Search Results for 'አረጋ ይርዳው'

Home Forums Search Search Results for 'አረጋ ይርዳው'

Viewing 3 results - 1 through 3 (of 3 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች አባል ኩዊንስ ሱፐርማርኬት እጅግ ዘመናዊ የሆነውን የቀራኒዮ ፕላዛ ቅርንጫፍ ሱፐርማርኬቱን አስፈላጊዎቹን ሕጋዊ መስፈርቶች አሟልቶ በማደራጀት ማክሰኞ ሐምሌ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ሁሉን በአንድ ባቀፈውና ማራኪ በሆነው በኮልፌ ቀራኒዮ ፕላዛ ቅጥር ጊቢው አስመረቀ።

    በዚሁ የምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ባደረጉት ንግግር፤ በዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ደንቦችን መሠረት ባደረገ ዲዛይን የተሠራው፤ ኩዊንስ ሱፐርማርኬት አካሄዱም ለደምበኞች ቀላልና ምቹ የግብይት ሁኔታ ለማስፈን ትኩረት የሠጠ ነው ብለዋል።

    ሱፐርማርኬቱ በሚገኝበት በቀራንዮ ፕላዛ፣ የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚ፣ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የነዳጅ ጣቢያ/ማደያና የተሽከርካሪ እጥበትና መለስተኛ ጥገና አገልግሎት መስጫ እና በትንሹ ከ150 በላይ መኪኖች ማቆሚያ፣ የእርሻ ምርቶች መሸጫ፣ ካፌና ሱቅ፣ ባንክ፣ እና ሁለገብ አዳራሽ መኖሩን የገለጹት ዶ/ር አረጋ፥ እነዚህ በአንድ አካባቢ መደራጀታቸው ደንበኞቹን በአንድ የንግድ ማዕከል በርካታ አገልግሎቶች እንዲያገኙ የሚያስችል በመሆኑ፣ሱፐርማርኬቱን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

    ለኩዊንስ ኩባንያ መቋቋምና በዚህ ደረጃ መስፋፋት ምክንያት ለሆኑት ለሚድሮክ ኢትዮጵያ ሊቀ-መንበርና ባለሀብት ለሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ በቅድሚያ ምስጋና ያቀረቡት ዶ/ር አረጋ፥ በዛሬው ቀን በመካከላችን ለተገኙት ወንድማቸው ለሼህ አብደላ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል።

    እንዲሁም፣ የቀራኒዮ ቅርንጫፍ ፕሮጀክት በዚህ ለገበያ አመቺ በሆነ ቦታ እንዲገነባ ለረዱን የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አመራሮች እና የሚመለከታቸው ሠራተኞች፣ በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች፣ መብራት ኃይል፣ የቴሌፎንና የውሃ ተቋማት፣ የአዲስ አበባ የመንገድ ሥራዎች ተቋም፣ የአካባቢው የፖሊስ እና የፀጥታ ኃላፊዎች እና ሌሎችም ላደረጉልን መተባበር ከፍተኛ ምስጋና አቅርባለሁ ብለዋል።

    ዶ/ር አረጋ በዚሁ ንግግራቸው፥ የኩዊንስ ቀራኒዮ ቅርንጫፍ ፕሮጀክት ለቅድመ መደበኛ አገልግሎት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ፣ ለሥራ ማስኬጃ እና ለሽያጭ የሚያገለግሉ ዕቃዎች (መደርደሪያዎች፣ ማቀዝቀዣዎች፣…) ግዢ፣ የሲስተም ዝርጋታ ወጪን ጨምሮ፣ ለሸቀጣ ሸቀጥ አቅርቦት ጠቅላላ ወጪ 59.3 ሚሊዮን ብር መሆኑን አስረድተው፤ ሕንፃው በ37.7 ሚሊዮን ብር ወጪ መገንባቱንና የኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ ንብረት በመሆኑ፣ ኩዊንስ በኪራይ እንደሚገለገልበት አስታውቀዋል።

