-
Search Results
-
Topic: ብሔራዊ የስፖርት ምክር ቤት በድጋሚ ተመሠረተ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የአገሪቱን ስፖርት በበላይነት እንዲመራ፣ እንዲከታተልና እንዲደግፍ የፌዴራል መንግሥት የአስፈጻሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1097/2011 እንዲሁም የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽንን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር አንቀጽ 9 መሠረት ብሔራዊ የስፖርት ምክር ቤት እንደገና ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
በዚህም ህብረተሰቡ በስፖርት ተጠቃሚ እንዲሆንና በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ባህሉ የዳበረና ሁለንተናዊ ስብዕናው የተሟላ ዜጋ እንዲሆን በሚደረገው ርብርብ የዘርፉን የባለድርሻ አካላት ሚናና ድርሻ ማሳደግ ዓላማ ያደረገና በቀጣይ የሀገሪቱ የስፖርት ልማት ዘርፍ ትልቅ ኃላፊነት የተሰጠው ብሔራዊ የስፖርት ምክር ቤት መሥራች ጉባኤ ህዳር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ሆቴል ተካሂዷል።
ይህ ብሔራዊ የስፖርት ምክር ቤት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን ሰብሳቢነትና የበላይ ጠባቂነት የሚመራ ሲሆን፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው በምክትል ሰብሳቢነት ይመሩታል። ይህም በስፖርት ልማት ዘርፍ በበላይነት በመምራት ተቀራርቦና ተቀናጅቶ ለመሥራት የሚያግዝና የስፖርት ልማት ዘርፉ የተሻለ አሠራርና አደረጃጀት ኖሮት ህብረተሰቡ ከስፖርት ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል።
በመሥራች ጉባኤው መክፈቻ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ክቡር አቶ ኤልያስ ሽኩር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። እንዲሁም ክብርት ዶ/ር ሂሩት ካሳው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ያስተላለፉት መልዕክት ይህ በእንደገና የተመሠረተው ብሔራዊ ምክር ቤት ለሀገሪቱ ስፖርት ልማት ዘርፍ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ላይ ታላቅ ኃላፊነት የተሰጠው ነው በማለት ጥልቅ ሀሳቦችን በማስቀመጥ አስገንዝበዋል።
እንዲሁም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን በዳግም ለተመሠረተው ምክር ቤት የሥራ መመሪያና ቀጣይ አቅጣጫ ያስቀመጡ ሲሆን፣ የስፖርት ኢንዱስትሪው በቃላት ሊነገር በማይችለው በላይ የሕዝባችንን ፍላጎትና ጥያቄ መመለስ ያለበት ነው። በመሆኑም የስፖርት ዘርፉ በሰው ኃይልና በቁሳቁስ እንዲጠናከር፣ ተወዳዳሪና ብቁ ስፖርተኞች በማፍራት በመዝናኛ ስፖርትነት፣ ለአብሮነትና ሀገርና ሕዝብ ታላቅነት ያስጠበቀ እንዲሆን በተወዳዳሪነትና ዓለም-አቀፍ ተሳታፊነት እንዲኖረን በተሻለ አደረጃጀትና አመራር የማጠናከር አቅም የማኖር ተግባር ከስፖርት ምክር ቤቱ የሚጠበቅ ነው ብለዋል።
በዕለቱ ለውይይት የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፎች ርዕስ በኢትዮጵያ የስፖርት አመጣጥና አጀማመር እንዲሁም ሀገር-አቀፍ የስፖርት ሪፎርም ፕሮግራም በተከበሩ በአቶ ሀብታሙ ሲሳይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ናቸው። በተሰጣቸው ሰዓት ገለፃና ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጓል።
በመሥራች ጉባኤው ላይ ከብሔራዊ ክልል ፕሬዝዳንቶች፣ ከከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ ከብሔራዊ ክልል የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነሮች፣ የስፖርት ፌዴሬሽኖች ፕሬዝዳንቶችና የጽሕፈት ቤት ኃፊዎች እንዲሁም የስፖርቱ ደጋፊና አፍቃሪ ቤተሰቦች መሳተፋቸው ታውቋል።
ምንጭ፦ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃሕፍት ኤጀንሲ፣ ከትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት “ግዕዝ እና ሥነ-ፈውስ” በሚል ቃል የተዘጋጀው 5ኛው ሀገር አቀፍ የግዕዝ ጉባዔ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አዲሐቂ ካምፓስ ሲካሄድ ቆይቶ ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ሰኔ 2 ቀን 2011ዓ.ም. ተጠናቋል።
