-
Search Results
-
የአዲስ አበባ የወጪና ገቢ ንግድ ማሳለጫ ኮሪደር የሆነው የቃሊቲ አደባባይ – ቱሉ ዲምቱ አደባባይ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ገፅታዎች
አዲስ አበባ (አአመባ) – የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን (አአመባ) በሥራ ተቋራጮች ከሚያስገነባቸው ግዙፍ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው የቃሊቲ አደባባይ – ቱሉ ዲምቱ አደባባይ የመንገድ ፕሮጀክት የትራፊክ ፍሰቱን ሊያሳልጡ የሚችሉ በርካታ ገፅታዎች አሉት።
የመንገድ ፕሮጀክቱ 11 ኪ.ሜ ርዝመትና 50 ሜትር የጎን ስፋት አለው። በመንገዱ ግራና ቀኝ መስመሮች ላይ በአንድ ጊዜ ብቻ 8 መኪናዎችን በቀላሉ ማሳለፍ የሚያስችል ነው። የመንገዱ ዋና ዋና መገጣጠሚያዎችና ማሳለጫዎች ላይ ደግሞ ከ70 እስከ 100 ሜትር የሚደርስ የጎን ስፋት ይኖረዋል።
ከመኪና መስመር ባሻገር በግራና በቀኝ 6.5 ሜትር ስፋት ያለው የሳይክል መስመር፣ እግረኛ በሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ 9 ሜትር ድረስ ስፋት ያላቸው የእግረኛ መንገዶች፣ በመንገዱ መሀል ላይ 11 ሜትር ስፋት ያለው ለብዙሃን ትራንስፖርት ብቻ የሚያገለግል መስመር እንዲሁም በመንገዱ ግራና ቀኝ ላይ 32 የሚሆኑ የአውቶቡስ ማቆሚያዎች ይኖሩታል። እነዚህ የአውቶቡስ ማቆሚያዎች ከ40 እስከ 60 ሜትር ርዝመትና ከ3 እስከ 7 ሜትር የጎን ስፋት ይኖራቸዋል።
የቃሊቲ አደባባይ – ቱሉ ዲምቱ አደባባይ የመንገድ ፕሮጀክት ሌላው ገፅታ ደግሞ ሦስት ዋና ዋና ማሳለጫዎች ያሉት ሲሆን የመጀመሪያው የፕሮጀክቱ መነሻ የሆነው የቃሊቲ አደባባይ ነው። ይህ ማሳለጫ በመሀላቸው ዘጠኝ ሜትር ስፋት ያላቸው 8 ስፓን እና 240 ሜትር ርዝመት ያላቸው ሁለት ድልድዮችን የያዘ ነው።
ሁለተኛው ማሳለጫ ጥሩነሽ ቤጂንግ ማሳለጫ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፥ 100 ሜትር ርዝመት የሚጠጋ ድልድይ አለው። ይህ ማሳለጫ ወደ አቃቂ ከተማ፣ ወደ ሄኒከን ቢራ (Heineken Ethiopia)፣ ወደ ደራርቱ ት/ቤት፣ ወደ ቱሉ ድምቱ አደባባይ እና ወደ ቃሊቲ አደባባይ በድምሩ አምስት ዋና ዋና የመንገድ መጋጠሚያዎችን ለማሳለጥ የሚያገለግል ነው።
ሦስተኛውና የመጨረሻው ማሳለጫ ቀድሞ ጋሪ ድልድይ እየተባለ የሚጠራው ሲሆን፥ በ50 ሜትር ርዝመትና በ20 ሜትር የጎን ስፋት እየተሠራ ይገኛል።
አጠቃላይ የቃሊቲ አደባባይ – ቱሉ ዲምቱ አደባባይ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱን የቻይናው ኮሚኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ በ2 .4 ቢሊዮን ብር በጀት እያከናወነው ሲሆን፥ እስካሁን ድረስም 65 በመቶ ገደማ አፈፃፀም አስመዝግቧል። የመንገዱ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ በመንገዱ በግራ መስመር 800 ሚሊ ሜትር ውፍረት ያለው ግዙፍ የውሀ መስመርና የመብራት ፖሎች ባለመነሳታቸው እንቅፋት ፈጥረውበታል። ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት እነዚህን የወሰን ማስከበር ችግሮች ለመፍታት ከመብራት ኃይል፣ ከከተማዋ ውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን እንዲሁም ከሚመለከታቸው የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በቅርበት እየሠራ ችግሩን በመፍታት ላይ ይገኛል።
