Search Results for 'ሂሩት ወልደማርያም'

Home Forums Search Search Results for 'ሂሩት ወልደማርያም'

Viewing 15 results - 1 through 15 (of 19 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር እስካሁን ድረስ አስር የማዕድን ምርመራ እና ሁለት የማዕድን ምርት ፈቃዶችን ሰጥቷል

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የማዕድናት ፍለጋ እና ልማት ለማካሄድ ፈቃድ ለጠየቁና የፈቃድ መውሰጃ መስፈርቶችን አሟልተው ለቀረቡ ለ12 የማዕድን ኩባንያዎች ፈቃድ ተሰጥቷል። ሁለቱ የምርት ፈቃዶች ሲሆኑ አስሩ የምርመራ ፈቃዶች ናቸው።

    የምርት ፈቃድ የተሰጣቸው የባዛልት እና የዕምነበረድ ማዕድን ምርት ሲሆኑ ሌሎች አስር ኩባንያዎች ደግሞ በደለል ወርቅ፣ ወርቅ እና መሰል ማዕድናት፣ ብረት፣ ማንጋኔዝ፣ ክሮማይት፣ ብር እና ጀምስቶን ማዕድናት ምርመራዎች ናቸው።

    ሁለቱ የምርት ፈቃዶች ለኢንቨስትመንት 270,186,310.00 (ሁለት መቶ ሰባ ሚሊዮን አንድ መቶ ሰማንያ ስድስት ሺ ሶስት መቶ አስር) ብር የተመዘገበ ካፒታልና ለ187 ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ሲሆን፥ የምርመራ ፈቃዶች ደግሞ 131,935,555.00 ብር (አንድ መቶ ሰላሳ አንድ ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ መቶ ሰላሳ አምስት ሽህ ዘጠኝ አምስት መቶ አምሳ አምስት) ብር የተመዘገበ ካፒታል እና በምርመራ ወቅት በድምሩ ለ293 ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ። ምርመራ ሂደታቸውን በስኬት አጠናቀው ወደ ሥራ ሲገቡም ከሥራ ዕድል ፈጠራ እስከ ውጭ ምንዛሬ ግኝትና ማዳን ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ።

    የምርመራ ፈቃዱ የውሉ ስምምነት ፊርማው ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ እንደ የፍቃድ ዓይነት ከ1 ዓመት እስከ 3 ዓመት የሚፀና ሆኖ፥ የፈቃድ ዘመኑም ሲጠናቀቅ በባለፈቃዱ ጥያቄ መሠረትና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሲያምንበት ሊታደስ የሚችል ነው።

    ስምምነቱን በፈቃድ ሰጪው መሥሪያ ቤት በኩል የፈረሙት ወ/ሮ ስመኝ ውቤ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ (የማዕድን ዘርፍ) ሲሆኑ፥ በባለፈቃዶቹ በኩል የፈቃድ ወሳጅ ኩባንያዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ናቸው። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኢትዮጵያ ለወጠነችው የኢንዱስትሪያዊነት መዋቅራዊ ሽግግር የኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚፈልገውን የማዕድናት ግብዓት ለሟሟላት በሁሉም ዓይነት የዘርፉ ሃብቶቻችን ላይ በስፋት እየተሠራ ይገኛል።

    ዛሬ ፈቃድ የወሰዱ ኩባንያዎች የምርትም ሆነ የምርመራ ሥራቸውን ሲያከናውኑ በፌደራልና በክልል የማዕድን አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን መሠረት አድርጎ በጥንቃቄ በትጋትና ቅልጥፍና በተሞላበት ሁኔታ በማዕድን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተቀባይነት ባለው የአሠራር ዘዴ ለማከናወን በስምምነቱ ውስጥ የተካተተ ሲሆን፥ ተመጣጣኝ ዕውቀት፣ ችሎታና ልምድ ላላቸው ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ቅድሚያ የሥራ ዕድል ለመስጠትና ለሥራው አስፈላጊ የሆነውን ሥልጠና የመስጠት ግዴታ አለባቸው።

    የአካካቢ ጥበቃን (environmental protection) በተመለከተ የሠራተኞቹን፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ጤንነትና ደህንነት በማይጎዳና ብክለት በማያስከትል መልኩ የምርት ሥራውን ለማከናወን ውል የተፈፀመ ሲሆን፥ ሥራውን ሲያቋርጥ በተፈጥሮ አካባቢ ላይ፣ በሰው ሕይወትና ንብረት እንዲሁም ዕፅዋት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ማናቸውም ቅሪቶችና ግንባታዎችን ያስወግዳል።

    የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የፕሮጀክቶችን ውልና አፈጻጸም በየጊዜው እየገመገመ በገቡት ውል መሰረት ሥራቸውን በአግባቡ የሚያከናውኑትን የመደገፍና የማበረታታት፣ በውላቸው መሠረት የማይሠሩትን ደግሞ ፍቃድ የመሰረዝና ሌሎች ሕጋዊ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።

    ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዜና ሳንወጣ፥ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የነበሩት ኢ/ር ታከለ ኡማ ነሐሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዕለቱ አስር ሹመቶችን በሰጡበት ጊዜ፥ የሚኒስቴሩ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ሳሙኤል ሁርካቶ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ሁነው ተሹመዋል። በዕለቱ የተሰጡት አስር ሹመቶች የሚከተሉት ናቸው።

    1. ዶ/ር ቀንዓ ያደታ – የመከላከያ ሚኒስትር
    2. ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቴዎስ – ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
    3. ዶ/ር ሳሙኤል ሁርካቶ – የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር
    4. ኢንጂነር ታከለ ኡማ – የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር
    5. አቶ ተስፋዬ ዳባ – ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
    6. አቶ ዮሐንስ ቧያለው – የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር
    7. አቶ ንጉሡ ጥላሁን – የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር
    8. አቶ እንደአወቅ አብቴ – የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር
    9. አቶ ፍቃዱ ጸጋ – ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
    10. ፕ/ር ሂሩት ወልደማርያም – በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ በመሆን መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅሕፈት ቤት አስታውቋል።

    የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ከ10,900 በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ

    አዲስ አበባ/ ጎንደር (ሰሞነኛ) – አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎችና መርሃግብሮች ያስተማራቸውን ተማሪዎች ሐምሌ 18፣ 2012 ቀን አስመርቋል።

    ዩኒቨርሲቲው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ በክብር እንግድነት በተገኙበት 5,642 ተማሪዎችን በቨርቹዋል አስመርቋል። ፕሬዝዳንቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ (COVID-19) ምክንያት ምርቃቱን በተንጣለለ አዳራሽ ማከናወን ባይቻልም ተመራቂ ተማሪዎች ትምህርታችሁን በማጠናቀቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

    ተመራቂዎች ቀጣዩ የሕይወት ምዕራፍ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት፣ ለሕዝብ እና ለሀገር ለውጥ ለማምጣት የሚተጉበት መሆኑን አመላክተው ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ እንዲከላከሉና ጥንቃቄ እንዳያጓድሉ እንዲሁም ችግር ፈቺ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ አሳስበዋል።

    የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና ዩኒቨርሲቲው ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 2,270 የሚሆኑት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የገፅ-ለገፅ ትምህርት (in-class and face-to-face education) ከመቋረጡ በፊት ጥናታቸውን ያቀረቡ ሲሆን 3,372 ተማሪዎች ደግሞ በትምህርት ዓመቱ መጨረሻ ማቅረባቸውን ገልፀዋል።

    ተመራቂዎቹ ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትና ወደሀገራችን መግባት በፊት በገፅ-ለገፅ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች፣ እና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የገፅ-ለገፅ ትምህርት ከተቋረጠ በኃላ በኦንላይን (online) ያስተማራቸው የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ናቸው።

    የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በዩኒቨርሲቲው 6 ኪሎ ግቢ ራስ መኮንን አዳራሽ የተከናወነ ሲሆን፥ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቀጥታ በማስተላለፍ ተመራቂ ተማሪዎች ከቤታቸው ሆነው በሥነ ሥርዓቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ መመቻቸቱ ተገልጿል።