በጉባዔው መክፈቻው ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ክብርት ወ/ሮ ብዙነሽ መሠረት የባህል ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ያስተላለፉት መልዕክት “አገራችን ከ80 በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባት ብዝሃ-ባህል ያለን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሀገር መሆናችን እንደአፍሪካ አህጉር መልካም አጋጣሚዎች ቢኖረንም ያሉንን ባህላዊ እሴቶችና ሀገር በቀል ዕውቀቶችን አስተዋውቀን በሚገባ አልተጠቀምንባቸውም። የራሳችን የሆነ ፊደልና የግዕዝ ቋንቋ ያለን ሲሆን፣ እነዚህ ልዩ ጥበቃና እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው በጥናትና ምርምር እየተደገፈ በመሰነድ ለትውልድ ማስተላለፍ የሁላችን ኃላፊነት ሆኖ ይገኛል ካሉ በኋላ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ላለፉት አራት ዓመታት ተመሳሳይ የጥናትና ምርምር መድረኮች የተካሄዱበት አግባብና ውጤታማነት ሲገመግም ጉባዔዎች በተባባሪ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ በጋራ የሚካሄዱ መሆናቸው እንደ ጥሩ ጅምር የሚወሰድ ነው ብለዋል።
አክለው ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ጉባዔያቱ በቋንቋው ጥናት ዙሪያ ያሉ ጠቃሚ ልምዶች፣ በቋንቋው ጥናት አስፈላጊነት በቂ ግንዛቤ ያገኘንባቸው ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። የዘንድሮው የመቀሌ ጉባዔ ለየት የሚያደርገው ከግዕዝ ወጣ ብሎ በሥነ-ፈውስ ላይ ትኩረት ማድረጉ ጭምር መሆኑ ነው። የግእዝ ቋንቋ በሥነ-ፈውስ ደረጃ ምን ይላል የሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጥባቸው፣ አቅጣጫና መፍትሄ የሚቀርብባቸው ጥናታዊ ጽሑፎች በጉባዔው የሁለት ቀን ውሎ ይቀርባሉ ተብሎ ታሳቢ ተደርጓል።ሥነ-ፈውስ ኅሊናዊ፣ ሥነ-ፈውስ ሥጋዊ፣ ሥነ-ፈውስ መድኃኒታዊ፣ ሥነ-ፈውስ መንፈሳዊ፣ እያልን ብዙ ነጥቦችን ማንሣት እንችላለን። ሰው በጎ አስተሳሰብ እንዲኖረው፣ ለአገር፣ ለወገን፣ እንዲኖር ጤናማና ያልተዛባ አእምሮ እንዲኖረው ያስፈልጋል። ሁሉን ጎጂ አድርጎ የሚመለከት አእምሮዊ ህልውናዊ እንደሚያስፈልገው አምናለሁ። በዚህ ጉባዔ የስነ-ፈውስ ደረጃ ምንድነው የሚለውን ጥያቄ መልስ የሚሰጡ አማራጮችን በስፋት መዳሰስና በጉባዔው ማጠቃለያም የተሳታፊዎች ንቁ ተሳትፎና ውይይት ለቋንቋው ልማት ለምናካሂደው ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ሊያግዙ የሚችሉ ምክረ-ሀሳቦች እንደሚመጡ ያለኝ ተስፋ ላቅ ያለ ነው በማለት መልዕክታቸውን በማስተላለፍ ጉባዔው በይፋ አስጀምረዋል።
5ኛው ሀገር አቀፍ የግዕዝ ጉባዔ በተያዘለት መርሃ-ግብሮች መሠረት በግእዝ ላይ የተደረጉ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎች ቀርበው ገለፃና ውይይት ተደርጎባቸዋል። እነዚህም ግዕዝና ሥነ-ፈውስ በመጋቤ ምስጢር ፍሬስብሃት ዱባሌ (ከኢ.ኦ.ተ. ቤተ ክርስቲያን)፣ ግዕዝና ለፈውስ የሚደረስ ጸሎት በዶ/ር አባ ዳንኤል አሰፋ (ከፍራንቺስኮ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ)፣ ግዕዝና የባህል መድሃኒት በመጋቤ ምስጢር ስማቸው ንጋቱ (ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ)፣ ዘይትረከቡ በውስጠ ልሳነ ግዕዝ ሕቡኣነ ስመ እግዚአብሔር ዘይህቡ ፈውሰ ድኅነት በአቶ ሃፍተ ንጉስ (ከአዲግራት ዩኒቨርሲቲ)፣ ግዕዝ (The General Features of the Geez Magical Texts) በአቶ ጉኡሽ ሰለሞን (ከአዲግራት ዩኒቨርሲቲ)፣ ጸበልና ማየ ጸሎት በግዕዝ ባህል ወፊዚክስ በዶ/ር ሀጎስ አብርሃ (ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ) ይገኙበታል።
ምንጭ፦ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ፊቼ ጫምባላላ በዩኔስኮ ከማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ ከተመዘገቡ ቅርሶቻችን ውስጥ አንዱ ነው። የፊቼ ጨምበላላ በዓል የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት በዓል መሆኑን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ ገልጸዋል።
ሀዋሳ (ሰሞነኛ) – የሲዳማ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል የሆነው ፊቼ ጫምባላላ በሀዋሳ ከተማ በድምቀት ተከብሯል። በበዓሉ ላይ ከተለያዩ ወረዳዎች የመጡ የሲዳማ አባቶች የቄጣላ ሥነ-ስርአት አድርገዋል።
በሀዋሳ ጉዱማሌ አደባባይ በልዩ ሁኔታ የተከበረው በዓል ላይ የሲዳማ ሴቶች በባህላዊ አለባበስ እና ባህላዊ የፀጉር አሰራር አሸብርቀው የበዓሉ ድምቀት ሆነዋል።
በበዓሉ ላይ ከተለያዩ ክልሎች የተጋበዙ ልዑካንም የተገኙ ሲሆን፥ ከደቡብ ክልልም ከተለያዩ ብሄረሰቦች የተውጣጡ ልዑካን ታዳሚዎች ሁነው ነበር።
የፊቼ ጫምባላላ በዓል በዩኔስኮ ከማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ ከተመዘገቡ ቅርሶቻችን ውስጥ አንዱ ነው። የፊቼ ጨምበላላ በዓል የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት በዓል መሆኑን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ ገልጸዋል።