የቃሊቲ አደባባይ – ቱሉ ዲምቱ አደባባይ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታው ሲጠናቀቅ በሀገሪቱ በምሥራቅ አቅጣጫ በኩል የሚደረገውን የወጪና ገቢ ንግድ ለማሳለጥ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል። ከዚህም በተጨማሪ የመዲናዋን ነዋሪዎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከማሻሻሉም ባሻገር የከተማዋን ገፅታ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀይራል ተብሎ ይጠበቃል።
ምንጭ፦ አአመባ
የመንገዶች የመብራት አገልግሎት አለመስጠት ምክንያቱ ኃይል ያልተለቀቀላቸው በመኖራቸው፣ መሠረተ ልማቶች ስለሚዘረፉ፣ የምሰሶና የአምፖል ማርጀት እንደሆነ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ጠቅሷል።
አዲስ አበባ (ኢዜአ)–በአዲስ አበባ ከተማ ካሉት መንገዶች ውስጥ የመብራት አገልግሎት እያገኙ ያሉት ከ40 በመቶ እንደማይበልጥ ያስታወቀው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን እስከሚቀጥለው ዓመት ዘጠና በመቶ የከተማዋ መንገዶች መብራት እንዲኖራቸው ከአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢሮ ጋር እየሠራሁ ነው ብሏል።
የመንገዶች የመብራት አገልግሎት አለመስጠት ምክንያቱ ኃይል ያልተለቀቀላቸው በመኖራቸው፣ መሠረተ ልማቶች ስለሚዘረፉ፣ የምሰሶና የአምፖል ማርጀት እንደሆነ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ጠቅሷል።
የመብራት ምሰሶዎች በየመንገዱ ቢተከልም ከሁለት ዓመት ወዲህ አብዛኛዎቹ አገልገሎት እንደማይሰጡ የጠቀሱት የአፍንጮ በር ነዋሪ አወል አማን፥ በምሽት ወደ መስጊድ ሲሄዱና ከሥራ አምሽቶ ወደ ቤት ለመግባት ስጋት ፈጥሮብናል ብለዋል። አክለውም ምሰሶዎችና አምፖሎች ተሰባብረው እንደሚገኙ ያነሱት ነዋሪው አገልግሎት የማይሰጡ መብራቶች እንዲጠገኑ ጠይቀዋል።
የጉለሌ አካባቢ ነዋሪ አቶ ፀጋዬ መኩሪያ መኪና አሽከርካሪ ሲሆኑ፥ መንገዶች የምሽት መብራት ከሌላቸው ለአሽከርካሪዎች ፈታኝ በመሆኑ የትራፊክ አደጋ ይከሰታል ብለዋል። አቶ ጸጋዬ እንደሚሉት ጉለሌ አካባቢ በርካታ መኪናዎችና እግረኞች የሚተላለፉበት ቢሆንም የምሽት መብራት የላቸውም፤ ብዙዎችም አደጋ እየደረሰባቸው ነው።
◌ ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስም ሆነ አሮጌ መኪናዎች ከሚገባው በላይ ውድ የሆኑበት ምክንያት ምንድን ነው?
የላዳ ታክሲ አሽከርካሪ ማቲዮስ ታምር ሥራው በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች እንዲዘዋወር ስለሚያደርገው በርካታ መንገዶችን እንዳየና መብራት እንደሌላቸው ተናግሯል። ውስጥ ለውስጥና በዋና መንገዶች መብራት በብዛት አለመኖሩ መሪን ያለ አግባብ የመጠቀም ዕድል ስለሚኖር የመጋጨት አጋጣሚውም ሰፊ ነው ብሏል።
ከስድስት ኪሎ ሽሮ ሜዳ፣ ከሰሜን ማዘጋጃ እንጦጦ፣ ከእንቁላል ፋብሪካ ዊንጌት ባሉ መንገዶች እንደሚሰሩ የገለፁት በአዲስ አበባ የጉለሌ ክፍለ ከተማ የትራፊክ ቁጥጥር አባል ምክትል ኢንስፔክተር አያሌው በለጠ ከነዚህ መንገዶችም አብዛኛዎቹ መብራት የላቸው ብለዋል።
መዲናዋ በተሽከርካሪዎችና በእግረኞች የተጨናነቀች በመሆኗ በጨለማ ወቅት መብራት አለመኖሩ የትራፊክ አደጋን አባብሷል ነው ያሉት ምክትል ኢንስፔክተሩ።
መብራት ከሌለ አሽከርካሪዎች ረጅም መብራት የመጠቀም ዕድላቸው ሰፊ ነው ያሉት ረዳት ኢንስፔክተር መራጭ ድንጌቻ፤ ከፊት ለፊት የሚመጡ መኪናዎችን እይታ ሙሉ ለሙሉ በመሸፈን ለአደጋ ያጋልጣል ብለዋል።
“ከእንቁላል ፋብርካ እስከ ዊንጌት ብዙ ሆስፒታሎች ስላሉ ህሙማንን የያዙ ተሽከርካሪዎች ቀንና ሌሊት ይመላለሳሉ፤ ባለፈው ዓመት በዚያ መንገድ በርካታ ሰዎች ተገጭተዋል” ነው ያሉት።
ምክትል ኢንስፔክተር አያሌው “ከዚህ ቀደም በአዲሱ ገበያ ዊንጌት በሚወስደው መንገድ አንዲት ሴት ተገጭታ መብራት ባለመኖሩ ምክንያት ሌሊቱን ሙሉ መኪና ሲመላለስባት አድሮ የገላዋ ዱቄት ነው የተነሳው” ሲሉ ያጋጠማቸውን አሳዛኝ ክስተት ነግረውናል።
በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ መብራት ክትትል ባለሙያ ኢንጅነር ደረጀ ኃይሉ የከተማዋ መንገዶች አንዳንዶቹ የመብራት አገልግሎት እንደሌላቸው ገልጸው “ከጉርድ ሾላ ኦቨር ፓስ፣ መገናኛ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ከስድስት ወር በፊት ተጠይቆ የዋጋ ግምት አልተመለሰልንም” ነው ያሉት።
የቦሌ አራብሳ መንገድ ከሁለት ዓመት በፊት ለአገልገሎት ክፍት ሆኖ የመብራት ምሰሶ ቢተከልም መብራት እንዳልተለቀቀ የገለጹት ኢንጅነር ደረጀ ከስድስት ኪሎ ፈረንሳይ ጉራራ ኪዳነምኅረት የምሰሶ ተከላና የገመድ ዝርጋታ የማሟላት ሥራ ተከናውኖ የኃይል ዋጋ ግምት እንዲላክለት ከአንድ ወር ወዲህ መጠየቁን ተናግረዋል።
በባለስልጣኑ የድንገተኛና አንሰለሪ ጉዳዮች ቡድን መሪ አቶ ዘውዱ ባይህ በበኩላቸው መብራት ተቋርጦባቸው የነበሩ 37 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የቀለበት መንገዶች ባለፈው ዓመት ተጠግነው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።
ጨለማን ተገን አድርገው ዝርፊያ የሚፈጽሙ አካላት የመብራት ቁሳቁሶችን ከአገልግሎት ውጪ እያደረጉና እየዘረፉ መሆኑን የተናገሩት አቶ ዘውዱ ከዮሴፍ-ቦሌ ሚካኤል፣ ከአየር መንገድ አደባባይ-ኢምፔሪያል፣ ሸጎሌ ከጎጃም በር-እስከ ዊንጌት እንዲሁም 18 ማዞሪያ፣ ከ3 ቁጥር ማዞሪያ-አለርት ቁሳቁሶቹ በየጊዜው እየጠፉ ተቸግረናል በማለት አስረድተዋል።
የተበላሹትን ወደ አገልገሎት ለመመለስ በራስ ኃይልና በጨረታ እየተጠገኑ መሆኑን ያነሱት ቡድን መሪው አሮጌ መብራቶችን ደረጃቸውን የጠበቁ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በከተማዋ መንገዶች ከ40 በመቶ የማይበልጡ የመብራት አገልግሎት ያላቸው ሲሆን ባለሥልጣኑ 25 ሚሊዮን ብር በመመደብ ጥገና እየሠራ ነው፤ በዚህ በጀት ዓመትም ሽፋኑን 90 በመቶ ለማድረስ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ክፍሌ በበኩላቸው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ባለው ውል መሠረት ቆጣሪና ትራንስፎርመር እየገጠምን ነው ብለዋል።
ሆኖም የሲቪል ሥራዎች በመንገዶች ባለስልጣን በኩል ባለመጠናቀቃቸውና የመንገድ ርክክብ ባለማድረጋቸው ምክንያት መብራት የማያገኙ መንገዶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
“የካ አባዶ አንድ መንገድ፣ ከስድስት ኪሎ ፈረንሳይ ጉራራ መንገድ ተገምቷል፣ ቦሌ አራብሳ እየተገመተ ነው፣ ጎሮ ቱሉ ዲምቱ ትራንስፎርመርና ቆጣሪ ተገጥሟል፣ ከሲኤምሲ አደባባይ እስከ ካራ ትራንስፎርመርና ቆጣሪ ቢገጠምም መንገዱን ርክክብ አላደረጉም፣ ከዊንጌት አደባባይ እስከራስ ደስታ ሆስፒታል ላለው መንገዶች ባለስልጣን ግምት አላመጣም፣ ዓለም ባንክ ቤቴል አየር ጤና ፍርድ ቤት ያሉት ያልተጠናቀቁ የሲቪል ሥራዎች ሲጠናቀቁ ኃይል ይለቀቅላቸዋል” ብለዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
የዘንድሮው የፀረ-ሙስና ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ለ14 ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ የተከበረ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበርያ ጽህፈት ቤት ዘግቧል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በአዲስ አበባ ከተማ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ እና በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ትብብር የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ዓመታዊ የፀረ-ሙስና ቀን “ሁለንተናዊ ሰላማችንና እድገታችንን ለማረጋገጥ በሙስና ላይ በጋራ እንዝመት፤ ጊዜው የተግባር ነው” በሚል መሪ-ቃል በፓናል ውይይት እሁድ ኅዳር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ተከብሮ ውሏል።
