Search Results for 'ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ'

Home Forums Search Search Results for 'ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ'

Viewing 4 results - 1 through 4 (of 4 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች አባል ኩዊንስ ሱፐርማርኬት እጅግ ዘመናዊ የሆነውን የቀራኒዮ ፕላዛ ቅርንጫፍ ሱፐርማርኬቱን አስፈላጊዎቹን ሕጋዊ መስፈርቶች አሟልቶ በማደራጀት ማክሰኞ ሐምሌ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ሁሉን በአንድ ባቀፈውና ማራኪ በሆነው በኮልፌ ቀራኒዮ ፕላዛ ቅጥር ጊቢው አስመረቀ።

    በዚሁ የምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ባደረጉት ንግግር፤ በዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ደንቦችን መሠረት ባደረገ ዲዛይን የተሠራው፤ ኩዊንስ ሱፐርማርኬት አካሄዱም ለደምበኞች ቀላልና ምቹ የግብይት ሁኔታ ለማስፈን ትኩረት የሠጠ ነው ብለዋል።

    ሱፐርማርኬቱ በሚገኝበት በቀራንዮ ፕላዛ፣ የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚ፣ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የነዳጅ ጣቢያ/ማደያና የተሽከርካሪ እጥበትና መለስተኛ ጥገና አገልግሎት መስጫ እና በትንሹ ከ150 በላይ መኪኖች ማቆሚያ፣ የእርሻ ምርቶች መሸጫ፣ ካፌና ሱቅ፣ ባንክ፣ እና ሁለገብ አዳራሽ መኖሩን የገለጹት ዶ/ር አረጋ፥ እነዚህ በአንድ አካባቢ መደራጀታቸው ደንበኞቹን በአንድ የንግድ ማዕከል በርካታ አገልግሎቶች እንዲያገኙ የሚያስችል በመሆኑ፣ሱፐርማርኬቱን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

    ለኩዊንስ ኩባንያ መቋቋምና በዚህ ደረጃ መስፋፋት ምክንያት ለሆኑት ለሚድሮክ ኢትዮጵያ ሊቀ-መንበርና ባለሀብት ለሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ በቅድሚያ ምስጋና ያቀረቡት ዶ/ር አረጋ፥ በዛሬው ቀን በመካከላችን ለተገኙት ወንድማቸው ለሼህ አብደላ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል።

    እንዲሁም፣ የቀራኒዮ ቅርንጫፍ ፕሮጀክት በዚህ ለገበያ አመቺ በሆነ ቦታ እንዲገነባ ለረዱን የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አመራሮች እና የሚመለከታቸው ሠራተኞች፣ በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች፣ መብራት ኃይል፣ የቴሌፎንና የውሃ ተቋማት፣ የአዲስ አበባ የመንገድ ሥራዎች ተቋም፣ የአካባቢው የፖሊስ እና የፀጥታ ኃላፊዎች እና ሌሎችም ላደረጉልን መተባበር ከፍተኛ ምስጋና አቅርባለሁ ብለዋል።

    ዶ/ር አረጋ በዚሁ ንግግራቸው፥ የኩዊንስ ቀራኒዮ ቅርንጫፍ ፕሮጀክት ለቅድመ መደበኛ አገልግሎት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ፣ ለሥራ ማስኬጃ እና ለሽያጭ የሚያገለግሉ ዕቃዎች (መደርደሪያዎች፣ ማቀዝቀዣዎች፣…) ግዢ፣ የሲስተም ዝርጋታ ወጪን ጨምሮ፣ ለሸቀጣ ሸቀጥ አቅርቦት ጠቅላላ ወጪ 59.3 ሚሊዮን ብር መሆኑን አስረድተው፤ ሕንፃው በ37.7 ሚሊዮን ብር ወጪ መገንባቱንና የኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ ንብረት በመሆኑ፣ ኩዊንስ በኪራይ እንደሚገለገልበት አስታውቀዋል።

    የሪቴል ግሩፕ ፕሪንሰፓል ኦፕሬሽን ኦፊሰር ወ/ሮ ታህሳሥ ወንድምነህ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር ኩዊንስ ሱፐርማርኬት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኀበር ሰኔ 25 ቀን 2002 ዓ.ም. 46 ቋሚ እና 5 ኮንትራት፣ በድምሩ 51 ሠራተኞች በመያዝ የተቋቋመ መሆኑን አስታውሰው፥ ኩባንያው የአግሮ ኢንዱስትሪ ውጤቶችን (የዶሮ፣ የወተት እና የሥጋ ተዋጽዖዎችን)፣ የእርሻ ምርቶችን (ሰብሎች፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ እና አበባዎች)፣ የባሕር ምግቦች (ዓሣ)፣ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች (ሣሙና….) የታሸጉ ምርቶች፣ መጠጦች እና ሌሎች የፋብሪካ ውጤቶችን (የጽሕፈት መሣሪያዎችን፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን እና የቤት ውስጥ የመገልገያ ዕቃዎች) በችርቻሮ እና በጅምላ በመሸጥ እና በማከፋፈል ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