በዓሉ በጋራና በድምቀት እንዲከበር ዋጋ ከፍለው በዓሉን እዚህ ላደረሱት አባቶች ምስጋና አቅርበዋል – አቶ ሚሊዮን። አክለም በዓሉ በይቅርታና በፍቅር የምናከብረው በዓል በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፍቅር እንዲያከብረውም ጥሪ አቅርበዋል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፥ ፊቼ ጫምበላላ የኛም ባህል በመሆኑ ለማድመቅ ሳይሆን ለማክበር ነው ወደ ሀዋሳ የመጣነው ሲሉ ገልጸዋል። ባህሉ ተጠብቆ የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲቆይ አባቶቻችን ታላቅ ሚና በመጫወታችሁ ምስጋና ይገባችሀል በማለትም ተናግረዋል።
አቶ ሽመልስ መልዕክታቸውን ከማጠቃለላቸው በፊት የሲዳማና የኦሮሞ ህዝብ አብሮ ብዙ መስዋዕትነትን የከፈለና ድል ያስመዘገበ ህዝብ ነው ሲሉም ገልጸዋል – አቶ ሽመልስ። እኩልነትን፣ ነፃነትንና ወንድማችነትን በማጠንከርና በማሳደግ የተገኘውን ድል ለማስቀጠል መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል። ልዩነታችንን ጠብቀን አንድ በሚያደርጉን ነገሮች ላይ በመሥራት ለበለጠ ድል መትጋት ይጠበቅብናል ብለዋል። በዚህም የሁለቱም ወገኖች የሆኑት ኤጀቶና ቄሮዎች ተባብረው ለክልሎቻቸውም ሆነ ለኢትዮጵያ እድገት መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው፥ ባህሉ ከትውልድ ትውልድ ተጠብቆ እንዲተላለፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ተገቢውን ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል። ከቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን የወረስናቸውን እንደ ፍቼ ጫምበላላ ያሉ ባህሎቻችንን ጠብቀንና ተንከባክበን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የፖለቲካ አክቲቪስትና የኦሮሚያ ሚድያ ኔትዎርክ (ኦ.ኤም.ኤን) ቴሌቭዥን ጣቢያ መሥራች የሆነው አቶ ጃዋር መሀመድ በበኩሉ፥ ፊቼ ጫምበላላ በዓልን ያለ አንዳች ችግር ማክበር መቻሉ እንደሚያስደስት ገልጿል። በዓሉ ቀደምት አባቶች በከፈሉት መስዋዕትነት እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ እየተከበረ ያለ ቅርስ መሆኑን ተናግሯል። በዓሉ እንዲህ እንዲከበር ኤጀቶና ቄሮዎች ለሰላም ያደረጉት ትግል ውጤት መሆኑንም ገልጿል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በአገራችን በሁሉም አቅጣጫ የተጠናከረ የመዳረሻ ልማት፣ የቅርስ ጥገናና እንክብካቤ ሥራዎችን በተቀናጀ መልኩ ለማከናውን እንዲያስችል በሙያው የተሠማሩ ከመሀንዲሶች እና የሥነ-ሕንፃ ባለሙያዎች ጋር ግንቦት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ በጌት ፋም ሆቴል ምክክር ተካሄደ።
በመክፈቻው ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ክብርት ዶ/ር ሂሩት ካሳው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ሲሆኑ፣ በመክፈቻ ንግ ግራቸውም የመርሐ ግብሩን ዓላማ “በኢትዮጵያ ሥነ-ሕንፃ ዲዛይን ጥበብ ከጥንት አባቶቻችን ዘመን ጀምሮ የነበረን ብሎም ዓለምን እስከ ዛሬ ድረስ የሚያስደምሙ ሕንፃ ጥበቦች አሁንም አሉን። እንደሚታወቀው በዓለም የሥነ-ሕንፃ ጥበብ ታሪክ የባቢሎናዊያን፣ የግሪኮች፣ የሮማውያን፣ የባይዛንታይን፣ የመካከለኛ ዘመን፣ የዘመናዊው (modern) ሥነ-ሕንፃ ብለን ማየት የምንችል ይሆናል። በኢትዮጵያ ሥነ-ሕንፃ ታሪክ ቅድመ አክሱም (የዳዓማት)፣ የአክሱማውያን ስልጣኔ፣ የዛጉዌ ስርወመንግስት ሥልጣኔ፣ የሰሎሞኒክ፣ የጎንደሮች ዘመን ሥልጣኔን ማውሳት ይቻላል። አንድ ሥነ-ሕንፃ ሲታነፅ በዋናነት የዚያን ዘመን ማኅበራዊ አደረጃጀት እና የተደረሰበትን አጠቃላይ የዕድገት ደረጃ ከማሳየቱም በላይ በየዘመኑ ያሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን ፍንትው አድርጎ የማሳየት ጥበብ አለው” ብለዋል።
ክብርት ሚኒስትሯ አክለውም “በሀገራችን የአርክቴክቱና የኢንጂነሩ የጥበብ አሻራዎች ለዚህ ላለንበት ዓለም እያበረክቱት ያለው ሙያዊ ድጋፍ ቀላል ግምት የሚሰጠው አለመሆኑንና በሀገር በቀል የሥነ-ሕንፃ ጥበባችን ዓለም ወደኛ እንዲመለከተን አስተዋጽኦቸው ከምንም በላይ የሚደነቅ ነው። አርክቴክቱና አንጂነሩ በሙያው የማኅበረሰቡን እምነት፣ ታሪክና ማንነት በሥነ-ሕንፃ ጥበብ ውስጥ በማኖር ማሳየት በመቻሉ ዘመን ተሸጋሪ አደርጎታል። ስለሆነም በዛሬው ዕለት የምናካሂደው ውይይት በመዳረሻ ልማት፣ በቅርስ ጥገናና እንክብካቤ እንዲሁም በኢትዮጵያ እየተገነቡ ያሉ ሕንፃዎች ኢትዮጵያዊ መገለጫነት የሌላቸው በመሆኑ እንዴት አብረን እንሥራ ብለን ስንነሳ በመጀመሪያ ከአርክቴክቶችና አንጂነሮች ጋር በመሆን የጋራ ቅርሶቻችንን የማወቅ፣ የመለየትና የማስተዋወቅ ሥራ፣ የቅርስ ጥገናና እንክብካቤ ሥራ በራስ ዕውቀት እንዲሆን በማድረግ በቅርስ ጥበቃ ኢትዮጵያዊ መልክ እንዲኖራቸው፣ የዕውቀት ሽግግርና ሕዝብ ሕህዝብ የማገናኘት ሥራ በአንድ ላይ ተሰባስበን የምንሠራበትና የጋራ አቅጣጫ የምንይዝበት ነው በማለት መድረኩን ክፍት አድርገዋል።
● SEMONEGNA on Social Media: Facebook | Twitter | Instagram | Pinterest | Video | Forum