    ቀደም ብሎ ከሁለት ሳምንታት በፊት (ሐምሌ 4 ቀን 2012 ዓ.ም.) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በዩኒቨርሲቲው የሳይንስ አምባ መሰብሰቢያ አዳራሽ 5,315 ተማሪዎችን አስመርቋል። ከተመራቂዎቹ መካከል ቀደም ብለው ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ለመመረቅ እየተጠባበቁ የነበሩ እንዲሁም ኤክስተርንሽፕ እና ፕሮጀክት ላይ የነበሩ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችና በኦንላይን ትምህርታቸውን የተከታተሉ የሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ይገኙበታል። ተመራቂዎቹ በየቤታቸው ሆነው የምረቃ ሥነ ሥርዓቱን በአማራ ቴሌቪዥን እንዲሳተፉ መደረጉን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን ገልፀዋል።

    የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተመራቂ ተማሪዎችን እንኳን ደስ አላችሁ እያለ የአገራችንና ሕዝባችንን ኑሮ የሚያሻሽሉ፣ ለወገን ፍቅር የሚሰጡ፣ ከድህነት የሚያላቅቁና ወደ ብልፅግና የሚያሻግሩ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ መልዕክቱን አስተላልፏል።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ

    Anonymous
    Inactive

    ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በዘጠኝ የትምህርት ዘርፎች የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር ይጀምራል
    መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ለ900 ተማሪዎች የትምህርት መከታተያ ሬድዮ እና ተንቀሳቃሽ ስልክ ድጋፍ አደረገ

    ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በመጪው የትምህርት ዘመን በዘጠኝ የትምህርት ዘርፎች የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር ለመጀመር ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ።

    የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፀጋዬ ደዮ በተቋሙ በተካሄደው የሥርዓተ ትምህርት ግምገማ ላይ እንዳሉት፥ በ2013 የትምህርት ዘመን በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ እንግሊዘኛ ቋንቋና ሥነ-ልሳን በተጨማሪ በሶሻል አንትሮፖሎጂ (social anthropology) ዘርፍ የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር ይጀምራል።

    እንዲሁም በጤና ሣይንስ ኮሌጅ የትምህርት ዘርፍ በሥነ ተዋልዶ፣ ሥነ ምግብ፣ ማኅበረሰብ ጤና፣ እናቶችና ሕፃናት ጤና የትምህርት ዘርፎች እንደሚከፈቱም አስታውቀዋል።

    ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በሚጀምራቸው ዘጠኝ የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር በእያንዳንዱ የትምህርት ዘርፍ እስከ 15 የሚደርሱ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምርና ይህም ዩኒቨርሲቲው አዲስ ከመሆኑ አንፃር ትልቅ ለውጥ መሆኑን ዶ/ር ፀጋዬ ገልጸዋል።

    የትምህርቱ ዓላማ ዩኒቨርሲቲው አቅምና ዕውቀትን ከማጐልበትና ከማሻገር በተጓዳኝ በጥናትና ምርምር የተደገፉ ችግር ፈቺ ሥራዎችን ለኅብረተሰቡ ለማመቻቸት ነው ብለዋል። በተለይ በትምህርት ጥራት ላይ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች እንዲወገዱ የትምህርት መርሃ ግብሩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም አመልክተዋል።

    የዩኒቨርሲቲው የውጭ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ዶ/ር የሺመቤት ቦጋለ በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው ለሚጀምረው የድኅረ ምረቃ መረሃ ግብር በቂ የሰው ኃይልና የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ማድረጉን አስታውቀዋል። መረሃ ግብሩ በትምህርት ተግባቦት ቴክኖሎጂ በቤተ ሙከራዎችና በኢንተርኔት በመታገዝ የ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥበት ቤተ መጽሕፍትን አደራጅተናል ብለዋል።

    የሚጀምረው መረሃ ግብር የተቋሙ መምህራንና ተማሪዎች አቅም ከማሳደግ ባለፈ ለሀገሪቱ ቋንቋና ባህል ትኩረት የሰጠ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርስቲው የኦሮምኛ ቋንቋ ዲፓርትመንት ኃላፊ ወ/ት ሁርሜ ደገፋ ናቸው።

    በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ለአንድ ቀን በተካሄደው የሥርዓተ ትምህርት ግምገማው ከ100 በላይ መምህራንና ተጋባዥ እንግዶች ተካፍለዋል።

    ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በ2009 ዓ.ም. ከተቋቋመ ጀምሮ በ33 የትምህርት ዘርፎች ከ4 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን ሲያስተምር መቆየቱም ተመልክቷል።

    ከከፍተኛ ትምህርት ዜና ሳንወጣ፥ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርታቸውን በሬዲዮ በመከታተል ላይ ለሚገኙ 900 ተማሪዎች የሬድዮ እና ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ድጋፍ አደረገ። ድጋፉ ከ700ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ 500 ሬዲዮኖችና 400 ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮች ናቸው።

    የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕ/ር ክንደያ ገብረሕይወት እንደገለጹት፥ ድጋፉ በመቀበያ ችግር ምክንያት የሬድዮ ትምህርት ፕሮግራም መከታተል ላልቻሉ ተማሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ድጋፉ የተደረገላቸው መቀሌን ጨምሮ በአምስት የክልሉ ወረዳዎች የሚገኙ ችግረኛ ተማሪዎች እንደሆኑ አመልክተው፥ በየቤታቸው ትምህርታቸውን በሬዲዮ ለመከታተል እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።

    የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳይቋረጥ እያደረገ ያለውን ጥረት ዩኒቨርስቲው የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል – ፕ/ር ክንደያ። ተማሪዎች በሬድዮ የሚተላለፍ ትምህርት በመከታተል ጥራትን ለማረጋገጥ እንደሚረዳም ፕ/ር ክንደያ አስረድተዋል።

    የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ባህታ ወልደሚካኤል በበኩላቸው፥ የተደረገው ድጋፍ በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል ላልቻሉ ተማሪዎች የሚውል መሆኑን ተናግረዋል። ከዓይደር ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነው የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ አይነስውሩ አለም ተስፋዬ በሰጠው አስተያየት የተደረገው ድጋፍ ከትምህርት መርሃ ግብሩ በተጨማሪ ወቅታዊ የዓለማችን ሁኔታ ለመከታተል የሚያስችለን ነው ብሏል። በተለይም ለአካል ጉዳተኞች የተለየ ድጋፍ ማድረግ ሰብአዊና ዜግነታዊ ኃላፊነት መሆኑን ተናግሯል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ

    Anonymous
    Inactive

    የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተማሪዎች የማካካሻ ትምህርት ተሰጥቷቸው የዓመቱን ትምህርት ያጠናቅቃሉ ― የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። የመግለጫው ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል።

    የ2012 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን አጋማሽ ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (COVID-19) በመከሰቱና በፍጥነት በመዛመቱ ምክንያት የዓለም ሀገራት የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ተቋርጦ መንግሥታት የዜጎችን ህይወት ለመታደግ ቅድሚያ ሰጥተው በመሥራት ላይ ይገኛሉ።

    እንደሚታወቀው ቫይረሱ ወደሀገራችን መግባቱ በምርመራ ከተረጋገጠበት ጀምሮ የሀገራችን መንግሥት ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፎ እየሠራ ይገኛል። በዚሁ መሠረት የቫይረሱን መስፋፋት ለመቀነስ ሲባል የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተማሪዎች የገጽ-ለገጽ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደቤተሰቦቻቸው መመለሳቸው ይታወሳል። ሆኖም ባሉበት ሆነው ከትምህርትና ንባብ እንዳይርቁ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል።

    የትምህርትና ስልጠና ማኅበረሰቡ በተደጋጋሚ ጊዜ ከትምህርትና ስልጠና ተቋማት መከፈት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን እያነሱ በመሆኑ ግንዛቤ ለመፍጠር ይህ ጋዜጣዊ መግለጫ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ተዘጋጅቷል።