    የሪቴል ግሩፕ ፕሪንሰፓል ኦፕሬሽን ኦፊሰር ወ/ሮ ታህሳሥ ወንድምነህ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር ኩዊንስ ሱፐርማርኬት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኀበር ሰኔ 25 ቀን 2002 ዓ.ም. 46 ቋሚ እና 5 ኮንትራት፣ በድምሩ 51 ሠራተኞች በመያዝ የተቋቋመ መሆኑን አስታውሰው፥ ኩባንያው የአግሮ ኢንዱስትሪ ውጤቶችን (የዶሮ፣ የወተት እና የሥጋ ተዋጽዖዎችን)፣ የእርሻ ምርቶችን (ሰብሎች፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ እና አበባዎች)፣ የባሕር ምግቦች (ዓሣ)፣ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች (ሣሙና….) የታሸጉ ምርቶች፣ መጠጦች እና ሌሎች የፋብሪካ ውጤቶችን (የጽሕፈት መሣሪያዎችን፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን እና የቤት ውስጥ የመገልገያ ዕቃዎች) በችርቻሮ እና በጅምላ በመሸጥ እና በማከፋፈል ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

    ወ/ሮ ታህሳሥ በዚሁ ንግግራቸው፤ ኩባንያው በአሁኑ ጊዜ የካፒታል መጠኑ ወደ ብር 23,786,000፣ የሠራተኞቹ ብዛት ወደ 142 (132 ቋሚ እና 10 ኮንትራት) ማደጉን አመልክተው፤ ዓመታዊ ሽያጩም ሥራ ሲጀምር ከነበረው ከብር 12,192,000 ወደ ብር 157,000,000 ማደጉን አሰታውቀዋል።

    አያይዘውም ኩባንያው ቅርንጫፎቹን ወደ ሰባት በማሳደግ ጥራት ያላቸውን ምርቶች በበቂ ሁኔታ በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ እና ተጨማሪም አንድ የዳቦ ማምረቻና መሸጫ በመቻሬ ቅርንጫፍ በማቋቋም ለሠራተኞችና ለኀብረተሰቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን አስረድተው፤ ሱፐርማርኬቱ ለ50 ተጨማሪ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንና ዓመታዊ ሽያጩም ብር 75,000,000 እንደሚሆን፤ የኩባንያውን ዓመታዊ የሽያጭ መጠንንም በግማሽ በማሳደግ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ አሰታውቀዋል።

    ወ/ሮ ታህሳሥ ለኩዊንስ ኩባንያ መቋቋምና በዚህ ደረጃ መስፋፋት ምክንያት ለሆኑት ለሚድሮክ ኢትዮጵያ ሊቀመንበርና ባለሀብት ለክብር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ፣እንዲሁም፣ የቀራኒዮ ቅርንጫፍ ፕሮጀክት በዚህ ለገበያ አመቺ በሆነ ቦታ እንዲገነባ የፕሮጀክት ሀሳብ በማቅረብ፣ አስፈላጊውን በጀት በመመደብ፣ በፕሮጀክቱ ሂደትም ያልተቋረጠ የዕለት ተዕለት ክትትል በማድረግ፣ የቅርብ አመራር በመስጠት እና አቅጣጫ በማስያዝ ፕሮጀክቱ በአጥጋቢ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ላበቁት ለዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር እና ፕሬዚዳንት፤ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

    በዚሁ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለፕሮጅክቱ መሳካት አሰተዋጽኦ ያበረከቱ ድርጅቶችና ግለሰቦች፤ የተዘጋጀላቸውን ሠርቲፊኬት ከዕለቱ የክብር እንግዳ ከሼህ አብደላ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ እጅ ተቀብለዋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ፤ የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ ተወካይና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ አመራሮች፣ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና ደንበኞች በተገኙበት ተካሂዷል።

