-
Search Results
-
ቅኔ ነው ሀገር ― የሦስት ሙዚቃዊ ዘመናት አንጋፋ እና ወጣት ድምፃውያንን እንዲሁም ታላላቅ የሙዚቃ ሊቃውንትን ያገናኘ ልዩ ኦርኬስትራዊ ኅብረ ዝማሬ!!!
- ከ1950ዎቹ እና 60ዎቹ አንጋፋ ድምጻውያን መካከል አንዱ የሆነው ጥዑመ ልሳኑ ድምጻዊ ታደለ በቀለ (ከሥራዎቹ በጥቂቱ፦ “አላስቀየምኳትም”፣ “ዉብ ዓይናማ” /ከሒሩት በቀለ ጋር/፣ “ሸንኮርዬ” /ከወይንሸት ሙሉነህ ጋር/)፣
- ከ1970ዎቹ እና 80ዎቹ የወጣትነት ዘመናቸው እስከ ዛሬ ዝናቸው እንደተጠበቀ እዚህ የደረሱት ድምጻውያኑ ንዋይ ደበበ (ከብዙ ሥራዎቹ በጥቂቱ፦ “የፍቅር ገዳም”፣ “አልዋሽም”፣ “ብትከዳኝ ታዘብኳት”፣ “ማዕበል ነው”፣ “ሸጊት ከሐረር፣ ሸጋው ከሐረር” /ከሀመልማል አባተ ጋር/) እና ጸጋዬ እሸቱ (ከብዙ ሥራዎቹ በጥቂቱ፦ “ሰንደቅ ዓላማ”፣ “ያይኔ አበባ”፣ “አላስገድድሽም”፣ “አንቺ ቅናተኛ”፣ “እናት ወደር የላት”፣ “ለሰርጓ ተጠራሁ”)፣
- ከ1990ዎቹ አይረሴ አልበሞቹ ጀምሮ እስከ ዛሬ ተወዳጅ የኾነው ድምጻዊ ኃይልዬ ታደሰ (ከብዙ ሥራዎቹ በጥቂቱ፦ “ሁሌ ሁሌ”፣ “እንደአፍሽ ያድርገው”፣ “እሷን ብቻ”፣ “በዘመኔ”፣ “ልትሄድ ነው”፣ “ይሞታል ወይ”)፣
- የሙዚቃ ልኬት በልዩ አጨዋወት እና ድንቅ ብቃት የታየበት እንዲሁም ብዙዎች ለመስማት የጓጉለት ሠርፀ ፍሬስብሐት (በኢትዮጵያን አይድል [Ethiopian Idol] ውድድር ላይ እጅግ ላቀ ባለ የዳኝነት ሙያው አንቱታን ያተረፈ)፣
- ከወጣቶቹ፣ ከዘመነኞቹ ከወደፊት የሙዚቃ ተስፋዎቹ ከሚካኤል ለማ ደምሰው፣ ከየማርያም ቸርነት (የሚ)፣ ከማኅሌት ነጋሽ ፣ ከማስተዋል ዕያዩ እና ከይድነቃቸው ገለታ ጋር በአንድነት “ቅኔ ነው ሀገር” የተሰኘ ድንቅ ኅብረ ዝማሬ አቅርበዋል።
ድርሰት፣ ቀረፃ፣ ቅንብር፣ ፕሮዳክሽን እና ዳይሬክቲንግ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህሩ በወጣቱ ድንቅ ሙዚቀኛ በኢዩኤል መንግሥቱ ውብ ሆኖ ተሰናድቷል።
የሙዚቃው የድምጽ ውኅደት በታላቁ ሙዚቀኛ በአበጋሱ ክብረወርቅ ሺዎታ ተከውኗል።
በሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችነት፥ ዶ/ር ዕዝራ አባተ፣ ረ/ፕ ኃይሉ ዓለማየሁ፣ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሰላማዊት አራጋው፣ ታዋቂው ሳክስፎኒስት አክሊሉ ወልደ ዮሐንስ (ጆኒ)፣ ኤፍሬም ውብሸት፣ ዳዊት ፍሬው ኃይሉ፣ ኢዩኤል መንግሥቱ፣ ለታሪክ ጥላሁን ፣ ሚሊዮን አብርሀም፣ ቴዎድሮስ አበራ፣ ዳዊት ቦስኮ እና ሌሎች በርካታ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች በሥራው ላይ ግሩም አጨዋወት ተሳትፈዋል።
ሀገር ሰምና ወርቅ ያላት ቅኔ ናት። የቅኔዋን “ወርቅ” የምናገኘው፣ “ሰው በሌለበት ሰው ሆነን ስንገኝ ነው፤” ሰውነት፣ ሀገር መውደድ፣ ሰው ሆኖ መገኘት… የዘመናችን እና የወቅቱ ትልቅ “የመሆን አለመሆን” (to be or not to be) ‘ሐምሌታዊ’ (ሼክስፒሪያን) ጥያቄ ስለመሆኑ ኅብረ ዝማሬው ይነግረናል።
ይህን ምርጥ የትብብር ውጤት የሆነውን ሙዚቃ ለማድመጥ/ ለመመልከት (ምነው ሸዋ ቲዩብ) እዚህ ጋር ይጫኑ።
ሠርፀ ፍሬስብሐት እንደጻፈው
በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በተካሄደው የሰላም ንቅናቄ ላይ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ እና በተለያዩ ሙያዎች ላይ የተሰማሩ የአገራችን ታዋቂ ሰዎች ስለ ሰላም እና በሰላም እጦት ምክንያት የሚከሰቱ አስከፊ ጉዳቶች ለታዳሚው አቅርበዋል።
ወልቂጤ (ሰሞነኛ)– “ጥበብ ለሰላም” በሚል መሪ ቃል በጉራጌ ዞን ከሚገኙ 17 ወረዳዎችና ከ4 ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የአገራችን ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ አመራሮች፣ የሲቪል ሰርቪስ (civil service) ሠራተኞች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ትልቅ ስብሰባ/ውይይት በድምቀት ተካሂዷል።