    አሁን ባለው ሁኔታ ከዚህ ቀደም ሲካሄድ የነበረው የኦንላይን ትምህርት የሚቀጥል ሆኖ፥ ከጤና ሚኒስቴር የሚሰጡ መረጃዎችን ታሳቢ በማድረግ ሌሎች መንገዶችንም በቀጣይ የሚታዩ ይሆናል። ለዚህም ሁሉም ዜጎች የቫይረሱን መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ መሥራት ያስፈልጋል። ስለዚህ ተማሪዎችና መምህራን ባሉበት ሆነው ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ሌሎችንም እንዲያስተምሩ ይጠበቃል። ያም ሲሆን የስርጭት መጠኑ ሲቀንስ ቀጣይ የትምህርትና ስልጠና አካሄዶችን ይፋ የምናደርግ ይሆናል።

    የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የለይቶ ማቆያና ምርመራ ማዕከላት በመሆን በማገልገል ላይ ሲሆኑ፥ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚደረገውን እንቅስቃሴ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ እንዲሁም መጠነ ሰፊ የማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ሥራዎችን በመሥራት እያገዙም ይገኛሉ። ስለሆነም ተማሪዎችን ለመቀበል የተለያዩ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው መገንዘብ ያስፈልጋል። ለዚህም የትምህርትና ስልጠና ተቋማቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ሁሉ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ የሚቆዩ ይሆናል።

    በዚሁ መሠረት ወደፊት በሀገራችን የሚኖረውን የቫይረሱን ስርጭት መጠን ባገናዘበ መልኩ ከሚመለከተው አካል በሚሰጠን መረጃ መሠረት ነባር ተማሪዎችን ከተለመደው አካሄድ በተለየ ሁኔታ ለማስተናገድ የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ሥራ ተጀምሯል።

    ነባር ተማሪዎችን በተመለከተ፡-
    ሙሉ በሙሉ ኮርስ ያጠናቀቁ ተመራቂ ተማሪዎች (ለምሳሌ፡- የሕግ፣ የእንስሳት ሕክምና /veterinary medicine/፣ የሕክምና ተማሪዎች ወዘተ)፥ የመጀመሪያ ሴሚስቴር ያላጠናቀቁ ተማሪዎች፣ ሁለተኛ ሴሚስቴር ምንም ያልጀመሩ ተማሪዎች በባች/በደረጃ ተለይተዉ፣ የሴሚስቴሩን ኮርስ እስከ 25% እና 75% ያጠናቀቁ ተማሪዎች የቀሩ ምዕራፎች ተለይተዉ ማካካሻ ትምህርት በማመቻቸት እንዲያጠናቅቁ የሚደረግ ይሆናል።

    ተግባራዊ ለማድረግም በሁለት ዙር ተከፍለው ወደ ተቋማቱ እንዲገቡ በማድረግ የገጽ-ለገጽ ትምህርት ወስደዉ እንዲያጠናቅቁ የሚደረግ ሆኖ በአጭር ጊዜ ለማካካስ እንዲቻል የኦንላይን ትምህርቱም የሚቀጥል ትምህርት የሚሰጥበት አካዴሚክ ካሌንደር (academic calendar)፣ ቀናትና ሰዓታት ማሻሻያ የሚደረግባቸው ይሆናል። ተማሪዎች ወደዩኒቨርስቲዎች ሲመለሱም በቤተ-መፃሕፍት፣ በመማሪያ፣ መመገቢያ እና ማደሪያ ክፍሎች የሚኖራቸው ቁጥርም የተመጠነ ይሆናል።
    በዚሁ መሠረት፡-

    • ተመራቂ ተማሪዎች እና ተመራቂ ያልሆኑ 4ኛ ዓመትና ከዚያ በላይ ያሉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፉ ደረጃ 3፣ 4 እና 5 ሰልጣኞች በመጀመሪያዉ መርሃ-ግብር ወደ የተቋሞቻቸዉ ገብተዉ በቀጣይ የቫይረሱን የስርጭት መጠን ባገናዘበ መልኩ በሚገለፁ ቀናት ቀሪዉን ትምህርት እንዲያጠናቅቁ ይደረጋል።
    • የ1ኛ ዓመት፣ 2ኛ ዓመት እና ተመራቂ ያልሆኑ የ3ኛ ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፉ ደረጃ 1 እና 2 ሰልጣኞች በሁለተኛዉ መርሃ ግብር ወደ የተቋሞቻቸዉ ገብተዉ በቀጣይ የቫይረሱን የስርጭት መጠን ባገናዘበ መልኩ በሚገለፁ ቀናት ቀሪዉን ትምህርት እንዲያጠናቅቁ ይደረጋል።
    • የ2013 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን አዲስ ገቢ ተማሪዎች እና የነባር ተማሪዎች ቀጣይ ዓመት ትምህርቶች የማካካሻ ፕሮግራሞች ከተካሄዱ በኃላ በቀጣይ የሚገለፅ ይሆናል።

    በዚሁ አጋጣሚ ተማሪዎች ወደትምህርት የሚመለሱበት ዕለት ተወስኖ እስከሚገለፅ ድረስ ከቫይረሱ ራሳቸውን በመከላከል ባሉበት ሆነው ንባባቸውን እንዲቀጥሉና በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ እንዲሁም በአከባቢያቸው ያሉ ወገኖችን እንዲያስተምሩ መልዕክት እናስተላልፋለን።

    ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም.
    ሂሩት ወልደማርያም (ፕ/ር)
    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር

    ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም

    Anonymous
    Inactive
    • በሥራ ላይ ያለው ሥርዓተ-ትምህርት በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በአዲስ ሥርዓተ-ትምህርት ይቀየራል።
    • በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ይበልጥ ተቀናጅቶ መሥራት አስፈላጊ ነው።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በሥራ ላይ ያለውን ሥርዓተ-ትምህርት በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በአዲስ ሥርዓተ-ትምህርት ለመቀየር የሚያስችሉ ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

    በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እሸቱ አስፋው በጉዳዩ ዙሪያ በተዘጋጀ የባለሙያዎች ምክክር መድረክ ላይ እንደገለፁት ከ2012-2014 የትምህርት ዘመን በሥራ ላይ ያለውን ሥርዓተ-ትምህርት ለመቀየር የአስር ዓመታት ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጅቷል።

    በሥራ ላይ ያለውን ሥርዓተ-ትምህርት መቀየር ያስፈለገው በፍኖተ ካርታው ምክረ-ሃሳቦች መሠረት ችግሮች ስላሉበት ነው። በመሆኑም በመጭዎቹ ዓመታት በአዲስ የሚተካው ሥርዓተ-ትምህርት የተማሪዎችን ሥነ-ምግባር ጨምሮ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚፈታ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቃዋል።

    በአውደ-ጥናቱም ከሀገሪቱ ሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የተውጣጡ የትምህርት ቢሮ ባለሙያዎች፣ የሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅት ሃላፊዎች፣ ከሁለተኛና ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ መምህራን፣ የመምህራን ኮሌጆችና ከአምስቱ የመምህራን ማሰልጠኛ ዩኒቨርስቲዎችና ሌሎችም ባለድርሻዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

    በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅት ባለሙያ የሆኑት አቶ ሰለሞን ወርቁ በበኩላቸው ሥርዓተ-ትምህርቱ እየተዘጋጀ ያለው ከፍኖተ ካርታው በተገኙ ምክረ ሃሳቦችና ጥቆማዎች (recommendations an suggestions) እንዲሁም የካንብሪጅ ኢንተርናሽናል አሰስመንትን (Cambridge Assessment International Education) ጨምሮ በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻዎች በተገኙ ምክረ ሃሳቦችና ተጨማሪ አስተያየት መሠረት ነው።

    በምክክር መድረኩም የሥርዓተ-ትምህርት ማዕቀፍ፣ የእያንዳንዱ የትምህርት ዓይነት መርህ አቅጣጫ (position papers) እና ሌሎችም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አቶ ሰለሞን መግለፃቸውን የትምህርት ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዘግቧል።

    ከሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ሁኔታ ጋር በተያያዘ ደግሞ፥ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ይበልጥ ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ።

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከሰው ሃብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት፣ ከሌሎች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ጋር በዘርፉ የተከናወኑ የለውጥ ሥራዎች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሒዷል።

    በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም “በዘርፉ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን በተሟላ ሁኔታ ተተገብረው ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሁም መልካም ሥነ ምግባር የተላበሱ ምሩቃን አፍርተን ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን እያለፍን የሀገራችንን የማስፈጸም አቅም በመገንባት በብልጽግና ከፍታ ላይ ለማድረስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተን እንሠራለን” ብለዋል።

    ሚኒስቴሩ በትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ጥናት ላይ የተቀመጡ ምክረ ሐሳቦችን መነሻ በማድረግ በነባሩ የትምህርት ሥርዓት ላይ ያለውን ጉድለት ለመሙላት እና ለማሻሻል አዳዲስ የለውጥ ኃሳቦችን በማካተት ከ2012 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ትግበራ ላይ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፥ ከነዚህም መካከል የከፍተኛ ትምህርትን ሥርዓተ ትምህርት የማሻሻል፣ የትምህርት አሠጣጥ ሥነ-ዘዴዎቹንና የትምህርቶቹንም ይዘት የመከለስና የኮርስ ካታሎግ (course catalog) የማዘጋጀት፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችንን በተልዕኮና በልህቀት ለይቶ የማደራጀት እንዲሁም አዳዲስ የሕግና የአሠራር ማዕቀፎችን የማውጣትና ነባሮቹንም የመከለስ ሥራዎች ይገኙበታል ብለዋል።

    እንደ ፕሮፌሰር ሂሩት ገለፃ፥ የምክክር መድረኩ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ሚኒስቴሩ በሚያከናውናቸው የለውጥ ሥራዎች ላይ የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ስለሚያምንና በተለይም በቂ ግንዛቤ ያለውና የተቀናጀ የባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ ለለውጥ ሥራዎቻችን ስኬት ቁልፍ ስለሆነ ነው ሲሉ አስቀምጠዋል።

    ለሁለት ቀናት በቆየው የምክክር መድረክ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ጉዳዮች፣ በፍኖተ ካርታ ምክረ-ሃሳብ መሠረት በከፍተኛ ትምህርትና በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሴክተር የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ እንዲሁም በሰላማዊ መማር ማስተማር ዙሪያ የተሠሩ አንኳር ሥራዎች፣ ተግዳሮቶችና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ቀርበው ውይይት ይካሄዳል።

    በመጨረሻም የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የሰው ሃብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የልህቀት ማዕከል የሥራ እንቅስቃሴን የሚጎበኙ ይሆናል።

    ምንጮች፦ የትምህርት ሚኒስቴር/ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 

    ሥርዓተ-ትምህርት

    Anonymous
    Inactive

    የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ቅበላ ጊዜ ይፋ ተደረገ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ቅበላ ጊዜን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ይፋ አደረገ። ሚኒስቴሩ በ2012 የትምህርት ዘመን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሠላማዊ የመማር ማስተማር እንዲኖር የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን እንዳደረገ መግለጫ ሰጥቷል።

    በተከለሰው አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሠረትም የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች የመጀመሪያ ሴሚስተር በአራት ቅበላ ዓይነቶች እንደሚሆን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።

    በተፈጥሮ ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ሳይንስ በመምህርነት፣ በማኅበራዊ ሳይንስና በማህበራዊ ሳይንስ በመምህርነት የቅበላ ክፍል በመምህርነት የተከፈለ ነው ብለዋል።

    በሁለተኛው ወሰነ ትምህርት ደግሞ የመጀመሪያውን ሴሚስተር ውጤት መሠረት በማድረግ በአምስት የሙያ መስኮች ማለትም በሕግ፣ ሕክምናና የጥርስ ሕክምና፣ ፋርማሲ፣ የእንስሳት ሕክምና እና ምሕንድስና ናቸው።

    ሌሎቹ የትምህርት መስኮች ምደባ የሚደረገው ከአንድ ዓመት የትምህርት ቆይታ በኋላ ነው። በ‹ቪዲዮ ኮንፈረንስ› ዝግጅት ግምገማ በማድረግ የመምህራን ቅጥር እንደሚካሄድም ተጠቅሷል።

    አዳዲስ ፟ዩኒቨርሲቲዎችም ለተማሪ ቅበላ ዝግጁ እንደሆኑ ተጠቁሟል። የቅበላው ጊዜም ለነባር ተማሪዎች ከመስከረም 5 እስከ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. እየተካሄደ ይገኛል ነው የተባለው። አዲስ ለሚገቡ ተማሪዎች ከመስከረም 25 እስከ 29 ቅበላው ይካሄዳል ተብሏል። ጥቅምት 03 ቀን 2012 ዓ.ም. ደግሞ ሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት የሚያስጀምሩ ይሆናል ነው የተባለው።

    አዲስ ተማሪዎች በክልሉ ወይም በየወረዳው ስለመብቶቻቸውና ግዴታዎቻቸው ስልጠና ይሰጣቸዋል። ወላጆችና ተማሪዎች በሚፈርሙት ውል መሠረት ወደ ዩኒቨርሲቲ ይገባሉ።

    142 ሺህ 943 ተማሪዎችን የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ተቀብለው እንደሚያስተምሩና የሴት ተማሪዎች ብዛት 43 ከመቶ እንደሆነ ተገልጿል።

    የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ዝውውር የሚጠይቁት በጤና እክል ምክንያት ብቻ እንደሆነም ተጠቁሟል።

    ከተፈጥሮ ሳይንስ ወደ ማኅበራዊ ሳይንስና ከማኅበራዊ ሳይንስ ወደ ተፈጥሮ ሳይንስ ዝውውር ማድረግ ይቻላል፤ ዝውውር ማድረግ የሚቻለው ግን የየመስኮቹን የማለፊያ ውጤት ሲያሟሉ እንደሆነ ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ተናግረዋል።

    ምንጭ፦ ዋልታ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    Anonymous
    Inactive

    አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ 1,859 ተማሪዎችን አስመረቀ
    —–

    አዳማ (ሰሞነኛ) – አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 353 ሴት ተማሪዎችን ጨምሮ 1859 ተማሪዎችን አስመረቀ።

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ምሩቃኑ በተማሩበት መስክ ጠንካራ ሠራተኛ በመሆን የአገልጋይነት ስሜት በመላበስ የተጣለባቸውን አደራ እንዲወጡ አሳስበዋል።

    የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸውም በዩኒቨርሲቲ የሚታዩ በዘርኝነት የሚከሰቱ መጠፋፋቶች ኋላ ቀር አስተሳሰብ በመሆናቸው ይህ ትውልድ መፍቀድ የለበትም ብለዋል።

    ናዝሬት የቴክኒክ ኮሌጅ በሚል ከ20 ዓመታት በፊት የተቋቋመውና ከ14 ዓመታት በፊት ወደ ዩኒቨርሲቲነት ያደገው አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በልዩ የመግቢያ ፈተና ተማሪዎችን የሚቀበል ሲሆን፥ በየዓመቱ 5,000 የሚሆኑ ትምህርት ፈላጊዎች የመግቢያውን ልዩ ፈተና ቢፈተኑም ፈተናዉን አልፈው ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ለለማር ዕድሉን የሚያገኙት 1,500 ተማሪዎች ብቻ መሆናቸው ተገልጻል።

    ዩኒቨርሲቲው የምርምር እና የጥናት የልህቀት ሥራዎችን የሚያካሂድበት 8 የልህቀት ማዕክላት (center of excellence) እንዳሉትና፤ በዩኒቨስቲው የሚገኘው ቤተ ሙከራ (laboratory) ለዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ጭምር አገልግሎቱን እንደሚሰጥ ተነግሯል።

    ምሁራን በዘርፉ ላይ ምርምር እና ጥናት ሊያካሂዱበት የሚችል በዓይነቱ ለየት ያለ የምርምር ማዕከል (research center) በዩኒቨርሲቲው ውስጥ እየተገነባ እንደሚገኝም ተነግሯል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    Anonymous
    Inactive

    ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ሐምሌ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ አስመረቀ

    የትምህርት ጥራትን ማጠናከርና ማሻሻል ቀጣይነት ያለዉ ሥራ ስለሆነ በዚህ ጉዳይ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ማህበረሰቡ የበኩላቸዉን ሃላፊነት ሊወጡ ይገባል ተባለ።

