በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሞታ በተገኘችው ተማሪ (ሃይማኖት በዳዳ) የተጠረጠረው ግለሰብ በቁጥጥር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ

Home Forums Semonegna Stories በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሞታ በተገኘችው ተማሪ (ሃይማኖት በዳዳ) የተጠረጠረው ግለሰብ በቁጥጥር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #14649
    Anonymous
    Inactive

    በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሞታ በተገኘችው ተማሪ (ሃይማኖት በዳዳ) የተጠረጠረው ግለሰብ በቁጥጥር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ

    አዲስ አበባ (ኢፕድ) – ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ የተገደለችው የወጣት ሃይማኖት በዳዳ ተጠርጣሪ ገዳይ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ስር ያዋለው የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ የሆነውና በ20ዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ደግነት ወርቁ የተባለ ወጣት ሲሆን፥ ወጣት ደግነት ወርቁን ፖሊስ የ27 ዓመቷን ሃይማኖት በዳዳ ሕይወት በማጥፋት ጠርጥሮት በቁጥጥር ስር አውሎታል።

    ግንቦት 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት ባካሄደው ክትትል ነው ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር የዋለው። ቀን ከሌሊት በተካሄደው በዚህ ክትትል የተያዘው ወጣቱ ደግነት ወርቁ ከሟች ጋር ምንም ዓይነት ትውውቅ እንዳልነበራቸው በቁጥጥር ስር በኋላ ለሰዓታት በተደረገ ምርመራ የወንጀሉን ዝርዝር ለፖሊስ አስርድቷል።

    ግለሰቡ የ12ኛ ክፍል ተማሪ እንደነበርና የኤች አይ ቪ ኤድስ መድኃኒት ለማግኘት ምርምር ላይ ስለሆንኩ የጥቁር አንበሳ ሐኪሞች ይርዱኝ በማለት ወደ ግቢው በተለያዩ ጊዜያት ይመላለስ እንደነበር ዘርዝሯል። ከዚያም በግንቦት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደልማዱ ለዚሁ ጉዳይ እንደመጣ ገንዘብ እንደተቸገረና ቢላዋ ይዞ በግቢው ውስጥ ከሚገኙ ቢሮዎች በአንዱ ላፕቶፕ ወይም ሞባይል ካገኘ ሰርቆ ሽጦ ለመጠቀም ሲዟዟር የሟች ክፍል ክፍት በመሆኑ መግባቱን አስረድቷል። ሟች ሃይማኖት በዳዳ ሞባይሏን እንድትሰጠው ጠይቋት እምቢ ስትለው መታገላቸውንና ከዚያም በያዘው ስለት ወግቷት ንብረቱን ይዞ መውጣቱን ተናግሯል።

    ፖሊስ ከሟች ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው 12 ተጠርጣሪዎችን ይዞ ተጨማሪ ምርመራ ማድረጉን የግድያ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክቶሬት ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) ገልጿል። ለፖሊስ ምርመራ ትልቅ አቅም የሆነው የሟች ወላጅ አባት ከሳምንት በፊት ለልጃቸው የሰጧት የ5 ሺ ብር ቼክ ነው።

    ገዳዩ በወቅቱ የሟችን ላፕቶፕና ሞባይል ፓስፖርት መታወቂያና ይህንን ቼክ ወስዶ ስለነበር ቼኩን የካ አካባቢ በአንድ ባጃጅ ተሳፍሮ አሽከርካሪውን መታወቂያ ስላልያዝኩ በአንተ መታወቂያ ይህንን ብር አውጣልኝ ብሎት የባጃጁ ሹፌርም (አቶ እንዳለማው ታረቀኝ) መልኩን አስተውሎ ስለነበር ምርመራው ከዚህ እንደጀመረ ፖሊስ ገልጿል፡

    ኮሚሽኑ በወቅቱ የሆስፒታሉ የደኅንነት (security) ካሜራ ከአገልግሎት ውጪ መሆኑን (‘update’ እንዳልተደረገ) እና የጥበቃ ሠራተኞችም ቢላዋ ተይዞ እስከሚገባ ፍተሻቸው አጋላጭ መሆኑንም ጠቁሟል ሲል የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ዘግቧል።

    ሃይማኖት በዳዳ ማነች?

    ወጣት ሃይማኖት በዳዳ ተወልዳ ያደገችው መተሃራ ከተማ ሲሆን፥ ወላጆች በአሁኑ ወቅት በአዳማ ከተማ ጎሮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ይኖራሉ። በ2009 ዓ.ም. ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በ’ክሊኒካል ፋርማሲ’ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በማዕረግ ያገኘች ሲሆን፥ በዚያው በተማረችበት ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ስታገለግል ነበር። ከዚያም በ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሁለተኛ ዲግሪዋን በመከታተል ላይ እንደነበረች አባቷ አቶ በዳዳ ፈይሳ ተናግረዋል።

    የሃይማኖት አባት አቶ በዳዳ ፈይሳ ልጃቸው 2009 ዓ.ም ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ በ’ክሊኒካል ፋርማሲስት’ በማዕረግ ተመርቃ በዩኒቨርስቲው በመምህርነት ስታገለግል መቆየቷን ያስታውሳሉ። ከዚያም ሁለተኛ ዲግሪዋን ለመማር ወደ ጥቁር አንበሳ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተልካ ትምህርቷን በመከታተል ላይ እንደነበረች ይናገራሉ።

    ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ኢፕድ) እና ቢቢሲ አማርኛ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 

    ሃይማኖት በዳዳ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.