በዕለቱም የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታከለ ሉሊና ሙስና ተሸሞንሙኖ የሚጠራ ሳይሆን ሌብነት እንደሆነ ሁሉም ዜጎች ተገንዝበው መታገል እና ሙስና በዓይነቱም የተለያየ እንደሆነ በመግለፅ ሁላችንም ተረባርበን መከላከል አለብን ብለዋል።
አቶ ታከለ አያይዘውም ከትንሽ ከህዝብና መንግስት ሰዓትና ንብረት ጀምሮ ትኩረት በመስጠት ያለአግባብ እናዳይባክኑ በቀጣይነትም ልንሠራ ይገባል፤ ለዚህም ሁላችንም የበኩላችንን ሚና መወጣት አለብን ብለዋል።
በዓሉን አስመልክቶ በተዘጋው የፓናል መወያያ መነሻ ሃሳብ ላይም የኢፌዲሪ ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የአዲስ አበባ ማስተባበሪ ቅርንጫፍ የሕግ ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ከፋለ እንደተናሩት በርካታ የሙስና መገለጫዎች አሉ እነዚህንም እንደየዓይነታቸው ነጣጥለን መከላከል ያስፈልጋል፤ ህብረተሰቡም ሊያግዝ ይገባል በጉዳዩም ላይ ባለቤት ነኝ ይመለከተኛል ማለት ይገባል ብለዋል።
ሙስና በአሠራር፣ በአስተሳሰብ፣ በአመለካከት፣ በጥቅም ትስስር፣ በዝምድናና በመሳሰሉት የሚፈፀም በረቀቀና ሚስጢራዊ በሆነ መንገድ የሚከወን በመሆኑ የኮሚሽኑን ስራም በተገቢው እንዳይወጣ ሲያደርግ እንደነበርም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
◌ የአዲስ አበባ ከተማ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ችግሯን ለመፍታት አማራጮች እየተፈለጉ ነው
አክለውም ሙስና ለአገር ዕድገት ፀር፣ ለዲሞክራሲ ጋንግሪን እንደሆነ በማስታወስ ለአንዲት አገር ህዝብ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ውድቀት የሚያስከትል በመሆኑ ሁሉም ዜጋ እንደሚመለከተው በማብራራት ይህን ለመከላከል ሁሉም ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል።
በመጨረሻም እንደአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ያለው የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ በመሆኑና ብዙውን ጊዜ ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚታዩ የሙስና ወንጀሎችን ለመቀነስ በትኩረት መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የዘንድሮው የፀረ-ሙስና ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ለ14 ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ የተከበረ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበርያ ጽህፈት ቤት (TPMO) ዘግቧል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሙስናን ለመዋጋት የተደረገው ስምምነት (United Nations Convention Against Corruption) እ.ኤ.አ ጥቅምት 31 ቀን 2003 ቀን መጽደቁን ተከትሎ በየዓመቱ ኅዳር 30 ቀን “የፀረ-ሙስና ቀን” ሆኖ እንዲከበር ተወስኗል።
ምንጭ፦ TPMO | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
Search Results for 'የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን'
Viewing 7 results - 1 through 7 (of 7 total)
Viewing 7 results - 1 through 7 (of 7 total)