    ይህን ያሉት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ሐምሌ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ ባስመረቀበት ወቅት በክብር እንግድነት ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

    ሚኒስትሯ አክለውም ከፍተኛ ትምህርትን የማስፋፋት፣ የጥራትና ፍትሀዊነት ሂደት ዉስጥ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዓይነተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ። በተለይም ተደራሽነትን ከማስፋት አንጻር መንግሥት ባዘጋጀዉ የሕግ ማዕቀፍ በመደገፍ ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቋቁመዉ ለዜጎች ሰፊ የትምህርትና የሥራ ዕድል ከፍተዋል። እነዚህ ተቋማት በትምህርት ፈላጊዎች እንደጥሩ አማራጭ ስለታዩና ተቀባይነትም ስላገኙ በአሁኑ ወቅት በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ብዛት ከ200 በላይ ደርሷል፤ በዚህም በከፍተኛ ትምህርት ከሚማሩት ጠቅላላ ተማሪዎች ውስጥ ከ20 በመቶ በላይ የሚሆኑትንም ያስተናግዳሉ ብለዋል።

    ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ለ36ኛ ጊዜ ተማሪዎቹን ባስመረቀበት በዚህ ዝግጅት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በማኅበረሰብ አገልግሎትና በጥናትና ምርምር ላይ እያሳዩ ያሉት መልካም ጅምር ሊበረታታ ይገባል ሲሉ ፕሮፌሰር ሂሩት ጨምረው ተናግረዋል።

    በመጨረሻም ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም እንዳሉት፥ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገ በሄደ ቁጥር የሚፈለገዉ የሰዉ ኃይልም በቁጥርና በጥራት እየጨመረ ይሄዳል። ለዚህም የወቅቱን የእድገት እርምጃና የሥራ ገበያ ፍላጎት የሚመጥን የማስተማር፣ የምርምርና ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ማስፋፋት አስፈላጊ ነው ብለዋል። አክለውም፥ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይሄንን ተገንዝበው የፕሮግራም አድማሳቸውንና አገልግሎታቸውን የአገሪቱን የአሁንና መፃኢ የሰው ኃይል ፍላጎት ባገናዘበና ጥራቱን ባስጠበቀ መልኩ በማሻሻል አጋርነታቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉ አስምረውበታል።

    ሚኒስትሯ በቆይታቸውም ከፍተኛ ውጤት ላስመዘጉ ተመራቂዎች የሜዳሊያና ዋንጫ፣ እንዲሁም የሚድሮክ ኢትዮጵያ ግሩፕስ ባለቤት በሆኑት በሼህ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስም በተሰየመው የሕይወት ዘመን አገልግሎት ሽልማት ዘርፍ ተሸላሚ ለሆኑ 4 ግለሰቦች የምስክር ወረቀት አበርክተዋል፡፡

    ዶ/ር አረጋ ይርዳዉ የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የሚድሮክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በበኩላቸው፥ ተማሪዎች በቆይታው ያካበበቱትን ዕውቀትና ልምድ ለአገራቸው በሚጠቅም መልኩ ሊያውሉት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

    ዩኒቨርሲቲው በአገራችን የመጀመሪያው የግል ዩኒቨርሲቲ በመሆን በመንግሥት ዕዉቅና ተሰጥቶት ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎችና መስኮች ለዜጎች ተደራሽነትንና ህትሃዊነትን ለማስፋት በሚደረገው ጥረት የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር

    Anonymous
    Inactive

    ክብርት ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምርቃት በዓል ላይ ያስተላለፉት መልዕክት
    —–

    ክብርት ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የምርቃት በዓል ላይ በመገኘት ለ2011 ዓ.ም. ምሩቃን (Class of 2019) “የዓመታት ልፋታችሁ ውጤት ለሚታዩበት ዕለት እንኳን በቃችሁ፤ እንኳን ደስ አላችሁ” በማለት የደስታ መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ምሩቃኑ ሚዛናዊና ምክንያታዊ በሆነ አስተሳሰብ በመመራት አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ፈታኝ ሁኔታ ለመታደግ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ፕሮፌሰር ሂሩት ጥሪ አቅርበዋል።

    መማር ማለት እውቀት መሰብሰብ ብቻ አይደለም ያሉት ሚኒስትሯ፥ የተማረ ሰው በእያንዳንዱ በሚያጋጥመው ነገር ላይ ጠለቅ ያለ ዕይታ ያለውና ለሁሉም ነገር በቂ ምርምር በማድረግ ሚዛናዊና ምክንታዊ መፍትሄ የሚፈልግ በመሆኑ ተመራቂ ተማሪዎች የቀሰሙትን ዕውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመቀየር ለአገርና ለወገናቸው እንዲሰሩበትም አስገንዝበዋል።

    የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሃይማኖት ዲሳሳ በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው ከ3ኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች (3rd Generation Universities) አንዱ ሲሆን ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ 2,711 ተማሪዎችን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ማስመረቁን ገልጸዋል።

    ፕሬዚዳንቱ ዘንድሮ በዩኒቨርሲቲው ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ ችግሮች ተቋቁሞ የመማር ማስተማር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን በአግባቡ በመፈፀም ለዚህ እለት እንዲበቃ ትብብርና ድጋፍ ላደረጉት የአካባቢው ህብረተሰብ፣ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ፣ የጸጥታ ኃይሎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

    ተመራቂ ተማሪዎችም በቀሰሙት ዕውቀት እና ክህሎት ህብረተሰባቸውን ከማገልገል ባሻገር ለሀገሪቱ ሰላምና እድገት መረጋገጥ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    null

    Semonegna
    Keymaster

    የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን አስመርቀዋል
    —–

    አዲስ አበባ – የተለያዩ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠኗቸውን ተማሪዎቻቸውን ሰኔ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. አስመርቀዋል።

    በዕለቱ ተማሪዎቻቸውን ካስመረቁ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥም የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ፣ መቱ ዩኒቨርሲቲ፣ ዲላ ዩኒቨርሲቲ እና አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ይገኙበታል።

    የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 313 ተማሪዎቹን በዕለቱ አስመርቋል። ከተመረቁት ውስጥም 1 ሺህ 112 በቅድመ ምረቃ መርሃ ግብር (በመጀመሪያ ዲግሪ) ያስመረቀ ሲሆን፥ 201 ተማሪዎችን ደግሞ በድህረ ምረቃ መርሃ ግብር ነው ያስመረቀው።

    ጅማ ዩኒቨርሲቲም በዕለቱ በመጀመሪያ ዙር ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 683 ተማሪዎቹን አስመርቋል። ከእነዚህም ውስጥ 341 በድህረ ምረቃ ሲሆን፥ 1 ሺህ 11 ደግሞ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል።

    በተመሳሳይ ዲላ ዩኒቨርሲቲም በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 4 ሺህ 726 ተማሪዎቹን በዕለቱ አስመርቋል። በዲላ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የምረቃ በዓል ላይ የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስተር ዲኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፥ በዘንድሮው ዓመት በመላው ሀገሪቱ ከ175 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንደሚመረቁ አንስተዋል። ተመራቂ ተማሪዎች ለሀገራቸው የሚሰሩ ሊሆኑ እንደሚገባም ፕሮፌሰር አፈወርቅ መልእክት አስተላልፈዋል። ዲላ ዩኒቨርሲቲ በዕለቱ ካስመረቃቸው ተማሪዎቹ ውስጥ 500 ተማሪዎችን በሁለተኛ ዲግሪ ነው ያስመረቃቸው።

    ወለጋ ዩኒቨርሲቲም በዕለቱ በተለያየ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 3 ሺህ 682 ተማሪዎቹን በዕለቱ አስመርቋል። ከተመረቁት ተማሪዎች ውስጥ 2 ሺህ 139 ሴቶች ሲሆኑ 1 ሺህ 543 ደግሞ ወንዶች መሆናቸው ተገልጿል። በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው 295 ተማሪዎችን በሁለተኛ ዲግሪ ያስመረቀ2 ሲሆን፥ 8 ተማሪዎችን ደግሞ በ3ኛ ዲግሪ ወይም በዶክትሬት ዲግሪ አስመርቋል።