    ምንጭ፦ ሚድሮክ ኢትዮጵያ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 

    ኩዊንስ ሱፐርማርኬት


    Anonymous
    Inactive

    ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በቡራዩ ካምፓስ በአካውንቲንግና ፋይናንስ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በካምፓሱ ለመጀመሪያ ጊዜ አስመረቀ
    —–

    ቡራዩ (ሰሞነኛ)– ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ.ም, ለመጀመሪያ ጊዜ በቡራዩ ገፈርሳ ካምፓስ በአካውንቲንግና ፋይናንስ በመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በቅድመ መደበኛ ትምህርት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሕጻናትን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አረጋ ይርዳውና የሴኔት አባላት እንዲሁም የቡራዩ ከተማ ከንቲባ ተወካይ አቶ ተረፈ ንጋቱ በክብር እንግድነት በተገኙበት አስመርቋል።
    ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት በ36ኛው ዙር በተለያዪ ካምፓሶች ከ1500 በላይ ተማሪዎችን ያስመርቃል። በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ገፈርሳ ካምፓስ ለመጀመሪያ ጊዜ 18 ተማሪዎችን በዲግሪ እና በመዋዕለ ሕፃናት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎችን አስመርቋል። በዕለቱ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የተጀመረው በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙሮች እና በአካባቢው አባ ገዳዎች ምርቃት ነው።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የቡራዩ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ተፈራ ንጋቱ ባደረጉት ገለጻ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በገፈርሳ ካምፓሱ ከተማሪ ብዛት ይልቅ የትምህርት ጥራት ላይ አተኩሮ በመንቀሳቀሱ ሊመሰገን እንደሚገባው ጠቅሰው የዛሬ ተመራቂዎች ዛሬ ተመርቃችሁ የጨረሳችሁ ሳይሆን ወደ ሌላ ምዕራፍ የሚያሸጋግራችሁ በመሆኑ በርቱ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

    ዩኒቨርሲቲው በገፈርሳ ካምፓሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሄደው በዚሁ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተገለጸው፤ ካምፓሱ ስፋት ባለው ቦታ ላይ የተመሰረተና በአካውንቲንግና ፋይናንስ፣ በማኔጅመንት፣ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት፣ በአኒማል ፕሮዳክሽን ቴክኖሎጂ እና በሆርቲካልቸር በመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት በመስጠት ላይ ይገኛል።

    በሌላ በኩል ዩኒቲ አካዳሚ ቡራዩ ካምፓስ በመጪው ዓመት መደበኛ እስከ 8ኛ ክፍል አካዳሚውን በማስፋፋት የቡራዩ ሕብረተሰብ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ የማስፋፋት ሥራ እየሰራ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

    በዚህ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተመራቂ ወላጆች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። በዕለቱ የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አረጋ ይርዳው በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የሜዳሊያና የፕሬዚዳንቱን ዋንጫ ሸልመዋል።

    ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ውጭ በደሴና በአዳማ የስልጠና መስኮችን በመለየት የተለያዩ ፕሮግራሞችን ለሕብረተሰቡ በመስጠት ላይ ይገኛል።

    ምንጭ፦ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ ለትምህርትና ጤና አገልግሎት የሚውል ከ452 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረገ። የጃፓን መንግስት አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲው በኩል ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ አራት ፕሮጀክቶችን ለመገንባትና ለማስፋፋት ያስችላል።

    በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ (Daisuke Matsunaga) የፕሮጀክት ግንባታና ማስፋፊያ ከሚደረግላቸው ትምህርት ቤቶች ኃላፊዎች ጋር የድጋፍ ስምምነት ተፈራርመዋል።

    ፕሮጀክቶቹ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን የጉንችሬ እና እነሞር ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታና በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የሀሮ ሾጤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ናቸው።

    በተጨማሪም ለሻሻመኔ ከተማ የአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች የምግባረ ሰናይ መጠለያ ግንባታና ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የዩሮሎጂ እና ድንገተኛ ክፍል የህክምና መሣሪያዎች ግዥ የሚውል ነው።