በዚህም ዞን አቀፍ የሰላም ንቅናቄ የአገራችን ታዋቂ ሰዎች (በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል ደራሲና መምህር ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ ደራሲ እንዳላጌታ ከበደ፣ ደራሲ ህይወት ተፈራ፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራልና የሙዚቃ ሀያሲው አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት እና ደራሲ ተስፋዬ ጎይቴ ስለ ሰላም እና በሰላም እጦት ምክንያት የሚከሰቱ አስከፊ ጉዳቶች ለታዳሚው አቅርበዋል። የሁሉም የመቋጫ ሀሳብ የአገራችን ህዝቦች አጥር ሳይገድባቸው በብሔር፣ በዘር፣ በጎሳ፣ በሀይማኖትና በመሳሰሉ ከፋፋይ ጉዳዮችን ትተው በአንድነትና በሰብዓዊነት ስሜት ተዋደውና ተቻችለው እንደቀድሞው አብረው ሊኖሩ እንደሚገባ ነው።
በዚህ ታላቅ የሰላም ንቅናቄ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማልና የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ወ/ሮ መሠረት አመርጋ ሰላም ለሁሉም ጉዳዮች መሠረት መሆኑ እና ሰላም በሌለበት ምንም ሊኖር እንዳማይችል ገልፀው የዞኑ ህዝብ በሙሉ ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል።
“ጥበብ ለሰላም” በሚል በተካሄድው በዚህ መርሀግብር ታዋቂ የአገራችን ደራሲያን፣ የጉራጌ ዞን የባህል ኪነት ቡድን፣ ከወልቂጤና ከቡታጅራ ከተማ አስተዳደሮች የኪነ ጥበብ ክበባት የተውጣጡ አማተር ኪያንያን ድንቅ የሙዚቃ፣ ድራማና የሥነ ግጥም ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል። እንዲሁም በሱዑዱ አብደላ የተሳሉ ድንቅ የሥነ ስዕል ሥራዎቹን አቅርቧል። የ11ኛ ክፍል ተማሪ ይዘዲን የፈጠራ ሥራዎች በመድረኩ ከቀረቡ ሥራዎች ይገኝበታል።
በመጨረሻም ለፕሮግራሙ መሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት የዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ያዘጋጃቸው ባህላዊ ስጦታዎች፣ የማበረታቻ ሽልማትና የምስጋና የምስክር ወረቀት አበርክቷል።
ምንጭ፦ የጉራጌ ዞን አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- ሚዛናዊነት ከራስ ቢጀምር ― ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)
- መርፌ ጨርቅ እንጂ አለት አይበሳም ― ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የምክር ደብዳቤ
- አጣየ፣ ካራቆሬ፣ ማጀቴ እና አካባው በሚኖሩ ዜጎች ላይ የታጠቁ ኃይሎች እያደረሱት ያለው ኢ-ሰብአዊ በደል
- ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ በሙዚቃ ሥራ ምርምርና ጥናት ውስጥ ቀዳሚ ኢትዮጵያዊ ናቸው ― አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት
- ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ መንግስት ስለጀመረው ለውጥ እና የሚታዩትን ጉድለቶች አብሮ በመሆን ስለመሙላት (በወልቂጤ ከተማ)
ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከተከፈተበት ከ1959 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋሙንም በመምራት እንዲሁም ታላላቅ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሙዚቃ ዕድገት አስተዋፅዖው የጎላ መሆኑን ለተሳታፊዎች አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት አውስቷል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)–በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥር ያለው የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ-ጥበባት ማዕከል 40ኛ የጥበብ ውሎ መድረኩን ቅዳሜ ኅዳር 8 ቀን 2011 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ አካሒዷል።
በዝግጅቱ ላይ የዕውቁ ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ሰው የፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ሕይወትና ሥራዎች ላይ ውይይት እየተደረገ ተደርጓል። ሥራዎቹን እና ሕይወቱን አስመልክቶ የሙዚቃ ባለሙያ እና በቅርቡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ሆኖ የተሾመው አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት የውይይት መነሻ ጥናት አቅርቦ በታዳሚዎች ውይይት ተካሂዶ ነበር።
“ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ <ባለዋሽንቱ እረኛ>(The Shepherd Flutist) በተሰኘ ታላቂ ሥራ የኢትዮጵያን መልክ በረቂቅ ሙዚቃ ያሳዩ ናቸው” በማለት አቶ ሠርፀ የገለጿቸው የሙዚቃውን ረቂቅነት በመጥቀስ ሲሆን፤ ፕሮፌሰር አሸናፊ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከተከፈተበት ከ1959 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋሙንም በመምራት እንዲሁም ታላላቅ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሙዚቃ ዕድገት አስተዋፅዖው የጎላ መሆኑን ለተሳታፊዎች አውስቷል።
በሙዚቃ ላይ ከሠሯቸው ከበርካታ የምርምር ሥራዎቻቸው ውስጥ “Roots of Black Music” የተሰኘው መጽሐፋቸው በብዙ የዓለማችን የሙዚቃ አጥኚዎች የተዘነጉ (የተዘለሉ) የአፍሪካ/የምሥራቁ ዓለምን የሙዚቃ ስልትና ፍልስፍናን አጉልተው ለተቀረው ዓለም ያሳዩበት እንደሆነም አቅራቢው አብራርተዋል።
በውይይቱም ከተሳታፊዎች የኢትዮጵያ ሙዚቃ በዘመናት መካከል የመድመቅና መልሶ የመደብዘዝ ችግር ከምን የመነጨ እንደሆነ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፥ “ዋናው ችግር በተለያዩ ምክንያቶች የኢትዮጵያ ሙዚቃ ተቋም ፈርሷል፤ እሱን መልሶ መገንባት የቤት ሥራችን ነው” ብለዋል አቶ ሠርፀ። አክለውም የኢትዮጵያ የሙዚቃ ትምህርት ሥርዓት ከተመሠረተበት ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከምዕራባውያን የሙዚቃ ሥርዓተ-ትምህርት ነፃ መውጣት ያለመቻሉም ሌላ ምክንያት እንደሆነ አቅራቢው ጠቅሰዋል።
ውይቱን የመሩት የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ እንዳለጌታ ከበደ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ማደግ ብርቱ ጥረት ያደረጉ የጥበብ ሰዎችን ፈለግ እና ሥራዎቻቸውን ለተተኪው ትውልድ ለማውረስ በሁሉም አካላት ጥረት መደረግ አለበት ብለዋል።
ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ አዲስ አበባ ግንቦት 8 ቀን 1930 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወለዱ። አባታቸው ግራዝማች ከበደ አድነው፣ እናታቸው ደግሞ ወ/ሮ ፋንታዬ ነከሬ ያባሉ ነበር። የሙዚቃ ፍቅርን ገና በልጅነታቸው ያሳደሩባቸው እናታቸው ቢሆኑም ታዳጊው አሸናፊ ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳሉ እናታቸውን በሞት አጥተዋል።
ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ መሠረታዊ ትምህርታቸውን በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት እና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (አሁን ኮከበ ጽባሕ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የሚባለው) ካጠናቀቁ በኋላ ከሐረር የመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጅ ተመርቀዋል። ከዚያም ወደ አሜሪካ በማቅናት ኒው ዮርክ ክፍለ-ሀገር ከሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሮቸስተር፣ ኢስትማን የሙዚቃ ትምህርት ቤት (University of Rochester’s Eastman School of Music) በ1954 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ ከተመረቁ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለሰ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትን መሥርተዋል። የትምህርት ቤቱም የመጀመሪያው ዳይሬክተር ከመሆናቸውም ባሻገር በመሆን ሙዚቃን ከማስተማሩ ባሻገር አገልግለዋል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወ.ወ.ክ.ማ.)፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የበጎ አድራጎት ድርጅት መርሓ-ዕውራን ትምህርት ቤት እና በመሳሰሉ የወጣቶች ማኅበራት እየተገኙ የሙዚቃ ትምህርት ይሰጡ ነበር።
በድጋሚ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ ተመልሰው፣ ኮነቲከት ክፍለ-ሀገር ከሚገኘው ዌስልያን ዩኒቨርሲቲ (Wesleyan University) በ1961 ዓ.ም የማስትሬት፣ እንዲሁም በ1963 ዓ.ም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ምዕራባዊ ባልሆኑ ሙዚቃዎች ምርምር (ethnomusicology) አግኝተዋል።
ከሙዚቃው መምህርነትና ተመራማሪነት ባሻገር ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ደራሲም ነበሩ። እ.ኤ.አ በ1964 ዓ.ም ኮንፌሽን (Confession)፣ እ.ኤ.አ በ1982 ዓ.ም ሩትስ ኦፍ ብላክ ሙዚክ (Roots of Black Music) የሚሉ መጻሕፍትን ያሳተሙ ሲሆን፣ በሙዚቃ ላይ ያተኮሩ በርካታ ጽሁፎችን፥ በተለይም ደግሞ በአፍሪካ-አሜሪካውያን ባህልና አኗኗር ላይ ለሚያተኩረው “The Chronicler” ለተሰኘው መጽሔት ጽፈዋል።
በአሜሪካ ፕሮፌሰር አሸናፊ ኑሯቸው ፍሎሪዳ ክፍለ ሀገር በሚገኘው ፍሎሪዳ ስቴት ዩኒቨርሲቲ (Florida State University) የሙዚቃ ኮሌጅ ውስጥ በመምህርነት የሠራ ሲሆን፣ ተቀማጭነቱን እዚያው አሜሪካ ያደረገውናታዋቂውን የኢትዮጵያ ምርምር ካውንስልን (Ethiopian Research Council) በዳይረክተርነት መርቷል።
ፕሮፌሰር አሸናፊ ከመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ባለቤታቸው (ወ/ሮ እሌኒ ገብረመስቀል) እና ሁለተኛ ባለቤታቸው (አሜሪካዊ) አራት ልጆችን (ሦስት ሴቶችና አንድ ወንድ) ልጆችን አፍርተዋል። ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ የ60ኛ የልደት በዓላቸው ዕለት በመኖሪያ ቤታቸው ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ሞተው የተገኙ ሲሆን፤ ምናልባትም የራሳቸውን ሕይወት ሳያጠፉ እንዳልቀሩ ብዙዎች ይገምታሉ።
PHOTO: Ethiopian Academy of Sciences
Search Results for 'ሠርፀ ፍሬስብሐት'
Viewing 3 results - 1 through 3 (of 3 total)
Viewing 3 results - 1 through 3 (of 3 total)