    መቱ ዩኒቨርሲቲም በተለያየ የትምህርት መሰኮች ሲያሰለጥናቸው የነበረውን ከ2 ሺህ 300 በላይ ተማሪዎቸ በዛሬው ዕለት አስመርቋል። በምረቃ ሥነ-ስርዓት ላይ የተገኙት ግብርና ሚኒስተር ዲኤታና የመቱ ዩኒቨርሰቲ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሳኒ ሬዲ መንግስት ለሰው ሀብት ልማት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥው እየሠራ ባለበት መመረቃቸውንና ከተመራቂ ተማሪዎች የሚጠበቀው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ተካልኝ ቃጄላ በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት ብዙ ፈታኝ የሆኑ የውስጥና የውጭ ተግዳሮቶችን አልፎ ለዚህ መብቃቱን አስታውሰዋል።

    በተመሳሳይ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ 2 ሺህ 714 ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መርሓ ግብሮች አስመርቋል። ከነዚህ ውስጥ 930 ሴት ተመራቂዎች መሆናቸው ታውቋል። ዩኒቨርሲቲው አሁን ለ6ኛ ጊዜ እያስመረቀ ሲሆን ከተመሰረተበት ከ2004 ዓም ጀምሮ አጠቃላይ 12 ሺ 450 ተማሪዎችን አስመርቋል። በዕለቱ በተካሄደው የምረቃ ሥነ-ስርዓት ላይ የሳይንስ እና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያምን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ተገኝተዋል። ፕሮፌሰር ሂሩት ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ እንድትወጣ የተማረው ሀይል ዋነኛ አካል ነው ብለዋል።

    ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

    Semonegna
    Keymaster

    በሦስት መስኮች ዩኒቨርሲቲዎቹን መደልደል ያስፈለገው፥ እስካሁን የትምህርት ተቋማቱ በሁሉም የትምህርት ዘርፎች ለማስተማር ያደረጉት ጥረት እምብዛም ውጤታማ ስላልነበር እንደሆነ ተነግሯል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር፣ የቲቺንግና የፖሊ ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ ተብለው ለሦስት ተከፍለው እንዲሠሩ የሚያደርግ ጥናት እያለቀ መሆኑንና በጥናቱ ውጤትም ላይ በቅርቡ ውይይት እንደሚደረግ፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ሂሩት ወልደማርያም (ዶ/ር) ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለጹ። ምደባው ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል።

    ዩኒቨርሲቲዎችን በተልዕኮና በትኩረት አቅጣጫ የመደልደል ነገር በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተመልክቷል ያሉት ሚኒስትሯ፥ ለምርምር የተሻለ የመሠረት ልማትና የሰው ኃይል ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች የጥናትና ምርምር ዩኒቨርሲቲ መደብ ውስጥ እንደሚገቡና በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ ፕሮግራሞችንም እንደሚሰጡ አስረድተዋል። የንድፈ ሐሳብና ተግባራዊ ትምህርት አጣምረው የሚሰጡ ፖሊ ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲዎች መደብ ሥር የሚገቡት ለተግባር ትምህርት የተሻለ የመሠረተ ልማት ዝግጅት ያላቸው ይሆናሉ ተብሏል። ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ ሠልጣኞችን እንዲያፈሩና ለቴክኒክና ሙያ ተቋማትም የበቁ መምህራንን እንዲያወጡ ይጠበቅባቸዋል ያሉት ዶክተር ሂሩት ናቸው። የተቀሩት የማስተማር ተግባር (ቲቺንግ) ላይ የሚያተኩሩ መርሀ ግርብሮች ላይ የሚያተኩሩ ዩኒቨርሲቲዎች ሆነው እንደሚቀጥሉም ታውቋል።

    በሦስት መስኮች ዩኒቨርሲቲዎቹን መደልደል ያስፈለገው፥ እስካሁን የትምህርት ተቋማቱ በሁሉም የትምህርት ዘርፎች ለማስተማር ያደረጉት ጥረት እምብዛም ውጤታማ ስላልነበር እንደሆነ ተነግሯል።

    ሰባት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና STEMpower ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ

    “ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በማስተማሩም፣ በምርምሩም፣ በቴክኖሎጂውም፣ በግብርናውም፣ በሁሉም ዘርፎች ነው የሚያስተምሩት። ይህ ደግሞ ውጤታማ ሊሆኑ በሚችሉበት መስክ እንዳይሠሩና ሀብትም እንዲበታተን አድርጓል” ያሉት ሚኒስትሯ፥ ድልድሉም ዩኒቨርሲቲዎቹ እንዳላቸው የመሠረት ልማት ዝግጅትና ያሉበት አካባቢ ከሚሰጣቸው መልካም አጋጣሚ አንፃር እየታየ ነው ብለዋል።

    እንደ ላሊበላና አክሱም ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች አርኪዮሎጂ ላይ ያተኮሩ የልህቀት ማዕከላት (center of excellence) ቢሆኑ የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኙ፣ በግብርና ላይ ተሞክሮና ታሪክ ያላቸው እንደ ሐሮማያ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በግብርና ውጤታማ የሆነ ባለሙያዎች ማፍራት እንደሚችሉ አስረድተዋል። “ሁሉም ላይ እንሥራ ሲሉ ግን ችግር ነው። በሁሉም ዘመናዊ ማሽኖችን፣ የምርምር ግብዓቶችን፣ ሪፈራል ሆስፒታሎችን መገንባትና ማሟላት አይቻልም፣ የአገርም ሀብት ይባክናል” ብለዋል።

    ምንጭ፦ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    ዩኒቨርሲቲዎች በሦስት መስኮች

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – STEMpower የተሰኘ መቀመጫውን USA (ሳሌም፥ ማሳቹሴትስ፣ አሜሪካ) ያደረገ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሒሳብ ትምህርቶችን በዩኒቨርሲቲዎች እየረዳ የሚገኝ ሲሆን በአገራችን 13 ማዕከላትን ከፍቶ በትብብር እየሠራና እየረዳ ይገኛል።

    ድርጅቱ የድጋፍ አድማሱን በማስፋት በኢትዮጵያ ተጨማሪ 10 ማዕከላትን (ሰባት ማዕከላትን በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሶስቱን በተለያዩ ከተሞች እ.አ.አ. በ2019) ለመክፈት ከኢፌዴሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከሰባቱ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የትብብር ስምምነት የካቲት 14 ቀን 2011ዓ.ም. ተፈራርመዋል።

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ሂሩት ወልደማርያም (ፕ/ር) STEMpower ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርቶችን ለማበልጸግ እያደረገ ያለውን ትብብር በማመስገን፥ ዩኒቨርሲቲዎችም ዕድሉን በመጠቀም በአግባቡ ማዕከላቱን ማሳለጥ እንደሚጠበቅባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

    አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተማሪያ ክፍሎቹ ውስጥ ዲጂታል ሰሌዳዎችን መጠቀም ጀመረ።

    የሳንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር) በበኩላቸው ለሰባቱ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲአዲግራት ዩኒቨርሲቲአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲጅማ ዩኒቨርሲቲ እና ወሎ ዩኒቨርሲቲ) ማዕከሉን በመጠቀም በአካባቢዎቻቸው ያሉትን የማኅበረሰብ ችግሮች መፍታት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

    የSTEMpower አስተባባሪ ዳይሬክተርና ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ቅድስት ገብረአምላክ፥ “STEMpower ከየት ወዴት?” በሚል ርዕስ ከድርጅቱ አመሠራረት ጀምሮ ዓላማውን፣ አሁን ያለበት ሁኔታ እና የወደፊት ዕቅድ አጭር ማብራሪያ ለተሳታፊዎቹ አቅርበዋል። ለወደፊትም ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በስፋት እንደሚሠሩ ፣ በ2040 የበለጸገች ኢትዮጵያን ማየት እንደሆነ ገልጸዋል።