    እነዚህ አራት የትምህርት እና የጤና ፕሮጀክቶች ከአራት ሺህ በላይ ህዝብ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።

    አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ እንዳሉት አገራቸው ለኢትዮጵያ ልማት ተሳትፎ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች። ጃፓን በኢትዮጵያ እ.አ.አ ከ1989 ጀምሮ በተለያዩ ክልሎች ከ400 በላይ ፕሮጀክቶችን በመሥራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገች ነው።

    በትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ በኢኮኖሚ ልማትና ሌሎችም መስኮች ድጋፍ ስታደርግም ቆይታለች።

    በስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽነር እርስቱ ይርዳው የተደረገው ድጋፍ የዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል የትምህርት ፍላጎት ለማሟላት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

    ድጋፉ በተለይም ትምህርት ቤት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች መሆኑ የትምህርት ሽፋንን በማስፋት የመንግስትን ጥረት እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡

    ከዚህ ጋር በተያያዘ የጃፓን ኤምባሲ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኘውን የራስ መኰንን አዳራሽ ለማደስ የ85 ሺሕ 679 ዶላር (2,403,500 ብር) ዕርዳታ መለገሱን ሪፖርተር ጋዜጣ በእሁድ ታህሳስ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. እትሙ ዘግቧል።

    አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ እና የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር አህመድ ሐሰን (ዶ/ር) የእርዳታ ስምምነቱን የተፈራረሙ ሲሆን፣ ገንዘቡም የራስ መኰንን አዳራሽ ባህላዊና ታሪካዊ ዳራው ሳይጠፋ ለማደስ፣ የተበላሹ ክፍሎችን ለመጠገን፣ ውስጣዊ ክፍሉን ለማደስ እና አዳዲስ ቁሳቁስ ለማስገባት መሆኑ ታውቋል።

    የጃፓን መንግስት ትምህርታዊ ድጋፍ ከማድረጉም በተጨማሪ የራስ መኰንን አዳራሽን ለማደስ መነሳቱ፣ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ኢትኖሎጂካል ሙዚየም በርካታ ጎብኚዎች እንዲስብ ያስችላል ተብሏል።

    በሙዚየሙ ከአሥር ሺሕ በላይ የኢትዮጵያ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች የሚገለጹባቸው አልባሳትና ቁሳቁሶች አሉ፤ ይህም በአፍሪካ አንዱ ታዋቂ ሙዚየም እንዲሆን አስችሏል።

    በቀድሞው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ሕንፃ ውስጥ የሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ ከ50 ዓመታት በላይ ዕድሜው በስሩ ያቀፋቸው ቤተ-መጻሕፍት፣ የኢትኖግራፊክ ሙዚየም የምርምርና የጥናት ማዕከልን ነው። በውስጡም መጻሕፍት፣ ታሪካዊ ሰነዶችና መዛግብት፣ የዳግማዊ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱን ጨምሮ የድምፅና የምስል ቅጂዎች፣ ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ የጥናት ድርሳኖች፣ ጆርናሎች፣ ረጅም ዕድሜን ያስቆጠሩ የብራና መጻሕፍትንም ይዟል።

    እንዲሁም እስከ 20 ሺሕ የሚደርሱ የኅትመት ክምችቶች ከቅድመ ምረቃ እስከ ድኅረ ምረቃ ተማሪዎች፣ ለተመራማሪዎች ጥናትና ምርምር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

    የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2010 ዓ.ም. መስከረም ወር ከጃፓኑ ኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ ጋር ትምህርታዊ ልውውጥና የጥናት ትብብር ለማድረግ የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙ ይታወሳል።

    ምንጭ፦ ኢዜአ እና ሪፖርተር ጋዜጣ

    የጃፓን መንግስት

Viewing 3 results - 1 through 3 (of 3 total)