    ወ/ሮ ታህሳሥ በዚሁ ንግግራቸው፤ ኩባንያው በአሁኑ ጊዜ የካፒታል መጠኑ ወደ ብር 23,786,000፣ የሠራተኞቹ ብዛት ወደ 142 (132 ቋሚ እና 10 ኮንትራት) ማደጉን አመልክተው፤ ዓመታዊ ሽያጩም ሥራ ሲጀምር ከነበረው ከብር 12,192,000 ወደ ብር 157,000,000 ማደጉን አሰታውቀዋል።

    አያይዘውም ኩባንያው ቅርንጫፎቹን ወደ ሰባት በማሳደግ ጥራት ያላቸውን ምርቶች በበቂ ሁኔታ በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ እና ተጨማሪም አንድ የዳቦ ማምረቻና መሸጫ በመቻሬ ቅርንጫፍ በማቋቋም ለሠራተኞችና ለኀብረተሰቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን አስረድተው፤ ሱፐርማርኬቱ ለ50 ተጨማሪ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንና ዓመታዊ ሽያጩም ብር 75,000,000 እንደሚሆን፤ የኩባንያውን ዓመታዊ የሽያጭ መጠንንም በግማሽ በማሳደግ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ አሰታውቀዋል።

    ወ/ሮ ታህሳሥ ለኩዊንስ ኩባንያ መቋቋምና በዚህ ደረጃ መስፋፋት ምክንያት ለሆኑት ለሚድሮክ ኢትዮጵያ ሊቀመንበርና ባለሀብት ለክብር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ፣እንዲሁም፣ የቀራኒዮ ቅርንጫፍ ፕሮጀክት በዚህ ለገበያ አመቺ በሆነ ቦታ እንዲገነባ የፕሮጀክት ሀሳብ በማቅረብ፣ አስፈላጊውን በጀት በመመደብ፣ በፕሮጀክቱ ሂደትም ያልተቋረጠ የዕለት ተዕለት ክትትል በማድረግ፣ የቅርብ አመራር በመስጠት እና አቅጣጫ በማስያዝ ፕሮጀክቱ በአጥጋቢ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ላበቁት ለዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር እና ፕሬዚዳንት፤ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

    በዚሁ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለፕሮጅክቱ መሳካት አሰተዋጽኦ ያበረከቱ ድርጅቶችና ግለሰቦች፤ የተዘጋጀላቸውን ሠርቲፊኬት ከዕለቱ የክብር እንግዳ ከሼህ አብደላ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ እጅ ተቀብለዋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ፤ የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ ተወካይና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ አመራሮች፣ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና ደንበኞች በተገኙበት ተካሂዷል።

    ምንጭ፦ ሚድሮክ ኢትዮጵያ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 

    ኩዊንስ ሱፐርማርኬት


    Anonymous
    Inactive

    ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ሐምሌ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ አስመረቀ

    የትምህርት ጥራትን ማጠናከርና ማሻሻል ቀጣይነት ያለዉ ሥራ ስለሆነ በዚህ ጉዳይ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ማህበረሰቡ የበኩላቸዉን ሃላፊነት ሊወጡ ይገባል ተባለ።

    ይህን ያሉት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ሐምሌ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ ባስመረቀበት ወቅት በክብር እንግድነት ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

    ሚኒስትሯ አክለውም ከፍተኛ ትምህርትን የማስፋፋት፣ የጥራትና ፍትሀዊነት ሂደት ዉስጥ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዓይነተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ። በተለይም ተደራሽነትን ከማስፋት አንጻር መንግሥት ባዘጋጀዉ የሕግ ማዕቀፍ በመደገፍ ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቋቁመዉ ለዜጎች ሰፊ የትምህርትና የሥራ ዕድል ከፍተዋል። እነዚህ ተቋማት በትምህርት ፈላጊዎች እንደጥሩ አማራጭ ስለታዩና ተቀባይነትም ስላገኙ በአሁኑ ወቅት በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ብዛት ከ200 በላይ ደርሷል፤ በዚህም በከፍተኛ ትምህርት ከሚማሩት ጠቅላላ ተማሪዎች ውስጥ ከ20 በመቶ በላይ የሚሆኑትንም ያስተናግዳሉ ብለዋል።

    ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ለ36ኛ ጊዜ ተማሪዎቹን ባስመረቀበት በዚህ ዝግጅት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በማኅበረሰብ አገልግሎትና በጥናትና ምርምር ላይ እያሳዩ ያሉት መልካም ጅምር ሊበረታታ ይገባል ሲሉ ፕሮፌሰር ሂሩት ጨምረው ተናግረዋል።

    በመጨረሻም ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም እንዳሉት፥ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገ በሄደ ቁጥር የሚፈለገዉ የሰዉ ኃይልም በቁጥርና በጥራት እየጨመረ ይሄዳል። ለዚህም የወቅቱን የእድገት እርምጃና የሥራ ገበያ ፍላጎት የሚመጥን የማስተማር፣ የምርምርና ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ማስፋፋት አስፈላጊ ነው ብለዋል። አክለውም፥ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይሄንን ተገንዝበው የፕሮግራም አድማሳቸውንና አገልግሎታቸውን የአገሪቱን የአሁንና መፃኢ የሰው ኃይል ፍላጎት ባገናዘበና ጥራቱን ባስጠበቀ መልኩ በማሻሻል አጋርነታቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉ አስምረውበታል።

    ሚኒስትሯ በቆይታቸውም ከፍተኛ ውጤት ላስመዘጉ ተመራቂዎች የሜዳሊያና ዋንጫ፣ እንዲሁም የሚድሮክ ኢትዮጵያ ግሩፕስ ባለቤት በሆኑት በሼህ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስም በተሰየመው የሕይወት ዘመን አገልግሎት ሽልማት ዘርፍ ተሸላሚ ለሆኑ 4 ግለሰቦች የምስክር ወረቀት አበርክተዋል፡፡

    ዶ/ር አረጋ ይርዳዉ የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የሚድሮክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በበኩላቸው፥ ተማሪዎች በቆይታው ያካበበቱትን ዕውቀትና ልምድ ለአገራቸው በሚጠቅም መልኩ ሊያውሉት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

    ዩኒቨርሲቲው በአገራችን የመጀመሪያው የግል ዩኒቨርሲቲ በመሆን በመንግሥት ዕዉቅና ተሰጥቶት ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎችና መስኮች ለዜጎች ተደራሽነትንና ህትሃዊነትን ለማስፋት በሚደረገው ጥረት የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር

    Anonymous
    Inactive

    ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በቡራዩ ካምፓስ በአካውንቲንግና ፋይናንስ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በካምፓሱ ለመጀመሪያ ጊዜ አስመረቀ
    —–

    ቡራዩ (ሰሞነኛ)– ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ.ም, ለመጀመሪያ ጊዜ በቡራዩ ገፈርሳ ካምፓስ በአካውንቲንግና ፋይናንስ በመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በቅድመ መደበኛ ትምህርት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሕጻናትን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አረጋ ይርዳውና የሴኔት አባላት እንዲሁም የቡራዩ ከተማ ከንቲባ ተወካይ አቶ ተረፈ ንጋቱ በክብር እንግድነት በተገኙበት አስመርቋል።
    ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት በ36ኛው ዙር በተለያዪ ካምፓሶች ከ1500 በላይ ተማሪዎችን ያስመርቃል። በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ገፈርሳ ካምፓስ ለመጀመሪያ ጊዜ 18 ተማሪዎችን በዲግሪ እና በመዋዕለ ሕፃናት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎችን አስመርቋል። በዕለቱ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የተጀመረው በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙሮች እና በአካባቢው አባ ገዳዎች ምርቃት ነው።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የቡራዩ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ተፈራ ንጋቱ ባደረጉት ገለጻ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በገፈርሳ ካምፓሱ ከተማሪ ብዛት ይልቅ የትምህርት ጥራት ላይ አተኩሮ በመንቀሳቀሱ ሊመሰገን እንደሚገባው ጠቅሰው የዛሬ ተመራቂዎች ዛሬ ተመርቃችሁ የጨረሳችሁ ሳይሆን ወደ ሌላ ምዕራፍ የሚያሸጋግራችሁ በመሆኑ በርቱ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