    አገራችን ኢትዮጵያ የራሷን የሆነ ጥንታዊ ታሪክና ባህል ያላት አገር እንደመሆኗ ድርጅቱ በማኅበራዊ ሳይንስ ላይም ትኩረት እንዲያደርግ ከተሳታፊዎቹ አስተያየት ተሰንዝሯል።

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ማዕከሎቹ በከፍተኛ ትምህርት እና በሳይንስ ትምህርቶች አከባቢ የሚስተዋሉትን ችግሮች በመቅረፍ የአገሪቱን ብልጽግና ከማረጋገጥ ረገድ መልካም ሁኔታ እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    STEMpower


    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የሰጣቸው ምሁራን በመማር ማስተማሩ፣ በጥናትና ምርምር፣ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አገልግሎት እንዲሁም በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት በዩኒቨርሲቲው ሴኔት ሊጅስሌሽን መሰረት የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ስለተወጡ ነው።

    አዲስ አበባ (አ.አ.ዩ)– በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚመለከታቸው የትምህርት ክፍሎች ተመርመሮ፣ በየኮሌጆች አካዳሚክ ጉባዔዎች ተፈትሾ፣ አጥጋቢ በሆነ መልኩ ተገመግሞ በዩኒቨርሲቲው ሴኔት ታይቶ እና ይሁንታ አግኝቶ የቀረበለትን መረጃ የተመለከተው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ ጥር 26 ቀን 2011 ዓ.ም. የዶ/ር ሂሩት ወልደማርያምን፣ የዶ/ር ተፈሪ ገድፍን፣ የዶ/ር ምሩፅ ግደይን፣ የዶ/ር ሃጎስ አሸናፊን፣ የዶ/ር መረራ ጉዲናን እና የዶ/ር ጌታቸው አሰፋን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አፅድቋል። ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የተሰጣቸው 6 መምህራን አጭር መግለጫ እንደሚከተለው ነው።

    1. ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም የመጀመርያ፣ ሁለተኛ እና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በቋንቋ ጥናት (Linguistics) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።

    ፕሮፌሰር ሂሩት በግላቸውና ከሙያ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በጥናትና ምርምር የተሰሩ ከ6 በላይ ጥናታዊ ፅሁፎችን በታወቁ ሀገራዊና አለምዓቀፋዊ መፅሄቶች ላይ ለህትመት በማብቃት ከሚጠበቅባቸው 35 የህትመት ነጥብ 42 ነጥብ አስመዝገበዋል። በተጨማሪም በተለያዩ የዩኒቨርሲቲ ቦታዎች ላይ አገልግሎ የሰጡ ሲሆን ብዙ የማህበረሰብ አገልግሎቶችና የሙያ ነክ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሂዩማኒቲስ፣ የቋንቋዎች ጥናት፣ የጆርናሊዝምና የኮሚዩኒኬሽን ኮሌጅ የቋንቋ ጥናት ትምህርት ክፍል ባልደረባ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

    2. ፕሮፌሰር ተፈሪ ገድፍ የመጀመርያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ዲግሪያቸውን በፋርማሲ (Pharmacy) ትምህርት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በፋርማሲ ትምህርት በጀርመን ከማርቲን ሉተር ሐለ-ቪተንበርግ ዩኒቨርሲቲ (Martin Luther University Halle-Wittenberg) አግኝተዋል።

    ፕሮፌሰር ተፈሪ በግላቸውና ከሙያ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በጥናትና ምርምር የተሰሩ ከ20 በላይ ጥናታዊ ፅሁፎችን በታወቁ ሀገራዊና አለምዓቀፋዊ መፅሄቶች ላይ ለህትመት በማብቃት ከሚጠበቅባቸው 35 የህትመት ነጥብ 104.56 ነጥብ አስመዝገበዋል። በተጨማሪም በተለያዩ የዩኒቨርሲቲ ቦታዎች ላይ አገልግሎ የሰጡ ሲሆን ብዙ የማህበረሰብ አገልግሎቶችና የሙያ ነክ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ፕሮፌሰር ተፈሪ ገድፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጤና ሳይንስ ኮሌጅ የፋርማሲ ትምህርት ክፍል መምህር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

    ቪዲዮ፦ ኢትዮጵያ ውስጥ ትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚከፈቱ የጫት እና የሁካ ቤቶች ተማሪዎች ለሱሰኝነት እየዳረጓቸው ነው

    3. ፕሮፌሰር ምሩፅ ግደይ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በባዮሎጂ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በባዮዳይቨርሲቲ (Biodiversity) ከ ከስዊድን የእርሻ ዩኒቨርሲቲ (Swedish University of Agricultural Sciences)፣ እንዲሁም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ቦታኒካል ሳይንስ (Botanical Science) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።

    ፕሮፌሰር ምሩፅ በግላቸውና ከሙያ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በጥናትና ምርምር የተሰሩ ከ18 በላይ ጥናታዊ ፅሁፎችን በታወቁ ሀገራዊና አለምዓቀፋዊ መፅሄቶች ላይ ለህትመት በማብቃት ከሚጠበቅባቸው 35 የህትመት ነጥብ 56 ነጥብ አስመዝገበዋል። በተጨማሪም በተለያዩ የዩኒቨርሲቲ ቦታዎች ላይ አገልግሎ የሰጡ ሲሆን ብዙ የማህበረሰብ አገልግሎቶችና የሙያ ነክ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ፕሮፌሰር ምሩፅ ግደይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአክሊሉ ለማ የፓቶባዮሎጂ ኢንስቲትዩት (Aklilu Lemma Institute of Pathobiology) በእንዶድና ሌሎች የመድሃኒት ዕጽዋት የምርምር ማዕከል (Endod and Other Medicinal Plants Research Unit) ባልደረባ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

    የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ

    4. ፕሮፌሰር ሃጎስ አሸናፊ የእንስሳት ህክምና ዲግሪያቸውንና የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በቤልጄም ከሉቨን የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ (Catholic University of Leuven) አግኝተዋል።

    ፕሮፌሰር ሃጎስ በግላቸውና ከሙያ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በጥናትና ምርምር የተሰሩ ከ24 በላይ ጥናታዊ ፅሁፎችን በታወቁ ሀገራዊና አለምዓቀፋዊ መፅሄቶች ላይ ለህትመት በማብቃት ከሚጠበቅባቸው 35 የህትመት ነጥብ 94.06 ነጥብ አስመዝገበዋል። በተጨማሪም በተለያዩ የዩኒቨርሲቲ ቦታዎች ላይ አገልግሎ የሰጡ ሲሆን ብዙ የማህበረሰብ አገልግሎቶችና የሙያ ነክ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ፕሮፌሰር ሃጎስ አሸናፊ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ህክምና እና ግብርና ኮሌጅ የፓቶሎጂና ፓራሲቶሎጂ (Pathology and Parasitology) ትምህርት ክፍል መምህር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

    5. ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በፖለቲካ ሳይንስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ኢን ካይሮ (The American University in Cairo)፣ እንዲሁም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በፖለቲካ ሳይንስ ከኤራስመስ ዩኒቨርሲቲ ሮተርዳም ኢንስቲትዩት ኦፍ ሶሻል ስተዲስ (Erasmus University Rotterdam – Institute of Social Studies) አግኝተዋል።

    ፕሮፌሰር መረራ በግላቸውና ከሙያ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በጥናትና ምርምር የተሰሩ ከ12 በላይ ጥናታዊ ፅሁፎችን በታወቁ ሀገራዊና አለምዓቀፋዊ መፅሄቶች ላይ ለህትመት በማብቃት ከሚጠበቅባቸው 35 የህትመት ነጥብ 37.25 ነጥብ አስመዝገበዋል። በተጨማሪም በተለያዩ የዩኒቨርሲቲ ቦታዎች ላይ አገልግሎ የሰጡ ሲሆን ብዙ የማህበረሰብ አገልግሎቶችና የሙያ ነክ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለማአቀፍ ግንኙነት (Political Science and International Relations) ትምህርት ክፍል መምህር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

    6. ፕሮፌሰር ጌታቸው አሰፋ የህክምና ዲግሪያቸውን (Doctor of Medicine) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የስፔሻሊቲ ዲግሪያቸውን በራዲዮሎጂ (Radiology) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ እንዲሁም የሰብ-ስፔሻሊቲ ዲግሪያቸውን በኒሮራዲዮሎጂ (Neuroradiology) በኦስትሪያ ከሜዲካል ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቭየና (Medical University of Vienna) አግኝተዋል።