በመቀጠል ሦስት ርዕሰ ጉዳዮች የመወያያ ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን፣ እነዚህም በአገራችንን ቅርሶች ነባራዊ ሁኔታ ዳሰሳዊ ጥናት በአቶ ኃይሉ ዘለቀ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን፣ በዘመናዊ የቅርስ አመራርና አስተዳደር ወቅታዊ ቁመና በረ/ፕሮፌሰር ሀሰን ሰዒድ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በተጠናከረ የመዳረሻ ልማት በአቶ ቴዎድሮስ ደርበው ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪስት አገልግሎቶች ብቃት የማረጋገጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው።
ጥናታዊ ጽሑፎችን ያቀረቡ ባለሙያዎች ተንተን ባለመልኩ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የቅርስ አስተዳደር ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበረ ከታሪካዊ ዳራው ጀምሮ የሀብቱ ጥበቃና እንክብካቤ የመንግስትና የሕዝብ ፍላጎት ላይ የተመሠረቱ መሆኑ አመላክተዋል። የሀብቱ ጥበቃና እንክብካቤ በግለሰብ፣ በማኅበረሰብ እና የባለሙያው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን በተያዘላቸው ጊዜ ቅደም ተከተል ገለፃ አድርገዋል።
በውይይቱም እያንዳንዱ ባለሙያው በቅርስ ጥገናና እንክብካቤ ዙሪያ በዕውቀትም፣ በሀሳብም በጉልበትም መደግፍ እንዲችል በተደራጀ መልኩ አቅም እንዲፈጠርለት የተጠየቀ ሲሆን በመዳረሻ ልማት (በከተማ ግንባታ) እየታዩ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በውይይቱ የተሳተፉ መሀንዲሶች እና የሥነ-ሕንፃ ባለሙያዎች እንደአገር የሚሠሩ የሥነ-ሕንፃ ሥራዎችን የዲዛይን ውድድር ውስጥ መሳተፍ እንዲችሉ ዕውቅና በመስጠት አገራዊ ቅርጽ እንዲይዙ ማድረግ ወሳኝ መሆኑ፣ በመዳረሻ ልማት ዘርፍ የሚሠማሩ ዜጎች የኢትዮጵያዊ ማንነት መገለጫ ያላቸው ሕንፃዎች እንዲኖረን በሕንፃ ግንባታ መስክ ትኩረት የሚሰጥ አስገዳጅ ቅድመ ትኩረታዊ ስልት (strategy) እንደአገር ሊኖረን ይገባል።
ምንጭ፦ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መፃሕፍት ኤጀንሲ አሠራሩን ለማዘመን የሚያግዙ ሀሳቦች ላይ ከእንግሊዝ ቤተ መዛግብት ኃላፊዎች ጋር ምክክር አደረገ።
በምክክሩ የቤተመዛግብት እና ቤተ መፃሕፍት አያይዝን ለማዘመን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የእንግሊዙ አቻ ተቋም ልምድ ምን እንደሆነ ያወያየ ምክክር ሚያዚያ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በኤጀንሲዉ የቪዲዮ ኮንፈረንስ አዳራሽ ተካሄደ። ለውይይቱ መክፈቻ የኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ የኩኖአምላክ መዝገቡ ለእንግዶቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ ኢትዮጵያ የብዙ መዛግብቶች መገኛና ባለቤት ብትሆንም እንኳን ያላትን ሀብት ለራሷም ለዓለምም ለማበርከት የዘመናዊ ቴክኖሎጂ እጥረት እንዳለባት በማንሳት ይህንን ክፍተት የእንግሊዝ ቤተ መዛግብት የቴክኖሎጂ ሽግግር እገዛ አንዲያደርግላቸዉ ጠይቀዋል።
በመቀጠል በእንግሊዝ ቤተ መዛግብት የኤሲያና የአፍሪካ የመዛግብት ስብስብ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሊዊሳ ኤሌና ሜንጎሊ (Luisa Elena Mengoni, Head of Asian and African Collections at the British Library) እንዳሉት በሁለቱ ሀገራት ዉስጥ ያሉ ተመራማሪዎች፣ ደራሲያን፣ እንዲሁም ሌሎች ፀሐፍት የእርስ በእርስ የልምድ ልዉዉጥ እንዲያደርጉ መንገዱን ማመቻቸት ለስነ-ፅሑፍ እድገት አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።
አቶ ክርስቲያን ጄንሰን (Kristian Jensen) የእንግሊዝ ቤተ መዛግብት ኃላፊ እንዲህ አይነት የምክክር መድረኮች ክፍተቶችን ለመለየትና መፍትሔ ለማበጀት እንደሚጠቅሙና ቀጣይነት እዲኖራቸዉ በተለይም የሥነ-ፅሑፍ ታሪኳ ከአክሱም ዘመነ መንግስት ጀምሮ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ እንደ ኢትዮጵያ ያለች ሀገር ቤተ መፅሐፍቷና ቤተ መዛግብቷን በማዘመን ረገድ የእንግሊዝ ቤተመዛግብት እንደሚያግዝ ተናግረዉ፥ ኃላፊዉ የማይክሮ ፊልም (የመፅሐፍት ላይ ፅሑፎችን ወደ ሶፍት ኮፒ የሚቀይር መሣሪያ) በእርዳታ መስጠቷ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር በዶ/ር ሂሩት ካሳዉ በኩል ለኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ለአቶ የኩኖአምላክ መዝገቡ ርክክብ ከተደረገ በኋላ ባህላዊ የቡና ጠጡ ሥነ-ስርዓት ተከናዉኖ ዝግጅቱ ተጠናቋል።
ምንጭ፦ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ሌሎች ዜናዎች፦- የልዑል አለማየሁ አፅም ወደ እናት ሀገሩ እንዲመለስ ተጠየቀ
- የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኪነ-ሕንፃ (አርክቴክቸር) ትምህርት ክፍል ተማሪዎችን አስመረቀ
- ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ እና ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ በደብረ ብርሃን ከተማ ሃውልት ሊቆምላቸው ነው