    ዩኒቨርሲቲው በገፈርሳ ካምፓሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሄደው በዚሁ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተገለጸው፤ ካምፓሱ ስፋት ባለው ቦታ ላይ የተመሰረተና በአካውንቲንግና ፋይናንስ፣ በማኔጅመንት፣ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት፣ በአኒማል ፕሮዳክሽን ቴክኖሎጂ እና በሆርቲካልቸር በመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት በመስጠት ላይ ይገኛል።

    በሌላ በኩል ዩኒቲ አካዳሚ ቡራዩ ካምፓስ በመጪው ዓመት መደበኛ እስከ 8ኛ ክፍል አካዳሚውን በማስፋፋት የቡራዩ ሕብረተሰብ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ የማስፋፋት ሥራ እየሰራ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

    በዚህ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተመራቂ ወላጆች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። በዕለቱ የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አረጋ ይርዳው በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የሜዳሊያና የፕሬዚዳንቱን ዋንጫ ሸልመዋል።

    ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ውጭ በደሴና በአዳማ የስልጠና መስኮችን በመለየት የተለያዩ ፕሮግራሞችን ለሕብረተሰቡ በመስጠት ላይ ይገኛል።

    ምንጭ፦ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    Semonegna
    Keymaster

    ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ለ13ኛ ጊዜ በሚያካሂደው ዓመታዊ የኪነ ህንጻ አውደ ርዕይ “ኪነ ህንጻና የከተማ ፕላን” በሚል መሪ ሀሳብ ከጥቅምት 8 ቀን እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓ.ም በብሔራዊ ቲያትር ይካሄዳል።

    አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በየዓመቱ የሚያካሂደው ዓመታዊ የኪነ ህንጻ አውደ ርዕይ ጥቅምት 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ይጀመራል።

    ለ13ኛ ጊዜ በሚካሄደው አውደ ርዕዩ “ኪነ ህንጻና የከተማ ፕላን” በሚል መሪ ሀሳብ በብሔራዊ ቲያትር ይካሄዳል።
    የዩኒቨርሲቲው የኪነ ህንጻና የከተማ ፕላን የትምህርት ክፍል ሃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ገብረጻዲቅ ለኢዜአ እንደገለጹት አውደ ርዕዩ የትምህርት ክፍሉ ተማሪዎች የሥራ ውጤቶቻቸውን የሚያቀርቡበት ነው።

    አውደ ርዕዩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደ ዘርፉ ኢንዱስትሪ ከመቀላቀላቸው በፊት ሥራዎቻቸውን ለኅብረተሰቡ፣ ለመንግስት ተቋማትና ለዘርፉ ባለድርሻ አካላት በማቅረብ ልምድ የሚቀስሙበት እንደሚሆን አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ተማሪዎቹ እርስ በእርስ እንዲማማሩም መልካም አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል።

    የተሻለ አቅም ያላቸው ተማሪዎች ወደ ሥራ ዓለም ሲገቡ በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት ከመቅረፍ አንጻር አስተዋጽዖ እንደሚያበረክቱም ነው አቶ ቴዎድሮስ ያስረዱት።

    አውደ ርዕዩ በየዓመቱ ሲካሄድ በአማካይ እስከ ሁለት ሺህ ሰው እንደሚጎበኘውና ዘንድሮም ከአንድ ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚጎበኙት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

    ALSO: EVENT: The 9TH ADDISBUILD: International Construction, Steel, Construction Machinery & Infrastructure Exhibition

    በአውደ ርዕዩ የዩኒቨርሲቲው የዘንድሮ የትምህርት ክፍሉ 60 ተማሪዎች የሥራ ፕሮጀክቶቻቸውን እንደሚያቀርቡና የተሻለ ሥራ ያቀረቡ ተማሪዎች የኢትዮጵያ የኪነ ህንጻ ባለሙያዎች ማኅበር (Association of Ethiopian Architects) በሚያዘጋጀው ዓመታዊ ውድድር እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል።

    በዚህ አውደ ርዕይ ሌሎች የመንግስትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንደሚሳተፉም ተናግረዋል።

    በብሔራዊ ቲአትር አዳራሽ የሚካሔደው አውደ ርዕይ ከጥቅምት 8 ቀን እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል።

    ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ከሚሰጣቸው የትምህርት ዘርፎች አንዱ “ኪነ ህንጻና የከተማ ፕላን” ሲሆን በዚሁ ትምህርት ዘርፍ ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ (bachelors degree) አስተምሮ ያስመርቃል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ

Viewing 4 results - 1 through 4 (of 4 total)