    ፕሮፌሰር ጌታቸው በግላቸውና ከሙያ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በጥናትና ምርምር የተሰሩ ከ17 በላይ ጥናታዊ ፅሁፎችን በታወቁ ሀገራዊና አለምዓቀፋዊ መፅሄቶች ላይ ለህትመት በማብቃት ከሚጠበቅባቸው 35 የህትመት ነጥብ 75.25 ነጥብ አስመዝገበዋል። በተጨማሪም በተለያዩ የዩኒቨርሲቲ ቦታዎች ላይ አገልግሎ የሰጡ ሲሆን ብዙ የማህበረሰብ አገልግሎቶችና የሙያ ነክ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ፕሮፌሰር ጌታቸው አሰፋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጤና ሳይንስ ኮሌጅ የዲያጎነስቲክ ራዲዮሎጂ (Diagnostic Radiology) ትምህርት ክፍል መምህር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

    አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የሚሰጣቸው ምሁራን በመማር ማስተማሩ፣ በጥናትና ምርምር፣ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አገልግሎት እንዲሁም በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት በዩኒቨርሲቲው ሴኔት ሊጅስሌሽን መሰረት የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ለተወጡ እና ለዓለም የዕውቀት ስርጸት መዳበር ስኬታማ አበርክቶ ላደረጉ ነው።

    ምንጭ፦ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ


    Semonegna
    Keymaster

    የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ካስመረቃቸው መካከል 86ቱ የህክምና ዶክተሮች መሆናቸውንና፣ ቀሪዎቹ በጤና መኮንን፣ ክሊኒካል ነርሲንግ፣ ሚድዋይፈሪና በሜዲካል ላቦራቶሪ ሳይንስ መስክ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መሰልጠናቸው ተጠቁሟል።

    አሰላ (ሰሞነኛ) – የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በህክምና ዶክትሬት፣ በጤና መኮንንና ሌሎች የጤና ትምህርት መስኮች ለ4ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 388 የህክምና እና የጤና ተማሪዎች አስመረቀ።

    የህክምና ሙያ ምሩቃን መከላከል በሚቻል በሽታ (preventable diseases) መሞት እንዲበቃ ጠንክረው በመሥራት ጤንነቱ የተጠበቀ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ሊረባረቡ እንደሚገባ የሣይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ወልደማርያም ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት አሳስበዋል።

    በጤና አገልግሎትና አጠባበቅ ረገድ በሚታየው ውስንነት መዳን በሚቻልባቸው በሽታዎች ሰዎች እንደሚሞቱና ታክሞ መከላከል በሚቻል ሁኔታም የአልጋ ቁራኛ እንደሚሆኑ ያብራሩት ዶ/ር ሂሩት፥ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሥራው ዓለም የሚፈልገውን ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ከማፍራት አንፃር ትኩረት የሚሹ ቀሪ ሥራዎችን ለመፈጸም መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል።

    ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በህክምና እና በነርስነት ይስተማራቸውን 220 ተማሪዎች አስመረቀ

    የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ኑዋማ ቢፋ ኮሌጁ ካስመረቃቸው መካከል 86ቱ የህክምና ዶክተሮች መሆናቸውንና፣ ቀሪዎቹ በጤና መኮንን፣ ክሊኒካል ነርሲንግ፣ ሚድዋይፈሪና በሜዲካል ላቦራቶሪ ሳይንስ መስክ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መሰልጠናቸውን ጠቁመዋል። በጤናው መስክ ሀገሪቱ ያለባትን የባለሙያ እጥረት ለማቃለል ዩኒቨርሲቲው ድርሻውን እየተወጣ መሆኑንም ዶ/ር ኑዋማ አመልክተዋል።

    የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዱጉማ አዱኛ ተመራቂዎቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት ከህይወት ተሞክሯቸው ጋር በማዋሃድ በተሰማሩበት መስክ ኃላፊነታውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

    ከተመራቂዎች መካከል በህክምና ዶክትሬት ዲግሪ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ ዶ/ር አዲሱ ነዲ በሰጠው አስተያየት፥ በሽታን አስቀድሞ መከላከል ላይ መሠረት ያደረገውን የጤና ፖሊሲ ውጤታማ እንዲሆን የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

    ከሴቶች ተማሪዎች በከፍተኛ ውጤት በማምጣት የተመረቀችው ዶ/ር አያንቱ ሆርዶፋ በበኩሏ በዩኒቨርሲቲው የቀሰመችውን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ለውጥ ለማምጣት እንደምትጥር ተናግራለች።

    የህክምና ትምህርት የተግባር ትምህርት እንደመሆኑ እርስ በእርስ የነበረ የመማማር ሂደት አሁን ለደረሰችበት ስኬት እንደረዳት ገልጻለች።

    ምንጭ፦ የሣይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ተመሳሳይ ዜናዎች፦

    የአርሲ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ


    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በቅርቡ ሥራውን በይፋ የሚጀምርበት በዳያስፖራው ማህበረሰብ እና በባለድርሻ አካላት ዘንድ ተልዕኮው በግልፅ ታዉቆ በጋራ እና በቅንጅት ሥራው እንደሚሰራ መገለጹን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመልክታል።

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን አገራዊ ተሳትፎ ለማረጋገጥና መብታቸውን ለማስከበር በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር የተቋቋመው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ሥራ ለመጀመር የመዋቅርና የሕግ ማዕቀፍ ሥራን ማጠናቀቁን አስታወቀ።

    የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት እና ምክትል ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እንድሪስ ታህሳስ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ለአገር ውስጥ እና ለዉጭ አገር መገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

    የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የመዋቅርና የሕግ ማዕቀፍ ሥራን ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ የኤጀንሲው ወደ ሥራ መግባት ዳያስፖራው በአገሩ ጉዳይ ብርቱ ተዋናይ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

    በዉጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን መብትና ጥቅሞችን ለማስጠበቅ የዳያስፖራ ምዝገባ እና መረጃ አያያዝ ስርዓት መዘርጋት፣ ዳያስፖራው በዕውቀትና በተክኖሎጂ ሽግግር አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ማስቻል እንዲሁም በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በቱሪዝም ተሳትፎውን ማጎልበት የኤጀንሲው ዋና ዓላማዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።

    ተጨማሪ፦ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ እና ለመሥርት ያላቸው ፍላጎትና የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች (ቪዲዮ)

    ኤጀንሲው በቅርቡ ሥራውን በይፋ የሚጀምርበት በዳያስፖራው ማህበረሰብ እና በባለድርሻ አካላት ዘንድ ተልዕኮው በግልፅ ታዉቆ በጋራ እና በቅንጅት ሥራው እንደሚሰራ መገለጹን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመልክታል።

    የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህን ኤጀንሲ ለማቋቋም የወሰነው በጳጉሜን ወር 2010 ዓ.ም. ሲሆን፥ በዚያን ጊዜ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በትውልድ ሀገራቸው እድገት ላይ የራሳቸውን አስተዋጽዖ ለማድረግ ከምን ጊዜውም በበለጠ እንደተነሳሱ ገልጸው ነበር።

    በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከሦስት እስከ አምስት ሚሊዮን እንደሚገመትና ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ በሰሜን አሜሪካ እና አውሮፓ እንደሚኖሩ ዘገባዎች ያመለክታሉ። እ.ኤ.አ ከ2009 በፊት ኢትዮጵያ ከእነዚህ የዳያስፖራ አባላት የምታገኘው ገቢ (remittance) ከ400 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በታች እንደነበረና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይህ አሀዝ እየጨመረ መምጣቱ ተጠቁሟል።

    በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ወደ ትውልድ ሀገራቸው የሚልኩት የገንዘብ መጠን ከአራት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ እንደሆነና ይህም ሀገሪቱ ከወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) ከምታገኘው ገቢ ጋር ሲነጻጸር በአንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ብልጫ አለው።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ


Viewing 15 results - 1 through 15 (of 19 total)