሮ የድምፅና የምስል ቅጂዎች፣ ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ የጥናት ድርሳኖች፣ ጆርናሎች፣ ረጅም ዕድሜን ያስቆጠሩ የብራና መጻሕፍትንም ይዟል።
እንዲሁም እስከ 20 ሺሕ የሚደርሱ የኅትመት ክምችቶች ከቅድመ ምረቃ እስከ ድኅረ ምረቃ ተማሪዎች፣ ለተመራማሪዎች ጥናትና ምርምር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2010 ዓ.ም. መስከረም ወር ከጃፓኑ ኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ ጋር ትምህርታዊ ልውውጥና የጥናት ትብብር ለማድረግ የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙ ይታወሳል።
ምንጭ፦ ኢዜአ እና ሪፖርተር ጋዜጣ
ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ለተቀናጀ የግብርና-ኢንዱስትሪ ፓርኮች ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የ15 ሚሊዮን የአሜርካ ዶላር (420 ሚሊዮን ብር) ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ኢትዮጵያ እና ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ልማቶችን በገንዘብ የሚደግፈው የአፍሪካ ልማት ባንክ ለተቀናጀ የግብርና-ኢንዱስትሪ ፓርኮች ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የ15 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራረሙ።
የፋይናንስ ስምምነቱን የፈረሙት በኢትዮጵያ በኩል የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ሲሆኑ በአፍሪካ ልማት ባንክ በኩል ደግሞ የባንኩ የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ አብዱል ካማራ (ዶ/ር) ናቸው።
ዋና መቀመጫነቱ በአቢጃን ከተማ (አይቮሪኮስት) የሆነው የአፍሪካ ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፉን ያደረገው በኢትዮጵያ በግብርና – ኢንዱስትሪ (agro-industry) ዙርያ እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ነው። ድጋፉ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ እና በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስታት ስር እየተገነቡ ላሉ አራት ኢንዱስትሪ ፓርኮችን እንደሚውል ተገልፃል።
ፕሮጀክቱ ሦስት ዋና ዋና ክፍሎችን ለመደገፍ የሚውል ሲሆን በኢንዱስትሪ ፓርኮች መሠረተ-ልማትን ለማሳደግ፣ በዘላቂነት የግብርና-ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ እንዲኖር ለማሰቻል እና በፕሮጀክት አስተዳደርና አተገባበር ላይ ለአራቱ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት እና ለንግድ እና ኢንዱስትሪ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ለማከናውን ይውላል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በፊርማ ሥነ-ሥርዓት ወቅት እንደተናገሩት፥ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካለቸው የአፍሪካ ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የተለያዩ መርሀ ግብሮችን ነድፋ እየተንቀሳቀሰች የምትገኝ ሲሆን፥ በተለይም ሁሉን አቀፍ እድገት እንዲኖር ማስቻል፣ ድህነት ቅነሳ እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር የማደረግ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ ልማት በስፋት ለመግባት እያደረገች ላለው ጥረት የአፍሪካ ልማት ባንክ እያደረገው ላለው ድጋፍ ምስጋናቸው አቅርበዋል።ባለፈው ወር የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ የዘረጋቸውን መሠረታዊ አገልግሎቶች ማሻሻያ መርሀ ግብር (Basic Services Transformation Program) ለመደገፍ 123 ሚሊዮን ዶላር ድጎማ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል።
ምንጭ፦ የገንዘብ ሚኒስቴር
——
ተጨማሪ ዜናዎች፦- አንበሳ የከተማ አውቶቡስ በአንዳንድ አካባቢዎች አገልግሎቱን በማቋረጡ ተገልጋዮች ለችግር ተዳርገዋል
- የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የፎረንሲክ ምርመራ በጋራ ለማከናወን ተስማሙ
- የጅማ–አጋሮ–ዲዴሳ ወንዝ ድልድይ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በተገኙበት በይፋ ተጀመረ
- ሐረር የሚኖሩ የጉራጌ ህብረተሰብ አባላት በመስቃንና ማረቆ ወረዳ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ100,000 ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ
- የዱባይ አቡዳቢው ኤግል ሒልስ በአዲስ አበባ ለገሀር የተቀናጀ የመኖሪያ፣ አገልግሎት መስጫና የመዝናኛ ስፍራ ሥራውን ጀመረ