- ጉዞ ዓድዋ ― ታላቁ የዓድዋ ድልን የሚገባው የታሪክ ማማ ላይ ለመስቀል የሚጥር ኢትዮጵያዊ ማኅበር
- የወልድያ ዩኒቨርሲቲ እና ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ በትብብር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የትምህርት መስክ ሊጀምሩ ነው
- ሀገር በቀል የመድኃኒት አምራቾች መሠረታዊ ችግሮች በጥናት ሊለዩ ይገባል ― የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ
የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ከስዊድኑ ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ (The University of Gothenburg) ጋር በትብብር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤን የሚመለከት ትምህርት ለመስጠት የሚያስችላቸው የመግባቢያ ሰነድ ይፈርማሉ።
በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ መስክ በሀገራችን ያለውን የባለሙያ እጥረት የሚቀርፍ መነሻ ሀሳብ ከስዊድን ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ የመጡ መምህራን ለክቡራን ሚንስትሮች ገለፃ አድርገዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ሀገራችን ኢትዮጵያ ከስዊድን መንግስት ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑ በተለይ በኪነ-ሕንፃ ትህምርት ዘርፍ ያላቸው ልምዶች ታሪካዊና ጠናካራ ግንኙነት የተፈጠረበት መሆኑ ብዙ ይወሳል።
በመሆኑም የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ስዊድን ውስጥ በትልቅነቱ ሁለተኛ ከሆነው ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ (The University of Gothenburg) ጋር በትብብር ለመክፈት ያሰበው የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ እውን እንዲሆንና የቅርስ ጥገና ተግባራዊ ትምህርት በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ እንዲሰጥ ታስቦ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በኩል ቅድመ ዝግጅት መጀመሩን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አርኪዮሎጂ (archeology) ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶ/ር መንግስቱ ጎበዜ፥ የታሰበው የትምህርት መርሀግብር ለክቡራን ሚኒስትሮች (ለፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፥ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እና ለወ/ሮ ብዙነሽ መሠረት፥ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ) የሥልጠናውን ዓላማና ግብ የሚያግባባ ገለፃና ትውውቅ አድርገውላቸዋል።
በመቀጠልም በልዑካኑ በስዊድን ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ በኩል የመጡት መምህራን ያላቸውን ዝግጁነትና ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲሁም የገጠሩ ሕዝብ ባህላዊ ሀብቱን እየተወ ወደ ከተማ ከሚኮበልል እዛው በቅርሱ ተጠቃሚ የሚሆንበት መሠረት የጣለ ልምድ መኖሩን የሚያብራራ ገለጻ በ‘Bosse Lagerqvist’ እና ‘Lars Runnquist’ የልዑኩን ቡድ ኑን በመወከል ገለፃ አደርገዋል። ተመራማሪ ፕሮፌሰሮች በነሱ በኩል ተግባራዊ ትምህርቱ ከቁሰቁስ አቅርቦት እንደሚደገፍ ጭምር በትብብር የሚሠራበት ሁኔታ ለመፍጠር በቻርትና ስዕላዊ መግለጫዎች ማብራሪያ አድርገዋል።
◌ ሰባት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና STEMpower ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ
ለመርሀግሩ ማጠቃለያ ክቡራን ሚኒስትሮችም በበኩላቸው በሁለቱም ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት መልካም በሚባል ደረጃ የደረሰ መሆኑን በማመስገን፥ ያቀረባችሁት ሀሳብ የሚጠቅመንና እንደኢትዮጵያ በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ መስክ የሚሰጡ ትምህርቶች በንድፈ-ሀሳብ ብቻ በመሆኑ በትብብር ስለምንሠራው ብዙ ባለሙያዎችን የምናፈራበት ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
የትምህርት ማስተማሪያ መርሀግብሩ የሁለተኛ ዲግሪ ለመስጠት የሚያበቃ ሲሆን፥ ለዚህ የመግባቢያ ሰነድ በቅርብ ጊዜ እንደሚፈረም እንዲሁም ተግባራዊ ትምህርቱ የሚሰጥበት ቦታ አንድ ካምፓስ በላሊበላ ቅርጫፍ የሚዘጋጅበት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
ምንጭ፦ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የአጼ ቴዎድሮስ ልጅ የልዑል አለማየሁ አፅም ከሀገረ እንግሊዝ ወደ እናት ሀገሩ እንዲመለስ ኢትዮጵያ ተጠየቀ። በተጨማሪም ለንደን ከተማ ውስጥ በቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም (Victoria and Albert Museum) የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥያቄ ቀርቧል።
በኢፌዴሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው የተመራው የልዑካን ቡድን መጋቢት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. በለንደን ጉብኝት አድርገዋል።
በዚሁ ወቅትም በለንደን የዊንዶዘር ቤተመንግስት (Windsor Castle) የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስን መካነ መቃብር እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አፄ ሃይለስላሴ ይጸልዩበት የነበረውን ወንበር ጎብኝተዋል።
ዶ/ር ሂሩት ካሳው በአጼ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል አለማየሁ መቃብር ላይ የአበባ ጉንጉን ማስቀመጣቸውን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን እንደመረጃ ምንጭነት በመጥቀስ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።
በጉብኝቱ ወቅትም “የአጼ ቴዎድሮስን ፀጉር ማግኘታችን ደስ ብሎናል፤ ይሁን እንጂ ከትውልድ ቦታው ተለይቶ ህይወቱ ያለፈው ልዑል አለማየሁ አፅም በትውልድ ሀገሩ እንዲያርፍ የኢትዮጵያዊያን ጥያቄ ስለሆነ በክብር ወደ አገሩ እንዲመለስ” ሲሉ ዶክተር ሂሩት ጠይቀዋል።
አፅሙ ወደኢትዮጵያ ተመልሶ ከአባቱ አጼ ቴዎድሮስና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር መቀላቀል እንደሚገባውና የዊንዶዘር ቤተመንግስት ለሚመለከተው አካል ጥያቄውን አቅርቦ በአፈጣኝ ምላሽ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርበዋል።
በዕለቱ ልዑካን ቡድኑን በመቀበል ከቡድኑ ጋር የተወያዩት የዊንዶዘር ቤተ-መንግስት ሃላፊ ዶ/ር ማርክ ፓወል በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንነጋገርበታለን ብለዋል። ሂደቱን በተመለከተ በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመከታተል እልባት እንዲያገኝ አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርግም ሚኒስቴሩ ተገልጿል።
በሌላ በኩል የልዑካን ቡድኑ መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ለንደን የሚገኘውን የቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም ጎብኝቷል። በዶ/ር ሂሩት ካሳው የተመራው የልዑካን ቡድኑና በለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሙዚየሙ ዳይሬክተር ዶ/ር ትሪስታራም ኸንት (Tristram Hunt, PhD) ጋር ተወያይቷል። በውይይቱ ወቅት በቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም የሚገኙ የመቅደላ ስብስብ ቅርሶች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥያቄ ቀርቧል።
እ.አ.አ በ2018 የቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም የሚገኙ የመቅደላ ስብስብ ቅርሶች ለኢትዮጵያ መመለስ እንደማይችል፤ ነገር ግን በረጅም ጊዜ ውሰት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ማድረግ እንደሚቻል መገለጹ ይታወቃል። የሙዚየሙ ዳይሬክተር ዶ/ር ትሪስታራም ኸንት ጥያቄው ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው ውሰት የሚለው ቃልም ለኢትዮጵያውያን ከባድ መሆኑን እንደተረዱት ተናግረዋል። በመሆኑም “የተቸገሩት ጉዳዩ የሕግ ጉዳይ በመሆኑና ምላሽ ለመስጠት ያለን አማራጭ ይህ ብቻ ስለሆነ ነው ” ብለዋል።
“ያለን አማራጭ ይህን ቀዳዳ በመጠቀም ሊስተካከሉ የሚችሉ አባባሎችን ተጠቅመን የሚመለሱበትን ሁኔታ መፍጠር፤ ይህን ካላደረግን ግን በሕጉ ላይ ጸንተን ወደፊት የሚሆነውን ነገር መመልከት ይኖርብናል” ሲሉም ዶ/ር ኸንት አክለዋል።
የባህል ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ቅርሶቹ የኢትዮጵያ በመሆናቸው በረጅም ጊዜ ውሰት ሳይሆን በቋሚነት ቅርሶቹ ለኢትዮጵያ መመለስ የሚችሉበት አማራጭ መፍትሄ ሙዚየሙ ሊያበጅ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በኤምባሲውና በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል በአስቸኳይ መግባቢያ ሰነድ በመፈራረም፣ ካለው ሕግ ጋር በማይጋጭና የኢትዮጵያን ጥያቄ ሊመልስ በሚችልበት ሁኔታ በመንቀሳቀስ ጉዳዩ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት እልባት እንደሚያገኝ ዳይሬክተሩ ገልጸፀዋል።
በለንደን ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲም ባለው ሙሉ አቅምና ጊዜ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በመወጣት ቅርሶቹ ወደ አገራቸው እንዲገቡ እንደሚያደርጉ በብሪታኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍስሃ ሻወል ገብሬ ገልጸዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲሱ የካቢኔ አባላት ሹመት የቀረበው የአስፈፃሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣውን አዋጅ እንደገና ለማሻሻል የቀረበውን አዲስ ረቂቅ አዋጅ በምክር ቤቱ መፅደቁን ተከትሎ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል።
አዲስ አበባ – የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ20 አዳዲስ የካቢኔ አባላት ሹመት ውስጥ 50 በመቶ ሴቶች ሆነው እንዲያገለግሉ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) የቀረበውን ሹመት ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ አፀደቀ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሚሾሙት 20 ካቢኔዎች ውስጥ 10 ሴቶች ሆነው በተሰጣቸው ኃላፊነት እንዲያገለግሉ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
አዲሱ የካቢኔ አባላት ሹመት የቀረበው የአስፈፃሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣውን አዋጅ እንደገና ለማሻሻል የቀረበውን አዲስ ረቂቅ አዋጅ በምክር ቤቱ መፅደቁን ተከትሎ ነው።
በዚህም መሠረት የሹመቱ ዋና መስፈርት ብቃት፣ የትምህርት ዝግጅትና ለውጥን የመምራት አቅም መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ከሚሾሙት ካቢኔዎች 50 በመቶ (በቁጥር፥ ወይም ከ20ዎቹ 10 ሴት) ካቢኔዎች መሆናቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
ይህም በኢትዮጵያ ምናልባትም በአፍሪካ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑም በምክር ቤቱ ተገልጿል።
በዚህ በተደረገው የካቢኔ ሹመት ለውጥ ውስጥ ከዚህ በፊት “የፐብሊክ ሰርቪስ እና ሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር” ተብሎ ይጠራ የነበረው ሚኒስቴር ተለውጦ አሁን “ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን” (Civil Service Commission) በሚል እንደተተካ ታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ ሶስት ኮሚሽኖችም በአዲስ መልክ ተካተዋል፤ እነዚህም (1) የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን (Job Creation Commission)፣ የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን (Environment, Forestry and Climate Change Commission) እና የፕላንና እድገት ኮሚሽን (Plan and Development Commission) ናቸው።
አዲስ በተዋቀረው ካቢኔ ውስጥ የተሰየሙት ባለስልጣናትና የተሰየሙበት ስልጣን ዝርዝር
- ዶ/ር ሂሩት ካሳው ― የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር
- ዶ/ር ሂሩት ወልደማርያም ― የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር
- ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ― የሰላም ሚኒስቴር
- ዶ/ር ሳሙኤል ሆርቃ ― የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር
- ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ― የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር
- አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ― ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ
- አቶ አህመድ ሺዴ ― የገንዘብ ሚኒስቴር
- ዶ/ር አሚን አማን ሐጎስ ― የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር
- ወ/ሮ አዳነች አበበ ― የገቢዎች ሚኒስቴር
- ኢ/ር አይሻ መሀመድ ሙሳ ― የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር
- አቶ ኡመር ሁሴን ― የግብርና ሚኒስቴር
- ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ― የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር
- ወ/ሮ የዓለምፀጋይ አስፋው — የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር
- ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ― የትራንስፖርት ሚኒስቴር
- አቶ ጃንጥራር አባይ ― የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር
- ዶ/ር ኢ/ር ጌታሁን መኩሪያ ― የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
- ዶ/ር ጥላዬ ጌጤ ― አምባዬ የትምህርት ሚኒስቴር
- ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ― የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
- ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ-እግዚአብሔር ― የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
- ዶ/ር ፍፁም አሰፋ ― የፕላን ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
በጥቅምት ወር ዓም የጸደቀው የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ የፊልም ኢንዱስትሪውን ዘርፍ በአግባቡ እንዲያሳድገው ከተፈለገ የማስፈጸሚያ ሰነድ ሊዘጋጅለት ይገባል – በሀገሪቱ ውስጥ በፊልም ሥራ ላየ እንደተሰማሩ ባለሙያዎች ማብራሪያ።
በጌትነት ተስፋማርያም (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)
አዲስ አበባ – የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ ዘርፉን በአግባቡ እንዲያሳድገው ከተፈለገ የማስፈጸሚያ ሰነድ ሊዘጋጅለት እንደሚገባ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፊልም ሠሪያዎች ማህበር የቀድሞ ፕሬዚዳንት አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ እንደገለጸው፤ የዘርፉን ችግሮች ለማቃለል የሚያስችል አ ሠራር ይኖረዋል የተባለው ፖሊሲ ባለፈው ዓመት ጸድቋል። ነገር ግን ፖሊሲው ዝርዝር ጉዳዮችን የማይዝ በመሆኑ እያንዳንዱን የዘርፉን ችግሮች ሊቀርፍ የሚችል የማስፈጸሚያ ሰነድ ሊዘጋጅ ይገባል።
እንደ አርቲስት ደሳለኝ ገለጻ፤ የፊልም ኢንዱስትሪው ለአምስት መቶ ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠር የሚችል መሆኑን በጥናት ተረጋግጧል። ነገር ግን እስካሁን በአግባቡ ስላልተሠራበት ውጤቱ እምብዛም ነው። ከአጠቃላይ የአገሪቷ ገቢ ውስጥ ያለው ድርሻም ዝቅተኛ ነው። የፊልም ፖሊሲው አስፈጻሚ አካል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ካለው የሰው ኃይል፣ የፊልም ጥበብ ዕውቀት ችግር እና አደረጃጀት አኳያ ዘርፉን በሚገባው ልክ እያገዘ አይደለም። በመሆኑም የፊልም ባለሙያዎች ዋነኛውን ድርሻ በመውሰድ ለፖሊሲው ማስፈጸሚያ ስትራቴጂ ለማውጣት ሌት ከቀን መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
የፊልም ባለሙያው ዮናስ ብርሃነ መዋ በበኩሉ፤ እንደ አንድ የፊልም ባለሙያ ፖሊሲው ሲጸድቅ በኢንዱስትሪው ያሉት ችግሮች ይቀረፋሉ ብሎ እንደጠበቀ ገልጿል። ዝርዝር ጉዳዮችን ለማስተካከል እና ወጥ አሠራር ለማምጣት የማስፈጸሚያ ሰነዱ የግድ መዘጋጀት እንዳለበት ባለሙያዎች ሊገነዘቡ እንደሚገባ ተናግሯል። የማስፈጸሚያ ሰነዱንም ለማዘጋጀት የሚያስችል ቡድን ከባለድርሻ አካላት ተውጣጥቶ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን በር በየጊዜው በማንኳኳት ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ የፊልም ሠሪዎች የዘርፍ ማኀበር ፕሬዚዳንት አቶ ቢንያም አለማየሁ እንደገለጸው፤ የማስፈጸሚያ ሰነዱ ቢዘጋጅ በመጀመሪያ ኢንዱስትሪው በማደጉ ተጠቃሚ የሚሆነው ባለሙያው ነው። በመሆኑም አርቲስቶች፣ ዳይሬክተሮች እና በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚሳተፉ ግለሰቦች ሳይሰለቹ ለፖሊሲው የማስፈጸሚያ ሰነዱ ዝግጅት መሥራት አለባቸው። በዘርፉ ያለውን የዕውቀት፣ የገቢ እና የአሠራር እድገት ለማስመዝገብ ማስፈጸሚያ ሰነዱ ቁልፍ ሥራ መሆኑን በመረዳት ማንኛውም ባለሙያ በንቃት ሊሳተፍ እንደሚገባ ገልጿል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ሰላም ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ የፊልም ሠሪዎች የዘርፍ ማኅበር በጋራ ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ፊልም ፖሊሲ ትግበራ ላይ ያተኮረ ውይይት ሰሞኑን በብሔራዊ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አዳራሽ ማካሄዱ ይታወሳል። በውይይቱ መጨረሻ ከ20 ያላነሱ በኪነጥበቡ ላይ ተሳትፎ ያላቸው በጎፈቃደኛ ባለሙያዎች የፊልም ፖሊሲው ማስፈጸሚያ ሰነድ ለማዘጋጀት በሚደረገው ጥረት ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ተመርጠዋል።
እንደ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ፥ የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ በኢፌዴሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. መጽደቁ ይታወሳል።
በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀውን የፊልም ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ሙሉ ዶሴ (ፋይል) በፒ.ዲ.ኤፍ (PDF) እዚህ ጋር ያገኙታል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት
Search Results for 'የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር'
Viewing 13 results - 1 through 13 (of 13 total)
Viewing 13 results - 1 through 13 (of 13 total)